156. ሁለገቡ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ

 

  ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-እውቀት/ ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ የሚድያ ባለሙያ ደመቀ ከበደ ነው፡፡

 

              ማንነት በአጭሩ

 

ጋዜጠኝነት በውል ከሚገነዘቡት የሚጠቀስ፣ ታታሪነቱና ለስራው የሚያሳየው ስነ-ምግባር የተመሰገነለትና በትምህርትና ልምድ የታገዘ ሙያዊ ክህሎት ካላቸው ሁለገብ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ባለሙያዎች ይመደባል፡፡ ደመቀ ልከኛ ገጣሚና ደራሲም ነው - ሶስት የግጥምና የድርሰት መጽሐፍትን አሳትሟል፡፡ ጋዜጠኝነትን በሁሉም የስርጭት አምዶች ማለትም በህትመት (ጋዜጣ) ፣ በብሮድካስት (በሬዲዮና በቴሌቪዥን) እንዲሁም በዲጂታል (ኦንላይ ሚዲያ) በተግባርና በዕውቀት ከሰሩ ጥቂት የሀገራችን ጋዜጠኞች ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ደግሞ በሙያዊ እርከኖች በማለፍ ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ሚዲያ መሪነት (ማኔጀርነት) የደረሰ ሙያዊ ልምድ በማካበት ስራውን ተግብሯል፡፡ በሙያው ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ስልጠናና ሽልማት ያገኘ ሲሆን ጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦትን የትምህርት መስክ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በማዕረግ ፣ የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ (ሁሉንም “A” በማምጣት) ተመርቋል፡፡ በወጣትነት ዕድሜው ለከፍተኛ የመሪነት ደረጃ የበቃው ደመቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዓይን ባንክ ምክትል ስራ አስኪያጅና የኮሙኒኬሽን ኃላፊ በመሆን አገልግሏል፡፡ የተለያዩ ሁነቶችን (ኤቨንቶችን) በማዘጋጀትና የሰራ ሲሆን በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጥናትና አማካሪነትም እየሰራ ይገኛል፡፡

 

ውልደትና ዕድገት

 

“ሞጣ ቀራኒዮ ፣ ምነው አይታረስ

በሬ ሳላይ መጣሁ ፣ ከዚያ እስከዚህ ድረስ”

 

እየተባለች በቅኔ በምትጠቀሰው ሞጣ ከተማ በ1976 ዓ.ም ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተምሮ ያጠናቀቀው በዚያው ሞጣ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ ደመቀ ዕድገቱ በአያቶቹ ቤት ሲሆን የሚጠራውም በአያቱ ነው፡፡ “የሰብዕናዬ ሀውልቶች” ሲል አያቶቹን ይገልጻቸዋል፡፡

ደመቀ በአያቶቹ ቤት እንደ “መቁረጫ” ልጅ እየታየ ያደገ ሲሆን ሬዲዮ በማድመጥ፣ ከአዲስ አበባ ተመላላሽ አውቶቡሶች ጋዜጣና መጽሔት ለምኖ በማንበብና በክበባት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ነው ባደገበት ሰፈሩ የሚታወቀው፡፡ ደመቀ ካለ የሬዲዮ ትረካ፣ ግጥምና የጋዜጣ ንባብ አለ፡፡ ጎበዝ ተመሪ በመሆኑ ቤተሰብ በሌሎች ሙያዎች እንዲማር ቢወተውተውም “ምኞቱን” የተማረና ምኞቱን እየተገበረ ያለ ነው - አብሮ አደጎቹ ጋዜጠኛና ገጣሚ የሆነው በልጅነቱ ነው ይሏችኋል ብትጠይቋቸው፡፡

 

 

 

የጋዜጠኝነት ሕይወት (ከጀማሪነት እስከ ሚዲያ ማኔጀርነት)

 

ደመቀ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ስራ አጀማመሩ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ተሸላሚና መጽሐፍ ያሳተመ መሆኑን ሰምተው የነበሩት የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረቦች የራሱን ታሪኩን በጋዜጣው ለማተም ቃለ መጠይቅ አደረጉለት - ታትሞ ወጣ፡፡ በዚያውም የወቅቱ የጋዜጣው ም/ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋና ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ብርሐኑ ባልደረባቸው እንዲሆን አደረጉት፡፡

በልጅነትና ዩኒቨርሲቲ ያጎነቆለውን ጋዜጠኝነቱን በተለይ የአጻጻፍ ስርዓትን በውል የተማረው ለአጭር ጊዜ (ስድስት ወራት) በሰራበት  በሪፖርተር ጋዜጣ በአለቆቹ ከነበሩት እሸቴ አሰፋ፣ ሔኖክ ያሬድና ቤተልሔም ነጋሽ ነው፡፡

ቀጥሎ ወደ ፋና ብሮድካስቲንግ ያመራው ደመቀ በመዝናኛና ኪነ ጥበብ ክፍል ለአራት ዓመታት ሰርቷል፡፡ ሁለገብነቱንና ታታሪ ጋዜጠኝነቱን በተግባር ያስመሰከረው ፋና ውስጥ ሲሆን ባሳየው ከፍተኛ የስራ አፈፃፀም ፋና ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የሰራተኞች ሽልማት ከተሸለሙት አስር ጋዜጠኞች አንዱና በዕድሜና ስራ ልምድ ትንሹ ነበር፡፡ በፋና ተወዳጅ የነበሩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን የተጋባዥ እንግዳ ሙዚቃ ግብዣን፣ ፋና ግለሰብን፣ የእሁድ ምሽት ምርጥ ሙዚቃን፣ የፋና ጥበባትንና ሰላም የተሰኙ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቷል፡፡ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለውለታ፣ በስራቸው ስመ ጥር የሆኑ እንግዶችን አነፍንፎ በማቅረብ ምስጉን ነበር፡፡ “ኮሎኔል ሳሕሌ ደጋጎን፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን፣ የመጀመሪያዋን ሴት ተዋናይ ሰላማዊት ገ/ስላሴን፣ አስካለ አመነሸዋን፣ ሰዓሊ አለ ፈለገ ሰላምን፣ ፍራንሲስ ፋልሴቶን፣ ካራላምቦስ ባምቢስን፣ አትሌት ዋሚ ቢራቱን፣ የመሳሰሉ ከ150 በላይ እንግዶችን በተለያዩ ፕሮግራሞች ቃለ መጠይቅ በማድረጌ እጅግ እደሰታሉ” ይላል ደመቀ፡፡

   

 

ከበረከት በላይነህ ጋር በየሳምንቱ የአድማጮች የሙዚቃ ግብዣን ያቀርብ የነበረው ደመቀ በተለይ “ጉብኝት በሬዲዮ” የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ሃሳብ በማፍለቅ ከሔኖክ ስዩም ጋር በጥምረት ሲያዘጋጁት ነበር፡፡ በፋና ብሮድካስቲንግ ያሳለፈውን ሙያዊ ቆይታ በተለይም የኤዲቶሪያል ግምገማ በበጎም በጥሩም ያስታውሰዋል - ለመማማር የነበረውን ጠቀሜታ ያህል ለሙያዊ ሽኩቻና ፖለቲካዊ ፍጆታ ይውል እንደነበር በመጥቀስ፡፡

ደመቀ ከፋና ለቆ በክልሉ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ከጓደኞቹ ጋር ወደ ባሕር ዳር በማቅናት በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በፕሮግራም ማሻሻያ ክፍል ተ/ኃላፊነትና በዜና ክፍል ዋና አዘጋጅነት አገልግሏል፡፡ የአሁኑ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የያኔው አ/ብ/መ/ድ ተቋማዊ አደረጃጀቱ እንዲሰፋና ሙያዊ ትግበራዊ የላቀ እንዲሆን በቆየባቸው ሶስት ዓመታት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ የወቅቱ ባልደረቦቹ ይመሰክሩለታል፡፡ ዛሬ ላይ ስመጥር የሆኑ በርካታ አዳዲስ ጋዜጠኞች እንዲቀጠሩና ሰልጥነው ስራ እንዲጀምሩ በማድረግ፣ ሰርቶ በማሰራትና አዳዲስ የፕሮግራም ሃሳቦችን በማፍለቅ አሻራ አኑሯል፡፡ “ሰዓተ ዜና” እና “የአርሶ አደር” ወግን የመሳሰሉ የፕሮግራም ፎርማቶችን በማፍለቅ ሚዲያ ተቋሙ ተወዳዳሪ እንዲሆን የበኩሉን ተወጥቷል፡፡ በ2005 ዓ.ም አዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሲመረቅ ለአበርክቷቸው ከተሸለሙት ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡

ደመቀ ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ የነበረውን የአየር ንብረትና አካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት ያደረገ “አክርማ” የተሰኘ ፕሮግራም ከፎረም ፎር ኢንቫይሮንመንት ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል፡፡ በ “ኢንቫይሮንመነት ኤንድ ክላይሜት ጆርናሊዝም” የጋዜጠኝነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ስልጠና ካገኙና በዘርፉ ልምድ ካላቸው ጥቂት ጋዜጠኞች አንዱ ሲሆን በአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት በሚዘጋጁ የአየር ንብረት ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እንዲሳተፉ ዕድል ከተሰጣቸው የዓለም ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የ “ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ኢንቫይሮንመንት ዲጂታል ሪፖርተርስ” አስተባባሪና አርታኢ ነው፡፡

ደመቀ ለአጭር ጊዜያት ቢሆንም የአፍሪኸልዝ ቴሌቪዥን የመቋቋም ጅማሮ ላይ የሚዲያ ማኔጀር ሆኖ የሰራ ሲሆን የኤዲቶሪያል ፖሊሲን ጨምሮ የተለያዩ ማንዋሎችንና የፕሮግራም ፎርማቶችን አዘጋጅቶ ሙያዊ አስተዋጽኦውን ተወጥቷል፡፡

ደመቀ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ በስራ ላይ ሲሆን ከ74 በላይ የዓለም ቋንቋዎችን እያሰራጨ በሚገኘውና አውስትራሊያ መቀመጫውን ባደረገ Special Broadcasting Service (SBS) የኢትዮጵያ ኮረስፖንደንት፣ የመልቲቾይስ/ዲኤስቲቪ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አማካሪ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡

 

 

     ገጣሚው ደመቀ ከበደ

 

በልጅነቱ ከትምህርት ቤት፣ በጉርምስናውም በሞጣ አራት ዐይና ጎሹ የከያንያን ማህበር፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና በሙሉዓለም ባህል ማዕከል እንዲሁም አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በፑሽኪን ባህል አዳራሽ የግጥም ስራዎቹን ሲያቀርብ ነበር፡፡ በተለይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል “ፌላኔሙኔሙኒም” በሚል የብዕር ስም ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ እነ ኑረዲን ኢሳ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ሸጋው ሙሉማር፣ ሀብታሙ የኔአባት፣ ዳንኤል አማረ፣ አስቴርና ሌሎችም ውብ ጥበባዊ ስራዎቻቸውን ያቀርቡ ስለነበር ደመቀ ከዓባይና ጣና ጋር የተዳጎሱ ግጥሞችን ያቀርብ ነበር፡፡ በተለይ በፊደላት የሚገጥማቸው “ኧረ በ ነ በ ነ” መሰል ስራዎቹ አድቆትን ያተረፈባቸውና የራሱ መለያ አሻራዎቹ ሆነው እስካሁንም በርካታ ግጥሞችን የተቀኘባቸው ዘየዎቹ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲ ሳለ በጓደኞቹ አማካኝነት “የራስ ጥላ” የተሰኘ መድብል ያሳተመው ደመቀ በኋለም በ2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስነ ፅሑፍ ታሪክ በብሬል፣ በምልክት ቋንቋ፣ በኦደዲዮና በፅሕፈት (ለአይነ ስውራን፣ መስማት ለተሳናቸው፣ ማንበብ ለሚችሉና ለማይችሉ እንዲሆን) የተዘጋጀ “አንድ ክንፍ” የተሰኘ የግጥም መድብል አሳትሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በከፍተኛ ድምቀት አስመርቋል፡፡

     

 

“ደመቀ ከበደ - ከ ጣና ዳር” እያለ በሶሻል ሚዲያ በሚያቀርባቸው የፌስቡክ ግጥሞቹ ዕውቅናን ያገኘ ሲሆን ከዓመታት በፊት የሸክስፒር 400ኛ ዓመት ሲከበር የምስራቅ አፍሪካ ወጣት የግጥምና ሙዚቃ ባለሙያዎች በብሪቲሽ ካውንስል አማካኝነት በተዘጋጀው የሱዳን ካርቱም ፌስቲቫል ከተመረጡ ሰባት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው፡፡ ለ15 ቀናትም የሸክስፒርን ቅኔዎች አተረጓጎም፣ የትወና ግጥም አጻጻፍና መሰል ስልጠናዎችን አግኝቶ ተመልሷል፡፡ ደመቀ በቅርቡ የሚለቀቁ ለበርካታ ሙዚቀኞች ግጥሞችን ያበረከተ ሲሆን ለባህል ሙዚቀኛው በውቀቱ ሰውመሆን ያበረከተው ተወዳጅ ዘፈን ማለትም “ ሞናሊዛን አይቶ ዓለም ተደነቀ - ጎጃም ያለሺውን አንቺን ያላወቀ” የሚለውን የባህል ሙዚቃ ግጥም ከዓመታት በፊት ማበርከቱ ይታወሳል፡፡

ደመቀ ለህትመት ዝግጁ የሆነኑ የተለያዩ የረጂምና ኖቬላ ድርሰቶች እንዲሁም ግጥሞች፣ የባህልና ታሪክ መጻህፍት ያሉት ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ከብርሐኑ በላቸው ጋር “የሞሳድ ስውር እጆች” የተሰኘ የትርጉም መጽሐፍ በማሳተም ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡

 

የስነ-ተግባቦትና ዲጂታልና መደበኛ ሚዲያ አማካሪው ደመቀ

  

 

ደመቀ ስነ-ተገባቦትን በከፍኛ ኃላፊነት ሰርቷል፡፡ በብሌን ጠበሳ ምክንያት ብርሐን ያጡ ወገኖችን በልገሳ በሚገኝ ብሌን ብርሐን ማየት እንዲችሉ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዓይን ባንክን በምክትል ስራ አስኪያጅነትና በኮሙኒኬሽን ኃላፊነት ለሶስት ዓመታት ተኩል አገልግሏል፡፡ በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአሜሪካና ህንድ የዘርፉ ምሁራንና ተቋማት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር የተጀመረውን ስራ ከማኔጅመንትና ቦርድ አባላት ጋር በመቀናጀት እንዲጠናከር እንዲሁም በኢትዮጵያ የብሌን ልገሳ ባህል እንዲሻሻል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በሕንድ አገር የጤና ተግባቦትና የአካል ልገሳ ተቋም አመራር ስልጠናዎችንና ወርክሾፖችን በተከታታይ የወሰደ ሲሆን የብሌን ልገሳ ባህል እንዲዳብር ሙያዊ አበርክቶ አድርጓል፡፡

ደመቀ ከስነ-ተግባቦት ዘርፎች አንዱ የሆነውን የሁነት ዝግጅት መድረኮች በመምራት የሰራ ሲሆን በዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን የሀገር ውስጥ ሁነቶች ክፍል ኃላፊ ሆኖ በሰራበት ወቅት ታላላቅ ሀገር አቀፍ ሁነቶችን (ኤቨንቶችን) አስተባሯል፣ መድረኮችንም መርቷል፡፡ 

በዲጂታልና መደበኛ ሚዲያዎች የስልጠናና ማማከር፣ የይዘትና ፎርማት ማበልጸግ የተለያዩ ድርጅቶችን እንዲሁም የተቋም አወቃቀርና ምስረታ ማማከር ስራዎችን ይሰራል፡፡

ደመቀ በተለያዩ ሚዲያዎች ሙያዊና ወቅታዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን አሜሪካን አገር ለሚገኙት “ናፍቆት ኢትዮጵያ” እና “ጎጆ” ለተሰኙ የዲጂታል መፅሔቶች መጣጥፍና ወቅታዊ ትንታኔዎችን ይፅፋል፡፡

 

 

ማህበራዊ ንቁ ተሳታፊው ደመቀ

 

አብረውት የተማሩትና በቅርበት የሚያውቁት ደመቀ “ሰው ወዳጅ” ነው ይሉታል፡፡ ብቻውን የመመገብ ባህል የለሌለው በመሆኑ ሰው አጠገቡ ከሌለ ምግብ ሳይበላ ሊውልና ሊያድር ይችላል፡፡ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ሲጠፋበት ደውሎ በመጠየቅ ይታወቃል፤ ጓደኝነትን በማጽናት የሚታወቀው ደመቀ ረጂም ዘመን የቆዩ በርካታ ወዳጆችአሉት፡፡

 

ደመቀ ብዙ ልሰራው የማሰበው አለኝ ከሚላቸው ጉዳዮች አንዱ የማህበረሰብ አቀፍ በጎ አገልግሎቶችን ነው፡፡ በ ትውልድ ከተማው በመስጊዶችና ቤተክርስቲያን ቃጠሎ የተነሳ አጋጥሞ የነበረውን ቀውስ ብልህነት በተሞላበት መልኩ እንዲረግብና ነዋሪዎች የቀደመ አብሮነታቸው እንዲቀጥል ከአብሮ አደጎቹ ጋር የሰራው ስራ የሚያስመግነው ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የአትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን አርአያነት በመከተል ከሶስት ጓደኞቹ ጋር ሆነው በዋግኽምራ ዳስ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎችን መማሪያ ክፍል ምቹ ለማድረግ እየሰሩ ነው፡፡ የወዳደቁ የቢሮና የቤት ቁሳቁሶችን በግሪንኢኒሺየቲቭ የልማት ድርጅት አማካኝነት በማሰባሰብና ወደ ገንዘብ በመለወጥ የብሎትኬት ሁለት የተለያዩ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ መማሪያ ክፍሎችን ማሰራት ጀምረዋል፡፡ በጦርነቱ ሰበብ ግንባታው የተቋረጠ ሲሆን አካባቢው ሰላም ሲሆን ፕሮጀክቱን ተረክቦ የሚያሰራው ግሪን ኢኒሺየቲቭ የልማት ድርጅት በቶሎ ጨርሶ ለማህበረሰቡ እንደሚያስረክ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡

 

 

 

 

ሽልማትና ዕውቅናዎች

 

ደመቀ ከታች ጀምሮ ለንቁ ተሳትፎውና ኪነ ጥበባዊ ስራዎቹ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዓመታዊ ስነ ፅሑፍ ልዩ ሽልማት፣ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የዓመቱ ምርጥ አፈፃፀም ተሸላሚ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አንዱ ተሸላሚ፣ የአብመድ ሚዲያ ኮምሌክስ ምርቃት ጋዜጠኞችና ሰራተኞች ሽልማት ልዩ ተሸላሚ፣ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የምርጥ ስራ አፈጻፀም ምስክር ወረቀት፣ የጣና ሶሻል ሚዲያ አዋርድ የ2012 የወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃ ዘርፍ አሸናፊ፣ የ “ኢንቫይሮንመንት ጆርናሊዝም” ፌሎሺፕ አሸናፊ ሲሆን ሌሎች በርካታ የምስክር ወረቀቶችም አግኝቷል፡፡

ደመቀ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነው፡፡

የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

ደመቀ ከበደ ገና በልጅነቱ ወደ ስነ-ጽሁፉ አለም የገባና በዚህ ዝንባሌው በመቀጠል እምቅ ክህሎቱን ያሳየ ባለሙያ ነው፡፡ ደመቀ በፍጹም አይደክመውም፡፡ ለመማር ፤ ለለውጥ ፤ ለአዲስ እይታ ሁሌም ዝግጁ ነው፡፡ ደመቀ ለስራ ትጉህ እንደነበር በተለይ ከ2000-2004 ፋና ይሰራ በነበረበት ጊዜ ለብዙዎች አርአያ ፤ የትጋት ተምሳሌት ነበር ፡፡ ይህ ትጋቱ ከ2004 በኋላም ቀጥሎ ባለፉት 10 አመታት በሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ የራሱን ትጋት ያሳየ ነው፡፡ ደመቀ ፤ ይጽፋል፤ ቃለ-መጠይቅ ያደርጋል-ሁነቶችን ያዘጋጃል፡፡ አይደክመው፡፡ ባለፉት 14 አመታት በሚድያው ዘርፍ ላሳየው ጥረት የዚህ ኢንሳይክሎፒዲያ አዘጋጆች አክብሮታችንን እንገልጻለን፡፡ ደመቀ በሙያው ላበረከተው አስተዋጽኦ ይህ ግለ-ታሪኩ ያንስበታል፡፡ ትውልድ የሰራውን እንዲያውቅ ደመቀን ሰንደናል፡፡  









 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች