138.ላእከማሪያም ደምሴ

          አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ላእከ ማሪያም አረፈ

      ከ 2ወር በፊት የጋሽ ላእከማሪያም ደምሴን ታሪክ ለመስራት ከቤቱ ተገኘን፡፡  ብዙ ከተጨዋወትን በኋላ የግለ-ታሪክን  አስፈላጊነት አምኖበት አንዳንድ የቆዩ ታሪኮችን አጫወተን፡፡ እናም ታሪኩን በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን  የግለ-ታሪክ ገጽ ላይ ልንሰራው ሀሳብ እንዳለን አውግተነው በሀሳቡ ተስማምቶ ታሪኩን ለመስራት ቃለ-መጠይቅ አደረግነው፡፡ እናም አንዳንድ ማድረግ ያለብንን ማስተካከያዎች ነግሮን ታሪኩን ልናወጣው በተዘጋጀንበት ሰአት ዛሬ ሀሙስ ጥር 26 2014 ጉምቱው ጋዜጠኛ ማረፉን ሰማን፡፡ 69 አመቱን ባከበረ በ4 ወሩ ህይወቱ ያለፈው ጋሽ ላእከማሪያም ጋዜጠኝነት ያለ አስተማሪ የተሰኘውን መጽሀፍ የጻፈ ለፕሮፌሽናሊዝም የሚድያ ስራ የሚሟገት በሳል ሰው ነበር፡፡ ለቤተሰቦቹ ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን እንመኛለን፡፡ ይህን የጋሽ ላእከማሪያም ደምሴን ግለ-ታሪክ እንድንሰራ በተለይ ጋሽ ላእከን ቤቱ ድረስ ተጉዘን ቃለ-መጠይቅ እንድናደርግ ለወዳጃችን ደረጀ ትእዛዙ የከበረ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡

 

1950 እና 60ዎቹ፣ አለፍ ሲልም 70ዎቹ የነበሩ አብዛኞቹ የአገራችን ጋዜጠኞች በልምድ፣ በተሰጥኦ እና በፍላጎት ነበር የሚሰሩት። ሳይንሳዊው የጋዜጠኝነት ትምህርት ባልነበረበት በዚያን ወቅት ሙያውን ጀምረው፣ በሒደት በትምህርትና ስልጠና አዳብረው፣ የውጪ ሚዲያ ወኪል እስከመሆን የደረሱ ብርቅና ድንቅ ኢትዮጰያዎያን ጋዜጠኞች ነበሩ፤ አሉም። ጊዮን ሐጎስ፣ አበበ አንዷለም፣ ጌታቸው ደስታ፣ ፀጋዬ ታደሰ፣.. እያሉ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ በልምድና በእውቀት ብስለትን የተላበሱ አንጋፋ ሰዎች ሀገርንና ሙያን በመውደድ ያገለገሉ ናቸው፡፡

 

የእነዚህን አንጋፎች ዱካ በመከተል ጋዜጠኝነትን የተካነው ላዕከማሪያም ደምሴ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ..ኤ፣ ቢቢሲ፣ ሬዲዮኖች ላይ ሰርቷል። የሩህ መጽሔት ምክትል ዋና አዘጋጅም ነበር። እንደሚታወቀው ሩህ መጽሄት ነጻ ፕሬስ በታወጀ ማግስት የተጀመረች መጽሄት ስትሆን ጳውሎስ ኞኞ ከአዘጋጆች አንዱ ነበር፡፡  በጋዜጠኝነት ህይወቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያየው ላዕከማሪያም፤ ከልምዱ በመነሳት ለጀማሪ ጋዜጠኞች መማሪያ የሚሆን መጽሐፍም አዘጋጅቷል። በጀርመን ሀገር በአድቫንስ ደረጃ ዓለም አቀፋዊ የጋዜጠኝነት ስልጠና (International institute of journalis) በጀርመን አገር ሰልጥኖ በማዕረግ ተመርቋል።







 

 

አባቱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር አባል ነበሩ። በመስከረም 11 1945 .. ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሚሊቴሪ ካምፕ ውስጥ ነው የተወለደው። ወላጆቹ ከወለዷቸው 9 ወንድና ሴቶች እሱ የመጀመሪያ ነው። አራት ዓመት ሲሆነው ቅድመ አያቱ ቤት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እየኖረ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት መማር ጀመረ። ቅደመአያቱ  ቀድመው በሰሩት ቤት ቤተሰቡ ማደግ ጀመረ፡፡  ለአራት ኪሎ ልዩ ትዝታና ፍቅር ያለው ጋሽ ላእከማሪያም ይላል ዶጁ ለተሰኘው የነጻነት መለሰ ዜማ ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡  በትምህርቱ ጎበዝ በመሆኑ ስኮላርሺፕ አግኝቶ በወቅቱ የመኳንንት ልጆች የሚማሩበት አሜሪካን ትምህርት ቤት በመግባት የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ  ውጤት አጠናቀቀ። በእዚህ ትምህርት ቤትም ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚሰጠውን ስኮላርሺፕ ተወዳድሮ በማሸነፍ ወደ አሜሪካን አገር በማቅናት ቾት የሚባለው ኮሌጅ ገባ።

***

 

‹‹..እዚያ እንደገባሁ ስሜቴ የፈቀደውን በዩኒቨርሲቲው ሊበራል አርትስ ነበር መማር የጀመርኩት። የተፈጥሮ እና የሶሻል ሳይንስ የተደባለቀበት ሳይኮሎጂ ነው። አንድ ዓመት ተኩል እንደተማርኩ በዚያን ወቅት የበላይ ጠባቂዬ የነበሩት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ምክር ሰጡኝ፤ ወደ አገሬ ተመልሼ ግዕዝ ተምሬ እንደገና ወደ የኒቨርሲቲው በመመለስ የጀመርኩትን እንድቀጥል። ምክራቸውን ተቀብዬ አቋርጬ ወደ አገሬ ተመለስኩ። በቃ ቀልጬ ቀረሁ።›› ይላል ጋሽ ላእከማሪያም፡፡

 

 

 

እንደተመለሰ ከዚያ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ማጥናት ጀመረ። ግዕዝን፣ የኢትዮጵያና የአፍሪካን ታሪክ ኮርሶች እየወሰደ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተጀመረ። ትምህርቱም ተቋረጠ። ተመልሶም ወደ አሜሪካን አገር መሄድ አልቻለም። በዚህ ምክንያት የትምህርቱን ግብ ሳያሳካ ቀረ። ግን አመፁ ቀዝቀዝ ሲል በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ኢኒስቲቲዩት ኦፍ ዴቨሎፕመኖ መስራት ቀጠለ።

‹‹……. የጎዳና ሕይወት በኢትዮጵያ Street culture in Ethiopia በሚል ለአንድ ዓመት ያካሄድኩት ጥናትና ምርምር ቀዳሚው ነው። ሌሎችም አሉ። በመቀጠል ደብረዘይት አድኣ ወረዳ ሲሺዩ ኢኮኖሚክ ጥናት ማድረግ ጀመርኩ። ከዚያ ለውጥ መጣ። ያኔ ተመልሼ ወደ አሜሪካን መሄድ እችል ነበር ግን ለውጡ ጣመኝ። በትኩሱ ደስ ይል ነበር። በዚህ ላይ እያለሁ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ማስታወቂያ አወጣ። ተወዳደርኩ። አለፍኩ። አቶ ተስፋዬ ታደሰ፣  ልዑልሰገድ ኩምሳ እና  ወይዘሮ ታቡቱ ወልደሚካኤል ፈተኑኝ አለፍኩ። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእንግሊዝኛው ክፍል ተቀጠርኩ። ይህ 1967 .. ነው።16 ወር እንደሰራሁ ግን ነገር መጣ። ለቀኩ።›› ሲል ጋሽ ላእከማሪያም በህይወት በነበረበት ጊዜ ለጋዜጠኛ ደረጀ ትእዛዙ በሰጠው ቃል ተናግሮ ነበር፡፡

 

 በጋሽ ላእከማሪያም እይታ ሲጀመር ለውጡ ደስ ይል ነበር። ኋላ ላይ ነው ፈተናው የመጣው። የተለያዩ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ሲበዙ ሙያው ፈተና ውስጥ እንደገባ ያስባል። እርሱም ብዙ ፈተና እንዳጋጠመው ያስታውሳል፡፡

 

 

 ጋሽ ላእከማሪያም ኢትዮጵያ ሬድዮ በነበረበት ጊዜ ከስቱዲዮ ቀጥታ ዜና ያነብ ነበር፡፡ፕሮግራም ያዘጋጃል፡፡ ሪፖርተርም ሆኖ መስክ ይወጣል፣ ቃለ መጠይቅ ያደርጋል። በአጠቃላይ አንድ ጋዜጠኛ መስራት ያለበትን ሁሉሰራ ነበር።

 

በስራው ላይ ፈታኝ ወይም አስቸጋሪ ነገር ገጥሞት ያውቅ እንደሆን ጋሽ ላአከማሪያም ሲናገር‹‹…ያውቃል እንጂ። ብዙ። ለምሳሌ ዲዲቲን ለወባ ብለው ሲረጩት በዝናብ ይታጠብና ሃይቅ ይገባል ዓሳና የባህር ውስጥ ነፍሳትን ይገድላል። ከዚየታም አልፎ ወፎችን፣ እንስሳትን ይገላል። በተዘዋዋሪ የሰውን ጤና ይጎዳል። ህብረተሰቡን የሚያጠፋ ኬሚካል ነው። ጉዳቱ ስለታመነበት አሜሪካን እና አውሮፓ ጥቅም ላይ እንዳይል ተከልክሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይረጫል። በዚህ ጥቅም የሚያገኙ ክልከላውን ይቃወማሉ። እና ያኔ አዋሽ ሸለቆ የተባለ ድርጅት ይህንን ኬሚካል ይጠቀም ነበር። ይህንን ለማጋለጥ የአማርኛው ፕሮግራም የምርመራ ዘጋቢው ንጉሴ ተፈራ (ዛሬ ዶክተር) የአፋርኛ ፕሮግራም ዘጋቢው ዑመር አሊ ሆነን ወደ ስፍራው ሄድን። እዚያ ሆነን እንደ አጋጣሚ ሬዲዮ ስንከታተል አፋር ውስጥ አላይደጌ የሚባል ቦታ አፋሮች መስፈራቸውን ያትታል። በጣም ገርሞን በማግስቱ ይህንን ስፍራ ለማየትና አጠናክረን ለመዘገብ ወደስፍራው አቀናን።ተመልሰን ስንመጣ ዋናው ስራችን ሆነ። ንጉሴ ሊዱን ሲሰራእንኳን የሰፈረ አፋር ወፍ አላየንም… ” ብሎ ጀመረ። እኔም በእንግሊዝኛው ዜና ሰራሁበት። በአፋርኛ ተሰራ። ትልቅ ድንጋጤ ተፈጠረ። በጉዳዩ ደርጎች ተናቆሩ። ያኔ ለሁለት ተከፍለው ነበር። በማግስቱ ጠዋት ንጉሴን ከቢሮው አፍሰው ወሰዱት። የሬዲዮ መምሪያ ሀላፊው አቶ ተስፋዬ ታደሰንም ጭምር።  እኔ የምሳ ሰዓት ተረኛ ስለነበርኩ አላገኙኝም። እነ ኮሎኔል መንግስቱ ጉዳዩን ሊያጣሩ በሄሊኮፍተር አዋሽ ሄዱ። ሲመለሱ እነ ንጉሴ ተለቀቁ። የሰራነው ስራ እውነት መሆኑ ስለታመነ ነው ይህ የሆነው። በተጻራሪው የቆመው አካል ግን በቢሮ ላይብረሪ ሰብስቦን ብዙ ፎክሮብን ነበር። ባንታሰርም ማስፈራሪያውና ማስጠንቀቆያው ደርሶናል።ይህንና ይህንን መሰል ብዙ ፈተና አይቻለሁ።›› ሲል የስራ ላይ ፈተናዎቹን በአጭሩ ነግሮናል፡፡

 

  የቀድሞ ጋዜጠኛ ላእከማሪያም ከሬዲዮ ኢትዮጵያ ሲለቅ  አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት ነበረ፡፡ ያን ሁኔታ ዛሬ መለስ ብሎ ሲያጫውተን

 

‹‹….ዜና ላነብ ስቱዲዮ ሆኜ ተዘጋጅ የሚለው ቀይ መብራት ከቴክኒሺያኑ ይደርሰኛል። በዚህ ጊዜ አንድ የዜና ክፍል ባልደረባዬ በታዘዘው መሰረት  ከዜና አገልግሎት በቴሌ ፕሪንተር የተላከ የተሞነጫጨረ ይሑፍ ይዞ ከመስታወቱ በኩል እንዳነብ አሳወቀኝ። እኔም በእጅ ምልክት እንደማላነብ ነገርኩት። ጊዜ የለኝማ። በተገቢው አሰራራችን የሚነበብ ዜና ለአንባቢው የሚሰጠው 30 ደቂቃ አስቀድሞ ነው። ለራሱ አንብቦ ወይም ተለማምዶ (Rehears) አድርጎ ስለ ዜናው ምንነት አውቆ በደንብ ተዘጋጅቶ ነው ዜናውን ለሚሊዮኖች ጆሮ የሚያደርሰው። ከቀናት በኋላም የሬዲዮ መምሪያ ሀላፊው ዘንድ ከፋለ ማሞ ቢሮ ተከስሼ ቀረብኩ። የፕሮዳክሽን ክፍል ሀላፊ ነው የከሰሰኝ። የሚኒስትሩ አማካሪ ደህኔ ረታና አለቃዬ ወይዘሮ ታቦቱም ነበሩ። ጉዳዩን አስረዳሁ። ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት ስርአት ጠብቄ እንደሰራሁ አመኑ።ከዚህ በፊት ምንም ጥፋት የለበትም፣ ታታሪ ሰራተኛ ነውብለው ነጻ አወጡኝ። ተጠንቅቄ እንድሰራም መክረውኝ ወደ ስራ ገባሁ።

 

እንዳላነብ የተሰጠኝ ዜና አንድ መግለጫ ነበር፡፡የደርግ መግለጫ ነው። አብዮታዊ እርምጃ ስለተወሰደባቸው ሰዎች የሚገለጽ ነው። እኔ ባላነበውም በቀዩ የዜና እወጃ ሰዓት ላይ ሌላ ጋዜጠኛ አንብቦታል። ግን ይህ ሁኔታ ኋላ ላይ ከፍተኛ ችግር አመጣብኝ፡፡ከአስራ አምስት ቀን በኋላ አገር ሰላም ነው ብዬ ለማዘጋጀው ፕሮግራም ሙቃዎችን ስመራርጥ ከደርግ ልዩ ምርመራ ክፍል ደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች መሳሪያቸውን አንግተው በሬንጅ ሮቨር መኪና ስቱዲዮ መጡ።

 

ፈልገንህ ነው የመጣነው፤ ለምርመራ ትፈለጋለህ!? ”

 

እናንተ እነማናችሁ?…” ጠየኩ። የመጡበትን ነግረውኝ ታዘው ስለሆነ በአስገዳጅነት እንደሚወስዱኝ ነገሩኝ።

 

አልወጣም!…” አልኩ። መጀመሪያ። ቴክኒሺያኑ ለመነኝ። ኋላ እነሱንም እንዳላስፈጅ ሰግቼ የሚመጣውን ለመቀበል ሄድኩ።

 

 

ከዚያ ደርግ ጽሕፈት ቤት ምርመራ ክፍል አንድ ገዳይ ሻለቃ ቢሮ አስገቡኝ። ሻለቃው በስድብ ተቀበለኝ።ለምን ትሰድበኛለህ ጥፋት ካለብኝ ንገረኝና ልወቀውአልኩት። ሁኔታው አናዶኛል። እየዛተ እየደነፋ ወደ ሌላ መርማሪ ሻለቃ ዘንድ ላከኝ። ሻለቃየፍየል ወጠጤሊያስብለኝ  ( ሊያስረሽነኝ ) የመደብ ጀርባዬን ሊያጠና በጥያቄ ያጣድፈኝ ጀመር። ርስት እንዳለኝ፣  የማን ቤተሰብ እንደሆንኩ። የፊውዳል ዘር እንዳለኝመየቀኝ። እንደሌለኝ መለስኩለት። ያኔ አባቴ ገነት ጦር ትምህርት ቤት አሰልጣኝ መሆኑን ሰነግረው ጥያቄውን አቆመ። ደጅ እንድቆይ አደረገኝ። ጾሜን ውዬ 11 ሰዓት ላይ ማዕከላዊ ተወሰድኩ። እዚያ በእኔ ጉዳይ ሲቪል ገዳዮችና ፖሊሶች መከራከር ጀመሩ። ለጥብስ ሊያቀርቡኝ ነው።

 

በዚያ ግቢ ውስጥ ሆኜ አንድ የማውቀው የሰፈሬ ልጅ ከግቢው ውጪ ከሩቅ ሲያልፍ አየኝና ሲፈራ ሲቸር ቀረብ አለ።  ምን ታደርጋለህ?” ሲልም ጠየቀኝ። ነገርኩት። ስልክ ቁጥርም ሰጠሁት። እየሮጠ ሄዶ የት እንዳለሁ ለቤተሰቦቼና ለቢሮ ባልደረቦቼ ነገረ። ስለእኔ መስረያ ቤቴ ተተራመሰ። እኔ አሰቃቂው እስር ውስጥ ገባሁ። ስገባም ጋዜጠኛ መሆኔ ስለተሰማ የደርግ ሰላይ መጣ ብለው ታሳሪዎቹ በጎሪጥ ያዩኝ ጀመር። የኢ.ኤል.ኤፍ፣ የበርበሬ አሻጥር ነጋዴዎች ይበዙበታል። ውሎ ሲያድር ንጹህ መሆኔን አምነው ወዳጅ አደረጉኝ። በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ 72 ሰዎች ነን የምንተኛው። አተኛኛችንምስክይባላል። (ግራና ቀኝ የሌላው ታሳሪ እግርና ጭንቅላት የተጠባበቀ ነው) ሙቀቱ አይጣል ነው። ጥበቱ መቀመጥም ሆነ መቆም አያስችልም። አብሮ እንደ መረብ መነሳት ነው። ስቃይ ነው። በዚያ ላይ ስጋቱ። ቅዠቱ። ወሰዱኝ፣ ገደሉኝ ነው።   ፀሎት ነው። ሌሊት የመኪና ድምጽ ሲሰማ መሳቀቅ ነው። ማን ይሆን የሚጠራው? ተረኛ የሚገደል ማን ይሆን? እያልን በፍርሃት መንቀጥቀጥ ነው። የፈለጉትን እየጠሩ ወስደው መግደል ነው የነሱ ስራ

 

         በዚህ ሁኔታ ጋሽ ላእከ  ምን  ያህል አመት ቆየ?

 

በዶክተር ንጉሴ ተፈራ አስተባባሪነት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረቦቼ ፈርመው አምስት ገጽ ደብዳቤ ለደርግ ጽህፈት ቤት በማቅረብ ተከራክረው አስፈቱኝ። ስፈታ በወቅቱ የደርግ ጸሐፊ በነበሩት ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ዘንድ ቀርቤይቅርታ ተደርጎልሃል ሁለተኛ እንዲህ አይነት ስህተት እንዳትፈጽምተብዬ ተግሳጽ ተሰጥቶኛል። መጀመሪያ ልቤ ንፁህ ስለሆነ የፈራሁት ነገር አልነበረም። መፈታቴ ሲነገረኝ ነው ምን አይነት አደገኛ ነገር ውስጥ እንደገባሁ የታወቀኝ። ተለቅቄ ስወጣ ክላሽንኮቩን ወጥሮ የያዘ አንድ ወጠምሻ ወታደር ነው ወደ መኪና አስገብቶ የሸኘኝ። ሁኔታውን ሳስታውስ  እንባዬ ዱብ ዱብ አለ። ይህ ሰው ግን መከረኝ።

 

አንተ ልጅ እንዳንተ ፀጉረ ልውጥ ሰው እዚህ ገብቶ የወጣ የለም። አታልቅስ ፈጣሪህን አመስግንአለኝ። እንባዬ ቀጥ አለ። በረታሁ። ዛሬ ሳስበው የሰፈሬ ልጅ የት እንዳለሁ ባይጠቁም አልቆልኝ ነበር። በዚያን ወቅት እዚያ እስርቤት ከነበርነው ሰዎች ውስጥ በህይወት የተረፈ አንድም አልነበረም።

 

 

 

መኪናው ቢሮ እንዳደረሰኝ ግቢው በእልልታ ቀለጠ። ምን ያህል ሰዉ የኔን ጉዳይ እንደሚከታተልና እንደሚወደኝ የተገነዘብኩበት አጋጣሚ ነው። እልልታውን ያቀለጡት በመስሪያቤቱ መሀይምነትን ለማጥፋት ከሙያ አጋሮቼ አበራ ለማ፣ ወንድሙ ነጋሽ እና ሌሎች ጋር ሆነን በፈቃዳችን የምሳ ሰዓታችንን ጭምር መስዋዕት እያደረግን ስናስተምራቸው የነበሩት ሰራተኞች ናቸው። መፈታቴ ደስታ ቢሰጠኝም ከዚያን ቀን ጀምሮ ከባልደረቦቼና ከምወዳቸው ሰራተኞች መለየቴ ሳያሳዝነኝ አልቀረም። ቢሮዬ እንደደረስኩ በእጄ ያሉትን የመስሪያቤቱ እቃዎች አስረክቤ ሁሉንም እየተሰናበትኩ ግቢውን ለቅቄ ወጣሁ። አልተመለስኩም። ምክንያቱም ጓድ ፍቅረስላሴ ከስራዬ መሰናበቴን አርድተውኝ ነበር። ይህ የሆነው ሚያዚያ ውስጥ 1969 . ነው።

 

     ከዚያስ ህይወት ወዴት አቀናች?

 

ሌላ መስሪያ ቤት መቀጠር አስቸጋሪ ነበር። ስለዚህ ጓደኞቼ ቤት ተቀምጬ አንዳንድ የትርጉም ስራዎችን እሰራ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ የአርሲ ገጠር ልማት ድርጅት የማስታወቂያና ትምህርት ክፍል ውስጥ ማስታወቂያ ወጣ፤ ተወዳደርኩ አለፍኩ፤ ተቀጠርኩ። ጥቂት እንደሰራሁ መታሰር መጣ፡፡ አብሮኝ የሚኖረው ጓደኛዬን አሰሩት። በቀጣይ እኔ እንደምታሰር ሲገባኝ አዲስ አበባ መጥቼ ጥቂት ተደብቄ ቆየሁ። ከዚያ በሚያውቁኝ ሀላፊ አማካኝነት  ከግብርና ሚኒስቴር ተጽፎልኝ ወደወላይታ እርሻ ልማት ድርጅት ተዛወርኩኝ። አንገቴን ደፍቼ የቀይ ሽብር ትርምሱ ዘመን አሳለፍኩ። ከዚያም ሐረር ቀጠና ግብርና ልማት በዚሁ ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆኜ መስራት ቀጠልኩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የግብርና ምርት መሳሪያዎች አቅራቢ ድርጅት ውስጥ በመስራት ላይ እያለሁ ኢህአዴግ ገባ።ወደ ቀደመ ሙያዬ የመመለስ እድል አገኘሁ። 

 

         ጋሽ ላእከ ከ1983 በኋላ

ያኔ የሚዲያ ስራ ትንሽ ለቀቅ የተደረገበት ነበር። ሩሕ መጽሔት ማስታወቂያ አወጣ ተወዳደርኩ አልፌ ተቀጠርኩ። በምክትል ዋና አዘጋጅ ደረጃ የዋና አዘጋጅነቱን ተግባር ሁሉ እየተወጣሁ እስኪዘጋ ቆየሁ።   በስራችን ሂደት ግን መንግስት የፕሬስ ተግባርን ጠበቅ ሲያደርግ በተለያዩ ጊዚያት ማእከላዊ ድረስ እየተጠራን እንጠየቅ ነበር። ነጻነት መጣ ስል መሳቀቅ ተከተለኝ። እየሰራን ዋና አዘጋጁ ሲሳይ ንጉሱ በሙያው ሰበብ ወደ ውጪ ይወጣል። ቦታውን ያዝ ስባል መዘዙን ስለማውቀው አልፈልግም አልኩ። በሱ ቦታም ከፋለ ማሞ ተተካ። ወከባው ሲበዛ አሳታሚዎቹ ፈሩና ዘጉት።

 

መጽሔቷ ተወዳጅ እንደነበረች አውቃለሁ፤ ዋውውው! በጣም አንባቢ ነበራት። ስርጭቷና ተፈላጊነቷ በጣም ከፍተኛ ነበረ። ብዙ ኮፒ ትሸጥ ነበር። የመጽሔቷ የመጀመሪያ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ ሲሞት ሙሉ ታሪኩን የሱን ነበር ያደረግነው፤ ያኔ አንባቢዋ በዛ። ከስር ከስር እያሳተምና 60 ኮፒ ደረሰች። ይህ የሆነው በሦስተኛ ዕትሟ ነበር። ከዚያ በኋላ ደረጃዋን እየጠበቅን የኮፒ መጠናን ሳናወርድ ቀጠልን። የማይነሳባት ጉዳይ የለም። ደረጃዋን ጠብቃ ማስታወቂያ እየተጨመረባት በአሜሪካን አገር ጭምር ትታተም ነበር።

 

            ወደ ..

 

የእንግሊዝኛው .. ሬዲዮ ተወዳድሬ በማለፌ ገባሁ።ለ4 ዓመታት ሰራሁ። ሁለት ደቂቃ ለማትፈጅ ዜና 50 ዶላር ይከፈለኝ ነበር። በእነዚህ አመታት አንዳንዴ ለፍራንስ ኢንተርናሽናል እሰራ ነበር። የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስዘግብ ደስተኛ ነበርኩ። በቀዳሚነት የሰራኋቸው ዜናዎችም ጥቂት አይደሉም።

 

 

          ጋሽ ላአከማሪያም የሰራቸው ዜናዎች

 

ጊዮን ሆቴል ላይ ደርሶ የነበረውን ፍንዳታ በተመለከተ በቀዳሚነት የዘገብኩት  እኔ ነኝ። ሂልተን ሆቴል .ኤን. ተወካይ ጋር ቁጭ ብዬ ፍንዳታው እንደተሰማ በቮልስዋገን መኪናዬ በርሬ ሄድኩ። ያየሁትን ዘገብኩ፤ ቀዳሚው የዓለም ዜና ሆነ። ነጮች ደግሞ እንዲህ አይነቱን ዜና ቀዳሚ ነው የሚያደረጉት። ሁከት፣ ብጥብጥና ጦርነት ይወዳሉ። 24 ሰዓት ሂደቱን  እየተከታተልኩ ዘግቢያለው። የያኔው አሊታሃድ የአሁኑ አልሻባብ ነው ይህንን ያደረገው። የትግራይ ሆቴል ላይ የደረሰው ፍንዳታንም ቀድሜ የዘገብኩት እኔ ነኝ። ወጣትነቱ ስለነበር መሯሯጥ ነው። በተመሳሳይ ብሉቶፕስ ላይ የደረሰው ጥቃትንም የዜና እፍታውን (Scoop)  የጨለፍኩት እኔ ነኝ። በዚህ ሁኔታ ቀጥዬ በመጨረሻ በራሴ ጊዜ ለቀኩ።

 

       የመልቀቁ ምክንያት

 

በስንት መከራ ያገኘሁትን ቀዳሚ ዜና አንድ ዘረኛሰዓቱ የዜና መቀበያ አይደለምበሚል ሰበብ ዜናዬን አልቀበልም በማለቱ ተናድጄ ነው። ዜናውን ግን በሌሎች ሚዲያዎች አስተላለፍኩት። ከዚያ ክስ መጣብኝ። አልሰራም አልኩ። በቃ። ጥቂት ቆይቶም ፈልገውኝ የምስራቅ አፍሪካ ዜና ወኪል ሆኜ እንድሰራ አድርገው ነበር፤ ሆኖም ስላልተመቸኝ ብዙም አልገፋሁበትም። ወደ ቢቢሲ ሬዲዮ ተሻገርኩ። በተጓዳኝም ለጥቂት ጊዜ ለኢንተር ፕሬስ ሰርቪስ (IPS) ኦን ላይን ሰርቻለሁ። በተለያየ አንግል እንደየፍላጎታቸው ነው እሰራ የነበረው።

ቢቢሲ ውስጥ የተሻለ ነገር አገኘሁ፡፡ በአንድ ዜና 61 ፓውንድ ነበር የሚከፈለኝ። ነጻነቱ፣ ሚዛናዊ ስራን ለመስራትም የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የኢትዮጵያ ተወካይ (correspondent) ሆንኩኝ። ለ8 ዓመት ሰራሁ። እንዳጋጣሚ እዛው ሆኜ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ተነሳ። የጦር ዜና ዘጋቢ ሆንኩ። እሌኒ መኩሪያ እና ሪቻርሊ የተባለ ፈረንጅም በወቅቱ እንደኔው የቢቢሲ ተቀጣሪ ነበሩ። በየራሳችን እንሰራለን። በተለያየ ጊዜ ባድመ እና ዛልአንበሳ የተካሄደው ጦርነትን የመዘገብ እድል አግኝቻለሁ። መቼም እድል አይባልም። ይቃይ መከራ ቢባል ይሻላል። ሁሉ አልፎ እርቅ ቢፈጠርም ያኔ በወንድማማች ህዝቦች መካከል ይህ መፈጠሩ ያሳዝናል። ዛሬ ዛሬ ብዙዎችን የሚያስቆጭ ሆኗል። የሰዉ እልቂት፣ መጨካከኑ፣ የወደቀ ሬሳ ማየቱይዘገንናል።

 

 

      ሌሎች ዘገባዎችስ?

 

በሀገራችን የተከሰተውን ማናቸውንም ነገሮች ስዘግብ ኖሬያለሁ። የሙያውን ስነ ምግባር ጠብቄ አገሬን እና ህዝቡን በማይጎዳ መልኩ እውነታውን ለመስራት ሞክሪያለሁ። የምርጫውን፣ የፖለቲካ ሂደቱን፣ ግጭቱን፣ ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሁነቱን፣ በአጠቃላይ ለውጪ ሚዲያ ፍጆታ የሚወለውን ሁሉ በአቅሜ ተግቼ ሰርቻለሁ ብዬ አምናለሁ። መጨረሻ ላይ እንዲሁ ያለመመቸት ሁኔታ ሲገጥመኝ ከቢቢሲም በራሴ ፈቃድ ለቅቂያለሁ። 2002 . መጨረሻ ማለት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጡረታዬን አስከብሬ ስለ ሙያው ማማከር እና ስልጠና መስጠት ላይ አትኩሪያለሁ።

 

     ጋዜጠኛና ደራሲ  ብርሀኑ ዘርይሁንና  ላእከማሪያም ደምሴ


ብርሃኑን የማውቀው ቀድሜ በስራዎቹ ነው። ኢትዮጵያ ሬዲዮ ስሰራ እሱ የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ ነበር። ወርቅ የሆነ ብዕር ነበረው። ርዕሰ አንቀፁን ተርጉሜ የማነብበት ፕሮግራም ነበረኝ። በደራሲነቱም፣ በጋዜጠኝነት ማህበር ውስጥም የነበረው ተሳትፎ ጥሩ ነበር። ለትውልድ የሚሻገር ስራ የሰራ ታላቅ  ሰው ነው። በአካል ተገናኝተን ጥሩ ወዳጅነት የመሰረትነው የማርክሳዊ ርዕዮት አዘጋጅ ሲያደርጉት በፈጠርነው የስራ ግንኙነት ነው። በወቅቱ ከኮሚኒስት አገራት የሚላከውን (International Marxist review) የተባለውን መጽሔት እየተረጎምኩ እንዲከፈለኝ ያደርግ ነበር። ከአዲሰ ዘመን ዋና አዘጋጅነት አስነስተው ነው እዚያ የከተቱት። እውነት እየተናገረ በሙያው ለመኖር የሚጥር እንጂ በፖለቲካዊ ጥቅም የማይገዛና የማያጎበድድ በመሆኑ ነው ዝቅ ያደሩት። በዚህም ይበሳጭ፣ ይጠጣ ነበር። እኔ ከጋዜጠኝነቱ ወጥቼ አዲስ አበባ የግብርና መሳሪያዎች አቅራቢ ድርጅት ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ስራ ላይ ተሰማርቼ በነበረ ጊዜ ነው ይህንን የምሰራለት። የቤት ኪራዬን የምሸፈነው በእርሱ ነው። በዚህ በዚህ ጥሩ ተግባብተናል።

 

 

ብርሀኑ ዘሪሁን የፊውዳል ቤተሰብ ነው። ግን ተራማጅ አስተሳሰብ ነበረው። ባለ ተሰጥኦ ነው። ብርሃኑ በጣም አድማጭ ነው። በራስ የመተማመን ብቃት አለው። ብዙ አይናገርም። ማንበብና መጻፍ ሱሱ ነው። ቤቱ ሰው አይጋብዝም እኔን ግን  ቤቱ እየጋበዘኝ ብዙ ቀናት ተዝናንተናል። ይወደኝ ነበር። መጠጥን ለስራ የተጠቀመበት ብቸኛ ሰው የማውቀው ብርሃኑን ነው። እኔ እስከማውቀው ቁጭ ብሎ በመጠጣት ጊዜውን አያባክንም። በቀን ውስጥ በተለያዩ ሰዓታት ደጋግሞ ጥቂት ጥቂት እየጠጣ የሚያነብ፣ የሚጽፍ  ሰው ነው። በሳል ጸሐፊ ነው። በስራውና በአገራዊ ሁኔታ ይበሳጭ ነበር።ጡረታዬን ቢፈቅዱልኝና ብጸፍ ይሻለኝ ነበርእያለ  ይነግረኝ ነበር። በዚህም ይበሳጭ ነበር። ግን የሀሳቡ አልሆነም። ያሳዝናል። ገና ብዙ ሊሰራ በሚችልበት ዕድሜው ነው ያጣነው። የሚያስቆጨን ባለ ዕውቀት ነው- ብርሃኑ። ሌሎችን እንደሱ እየበገኑ ያለፉ ምርጥ ጓደኞች ነበሩኝ፤ ምንያደርጋል

 

 

    ጋዜጠኝነት ያለ አስተማሪ

ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ በአማርኛ የተጻፈው የመጀመሪያ መጽሐፍ እሱ ነው። ልጽፈው የተነሳሳሁት አንድ ወቅት የግል ሚዲያዎች ነጻነት ተሰጥቷቸው ስለነበረ እንደልባቸው መጻፍ ጀመሩ። የጋዜጠኝነት ህግን  አይከተሉም። የሚዲያን ባህሪና ስነ ምግባር የጣሱ በርካታ ነገሩችን ስመለከት አንድ ማስተማሪያ ማዘጋጀት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። USID ፕሮፖዛል ጻፍኩኝ፤ እንደሚከፍሉኝና እንደሚያሳትሙልኝ ተፈቀዱልኝ። ጋዜጠኞችን ለመርዳት ፍላጎት ስለነበራቸው የተለያዩ መጽሐፍ እያቀረቡልኝ ማጥናት፣ ማንበብ፣ መተርጎም ጀመርኩ። በዚህ ሁኔታ 22 ወራት ጨረስኩት። ሲወጣ ጥሩ ተቀባይነት ነበረው። በርካታ ጀማሪ ጋዜጠኞች ተጠቅመውበታል። እንደማጣቀሻም እያገለገለ ይገኛል። ይህ ለእኔ ትልቅ የምለውና ሙያዬን በሚመለከት አስተዋጽኦ አደረኩበት የምልበት ሰራዬ ነው።

 

ሌሎች መጽሐፍትም አሉህ?

 

በመቀጠል የቀድሞ አለቃዬ ወይዘሮ ቷቦቱ Hand book of journalisom የሚለውን መጽሐፍ ወደ እንግሊዝኛ እንድተረጉም አድርጋኛለች። እንደገና busnes and economic reporting የሚል ሌላ መጽሐፍም ተርጉሜ ለንባብ አብቅቻለሁ። ሁሉም ጥቅም ሰጥተዋል ብዬ አምናለሁ።

 

የአገራችንን የጋዜጠኝነት አተገባበር

በጋዜጠኝነት መርህ ውስጥ ትክክለኝነት፣ ሚዛናዊነትና ግልጸኝነት Accuracy, balance and clarity ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። ይህ በእኛ አገር አይተገበርም። የመንግስም ለመንግስት ፕሮፓጋንዳነት፤ የግሉም ለሚወግነው ወገን በተጻራሪ ቆሞ መስራት ነው የተለመደው። ጋዜጠኝነት ግን እንደዚያ አይደለም። በመጽሐፎቼ ይህንን ግልጽ አድርጌ አስቀምጫለሁ። ይጠቅመኛል ያለ ከዚያ ይማራል። በተረፈ የዘመኑ ጋዜጠኞች በቴክኖሎጂ እገዛ መረጃን ቶሎ የማግኘት እድል አላቸው። በኛ ዘመን መረጃ ለማግኘት መከራ ነው። ኢንቴርኔት የለም። እንደዛሬው የተስፋፋ መረጃ ሰጪ ሚዲያ የለም። በዚያ ላይ ቅድመ ሳንሱሩም መከራችንን ያበላ ነበር። ጥቂት ሳት ያለው መታሰር፣ መባረር ከዚያም ባለፈ ሌላ እርምጃ ይወሰድበት ነበር። ይህ ፈተና በተለያየ መልኩ ዛሬም አለ። ግን ከእኛ ዘመን ይሸሳላል።  ሙያው በራሱ ፈተና ነው።

 ቤተሰባዊ ሕይወትስ?

 

አግብቼ ነበር አጋጣሚ ሆኖ አብረን መኖር አልቻልንም። ቀረ። ሌላ የውጪ ዜጋም አግብቼ ነበር፤ ወደ አገሯ እንሂድ ስትለኝ ስላልተስማማን እሷም ቀረች። አሁን ብቻዬን ነኝ። ልጅ፣ ሚስት፣ ድስት የሚሉት ጠጣ የለብኝም። ባይሆን ጥሩ ነበር። በነጻነት እኖራለሁ።

 

ለኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች  የሚላቸው ትንሽ ቃል

የጋዜጠኝነትን ሀሁ መተርጎም፣ አንባቢ መሆን፣ ጥሩ አዳማጭ መሆን። አንድን አካል ለመጥቀም ብሎ ሌላውን ለመጉዳት ከማሰብ መቆጠብ ያስፈልጋል። ሌላው ሌላው በሂደት የሚመጣ ነው።

የቀድሞ ጋዜጠኛ ላእከማሪያም ደምሴ በተወለደ በ69 አመቱ ሮብ ጥር 25 2014 ህይወቱ ልታልፍ ችላለች፡፡

 

Guenet Ayele Gruenberg ገነት አየለ የጋዜጠኛ ላዕከማሪያም ደምሴን https://www.facebook.com/laekemariam.demessie? ሞት አስመልክታ የሚከተለውን

አጋርታናለች

  ላዕከ ማርያም ደምሴ

ሳልሰናበትህ ዕረፍትህን ሰምቼ መቀበል አቃተኝ:: የረጅም ጊዜ ጓደኛዬ: የሙያ አጋሬ ላዕከዬ በንባብ የዳበረ ዕውቀትህ በልምድ የደረጀ አስተያየትህ ከእንግዲህ ዳግም ላላገኘው ሊቀር ነው? የኢትዮጵያ ሬዲዮው ትዝታህን በየክፍለ ሃገሩ ስትሄድ ያጋጠመህን የጋዜጠኝነት ልምድህን የምታጫውተኝ ከእንግዲህ ትዝታ ብቻ ሊሆን ነው? የረዢም ሰዓት ክርክራችን አንዳንዴም የግድ የኔን ሃሳብ ካልተቀበልክ ብዬ ድርቅ ስልብህ ስቀህ የምታሳልፈውና በትዕግሥት የምታስረዳኝ አይረሳኝም:: የቢቢሲው የቪኦኤው የፈረንሳይ ሬዲዮው ወኪል ላዕከ ማርያም ደምሴ ነፍስህ በሠላም ትረፍ:: መላው ቤተሰቤ ደህና ሁን ይልሃል ላዕከዬ::

ላዕከን በተደጋጋሚ አገኘው ነበር ፒያሳ መውጫው ላይ ከድሮው አፋር ኬክ ቤት ህንጻ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ስር ከሚገኘው ሬስቶራንት ነበር መገናኛችን ። ኮሮና መጣና በስልክ ብቻ ሆነ ሰላምታችን። ከ 2 አመት በፊትም ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የኢትዮጵያ መጻኢ ሁኔታ ውይይት ላይ ኩሪፍቱ ለ 5 ቀናት ላዕከን ጨምሮ አንጋፋ ጋዜተኖች በተገኙበት ኣኔም ታድሜ ነበር ። እንዳለመታደል ሆነና በዚያን ጊዜ ከነበሩት አንጋፋ የጋዜተኝነት አባቶች 3 ተከታትለው አረፉ ። ጋሽ መሀመድ እድሪስ ፣ ጋሽ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ፣ ዛሬ ደግሞ ጋሽ ላዕከ ማሪያም ደምሴ። ሶስቱም ለጋዜጠኝነት የተሰጡ በእድሜያቸውም ብዙ ነገሮችን ያበረከቱ መጻህፍትን የጻፉ ፣ ህይወታቸውንም ለሙያቸው የለገሱ ናቸው ። የኩሪፍቱ ስልጠና ላይ ያነሳሁትን ፎቶ ግራፍ አንጋፋዎቹን በጋራ ፎቶግራፍ ለማንሳት እድል ነበረኝ ። ከግራ ወደ ቀኝ ጋሽ መሀመድ እድሪስ ፣ ላዕከ ማሪያም እና ጋሽ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ናቸው ። ሚሊዮን ተረፈ እና ዶክተር ንጉሴ ተፈራ ይቀጥላሉ ። ጋሽ ማዕረጉ በዛብህ ከኋላ ናቸው ። ቀሪዎቹን እድሜ ይስጥልኝ። ያረፉትንም መንግስተ ሰማያት ያውርስልኝ።









 

መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ ሀሳብ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሀሳብን የሚያንጸባርቅ ነው

ጋሽ ላእከማሪያም በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ ውስጥ የራሱን ደማቅ አሻራ ያኖረ ታላቅ ባለሙያ ነው፡፡ በሙያው ባሳለፋቸው 44 አመታት ፕሮፌሽናሊዝምን የተከተለ ጠንካራ የሙያ ስራ እንዲሰራ ፈር ቀዷል፡፡  ጋሽ ላእከ በእንግዚኛ የዳበረ እውቀት ያለው በመሆኑ በሳል የብእር ሰውነቱን ለማሳየት የቻለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ የግለ-ታሪክ ጽሁፉ ላይ እንዳየነው በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ የሙያው አባት ነው፡፡ የዚህ ግለ-ታሪክ ጽሁፍ አዘጋጆች ጋሽ ላእከን ለማነጋገር ፒያሳ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ባቀናንበት ጊዜ ወርቃማውን የጋዜጠኝነት ዘመን ተርኮልናል፡፡ ከብዙ አንጋፋዎች ጋር እንደመስራቱ ወግ የያዘ የጋዜጠኝነት የአሰራርን ደንብን መከተል የቻለ  ነበር፡፡ ለአለም አቀፍ ሚድያ እንደመስራቱም የሙያውን ከፍታ አስጠብቆ ለማቆየት የጣረ ሰው ነበር፡፡ ጋሽ  ላአከማሪያም ህይወቱ ከማለፉ አስቀድሞ ህዳር 2014 ከዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ጋር ተወያይቶ ነበር፡፡ ብዙ ጉዳዮች አንስተዋል፡፡ ጋሽ ላእከማሪያም ብዙ ያነበበ ብዙ የሰራ በብዙ መንገዶች ያለፈ የበሰለ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ጋሽ ላእከማሪያም ያወቀውን ለማሳወቅ ወደ ኋላ የማይል ብርቱ ሰው ነበር፡፡ 22 ወራት የፈጀበትን ጋዜጠኝነት ያለ አስተማሪ የተሰኘውን መጽሀፍ ለሙያው ሰዎች እንደ አንድ ትልቅ ስጦታ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ጋዜጠኛ ላእከማሪያም ለኢትዮጵያጋዜጠኛ ትልቅ አሻራ ያኖረ ታሪክ ፍጹም ሊዘነጋው የማይገባ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ታላቅ ሰው በአጭሩ ታሪኩን ሰንደን አስቀምጠናል፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን  ደረጀ ትእዛዙ ታዛ መጽሄት ላይ ከጻፈው ጽሁፍ ሀሳቦች ተወስደዋል፡፡ለዚህም ደረጀ ትእዛዙን ማመስገን እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም ራሱ ጋሽ ላእከማሪያም የሰጠን ብዙ ሰው ያልተመለከታቸው ምስሎች በዚህ ግለ-ታሪክ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ጥር 26 2014 ከቀኑ 7ሰአት ከ24 በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና በተወዳጅ የግለ-ታሪክ ድረ-ገጽ ላይ የተጫነ ነው፡፡ በየጊዜው አስፈላጊው  ማሻሻያ እየተደረገ ተስተካክሎ እንዲሰነድና እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡/ ›

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች