152.ኤልያስ ተክለወልድ ገብረጊዮርጊስ ማን ነው?
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣
በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ
አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ኤልያስ ተክለወልድ ነው፡፡ ኤልያስ ተክለወልድ በፋና ሬድዮ ለ11 አመታት ፤
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ደግሞ ላለፉት 3 አመታት በትጋት እያገለገለ የሚገኝ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ነው፡፡ ከ2000
አ.ም በኋላ ወደ ሚድያው አለም ከመጡ ባለሙያዎች አንዱ ስለሆነው ኤልያስ እዝራ እጅጉ ያጠናከረውን አጭር ግለታሪክ በጥሞና እናንብብ፡፡
‹‹……..ጎላ ብለው የተፃፉ በቀይ የደመቁ፤በጥቁር ቅብ ቀለም ዋና ርዕሳቸው ከዝርዝር ሀተታቸው ገዝፈው የሚታዩት የሰርቶ አደር እና የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ፤ አሁን ላይ ስማችውን በቅጡ የማላስታውሳቸው እንደ ብርቅ የሚታዩ የቀለማት መጽሄቶች በቤታችን ግድግዳዎች ላይ ተለጥፈዋል።
እነርሱን ደግሞ ደጋግሞ ማንበብ፤በቦታ ለይቶ በቃል መያዝ፤ ከታናናሽ ከታላላቅ እኩያ ጓደኞች ቤተሰቦች ጋር ግድግዳን እየዳሰሱ ፤ይህ ጽሁፍ የት ላይ ይገኛል?እያሉ በእጅ እየጠቆሙ ንባብ መሰል ውድድር ማካሄዳችን እርግጥ ነው።
አውደ ዓመትን ከሚያስናፍቁኝ ገጠመኞች አንዱ እነዛ በጋዜጣና በመጽሄት የተሸፈኑ የቤታችን ግድግዳዎች ተቀደው ሳይሆን በላያቸው ላይ ለእኔ አዳዲስ የምላቸው ጋዜጦች ተደርበው ስለሚለጠፉ ከግድግዳ ወደ ግድግዳ እየተዘዋወሩ ማንበብ ልዩ የበዓል ትዝታዎቼ ናቸው፤ በዓልና የግድግዳ ላይ ንባብ ሰለማይነጣጠሉብኝ አይረሱኝም።
የልጅነት ቋሚ ቤተ-መፅሐፍታችን እነሱ የግድግዳ ላይ ጋዜጦች መዋቢያም መማሪያም ነበሩ ፤ጎረቤት ዘመድ አዝማድ ቤት ስሄድም ይዘቱ ይለያይ እንጂ ጋዜጦቹ ተመሳሳይ ዓላማና ግብ ስላላቸው ግድግዳዎቹ ቋሚ መምህራን ነበሩ።
በዛ በልጅነት አንደበት በክፍል ውስጥ የአማርኛ መጻህፍትን ማንበብ፣በሰንበት ትምህርት ቤት መንፈሳዊ ግጥሞችን ሞነጫጭሮ ማቀረብ ወዘተ …. ምናልባትም ለዛሬው የሙያው ሚዛን መድፋት መሰረቶች ናቸው ብዬ አምናለው።›› ሲል ባለታሪኩ ለሙያው ጅማሬ የሆነውን ታሪክ አጫውቶናል፡፡
ትውልድና ዕድገት
ከአዲስ አበባ ከቀድሞው ንጉሥ አፄ - ሚኒሊክ አዲስ ዓለምን ዋና ከተማቸው እንድትሆን አጭተዋትም ነበር።
የመጀመሪያ አውራ ጎዳና መንገድም በእሷ ተዘረጋ።
ንጉሱም ለመጀመሪያ ጊዜ በወቅቱ የነበረውን ሩሎ መኪና እየነዱ በእርግጥ ስንት ሰዓት እንደፈጀባቸው ለመድረስ
እንጃ በእሷ
ተጓዙ ።
ኤልያስም ትውልድና ዕድገቱ
አዲስ- አለም ከተማ ልዩ ስሙ አራዳ ቀበሌ 03 ወርሀ ሚያዚያ በ1976 ዓ ም ተወለደ።
እናቱ ወይዘሮ
ትርሲት ደምሴ ከአባቱም ከአቶ ተክለወልድ ገብረጊዮርጊስም በላይ የማሳደግ ኃላፊነትን ይበልጥ ተወጡ።
ኤልያስ ከመጨረሻው
ከተቆጠረ አንደኛ ከፊተኛው ሲቀናነስ ደግሞ የመጨረሻ ልጅ በመሆን ሶስት እህቶች እና ስድስት ወንድሞች አሉት።
ኤልያስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በወቅቱ ስያሜ በአለቃ- ኪዳነወልድ ትምህርት ቤት በአሁኑ ኤጄሬ ጨንገሬ።
የሁለተኛ ደረጃ
ትምህርቱን ደግሞ
በአዲስ አለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤የመሰናዱ ትምህርቱን በሆለታ -ገነት አጠቃላይ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
ኤልያስ በመልኩ ጥቂት ጠቆር በማለቱ ከቤተሰብ መልከ - ገጽታ ትንሽ ይለያል።በዚህ ብቻ ሳይሆን በጸባይ ነጭናጫ እና እልህን ከሀይለኝነት አዳምሮ የያዘም ነበር።
በዚህ ሀይለኝነቱ ሳቢያም ከቤት እስከ ሰፈር በጓደኞቹም ዘንድ ልዩ የመታወቅ ዕድል ነበረው ። ኤልያስ የልጅነት እልህ ይኑርበት እንጂ ግን በልጅነቱ ሁሉን ታዛዥ ስራ ወዳድ ፣ለሁሉ ተላላኪ የሰፈሩ መልዕክተኛ ጭምር በመሆኑ አሁን ከሚታወቅበት መጠሪያ ስያሜው
ኤልያስ በፊት ማሙሽ በሚባለው ስሙ ይቀድማል፡፡
በእርግጥ አሁንም ከፊሉ የአዲስ አለም ቤተሰብ ዘመድ አዝማድ በዚሁ መጠሪያው ይጠቀሙበታል ፤እሱም ታሪክን የሚጭር በመሆኑ በድሮ ስሙ ሲጠሩት በአዲሱ የስያሜ ለውጤ ስለምን አልጠራችሁኝም አይልም፡፡ ይልቁንም እድሜውን ሳይሆን ትዝታዎቹን እያስታወሰ ደስ ይለዋል።
ከማሙሽ ስያሜው በተጨማሪ ከዛፍ ላይ ሲንጠላጠሉ መውደቅ፣ በፈረስ በአህያ ሲጋልብ መፍረጥ ኳስ ሲጫወት መንከባለል፣ ሌባና ፖሊስ ወዘተ እንዲሁም የልጅነት መለስተኛ የቮልስ ዋገን የመኪና አደጋ መሰል ገጠመኞችን አስተናግዶ ስለሚያውቅ ተደማምረው በድሉ የሚል ተቀጽላ ስያሜንም አግኝቶ ነበር።
በወጉ ለብሶ እንዲሁም ተጫምቶ ከማደግ ይልቅ እርቃነ ገላን መለመላውን ከሚሯራጡ ልጆች መካከል የሚመደብ በመሆኑ ከእነዚህ ሁሉ ጉዳቶች ተጠብቆ ያድግ ይሆን? የሚል ጥርጥር የገባቸው ቤተሰቦቹ በድሉ የሚል ተጨማሪ ስያሜንም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አውጥተውለት ነበር።
ኤልያስ ጥቂት እንዳደገ ለአቅመ -ትምህርት ቤት መዋልም ሲደረስ ቁጥብነት ዝምታን ማስተዋልን ጭምትነትን ያዘወትር ጀመር።
በዋናነት መምህርት መስከረም በምታስተምርበት በእዚያው በቤታቸው አቅራቢያ በሚገኘው የመንግስት መዋህለ -ህጻናት ገባ ።
ልዩ ልዩ መጫወቻዎች ስነ-ምግባርን የሚያስተምሩ ኢትዮጵያዊ መዝሙሮችን ተማረ።መምህርት መስከረም አንድ ቀን ታዲያ ተማሪዎቹ በጣም ያስቸግሯት እና አንድ የቤት ስራን ሰርታችሁ ኑ ሳይሰራ የመጣ ይቀጣል ስትል ትእዛዝ ሰጠች፡፡
እሱም ምን መሰላችሁ ሁላችሁም ሰኞ ስትመጡ ለወላጆቻችሁ ነግራችሁ ጸባይ ገዝታችሁ ኑ ጸባይ ሳይገዛ የመጣ ይቀጣል አለች ።
ሰኞ ደረሰና ሁሉም ተማሪዎች ክፍል ገብተው ሁሉንም ልጅ ተራ በተራ መምህርት መስከረም ትጠይቅ ያዘች።
የት አለ ጸባይ ገዝታችሁ የመጣችሁት አሳዩኝ አለች።
ሁሉም የክፍሉ ተማሪ የተባለውን ሳይሆን ጸባይን አንድ ከሚገዛ የቁስ ዕቃ ጋር አመሳስሎ ለጥያቄው አፉ ላይ የመጣለትን ምላሽ መስጠት ጀመረ።
እማዬ ገዝታልኝ ሳጥኑ ውስጥ እረስቼ መጣሁ ነገ አመጣለው ፤የገሚሱ ልጆች የጸባይ ግዙ የቤት ስራ ምላሽ ነበር …
እማዬ ቅዳሜ ከገበያ እገዛልሃለው ብላኛለች የሌሎቹ ቀጠለ ……. አባዬ አሁን እቁብ አልደረሰኝም በሚቀጥለው እገዛልሃለው ብሎኛል…
ከማልቀስ እስከ ዝምታ ልዩ ልዩ ምላሾች ተስተናገዱ…. መምህርት መስከረም በጥሞና የሁሉንም ተማሪ ምላሽ በአንክሮ ትከታተል ነበር።
አሁን የእኔ ተራ ደረሰና አንተስ ማሙሽ የታለ ያመጣኸው ስትል ጠየቀችው?ማሙሽ /ኤልያስ/ መለሰ
አይ መምህር ጸባይ
መግዛት ማለት እኮ አለመረበሽ ማለት ነው ሲል
ምላሽ ሰጠ ።
እስቲ ድገመው ማሙሽን ሰማችሁት ተማሪዎች ……. ኤልያስ አለመረበሽ ነው ጸባይ መግዛት ሲል ደገመው ።
ለመሆኑ ማን ነገረህ ?አለችው መምህርቷ አይ መምህር ብዙ ሰዎችን ጠይቄ ነው አላት።ውስጡ ግን ለከፋ ቅጣት እየተዘጋጀ እንባውን በጉንጮቹ ዱብ ዱብ እያደረገ።
በሉ ሁላችሁም ቁሙና አጨብጭቡለት እርሱ ብቻ ነው ጸባይ ገዝቶ የመጣው ሲባል
የቅጣት እንባው ፍራቻ
ወደ ደስታ ተለውጦ የልጅነት ምሁር የሆነ መሰለው ።
መምህርት መስከረም “ቀጠለች……. አንተ” ማሙሽ በወቅቱ ስሜ ጋዜጠኛ ነው የምትሆነው! ጎበዝ እሺ እኔ ደግሞ ጋዜጣን እንጂ ጋዜጠኝነትን አላውቅ! ሌላ ስያሜን የማፈላለግ ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ ……በሬዲዮ ዜና የሚናገር በወቅቱ ንግስት ሰልፉ፣ ብርቱካን ሀረገወይን፣ ነጋሽ መሀመድ ፣አለምነህ ዋሴ
እኔ እንደ እነርሱ እንዴት ሆኖ ብቻ የኤልያስ የሙያው መሰረት ከዚህ ታሪክ ገጠመኝ አስተውሎት ይመዘዛል ።
አይዋ ቤት / አብነት ትምህርት
ከታች ከበቂ በላይ የአዋራ ቡናኝ ፤ከታዛ ስር በድንጋይ ከተደገፉ ግንድላ እንጨቶች ላይ በተለያዩ ቀለማት የተሰፉ ልብሶችን፤ የተቀደዱ ሱሪዎችን ፤አንገት ላይ ጣል የሚደረጉ አሊያም የሚጠመጠሙ ፎጣዎችን ያነገቱ በርካታ ህጻናት 03 ቀበሌ በምትገኘዋ የፊደል ገበታ መአድ አይዋ ቤት ኤልያስ ፊደልን ተምረው ከሚያስተምሩ እኩዮቹ ጋር የፊደል ገበታን ተቋድሷል።
ግብረ-ገብነት፤ስነ-ጽሁፍ ፤የኔታን የማክበር ባህልን ኢትዮጵያዊነትን
አራዳ በምትገኘው አይዋ
ቤት ኤልያስ ተምሯታል ።
ዕድሜ አይከበርም ማለት ሳይሆን እውቀት በግልጽ ተነጻጽሮና ተወዳደሮ መስፈርት ተቀምጦለት አቀማመጡም በዕውቀቱ
ልክ መሆኑን ልብ ማለት የጀመረው ከዚያው ነው።
እጅግ ተከብረው ከሚፈሩት ፈተናን ፈትነው በእጅጉ ከሚቀጡት ፤ ደግሞም ወደ ቀጣዩ ምራፍ ከሚያሸጋግሩት
አይዋ የፊደል ትምህርትን ኤልያስ ተከታትሏል ።
አዲስ አለም ለአብነት ትምህርት በጣሙን ቅርብ ናት ።በተለይም የዲያቆናት ማፍሪያ ናት።ኤልያስም በርዕሰ-አድባራት ወገዳማት ዳግማዊት ጽዮን አዲሰ አለም ማርያም ይህንኑ ትምህርት ከንውረድ የውስጣጢዎስ ከ የኔታ ገብረ መስቀል ከአባ ኃይለማርያም ዘንድ ቀስሟል ።
አዲስ አለም ማርያም የፍሬ ሀይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤትም በመዘምራን ፤በኪነ ጥበብ ፤በድራማ በበጎ አድራጎት ክፍሎች በመግባት ለተቸገሩ ምንዱባን ድጋፍን፤በርካታ ድራማዎችን ጭውውቶችን የዜና ዝግጅቶችን ሰርቷል ፡፡
ይህ ሂደት ለቀጠለው የጋዜጠኝነት ፍላጎት ተጨማሪ ሚና ማበርከቱ አልቀረም፡፡
ህዳር
ጽዮን
ማርያም
እና
ኤልያስ
/የልጅነት
ትዝታ በጨረፍታ /
አዲስ አለም ሁሉን ኢትዮጵያዊ አሰባጥራ ባላት አንድ ትምህርት ቤት አስተምራ በአንድ እቁብ አደራጅታ በአንድ እድር ሀይማኖትን ሳትልይ አስተሳስራ ታሪክን ያኖረች ከተማ ናት።አሁንም ብዙ ነገር ተቀያይሮ እንኳን ይኸው ባህሏና
በጎ ገጽታዋ ያመዝናል።
ኤልያስም ሆነ ጓደኞቹ ትላልቅ
አዛውንት እናት አባቶች ሰፈር ጎረቤት
ወይ በአመዛኙ የመጀመሪያ ልጅ ስም ተጠቅሶ የእከሌ አባት አሊያም የእከሊት እናት ተባብሎ መጠራራት የተለመደ ነው።
ከሩቅ ሀገር የሚመጣ እንግዳ እንኳን አጋጣሚ ይሁን ወይም ባህል በዚሁ በአካባቢው ስያሜ ይጠቀማል የታሪክ ተመሳስሎነቱ አሁን ላይ ያስገርመዋል።
ለኤልያስ ሙሉ ስም ማለት በቃ ይኸው ነው፡፡እሱ በተለይ ባደገበት ማህበራዊ መስተጋብሩ ይበልጥ በጎለበተበት የአዲስ አለሟ አራዳ ከተማ ።
ኤልያስ እናቱን እትዬ ይል እንደሆን ሌሎችም የእናቱ እኩዮች የጓደኞቹ ቤተሰቦች ጋሼ እትዬ እማዬ ከመባባል ውጪ መጠሪያ ስማቸውን አንድም አያውቁም::
አሊያም ትዝ አይላቸውም፤እንዲያም ሲል በነጠላ ስም መጥራቱ
የመራራቅ ምልክት አድርገው ስለሚቆጥሩት ይሆናል ፈጽመው አይጠቀሙበትም ።
እናም አንድ ቀን ዓመታዊው የህዳር ማርያም በርካታ ህዝብ የሚታደምበት ክብረ በዓል ሆነና ኤልያስ ያለቤተሰብ ፍቃድ ተነስቶ ለብቻው ተጓዘ ።
ክብረ በዓሉ አልቆ ሁሉም ወደ መጣበት ሲመለስ እርሱ ወዴት ይሂድ ያቺ ሆደ ሰፊዋ ግን ደግሞ ጠባቧ ሰው የሚርባት ከተማ እንደ መስከረም ወፍ በአመት አንዴ በምዕመናን ትጥለቀለቃለች ።
በቁጥር ከሚታወቁ ጥቂት ፎርድ መኪኖች ውጪ ዝር የማይልባት አዲስ አለም በዚያን ወቅት ያን ሁሉ ሰውና ተሽከርካሪ ሲተረማመስባት ሲያይ የመጣበትን አቅጣጫ ስቶ መኖሪያ ቤቱን ፈጽሞ ዘነጋው ።
የእናቱን ቤት አቅጣጫ ፈጽሞ ማስተዋል አቅቶት ቆሞ ማልቀስ ጀመረ። ለእርዳታ ሰው ከበበው፡፡ ቀበሌ ሰፈር የማን ልጅ ነህ ሲሉ ጠየቁት? በጥያቄያቸው አለማወቅ መልሶ ተገረመ!
እንዴት እሱን የእትዬን ልጅ ማን ነህ ብለው ይጠይቁታል? የእትዬ ልጅ ነኝ ሲል መለሰ፡፡እትዬ ስሟ ማን ነው? እትዬ የእኔ እናት ናታ በቃ ሌላ ስም የላትም!
እትዬ እኮ ለቅሶውን ቀጥሎ …..ጭራሽ እትዬንም አለማወቃቸው ለእሱ ድንጋጤን ፍርሃትንም ጨመረበት፡፡
እትዬም እንደሱ ጠፍታ ይሆን እንዴ ሲል ተጨነቀ፡፡
እድር፣እቁብ ቤት ወይም ቤተክርስቲያን እናትህን ማን ናት?ብለው ነው የሚጠሯት እሱን ንገረን? “ከከበቡት ሰዎች መካከል የተፍታታ ጥያቄ መጠየቁ ነው” :: የእኔ እናት በቃ ሌላ ስም የላትም ስሟ እትዬ ነው፡፡
ለቅሶውን ቀጠለ ……..ቀጠለ ጥያቄውም ከከበቡት
ሰዎች ከያቅጣጫው በንዴትም በሀዘኔታም በአግራሞትም
ተጧጧፈ ፡፡
እንዴት የእናቱን ስም አያውቅም? አውቃለው! የእትዬ ልጅ ነኝ አለ እሱም በብስጭት ቤታችሁ የት ነው?
እዛጋ ቤታችን ላይ ደጅ ላይ እንኳን ምልክቱ አበባ አለ ቀይ አበባ አለ::ደጋግሞም እረዥም ለቅሶውን……….
በስም ያልተደገፈ በአቅጣጫ ያልተጠቆመ በቀበሌ ያልተረጋገጠ የእናት ስም እትዬ ከየት ይምጣ ነው የሚለው?
በአቅጣጫ የማይታወቅ
አበባ ያለው ደጃችን ምልክት ሰዉን ግራ አጋባው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ኤልያስን ፍለጋ
ከተሰማራው ግብረ ሀይል መካከል
በታላቅ ወንድሙ ዘላለም
የሚመራው ክንፍ ኤልያስን ከከበበው ህዝብ መካከል
ደረሰ።
ኤልያስ ወንድሙን ሲመለከት በደስታም በድንጋጤም ዘሎ ተጠመጠመበት።በዚህ ምክንያት እናቱ ያልነገረችው
ሌላ የደበቀችው ስም እንዳለ ጠረጠረ።
ትርሲት ደምሴ ለኤልያስ የእናት ስም ብቻ ሳይሆን የአደጋ ጊዜ መውጫ መሆኑን ተረዳ፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ
እውነተኛ ግለ
ታሪክ ጻፉ ተብለው የቤት ስራ ተሰጣቸው።
ኤልያስም ምክንያት ይፈልግ ነበርና ይህን ግለ-ታሪኩን መዝዞ ጻፈው።ዳጎስ ያለ ማርክ አግኝቶበታል፡፡
በጣም ምርጧ ተብላ በመፅሄት
ለመታተም በቃች፡፡ እርዕሷም
ኤልያስ የእትዬ ልጅ ተባለች፡፡ በተቋሙ ቆይታው የእትዬ ልጅ ኤልያስ ተጨማሪ ስያሜንም አግኝቶበታል።
ኤልያስና
ሆለታ
ገነት
/የመሰናዶ
ትምህርት
ቤት
/ ቆይታው
ኤልያስም ሆነ
ጓደኞቹ በጋራ ከሚጋሯቸው በርካታ ባህሪያት መካካል የነገ ዓላማን አርቆ ማሰብ ስራን መውደድ የቤተሰብ ጫናን ማቅለል ተደጋግፎ ተረዳድቶ መኖር ባህላቸው ነው።
ይህን የበለጠ ያጠናከረላቸው ደግሞ በወቅቱ አዲስ አለም ከተማ ላይ የመሰናዶ ትምሀርት ቤት ገና ባለመከፈቱ
ከትውልድ ቦታቸው በቅርብ እርቀት ላይ የምትገኘው ሆለታ ገነት በጋራ በመሆን ቤት ተከራይተው ለሁለት አመታት ትምህርቱን ተከታተለ።
በወቅቱ አርባ የሚሆኑ የአዲስ አለም ልጆች ጥሩ ውጤት አምጥተው ነበር ሆለታ መሰናዶ ትምህርት ቤት የገቡት ።
ይህም አጋጣሚ ይበልጥ የወንድምና የእህት አይነት ፍጹም ግንኙነትን ይበልጥ አጠናከረ፡፡ ኤልያስ ከጓደኞቹ ይበልጥ የሚለየው የአባት አይነት ባህሪን ይላበሳል ።
በዚህም ምክንያት በጓደኞቹ ዘንድ የማክበር ፍራቻን ይፈሩታል ።ልጅነት ወይም ወጣትነት አዘንብሎበት የተለየ ፍላጎት አይጫነውም።
በዚህ ባህሪው የተነሳ/በእውነቱ/ አባ የሚሉ ተጨማሪ ቅጥል ስሞችን በሆለታ ቆይታው አግኝቷል፡፡ እስካሁንም የቅርብ ጓደኞቹ በዚሁ ስሙ ይጠሩታል።
ጥቂት ያስከፋዋል ብለው የሚያስቡት ክፍተት እንኳን
ሲፈጠር አባ
ወይም በእውነቱ ሳይሰማ ይሉና ይጨነቃሉ፡፡
ወይም የተፈጠረውን እንዳልተፈጠረ ያስመሰሉታል፡፡
ድንገት ተጣልተውም ከሆኑ ይታረቃሉ፡፡
ማትሪክን በበቂ ዝግጅት እና ጥናት ሁሉም እንዲያልፉ ማስተባበር መረዳዳት ማስጠናት በተለይም ለሴት ተማሪዎች ከጥቃትም መከላከል እና ማጥናት ላይ እንዲያተኩሩ አደረገ፡፡
በውጤቱም ከአንድ ተማሪ በስተቀር እሱም ፍቅር ነገር ጀማምሮት ሁሉም ጓደኞቹ ከፍተኛ ነጥብ አምጥተው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ የበኩሉን ሚና አበረከተ።
የተመደቡበትን ዩኒቨርስቲ
እስኪያውቁ ድረስ ሁሉንም ጓደኞቹን አስተባብሮ የክረምት በጎ ሰራ ላይ እንዲሰማሩ አደረገ ።ችግኝ መትከል ማስጠናት ቤተ-መፅሀፍት ንባብ ላይ እንዲያተኩሩ አደረገ።
የቤተሰብ ጫናን ለማቃለል ስራ ወዳድነትን በተጨባጭ ለማሳየት የተለያዩ የቀን ስራዎችን ቀድሞ ገብቶ ጓደኞቹም እንዲገቡም ያደርግ ነበር።
በተለይ ኪሞዬ ተብላ በምትጠራው የገጠር ቀበሌ ከአዲስ አለም አምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በወቅቱ አንድ የሆላንድ የአበባ አምራች ድርጅት ከፍቶ ስለነበረ በቀን 8 ብር እየተከፈለው ይሰራ ነበር።
እሱን ተከትለውም በርካታ ጓደኞቹ የቀን ስራውን ተቀላቀሉ፡፡ ሲሚንቶ መሸከም፣ መቆፈር፣ አበባ መልቀም፣ አስቸጋሪ የሚባሉ የጉልበት ስራዎችንም ይሰራ ነበር።
ከሚያገኘው ላይ ለትራንስፖርት ደርሶ መልስ ሁለት ብር ይከፍል ስለነበር ይህን ለማዳን በእግሩ ከጓደኞቹ ጋር እየተጓዘ ይሰራ ነበር።
በአበባ ልማት ስራ ቆይታው ድርጅቱ በሰራተኞቹ ላይ ያልተገባ ጉልበት ብዝብዛን የክፍያ ማነስ የኬሚካል ርጭት ጥንቃቄ ጉድለት ይስተዋል ስለነበር ይህ እንዲታረም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎች እንዲገኙ በማድረግ ችግሩ እንዲቃለል አድርጓል ።
በዚህም የቀን ውሎ አበል ከ 8 ወደ 12 ብር እንዲያድግ ኬሜካል ለሚረጩት ወተት እንዲቀርብ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲጀመር ሌሎች ለስራ የሚያስፈልጉ የጥንቃቄ ቁሳቁሶች እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ ሚናውን አበርክቷል ።
ጉዞ ወደ ዩኒቨርሲቲ
ከቀን ስራ
ከአበባ ልማት የቀን ገቢ ከወዳጅ ዘመድ በተገኘ ስጦታ
ለዩኒቨርስቲ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ኤልያስ ሸማመተ ።
ሸውደው ከሚያሸውዱ የፍሬሽ ተማሪዎች ይጠብቀው ዘንድ መረጃን ሰበሰበ።ድሮ ሰው ከቤት ወጥቶ ትንሽ ሲርቅ ቤተሰብ ጎረቤት ያለቅስ ነበር።
የኤልያስ ሽኝትም በተመሳሳይ በለቅሶ የታጀበ ነበር ።በአጋጣሚ ሆኖ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ከእሱ ጋር አብረው የተመደበው ጓደኛው ብሩክ አለሙ ይባላል ።
በቅልጥፍናም አዲስ አበባን ቀድሞ በማወቅ ብሩክ ከሁሉም ጓደኞቻቸው በላይ ስለ ሸገር መረጃ ነበረው፡፡ በዚህም ምክንያት የኤልያስ ቤተሰቦች በብሩክ አብሮ መመደብ የብሩክ ቤተሰቦች ደግሞ ልጃቸው ቀዥቃዣ ነው ብለው ስለሚያምኑ እርጋታ ካለው ከኤልያስ ጋር በመመደቡ በጣም ደስ አላቸው።
እንደውም መላው ቤተሰቡ ለኤልያስ አደራ አንተ አባቱ ነህ ብለው አሳሰቡት።ቀደም ብሎ የደረሰው የትምህርት አይነት ህግ ቢሆንም ወደ ጋዜጠኝነት ቀይሮ የልጅነት የመምህርት መስከረምን ጋዜጠኛ ነው የምትሆነው የሚለውን ህልም ሊያሳካ የእሱንም ፍላጎት ሊፈጽም ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።
በእርግጥ በወቅቱ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል በግብአትም በመምህራንም በቅጡ የተደራጀ አልነበረም ።
ከእሱ የሚቀድመው አንድ ባች ሲሆን እንደውም ብዙ ነገር ተሻሽሎ ነው እነ ኤልያስ የገቡት ይሏቸው ነበር የእነሱ ሲኒየሮች።
ኤልያስ ፈጥኖ ባለመናገር በእርጋታና በማስተዋሉ በተማሪዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ቶሎ በመፍታት በማስታረቅ ይታወቅ ጀመር።
በዚህም ምክንያት የዶርሙ ተጠሪ አድርገው መረጡት፤ጥቂት ቆይተው ደግሞ የብሎኩ ተወካይ ሲሉ ሰየሙት፡፡ ኤልያስ በዶርምና በብሎክ አካባቢ የሚያስፈልጉ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲሟሉ የዲሲፕሊን ግድፈቶች እንዲታረሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መስራት ጀመረ ።
የክፍል እና የዲፓርትመንቱ ተወካያቸውም እራሱ ነበር ።በሂደትም ከፍተኛ ፉክክር እና ምርጫ በሚካሄድበት አመታዊው የተማሪዎች መማክርት ምርጫ ላይ ተጠቁሞ እና ተወዳድሮ ትምህርት ክፍሉን በመወከል የተማሪዎች መማክርት አባል ሆነ።
መማክርቱ ተሰብስቦ ሲቋቋም ቅድሚያ ጥናት ይካሄድ ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር የተማሪው ፍላጎት
የእኛ ስራ ወዘተ በሚለው የጥናት ቡድኑን በመምራት ግኝቶችን
አቀረበ ።
በጣም ጠንካራ
በእውቀትም በስራ ልምድም የዳበረ የመማክርት አባላት የነበሩበት ስብስብ በመሆኑ ጸጋ ጥበቡ ሰብሳቢ ኤልያስ ተክለወልድ ደግሞ በጣም ብዙ ችግሮች የሚስተዋልበትን የምግብ ክፍል ኮሚቴን እንዲመራ በተደራቢነትም አካዳሚክ ኮሚቴን እንዲያግዝ ኤልያስን መረጡት።
ኤልያስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አበርክቶት
መቼም በዩኒቨርስቲ ውስጥ የተማሪዎች ትልቁ የቅሬታ ምንጭ የምግብ ጥራት አጀንዳ ነው ። ዓመታዊ በጀቱን ማወቅ
የምግብ አሰራሩን የሰራተኛውን ብቃት እና ሙያ የዳሰሰ የአብዛኛው ተማሪዎችን የመመገብ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የዳሰሳ ጥናት በመስራት ከሚመለከተው አስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር አስቸኳይ መፍትሄ ላይ እንዲደርስ አደረገ ።
ለተማሪዎች የሚቀርበው በርበሬ ከገበያ ላይ የሚገዛ በመሆኑ ሰራተኛ ተቀጥሮ ዛላው ተገዝቶ ተፈጭቶ እንዲቀርብ አስወሰነ ።
አጠቃላይ ሳምንታዊ የምግብ ሜኑ ለውጥ እንዲመጣ አዳዲስ የምግብ አይነቶች ለምሳሌ በወቅቱ ፖስታ መኮረኒ እንቁላል ተጠናክሮ እንዲቀርብ አደረገ ።
ጠንካራ ኮሚቴን በስሩ በማደራጀት ክትትሉን አጠናከረ። መላው ተማሪ ከሳምንት ሳምንት ምን እንደሚመገብ በዝርዝር ተለጥፎ እንዲያውቀው አደረገ።
ልዩ የበዓል አቅርቦት ከገበያ ላይ የበግ ስጋ ለስላሳ መጠጦች የፍራ ፍሬ አቅርቦቶች ለተማሪዎች እንዲቀርቡ አደረገ ።
ከዚያ በፊት የነበሩ የመማክርት አባላት ብዙ ጠንካራ ጎን ቢኖራቸውም የተማሪዎች ካፌ ገብተው ሲመገቡ አይታይም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ላይ ያላቸው አተያይና ተቀባይነት እምብዛም ነበር።
የነኤልያስ መማክርት በአንጻሩ ሰልፍ ይዞ ከተማሪዎች ጋር የሚመገብ ትሪን ሰብስቦ የሚያነሳ በተለያዩ የተማሪዎች የመመገቢያ አዳራሾች እየተዘዋወረ የሚቃኝ በመሆኑ በተማሪዎች ዘንድ አመኔታንም ክብርንም ያገኘ ነበር ።
አንድ ቀን በወቅቱ ስጋ አቅራቢ ግለሰቡ በቄራ መታረዱን የሚያረጋግጥ ማስረጃን ሳያቀርብ ጥራቱን ያልጠበቀ ስጋ ወደ እስቶር
እየተራገፈ እያለ ኤልያስ ደረሰ።
ማረጋገጫ ቢጠይቅም ማቅረብ አልቻለም። ኤልያስን እዛው በአቅራቢያ በሚገኘው
አንድ ቢሮ እስቲ እንነጋገር ብለው
አስገቡት እና
በጣም በርከት ያለ የታሸገ በወቅቱ ለተማሪ የሚያስደነግጥ ብር እጅ መንሻን ለኤልያስ አቀረቡለት፡፡
ምንድነው ይሄ ሲል ጠየቀ? ማረጋገጫ የለኝም ለዛሬ እለፈኝ በቀጣይም አብረን እንሰራለን ሲል ለማግባባት ሞከረ፡፡
ኤልያስ የሚለውን አጣ! አባ ቀደመው…… እኔ ተማሪ እጅን አውጥቶ የመረጠኝ ብር ተቀብዬ በተመረዘ ስጋ በሽተኛ እንዳደርገው ነው? ሲል ጠየቃቸው በአስቸኳይ ስጋው እንዲመለስ አደረገ፡፡
ከዛን ዕለት ጀምሮ ስጋ ይቀርብ የነበረው በጋሪ እና በግለሰብ መኪና በመሆኑ በቄራ መኪና ብቻ እንዲቀርብ አስወሰነ።
በሌላኛው ቀን
በተመሳሳይ በትልቅ ተሳቢ መኪና ውሃ በጣም በተነከረ ጆንያ ምስር አተርና ሩዝ ሲራገፍ ደረሰ፡፡ ተመሳሳይ
መደለያዎች ሊያውም ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጭምር ታክለውበት ለማግባባት ሞከሩት፡፡
አሻፈረኝ በማለት የተራገፈውን አስቁሞ እዛው ከሳምንት በኋላ ደርቆ ተመዝኖ ሲታይ እስከ አርባ ኪሎ ጉድለት አሳየ- ተስተካክሎ እንዲገባ አደረገ።
በዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ኤልያስ ላይ ጥርስ ተነከሰበት ።በርካታ ማስፈራሪያም ደረሰበት፡፡ አንድ ቀን ከጊቢ ውጪ ወጥቶ ከተማ ላይ እያለ በርከት ያሉ ጎረምሶች በቅርብ እርቀት እየተከታተሉት እንደሆነ
ሲረዳም ባህር ዳር ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እሮጦ ገባ፡፡ ተከተሉት
ለሰዓታት በዙሪያው ቆመው ጠበቁት፡፡
አንዱ ደፍሮ፤ ዛሬ ብታመልጠን ነገ እናገኝሀለን ፤እንገልሃለን፤ ስራችንን አላሰራ ብለኸናል አለው ።ኤልያስ ምላሽ አልነበረው የሰራው ወንጀልም የለም።
ከደሃ ቤተሰብ ተወልዶ ተምሮ ለመመለስ እያሰበ ብዙ አላማ እያለው ድንገት በሰዎች እንደሚገደል ሲያውቀው ሆድ ባሰው፡፡ ወዲያው ለዩኒቨርስቲው ን ዶክተር ጸሀይ ደውሎ አሳወቀ፡፡
ከጥበቃ
ጋር መኪና ተላከለት፡፡ የተማሪዎች መማክርትም አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ ጥቃቱን አወገዘ፡፡ኤልያስ በማግስቱ ወደ ሌላ ዩኒቨርስቲ ትራንስፈር ጠየቀ፡፡ በፍጹም ስራህን በሰራህ ሌባን በተዋጋህ አንተን ከቀየርኩማ የሞትኩት እኔ ነኘ! አለው የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸሀይ፡፡
ወዲያው ከሁሉም የምግብ አቅራቢዎች ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ተካሄደ።ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ በጽሁፍ ለሁሉም ተሰጠ፡፡
ኤልያስን በተመለከተ ለሚደርስበት አይደለም አካላዊ ጉዳት የጤና እክል እንኳን ተጠያቂዎቹ እነሱ እንደሆኑ ተነግሯቸው ቃለ- ጉባኤ ላይ ተፈራረሙ።
ኤልያስም ከግድያ ሙከራ ማምለጡ የመማክርቱ እና የዩኒቨርስቲው የወሰዱት እርምጃ ይበልጥ ሞራል ሆኖት ብዙ ስራዎችን አከናወነ ።
በተለምዶ የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች ዘግይተው ስለሚገቡ ለዕረፍት ክረምት ላይ ወደ ቤተሰቦቹ መሄድ እንኳን አቁሞ በመደበኛነት ይሰራ ነበር።
ከመማክርቱ ሰብሳቢ ጸጋ ጥበብ / አሁን ዶክተር የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ/ጋር እና ሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን
የልማት ስራዎች እንዲሰሩ አድርገዋል ።
የተማሪዎች መዝናኛ ስፍራዎች የፋውንቴን ግንባታ ፣የዋናው ግቢ በር ግንባታ ጅማሮ፣ ተጨማሪ ቤተ መጽሀፍት እንዲከፈት ፣የመንገድ እና መሰል ስራዎች እንዲፈጸሙ ኤሊያስ የበኩሉን ሚና አበርክቷል። የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል/ የጆኮ / ክበብ እንዲቋቋም በሂደቱም ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ጋር በመነጋገር ተማሪዎች የሬዲዮ የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ በተደረገው ጥረት ኤሊያስ ሚናው የጎላ ነበር፡፡
በኋላም ድርጅቱ ነጻ የሬዲዮ የአየር ሰዓት እንዲያገኝ ሆነ። የመጀመሪያው የዲፓርትመንቱ ብለው የዩኒቨርስቲው ነጸብራቅ የተሰኘች መጽሄትም ታትማ ለንባብ በቃች ይህ እንዲሳካም ድጋፍ ክትትል አድርጓል፡፡
ምርጫ 97 ዓም ተከትሎ የተፈጠረውን እጅግ አስቀያሚ ግጭት እንዲረግብ በሂደትም ውይይቶች እንዲካሄዱ ወደ ሰላም የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲመለስ ካደረጉት መካከል ኤልያስ ግንባር ቀደሙ ነው።
ኤልያስ ተክለወልድ በነበረው አጠቃላይ ተሳትፎ ባልተለመደ መልኩ ለሁለተኛ ዙር ካውንስሉን እንዲያገለግል በሀገር አቀፋ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህብረት ላይ በአባልት እንዲሳተፍም ተደርጓል።
አጠቃላይ ላበረከተው ሁለተናዊ አስተዋዕፆ የባህርዳር ዩኒቪርስቲ ሴኔት የማህበራዊ ዘርፍ የላቀ ብቃት
የወርቅና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ በመሆን ከዩኒቨርስቲው ተበርክቶለታል።
አዲስ አለምና ልዩ ትዝታዎቹ
መወቅ ሲመጣ መዘናጋትን እንዳያስከትል በብዙ ደጋፍና ክትተል ለዚህ ያበቁንን ደግሞም ለማመስገን
ብዙ ቁም ነገርን
ለቀጣዩ ትውልድ ጥሎ ለማለፍ
በተለየ መለኩ እነዛ አብረውት ከተማሩት ጋር ደግሞም ካስተማሩት እንዲሁም ከታናናሾቹ ጋር ከወላጆች ጋር ብክነትን የቀነሰ አንድነትን የሚያጠናክር የጋራ የምርቃት መርሃ- ግብር እናዘጋጅ የሚል ሀሰብን ኤልያስ አፈለቀ፡፡
ይህንንም ለጓደኞቹ አጋራ፡፡ ሀሳቡ ዳበረ፡፡ በ1999ዓም በአዲስ አለም ከተማ እና ወረዳዋ በወቅቱ የተመረቁ 50 የሚደርሱ ተማሪዎች ሀሳቡን ወደዱት፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ወረዳው ተጋራ ። ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርታቸው ትጉሃን የሆኑ እና በጣም ሰነፍ የሚባሉ ተማሪዎች ተለይተው ያስተማሩን መምህራን በሙሉ የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች በአጠቃላይ የሀገር ሽማግሌዎች ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት እኛ የእናንተ ፍሬ ነን እና መርቁን የነገ ተስፋዎች ደግሞ ከዚህ ፈለግ ተምራችሁ ይበልጥ አጎልብቱት በሚል መርህ በልዩ ሁኔታ በአዲስ ዓለሟ አዳራሽ ወልደው ያሳደጉን ትንሽ ትልቁ በጋራ ደጋግመው መረቁን፡፡ ዛፍን ተክልን የአቀመ ደካማ ቤቶችን ጠጋግነን በአድን በጋራ ተቋድሰን ለቀጣይ ስራዎች ቃል ተገባብተን አሳለፍን። ኤልያስ ያነሳው ሀሳብ የቤተሰብ የተናጥል ድግሶችን አስቀርቶ የጋራ ደስታን አጎናጽፎ ለትውልድ ምሳሌን ትቶ ከሁሉም ዘንድ ምርቃትን አስገኝቶ ሽልማትን አቋድሶ አብሮነትን አጠናከረ ። ይህ መሰረት ሆኖ ባለፈው አመት በኮረና ምክንያት የተቸገሩትን ገንዘብ አሰባስበው ለመርዳት በተደረገው ጥረት ይህ ግንኙነት ቀድሞ መፈጠሩ የላቀ ሚናን አበረከተ፡፡
በሁለተኛ ዙር የሚደገፉትን በመለየት በቀጣይ የተጠናከረ ማህበር እንዲኖርም እያደረገ ይገኛል።
መጻህፈት አሰባስቦ እንዲለገስ የአዲስ አለም ማርያም ሙዜም ምንገድ እንዲጠገንም አስተዋጽኦ
አድርጓል ።
ኤልያስና
የስራ
ዓለም
በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈው ኤልያስ ያለ ስራ ውሎ ማደር የሚከብደው አዲስ አበባ የስራ ማስታወቂያን በየቀኑ ይዳስስ ጀመር። የተለጠፈ ማስታወቂያ ማንበብ ግድ ሆነበት፡፡ የተለያዩ ተቋማት ይፈተን እና ለሴቶች ቅድሚያ ወይም ተጠባባቂ ወይም እንጠራሃልን በሚል ተስፋ ስድስት ወራትን አሳለፈ። ብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በሎተሪ ቆጠራ ስራ ተወዳደረ አልፈሃል ተብሎ ተጠራ፡፡ ስራን ለመስራት በመቻሉ ብቻ እጅግ ደስ አለው፡፡ ለቃለ መጠይቅ ሲቀርብ
አንተማ ከመስፈርቱ በላይ ነህ አይሆንም ብለው መለሱት፡፡ እንዴት እኔ ማንኛውንም ስራ ለመስራት ዝግጁ ሆኜ ስምምነቴን ገልጬ እነሱ ይመልሱኛል ብሎ ዋናው አሰተዳዳሪ ጋር ለቅሬታ ቀረበ፡፡ መመሪያው ነው በቀጣይ ይወጣል አይዞህ ብለው በዲፕሎማሲ ሸኙት። አቶ እርግጤ የተባሉ የባህል ህክምና ላይ የተሰማሩ ግለሰብ በወቅቱ ለሚያሳትሙት ጋዜጣ በባህል ህክምና ላይ የምታተኩር ሌቃ የተሰኘች ሳምንታዊ ጋዜጣ ስራን ተወዳደረ፡፡
በርካታ ስራ ፈላጊዎች ተሰለፍው ነበር፡፡
ለቃለ መጠይቅ ገብተው የወጡ ተማሪዎች አንዳንዶቹ እየሳቁ ሌሎቹ ደገሞ እንደመነጫነጭም እንደ መሳድብም እያረጋቸው ይመለሱ ነበር፡፡ የእሱ ተራ ደረሰ አቶ እርገጤ ፈታኝ ነበሩ፡፤ ፈተናው እኛ መክፈል የምንችለው አራት መቶ ብር ነው ትሰራለህ አትሰራም አጭርና ግልጽ ኤልያስ በሶሰት መቶ ብርም ቢሆን እሰራለው አላቸው፡፡ በል እንተ ትልቅ ቦታ ነው የምትደርሰው፡፡ ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ተቀጥረሃል፡፡ ስራ ጀምር አሉት እጅግ በጣም ደስ አለው ስሜቱ ማታ ስራ ሰራው ብሎ ማደር ጥዋት ደግሞ ወደ ስራ ልሄድ ነው ብሎ መነሳት ከገንዘቡ ማ|ንስና መብዛት በላይ ይህ የላቀ መሆኑን ተረዳ፡፡ በሌቃ ጋዜጣ ላይ ለአራት ወራት በአራት መቶ ብር ደሞዝ ስራ ጸባዩን እና ትጋቱን ያዩት አቶ እርገጤ በአንዴ ሁለት መቶ ብር እንደተጨመረለት ነገሩት፡፡ አመሰገነ፡፡ በዚህ መሃል ሬዲዮ ፋና ስራ አወጣ፡፡ ተወዳደረ፡፡ ስራ ጀምር ተባለ፡፡ ጀመረ።
ኤልያስና ሬዲዮ ፋና
ወገንተኛ ነው የሚባለው ተቋም ውስጥ ተወዳድሮ ማለፉ ገርሞታል፡፡ በጥርጣሬ ነበር የሚመለከተው ሬዲዮ ፋናን በእርግጥ እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ይጋሩታል ።
የቅድመ ስራ ስልጠናን ለ15 ቀን ተከታተለ፡፡ ሙያዊ የሆኑ ስልጠናዎች ስለሆኑ ከወዲሁ ወደደው፡፡ በዜና እና ወቅታዊ ክፍል በወር 1ሺህ 180 ብር ተከፍሎት ስራውን ከአደራ ጭምር እንዲከወን የቋሚ ቅጥር ደብዳቤ ተሰጠው ።
ዜና ክፍል አጣዳፊ አስቸኳይ የበላይ አለቆቹም ቆንጠጥ ያለ ሀይል የተቀላቀለበት አመራርን የሚሰጡ በመሆኑ ስራው ሳይሆን በወቅቱ የሰው አመል ለጊዜው ከበደው።
ስራውንም ይበልጥ የሰውንም ጸባይ እየለመደው መጣ፡፡ ይበልጥ ዋና ስራው ላይ አተኮረ።ቀድመው ከገቡት እኩል ጠንካራ ጋዜጠኛ የሚላክበት የዜና ሽፋን ስምሪት ቦታንም እየሄደ መዘገብ ጀመረ፡፡
ደረጃውም ከሪፖርተርነት ወደ ከፍተኛ ሪፖርተርነት አመት ሳይሞላው አደገ ።ተቋሙ መዋቅር ሰራ፡፡ ባሳየው የስራ ተነሳሽነት ሁለት ደረጃዎችን በአንዴ አድጎ የዜና አዘጋጅ ሆነ፡፡
ስራውም እድገቱም ቀጠለ ከፍተኛ አዘጋጅ ረዳት ዋና አዘጋጅ በስተመጨረሻም ዋና አዘጋጅ እስከመሆን ደረሰ።
ኤልያስና የጋዜጠኝነት ሙያዊ አበርክቶው
ከፋና አመራር በተለይም አንጻራዊ የሙያ ነጻነት ስራ ላይ ማተኮር በየጊዜው የሚሰጡ ስልጠናዎች የዳበረ ልምድ እንዲያገኝ አድርጎታል።
ተቋሙ ባካሄደው የዜና ማሻሻያ ምክረ ሀሳብ ላይ ጠቃሚ የሚላቸውን ሀሳቦችን በመስጠት እንዲዳብር አድርጓል።
በተለይም የችሎት ዜና የቀጥታ ዘገባ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጀመር ያቀረበው ሀሳብ ተቀባይነት ሲያገኝ እርሱም የመጀመሪያው የዜና ችሎት ዘጋቢ በመሆን አገለገለ።
ለተወሰኑ ጊዜያት ቋሚ ዘጋቢ በመሆን የሰራ ሲሆን በሂደት ሌሎች ባልደረቦቹንም አብቅቷል።የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቋሚ ዘጋቢ፣የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ኢሲኤ ቋሚ ዘጋቢ፣በርካታ አህጉራዊ እና አለማቀፋዊ ስብስባዎችን በመዘገብ ትንታኔዎችን በጥልቀት ሰርቷል፡፡
ሀገራዊ ትላልቅ መድረኮች የቀጥታ የስልክ ዘገባዎችን ቀድመው ከሚሰሩ እና ከሚመደቡ ጋዜጠኞች ግንባር ቀደሙ ኤልያስ ነበር።
የመሪዎች መደበኛ መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ እና የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የሚሰጡትን መግለጫዎች በቋሚነትም የሚዘግበው ኤልያስ ነበር፡፡
የፖርላማ መደበኛ እና ልዩ ስብሰባዎችን ፣የምርጫ ዘገባዎችን ፣ልዩ የምርመራ እና የቅሬታ ዜናዎች፣ የውጭ ትንታኔ ዜናዎች ፣ የ 90 ደቂቃ የሀገር ወስጥ እና የውጭ ትንታኔንም ይሰራ ነበር።
ዜና መጽሄት መምራት መደበኛ የኤዲተር ስራውን መከወን ሳምንታዊ የዳሰሳ ፕሮግራሞችን መሸፈን ላይም ሰርቷል።
አስቸጋሪ የፊልድ
ስራዎችን ሀገራችን በድርቅ በተጎዳች ጊዜ መላውን የደቡብ ክልል ለወራት በመዞር ያለውን ችግር ከቦታው በማሳየት መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ በዘገባዎቹ ሚናውን አበርክቷል፡፡
የሶማሌ ክልል ድርቅ ጠረፍ ድረስ በመሄድ ዶሊ አዶ ላይ የነበረውን ሁኔታ በመዘገብ አፈጣኝ እርዳታ እንዲደርሳቸው በዘገባዎቹ አስተዋፆ አድርጓል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የሙስና ተግዳሮቶች መኖራቸውን የሚያጋልጡ ዜናዎችን ብሄራዊ በዓላት በተለይም የአድዋ እና መሰል የታሪክ ዘገባዎች መሳሳት ይታይ ስለነበር እነዚህ ተገቢውን ሚዛን አግኝተው እንዲሸፈኑ ጥረት አድርጓል ።
ከዜና ባለፈ በፕሮግራም ክፍል የነበረውን የአመራር መሳሳት እንዲሸፈን ወደ መደበኛ ፕሮግራም ክፍል ሲዛወር ስራውን በአግባቡ መከወን ጀመረ።
ፕሮግራሞች በጥራት እንዲሰሩ የበዓላት እና ልዩ ፕሮግራሞች እቅዶች እንዲዳብሩ አደረገ።ለተቋሙ ገቢ የሚያስገኙ ፕሮግራሞች ከፍ እንዲሉም አሰተዋጾ አድርጓል።
ኤልያስ አጠቃላይ የፕሮግራም ማሻሻያ እንዲደረግ የማሻሻያ ሰነድ በማዘጋጀት ለኤዲቶሪያሉ በማቅረብ ሚናውን ተወጥቷል ።
ሳምንታዊ የዳሰሳ ፕሮግራምን በቋሚነት በማስተባበር እና በመስራት ወቅታዊ እና ጥልቀት ያላቸው መረጃዎች ለአድማጮች እንዲደርሱ ሰርቷል።
የተለያዩ የሬዲዬ ዶክመንተሪዎችንም ለአየር እንዲበቁ አድርጓል።በተለይም ኤልያስ በፕሮግራም ክፍል የተረጋጋ የተናበበ ሁሉንም እንደ ዝንባሌው በማሰራት የነበረውን ክፍተት በመድፈን ፍጹም ሰላማዊ የሰርቶ ማሰራት ክፍል እንዲሆን አድርጓል።
በኤዲቶሪያል መደበኛ ስብሰባ እና ከዚያ በላይ ባሉ ግንኙነቶች ሀገራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ተቋማዊ የሰራተኞች ፍላጎቶች እና ነጻነቶች ይበልጥ እንዲከበሩ በልዩነት አቋምን ያራምድ ነበር።
በተቋሙ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ግለሰባዊ እና ቤተሰባዊ ችግሮች ሲያጋጥማቸው ፈጥኖ በመድረስም ይታወቃል።
የሁሉ ልባዊ ሚስጥረኛ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።ጓደኝነት መቀራረብ የተለየ የአድሎ ተፅእኖ አያሳድርበትም፡፡ ሁሉን እኩል ለማየት ይሞክራል፡፡
ሀይማኖት ዘር ፖለቲካ ሌላም ሌላም ልዩነቶች ለእሱ ቦታ የላቸውም ፤ሁሉን በሰውነቱ ብቻ ይቀርባል፤ የሁሉም ጓደኛ አማካሪ ነው፤ ይህ ባህሪው በተለይም ፋና ካሉት አመራሮች ለየት ያደርገዋል።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የስራ አለቆች ሰራተኞቻቸውን የሚያስከፋ ነገር ሲወስኑ በፅናት ይቃወማል፡፡ሀሳቡን እዛው በመድረክ ይገልጻል።
ተቋሙን ማክበሩ ሚስጥር መጠበቁ ደግሞ ለየት ያደርገዋል።የፋና ቲቪ እውን እንዲሆን በነበሩ የፎርማት ውይይቶች በተግባርም ለተወሰነ ጊዜ ሰርቷል፡፡
ተቋሙ ላመጣው
አንደ ሀገርም ለታየው አንጻራዊ ለውጥ ሚናውን አበርክቷል፡፡በዚህም ልዩ ቆይታ በተለይም የፕሮግራም ክፍል ስራተኞች የዜና እና የ90ደቂቃ ክፍል የስራ ባልደረቦች ስራ መልቀቁን ተከትሎ በርካታ ስጦታዎችን
ልዩ የሽኝት
መርሃ ግብርን ለቤተሰቡና ለባለቤቱ አበርክተዋል። ዛሬም ይህ ግንኙነት እንደ ቤተሰብ ከመላው የፋና ባልደረቦቹ ጋር እንደቀጠለ ነው፡፡
ኤልያስ እና የስራ ለውጡ አውራ ጎዳና
ስም ይወጣል ከቤት ይከተላል ከጎረቤት ነው እና አስራ አንድ አመት የፋና ቆይታውን የሚያሳጥር አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡
ኤልያስ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ቢመጣ ይጠቅመናል ፤ይሰራልናል፤ የሚል መረጃ ደርሷቸው ነበርና በተለይም የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ሳምሶን ወንድሙ እኛ ጋር ብትመጣና ብታግዘን የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በረቱበት፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝም ታክለውበት ገና መልቀቂያ ሳላስገባ እዛው ፋና እያለ የቅጥር ደብዳቤ ከመንገዶች ባለስልጣን ደረሰው ፡፡
መንግስት ቤት ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎት ፈጽሞ አልነበረውም፡፡
ግን ፋና ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከዚህ በላይ መቆየት እንደሌለበት ወስኖ ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከመግባቱ በፊት መረጃዎችን ያሰባስብ ነበር፡፡
በተቋሙ የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንዲገኝ ተጋብዞ ሁለንተናዊ የተቋሙ ለውጥ እጅግ አስገረመው በርካታ ስራዎችም ይሰሩ ነበር፡፡
ኤሊያስ ስለ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሲያስረዳ
‹‹….መላው ሰራተኛ በተለይም ለተቋሙ መሪ የሚሰጡት ክብር እና ምስጋና ከልብ አስደሰተኝ ፡፡በዚህም ምክንያት ፋናን ለቅቄ መንገዶች ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነት የሚዲያ ቡድን መሪ ስራን በይፋ ተረክቤ መስራት ጀመርኩ።›› ይላል ኤሊያስ፡፡
ኤልያስና
መንገዶች
ባለስልጣን
አበርክቶት
‹‹….ምቹ የሆነ የሀሳብ ተቀባይነት ሁሉንም ነገር አድርገህ አሳየን የሚሉ የአለቆች ቀና ሀሳብ ብዙ መስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ነበር ያጋጠመኝ ።›› ይላል ኤሊያስ ከአዲሱ መስሪያ ቤት ጋር
የነበረውን ትዝታ ሲያጫውት፡፡
በዚህም የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ እና ሲጠናቀቁ ትላልቅ ሀገራዊ ሁነቶችን መምራት ጀመረ። ከሚዲያዎች ጋር የትብብር ግንኙነት እንዲፈጠር ግልጽ የሆነ መረጃዎች እንዲፈሱ አመታዊ የመገናኛ ብዙሃን መድረኮች እንዲመቻቹ አደረገ፡፡
ተቋሙ እና መገናኛ ብዙሃኖች ተቀራርበው እንዲሰሩ ይበልጥ መሰረትን ጣለ።የማህበራዊ ትስስር ገጾች እና ድህረ ገጾች የመረጃ ፍሰት እንዲጨምር ወቅታዊ መረጃዎች በፍጥነት እንዲጫኑ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሰርቶ እንዲሰሩም አደረገ።
ብዙም ያልተለመደው የህዝብ ግንኙነት ተቋማዊ ማስታወቂያዎች በራስ አቅም ተሰርቶ እንዲሰራጭ አደረገ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የ 70 አመት ታሪክ በቋሚ ኤግዚቢሽን ውስጥ ተሰድሮ እንዲካተት አደረገ፡፡
በዚህም የተቋሙን ታሪክ የሚገልጽ ዶክመንተሪ ፣ የኢትዮጵያ የድልድይ ታሪክ የሚገልጽ ዶክመንተሪ ፣የገጠር መንገድ አጀማመርና ስራን የሚገልጽ ዶክመንተሪ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ከጥንቱ እስከ ቅርቡ በመንገድ ልማት ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጾ የሚገልጽ የታሪክ ዶክመንተሪ፣ የመንገድ ፋይዳን የሚገልጽ ዶክመንተሪ በመስራት በቋሚ ኤግዚቢሽኑ እንዲካተት አደረገ።
ቋሚ ኤግዚቢሽኑን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ክፍት በማድረግና በማስጎበኘት አገልግሎቱም እየሰራ ነው።
በርካታ የሀገር ሀብትን አካቶ የያዘው የተቋሙ የድምጽ እና የምስል ክምችት ሀብቶች በአርካይቭ ስርአት እንዲደራጅ ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠብቆ እንዲቆይም አድርጓል።
የአሰራር ማንዋል የፕሮግራም ማስጀመሪያ እና ማጠናቀቂያ የፕሮቶኮል ሰነድ ለሙያው የሚያግዙ ጽሁፎችን በማዘጋጀትም የክፍሉም የተቋሙም ሰዎች እንዲማሩበት አድርጓል፡፡
ተቋሙ የራሱን ሳምንታዊ የቴሌቪዥን እና የሬዲዬ ፕሮግራሞችን በራሱ አቅም እና ይዘት በራሱ ባለሙያተኞች እንዲጀምር የሚያስችል ፎርማት ቀርፆ ለማኔጅመንቱ በማቅረብ እንዲጸድቅ አድርጓል።
በተቋሙ ውስጥ እስቱዲዮ እንዲገነባ ምክረ- ሀሳብ በማቅረብ እውን እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ ነው።በዚህም ምክንያት ክፍሉ በየአመቱ የትጋት ሽልማት ዋንጫን እንዲያገኝ አድርጓል፡፡
እንደ ሀገርም ምሳሌ የሆኑ ቋሚ ኤግዚቢሽኑን ጨምሮ በርካታ ዶክመንተሪዎች በህዝብ ግንኙነት በኩል ሰርቶ እንዲሰራ በማድረጉ በርካታ ተቋማት በምሳሌነት እንዲጎበኙ ልምድ ተሞክሮውን እውቀትን እንዲቀስሙም እያደረገ ነው።
ገና ከጅምሩ የስራ ታታሪነቱን እና ትጋቱን የተመለከተው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ገና ገብቶ ስድስት ወራት ሳይሞላው ውጪ ሀገር ለስልጠና በመላክ ለኤልያስ ያለውን አድናቆቱን ገልጾለታል።
የተቸገሩትን በሚደግፈው አሳዳጊ ያጡትን ተንከባክቦ በሚያስተምረው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በፀሀፊነት በማገልገል ሀገራዊ ሀላፊነቱን መወጣቱን ቀጥሏል፡፡
በቅርቡም በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ800ሺህ ብር በላይ ከማህበሩ አባላት ጋር እንዲሰባሰብ በማድረግ ለቀይ መስቀል እንዲረከብ አድርጓል።በተለያዩ ምክንያቶች ለተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ የማስተባበር ኃላፊነቱን ተወጥቷል።
ኤልያስና
ትምህርት
በማንኛውም መልኩ መማር ማንበብ መጠየቅን አብዝቶ የሚወደው ኤልያስ የተለያዩ አጫጭር በርካታ ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡
በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከገኘ በኋላም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ወስዷል፡፡አሁን ደግሞ በቢዝነስ ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪውን ለማጠናቀቅ አጋምሷል።
በፋና ቆይታው በደቡብ ኮሪያ አለማቀፍ የሰላም ጉባኤ ላይ ከባልደረባው ጋር በመሆን ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ገለጻን አድርጓል፡፡በኡጋንዳና በኬኒያ በተካሄዱ አለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይም ልምድ ተሞክሮውን አጋርቷል።
ኤልያስና ቤተሰባዊ ሀላፊነት
የተለያዩ ሀላፊነቶችን የመወጣት ልምዱ የፈጣሪ እገዛ እና መልካም ፍቃዱ ትዳሩን በአገባቡ እንዲይዝ ተጨማሪ የስኬት ህይወትን እንዲመራ አድርጎታል።
ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ከ ወሰንባንቺ አዱኛ ጋር ለስራ መጥታ /ለአባ ጃንቦ ድራማ ቀረጻ /እዛው ሬዲዮ ፋና ቅጥር ግቢ ውስጥ ተያይተው እዛው ተጋቡ።
ፍቅራቸው ፀና፡፡ ዛሬ የሁለት ወንዶች እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው። ትላንትን አቅም ጉልበት ጊዜ በፈቀደለት መጠን የሚችለውን አድርጓል፡፡
ዛሬም የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው፡፡ነገን ለላቀ ሀገራዊ ስኬት ያልማል ለበለጠ ሀላፊነት ለመስራትም ይታትራል፡፡
ደግሞም ሊቀጥል ………...ተፈጸመ!!!
የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ
መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ኤሊያስ ተክለወልድን በ3 መንገድ ልንገልጸው እንችላለን፡፡ 1ኛ ጎበዝ ጋዜጠኛ
ነው 2ኛ ልዩ የማስተባበር አቅም አለው 3ኛ በኮሚኒኬሽን እና በማህበራዊ
ግንኙነት ከወጣትነቱ ጀምሮ በልዩ ክህሎት ዳብሯል፡፡
ኤሊያስ አብረውት በሰሩት
ሰዎች አንደበት ሲገልጽ መልካም ገጽታው ያመዝናል፡፡ ለስራው ያለው ተነሳሽነት ብሎም የተረጋጋ ሰብእናው ሚድያ ላይ ለሚሰራ ሰው
የሚመች ብሎም የሚመረጥ ሰብእና ነው፡፡ ኤሊያስን እንደሚድያ መሪ
ብንወስደው፣ የስራ መሪ በነበረባቸው ጊዜያት ለነገሮች መፍትሄ ሲፈልግ እንጂ ነገሮችን ሲያበላሽና ሲቸገር አይታይም፡፡ በተለይ ከ2009
-2011 ባሉት የፋና ቆይታው መልካም መሪነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡ ሰው የሚለካው በሚመራቸው ሰዎች ነውና ይመራቸው የነበሩ ሁሉም
ጋዜጠኞች በሙሉ ድምጽ የኤሊያስ መሪነት ይዋጥላቸው ነበር፡፡ ስራ ላይ ተግባብቶ መስራትን ያውቅ ስለነበር ብዙዎች ተጠቅመዋል፡፡
ኤሊያስ ፋና ሬድዮ በቆየባቸው ጊዜያት በአቅሙ ብዙ ስራዎችን ተሸክሞ ለመስራት ሙከራ አድርጓል፡፡ ኤሊያስ ይህንን ሁሉ የስራ ሃላፊነት
ከመጀመሩ አስቀድሞ በ1995 ግድም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ተወካይ ሆኖ ማሳለፉ ጠቅሞታል፡፡ የማስተባበር ክህሎቱን በጠዋቱ
በማዳበሩ ዛሬ ፋናም ሆነ መንገዶች ባለስልጣን ገብቶ ማስተባበሩ ቀላል ሆኖለታል፡፡ ኤሊያስ ከፋና ቀጥሎ መንገዶች ባለስልጣን ከገባ
በኋላ የሚያኮራ ባለሙያነቱን ማስመስከሩ ግድ ነበር፡፡ ለዚህም የቀድሞ መስሪያ ቤቱ ፋና የሠጠው ልምድ ትልቅ ሚና አበርክቶለታል፡፡
ኤሊያስ ይህን ግለ-ታሪክ ለማጠናከር ስንፈልግ ታሪኩን እንዲያጫውተን ስንጠይቀው በቂ የሰነድ መረጃዎች አብሮ በማያያዝ ነበር፡፡
የቅጥር ደብዳቤዎቹን ፤ ያገኛቸውን የምስክር ወረቀቶች ሁሉ አንድ ላይ በማድረግ ሰጥቶናል፡፡ ይህም ለሰነድ የሚሰጠውን ልዩ ስፍራ
ያሳያል፡፡ ከኮሚኒኬሽን ባለሙያም የሚጠበቀው ይህ ነው፡፡ ኤሊያስ ከተማሪነት -ፋና -ከፋና መንገዶች ባለስልጣን በተጓዘባቸው ጎዳናዎች
ብዙ ልምድ መቅሰሙ አልቀረም፡፡ በአሁኑ ሰአት በተለይ ሀገሪቱ በመንገዶች ማስፋፋት ትልቅ ስራ እያከናወነች ባለችበት ሰአት የእነ
ኤልያስ አይነት የኮሚኒኬሽን ሰው የግድ ያስፈልጋል፡፡ ሁሌ ታሪክ የሚጻፈው ጀብድ ለፈጸሙ ስለሆነ ነው እንጂ በየጓዳው ለዚህ ሀገር
መሰረት የጣሉ በየቤቱ ብዙ አሉ፡፡ ኤልያስ ታሪኩ በዚህ ኢንሳይክሎፒዲያ ሲሰነድለት ስላከናወነው ታላቅ ነገር ነው፡፡ ወደፊት የሚሰራውን ደግሞ ለማየት ያብቃን፡፡ እስከዚያው ግን ይህ ግለ-ታሪኩ
ሌሎችን እያነቃቃ ይቆያል፡፡/ ይህ ግለ-ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አቅራቢነት ኤልያስ ግለ-ታሪኩ እንዲሰነድ በተጠየቀው መሰረት የተሰናዳ
ነው፡፡ ይህ ግለ-ታሪክ ባለታሪኩ የሰጠውን መረጃ መሰረት በማድረግ አብረውት የሰሩ ባለሙያዎችን በማነጋገር እንዲሁም አየር ላይ
ያዋላቸውን የሬድዮ መሰናዶዎች በማድመጥ የተሰራ ነው፡፡ ይህ አጭር ግለ-ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የግለ-ታሪክ ገጾች የተቀመጠ ሲሆን
በየጊዜው አስፈላጊ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት እንዲጫን ይደረጋል፡፡ ይህ ግለ-ታሪክ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰናዳ ሲሆን ዛሬ እሁድ
የካቲት 27 2014 ለድረ-ገጽ አንባቢያን ቀረበ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ