158. አለምነህ ዋሴ
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ
ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ አለምነህ ዋሴ
ነው፡፡ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና ጋዜጠኛ ባንቺአየሁ አሰፋ የአለምነህ ዋሴን ታሪክ ታነቡ ዘንድ ጋብዘዋል፡፡
በአንጋፋው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ ፣ በፋና ሬዲዮ፣ በአዋዜ ሬዲዮ ፣ በማህበራዊ ሚዲያና በማስታወቂያ ሥራ ከ35 ዓመታት በላይ አገልግሏል።
በአስገምጋሚ ድምፁ የብዙዎችን ጆሮ
እንደፀጉር አበጥሯል: የመርካቶን ነጋዴዎች ሬድዮ ከችርቻሮ እስከ ጅምላ አሽጧል ፡፡ በቃላት ኮርቻው አፈናጦ ከሀሳብ ስልቻው እያፈሰ የዓለም መረጃን ለህዝብ መግቧል። አመለሸጋው
ስመገናና የሬድዮ ጋዘጠኛ የዜና ፋይል ቁንጮ አለምነህ ዋሴ ፡ ውልደቱ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የብዙ ከያኒያን መንደር በሆነችው
መሀል ፈረንሳይ ለጋሲዎን ነው።
ምንም'ኳ የእሱ የልደት ቀን እንድሆን የሚፈልገው የሬዲዮ ቀን ላይ ቢሆንም በሺህ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ዘጠኝ ዓ.ም (1959) የካቲት 30 ቀን ከእናቱ ወ/ሮ አረጋሽ አስናቀ እና ከአባቱ ዋሴ መስፍን ተወልዷል ።
አለምነህ የቤቱ አራተኛ ልጅ
ቢሆንም እንደመጀመሪያ ሁሉ 'አለምነህ' የሚለውን አስደናቂ ስም ተጎናፅፏል።
አለምነህ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው ከእናቱ አረጋሽ አስናቀ ጋር በመሆን
ነበር። ይህ ታዲያ የቤቱን ውስጥ ገፅታ በሚገባ ለመቃኘት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ሳይፈጥርለት አልቀረም።
የወታደር አባቱ ዋሴ መስፍንን የቤት ግርግዳ ተለጣጥፈው
ያቆሙት የኢትዮጵያ
ፕሬስ ድርጅት በየቀኑና በየሳምንቱ የሚያትማቸው ጋዜጦች እስኪመስሉ ድረስ ቤቷ በቀለማም ጋዜጦች የታጀለች ነበረች።
አለምነህ ዓይኑን ከግድግዳው ሳይመልስ ከጋዜጣው ላይ ያሉትን ርዕሶችና ፊደላት በምላሱ እየለቀመ በዓይኖቹ እየነቀለ ሲያነበንብ ድምፁ ቤት ውስጥ ማስተጋባት ጀመረ።
የተሰማው ድምፅ እንደቄስ ቅዳሴ እንደሸሂ አዛን በሁሉም ዘንድ ተወደደ።
አለምነህ
የማንበብ ፍላጎቱ እየጨመረ ጋዜጦቹን
ከርዕሳቸው አልፎ ትንታኔያቸውን በመጮህ ሲያነበንባቸው
ነገን የሚያመላክቱ አዎንታዊ መላምቶች ከየአቅጣጫው ተሰነዘሩ።
በትምህርት ቤት የቀለም ትምህርቱ እና የሚሰጥበት ይዘት እንደልቡ ያላስኬደው እንደንባብ ፍላጎቱ ሰቅዞ ያልያዘው ቢሆንም ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል።
በበርካቶች ዘንድ በጨዋታ አዋቂነቱና በጥኡም አንደበቱ እውቅና አግኝቷል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በህዝባዊ ሰራዊት እስከ ስድስተኛ ክፍል ሲማር በውጤቱ 99 ነጥብ
በማስቆጠር ቀደሚውን የአንደኝነት ደረጃ ይዟል።
ባለው ልዩ የንባብ ፍቅርና የአነባበብ ስልት ታዲያ ዘወትር ጠዋት በሰልፍ ላይ የማለዳ ዜና ነጋሪ የመሆን ዕድልም አግኝቷል ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሚያዚያ 23
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀጠለ ሲሆን በዚህም የክፍል ውስጥ ደረጃውን ሳይለቅ ለመቶ አንድ ጉዳይ ነጥቡን ይዞ በአንደኝነት
አጠናቋል።
የቤታቸውን
አነስተኛ ሬድዮ አቅሟን አሟጦ በመጠቀም የዜና ዘገባዎችን እና የስፖርት ዜናዎችን በማድመጥ እንዲሁም ተርጉሞ በማዘጋጀት የወቅቱን ትላልቅ የሚባሉ ስለጋዜጠኝነት የተፃፉ ፅሁፎችን በማንበብ ድምፁን በመሞረድ እይታውን በማስፋት ጉዳይ በማነፍነፍ እራሱ ላይ በትጋት ሰርቷል ።
በኋላም ወደእንጦጦ አጠቃላይ የመሰናዶ ትምህርት ቤት አቅንቶ ትምህርቱን የጨረሰ ሲሆን በአካውንቲንግ ዲፕሎማ አግኝቷል።
ይሁን እንጂ አለምነህ ጣቱን እየቆጠረ ተመሳሳይ የሂሳብ ስሌት ለመቀመር የተፈጠረ ሳይሆን የዓለም መንግሥታትን ደባና አሻጥር ፡ እረቂቅ የሴራ ጥምጥም በተባ ብዕሩ እየከሰከሰ ፣ እየነቀሰ በአደባባይ
ማስጣት ሆነ። አዝማሚያውን ከልጅነቱ ጀምሮ የተከታተሉት ሀምሳ
አለቃ መርሻ ይሄ ልጅ ጋዜጠኛ መሆን ይኖርበታል ሲሉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ዜና ክፍል ኃላፊ በመሆን ስታገለግል ከነበረችው የፈረሳይ ልጅ ፀሐይነሽ ቸርነት ቤት እጁን ይዘው ይወስዱታል ።
የልጁን አቅምና እስካሁን የመጣበትን ሂደት ቁጭ ብለው ለፀሐይነሽ ያጫውቷታል ። ያስተዋውቋቸዋልም።
ሁኔታውን ስታዳምጥ የቆየችው ጋዜጠኛ ፀሐይነሽ በወቅቱ ስለነበረው የጋዜጠኝነት ህይወት እና የሥራ ሁኔታ ስለሚጠይቀው አቅም ቅድሚያ ገለፃ አደረገችለት። ልበ-ሙሉው ጋዜጠኛ ይቅር ያሳደገኝን ጥርሴን የነቀልኩበትን
አማርኛ እንግሊዝኛም
ቢሆን አያቅተኝም ሲል በወኔ ያረጋግጥላታል።
ወቅቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል የሚጀመርበት ስለነበር የትምህርት ማስረጃውን በመያዝ ሄዶ
ለመወዳደር የሚያስችለውን አቅጣጫ በቅርብ እርቀት ላይ ሆና ትጠቁመዋለች።
አለምነህ የጥቆማ አቅጣጫውን ይዞ ወደጣቢያው ያቀናል። በዚያም የወቅቱ የሬዲዮ ዜና ፋይል ኃላፊ የነበረውን ጋዜጠኛ ጌታቸው ሃይለማርያም ያገኘዋል። እርሱም ለፈተና የስልክ ጥሪ እንደሚያደርግለትና እንዲጠባበቅ በመንገር ያሰናብተዋል። ለአለምነህ ምዕራብ አልባ ፀሐይ እየወጣች ለመሆኗ እሩቅ መገመት አያሻም።
የግል
ስልክ የሌለው አለምነህ የስልክ ጥሪ ሳይደርሰው ቀርቶ ሌሎች ተወዳዳሪዎች የመወዳደሪያ ፈተና እየወሰዱ መሆኑንና በፍጥነት እንዲሄድ በሰፈር ውስጥ ያገኘችው ጋዜጠኛ ፀሐይነሽ ቸርነት ትነግረዋለች ። እሱም በፍጥነት ወደቤቱ ተጉዞ ልብሱን እና ጫማውን ለውጦ
እራሱን ካስተካከለ በኋላ ከጎረቤቱ ወ/ሮ ዘውዴ አንድ ብር ተቀብሎ አቡነ ጴጥሮስ ወደሚገኘው የሬዲዮ ጣቢያ በማቅናት ጌታቸው ኃይለማሪያምን ያገኘዋል። የመጣበትን ጉዳይ በውል ቢያስረዳም ስልክ ተደውሎለት እንደነበር እና ስልኩ እንደማይሰራ ይነግረዋል።
ሌሎች ተፈታኞች የሦስተኛ ዙር ፈተና እየወሰዱ ስለሆነ እሱ እንደማይደርስ
እና ጊዜ እንደማይበቃው በማሳወቅ እንዲመለስ ይደረጋል ። እርሱ ግን የለም ያለኝ ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እችላለሁ ሦስቱንም ፈተና በቀረው አንድ የፈተና ስዓት እፈተናለሁ አለ። ቢሆን ነገሩ ጉንጭ ማልፋት ብቻ ሆነበት ። ፊት የነሱትን የመፈተኛ ቦታና ፈታኞች ጀርባውን ሰጥቷቸው ከንፈሩን በጥርስ አጣብቆ ግቢውን መልቀቅ ጀመረ።
ሳይደግስ አይጣላም ነውና የፕሮግራም ከፍል ኃላፊ የነበረው ኃይሉ ወልደፃዲቅ ስለ አለምነህ ዋሴ እዚህ መገኘት ጌታቸው ኃ/ማርያምን ይጠይቀዋል። እሱም የተገኘው ለፈተና ቢሆንም አርፍዶ መገኘቱን ያጫውተዋል።
ኃይሉ ወልደፃዲቅ ታዲያ ሌላ ያረፈደች ልጅ እንዳለች እና ከእርሷ ጋር ከሰዓት በኋላ ፈተናውን መውሰድ እንደሚችል ለጌታቸው ይነግረዋል።
ዕድል
በሯን ያልከረቸመችበት አለምነህ ዋሴ ከሰዓት በኋላ ፈተናውን እስኪበል እንሞካከር እና ይዋጣልን ብሎ በሜዳው ግጥሚያ ጀመረ። ሚዲያ ይከታተል ስለ ነበር ፈተናው እምብዛም ፈታኝ ሆኖ አለገኘውም። በመጨረሻም የመምሪያው ኃላፊው
የሰጡትን መግለጫ ወደ ሪፖርት በመቀየር የሦስተኝነት ደረጃ ይዞ እንዳጠናቀቀ ማወቅ ቻለ፡፡
ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ ዓ.ም (1979) ጥር
1 ቀን በ230
ብር ደመወዝ ተቀጥሮ የዜና ፋይል አባል በመሆን በዚህ ዝግጅት ምስረታ ላይ ከዋጋዬ በቀለ ፣ አዜብ ተፈራ ፣ ዕፀህይወት ደምሴ ፣
ደበበ ዱፌራ ጋር የዜና ፋይል መስራች ለመሆን በቃ፡፡
ፈረሱም ሜዳውም ያውልህ ስላሰጋገሩ ባለቤት ያውቃል ተባለ።
በዚያን ወቅት በቃላት ውርወራ የተጀመረው የባግዳዱ ሳዳም ጉዳይ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ወቅታዊ ሁኔታ ነበር። ጉዳዩ ትክክለኛውን ሰው አገኘ።
ይህ ዓለምን ያስደነገጠውና ብዙ ሚሊዮኖችን የቀጠፈው አሰቃቂው የሳዳም ሁሴን ኩዌትን ወረራ ገና ብቅሉ ሲረገጥ፣ ጌሾው ሲወቀጥና ሲሾም አለምነህ ዋሴ አብሮ የነበረና ዕቃ ያቀበለ እስኪመስል ድረስ የመጠጡን ክፋት ብቻ ሳይሆን መቼ እንደሚፈላ ሁሉ ልብ በሚገምሰው አስገምጋሚ ድምፁ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲያስተጋባ በተመስጦ ተደመጠ ።
አድማጮች አለምነህ ዋሴ ነኝ ሲል የተጎነጩትን ውኃ ሳይጠጡ። ያኘኩትን እህል ሳይውጡ
አፉን በንቃት ተጠባበቁ።
የፈረንሳይ 12 ቁጥር
የባስ ተሳፋሪዎች ባሱ ሬዲዮ ከሌለው አንሄድም አሉ።
የ15
ቀናቱ የቃላት ጦርነት የእሳት በረዶ ሲያዘንብ መካከለኛው ምስራቅ ሲርድና ሲነድ በርካቶች በነበልባል ሲጠመቁ በደመማቸው ተቀቅለው ሲበስሉ የአንዱ ሞት ለሌላው ሰርጉ ነውና አለምነህ ዋሴ የማይወጣ ምጣዱን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጥዶ እንጀራውን ሲጋግር ማንም ከማይደርስበት የእውቅና ጣሪያ ላይ ስሙን ሲሰቅል ከረመ። በኩዌት የጦር ሜዳ ተገኝቶ
በባግዳድ ጉባኤ ተካፈለ። ጊዜው ያመጣውን ጦርነት አስመልክቶ በርካታ ዘገባዎችን ሰፋፊ ትንታኔ በመስጠት አስደመጠ።
አለምነህ
ዋሴ ፣ ስሙ እየገነነ ሥራው እየተወደደ በዜና ፋይል ዘገባው በዓለም አቀፍ ትንታኔው ከነጩ ቤተ-መንግስት እስከ ቀደማዊ ኃይለስላሴ ቤተመንግሥት ድረስ ዓይኖቹን በልጥጦ ጆሮዎቹን አቁሞ አፍንጫውን ምጎ እንኳን በቀን የሰሩትን በህልማቸው ያዩትን ሳይቀር ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ዘከዘከ።
የባህረ ሰላጤው ሀገራትን የፖለቲካ ትንቅንቅ
የኢራንና ኢራቅ ግብግብ የአሜሪካን
ማሽቃበጥ አፍጋኒስታን ሌሎች ሃያላን ሀገራት ፍትጊያ እና ጦርነቱ ያስከፈለው ዋጋ በአለምነህ ዋሴ ዘገባ ሰፊ ሽፋን አገኘ።
ከፖለቲካ ምሁራን የሚሰነዘሩ መላምቶችና የሚሰጡትን ሀሳቦች በማንሳት ስለጦርነቱ
ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደረገለት ቃለ-መጠይቅ የባህረ ሰላጤው ጦርነት መፈንዳቱ አይቀሬ ነው ሲል
እውነት ያዘለ መላምቱን ሰንዝሯል ። ይህም ሌላው እውቅና እና አድናቆት ያገኘበት ሆነ።
የባህረ -ሰላጤው ሀገራት ጦርነት በአየር ድብደባ ሲናወጥ አለምነህን የሚያዳምጥ ሁሉ ቆርቆሮ ሲወድቅ በድንጋጤ የምር ጦርነትን እየተካሄደ መስሎት የሸሸም እንደነበር የሚናገር አልጠፋም።
የዚህ ጦርነት ዜና ካበቃ በኋላም ሌሎች የውጪ ዜናዎችን በስፋት ሰርቶ አስደምጧል። እጅግ አስገራሚ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በሚገርም አተያይ የማየት ተሰጥኦ ያለው የቃላት አመራረጡ እና የአነባበብ ስልቱ የአድማጭን ልብ ከጉዳዩ የሚያቆራኝበት ብልሃት አለምነህን ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ አለምነህ በሀገራዊ ጉዳዮችም አነጋጋሪ ሰው ነው። በዚሁ በሀገር ውስጥ አንድ አስገራሚ መረጃ ይደርሰዋል።
ይኸውም በድሬደዋ ከተማ በሰዓት 10ሺህ ዶሮዎችን አርዶ እና በልቶ የሚያቀርብ ፋብሪካ በ30 ሚሊዮን ብር በጀት ሊቋቋም ነው።' የሚል ነበር። ቀልጣፋው አለምነህ ዋሴ የዚህን ግዙፍ ፕሮጀክት ባለቤት ዶ/ር ገነቴን
አግኝቶ ቃለ-መጠይቅ ያደርግላቸውና በደብረዘይት የሚገኘውን የዶሮ ዕርባታ ጣቢያ/ ስፍራ ይጎበኛል።
ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ምስጋና ይሆን ዘንድ ከዶክተሩ 3 ካርቶን እንቁላል ይቸረዋል። ዜናውን ሰራ። የሦስት ሳምንታት ቁርሱን ዘጋ።
ዜናው ተሰርቶ ካበቃ በኋላ
ቀድሞ በሰርቶ አደር ጋዜጣ ላይ ስለሞቱት ጫጩቶች እና ቁጥራቸው ከበድ ያለ ሂስ ተፅፎባቸው ኖሮ
ዶክተሩ በዚህ ጋዜጣ ላይ የጠፋ ስማቸውን ለማደስ ሲሉ ከአለምነህ ዋሴ ጋር ተነጋግረው በብሔራዊ ሬዲዮ ዜና አሰርተዋል ፡ የሚል ክስ ይቀርባል ። ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ሆነ። በደብረዘይቱ ጉብኝት ዳጎስ ያለ የ 300 ብር አበል ተከፍሏቸው ስለነበር የተሰጣቸው የውሎ አበል ብር የተጋነነ ነው። የሚልም ተጨማሪ ጥያቄ ቀረበበት።
ለጥያቄውም
ዳጎስ ያለ ምላሽ ከአለማየሁ ዋሴ ተሰጠ።
በተሰጠኝ ገንዘብ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ሲል በመግለፅ እነርሱ የሚከፍሉት ደሞዝ የትኛውንም ስጦታ እምቢ እንደማያሰኘውና ነገርግን ለገንዘብ እንደማይሰራ ገንዘብ ከሰጡት ግን እንደሚቀበል ረገጥ አድርጎ ይናገራል። ቢሆንም
ከደሞዙ ሃምሳ ብር እንደሚቀጣ ይነገረዋል።
ይህችም ምን ሆና ምን አማራት ነውና ነገሩ ከደመወዜ ከምቀጣ
ስራውን ብለቅ እመርጣለሁ አለ።
ባልደረባው የነበረው ሳምሶን በዚህ ምክንያት ከስራው ተሰናበተ።
ከያዘ አይለቅ ቶፋቸው
ከተናገረ እያባራ አፋቸው.... ሆኖበት አለምነህ በድጋሜ ከሦስት ወራት በኋላ የነዚሁ ዶሮዎች መዘዝ መጣበት። የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል ሥራ አስኪያጁ አቶ ሞገስ ታፈሰ ወደ ቢሯቸው አስጠርተው ዶሮ እንደሰረቀ እና በሌብነቱም ከስራ አለመባረሩ ዕድለኝነት እንደሆነ የሚገልፅ አስደንጋጭ ንግግር ያደርጉለታል ። ሰውዬው መልሰው
ነገር ግን በስራው እጅግ በጣም ጥሩ እንደሆነ የማይገናኝ ሙገሳን በመቸርቸር ደመወዙ ከ230 ወደ 285 ማደጉን እኝሁ ሥራ አስኪያጅ ይነግሩታል ። የዶሮዎቹም ጉዳይ እዚህ ላይ ተቋጨ።
አንጋፋውና ዝነኛው የሬዲዮ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ በብዙዎች ልብ ውስጥ ድምፁን ተጠቅሞ ለዘለዓለም የሚኖርበትን ጎጆ መቀለስ የቻለ ብርቱ ባለሙያ ነው።
በተለይም ደግሞ በሌላ የመገናኛ ብዙሃን እና በሌላ ሰው አንደበት የተሰሩ ጉዳዮች አለምነህ ጋር ሲደርሱ መልካቸውን ቀይረው እንደ አዲስ ይደመጣሉ። ይህ የአለምነህ የጉዳይ አያያዝ ጥበብ ነው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በላከው ዜና ላይ ' ሙኒት ታፈሰ አውሮፕላን በመጥለፍ አስራ ሰባት ዓመት ተፈረደባት ብሎ ' ነበር። ዜናው ከአለምነህ ዋሴ እጅ ሲደርስ ግን በመጀመሪያው ዜና ላይ ተቀብሮ የነበረው እንድምታ ልውጥ ሌላኛው መልኩ ፍጥጥ አለ። በሁለት ሰዓቱ የዜና እወጃ ላይ አለምነህም ዜናውን በዚያ ባስገምጋሚ ድምፁ ሲያቀርበው ' የአስራ ሰባት ዓመቷ ሙኒት ታፈሰ የአስራ ሰባት ዓመት እስራት ተፈረዳባት '። አለው።
ይህ ጉዳይ እንዲህ ከተደመጠ ከምላስ ከተንሸራተተ ከአየሩ ሞገድ ጋር ተደባልቆ ባፍታ ሚሊዮኖች ጋር ከደረሰ በኋላ በዚያው ምሽት ከዋና ስራ አስኪያጁ ፍቃደ የምሩ ጋር በመሆን ልደታ ፍርድቤት እንዲቀርብ ጥሪ ቀርበበት።
ጋዜጠኛ
ነውና የራሱን ጉዳይ ወደጎን ገፍቶ ለ17 ዓመቷ ሙኒት ታፈሰ በዜናው ላይ ድምፅ በመሆን እሱ ወደፍርድ ቤቱ አቀና።
ፍርድቤቱ "ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ" ለሆነ ክሱ
ማስጠንቀቂያ
ብቻ ሰጥቶ ያለምንም ተጨማሪ
ቅጣት ነፃ እንዲወጣ አደረገ ፡፡
በኋላም ከዜና ፋይል መሪነት ተነስቶ ባነበበው ዜና ክፍያ እንዲፈፀምለት ተደረገ።
ጠዋትና ምሽት 3 ሰዓት ላይ ዜና እንዲያነብ በዚህም ለምሽት ዜናው 20 ብር ለማለዳ ዜናው 10 ብር እንዲከፈለው ሆነ። በዚህም ምክንያት ለአሥር ዓመታት ቆይታ ያደረገበትን አንጋፋውን ብሔራዊ ሬዲዮ በመተው 1989 ዓ.ም ብሔራዊ ሌተሪን ተቀላቀለ፡፡
ያ በትምህርት ቤት ሰልፍም ላይ ዜና ይነግር የነበረው ተማሪ ፤ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ የዜና ፋይል መሪ የነበረው ፤ ከዓለም መሐል እንብርት ላይ እንደተቀመጠ ሁሉ ዙሪያ ገባውን እና ውሎ አዳሩን ፤ መንግሥታት የጠነሰሱትን ደባ የሀገራትን ህመምና ሽረት ያስቃኝ የነበረው ባለነጎድጓድ ድምፁ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ
የብሔራዊ ሎተሪ የማስታወቂያ ክፍል ሀላፊ
ሆነ። የጆሮ አድባር ሸሸ።
እነዚያ 46 ጎራሽ
እግሮቹ እነዚያ
እሩቅ ደራሽ ብዕሮቹ
በአንድ ቢሮ ውስጥ ተሰበሰቡ።
ደመወዙ ከቀድሞው በ195 ብር ዕድገት አሳየ።
ይሁን እንጂ እዚህም በለስ ያልቀናው አለምነህ በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቢሮ አማካሪ የነበሩአቶ ከበደ ታደሰ የተባሉ ግለሰብ ለብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አንድ ደብዳቤ ይፅፋሉ። ደብዳቤውም ሲከፈት ማስታወቂያ ክፍሉ በአለምነህ ዋሴ መመራቱ ቀርቶ ለሌላ ሰው ሀላፊነቱ እንዲሰጥ የሚያዝ ነበር።
ነገር ግን አማካሪው የተሰጡት ምላሽ አለምነህ ዋሴ ለቦታው ትክክለኛ እና ተገቢ ሰው እንደሆነ የሚገልፅ ነበር። እኝህ ሰውዬ ግን እሱ ሳይነሳ እንቅልፍ አልተኛም ብለው ደብዳቤ መፃፉን ቀጠሉ። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ተከታታይ ደብዳቤዎችን በመላክ እሱ ሰው ከቦታው የማይነሳ ከሆነ ሙሉ በሙሉ የመስሪያ ቤቱን ማኔጅመንት እንደሚበታትኑት ዛቻ አክለው ፃፉ።
በዚህም ምክንያት አለምነህ ዋሴ በግድ ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ተደረገ፡፡
ከኃላፊነት የተነሳው አለምነህ የግሉን የማስታወቂያ ድርጅት ከፍቶ መስራት ጀመረ።
የማስታወቂያ ፍቃድ ሰላልነበረው
ክፍያዎችን ይፈፅም የነበረው በሌሎች ፍቃድ ባላቸው ሰዎች በኩል ሆነ።
አለምነህ ማስታወቂያ ሰርቶ ለቴሌቪዥን ጣቢያ ለማስገባት ቢሞክርም ያንተ ማስታወቂያ በዝቷል እንዲሁም በሌሎች ትናንሽ ምክንያቶች ተፈልገው የማስታወቂያ ሥራውን ፈታኝ አደረጉበት ።
በዚያን ወቅት የነበረው የሙስና አሰራር በእጅጉ ያስቸገረው አለምነህ ዋሴ ከኃላፊነት ከማንሳት ጀምሮ እርሱና የሥራ አጋሮቹ በሥራቸው እንዳይቀጥሉ በማድረግ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊዎች እና የመንግሥት አማካሪዎች ህይወቱን አስቸጋሪ አድርገውበት እንደነበር ይናገራል።
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ የነበሩ የወቅቱ አመራሮች በይበልጥ ደግሞ የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊዎች እርሱ የሰራቸውን ማስታወቂያዎች እንዳይተላለፍ ከማድረግ ባለፈም በሰዓቱ ማስታወቂያው እንዳይሄድ በማስተጓጎል አብረውት ይሰሩና ያሰሩት ከነበሩ ሰዎች ጋር ቅሬታ እንዲፈጥርና ጥላቻን እንዲያተርፍ አድርገውት እንደነበር ያስታውሳል። ሚዲያ ሀገር ይገነባል። እንደ አራተኛ መንግሥት ሆኖም ሀገር ይመራል ከተባለ ዘንድ ግንባታውም አመራሩም ምን እንደሚመስል በአለምነህ ጫማ ላይ ቆሞ ማየት ነው። ጉዳዩ ለመሆኑ ስንት አለምነህዎች የዚህ ስርዓት በትር አርፎባቸው ይሆን?
የሚል ጥያቄን ያስነሳል።
በጊዜው ድምፁን ከሚዲያ ላይ አጥፍቶ ለመስራት የወሰነ ቢሆንም በወቅቱ በነበረው ፖለቲካ ምክንያት ስሙ በተለያዩ ጉዳዮች መብጠልጠሉ አልቀረም።
ይሄንኑ ነገር ለመመለስ ለራሱም ደህንነት ሲል እንደገና ከሬዲዮ ፋና ጋር ለመስራት ወስኖ
ከሥራ አስኪያጁ ሙሉጌታ ገሰሰ ጋር በመነጋገር ስምምነቶችን አደረገ። ስምምነቶቹም የግምገማ ስራዎች ውስጥ እንደማይገባ ዜናዎችን ብቻ ማቅረብ እንደሚፈልግ እና እርሱ መስራት የሚፈልጋቸውን የዘገባ ጉዳዮች ብቻ እንዲሰራ የሚሉ የቅድመ ሁኔታ ስምምነቶች ነበሩ።
በ420 ብር ፍሪላንስ አገልግሎት ለመስጠት በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዓ.ም (1990) ፋና ሬዲዮን ተቀላቅሏል።
ታዲያ የቀድሞው መስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ በዜና ፋይሉ ላይ የአድማጭን አስተያየት በሚሰበሰብ ጊዜ አለምነህ ዋሴ እንዲመለስ ግፊት ያደርጉ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ አስተያየት ተቀባዮች ይናገራሉ።
ቢሆንም ግን በወቅቱ የነበሩት የስራ ኃላፊዎች መልዕክቶቹ መልሰው አየር ላይ እንዲውሉ ስለማይፈልጉ አስተያየቶቹ በተቀባይና በሰጪ መካከል ባለው ሬዲዮ ጣቢ ውስጥ ቀልጠው ይቀራሉ። ።
ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴም በፋና ስፖርት ዘገባው ከወንድወሰን ከበደና ኤደን መሐመድ ጋር በመሆን ሰርቷል። በወቅቱ በነበረው የስፖርት ውድድር ላይ የተንፀባሩቁን ስሜቶች እና የተፈጠሩትን ክስተቶች ጭምብላቸውን በማንሳት ያለምንም ፍርሀትና ጭንቀት በግልፅ ዜናዎቹ አስደምጧል።
በስፖርት ዘገባዎቹ እጅግ ብዙ አድናቂዎች የነበሩት አለምነህ ዋሴ በዘገባዎቹ መጠጠርና በቃላቶቹ እምቅነት የተነሳ ብዙዎችም ተችተውታል።
በሩጫ
ስፖርት ዜናው ላይ የኬኒያውን እሯጭ እና የሀይሌ ገ/ስላሴን ፉክክር ያየበት ዘገባው አንተ ኬኒያዊ ነህ እንዴ? እስኪባል ያደረሰው ሲሆን በተመሳሳይ ደግሞ ለብሔራዊ ሬዲዮ በስፖርት ዜና ፋይል በሰራበት አንድ ወቅት
የምድር ጦር
አዲስአበባ ስታዲየም በነበረው ጨዋታ ላይ ባደረገው የስታዲየም ውስጥ ድብደባ የተቋረጠውን ጨዋታ እንዲሁም በሌላ ጊዜ ደግሞ ይኸው ምድርጦር በድሬደዋ ለጨዋታ ተገኝቶ የዳኛውን ብልት በመምታት በድጋሜ መቋረጡን በስፖርት ዜናው ' ኳሱ ወደቡጢ ተቀይሯል ' በሚል ይሰራዋል።
በማግሥቱ ጉዳዩ በፖለቲካ ዓይን ተቃኝቶ ኖሮ አንዱ ኮሎኔል ወደሚኒስቴሩ ቢሮ አቅንተው አለምነህን ከስፖርት ስፖርትን ከዜና ፋይል እንዲነሳ ያደረጉ መሆኑን አለምነህ በሬዲዮ ቀን ከፋና ቴሌቪዥን ባደረገው ቆይታ አስታውሶ ነበር።
በቁም ነገር የመፅሔት ሥራው በወቅቱ አለም አቀፍ ስራዎችን ጨምሮ ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች በተለይም በስፖርታዊ ጉዳዮች ማራቶን ላይ ትኩረት አድርጎ ፅፏል።
በአብዛኛው አትሌት አበበ ቢቂላ ላይ ትኩረት ያደረጉ ፅሁፎቸን ለአንባቢያን በማድረስ በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል።
ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ የዶስቶቭሰኪ
"notes from underground የተሰኘውን
መፅሐፍ 'ሰውዬው'
በማለት ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ
5ሺህ ኮፒ በ21 ቀናት ውስጥ ተሽጦ አልቋል።
በተጨማሪም
"Gentle Creature" "የህዋዋ
ፍጡር" "
The Cardinal "
"The
dream of the rediclous man" የተሰኙ
ስራዎችን ተርጉሟል። ነገርግን በወቅቱ በነበረው የግል ህይወቱ ገጠመኝ ምክንያት ለህትመት ሳይበቃ ቀርቷል።
በሄራልድ ጋዜጣ ላይ እንግሊዘኛ አርቲክሎችን ይዞ ፅፏል። The sun በተሰኘው ጋዜጣ የአፍሪካ እግር ኳስ የናይል ፖለቲካ አካል ነው ወይ? በሚል እርዕስ ይፅፍም ነበር፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ፡ የቃላት ሀብታሙ ፡ አድማጩና ትንታጉ አለምነህ ዋሴ በሥራ ዘመኑ ከታላላቅ ሰዎች አክብሮትና አድናቆትም ተችሮታል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ህይወታቸው እስካለፉበት ጊዜ ድረስ በእጅጉ ያደንቁት የነበረ ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነው፡፡
በሞያው ላበረከተው አስተዋጽኦ ምንም አይነት እውቅና እና የክብር ሽልማት ያልተበረከት ቢሆንም ነገርግን ሰዎች የሚያከብሩት አለምነህ ዋሴ ለውጡ ባመጣቸው በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድም ጭምር በእጅጉ የሚወደድ እና የሚደነቅ ጋዜጠኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ
በጉዟቸው ወቅት አሀዱ ሬዲዮ በር ላይ ተመልክተውት ከመኪናቸው ወርደው ደቂቃዎችን ወስደው ከእርሱ ጋር ንግግር አድርገዋል። ጤናው ተጓድሎ ባለበት ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ደውለው እንደጠየቁትም አለምነህ ያስታውሳል፡፡
ተወዳጁ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ እጅጉን አድማጭና አንባቢ ሰው በመሆኑ የሚወዳቸውን ቃላቶችና ድምፆች ይቀዳል። የኔ ድምፅ የኔ ብቻ አይደለም በእኔ ውስጥ ዳሪዎስ ሞዲ አለ። ከዳሪዎስ ሞዲ ብዙ ነገሮችን ወስጃለሁ። ቃል ወስጃለሁ። ድምፅ ወስጃለሁ። ከብዙዎች ብዙ ተምሬያለሁ። ይላል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ ፣ በፋና ሬዲዮ፣ በአዋዜ ሬዲዮ በማህበራዊ ሚዲያና በማስታወቂያ ከ35 ዓመታት በላይ አገልግሏል። እያገለገለም ይገኛል።
በተለይም በአዋዜ የሬዲዮ ቲውቡ ላይ አስገራሚና አስደንጋጭ እውነታዎችን ይመረምራል። በሰበር ዜናዎቹ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ መረጃዎችን ይዳስሳል።
የሚዲያ ሙያ በፖለቲካ ዓለም
እና በፖለቲካ ተሳትፎ ተቃኝቶ ባለሙያው ለሀገሩ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምንም አይነት እውቅና ሳይሰጠው መቅረት እንዳሌለበትና ይህም መለወጥና መስተካከል ያለበት አሰራር ነው። ሲል ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ
ያምናል።
አለምነህ በግል ህይወቱ በኩል ትዳር የመሰረተው በ32 ዓመቱ ከወ/ሮ ገነት ቱፋ ጋር ነበር። ጋዜጠኛው ከባለቤቱ ገነት ቱፋ
አምስት ልጆችን አፍርቷል። በኋላም በመሰረተው ሌላ ትዳር ስድስተኛ
ሴት ልጅ ወልዷል።
ጋዜጠኛ አለምነህ ህይወቱ ቀለል ያለ እጅግ በጣም ሙዚቃ የሚወድና የሚያዳምጥ
አፍቃሪ ሰውም ነው። አለምነህ ስለፍቅር ሲያወጋ እንዲህ ብሎ ነበር።
"የምወዳትን
ሴት ሽበቷን ነው ማየት የምፈልገው"
አለምነህ ህይወት በአቅራቢያው የሚማር ድንቅ ሰው ነው።
ተሰጥኦ ፣ ግብረገብን ፣ ማህበራዊ ህይወት እያንዳንዱ አብረው የሚሄዱ አንዳንቸው ካንዳቸው የማይነጠጣሉ በህይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን
ከተሞክሮው ያካፍላል ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፡፡
" በህይወቴ የሚያዝናናኝ ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር ተገናኝቼ መጫወት እና ዐይን እና ጆሮ መሆን ነው " ይላል
ዓይናማው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ!
የመዝጊያ ሀሳብ ፤
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
አለምነህ
የ1980ዎቹን የሬድዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ ስናነሳ በቀዳሚነት
ከሚነሱት አንዱ ነው፡፡ አለምነህ በዚያ ነጎድጓዳማ ድምጹ ብቻ በቃላት አጠቃቀሙ ለሙያው ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ ነው፡፡ በተለይ
የባህረሰላጤው ጦርነት በ1982 ተገቢውን የአድማጭ ትኩረት እንዲያገኝ የአለምነህ ሚና ትልቅ ነበር፡፡ አለምነህ ነገርን አጣፍቶ
ወይም ለዛ ሰጥቶ ማቅረብን ተክኖበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ብዙዎች ወደ ጋዜጠኝነት እንዲሳቡ አለምነህ ትልቅ አስተዋጽኦ
አበርክቷል፡፡ አለምነህ የውጭ ትንታኔዎችን ሲያቀርብ ፤ አንዳንድ ወቅታዊ ለሰው የሚስቡ ጉዳዮችን እንካችሁ ሲል በቃላት
አመራረጡና አጠቃቀሙ ብዙዎች የመማረክ ጉልበት አለው፡፡ አለምነህ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ባለፉት 35 አመታት
በቀላሉ የማይረሳ አሻራ ትቶ ያኖረ ድንቅ የሙያ ሰው ነው፡፡ አለምነህ በሬድዮ ሳይወሰን የተለያዩ መጽሀፎችን በመተርጎም
ከአንባቢ ጋር ቁርኝት ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ አለምነህ በማስታወቂያው ዘርፍም ላይ የራሱን ምልክት ያኖረ ሰው ሲሆን ቁምነገርን
በመሰሉ ምርጥ መጽሄቶች ላይም የጻፈ ነው፡፡ አለምነህ ዘንድሮ
በ2014 የሬድዮ ቀን ሲከበር የ50000 ብር ስጦታ ወይም ሽልማት ከቀድሞ መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ሬድዮ ተበርክቶለታል፡፡ ተወዳጅ
ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ግለ-ታሪክ ላይ አለምነህን ለማካተት ስናስብ የ2ኛው ትውልድ ፈርጥ በመሆኑ ነው፡፡ አለምነህን ጨምሮ በርካታ ፈርጦች ታሪካቸው ሲዘከር ትውልድ ያስታውሳቸዋል፡፡
/ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በጋዜጠኛ ባንቺአየሁ አሰፋ የተሰናዳ ነው፡፡ የቁምነገር መጽሄት መስራች ታምራት ሀይሉ
ላደረገልን ትብብር ምስጋናችን ይኑር/
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ