144 «በሪሳ ጋዜጣ የተጀመረችው በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ፊርማ ነው».ዶክተር መሃዲ ሀሚድ ሙዴ የበሪሳ ጋዜጣ መስራች
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ
ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ የበሪሳ ጋዜጣ
መስራቹ ዶክተር መሃዲ ሀሚድ ሙዴ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ያበረከቱት ሚና ግን በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡
በተለይ በአፋን ኦሮም ዛሬ ድረስ ለህትመት መብቃት የቻለው ‹‹በሪሳ›› ጋዜጣ የህትመት ብርሀን እንዲያይ ያደረጉ ባለውለታ
ነበሩ፡፡ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ አዲስ ዘመን ጋዜጣን እንደ ምንጭነት በመጠቀም እንዲሁም የሚውቋቸውን ሰዎች በማነጋገር
ግለ-ታሪካቸውን እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
አባ ዲክሽነሪ
አባ በሪሳ፣ አባ ዲክሽነሪ ልዩ መጠሪያ ስማቸው ነው። የትውልድ ቦታቸው ምሥራቅ ኦሮሚያ በወቅቱ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ደግሞ ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ ሲሆን፣ 1943 ዓ.ም የትውልድ ዘመናቸው ነው። እኚህ በ70 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈ የዕድሜ ባለፀጋ የተወለዱት ከአባታቸው ከአቶ ሀሚድ ሙዴ ኡርጊ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሀሚዳ አህመድ ነው። እናታቸው 14 ልጆችን የወለዱ ሲሆን፣ እርሳቸው ደግሞ 10ኛ ልጅ ናቸው።
ወደ መደበኛው ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት የተማሩት የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች የሚማሩበት መድረሳ በመባል በሚታወቀው ውስጥ ነው። ወደ መደበኛው ትምህርት ቤት ሲመጡ ቀጥታ የገቡት ሦስተኛ ክፍል ሲሆን፣ በወቅቱም ዕድሜያቸው ዘጠኝ ዓመት የሚጠጋ ነበር። አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በስድስት ዓመት ውስጥ ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ይህ መሆን የቻለው ደግሞ በግማሽ ዓመት (ሴሚስተር) ከክፍል ወደክፍል
ማለፍ በመቻላቸው ነው።
በጭሮ ከተማ በደጃዝማች ወልደገብርኤል አባሰይጣን ተብሎ ይጠራ በነበረው ትምህርት ቤት የተጠናቀቀው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዝልቋቸው በአራት ኪሎ ካምፓስ የፊዚክስ ተማሪ በመሆን እንዲቀላቀሉ አስችሏቸዋል። ይሁንና የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያሉ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ቆም አድርገው ወደ ጎጃም አቅንተዋል –የበሪሳ ጋዜጣ መስራቹ ዶክተር መሃዲ ሀሚድ ሙዴ።
ዶክተር መሃዲ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ
ሦስተኛ ዓመት ላይ ያቀኑት ወደ ጎጃም ደብረማርቆስ ነበር። የሄዱትም በመምህርነት ተቀጥረው ሲሆን፣በዚያም በንጉስ ተክለኃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ሦስት ወር ያህል አስተማሩ። በመቀጠልም ወደ ባህር ዳር
አቀኑ፡፡
በባህር ዳር ሁለት ዓመት ተኩል ያህል ካስተማሩ በኋላ የ66ቱ አብዮት መጣ፤ በወቅቱ የሚያስተምሩት አንድ ፈረቃ እንደመሆኑ ግማሽ ቀን ያህል በኦሮሚኛ ቋንቋ አንዳንድ ነገር ይፅፉ ነበር።ልጆች የሚማሩባቸው ዓይነት መጽሐፎችን በኦሮሚኛ ቋንቋ ያዘጋጁ ጀመር።
የእድገት በህብረት ዘመቻ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ይሂዱ በመባሉ በኦሮሚኛ ቋንቋ ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በወቅቱ የዘመቻው አስተባባሪ ለሆነው ለሻምበል ኪሮስ አለማየሁ አደረሱ፡፡ ኪሮስም በጣም ደስተኛ ሆኖ ተቀበላቸው።
በአንድ ወቅት ዶክተር መሀዲ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ:
‹‹…..የፃፍኩት
የኦሮሚኛ ጽሑፍ በላቲን ፊደል ለምን እንደተፃፈ ሲጠይቁኝም እስከዛሬ ድረስ የኦሮሚኛ ቋንቋ በተለያዩ ፊደላት ተፅፏል። የሳባ ፊደል ለኦሮሚኛው ጽሑፍ ምቹ አይደለም። የላላና የጠበቀን ፊደልም በአግባቡ ማሳየት አይችልም። የአረብኛው ፊደል ደግሞ እንደ እነ ጫ፣ ጳ፣ ኛ እና ጋ የመሳሰሉ ፊደሎች የሉትም። ስለዚህም ነው የላቲኑን ፊደል ለመምረጥ የተገደድኩት ስል እሺ ቁጭ በል አለኝ።
ይህ ሰው ሰበብ የማብዛቱ ምስጢር ትግርኛ ቋንቋ የማስተማሪያ ቋንቋ እንዲሆን ፍላጎት ስለነበረው ነው። ይሁንና ሊሳካ ባለመቻሉና ባለማወቁ የትግርኛን ቋንቋ ከኦሮሚኛ ጋር ተለጣፊ ሆኖ እንዲሳካለት ጉዳዩን የደርግ አባላት ወደሆኑት የኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ አደረሰው። በወቅቱ እድገት በህብረት ዘመቻ ላይ በኦሮሚኛ ቋንቋ ለሚፃፈው የክፍለ ትምህርት ኃላፊ እኔ ስሆን፣ በትግርኛ ለሚፃፈው ደግሞ ኃይሉ አርአያ ነበረ። የሒሳብ ትምህርትን ጨምሮ ወደ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚነበቡ መፅሐፍት አሳትመን እንደ አገር መማሪያ እንዲሆን አድርገናል። ይህ ማለት
ጊዜው
1966 እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ሲሆን፣ እኔ እዛው እያለሁ ነው በሪሳን ጋዜጣን የጀመርኩት። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ያለመጨረሴ ምክንያት በትግል ላይ ስለነበርኩ ነው።›› በማለት ስለ ጉዳዩ አስረድተው
ነበር፡፡
በሪሳን የማሳተሙ ነገር
ዶክተር መሃዲ በተፈጥሮአቸው አንድ ሰው መልካም ነገር እንዲገጥመው ሁሌም የሚመኙ ሰው ነበሩ፡፡ ሌላው ብሔር ያገኘውን መልካም ነገር የእርሳቸውም ብሔር እንዲያገኝ ይመኛሉ። በዛን ወቅት በተለያየ ቋንቋ ማለትም በእንግሊዝኛና በአማርኛ እንደ እነ የዛሬዪቱ፣ አዲስ ዘመን፣ ፖሊስና እርምጃው፣ ወታደርና ዓላማው በመባል የሚታሙ የተለያዩ ጋዜጦች ነበሩ።
በመሆኑም ለምን በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚታተም ጋዜጣ አይኖረንም የሚል ሐሳብ ዶክተር መሀዲን ይሞግታቸው ነበር። ይህ ውስጣዊ ሙግት የፈጠረባቸው ጉዳይ
ሐሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ደግሞ እውን ማድረግን አጥብቀዉ አሰቡበት። በወቅቱ ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ ይሆናል የሚል ነገር በውስጣቸው አልነበረም። እንዲያውም ነገሮች አልጋ በአልጋ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ይሁንና ወደ እንቅስቃሴው ሲዘልቁ ጠጠር ያለ መሆኑን ተረዱ። ይህ ጊዜ 1963 እና 1964 አካባቢ ነበር። ዶክተር መሀዲ ከ50 አመት በፊት የነበረውን
የበሪሳን አጀማመር ሲያስታውሱ:
‹‹……በዚያን ጊዜ የማስታወቂያ ሚኒስትር የኤርትራ ተወላጅ የሆኑ ዶክተር
ተስፋዬ ገብረእግዚ ይባሉ ነበር። .አቡነ ጴጥሮስ ወደነበረው ቢሯቸው በመሄድ በአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ ማሳተም እፈልጋለሁ አልኳቸው። እርሳቸውም የሰጡኝ ምልሽ አርኪ አልነበረም፡፡ በጣም
ተናደድኩ። ነገር ግን በመምህርነት ባህር ዳር እሰራ ነበርና ያንኑ ቀጠልኩበት።›› ሲሉ ትዝታቸውን አውግተው
ነበር፡፡
በ1966 ዓ.ም ወታደሩ «የወር ደመወዝ ይጨመርልን» በሚል ከአስመራ በኦጋዴን አካባቢና በሌላውም ቦታ ሲነሳሳ አክሊሉ ሀብተወልድ ወርደው እንዳልካቸው መኮንን የሚባሉ ቦታውን ያዙ። እንዳልካቸው የሚባሉ ደግሞ አሃዱ ሳቡሬን ሚኒስትር አድርገው አመጧቸው። ዶክተር መሀዲም ተስፋ ሳይቆርጡ የጀመሩትን ሐሳብ ይዘው ወደ አሃዱ ሳቡሬ ሲሄዱ እንደ ሚኒስትሩ ተመሳሳይ ምላሽ ተሰጣቸው።
በ1966 ዓ.ም
ማጠናቀቂያና በ1967 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ጃንሆይ ከሥልጣን ለቀቁ፤ ደርግ ደግሞ ቦታውን ተቆናጠጠ። በወቅቱ ሁሉም ወደጦር
ሜዳ ይሂድ ተብሎ ተወሰነ። ዶክተር መሀዲ ደግሞ በዚያን ጊዜ
ማስተማሩን ትተው እድገት በህብረትን ጀመሩ። እዚያው እያሉ ወደ ሦስት ያህል መጽሐፍትን ከፃፉ በኋላ /በእርግጥ በርካታ
መጽሐፍትን ነው ለማሳተም የሚፈልጉት/ አለቃቸው ግን «በቃህ እዚህ ላይ አቁም» ሲላቸው፣ ምነው እኔ አልደከምኩ፤ እናንተ
ስለምን ደከማችሁ ሲሏቸው ። «አይሆንም በቃ» ተባሉ።
«እንድትጽፍ የተደረገው ለመሸጋገሪያ ነበር» ተባሉ።
የበሪሳ
አጀማመር በዶክተር መሀዲ አንደበት
‹‹….ምን ማለት
ነው? ስል ሌላ ሰው ስጠይቅ በሳቢኛ ፊደል ተጠቅመው በኋላ ላይ አማርኛን በደንብ እንዲያነቡ ታስቦ ነው የሚል ምላሽ በተሰጠኝ
ጊዜ በጣም ተቆጨሁ፤ ወዳላሰብኩበትም ነገር መግባቱን አንስተዋል።
እንዲያም ሆኖ የእኛ
ሰዎች ማንበብ ለመዱ። በመሆኑም አሁን ይህን ያህል ፊደሉን አውቀው ማንበብ ከቻሉ በይበልጥ ደግሞ ጋዜጣ በማንበብ ምቹ ሁኔታን
ይፈጥርልና በማለት ቀደም ሲል የተኮላሸውን ሐሳብ እንደገና ነፍስ እንዲዘራ በማንሳት ደግሜ ወደ ሻለቃ ግርማ ይልማ ወደሚባሉ
የማስታወቂያ ሚኒስቴር ዘንድ ሄድኩ። በኦሮሚኛ ቋንቋ ጋዜጣ ማዘጋጀት እንደምፈልግ ስጠይቃቸው «ተቀመጥ» አሉኝ። ማኪያቶም
አዘውልኝ ጠጣሁ። «ስማ» አሉኝ፤ «ሁለት የሚያስቸግሩ ነገሮችን ነው የጠየቅከኝ። የመጀመሪያው ጋዜጣ ላሳትም የሚለው ሲሆን፣
ይህ ደግሞ ጭራሽ የማይሆን ሐሳብ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ጋዜጣ ካልሆነ በስተቀር ሰው በግሉ ጋዜጣ ማሳተም
አይችልም።» አሉኝ። እንዴ! ጎህ፣ ፀደይ መጽሄት፣ቁም ነገር የመሳሰሉ አሉ አይደል እንዴ!? ምነው የእኔ ብቻ መከልከሉ ስላቸው
እነሱ መጽሔት መሆናቸውን ነገሩኝ።
ወታደርና ዓላማው
እንዲሁም ፖሊስና እርምጃውስ አሉ አይደል ስላቸው እነሱም የመንግሥት ድርጅት ጋዜጣዎች መሆናቸውን ነገሩኝ። ስለዚህም «በግል
ከሆነ መጽሔት እንጂ ጋዜጣ የለም።» አሉኝ። ቀጥለውም «ሁለተኛው ጥያቄህ ደግሞ በኦሮሚኛ ቋንቋ ማለትህ ነው፤ በዚህ ቋንቋ
ደግሞ የመንግሥት ፖሊሲ የለም።» ሲሉ ተናገሩ። «በአማርኛ፣ በፈረንሳይኛ በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተም መጽሄት
ካልከኝ ግን ዛሬውኑ ታገኛለህ። በኦሮሚኛ ቋንቋ ግን አይቻልም። ጋዜጣም አይቻልምና የማይሆኑ ሁለት ነገሮችን ነው የጠየቅከኝ።»
ሲሉኝ፣ እሺ ምን ላድርግ አልኳቸው «ልምከርህ፤ የምታውቅ ከሆነ ወደ ደርግ ሰዎች ሂድና አስፈቅድ፤ ሊፈቅዱ የሚችሉ እነሱ ብቻ
ናቸው።» አሉኝ።
ከአቶ ሌንጮ ለታና
ከሌሎችም አካላት ጋር ተመካከርንና አንድ በደርግ ውስጥ ኦሮሞ የሆነና ኦሮሞን የሚወድ ሰው እንዳለ አጣራን፤ ልናነጋግረውም
ወስነን በሄድንበት ጊዜ «ለምን ማስታወቂያ ሚኒስቴር አትጠይቁም?» ሲሉ የቀድሞው የደርግ ባለሥልጣን ኮሎኔል ተካ ቱሉ ጠየቁን።
እኛም ጠይቀን እንደነበርና ደርግን ጠይቁ ስለተባለን ወደእነርሱ መምጣታችንን በነገርናቸው ጊዜ እርሳቸውም መጠየቅ የሚገባውን
አካል እንደሚጠይቁልን ነገሩን። እኛም ነገሩን እንዲያፋጥኑልንና ደርግ የሚሰራውን ሥራ እንደ መሬት ላራሹ ላይ የምትሰሩትን
አድሃሪያንን ለማጥፋት የምትጥሩትንና የመሳሰሉ ሥራዎቻችሁን ማወዳደር እንፈልጋለንና ነገሩን ከግብ አድርሱልን አልናቸው።ጋዜጣውም
በየሁለት ሳምንት እንደሚወጣ በመስማማት 20 ሺ ኮፒ አዘጋጅተን አንድ ሺ ኮፒውን ለአንደኛ ክፍለ ጦር ሰጠን።
ለአራተኛ ክፍለ
ጦርም እንዲሁ አንድ ሺህ ኮፒውን፣ለፈጥኖ ደራሽም አንድ ሺ፣ ለአየር ኃይልም ሆነ ለባህር ኃይል አንዳንድ ሺ እንዲሁ ለአርሶ
አደሩና ለሰርቶ አደሩም ከሰጠን በኋላ የቀረንን በአስር ሳንቲም ሒሳብ ሸጥን። የቀረውን ደግሞ የሚገዛን ስናጣ በወቅቱ ሌንጮ
ቀጠን አጠር ያለና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪም ስለሚመስል ኮፊያ ቢጤ አናቱ ላይ ጣል አድርጎ ወደ አብዮት አደባባይ ብቅ በማለት
ይሸጥ ነበር። በድጋሜ አርቲክሎቻችንን ፅፈን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በምንሄድበት ጊዜ «በቃ ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነት
ነገር አይኖርም።» ተባልን። ምክንያት ስንላቸው ደግሞ «በቃ ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው የተፈቀደው።» አሉን። ወደ ላይ ከፍ ብለን
የደርግ ሰዎችን ስንጠይቃቸው «አይ እናንተ ጭራሽ ሕዝብን አሳስታችሁ የኦሮሞን ሕዝብ ከደርግ ጋር ለማጣላት መንግሥት
ያልፈቀደውን ተፈቀደ እያላችሁ ነውና ወንጀለኞች ናችሁ፤ በመሆኑም በወንጀል ትፈለጋላችሁ።» በማለት ጭራሽ እኔኑ ይዘው ወደ
ማዕከላዊ አደረሱኝ።
ለአራትና ለአምስት
ወር ገደማ ጋዜጣውን ከለከሉ። በዚህ መሃል አንድ ነገር ሆነ። እሱም ኮሎኔል አስራት ደስታ የሚባል የደርግ የማስታወቂያና
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የዘመናዊ የሶሻል ፕሮፓጋንዳ ለመማር ከፕሬስ መምሪያ ሰዎችንም ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎችን በመያዝ ወደውጭ
አገር ለመጎብኘት ሄደ። በዚህ ጊዜ በእርሳቸው ቦታ በመተካት ተጠባባቂ የሆኑ ሰው ዘንድ ሄደን ስናነጋግር «ኮሎኔል አስራት
ያልፈታውን እና አይሆንም ያለውን ነገር አልሰራም። ሲመለስ እኔንም ያስረኛል። ግን አንድ መላ የምነግራችሁ ነገር ቢኖር
ከኮሎኔል አስራት ይልቅ ከበድ ወዳለው ሰው እና ኮሎኔል አስራት የሚፈራው ሰው ዘንድ ወስጄ እንዲፈቀድ አደርግላችኋለሁ።» አሉና
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘንድ ወስደው አስፈረሙልን። እናም እርሳቸው «ይፈቀድ» ሲሉ በመፈቀዱ በሪሳ በኮሎኔል መንግሥቱ
ኃይለማርያም (በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት) ፊርማ ተጀመረ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በ1968 ዓ.ም መሆኑ ነው። እርሳቸው
በወቅቱ በየሳምንቱ ይታተም ሲሉም ነው የፈቀዱት።
ይህን ተከትሎ
በብስራተ ወንጌል ሬድዮ ጣቢያ በኦሮሚኛ ቋንቋ ስርጭት ተጀመረ። በመሆኑም የብስራተ ወንጌልና በሪሳ በአንድ ላይ በመስራት
ለአንድ ወር ከግማሽ ያህል ከተማውን ማንቀሳቀስ ጀመርን። በዚህ ጊዜ ወደ ውጭ አገር የሄደው ኮሎኔል አስራት በመምጣቱ
የተደረገውን ሁሉ አየና «ምነው በጎዶሎ ቀን ከአገሬ ባልወጣሁ፤ እግሬ በተቆመጠ» ሲል መናገሩን አልረሳውም። በዚያ ጊዜ እኛ
ከእርሱ የሚበልጡ ኮሎኔል መንግሥቱ ፈርመውልን ነው ወደሥራ መግባት የቻልነው። ነገር ግን ነገሮችን ሊያበላሽብን ተጋ። የብስራተ
ወንጌል የሬድዮ አገልግሎቱን «ለፕሮፓጋንዳ እንፈልገዋለን» በሚል ወረሰ። የእኛም ብዙ ሳይቆይ በ1969 ዓ.ም ወሰዱት።
ይውሰዱት እንጂ
ብዙም መልካም ሊሆንላቸው አልቻለም፤ የኦሮሞ ሕዝብ ስለምን በኦሮሚኛ ቋንቋ ጋዜጣ አይኖረውም? ወዲያ በአስመራ በትግርኛም ሆነ
በጣሊያንኛ የሚታተም ጋዜጣ አለ፤ እንዲሁም በአረብኛ የሚታም አለ። እንዲያ ሆኖ ሳለ ስለምን በኦሮሚኛ የሚታተመው የዚህን ያህል
መቆየት አቃተው? የሚል ጫና ከሕዝቡ መምጣት ጀመረ።
በመጨረሻም አንድ
ማሳያ የሚሆን የኦሮሞ ባህል በማለት በ1977ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዘጋጀን። ከእኛ በፊት ትግራይ አድርጓል። ይህን ስናደርግ
ከሁሉም የኦሮሚያ አካባቢ ሰዎችን በመጋበዝ ነበር። በወቅቱ ከተማዋ በአንድ እግሯ ቆመች ማለት ይቻላል፤ ተቃውሞም ነበር።
ይሁንና በሪሳ እንደገና በፕሬስ ስር ሆኖ እንዲቀጠል አደረጉ፤ በሪሳ ተወረሰ ማለት ይቻላል። እኔም የወር ደመወዝ ተከፋይ
እንድሆን ተደረኩ።
በዚያን ወቅት
ለበሪሳ ብቻ በጀት 500 ሺ ብር በመበጀቱ ትልቅ ብር ነበረ። በተጨማሪም አንድ ተሽከርካሪም ተገዛልን። በወቅቱ የተቀጠሩት
ሪፖርተሮች ደግሞ ጫልቺሳ ጪብሳ፣ ዋቅጋሪ ጉንጆ፣ መሀመድ ሀሰን፣ ቡሎ ሲባ፣ ኢብራሂም ሐጂ እና ሌሎችም ተቀጥረው ነበር። አራሚ
ተብለው የተቀጠሩም ነበሩ። ሌሎች እንደ እነ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ ዓይነቶች ደግሞ ይሰሩ የነበረው በፍሪላንስነት ነበር።
ኢብራሂም ሐጂ ያለአንዳች ሳንቲም ለሁለት ዓመት ሰራ። እኔም በወቅቱ ደመወዜን የሚከፍለኝ የእድገት በህብረት ሲሆን፣ የምሰራው
ደግሞ ለበሪሳ ነበር።›› በማለት ተርከው ነበር፡፡
የበሪሳ ይዘት
ዶክተር መሀዲ፣
በኋላ በጋዜጣ ሥራ የመቀጠል ሐሳብ እንደሌላቸው ለራሳቸው አረጋገጡ። ይሁንና በስራቸው ያሉትን ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው አስተዋሉ።
ኃላፊዎቹም ልለቅ ነው ባሏቸው ጊዜ ሰዎችን እንዲያሰልጥኑ ጥያቄ በቀረበላቸው ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን ለማሳየት ቆዩ። ያኔ
ዶክተር መሀዲ ትልቁ ስጋታቸው እርሳቸው በመሄዳቸው ጋዜጣዋ ሙሉ
በሙሉ እንዳትሞት ነበር፡፡ በመሆኑም የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ፤
ጋዜጠኞቹም በራሳቸው መተማመን እንዲኖራቸው ወደ ሦስት ወር ያህል አሰለጠኗቸው። በወቅቱ ጋዜጣዋ ለህትመት ትበቃ የነበረው
በዕለተ ሐሙስ ነበር። እንዳጋጣሚ ሆኖ ደግሞ በዚያን ጊዜ የኢትዮ ሱማሊያ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ወቅት ነበር።በመሆኑም ሱማሊያ
በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ፕሮፓጋንዳዋን አጠናክራ ስለነበር በምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለውን ሚዲያ በማሰልጠን የፕሮፓጋንዳ ሥራ እንዲሰሩ
ተነገራቸው፡፡
የጋዜጣው መጠሪያ በሪሳ የተባለበት ምክንያት
በሪሳ የተባለበት ምክንያት ልክ የጨለማው ጊዜ የሚያበቃበትና የብርሃን ጊዜ
የሚጠበቅበት ሆኖ፤ ነገር ግን ብርሃን ነው እንዳይባል ፀሐይ ያልፈነጠቀችበት፤ ጨለማ ነው እንዳይባል ደግሞ ሊነጋ ያቅላላበት
በመሆኑ ግን ደግሞ ጨለማውም ገፎ የብርሃን ውጋገን በሚታይበት መካከል በመሆኑ ነው በሪሳ የመባሏ ምስጢር።
አባ በሪሳ ሌላው
የዶክተር መሀዲ መጠሪያ
ዶክተር መሃዲ፡-‹‹…..
ከሚሰሩት መካከል እኔ አንዱ ስሆን፣ ኢብራሂም ሐጂ፣ ለሜሳ ቦሩ፣ እምሩ አንጎሴ ነን። በወቅቱ እስከለቀቅኩበት ጊዜ ድረስ
የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ እኔ ነኝ።አባ በሪሳ እና አባ ዲክሽነሪ የሚባለው መጠሪያ የወጣልኝ ውጭ አገር ከሚኖሩ ሰዎች ነው። እኔም
አሜን ብዬ ተቀብዬዋለሁ።
በወቅቱ ጋዜጣዋ
ፖለቲካዊ የሆኑ ይዘቶችንም ይዛ ትወጣ ነበር። በወቅቱ የበሪሳ ዋና አዘጋጅ ልሁን እንጂ ኦነግ ነበርኩ። ምክንያቱም እኔ በአገሬ
የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲቆጠርና ሲገፋ ማየት ስለማልፈልግ እታገል ነበር።
በሪሳን ከለቀቁ
በኋላ
ዶክተር መሃዲ፡-‹‹……
በኦነግ ሥራ ተመድቤ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት እዚያ ቢሮ ከፈትኩ። አካሄዴም በሽሽት አይደለም። በዚያም ዋና ሥራ የነበረው
ሰዎቻችንን ማደራጀትና ማጠናከር ሲሆን፣ አንዳንድ እንደ መድኃኒትና መሰል ድጋፎችን ለኦሮሚያ የማስገኘት እንቅስቃሴም እናደርግ
ነበር። ለውጭ አገር መንግሥታት የኦሮሞ ወጣትና ሕዝብ ችግር ምን እንደሆነ እና ኦሮሞ ለምን እንደሚታገል እንዲሁም ኦነግ ለምን
እንደተደራጀ ስናሳውቅ ቆየን።
እኔ ከወጣሁ በኋላ
በሪሳ የኦሮሞን ድምፅ ሲያሰማና ትግል ሲያካሂድ ቆየ። የኦሮሚያንም ፖለቲካዊ ትግል ማጠናከር ቀጠለ። ከዚህም በመነሳት «ይህ
የኦነግ ጋዜጣ ሆነ፤ ጠባብ ነው» በሚል ትኩረት ስላደረጉበት እነ ሌንጮ ሥራውን ለቀቁ። ሌሎች የለቀቁም በርካታ ናቸው።
የተገደለም ነበር። በወቅቱ እነዚያ ጋዜጠኞች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲ ነው ጋዜጣውን እንዲቀላቀሉ
ያደረኩት።
እኔ በወቅቱ ወደ
ውጭ አገር ስሄድ በርካታ መጽሐፍትን ትቼ ነበር። እነዚያም መጽሐፍት እኖርበት ከነበሩ ሦስት የተለያዩ ቤቶች መካከል አንዱ
በሆነው የአሁኑ ውል እና ማስረጃ ውስጥ ስለነበር ለአቶ ሌንጮ የቤቴን ቁልፍ በመስጠት መጽሐፍቱንና አልባሳቱን ቀስ ቀስ እያለ
እንዲያወጣ ነግሬው ነበር አገሬን ለቅቄ የወጣሁት። ይሁንና ከቆይታ በኋላ መጽሐፍቱን ስጠይቀው «እንኳን የአንተን ዕቃ ላወጣ
ቀርቶ ነፍሴንም በመከራ ነው ያወጣኋት።» ሲል መለሰልኝ። ምክንያቱስ ምንነበር ስለው የደህንነት ሰዎች መጥተው መጽሐፍቱን
እንደወሰዱት ነገረኝ። በእርግጥ መጽሐፍቱ ይኑሩ ይቃጠሉ የማውቀው ነገር የለም፤ ቢመለስልኝ ግን በጣም ዕድለኛ ነበርኩ።
ዶክተር መሃዲ፡-‹‹…..
በወቅቱ ፕሬስን ጠላሁ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቴ በትውልድ ኤርትራዊ የሆነ ገዳሙ አብርሃ የሚባል ሰው በጣም ያስቸግረን ነበር።
ወደ እርሱ ቀርበን ሥራው በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰራ እንደሆነና ለኦሮሞ ሕዝብ አንድነት የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ከሆነ ጋዜጣዋን
እንዲያግዟት በምንጠይቅበት ጊዜ አንዲት ሳንቲም እንኳ ሊሰጡን አልፈቀዱም። በወቅቱ የተለያዩ ሰዎች ግን በሪሳን ደግፈዋታል።
ከእነዚህም መካከል ብርሃኑ ዘሪሁን አስር ብር ሰጠን፤ ተፈሪ በንቲም 20 ብር እንደሰጠን ሰማን። ሌሎችም የየበኩላቸውን
አድርገው እንደነበር ተረዳን።
እናም ፕሬስን
የመጥላቴ ምስጢር በመንግሥት በኩል «ይህን አድርግ ያንን አታድርግ የሚሉ ትዕዛዞች እና የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች በረከቱ። የተለያዩ
አዋጆችንና ማስታወቂያዎችንም ሲያበዙብኝ እኔም ለአቶ ገዳሙ አንድ ገፅ ማስታወቂያ መስራት ከፈለክ 750 ብር ነው፤ ስለው
«እንዴ በመንግሥት አዋጅ የምን ማስታወቂያ መክፈል ነው» አለኝ። እኔም አክዬ እኛ እኮ ከሕዝቡ አንዳንድ ብር ለቅመን ነው
ጋዜጣዋን በማሳተም ላይ ያለነው አልኩት። ለሕዝቡ ይጠቅማል የሚለውን አይተን ነው የምናወጣው፤ አዋጅም ቢሆን ደግሞ ጠቃሚነቱን
አይተን አሳጥረን ነው የምናወጣው። የምትፈለልጉ ከሆነ ደግሞ ሌላ በኦሮሚኛ ቋንቋ ማሳተም ትችላላችሁ ስንላቸው ቆየን።
ሰውዬው «የበሪሳ
ጋዜጣ የመንግሥት ስለሆነ የምትተዳደረው በእኛ መመሪያ ነው።» ያሉኝ ገና በጅምሩ ነበር። እውነት ለመናገር ያኔ ነበር በጣም
የጠላሁት፤ ብችል ኖሮ የዕለቱ ዕለት ነበር መልቀቂያ አስገብቼ እወጣ የነበረው። ግን አልቻልኩም። ወዲያው ትቼ ብሄድ ደግሞ
የጋዜጣዋ ሪፖርተሮች ገና አዲስ የተቀጠሩ ናቸው። በትኛቸው መሄድ አልፈለኩም። ላስተምራቸውና ላሰለጥናቸው በማሰብ ሦስት ያህል
ወራት ልቆይ ግድ ሆነብኝ። እንጂ እንደ እኔ ቢሆን በሪሳ ተወርሷል የተባለ ዕለት ነበር ቤቱን ለቅቄ መውጣት የፈለኩት።››
ብለው ነበር ዶክተር፡፡
በሪሳ
ጋዜጣ መረጃ የሚያገኘው በምን ዓይነት መንገድ ነበር?
ዶክተር መሃዲ፡-
ኦሮሞዎች ሁሉ ሪፖርተሮቻችን ነበሩ ማለት ይቻላል። በወቅቱ ይመጡልን የነበሩ ደብዳቤዎች በአሁኑ ሰዓት በበሪሳ ዝግጅት ክፍል
ውስጥ ቢፈለጉ የሚጠፉ አይመስለኝም። እነዚህን በአስተያየት መልክ የሚመጡ ደብዳቤዎችን በምናስተውልበት ወቅት ሕዝቡ ሁሉ
ሪፖርተራችን እንደሆነ እምነት ያድርብናል። እኛ በወቅቱ አንተኛው ሪፖርተር ጅማ፣ ቦረና፤ አንተኛው ደግሞ ነቀምቴ ሂድ ብለን
የምንልክበት ሁኔታ የለም። በሪሳን መንግሥት ከወሰደው በኋላ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረው 500 ሺ ብር በጀት ስላለው ሪፖርተሩ
አጀንዳ ቀርፆ አበል ተከፍሎት ወደፈለገበት በወጣው ደንብ መሠረት የሚሰራውን ነገር ብቻ በማረጋገጥ ይላካል። በመሆኑም መንግሥት
ጋዜጣውን ከወሰደው በኋላ የገንዘብ ችግር አልነበረም።
ቅድመ ምርመራ ይደረግበት ነበር?
ዶክተር መሃዲ፡-
የአርትዖት ዓይነት ሥራ ነው፤ የአርትኦት ሥራውን የሚሰራው ሰው ደግሞ በአብዛኛው ሥራው በአማርኛ ቋንቋ ለሚታተመው ጋዜጣ ነው።
እግረ መንገዱን ግን ኦሮሚኛ ቋንቋ ስለሚችል በሪሳንም ያየዋል። እሱም ካየው በኋላ ይፈረምበትና ይታተማል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
የህትመት ሚዲያዎች ያሳተሟቸው ሥራዎች ይተነተን ነበርና የበሪሳ ጋዜጣ በዛሬው እትሙ ይህን ነገር ይዞ ወጥቷል ይባልና
ይነገራል። ይህም የሚባለው ደግሞ ለአቅራቢዎቹ ሰዎች ኦሮሚኛውን ወደ አማርኛ ተርጉመውላቸው ነው። በእርግጥ እንደዚያም ሆኖ
ውስጠ ወይራ በሆነ መንገድ ነው ብዙ መልዕክቶችን የምናስተላልፈው። በወቅቱ የአርትዖት ሥራውን ይሰራ የነበረው ሰው እንዳልኩት
ከማንበቡ ይልቅ መስማቱ ላይ ስለሆነ ግንዛቤ ያለው በቴሌቪዥንና በሬድዮ ጉዳዩን ሲሰማ መሸወዱ ያበሳጨው ነበር።
ስለዚህም ዓላማችንን
በይበልጥ እንድናራምድ ሁለት ነገሮች አግዘውናል ማለት ይቻል ነበር፤ አንዱ ሰውዬው ቋንቋውን በአግባቡ አለማወቁ ሲሆን፣ ሌላው
ደግሞ በሳብኛ ፊደል ኦሮሚኛ ቋንቋ መታተሙ አሻሚ የሆኑ ነገሮች መኖራቸው ነበር። በዚህም ውስጠ ወይራ የሆነ ሐሳብ እንዲተላለፍ
አግዞናል የሚል እምነት አለኝ።
የነበረው ጫና
ዶክተር መሀዲ፡-፣‹‹
ሁልጊዜ ጥቃት ይደርስብኝ ነበር። ሁኔታው ገደል ጠርዝ ላይ እንደሚሄድ ዓይነት ሰው ስጋት የሞላበት ነበር፤ የነፋስ ሽውታ
ሊገፋው እንደሚችል ዓይነት አካሄድ የነበረው ማለት ነው። በእርግጥ ልጅነት እንዴት ደግ ነገር መሰላችሁ። አሁን በዚህ ዕድሜዬ
ቢሆን እፈራለሁ። በወቅቱ ግን የቱንም ያህል ጫና ቢያሳድሩብኝ ያስሩኝ ይሆን? ሥራ አጣ ይሆን? ይገድሉኝ ይሆን? የሚል ነገር
እምብዛም አያሳስበኝም።
በወቅቱ ወደ ሦስት
ያህል ቤት የነበረኝ ሲሆን፣ በሳምንት ውስጥ በሦስቱ ቤት እያፈራረቅሁ አርፋለሁ። አንዳንዴም ደግሞ ነገር የሚከፋ መስሎ
ከተሰማኝ ሆቴሎች ስለማድር ገንዘቤም ያልቃል። ከምንም በላይ ግን በኔ ላይ ከደረሰው ጫና ይልቅ በእናቴ ላይ የደረሰው ነገር
ሁሌም ቢሆን ያበሳጨኛል፤ ያናድደኛልም። አንዴ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ እናቴን በር አስከፍተዋት «ልጅሽ የት ነው
ያለው?» ሲሉ ይጠይቋታል። እርሷም በዚያ በውድቅት ተነስታ «ልጄ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ልማር ነው ብሎ ከቤት ከወጣ አስር ዓመት
ሆኖታል። ሥራም የያዘ ከመሆኑም በላይ ከዚህ በኋላ ትልቅ ሰው በመሆኑ በእኔ ቁጥጥር ስር አይደለም። ራሱን ችሏል። እንደዛም
ብትላቸው ወደፖሊስ ጣቢያ ደርሰሽ ምርመራ ይደረጋል ብለው ይዟት ሄዱ።
በእርግጥም እናቴ
በወቅቱ ምን እንደምሰራ የምታወቀው አንዳች ነገር አልነበረም። እኔ በአፍላነት ዕድሜዬ ነው ከቤት የወጣሁት። በወቅቱ የ17
ዓመት ታዳጊ ወጣት ነበርኩ። ቤቱን ትቼ ስወጣ አላማከርኳትም። ምንም የማታውቀዋን እናቴን ግን በዚያ ውድቅት ሌሊት ፖሊስ ጣቢያ
ወስደዋት ስለልጅሽ ካልነግርሽን ብለዋት የደበደቧትን መቼም ቢሆን ከውስጤ የማይወጣ የእግር ውስጥ እሳት ሆኖ እስከዛሬ
ይለበልበኛል።
የመረጃ ምንጭ
ዶክተር መሃዲ፡-
እኛ መረጃ ማስተላለፍ የምንፈልገው የሕዝብን ፍላጎት እንጂ የመንግሥትን አልነበረም። በዚህም የተነሳ የሕዝብን ጉዳይ ነው
ለመንግሥት የምናስተላልፈው። በዚህም ምክንያት ለእኛ መንግሥት ማለት የመረጃ ኢላማችን እንጂ የመረጃ ምንጫችን አልነበረም።
እነሱ ይሰሩ የነበረውን እናውቅ ስለነበር እነሱን የመረጃ ምንጭ አናደርግም። እኛ በወቅቱ የምንሰራው ሕዝቡ መጨቆኑን፣ ንብረቱ
መቀማቱ፣ ቋንቋውን መናገር አለመቻሉን፣ ባህሉ መጥፋቱን ማሳወቅ፣ ሕዝቡ በኦሮሚኛ ቋንቋ መማር አለበት የሚል ሲሆን፣ ሕዝባችን
ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት የሚለውን ነበር የምንዘግበው።
እነሱም ደግሞ
በወቅቱ ሲመልሱ የነበረው በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት እያንዳንዱ ብሔር በራሱ ቋንቋ እንዲማር ጥናት እያስደረገ መሆኑን
ይናገራል። ይህ እንግዲህ ጥናት እያደረግን ነው በማለት ሁለትና ሦስት ዓመት ያህል እንዲያልፍ የማድረግ ሐሳብ ያለው በመሆኑ
ወደትምህርት ሚኒስቴር በመሄድ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ክፍል የሚያስተምሩበትን መጽሐፍ ጠይቀን ወሰድን። እኔም ኢብራሂምም ሆነ
ጫልቺሳ መጽሐፉን ተቀባብለን ወደ ኦሮሚኛ ተረጎምን።
በሪሳ ጋዜጣ ዛሬ
ዶክተር መሃዲ ከ2 አመት በፊት ማለትም ህይወታቸው ሳያልፍ ይህ
ቃለ-ምልልስ በተደረገላቸው ጊዜ በሪሳ 42 አመት ከሞላት በኋላ መኖሯ በራሱ አስገረማቸው- ፣‹‹የሚሰማኝ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት
ነው። ደስታም ሀዘንም ይሰማኛል። የሚሰማኝ ደስታ እኔ ትቼያት ብሄድም የተጣለው መሠረት መልካም ስለነበር ከ42 ዓመት በኋላ
ተመልሼ ስመጣ መኖሯን በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ። ነገር ግን ደግሞ የሚያሳዝነኝ ነገር ቢኖር የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ከፍ ያለ ሆኖ
ሳለ 45 እና 50 ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝብ አንዲት ጋዜጣ ብቻ መሆኗ በጣም ያስከፋኝል። ሲሆን፣ ሲሆን ከአራት እስከ አስር
የሚጠጋ ጋዜጣ ሊኖር ይገባ ነበር። ሌላው ደግሞ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ (በእርግጥ በሳምንት ሦስቴ
እናደርጋለን እየተባለ መሆኑን ሰምቻሁ) በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ መውጣቷ ቅሬታን ይፈጥርብኛል።›› ብለው ነበር ዶክተር
መሀዲ፡፡
የኮፒ
ብዛትስ
፡- ከ44 ዓመት
በፊት በሪሳ ወደ 20 ሺ ህትመት ነበር ሲታም የቆየው። ያኔ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 25 ሚሊዮን አካባቢ ነበር። ዛሬ ደግሞ ወደ 100 እና 110 ሚሊዮን አካባቢ ይጠጋል ተብሎ ይታሰባል።
ስለዚህም እንዴት ነው የበሪሳ ጋዜጣ ኮፒ በቁጥር ማደግ ሲገባው ቁልቁል የመሄዱ ምስጢር ሲሉ ዶክተር መሀዲ ይጠይቃሉ፡፡
ዶክተር መሀዲ ውጭ አገር ከወጡ በኋላ ወደ አስር ያህል መጽሐፍትን አሳትመዋል ፡፡ዲክሽነሪም ጨምሮ ማለት
ነው። በብዙ መንገድ የኦሮምኛን ቋንቋ የቴክኖሎጂ ቋንቋ የማድረግ ፍላጎትም ነበራቸው። እኤአ 1998 አካባቢ ‹ቁቤ ኦሮሞ
ሶፍትዌር› የሚባለውን በማዘጋጀት በውጭ አገርም ሆነ በአገር ቤት አድርሰዋል። ከእርሱ ጋር የሚሄድ ማኑዋልም እንዲሁ አበርክዋል።
ለረጅም አመት በአሜሪካን አገር በጡረታ ላይ ይገኙ ነበር። ምንም እንኳን ጡረታ ብወጡም በሙሉ ጊዜ ሳይሆን በትርፍ ጊዜ ደግሞ ያስተምራሉ፡፡
የመዝጊያ ሀሳብ ፤
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ዶክተር መሀዲ ሀሚድ በተለይ ስለ በሪሳ ጋዜጣ አጀማመር ሲነሳ በቀዳሚነት ስማቸው ጎልቶ ሊወጣ የሚገባ ሰው ናቸው፡፡ በሪሳን ለማሳተም ወገባቸውን ታጥቀው በተነሱበት ጊዜ በንጉሱ ዘመን የተቀበላቸው የመንግስት ሃላፊ አልነበረም፡፡ በአፋን ኦሮም ጋዜጣ ያስፈልጋል ብለው በግል ለማሳተም በፈለጉበት ጊዜ የገጠማቸው ፈተና ከባድ ነበር፡፡ ግን በቀላሉ ሳይረቱ ከዛሬ 46 አመት በፊት በ1968 በሪሳ ጋዜጣ በመንግስት ሀይለማሪያም ይሁኝታ የህትመት ብርሀን አየች፡፡ እንዲህ ነው ለሚድያ ስራ አሻራ ማኖር ማለት፡፡ ዶክተር መሀዲ ህልማቸውን ያሳኩ በመሆኑ ከ42 አመት በኋላ በሪሳን ሲያዩ መደነቃቸው አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ አሻራ ለማኖር የማይደክሙ ልጆችን ወልዳለች፡፡ ለፍሬም እያበቃች ነው፡፡ ዶክተር መሀዲ ስለ ኢትዮጵያ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጠኝነት ሲነሳ ስማቸው በወርቃማ ስፍራ ሊቀመጥ የሚገባ ሰው ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ለቋንቋው ማደግ በተለይም የአፈን ኦሮሞ ባህል ሰው ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ የተቻላቸውን ያደረጉ ናቸው፡፡ የጻፏቸው መጽሀፎች ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዶክተር መሀዲ አይነት ሰዎችን በትልቁ ማክበር አለባት፡፡ ይህች ሀገር ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት እንደመሆኗ ለቋንቁዋ እድገት የሰሩ ታሪክ የሚከትበው ስራ ስተዋልና ስማቸው ከመቃብር በላይ ሊውል ይገባል፡፡ መቼም ታሪክ የሚሰነደው አንድ ቁምነገር ሲከወን ነውና እነሆ አንድ ታላቅ ነገር ለሀገር ያበረከቱ ሰው አስተዋወቅን፡፡ / ይህ ግለ-ታሪክ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን መረጃ እና ምስል በመስጠት እገዛ ያደረገው ደግሞ የበሪሳ ጋዜጣ የአሁኑ ዋና አዘጋጅ ቸርነት ሁንዲሳ ነው፡፡ ለዚህም የከበረ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ይህ አጭር ግለታሪክ በየጊዜው አስፈላጊው ማሻሻያ እና እርማት የሚደረግለት ሲሆን ተጨማሪ መረጃ ያላችሁም ሰዎች ብትተባበሩን ደስታውን አንችለውም፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ የካቲት 19 2014 ከሌሊቱ 6ሰአት ከ44 በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽና የግለ-ታሪክ ብሎግ ላይ ወጣ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ