143.ቸርነት ሁንዴሳ ሚደቅሳ የበሪሳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ጋዜጠኛ ቸርነት ሁንዴሳ ይጠቀሳል፡፡  ቸርነት በአፋን ኦሮሞ በሚታተመው በሪሳ ጋዜጣ ላይ ከ1988አ.ም ላለፉት 26 አመታት እያገለገለ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት ደግሞ የበሪሳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሙያዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ያለ ባለሙያ ነው፡፡  በጠንካራ ችሎታው የተመሰከረለት ቸርነት በ1990ዎቹ በአፋን ኦሮሞ የህትመት ጋዜጠኝነት የላቀ አሻራ ካኖሩት አንዱ ነው፡፡ ከጋዜጠኛ ቸርነት የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ እዝራ እጅጉ ግለ-ታሪኩን  እንደሚከተለው አጠናክሮታል፡፡


ቸርነት ሁንዴሳ ከ1988 ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር በየሳምንቱ በአፋን ኦሮሞ ቅዳሜ በሚታተመው በሪሳ ጋዜጣ በአራሚነት ተቀጥሮ በዚሁ የስራ መደብ ለስድስት ዓመታት ካገለገለ በኃላ ከጀማሪ ሪፖርተርነት በሪፖርተርነት በከፍተኛ ሪፖርተርነት በአዘጋጅነትና በከፍተኛ አዘጋጅነት በላይብረሪና ዶክመንቴሽን ተጠባባቂ ኃላፊነት  የስራ መደቦች እንደዚሁም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ሆኖ በከፍተኛ ትጋትና ታታሪነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በቅንነትና በታማኝነት ሙሉ ጊዜውን በመስጠት ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡


1.             የልጅነት ሕይወት

 በ1968 ነሀሴ 21 ተወለደ፡፡ከአባቱ ከአቶ ሁንዴሳ ሚደቅሳ ዳባ እና ከእናቱ ከወይዘሮ አፀደ ኃይሌ ልኪ በኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ወንጪ ወረዳ ፊቴ ዋቶ ቀበሌ የተወለደው ቸርነት፡ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ያለውን ትምህርቱን እዚያው በሚገኘው ጨቦ ወንጪ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተማ ማለትም ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በሽመልስ ሀብቴ አጠቃላይ (9ኛና 10ኛ) እና በነፋስ ስልክ አጠቃላይ (11ኛና 12ኛ) ትምህርት ቤቶች ነው የተማረው፡፡

እናትና አባቱ እዚያው ወንጪ ወረዳ ፊቴ ዋቶና ዋራቡ ማሲ በሚባሉ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ የተወለዱ ሲሆን አባቱ በተሰማሩበት የልብስ ስፌት ሙያ ነበር ያፈሩአቸውን 12 ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩ የነበረው፡፡ ቸርነት ከእነዚህ የቤተሰብ አባላት ሁለት ሴቶችን ሁለት ወንዶችን አስከትሎ 5ኛ ልጅ ነው፡፡



      የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ሁኔታ

በማህበራዊ የትምህርት ዘርፍ በንግድ ስራ የትምህርት ወይም በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ በ1985 ዓ.ም ከነፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  በሰርተፊኬት የተመረቀው ቸርነት፡ በዚሁ በተጠቀሰው ዓ.ም እና ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ወስዶአል፡፡

ከዚሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሂደት ጋር በተያያዘ ቸርነት ሳይጠቅስ የማያልፈው 1983 የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ወቅቱ በደርግና በተለያዩ ቡድኖች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ ሲካሄድ የነበርና በዚህም ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የተቆጣጠረበት ቀውጢ ወቅት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት ትምህርት እንደምንም ተጠናቅቆ ሁለተኛውን መማርም ሆነ ፈተናን መውሰድ ስላልተቻለ የመጀመሪው መንፈቀ ዓመት ውጤት ተይዞ ወደ ቀጣዩ ክፍል ዝውውር እንደተደረገ ቸርነት ማስታወስ ይወዳል፡፡


የአፋን ኦሮሞ (ቁቤ) ትምህርት

በወቅቱ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የቁቤ ወይም የአፋን ኦሮሞ አጻጻፍ እና ሰዋሰው ትምህርት በመሰረታዊነት ይሰጥ ነበር፡፡ ቸርነትም መደበኛ ትምህርቱን ሲከታተልበት በነበረው ነፋስ ስልክ አጠቃላይ ትምህርት ቤት ከማስታወቂያ ሰሌዳ አንብቦ በመመዝገብ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠብቅ የነበረውን ትምህርት በማታው ክፍለ -ጊዜ ተምሮ በማስተማር እየሰራበት ይገኛል፡፡

በታችኛው የትምህርት እርከኖች ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ስሙ ሲጠራና ሲሸለም የነበረው ቸርነት ሁንዴሳ እርሱ ሁለተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት አገሪቱ ውስጥ በነበረው ጦርነትና ግርግር ምክንያት ከታች የነበረውን ደረጃ ይዞ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ በዚህም በወቅቱ የነበረው ትውልድ በብዙ መልኩ የተጎዳ ነው ብሎ ያምናል፡፡

በዚሁ በተጠቀሰዉ ምክንያት በ1985 በተሰጠው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ያመጣው ውጤት ከፍተኛ ትምህርት ተም የሚያስገባው ስላልነበረ በወቅቱ በየዓመቱ ሲሰጥ የነበረውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለተከታታይ ዓመታት በመውሰድ ውጤቱን አሻሽሎኣል፡፡









          በጎ አድራጎት

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጉጉት ሲጠብቀው የነበረውና ተምሮም በደንብ የገባውን የአፋን ኦሮሞ ሰዋሰው ትምህርትን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ተመረቀ፡፡ የተማረውን የአፋን ኦሮሞ ትምህርትን ለሌሎች ለማካፈል ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ፡ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፡ በወቅቱ አፋን ኦሮሞንና የኦሮሞ ህዝብ ባህልን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከነበረው ከሜጫና ቱለማ ማህበር እንዲሁም አፋን ኦሮሞንና የኦሮሞ ባህልን ለማሳደግ ቋቁመው  ከነበሩ ከተለያዩ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን በወቅቱ እንደአሁኑ ቋንቋውን በስፋት የሚጠቀሙ ሰዎች በሌሉበት በአዲስ አበባ ከተማ የተማረውን ወደ ማስተማር ገባ፡፡

ቸርነት በተለይም ቄራ አከባቢ በሚገኙት አፄ ዘርዓ ያዕቆብና አብዮት ቅርስ በሚባሉት ትምህርት ቤቶች ከ1985 ዓ.ም ክረምት ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ቋንቋውን አስተምሯል፡፡ በዚህም ብዙዎች አፋን ኦሮሞን ተምረው ባህላቸውን አውቀውበታል፣ የስራ ዕድል አግኝተውበታል፣ ተጨማሪ ቋንቋንም ለመቻል በቅተዋል፡፡

        ለዛሬው ጋዜጠኝት መሰረት የሆነው የስነ ጽሁፍ ስልጠና

ይህ አፋን ኦሮሞን የማስተማሩ ሂደት እየተከናወነ እያለ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከ1987 ጀምሮ ሲሰጥ በነበረው የአፋን ኦሮሞ ስነጽሁፍና ላይብረሪ ሳይንስ ስልጠናዎችን በመከታተል የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል፡፡ በእነዚህ ስልጠናዎችም አሁን ያለበትን ተም አገልግሏል፤ እያገለገለም ነው፡፡

     በፕሬስ ድርጅት የመቀጠር ሂደት

ቸርነት ከላይ በተጠቀሰው ቢሮ በኩል የሚሰጠውን የስነ ጽሁፍ ስልጠና እየወሰደ እያለ በሪሳ ጋዜጣ በ1987 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ በእርምት (ፕሩፍ ሪደር) የስራ መደብ ላይ ሁለት ሙያቶኞችን በፍሪላንሰርነት ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ ላይ አብረውት አፋን ኦሮሞን ሲያስተምሩና የስነጽሁፍ ስልጠና ሲወስዱ ከነበሩ በርካታ ሰዎች ጋር በመወዳደር በጽሁፍም ሆነ በቃል ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ከመስከረም 2 ቀን 1988 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሀምሌ 17 ቀን 1994 ዓ.ም በፍሪላንስ ቅጥር፣ ከሀምሌ 18 ቀን 1988 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ደግሞ ሚነት የተቀጠረበትን መስሪያ ቤት እና ህዝብን ብሎም አገርን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

       የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታ

ቸርነት በነፋስ ስልክ አጠቃላይ ትምህርት ቤት በሰርፍኬት የጀመረውን የአካውንቲንግ ትምህርት ለመቀጠል 1990 ዓ.ም ወደ ጄኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ተዋም በማምራት በተጠቀሰው የትምህርት ዘርፍ በ1992 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡

በ1997 ዓ.ም በወቅቱ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብቶ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በ2000 ዓ.ም በዲፕሎማ ሲመረቅ፤ በ2004 ዓ.ም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ድግሪውን ወስዶኣል፡፡ እንዲሁም በ2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፋን ኦሮሞ ሁለተኛ (ማስተርስ) ድግሪ ተመርቆኣል፡፡

ሙያ ነክ ስልጠናዎች

ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በመሰረታዊ የጋዜጠኝነት ሙያ፤ በችሎት አዘጋገብና በሌሎች በርካታ የሙያ ዘርፎች ስልጠናዎችን በመከታተል የምስክር ወረቀት ተቀብሎበታል፡፡

ሽልማቶችና የምስጋና ወረቀቶች (ደብዳቤዎች)

ቸርነት አፋን ኦሮሞን በበጎ ፈቃደኝነት ስያስተምር በነበረት ወቅት አስከ ወርቅ የደረሱ ሽልማቶችንና ሌሎች ማበረታቻዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት በታታሪ ሰራተኝነት የገንዘብ ሽልማትና የምስክር ወረቀቶችን ተቀብሎኣል፡፡

 የቤተሰብ ሁኔታ

በ2010 ዓ.ም ከውድ ባለቤቱ ከፓስተር አበበች በንቲ ጋር ትዳር መስርቶ ሕይወቱን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡









         ተማሪ ሀላፊነት

ከበሪሳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት በተጨማሪ የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበርን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እየመራ ይገኛል፡፡

              የሙያ ሕይወቱ

ቸርነት በሙያ ሕይወቱ ከፍተኛ የአገራችንን መሪዎች ማለትም የቀድሞዎቹን የኢትዮጵያ ርዕሳነ ብሄሮች፤ አምባሳደሮችና ሚኒስትሮችን ጭምር ቃለ-መጠይቅ በማድረግ የሕይወት ተሞክሮአቸውንና የስራ ልምዳቸውን ለአንባቢ አቅርቧል፤ እያቀረበም ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የዶክተር ሙላቱ ተሾመን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመጣጥፍ ረገድም  በተለይም ለአፋን ኦሮሞ ዕድገት የሚበጁ ስራዎችን ምሁራን በመጠየቅ እንዲሁም የመመረቂያ ጽሁፉን ዕድገት ከሙያና ከአፋን ኦሮሞ ጋር አያይዞ ስለሰራ ሙያው የፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀም በኦን ላይን ሚድያና በበሪሳ ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ እንደ አንጋፋነቱም ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የሚቀላቀሉ አዳዲስ ሙያተኞችን  በማሰልጠን እና በማብቃትም የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

          የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ

ለቸርነት ከሁሉም በላይ የእረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ የሚወደው ከቤተሰቡ ጋር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ሚዲያዎችን በመከታተል በተለይም ሬዲዮን ከስራ ወደ ቤት ከቤት ወደ ስራ ቦታ ሲሄድ ጭምር በመከታተል ትርፍ ጊዜውን ማሳለፍ ይወዳል፡፡ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ማዳመጥም ሌላኛው ጊዜ ማሳለፊያው ነው፡፡

በዚህ ወቅት በተለይ 128 ሺህ ለሚጠጉ የበሪሳ ወዳጆች፤ ከ600 ሺህ ለሚበልጡ ተከታዮች የሚሆኑ መረጃዎችን በማንኛውም ጊዜ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት እያደነ (ሞኒተር እያደረገ) ማቅረብን እንደዋነኛ የጊዜ ማሳለፊያ አድርጎ ይወስዳል፡፡

በዚህም በአፋን ኦሮሞ ምሉዕ፤ ተዓማኒ፤ ሚዛናዊና ትኩስ መረጃዎችን ሳይቀደም በመቅደም ለውድ አንባቢዎቹ ማቅረብ ለእርሱ ትልቁ የጊዜ ማሰለፊያው ነው፡፡ ረጅም ጊዜውን መረጃን በማፈላለግ በመወጠሩ ምክንያት አልፎ አልፎም ቢሆን ከቤተሰቡ በተለይም ከባለቤቱ “የበልኩ ይሁን” ምክር ይለገሰዋል፡፡ እናም ቸርነት በማንኛውም ጊዜ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መረጃን አፈላልጎ ቶሎ ለአንባቢው ማድረስን እንደዋና የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ይወስዳል፡፡

ቸርነት የበሪሳ ቤተሰብን ገና በወጣትነቱ የቀላቀለ በመሆኑ እና ለረጅም ጊዜም በጋዜጠኝነት ሙያ እያሳለፈ ስለሆነ ለስራው ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ መካከለኛ አስተሳሰብ ያለው፣ በህዝቦች እኩልነት የሚያምን፣ ሰውን በሰብአዊነቱ የሚቀበል ስለሆነ በተለይ አገራችን በአሁኑ ወቅት ከተጋረጡባት ችግሮች እንድትላቀቅ የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር በተለይም ወጣቱ ትውልድ የሰከነ ስብዕና እንዲኖረው ሙያው ባጎናጸፈው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሀይማኖት አባቶችን፣ አባ ገዳዎችን፣ ምሁራንን ወዘተ ራሱ ቃለ መጠይቅ በማድረግና ቃለ መጠይቅ እንዲደረግላቸው ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰርቷል፡፡

መጋቢ አእምሮ የሚባል ገጽ በመክፈትም በመስኩ የካበተ ልምድና የትምህርት ዝግጅት (ዶክትሬት ዲግሪ) ባላቸው ምሁር ትውልድን የሚቀርጹ ጽሁፎች እንዲቀርቡበት ሀሳብ በማቅረብ ጭምር ለሀገሩ አንዳች ትልቅ አሻራ ለማኖር ችሏል፡፡

 

የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

ቸርነት በአፋን ኦሮሞ የጋዜጠኝነት ስራ ውስጥ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ መቻሉ ትውልድን የሚጠቅም ነገር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በበሪሳ ጋዜጣ ላይ በልዩ ልዩ ስራ መደቦች በማገልገል የሚጠበቅበት ማከናወን ችሏል፡፡ ቸርነት ቁቤን መማር ብቻ ሳይሆን በማስተማርም የኦሮም ባህልና እሴት እንዲታወቅ አድርጓል፡፡ በተለይ ደግሞ በሪሳ ጋዜጣ ላይ ከመጣ በኋላ ብዙ መጣጥፎችን በማቅረብ የጋዜጠኝነት ስራውን በሚገባ ማከናወን ችሏል፡፡ ቸርነት ባለፉት 26 አመታት በበሪሳ ጋዜጣ ላይ ከአራሚነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ባለፋቸው መንገዶች ብዙ  እውቀት ቀስሟል፡፡ ወደፊትም ይቀስማል፡፡ የቸርነት ልዩ መለያው ወይም ብዙዎች አድናቆታቸውን የሚቸሩት መረጃ እና እውቀትን ለማካፈል ያለውን ትጋት እና ተነሳሽነት ነው፡፡ ቸርነት ከቴክኖሎጂ ጋር ቅርብ ስለሆነም እርሱ ያወቀውን ለማሳወቅ የተቻለውን ይጥራል፡፡ በተወዳጅ ሚድያ የሚዘጋጀው የሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ ላይም አንጋፋ  የአፋን ኦሮሞ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችን መገኛ እና መረጃ ያቀበለን ቸርነት ነው፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ ራሱ ቸርነት በሙያው ያደረገው አስተዋጽኦ ትልቅ ሆኖ ሳለ ሌሎች ታሪካቸው እንዲሰነድ ያደረገው ጥረት በእኛ በኩል አድናቆት የሚያስቸረው ነው:: ቸርነት ይሏል እንዲህ ነው፡፡ ስምን መላአክ ያወጣዋል እንዲል ብሂሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደቸርነት አይነት ሰዎች  አሏት፡፡ ግን አስተዋጽኦዋቸው ሲነገር አይታይም፡፡ ኢትዮጵያ ልታይ ልታወቅ የማይሉ ሰው ደብቋቸውና ራሳቸውን ደብቀው የሚሰሩ ትጉሀን ሞልተዋታል፡፡ ግን ግለ-ታሪካቸው እና የስኬት ሚስጢራቸው ይፋ ሲሆን አያጋጥመንም፡፡ ቸርነት በዚህ ጥረቱ እንዲቀጥል፤ እንዲሁም የበለጠ ለሀገሩ እንዲሰራ መልካም ምኞታችንን እየገለጸን ታሪኩን ትውልድ አንብቦ አንዳች ትምህርት እንዲቀስምበት እነሆ አቅርበነዋል፡፡ / ይህ ግለ-ታሪክ ከባለታሪኩ የተወሰዱ መረጃዎችን ፤ ምስሎችን መሰረት በማድረግ ተጠናክሮ የቀረበ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰናዳ ሲሆን በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና በተወዳጅ የግለ-ታሪክ  ብሎግ ላይ ዛሬ አርብ የካቲት 18 2014 ወጣ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው ተስተካክሎ ይቀርባል፡፡   

 

 

አስተያየቶች

  1. ቸርነት ከተገለጸውም በላይ ሙሉ ሰው ነው። ጸባዩ ልዩ፤ በስራው ተጠቃሽም ተወዳሽም የሆነ፤ ከተሰጠውም በላይ ሌሎች ሥራዎችን በኃላፊነት ወስዶ የሚሠራ፤ እንኩ እንጂ አምጡ የማያውቅ፤ እንሥራ እንጂ ሥሩ የማይል፤ በሳል እና አስተዋይ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጠኛ ከተባለ ከቸርነት ውጭ መጥቀስ ይከብዳል።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች