145.ጋዜጠኛ እና መምህር አዲስአለም ሀድጉ-ADDISALEM
HADIGU
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡
በዚህ ታሪክ ላይ ስራቸውና ስማቸው ተሰንዶ መቀመጥ ይገባቸዋል ካላቸው እና በሙያቸው ሀገርና ህዝብ ካገለገሉ ሰዎች አንዱ መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀድጉ አንዱ ናቸው ።
አዲስዓለም በአሁኑ ሰዐት ጡረታ ወጥተዋል ። ሆኖም በኢትዮጵያ ሬድዮ 93.1 ላይ በሚወዱት የዜና ክፍል በኮንትራት እየሰሩ ይገኛሉ ።
አዲስዓለም ከመምህርነት እስከ ጋዜጠኝነት በነበራቸው ቆይታ በሙያቸው ያበረከቱት ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ቲቪ የትግርኛ ክፍል ውስጥ በዜና አዘጋጅነት ከ25 አመት በላይ አገልግሏል፡፡
ባንቺአየሁ አሰፋ እና እዝራ እጅጉ የጋዜጠኛ አዲስአለም ሀድጉን ታሪክ እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡
ለ18 ዓመታት በመምህርነት ሙያ አገልግሏል ። ለ25 ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትግርኛ ቋንቋ
ዜና ክፍል ውስጥ በርካታ ሥራዎችን አየር ላይ አውሏል። በሙያቸው ያላቸውን ዕምቅ አቅምና እውቀት ለሀገር ካፈሰሱ ብሎም አንቱታን ካተረፉ ግለሰቦች አንዱ ለመሆንም በቅቷል ። መምህርና
ጋዜጠኛ አዲስዓለም
ሀድጉ ኪዳነማርያም ።
ትውልዱ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በጥንቱ የትግራይ ክፍለ-ሀገር ሽሬ አውራጃ ላይ ቆራሮ ወረዳ ነው።
በአሁኑ አጠራር
ደግሞ በሰሜን ትግራይ ሰሜን ዞን አስተዳደር አስገደ-ፅምብላ ወረዳ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ሁለት ( 1952)ዓ.ም
የካቲት ሀያ ዘጠኝ ( 29) ቀን ከአባቱ አቶ ሀድጉ ኪዳነ ማሪያም እና ከእናቱ ወ/ሮ በላይነሽ ገብረ ዋህድ ተወለደ ።
ቀጠን ያለውና ቀልጣፋው አዲስዓለም የትግራይን ጥዑም ጥህሎና አንባሻ እየጎረሰ፣
በለሶቿን እየቀነጠሰ ሲቦርቅ አደገ።
ከዚያ በተወለደ በስድስት ዓመቱ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ስምንት (1958) ዓ.ም ነበር ፊደል ለመቁጠር ወደ ትምህርት ተቋም ያቀናው።
ከሺህ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ስምንት እስከ ሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ (1958-1960) ባሉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ከተማረ በኋላ በሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ አንድ (1961) አራተኛ እና አምስተኛ ክፍልን በሴሚስተር ተሸጋግሮ አጠናቀቀ።
በሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሁለት (1962) ስድስተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዶ በድጋሚ በሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ አራት (1964) ለስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተቀመጠ ። ቀጥሎም ዘጠኝና አሥርን በሽሬ
ቀዳማዊ ኀይለስላሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሎ ወደ አሥራ አንድ ተዛወረ።
ወቅቱ አብዮታዊ ንቅናቄ የተጀመረበት በመሆኑ ለወራት ያህል የመማር ማስተማር ሂደቱ ተስተጓጎለ። ይህ ታዲያ የአንድ አዲስዓለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ ያናወጠ ሆነ።
መሬትም ቃጤ አከለች ።
በወታደራዊ
በአመፅ የተቀጣጠለው
አብዮቱ አሥራ አራቱምቱንም (14) ጠቅላይ ግዛቶች እንደግንድ ቀስበቀስ ለበለባቸው። ተማሪዎች በድንጋይ ውርወራ እና መፈክር ጎዳናውን ሞሉት ።
አንዳንዶች አሥራ አንደኛው ሰዓት ፣ አንዳንዶች የኢትዮጵያ አቢዮት ዋዜማ ሲሉት አንዳንዶች ደግሞ የዘውዳዊ ስርዓቱ ማብቂያ ይሉታል ። ሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስትን (1966) ።
የወታደራዊ ብሶት ያፈነዳው ማዕበል መሬት ላራሹ አለ ። ቀደምቷ ኢትዮጵያ በዳግም ወታደራዊ አገዛዝ
ኢትዮጵያ ትቅደም
ተብላ በረዣዥም እንጨቶች ላይ ተፅፋ ተሰቀለች። በሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት(1966) ዓ.ም የአዲስዓለም ሀድጉ ተማሪነት ቁርጡ ላልታወቀ ጊዜ ያህል ቆመ።
ሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት ወርሃ የካቲት
ሀገር ከባድ የሆነ ውጥንቅጥ ውስጥ የገባችበት ወታደር አኩርፎ እንደፈጣሪ የሚመለኩትን እንደሰይጣንም የሚኮነኑትን አፄውን ካልፈነገልኩ አልተኛም አለ። ንቅናቄው ቀስ በቀስ ውስጥ ውስጡን እየተዘረጋ
በመጣው የተማሪዎችና የወታደሮች
መረብ "እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል " ያሉትን ንጉስ በተቀመጡበት አጠመዳቸው።
ከአሥረኛ ክፍል በላይ ያሉ ተማሩ እድገት በህብረትን እንዲቀላቀሉ ሆነ ። በርካቶች ዘመቻውን ተቀላቅለው
መሃይምነት ላይ ዘመቱ ። ድንቁርና የተባለን አጋንንት ከየማጀቱ እያነቁ በየሜዳው ላይ በፊደል ፀበል
ማጥመቅ ያዙ ።
አደባባዩን የወታደራዊ ካህናቱ መዝሙር ሞላው ። አዲስዓለም ከዘማቾቹ መካከልም ሆነ።
እንበል ሁሌ ሉያ እንበል የምስራች
ከብዙ እስር ዘመን ኢትዮጵያ ተፈታች
ለእድገት በህብረት እንዝመት
ወንድ ሴት ሳንል በአንድነት
ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበረታ
ላገር ብልፅግና ለወገን መከታ
በርካታ ስንኞች በወታደሩና በአብዮቱ ደጋፊዎች ምላስ ተቋጠረ። የያኔው መምህር የአሁኑ ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀድጉ ታዲያ በዚያን ጊዜ ነበር ወደእድገት በህብረት በምደባው መሰረት ያቀናው ።
ምንምኳ ውጤቱ ለየቅል ቢሆንም በጊዜው እድገት በህብረት በርካቶችን ቀለም እንዲለዩ ፣ ፊደል እንዲቆጥሩ ፣ ቃል እንዲፈጥሩ ፣ እና ማንበብ መጻፍ እንዲችሉ በማድረግ
ዘመን የማይረሳው የፈውስ ገድል ሰርቷል ።
አዲስዓለም
ከሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስት እስከ ሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስምንት ዓ.ም (1966-1968) ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የዚህ ገድል ተቋዳሽ ሆነ ። ምንምኳን የተመደበበት ወረዳ የፀጥታ መደፍረስ ቢኖረውና ተልዕኮውን ለመወጣት ባይችልም
ዝውውር በመሙላት ወደሽሬ ምድብ ጣቢያ ሄዶ ለ6 ወራት ያህል ተሳትፏል። ምስለኔዎች ማመልከቻ/ በዘመኑ አጠራር ራፖር ለመፃፍ እንዲችሉ ከጣት ፊርማ ወደብዕር እንዲሸጋገሩ እና የመሃይምነት ጭንብልን እንዲያወልቁ በተደረገው ዘመቻ ላይ
ወታደራዊ መንግሥቱ በመደበበት ቦታ ፈቃደኛ በመሆን በትዕግሥት በመጠበቅ የድርሻውን ስለተወጣ ከሀገሪቱ የእድገት በህብረት ዘማቾች እኩል የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል ።
አዲስዓለም
የእድገት በሕብረት ተልዕኮውን ተወጥቶ ማንኛውም ሰው የሚያገኘውን ዕድል በማግኘቱ በሺህ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓ.ም (1969) በመምህርነት
ሙያ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። ትምህርቱንም ካቆመበት በመቀጠል በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ (1970) ዓ.ም ማትሪክ በመፈተን
ወደዩኒቨርስቲ የሚያስገባውን ውጤት አገኘ ። ይሁን እንጂ ታዲያ በግል ጉዳይ ዩኒቨርስቲ ሳይገባ እንደቀረ ይናገራል ። የተረጋጋ ስብእናን የተለበሰው ሥራ ወዳዱ ፣ ሙያውን አክባሪው፣ መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀድጉ ።
ከሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ
እስከ ሽህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሦስትዓ.ም (1970-1983) ድረስ በአንደኛ ደረጃ መምህርት በቋሚነት ተቀጥሮ በሽሬ ፣ ጨለቅለቃና ሌሎች የትግራይ ክፍለሀገራት ሰርቷል ። የትግራይ ክልል የህዝብ ልጆች ለጋ አእምሮ ላይ ያለውን አቅም ተጠቅሞ የህይወት ዘርን ለዓመታት ዘርቷል ። የእውቀት ሞሰቡን ዘርግቷል ። ያለውን ያለመሰሰት ሰጥቷል ።
ብዙ ባለሙያዎችንና ባለሃብቶችን አፍርቷል ። የተንከባከባቸው ቡቃያዎች ዛሬ ፍሬያቸው ጎምርቶ ሲመለከት በህይወቱ ያፈራው ሀብትና የኖረለት ዓላማ እንደሆነ ይናገራል ። መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀድጉ። ለአንዲት ታዲያ ሀገር ቀና ብላ እንድትሄድ የሚስፈልጋት የተማረ የሰው ሀይል እንደመሆኑ መጠን
የሁሉም ሙያዎች ቁልፍ የሚገኘው በመምህራኖች እጅ ላይ ነው ።
"Teacher is The Backbone of All
Profession " እንዲሉት
ነጮች ።ወይም መምህርነት
የሁሉም ሙያዎች የጀርባ አጥንት ነው እንደማለት ነው፡፡
ታዲያ መምህሩ ትዳርም የመሰረተው በዚሁ ወቅት በማስተማር ላይ ሳለ ነበር። በሚያስተምርበት ትምህርትቤት ታስተምር ከነበረችው ኤርትራዊቷ ምፅላል አብርሃ
ጋር ገና ወጣት ሳለ
በፍቅር ወደቀ ። በኋላም ከሚወዳት ምፅላል ጋር በ20 ዓመቱ ትዳር የመሰረተ ሲሆን በ1973 ዳናይት ሀደጉ የተባለች ሴት ልጅ ወልዷል። ቀጥሎም በ 1975 ሁለተኛ ወንድ ልጃቸው የሆነውን ማዕረግ ሀደጎን ወለዱ ። 1989 ላይ ሁለተኛ ሴት ልጃቸው አዝመራ ሀድጎ ቤተሰቡን ተቀላቀለች ። አዲስዓለም የሦስት ልጆች አባት ለመሆን በቃ።
ከትምህርትቤት ባለፈ ከ1978 ጀምሮ በትግራይ ትምህርት ቢሮ በመቀሌ የሬዲዮ ትምህርት ማሰራጫ ላይ በፍቃደኝነት/በነፃ
ማስተማር ጀመረ ። በህብረተሰብ ሳይንስ በኩል ስለዕድር ምንነት፣ የዕድር ጥቅም ፣ ዕድር ለማህበረሰቡ ያለው አዎንታዊ ሚና ምንእንደሚመስል ዳሰሳ በማድረግ ለህብረተሰቡ ግንዛቤን በማስጨበጥ ፤ በስነተዋልዶ ስለእናት ጡት ወተት ፣ የእናት ጡት ወተት ለህፃኑ ያለው ፋይዳ ስንት ወራት መጥባት እንዳለበት እንዲሁም ደግሞ በክልሉ ስላሉ የልማት ስራዎች ፣ ልማት ለማህበረሰቡ ያለው ጥቅምና ይዞት የሚመጣው ለውጥ ምን ያህል እንደሆነ መምህሩ ገና በልጅነቱ የትግራይን ማህበረሰብ በትጋት ሲያስተምር ቆይቷል ። ቁጥቡ፣ ለምንም ነገር የማይጓጓው ፣ መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀደጎ።
በሰንበት መዝናኛ ፕሮግራሞች
እጅግ ጎበዝ ስክሪፕት ፀሐፊ ከሆኑትና ጥዑም የሬድዮ ድምፅ ካላቸው ከነመብራቱ ገ/ማርያም ፣ አልማዝ ሚኒሊክና ታደሰ ነጋሽ ጋር በመሆን
አዲስዓለም የደራሲያንን ስራዎችና የደራሲያንን ህይወት ፣ የሙዚቀኞችን ሥራዎችና ሙዚቀኞችን ፣ የፊልም ሰዎችን ህይወትና ፊልሞችን በጥልቅ ብዕር ተመልክቶ ለትግራይ ክፍለሀገራት በሞላ እያዝናና አስተምሯል ። መምህርነት ዋና ግቡ ካለው
ላይ ሳይለካ ማጋራት በመሆኑ ያገኘውን አዲስ እውቀት ለዘመናት በሬድዮ በድምጽና በትምህርት ተቋም በአካል
ወረቀት ከስኪብሪቶ ድንጋይ ከድንጋይ እያፋፋቀ ያለውን ሲዘረጋ ቆይቷል። በዚሁ ወቅት በመቀሌ በሚካሄደው የብስክሌት ውድድር ፣ የሚኒሚዲያ ክበባት እና ስነፅሁፍ ዝግጅት ላይ
በመምራት ይሳተፍ ነበር።
መምህሩ ከተወዳጅ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ጋር በነበረው ቃለምልልስ ወቅት "ሬድዮ በማስተምርበት ወቅት ምንም አይነት ገንዘብ ሳይከፈለኝ ነገርግን ለሙያው ባለኝ ፍቅርና አክብሮት ብቻ ሲሆን
አስተማሪዎቼ እና የትምህርት ጓዶቼ ተሰብስበው ስለሚያደምጡኝ የሚሰማኝ ውስጣዊ ሀሴት ስለነበር ነው ይላሉ ።"
የመምህር ደመወዙ አድማጭ ማግኘት ነው ቢባል ጉዳዩን አላጋነነውም።
በሺህ ዘጠኝ ሰማንያ ሰማንያ ሁለት (1982) በነበረው አብዮቱን የመገርሰስ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማምጣት ሽኩቻ መንግሥት ክልሉን ሲለቅ አዲስዓለም ከመቀሌ ወደ ደሴ ቤተሰቡን ይዞ ተሰዷል ። ከአንድ ዓመት የደሴ ቆይታ በኋላም በድጋሚ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሦስት (1983) ወደሲዳሞ
ተሰዶ ለአንድ ዓመት ያህል አስተምሯል ።
መንግስቱ
የገቡበትን በር ለኢህአዴግ ጥለው በመስኮት ሾለኩ ሲባል አዲስዓለም በድጋሜ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት (1984) ማዕበሉ መርጋት ሲጀምር ከነቤተሰቡ ተመልሶ ወደትግራይ መቀሌ በመሄድ በአካባቢው የትምህርት ማሰራጫ ሬድዮ ህብረተሰብ ሳይንስ በቋሚነት ማስተማር ጀመረ።
በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሁለት (1992) ዓ.ም እናትና ልጅ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዐይንሽን ለአፈር ተባባሉ። እንደባላንጣ የጎሪጥ መገረማም ጀመሩ ። ኤርትራ ጨርቋን ማቋን ሰብሰባ መንገድ ገባች ። ዜጎች ባርነት ወይስ ነፃነት ምሩጡ ተባሉ ።
መምህሩ አዲስዓለም ባለቤቱን ነፃነትን ምረጪ አለ። የለም ባርነትን እመርጣለሁ አለች። መጨረሻ ልጆች አሉን ለክፉም ለደጉም ብሎ በማሳመን
አዲስዓለም ድል አድርጎ ምፅላል ነፃነትን መረጠች ። በምርጫዋ ከመምህርነት ሙያዋ ታገደች። በጦርነት እልህ ሥራ መስራት ሀገርን በሙያ ማገልገል ለዚያውም ኤርትራዊ ሆኖ ፍፁም ሐጢያት ነው አለ የኢትዮጵያ መንግሥት ። በአንድ አባዋራ የመምህር ደመወዝ 5 ቤተሰብ ማስተዳደር ተያዘ።
በኋላ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬት ) የቴሌቪዥን ስርጭት በጀመረ በሦስት ዓመት ተኩል አካባቢ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስምንት (1988) ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ አማካኝነት ተወዳድሮ በአንደኝነት በማሸነፍ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ዓ.ም(1989) ጥር
አንድ ቀን በቀድሞው የመምህርነት ደመወዙ (751.00)ብር ተቀጥሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ተቀላቀለ ። መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀደጉ።
አንቱታን ያተረፈው አንጋፋው መምህር አዲስዓለም
ከ18 ዓመታት በላይ የመምህርነት የሥራ ልምድ ይዞ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትግርኛ ዜና አዘጋጅ ሆኖ ስራውን ጀመረ ። ኑሮውንም ከነቤተሰቡ በአዲስ አበባ አደረገ። ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራውያንን እየመነጠረ ማስወጣት ያዘ ። በሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ቁርሾ ህዝቦች የፍዳ ናዳ ወረደባቸው ። ዓይኖች እስኪሟሙ ተለቀሰ ። ምጥ በአንጀት ተጀመረ ። ይህ መከራ ከአዲስዓለም ቤት እጆቹን አስረዝሞ ገባ። ምፅላልንና ሁለት ሴት ልጆቿን ያለውል በግድ አውጥቶ አሥመራ ወረወራቸው። ቤተሰብ መካከል ሀገር የተባለ ቀን ይገፋዋል ተብሎ የማይታሰብ ግርግዳ ቆመ። አዲስዓለም ከወንድ ልጁ ጋር ብቻውን ቀረ ። ሚስትና ሁለት ሴት ልጆቹ ብቻቸውን ሄዱ።
ካልሞቱ ህይወት ይቀጥላልና አዲስዓለም የጋዜጠኝነት ሥራውን በሀዘን እንደተኮማተረ ቀጠለ። ምንምኳን ለዜና አንባቢነት ተፈልጎ የተቀጠረ ቢሆንም በቲቪ ስክሪን ከመውጣት ይልቅ ወደውጪ ወጥቶ እንዲዘግብ ሆነ ። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ህዝብ ነገውን የሚገምትበት ትክክለኛ ፣ ሀገራዊ ፣ ወቅታዊ እና ትኩስ መረጃንዎችን ከቦታው ሆኖ በትግርኛ ቋንቋ ማድረስ ያዘ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግርኛ ዜናዎችን በማዘጋጀት ፣ ኤዲተር በመሆን አመረተ።
ጋዜጠኝነት ሙያው ብዝሃነት እንደመሆኑ መጠን እራስን አሳልፎ እስከመስጠት ድፍረትን ይሻል ።
ቦታ ቀየረ እንጂ ጋዜጠኝነትም መምህርነት ነው።
ታዲያ የልቡን በልቡ አድርጎ ሚስትና ልጆቹን ላባረረችበት ሀገር በስሟ በፅናት (የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን) ማገልገሉን ቀጥሎ ለየትኛውም ፓርቲና ሀሳብ ሳይወግን የቱጋ መቆም እንዳለበት ሳይጠፋው ስለሀገር ሰላም ስለትግራይ መልሶ መቋቋም እስከጥግ ድረስ ፕሮግራም በመስራት ሁሉ ተሳትፏል ።
የሀገር ውስጥ እና የሀገር ውጪ ጉዳዮችን በተለይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ
በአንክሮት በማየት ሽፋናቸውን በማንሳት ህዝብ ሊያውቃቸው ይገባል ያላቸውን ዓብይ ርዕሰ-ጉዳዮችን ከምላስ ላይ በማይክ እየነጠቀ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትግርኛ ቋንቋ ክፍል አቀብሏል ።
እንዳስፈላጊነቱ በሦስት ቋንቋዎችም በመተርጎም ጭምር ከዓለም ሀገራት ጉባኤ እስከ ህዝብ በዓላት ድረስ በትግርኛ ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተቀላጠፈ ሰውነት በተቀላጠፈ ጥያቄና የአጠያየቅ ብልሃት ሰርቷል።
በክህሎቱ አዎንታዊና አሉታዊ የሆኑ አስተያየቶችንም ሰብስቧል ።
ውስጡን የልጅና የሚስት ናፍቆት እንደምስጥ እየሰረሰረው ሥራውን በዝምታ ገፍቷል ።
በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ሙያዊ ቅኝት ሲያደርግ
በሥራ ጉዞ ወቅትም አሰቃቂ ገጠመኞችን አሳልፏል ። አዲስዓለም ለሥራ ወደቤንሻንጉል በሄደበት ወቅት የገጠመውን እንዲህ ሲል ለተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን አስታውሷል። "ጉዞ ላይ እያለን ድንገት መኪናችን ነዳጅ ጨርሶ በምሽት መንገድ ላይ ቆመ
፤ ይላል ።
የመኪናችንን መቆም ያዬ አንድ ባለመኪና ነዳጅ በቅርበት እንደማናገኝ በመንገር አውላላ ሜዳ ላይ በንግግሩ ተስፋ አስቆርጦን ሄደ ። እኛም
አማራጭ ስላልነበረን ብርዱን ለመቋቋም እንጨት ለቅመን በመኪናው እንጥፍጣፊ ነዳጅ ክብሪት በመጫር እሳት አነደድን።
እሳቱን እየሞቅን ሳለ በኋላ የታጠቁ ሰዎችና ፖሊሶች መኪና ይዘው እኛ ወዳለንበት እየተጯጯኹ መጡ
። ስለምን ነው እሳት የምታነዱት? ሲሉን ስለበረደን ብለን መለስን ።
ያተረፋችሁ እሳቱ ነው ። ይህ አካባቢ በምሽት አዞዎች ለውኃ ፍለጋ አንበሶች ለአደን የሚንቀሳቀሱበት ነው። ሰዓቱም ቦታው የሰው አይደለም ።ፈጣሪ አትርፏችኋል ።
በማለት በፍጥነት ወደከተማ ወሰዱን ። ህይወታችንን የታደገለን ቀድሞ ተስፋ ያስቆረጠን መንገደኛ ሾፌር ነበር ። ከተማ ሄዶ ስለጉዳዩ በመንገር ፤ እኛም ጉዳዩን አጀንዳ አድርገን ተጫወትንበት" ይላል ።
እንግዲህ ጋዜጠኝነት ከባድ ሙያ ለመሆኑ በቂ ማሳያ ነው። ለዚያውም ለአዲስዓለም ህይወት ። ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለማድረስ በጦር ግንባር ለጦር ዘገባ ወጥቶ ተመትቶ መቅረት ፣ በፖለቲካ ጉዳይ ለእስር መዳረግ ፣ በወንጀል ጉዳይ በሰው እጅ እስከማጥፋት ያደርሳል ጋዜጠኝነት ።
ሌላው አዲስዓለም ዜና አርታኢም ነው ። ዜና እንደሙሽራ ክንብንብ ስለማትወድ ጠርቦ አስተካክሎ ማለት የተፈለገውን ጉዳይ ብቻ መባል ባለበት ጊዜ ለዐይን በማይሰቀጥጥ ለጆሮ በማይጎረብጥ መልኩ እንዲደርስ በማድረግ ይታወቃል ። በተለይም የእንግሊዝኛ ዜናዎችን በሚተረጉሙበት ጊዜ በረቀቀ ስልት በጥሩ ቋንቋ ከሀገራችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስርዓት እና ፖሊሲ በማይፋለስ መልኩ በመተርጎም እና አርትኦት በማድረግ ለብዙዎች ዜና አውዱን ጠብቆ እንዴት እንዲሚሰራ ጭምር ማስተማር የቻለ አንጋፋ የሙያ ሰው ነው።። ጋዜጠኝነት እና መምህርነት በአዲስዓለም እይታ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው ።ሁለቱም የመማማር ሂደትን የሚያጎለብቱ በየጊዜው አዲስ ነገርን የሚጨምሩ ሙያዎች በመሆናቸው የሰው ልጅ ጋዜጠኛ ሲሆን ሁሌም እየተማረ ነው ይላል። አዲስዓለም
የትኛው ዜና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የትኛው ጉዳይ ከየትኛው አንገብጋቢ እና ሰውጋ መድረስ እንዳለት ማወቅና መልዕክቱን መረዳት እንደሚያስፈልግ የተባለውን ሁሉ ማለት ሳይሆን ምን ለማለት እንደተፈለገ
የዜናውን ጀርባ በሚገባ ማጤን
ይገባል ይላል። በቋንቋ በኩል ሰውጋ የሚደርስ አንድ ቃል አውዳዊ ፍቺው ምን ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መጠንቀቅ ያሻል ሲል ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትግርኛ ቋንቋ ዜና ክፍል
ሦስት ነገሮችን
በአሻራነት አስቀምጧል ።
1ኛ, የእንግሊዝኛ የዜና አተረጓጎም ስልት ከአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፖሊሲ አኳያ
2ኛ, የዜና ቅደም ተከተል ከጉዳዩ ይዘት አንፃር እንዲሁም የሚነገርበት ቋንቋና አውድ Context
በቋንቋው አርትኦት ስራው ዲክሽነሪ ነው ይሉታል ።
3ኛ, ምን ቢነገር ምን ይዞ ይመጣል ( ከብሔርና ከሐይማኖት አኳያ)
ለ25 ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትግረኛ ቋንቋ ዜና ክፍል ላይ የሰራው አዲስዓለም
ዜና ስለሀገሬ በደንብ እንዳውቅ አድርጎኛል ። መንግሥት መኪና አዘጋጅቶ አበል ከፍሎ ሀገሬን እንዳውቅ ያደረገኝ ጋዜጠኛ ስለሆንኩ ነው። የሀገሩን አሁናዊ ሁኔታ በቅርበት የሚረዳ እና ስለወደፊት እጣፋንታዋ መገመት የሚችለው ጋዜጠኛ ነው። ሌላው ሌላው ቢቀር ሚዛናዊ ያደርጋል በተለይም ለዜና ክፍል ይላል ሙያውን አክባሪው መምህር እና ጋዜጠኛው ቤተሰብ ናፋቂው አዲስዓለም ሀድጉ።
በስራ ቦታው የእርሱን ፈለግ የተከተሉ ብዙዎች ያሉ ሲሆን በጠማማ አረዳድም የተረዱት አልጠፉም ።
አንድ ሰው በሁሉም ሰው ሲታይ ልክ ከሆነ ነውና ልክ የማይሆነው ይህ የሱ ጉዳይ አይደለም ።
ከሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ስምንት
አሁን እስካለንበት ሁለት ሺህ አስራ አራት ዓ.ም (1978-2041) ለ36 ዓመታት በመምህርነትና ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሙያዊ ስክነት ያገለገለ አንጋፋ መምህር እና ጋዜጠኛ ነው። በትምህርት ተቋማት ተቀጥሮ ማስተማር ከጀመረበት 1969ዓ.ም ጀምረን ስንቆጥር ግን የአገልግሎት ዘመኑ ወደ 43
ዓመታት ያድጋል ። ሀገራችንም አለመደባት እሱም መሾም መሸለም አያምረውም። ለሞያዊ አገልግሎቱ እንጂ ለአምሮቱም አልተጋም። አገልግሎቱን ያስተዋለ የለምና እውቅናም አልተቸረውም። አለመታወቁ ከመስራት ስለማያግደው ለአዲስዓለም ግድ አይሰጠውም ።
አሁንም ጡረታም ወጥቶ የኢትዮጵያ ሬድዮን በኮንትራት እያገለገለ ይገኛል ። በፖለቲካ አቋም ከጣቢያው በርካቶች የታሰሩ እና የታገዱ ሲሆን አዲስዓለም አንድ ተቋም እስኪባል አሁንም በዜና ክፍል እየሰራ ይገኛል።
"ጡረታም ወጥቼ እንድሰራ መደረጉ ለእኔ ሽልማቴ ነው።"ይላል
ከትግራይ ማህፀን የበቀለው ሀገር እና ህዝብ ወዳዱ የስድሳ ሁለት (62) ዓመቱ አዲስዓለም ሀደጎ ።
የለውጡ መንግሥት ከመጣ ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ እንደወጡ ሰሞን በ2010 መጨረሻ አካባቢ ነበር አዲስዓለም ከ20 ዓመታት በኋላ ባለቤቱን እና ልጆቹን ወደኤርትራ ተጉዞ ያገኛቸው ። ምንም እንኳን አብረው ለመኖር የሚያስችላቸውን ዕድል ባያገኙ ቤተሰቡ ከዓመታት በኋላ በህይወት መኖራቸውን አረጋግጠዋል ። ናፍቆት በልቶ
የጨረሳቸው መምህራን ወላጆችና ልጆቻቸው ለዓይነ-ስጋ በቅተዋል ።
" እኔ መምህርነትን እና ጋዜጠኝነት በጣም እወዳለሁ ። ሁለቱን ለመለየት እቸገራለሁ " ይላል
መምህርና
ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀደጉ !
የመዝጊያ ሀሳብ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀደጉ ከትግራይ ክልል የኢትዮጵያ የሬድዮ የትምህርት ማሰራጫ ጣቢያ እስከ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድረስ በሚዲያው ዘርፍ ለ36 ዓመታት ያገለገለ ብስል ባለሙያ ነው። ከመምህርነት እስከ ጋዜጠኝነት ድረስ ሰርቷል ።
በሰራባቸው ጊዜያት ሁሉ ድምፁ ሳይሰማ ስራውን በአግባቡ የሚከውን ጥንቁቅ ሰው ሲሆን በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የትግርኛ ቋንቋ ክፍል ዘመን የማይሽራቸው የግሉ የሆኑ
አሻራዎችን አሳርፏል ። በስራ ዘመኑ መረጃ በህዝብና በሀገር ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ እና ሰላም ያለውን ዋጋ ጠንቅቆ ያውቃል።
ዜና በሚተረጎምበትና በሚተላለፍበት ወቅት እንዲሁም ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ከቋንቋና ሀገራት ካላቸው ዲፕሎማሲ አኳያ እንዴት መታየት እንዳለበት ለሙያ አጋሮቹ ያስተማረ አንጋፋ ሰው ነው። ሀገራችን እጅግ በርካታ ባለሙያዎችን ይዛ ዛሬም ድረስ መስራት ያለባትን ያህል መስራት ያልቻለችው እና እጇን ከሰው ሞሶብ መሰብሰብ ያቃታት ሰራተኞቿን በሚገባ ስለማታውቃቸው ነው።
ስለማታውቃቸው አታስተዋውቃቸውም፡፡
ሚዲያው ላይ በየመስኩ አንገት ደፍተው የሚሰሩ በርካታ መሪዎች እንኳን ሥራቸው ስማቸው የማይታወቅ ሳይታወቅም ህይወታቸው የሚያልፍ ብዙዎች አሉ ። ለነዚህ የሀገር መሪዎች፣ ባለውለታዎች ምንምኳ የሥራቸውን ባያክልም አስፈላጊውን እውቅና እና ክብር ሊያገኙ ይገባል።
ከነዚህ ባለውለታዎች መካከል የመምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀደጎን ታሪክ ሰንዶ ማስቀመጥ እንዲሚያስፈልግ ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስላመነ በሁሉም ጊዜው ከመምህርነት እስከ ጋዜጠኝነት ከ43 ዓመታት በላይ ሀገሩን ስላገለገለው የሀገር ልጅ መምህርና ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀደጉ ታሪክ በፅሁፍ ተሰንዷል።
አዲስዓለም ስላበረከታቸውና ወደፊትም ስለሚያበረክታቸው አገልግሎቶቹ እንደተወዳጅ ሚድያ አክብሮታችንን እንገልጻለን፡፡/ ይህ ጽሁፍ ባለታሪኩን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ፤የባለታሪኩን
የቅርብ ሰዎች በማነጋገር ፤ የተጻፈ ነው፡፡
ጽሁፉ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና
በጋዜጠኛ ባንቺአየሁ አሰፋ የተጻፈ ነው፡፡ይህ ጽሁፍ ዛሬ እሁድ የካቲት 20
2014 ከቀኑ 8 ሰአት ከ22 ደቂቃ ላይ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና የግለ-ታሪክ ብሎግ ላይ የተጫነ ሲሆን አስፈላጊው
ለውጦችና ማስተካከያዎች ካሉም በየጊዜው ተሻሽሎ የሚቀርብ ነው፡፡ ይህን ግለ-ታሪክ እንድንሰራ ትልቅ ትብብር ያደረገችልንን ጋዜጠኛ
ፍሬወይኒ ገብረጻድቅን ከልብ ልናመሰግናት እንወዳለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ