ጋዜጠኛ

    የሬዲዮ ድራማ ተዋናይ

       ኤዲተር

የውሎ አዳሯ ንግስት አስካለ ተስፋዬ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዷ የውሎ አዳሯ ንግስት አስካለ ተስፋዮ ናት፡፡ ታሪኩን ባንቺአየሁ አሰፋ አጠናክራዋለች፡፡

ከ22 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም በማዘጋጀት እና በማቅረብ አገልግላለች። እጅጉን ጠንካራ እና ብርቱ ሴት ነች። ይህች ፍልቅልቅ  ፤ መንፈሰ ጠንካራ ፤ ጀግና አገልጋይ ሴት  ትውልዷ  በኢትዮጵያ ደቡብምዕራብ ክፍል ሲሆን ከአድስ አበባ በአማካኝ 353 ኪሎሜትር እርቀት ላይ በምትገኘዋ ታላቋ የአባጅፋር መናገሻ  ጅማ ከተማ ቦሳ ቀበሌ 04  ነበር ተወልዳ ያደገችው ።

ቦሳ ቀበሌ 04 ለእሷ ልዩ ትዝታ እንዳላት ትናገራለች ። ምንም እንኳን ከቦሳ የፍራፍሬ ዛፎች ላይ ተንጠላጥላ ፍሬዎችን ባትለቅምና ወድቃ ተጫጭራ በሰውነቷ ላይ ጠባሳ ባታስቀርም ስለጅማ ሲነሳ በየጓሮው በየስፍራው ስላለው የዘይቱና ፍሬ፣ አናናስ ፣ ማንጎና ቡና ማውጋቷ አይቀርም ። በተጨማሪም የቦሳ ቀበሌ 04 በታዳጊዎች ኪነት ይታወቃል። የታዳጊ ኪነት ቡድኑ መዝሙር የሆነውና  በመምህር ታረቀኝ ወንድሙ ደራሲነት የቀረበው " የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና " የጋዜጠኛዋ የያኔ የልጅነት ትዝታ ነው። ፍራፍሬዎቹ ሰውነቷን ድንቡሽቡሽ ሲያደርጓት ኪነቱ ደግሞ ልክ እንደቁራኛ ነፍሷን ማርኮ ተጋብቷት አድጓል ።

እንግዲህ ጅማ ከቡና ፣ የአትክልትና ፍራፍሬዎቿ በተጨማሪ እንደጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ (ውሎ አዳር) ያሉ ፍሬያማ ልጆችንም ታበቅላለች።  አስካለ ትውልዷ እና እድገቷ በጅማ ሲሆን ትምህርቷንም  ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ በዚያው ተከታትላለች።  ከዚያም መነሻውን ቅዝቃዜ ባደረገ የሳይነስ ህመም ምክንያት ተወልዳ ያደገችበትን ቀበሌና ከተማ የልጅነት ትዝታዎቿን በሙሉ ወደኋላ በመተው ወደመዲናችን አድስ አበባ ቤተሰብ ጋር ለህክምና መጣች ። የአዲስ አበባን ውኃ የተጎነጨ ሁሉ መውጫው ጠባብ በመሆኑ ይህ እጣ ፋንታ ለሷም ደረሳትና በከተማዋ እስከወደፊት ከተመች ።

 

 

 የስድስተኛ ክፍል ትምህርቷን በጆንኤፍ ኬኔዲ ቁጥር አንድ ትምህርትቤት ስትማር ሰባትና ስምንትን ደግሞ በኡራኤል መለስተኛ ትምህርትቤት የቀጠለች ሲሆን  የዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል  ትምህርቷን ደግሞ በዳግማዊ ሚኒሊክ መከታተል ያዛች። በዚህን ወቅት የአስካለን ወደፊት የሚያመለከት አንድ ክስተት ተፈጠረ ።  መንገዷ በስስ በስሱ መጠረግ ጀመረ ። የቀድሞው የባህል ሚስቴር ባወጣው የጹሑፍ ውድድር ላይ የራሷን ርዕስ መርጣ ተሳተፈች ።

 ርዕሱም 'ዘማቹ አባቴ'  ይሰኝ ነበር። ዘማቹ አባቴ የተሰኘውን ግጥሟን  ጽፋ ስትጨርስ ለማስገባት በመፍራቷ የእጀራ አባቷን እንዲያስገባላት ጠይቃ ተሳካላት ።

 

ይሁን እንጂ ውድድሩን ያወጣው አካል ስለግጥሟ ምንም ሳይል በመቆየቱ አስካለ ዘንግታው ትምህርቷ ላይ ትኩረት አድርጋ ሳለ በመሐል አልፈሻል የሚል የምስራችን ይዞላት ከተፍ አለ። ከዚያም  ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ትያትር ቤት ( በታላቁ  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ) ተገኝታ ግጥሟን በመድኩ ላይ ቆማ ለታዳሚ በማቅረብ ፊቷን በሰው ዐይን ማስመታት ቻለች ። የሰው ዐይን የሚጥልና የሚያነሳ በመሆኑ እሷ ከሚቆሙት ተርታ መሰለፏን ያረጋገጠችበትም ሆነ።

 

በዚህ ውድድር አሸናፊነቷ ምክንያት ወደኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬት ( በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጂት )  ዘወትር አርብ ሚኒሊክ ትምህርትቤት በሚመጣላቸው  መኪና ተሰብስበው በመሄድ በጋሽ ሰለሞን ገ/ስላሴ አማካኝነት የተጋጀ ስክሪፕት በማጥናት በልጆች ዓለም ፕሮግራም ላይ ስራዋን ጀመረች ። የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ነውና ባላት ልዩ ቅልጥፍና እና ተሰሚ ድምፅ ምክንያት በጋሽ ሰለሞን ተመርጣ የልጆች ፕሮግራም አስተዋዋቂ ለመሆን በቃች ። ልጆች ያለመሰልቸት ዝግጅቱ እስኪያልቅ ድረስ ቁጭ ብለው ጣፋጭ የልጅነት አንደበቷን በልጆች አለም ሬድዮ እንዲያደምጡ ሆነ።

ቀስ በቀስ ከልጆች ፕሮግራም ወደወጣቶች ፕሮግራም ተሸጋግራ ከዕድሜዋ እና ከአመለካከቷ ብስለት እኩል የምታቀርባቸው ፕሮግራሞች ይዘት ዕድገትን እያሳዩ መጡ።  ሬድዮ ላይ ለረጅም ጊዜያት የሰራች ቢሆንም በፕሮግራም ደረጃ ግን የወጣቶች ፕሮግራም ላይ ዘለግ ያለ ቆይታን አድርጋለች ።

አስኩ ( በወዳጆቿ አጠራር ) አስኩዬ  በትምህርት ላይ ቆይታዋ ከአድስአበባ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት ሙያ ድፕሎማ ስትይዝ ከባህዳር ዪኒቨርሲቲ ደግሞ በቋንቋ እና ስነጽሑፍ የጀመሪያ ድግሪዋን አግኝታለች ። ልበቀናዋ ፣ ታታሪዋ  ፣ ፍልቅልቋ (ባለቃጭል ቀጭን ድምፅ ) ይሏታል አድናቂዎቿ  ከትውልድ ቦታዋ ጀምሮ ጉዞዋን ለተመለከተው እጅግ ጥንካሬን የሚጠይቅ ነው። ብዙ መገላበጥ ጎኗን ሳያሳሳው ጉልበቷ ውኃ ሳይቋጥር ሀሞቷን ክትት አድርጋ የተጓዘች ብርቱ ሴት ነች።

ይህች ብርቱ ታዲያ የመገናኛ ብዙሃን ሬድዮን በበርካታ ፕሮግራሞች የአቀራረብ ለዛ እና ዝግጅት ከአድማጭ እንዲደርስ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ። የሙዚቃ ሰዎችና ስራዎቻቸው ላይ " እኛም አለን ሙዚቃ ስሜት የሚያነቃ " በሚል አስጀምራ ንቅት ባለመንፈስ የአድማጭን ልብና ጆሮ ከፕሮግራሙጋ ማጣመር ሬድዮን ማስናፈቅ የቻለች ድንቅ ሴት ጋዜጠኛ  ናት። የወጣቶች የሬድዮ ፕሮግራምን በማዘጋጀት እና በማቅረብ ከባልደረቦቿ  አስቻለው ጌታቸው እና ብርሃኑ ገ/ማሪያም ጋር ሰርታለች። በተጨመሪም የህብር ኢትዮጵያ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ ሆና አገልግላለች ። አስካለ እጅግ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ በሆነው አውደገጠር የሬድዮ ዝግጅት ላይም የተዘጋጁ ደብዳቤዎችን በማንበብ ሰርታለች ። በሬድዮ ቆይታዋ በርካታ ወዳጆችን ለማፍራትም የቻለች ሲሆን ከህብር ኢትዮጵያ ዝግጅቷ ጥዑም የዕድሜ ልክ ትዝታን ስለማትረፏ ትናገራለች ። ከአድማጮች ለፕሮግራሙ ከየሚላኩ ግጥምና ሃሳቦች ግርጌ የአስካለ ስም ቁልቁል በተናጠል ሰፍሮ ይመጣም ነበር። ይህም ማለት በዚህ መልኩ መሆኑ ነው።

 

አ                    

 

 

ከእነዚህ ባሻገር ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ሬድዮ ላይ በቆየችባቸው ጊዜያት እጅግ በርካታ የሬዲዮ ድራማዎችን የተወነች ሲሆን በጋዜጠኛ መአዛ ብሩ ደራሲነት ለሬዲዮ የተዘጋጁትን ዲራማዎች ለበርካቶቹ ልጅ በመሆን ሰርታለች ። ለምሳሌ ያህል ሰኞ ጠዋት በኢትዮጵያ ሬዲዮ በሚተላለፈው የዶጮ ቤተሰብ ላይ ልጅ በመሆን ለረጂም ጊዜ የተወነች ሲሆን ዘወትር እሁድ ጠዋት በሚተላለፈው የክንደ እንጉርጉሮ ደግሞ ከጥላሁን ጉግሣ ጋር ልጅ በመሆን ሰርታለች ። ድራማዎችን በምተውንበት ጊዜ ልጅ ያልሆንኩት የለም ትላለች ። ይህ ደግሞ የድርብ ተሰጥኦ ባለቤት ያደርጋታል ።

የኋላ ኋላ ሬድዮና ቴሌቪዥን ሲቀላቀሉ ህብር ኢትዮጵያ እና የሙዚቃ ሰዎች እና ስራዎቻቸው በቴሌቪዥን በራሷ በአስካለ ተሰርተዋል ። ምናልባትም ቴሌቪዥን ላላቸው  በድምፅ ብቻ ለሚያውቋት አስኩዬ ፣ አስኩ ፣ አስኩቲ እያሉ ለሚያንቆለጷጵሷት ፤ አድናቆትን ለሚቸሯት ፤ ለአመለሸጋዋ ብርቱዋ ሴት ወዳጆች ጥሩ አጋጣሚ እና ታላቅ የምስራች መሆኑ አልቀረም ። ፊት ለፊት ቁጭ ብለው  በትንቯ የቲቪ መስኮት ስር ከጆሮም ባሻገር ከሙዚቃው አልፈው ሙዚቀኛውን እና የሙዚቃ መሳሪውን የኢትዮጵያ ሀገራችንን መልክ እንዲሁም ባህል ለመቃኘት እንዲቻል የጀርባ አጥንት ሆና የምታስኬደው የመዝናኛ ጋዜጠኛዋ አስካለ ተስፋዬ  በየቤቱ ከጆሮም ወዲያ በዐይን ለመግባት ቻለች።

 

የሀገራችንን ሁለንተናዊ ገፅታ በዝግጅቶቿ ላይ ለማሳየት በርካታ ጥረቶችን አድርጋለች ። ታትራለች ። ባህልና ወጎቻችን እያዝናኑ እንዲያስተምሩ ለማድረግ የክልል ምክርቤት አባላት ለእረፍት ወደመጡበት ሲመለሱ የያኔዎቹን በቅርብ የማይገኙ ሙዚቃዎቻቸውን  በካሴት እንዲያመጡላት እና  አየር ላይ እንዲውል ብሎም የተሻለ የማህበረሰብ  ትስስር እንዲፈጠር ለማድረግ ከባልደረቦቿ ጋር በመሆን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

ይህም ታዲያ ውሎ አድሮ ምናልባት የስበት ህግ ነው ሊባል በሚችል መልኩ በ2011  ይህም የዛሬ አራት አመት ገደማ እጅግ ተወዳጁ የውሎ አዳር የቴሌቪዥን  መዝናኛ ዝግጅት በመዝናኛ የዝግጂት ክፍሉ ታቅዶ  ተዘጋጅቶ ለአስካለ ተስፋዬ ይሰጣታል ። እሷም በአመቱ የመጀመሪያ ወቆቶች አካባቢ ፕሮግራሙን በይፋ ሰርታ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን መስኮት በሰፊው መጣች ። አንጋፋዋ ፣ ትሁቷ ፣ ቀልጣፋዋ የመዝናኛ ዝግጅት ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ በዚህም ተወዳጅነትን አገኘች ።

ታዲያ ለጉዞ ሄዶ ከቀዬ መቆም ሳይሆን ከጓዳ ገብቶ መታተርን ታውቅበታለች ። "የሴት እንግዳ የለውም " የሚለውን ብሂል ስጋ አልብሰን ነፍስ ስንዘራበት ምስሉ ጋዜጠኛ አስካለ ተስዬን ነው። በሀገራችን ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ተጉዛ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣባትን ተጽዕኖ በመቻል የመንገዱ መራቅና አለመመቼት ከጉዞዋ ሳይገታት ፀጉረ-ልውጥነት ሳይሰማት የአመጋገብ ስርዓትና ምግቡ የሚፈጥርባት ሁኔታ ሳይፈትናት ህመሟን ሳታዳምጥ ወገቧን ሸብ አድርጋ ከእናቶች እኩል እንደእናት ጎንበስ ቀና ስትል ዐጃኢብ ታሰኛለች ።

 

 

ከተመልካቾች የይቅናሽ በሉኝ ምርቃቷን ጠይቃ ፤ እሩቅ ተጉዛ የእያንዳንዱን ሰው ቤት እያንኳኳች ቤት ለእንቦሳ ስትል አንዱ እንቦሳ እሰሪ ሲላት ሌላው ፊት ሲነሳት ሞያ በልብ ነውና እንደነብር የተዥጎረጎረችዋ መዥጎርገሯ ውበት የሆናት ባለብዙ አንደበቷ በሁሉም ብታወጋ ሁሉን በአንድ የምታግባባ በረከተ ብዙ ሀገራችን የሆነችውን ኢትዮጵያ በዐይኖቿ ያየችውን ሁሉ ለዐይን መግባለች።

 

 

ጋዜጠኛ አስካለ ከስራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን በምታቀናባቸው ቦታዎች ሁሉ ከመምሳል ተሻግራ የሆኑትን ትሆናለች ። የበሉትን በልታ የጠጡትን ትጠጣለች። የልብ ወዳጅም ያደርጓታል ።

 እንደ ዐይን እንደ ጆሮ

እንደ እግር እንደ እጅ

ወዳጅ ማለት አብሮ

የሚጓዝ ነው እንጂ  .....እንዲሉ

 

መጁን ጨብጣ  ወረድ ወረድ ፣ ቡኑን ፣ ቁርሱን ፣ እኔአደርገዋለሁ ፣እኔ እሰራዋለሁ በማለት እንደልጅ ቅልጥፍ ብላ ስትታዘዝ  ስታነሳ ስትጥል  የምትመለስ እንግዳ ሳትሆን ቤተኛዋ እሷው ትሆናለች ። በሀገረኛ ለዛ እያወጋች እየጠየቀች እየመለሰች እየሰራች አድማጭ ተመልካችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ግርታ እንዳይፈጠር  ግልፅ በሆነ ቋንቋ በጥሩ ምስል ክንዋኔዎቹን እዚያው ያሉ እስኪመስል ድረስ ታስቃኛለች ።

 

 

ለስራ ከተዘዋወረችባቸው ቦታዎች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓንጓ ወረዳ ስጋዴ ቀበሌ ተገኝታ እንደባህሉ ለብሳ ፤ እንጀራውን ጋግራ ፤ ወተቱን አስተላልባ ፤ በጓዳው ስትንጎዳጎድበት ፤ ዐይኗን ጭስ ሲጋርዳት ፤ ፊቷን እሳት ሲለበልባት  እናያለን ። የተለያዩ ዕቃዎችን መጠሪያ ስያሜ እየጠየቀች እየፈታች ወደተመልካች ታስተጋባለች። በሌላ ወቅት ደግሞ በኮንሶ ዞን በካላ / ንጉስ / ገዛኸኝ ቤት ተገኝታ አስደናቂ እና አይረሴ ስለሆነው የሬሳ አቀማመጥ  ባህል  እሬሳ አፈር ሳይቀምስ እንክብካቤ እየተደረገለት 9 ዓመት ከ9 ወር ከ 9 ሳምንት ስለሚቆይበት ስርዓት አስቃኝታለች ። ተመልካችም እጁን አፉ ላይ በመጫን አጀብ ባህል ብሏል።

 

 

እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአንድ አባዋራ ቤት አቅንታ ጥጥ ለመፍተል ስትሞክር ሸማ ቀሚስ ለብሳ ለውቂያ (ጅጌ) ምሳ በአገልግል ቋጥራ ከእማዋራዋ ጋር ወደ አውዱማ ስታመራ በሌላው ጊዜ ደግሞ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን  ከሚሴ ከተማ በቆነጃጅቱ ሹርባ ተሰርታ አንባር፣ አሸንክታብ ፣ ጉሜ ለብሳ እንደጉብሎቹ ሁሉ ማማሯን ለማረጋገጥ በመስታወት እራሷን ስትገላምጥ ቡኑን አፍልታ ገበያ አቅንታ ሸጣ ለውጣ ገበያውን ስታስቃኝ ደግሞ በዚያው አልፋ የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችው አፋር ክልል አፋንቦ ወረዳ ሜጉ ቀበሌ አድማጭ ተመልካቾቿን ባሉበት ሆነው እንዲጓዙ በማድረግ  እንደባህሉ ተውባ በምግብ አዘገጃጀቱ ንክር በቆሎ ስትድስ  እረኝነት  ተሰማርታ ፍየል ስትከተል ዱር ሜዳውን አይታ በጠጡበት ዋንጫ ጠጥታ እንጨት ሰብራ የሰው ፍቅር ተቋድሳ  ሙቀቱ ሳይበግራት በረሃው ሳያስፈራት አይደክሜ እግሯ ዞሮ በደቡብ ክልል ታርፋለች። በደቡብ ክልል ካሉት ቀበሌዎች በአንዱ የም ልዩ ወረዳ ፎፋ ከተማ እሸት ስትፈለፍል  እናገኛታለን። ብርቱዋ ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ።

 

በስልጤ ዞን ጀረሞ ሰንቦዬ ቀበሌ ጀረሞ ጎጥ መንደር  ተገኝታ ከቁርበት ላይ አረፍ እንዳለች ቡና በቅቤ  እየጠጣች አነቀላ የተባለ በቅቤ የታሸ ቆሎ ለቁርስ ሲቀርብላት ደሞ ኑ ስራ እንስራ ብላ ውሎ አዳራቸውን አብራ ስትከውን ቆጮ ቆረጣ ስትጓዝ ሌላ ሌላውንም ካሜራዎቿ ምስክሮች ናቸው።

 

ጋዜጠኛዋ በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ኤሪያ ኡንቡላ ቀበሌም ተጉዛለች። እንደሐመሮቹ  ፀጉሯን በአፈር ፈትላ (ለማስለቀቅ አንድ ሻንፖና ኮንዲሺነር አልበቃውም ትላለች ) በዛጎል ያጌጠ አልባሳቱን ተጎናጽፋ ቡና አፍልታ የሐመርን ህዝብ ድንቅ የቡና ስርዓት እና ባህላዊ የቅል ሲኒያቸውን በካሜራዎቿ ለተመልካች አድርሳለች። ለቤተሰቡ ቀድታ ስታዳርስ አባዋራው ደግሞ የመጨረሻውን ቡና አፉ ላይ በመቋጠር በጥርሶቹ መካከል አሾልኮ እጁን ሲታጠብና ሲመርቅ ለመመልከት ተችሏል ።

 

በምስራቅ ትግራይ ዞን ኢሮብ ወረዳ ተጉዛ የትግራይ ሹርባ ተሰርታ በሀገሬው ባህል በወንድ  እጅ የተፈላ ቡና ጠጥታ ወደስራ ተሰማርታለች። በለስ ስትቆርጥ የተከሰከሰባትን የበለሱን ደቃቅ እሾህ ግርፋት አትዘነጋውም። መዳፏ በአፈር እየታሸ እሾሁ እየተለቀመ በገጠመኙ እየተቀለደ እንደተለመደው ስራዋን ከሴቶቹ ጋር ቀጥላ እንቅስቃሴዋን ለካሜራ ባለሙያው ጥላ ተመልካች ጋር ትደርሳለች ።  በተጨማሪም በምዕራብ አርሲ ኮፈሌ፣ አላባ ፣ቤንች ማጂ ዞን ፣ ጋሞ ዞን ጤንቻ ወረዳ ፣ በአፋር አርጎባ ፣ በኮንሶ ዞን ፣ በደቡብ ትግራይ አፍላ ወረዳ ፣ በከፋ ዞን ጨና ወረዳ ፣ ሀዲያ ዞን ጊቤ ወረዳ ሆመቾ ቀበሌ እና በርካታ ያልተዘረዘሩ አካባቢዎች ላይ ተጉዛለች ።

 

 

በኗሪዎቹ ተወዳጅነትን ያገኘችው ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ በብዙዎች ዘንድ ቤተሰብ ሆና አብራ እንድትኖር ትለመናለች ። በሄደች በደረሰችበት ሁሉ ፈገግታ እየቀደማት ፍልቅልቅ በማለት ስትስቅ ስራው ላይ ድፍት ድፍት እያለች ከልቧ በመነጨ የደስታ ባህር ውስጥ ሰጥማ ከኗሪዎቹ እኩል በኑሮው ትዋኛለች። ምንም እንኳን ለሰሚና ለተመልካች "ከበሮ በሰው እጅ ያምራል" ቢሆንም'ኳ እሷ ግን በተግባር አዘባ ዝቃ ፤ ቅርጫት ተሸክማ ፣ ሳር አጭዳ ፣ ምድጃ ለምድጃ ፣ ጓሮ ለጓሮ ፣ አመድ ለአመድ ሄዳ የማህበረሰቡን ውሎ አዳር  አሳይታለች። ይህች ትጉህ ጋዜጠኛ ሴት በኑሮዋ ስራና ፆታ ለየቅል መሆናቸውን ለማሳዬት የቻለች አርዓያም ናት ።

 

አስካለ በወዳጆቿ ስትገለጥ ትሁት ነች ። ደግ ነች ። ፍልቅልቅ ነች ።ጠንካራ ነች ። ምሳሌ ነች ። ጋዜጠኛዋ ኤዲተርም ነች ። እንድህ በየቦታው ሄዳ የሰራቻቸውን የምስልና ድምፅ ስራዎች ተመልሳ በቢሮዋ በመሆን ኤዲትም ታደርጋለች ። በስራ እረጅም ሰዓታትን ስለምታሳልፍ የቋጠረችውን ምሳ እስከመመለስ ግድ የሆነ ቀን በቢሮ ውስጥ አድራ እስከመስራትም ትደርሳለች ።

 

 

The Queen of (Wulo Adar) የውሎ አዳር ንግስት የሚል ስያሜን ከአንዳንዶች ዘንድ ያገኘችው  ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ በ2012 ዓ.ም በተዘጋጀው የአርዓያ ሰው ሽልማት ላይ  ከአድዋ የባህልና የታሪክ ማህበር ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላታል። ጋዜጠኝነትን እንድትወደው እና እንድታገለግልበት በልጅነቷ የጉዞዋን ፈር የቀደዱላትን ጋሽ ሰለሞን ገ/ስላሴ እንዲሁም የኤዲቲን ሙያን ያስተማራት ባልደረባዋን ኤዲተር ፋንታሁንን እንዲሁም አብረዋት የሚሰሩ የጉዞ ጓዶቿን የካሜራ ባለሙያዎች እና ሹፌሮች የስኬቴ ቁልፎች የህይወቴ  ባለውለታዎች ናቸው ። ስትል ትናገራለች ።

 

የሀገራችን የኑሮ ውጣውረድና እንግልት ፤ ማግኘትና ማጣት  ፤ የጉልበት ድካም  በተቻለ መጠን በውሎ አዳር ዝግጅት ሲቃኝ የአርብቶ አደሩን ጉሮኖ ፤ የአርሶ አደሩን ጎተራ ፤ የእማዋራዋን ማጀት ፤ የአባዋራውን ኪስ እንዲሁም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጠለቅ ባለመልኩ አስካለ በሀሳብና በካሜራ ለማስቀረት ችላለች ።

 

የውሎ አዳራችንን የህይወት ድግግሞሽ ፤ ጉራማይሌ የሆነውን ማንነታችንን ከተፈጥሮ ጋር የሚደረገውን ትንቅንቅ በቴሌቪዥን መስኮታችን አጮልቀን ለመመልከት እና ለመታዘብ ችለናል ። በሀገራችን የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እንደት ህይወታቸውን ይመራሉ ? እንደትስ ተደርጎ ቢሰራ ውስጣቸውን በደንብ ለማወቅ ይረዳል ? የሚለውን ለመረዳት እና ለመተግበር በእርግጥም ቆራጥ ልብ ፤ የዳበረ ንቃተህሊና  እና ጀግንነት ይጠይቃል ። የዘመናችን ጀግና የሆነችው ጋዜጠኛ አስካለ ይህንን ደፍራ ያደረገችው ሲሆን ይኸውም ተሳክቶላታል።

 

 

ውሎ አዳር ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ በኋላ ሦስተኛ አመት መጀመሪያ አካባቢ በአውራንባ ደርሳ ስትመለስ ስራዋን አየር ላይ ሳታውል በጠና ታማ ካልጋ ወደቀች ። የጭንቅላት ውኃ መቋጠርና የጀርባ ድስክ ህመሞች ተባብረው ጣሏት።

 እነዚያ መሮጥ የለመዱ እግሮች ሸብረክ አሉ። እናዚያ ሳቆች ደበዘዙ ። ጥርሶቿ ከንፈር ለበሱ ። ውሎ አዳር በባልደረባዋ ቀጠለ። አስካለም ወደህንድ ለህክምና አቀናች ። ህክምናዋን ጨርሳ ወደሀገር ቤት በመመለስ መድኃኒቶቿን በመከታተል ላይ ስትሆን በቅርብ ቀን ወደመደበኛ ስራዋ እንደምትመለስ ከአንደበቷ ሰምተናል።

 

 

"አንድን ስራ ወደነው ከልባችን ስንሰራው ስኬታማ ነን ። ለቁስ መሰብሰቢያ ከሆነ ግን አይመጣም ። ባህልና ወጎቻችን በያለንበት ልጠብቃቸው ይገባል ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሄዶ ሄዶ አንድ ነው"

 

 

 

 

                     ጋዜጠኛዋ ።

 

 

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት በቀጥታ ከጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ እና ከሚዲያዎች ጋር ያደረገቻቸውን ቆይታዎች እንዲሁም ከወዳጆቿ የተገኘን መረጃ መሰረት በማድረግ ነው።ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን በበኩሉ ጋዜጠኛ አስካለ ተስፋዬ ጤንነቷ ተመልሶ የምትወደው ስራዋን እንድትቀጥል ይመኛል።

 

 

 

 

 

 

 

 





 

 

 


አስተያየቶች

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች