148.
ኡመር አሊ ከይሪ -የአፋርኛ ጋዜጠኛ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ
የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው
አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ኡመር አሊ ከይሪ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው በተለይ በአፋርኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ካኖሩት ውስጥ ናቸው፡፡
ግለ-ታሪካቸው እንደሚከተለው ተጠናክሯል፡፡
የሚድያ ሰው
ኡመር አሊ ከይሪ 1942 ዓ.ም በቀድሞ አዳልና ኢሳ አውራጃ ከድሬዳዋ 30 ኪ.ሜ ትር ርቀት ላይ በምትገኝ ኤሬር በምትባል ቦታ ተወለዱ፡፡ ኡመር እንደማንኛውም የአፋር አርብቶ አደር ልጆች ፍየል፣ ከብትና ግመል በመጠበቅ ነው ያደጉት፡፡ በዚህ ጊዜ አዲስ አበባ በሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት የመማር እድል አግኝተው በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርታቸው ተከታትለዋል፡፡
12ኛ ክፍል እንደጨረሱ ተንዳሆ፣መልከወረር እርሻ ምርምር ተቀጥረው ለ2 አመታት ሰርተዋል፡፡ እዚህ እየሰሩ ባለቡት ጊዜ ነበር የኢትዮጵያ ሬድዮን ማስታወቂያ ከጋዜጣ አንብበው፣ ከልጅነታቸው ጀምረው የህዝብ ጉዳይ በጋዜጠኝነት ሙያ ህዝቤን የማገልገል ፍላጎት ስለነበራቸው ሳይውሉ ሳያድሩ በፍጥነት አመልክተው የፈተናውን ቀን መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ከጣቢያው ለፈተና ተጠርተው ብቸኛ ተወዳዳሪ ስለነበሩ አስፈላጊው ጥያቄና መስፈርቱን ካዩ በኋላ ነበር በ1967 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሬድዮ ላይ በጋዜጠኝነት ሞያ ስራ ሀ ብለው ጀመሩ፡፡ በነገራችን ላይ ኡመር ኢትዮጵያ ሬድዮ ሲቀጠሩ ደሞዛቸውን በግማሽ ቀንሰው ነበር የገቡት፡፡ በኋላም ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
በጊዜው ከአማርኛ ተተርጉሞ ነበር ዜናው ሲቀርብ የነበረው፡፡ ይህ ጉዳይ ለአፋር ህዝብ አይጠቅምም፡፡ ወደታች ተወርዶ መሰራት አለበት በማለት ወደ አፋር በመሄድ የህብረተሰቡ ድምፅና የመንግስት አካላትን ምላሽ በማካተት መስራት ጀመረ፡፡
በአንድ ወቅት ተመልክቶት በመጣው ጉዳይ በአፋርኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቋንቋዎች መሰራት አለባቸው በማለት እቅድ ይዘው ከያኔው ጋዜጠኞች ንጉሴ ተፈራ (ዶር) እና ከእንግሊዝኛ ክፍል ባልደረባ ጋር በመሆን ወደ አሚባራ ተጉዘው በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለው ኡመር አሊ ከይሪ የህዝብ ጉዳይ ላይ በጣም ያንገበግባቸው ስለነበር የህዝብ ቅሬታ “ከምናዬውና ከምንሰማው” የሚል ፕሮግራም ስለ ነበረ ይህንኑ ጉዳይ በአካል ሕዝቡ ድረስ በመውረድ ቀርፀው ይመጣሉ፡፡ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስተር ተጠሪ የነበሩት ሰው ፕሮግራሙ ጥሩ ነው ነገር ግን አየር ላይ ከዋለ ትታሰራላችሁ፡፡ ኃላፊነት ከወሰዳችሁ ማስተላለፍ ትችላላችሁ አለን፡፡ እኛም ጉዳዩ ላይ ተወያይተን ከታሰርን እንታሰር እንጂ አየር ላይ መዋል አለበት በማለት ያዘጋጁት ዝግጅት በአፋርና በአማርኛ አየር ላይ ዋለ፡፡ ነገር ግን እንግሊዝኛው እንዳይውል ተደረገ፡፡ መረጃው መንግስት ሹማምንት ጆሮ ደርሶ ስለነበር በወታደር ከየቤታችን ተይዘን ተወሰድን፡፡ ሁላችንም በተለያየ ቦታ ነበር የታሰርነው ይላሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ጠቁመህ እየመራህ የወሰድካቸው አንተነህ በማለት እኔን ማስፈራራት ጀመሩ፡፡ እውነት ይዘው ስለነበር ምንም አልመሰላቸውም፡፡ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ በማለት ያለው ነገር ማስረዳት ጀመሩ፡፡ ጉዳዩ ትክክል መሆኑን ሲያዩ የሰራችሁት ጉዳይ ትክክል ቢሆንም አሁን ግን ወቅቱ አይደለም በማለት ከእስር ለቀቁን ይላሉ፡፡
የዛኔ ወጣቱ ጋዜጠኛ ኡመር አሊ ከይሪ በዚህ ብቻ አላቆመም፡፡ የህዝብ ጉዳዮችን አየር ላይ እንዲበቃ ከቅርብ ቦታዎች ራቅ በማለት ከአብአላ እስከ ዳሎል ድረስ በመሄድ ህዝቡን ቃለ- መጠይቅ በማድረግ አየር ላይ እንዲውል ያደርግ ነበር፡፡ በእግረ መንገዱም ህዝቡ ሬድዮ እንዲያዳምጥ ይነግራቸው ነበር፡፡
ከቅሬታ ዜና በተጨማሪም ትምህርታዊ የሆኑ ዝግጅቶች እያዘጋጀ፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ መለወጥ የሚችሉ ዝግጅቶች አየር ላይ አውሏል፡፡
ኡመር፣ ለስራ ስምሪት በሄደበት ወቅት በመንገድ ላይ ድንገት በተከፈተባቸው ጥቃት ምክንያት እጁ በጥይት ተመትቶ የመጀመርያ ህክምና ተደርጎለት ያመጣሁት ግብአት አለ ህዝቡ ይጠብቀኛል ብሎ ከእነህመሙ ወደ መስሪያ
ቤት
በመሄድ አቀነባብሮ ለአየር አብቅቷል፡፡
ኡመር፣ በአንድ ቀን በወቅቱ የጅቡቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ለስራ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ አፈላልጎ ኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ያላቸው ጠቀሜታ የተመለከተ ዝግጅት ተዘጋጅቶ አየር ላይ ከዋለ በኋላ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለሬድዮ ጣቢያ በመደወል የቀረበው ዝግጅት በጅቡቲ ብዙም ተደማጭነት ስላላገኘ ተደጋግሞ አየር ላይ እንዲውል፤ በተጨማሪም በሶማሊኛ ቋንቋ ተተርጉሞ አየር ላይ እንዲውል በማለት ተናግረዋል፡፡ መረጃው ያልነበረው ኡመር አሊ ከይሪ አለቃቸው አቶ በአሉ ግርማ ኡመር ና ብልው ግንባሩን ሳም አድርገው የምታድግ ወጣት ነህ በርታ ብሎ አመስግኖታል፡፡ በኢትዮ- ጁቡቲ ጉዳይ ላይ የሰራኸው ዝግጅት በጣም ተወዶልሃል….. እንኳን ደስ አለህ ብለው በቀጣይ ማበረታቻ ላይ ስምህ ይኖራል ብለውት ሄደዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከማበረታቻው አንዱ ራሽያ ሄደው እንዲማሩ የሚል ነበር፡፡ ለጉዞ የሚሆን ሁሉም ሂደት ከተጠናቀቀ በኃላ ለጉዞ ቦሌ አየር ማረፍያ ይገኛሉ፡፡ በማያወቃቸው ሰዎች የሆነ መልእክት እንደመጠና መሄድ እንዳማይችሉ ይነገራቸውና በዛ ምክንያት ተመልሰዋል፡፡
ኡመር አሊ ከይሪ በአፋርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ በሶማልኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ዝግጅቶች ያቀርብ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ኡመር ከአፋርኛ ውጭ እንዲሰራ ያነሳሳውም አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ በጊዜው ለአፋርኛ ክፍል የወር ደሞዝ 280 ብር ነበር፡፡ ለአማርኛ 500 ብር ክፍያ ነበር የሚከፈለው፡፡ ከማን አንሰን ነው በማለት ካሁን በኃላ ጥሩ ክፍያ ባለው ክፍል ላይ ነው መስራት የምፈልገው በማለት ለአለቆቹ ጥያቄ ያቀርብና ለስምሪት ሄዶ ለሁሉም ቋንቋዎች የሚሆኑ ግብአቶች በመሰብሰብ አቀነባብሮ ይኸውላችሁ ከአሁን በኃላ በአፋርኛ አልሰራም በማለት ይጠይቃል፤ከዚያም አለቆች ተመካክረው ጥያቄው አግባብነት እንዳለው ተገንዝበው እኩል ክፍያ እንዲከፈላቸው ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአሚባራ እርሻ ልማት ውስጥ ፈረንጆች እርሻን በግመል እያረሱ ሲያስተምሩ አይቶ ቃለ- መጠይቅ በማድረግ ለእንግሊዝኛ ክፍል አዘጋጅቶም ያቀረበበት ዝግጅት በጣም ይደነቅለት ነበር፡፡
ኡመር አሊ ከዜና አንባቢነት በተጨማሪም ኢትዮጰያ ያዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ከአዲስ አበባ ስታድየም በቀጥታ ስርጭት የእግር ኳስ ጨዋታ አስተላልፏል፡፡ በዚህም ሲያስተላልፍ በብዛት ይጠቀማት ከነበረችው ቃል አፋር ህዝብ የቅጥያ ስም አድርጎ ይጠሩት ነበር፡፡ ይህች ቃልም “ያ ሳላም” ነች፡፡ የሚያውቁት ሁሉ ኡመር ከሚሉት “ያ ሳላም” ይቀናቸው ነበር፡፡
በዚህ ሙያ ላይ እያለ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በሹመት እንዲሄድ ከመንግስት ትእዛዝ ይመጣል፡፡ የሬድዮ ዝግጅት ኃላፊዎች ኡመር በተለያየ ቋንቋ የሚሰሩ ስለሆነ አትወሰዱብን በማለት እንዳይሄድ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም የፖለቲካ ውሳኔ ስለነበር ወደ ተመደበበት ስራ እንዲሄድ ትእዛዝ ተሰጣቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ጦርነቱ ላይ የህዝብ ንቅናቄ ላይ እንዲሰራ ተብሎ የአዳልና ገብረ-ጉራቻ አውራጃ ኃላፊ ሆኖ ተሹሞ ይሄዳል፡፡ እዛ እያለ ለሬድዮ ጣቢያ የሚሆኑ መረጃዎችን ያስተላልፍ ነበር፡፡ በተለይ ለአፋርኛ ክፍል በቀጥታ እየገቡ ይዘግብም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ 11 አመታት አለፉ፡፡ በኃላም ተቀይሮ ወደ አዲስ አበባ የንግድ መምሪያ ሃላፊ ተደርጎ ተሾመ፡፡ ከአዳልና ጋራ-ጉራቻ ሲነሱ ህዝቡ በጣም ይወደቸው ስለ ነበር እንዳይቀየር በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ አፋር፣ ኦሮሞና የሶማሌ ሀገር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ ህዝቡ እንዲረጋጋ እንዲያሳምኑ በመንገር ህዝቡ በበዛ መንገድ መረጋጋት ችሏል፡፡ በኃላም ህዝቡ የሽኝት ፕሮግራም ባዘጋጀበት እለት ሁሉም ጎሳዎች በወርቅ የተሰራ የአንገት ሀብል በስጦታ መልክ በማበርከት በለቅሶ ነበር የሸኛቸው፡፡ ኡመር ከሁሉም ጋር የሚግባባና ሩህሩህና ቅን ሰው እንደነበር የቅርብ ጓደኞቹ ይመሰክሩለታል፡፡
በመቀጠልም በልደታ ክፍለ-ከተማ ከ1995-2000 ዓም ድረስ የክፍለ ከተማው የንግድ ፅ/ቤት ኃላፊ በመሆን አግልግለዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት በኢጋድ አስተዳደር ረዳት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ኡመር ለአፋርኛ ቋንቋ እድገት ወጣቱን በማማከር፣ የአፋር ባህል እንዳይበረዝ ትልቅ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ለወጣት ጋዜጠኞችም ህይወታቸውን በማጋራት ውጤታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰው ናቸው፡፡
ኡመር አሊ ከይሪ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅና የአንድ ሴት ልጅ አባት ናቸው፡፡
የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት
አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
የአፋርኛ ጋዜጠኝነት ላይ ትልቅ የመሰረት ድንጋይ እንዳስቀመጡ የሚነገርላቸው ጋዜጠኛ ኡመር አሊ ከይሪ በወጣት የአፋር ጋዜጠኞች እንደ ትልቅ አርአያ የሚታዩ ናቸው፡፡ ወጣቶችን
በእንዴት ያለ መልኩ መምከር እንዳለባቸው ያውቁበታል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ለሙያቸው ያላቸው ታማኝነት በብዙዎች ይመሰከርላቸዋል፡፡
ጋዜጠኛ ኡመር አሊ ከይሪ በአማርኛ እንዲሁም በሌሎች የጋዜጠኝነት ፍቅራቸውን የተወጡ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥረታቸውም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ
ኮርፖሬሽን 10ኛው የሬድዮ ቀን በተከበሰ እለት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ50000/ የሀምሳ ሺህ ብር ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡
እርሳቸውም በዚህ ደስ ተሰኝተዋል፡፡ ሰው ለፍቶ ሲታወስ ደስ ይላል፡፡ እኛም ታሪካቸው በዚህ የጋዜጠኞች የታሪክ ሰነድ ውስጥ እንዲካተት
የፈለግነው በዘመናቸው ጥሩ አሻራ ያኖሩ በመሆኑ ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ