141.መዓዛ ብሩ ገብረወልድ
በመጨረሻም ከፊቷ ለቆሙ ሁለት ሞጋቾቿ ተረታች። ተረታችና የእሁድ ፕሮግራም ላይ ጭውውት ልትሰራ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተገኘች። ጭውውቱን በመስራት እግረ መንገድ የነፍስ ጥሪዋን አገኘች፦ ሬዲዮ። በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ቀዳሚውን የኤፍ ኤም ሬዲዮ ከወዳጆቿ ጋር ቆርቁራ አንጋጠው የሚያዩዋት የጋዜጠኞች ሰማይ ሆናለች፦ መዓዛ ብሩ።ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሸን በሚድያ ዘርፍ
ባለፉት 50 አመታት አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሰዎች ታሪክ እየሰነደ፤ በድረ-ገጽ ፤ በኢንሳይክሎፒዲያ ፤ በኦድዮ እየሰነደ እንደሆነ
ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ታሪካቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ ከታሰቡ ስኬታማ ሰዎች በቀዳሚነት የምትመጣው መአዛ ብሩ ናት፡፡ እዝራ እጅጉና አማረ ደገፋው የመአዛን ግለ-ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልሳን የመጨረሻ ዓመት ተማሪ በነበረች ጊዜ ነው፤ የዶርም ተጋሪዋ የነበረችው መንበረ ታደሰን ፍለጋ የመጡ አስታጥቃቸው ይሁንና ተፈሪ ዓለሙ መንበረን ስላጧት በእርሷ ፋንታ መዓዛ አብራቸው ሂዳ ጭውውቱን እንድትሰራ የሞገቷት። እንኳንም ሞገቷት፤ እንኳንም ሙግቱን ተሸንፋ ሄደች። የታደሰ ሙሉነህ የእሁድ ፕሮግራም ላይ ድምጿን አሟሽታ በኤፍኤም አዲስ በኩል ተሻግራ በሸገር የተገለጠችውን መዓዛ እንድናገኝ ሁነናልና።
ተወዳጅ ሚዲያ ኢትዮጵያዊ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ለመሰነድ ሲነሳ መዓዛ ብሩ አንዷ መድረሻው ነበረች። "ገና ምን ሰራሁና" የሚለው ምላሿ ግን ታሪኳን ሳይሰንድ እዚህ አድርሶታል። አሁንም ከዚህ ትህትናዋ ዝንፍ ባትልም በስሱ እራርታልን ከዚህ ቀደም በጥቂት አጋጣሚዎች ስለራሷ የተናገረችባቸውን ምንጮች እንድንጠቀም ፈቅዳልናለች።
"ኪነ ጥበብ ደስ ይለኛል፤ አደባባይነቱ ነው ደስ የማይለኝ" የሚል ንግግሯን አምነን በመታመን 'ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውን ሴቶች' የሚል መጽሐፍ ላይ የሰፈረ ታሪኳን እና የጨዋታ ፕሮግራም 20ኛና የሸገር ሬዲዮ 13ኛ ዓመት ሲከበር ለራሱ ለሸገር ሬዲዮ የሰጠቻቸውን ሁለት አጫጭር ቃለ- ምልልሶች እንደ ምንጭነት ተጠቅመን ታሪክ ስነዳችንን እንጀምራለን።
ከነጋዴ ወላጆቿ 1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው የተወለደችው። እስከ ዘጠኝ አመቷ "የበለጸገ የባህል መስተጋብር ባለቤት" በምትላት ሂርና ከተማ ካደገች በኋላ አባቷ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስተ ማርያም የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቧት። የተፈጠረባትን ብቸኝነት ለመሸሽ አባቷ ቀድመው በገለጡላት ንባብ ቆየች። 10ኛ ክፍል ስትደርስ በእድገት በህብረት ዘመቻ ትግራይ ውቅሮ የቆየችባቸው ስድስት ወራት "ትክክለኛው ኃላፊነት ምን እንደሚመስል የተገነዘብኩበት የመጀመሪያ አጋጣሚዬ ነበር" ትላለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ- ልሳን ትምህርቷን ስትጨርስ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተመደበች። በዚያም መርሃ ስፖርት የተባለ ጋዜጣ ላይ የስፖርት ዘጋቢ ሆነች። ለጋዜጠኞች በተለየ መግቢያ ስቴዲየም ዘልቃ፤ ደምሴ ዳምጤን ጨምሮ ስማቸው የገዘፈ ጋዜጠኞች ጋር ተካክላ የየዕለቱን ጨዋታዎች ዘግባለች። ዛሬም ድረስ ያለ የስቴዲየም ትዝታዋ ከቆሎ ሻጯ እስከ ደጋፊዎቹ ጭፈራ ይዘልቃል።
ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ጎራ ብላም "ብሪቱ" የተባለች የባንኩን ወርሃዊ መፅሔት በዋና አዘጋጅነት ስታሰናዳ የቢዝነስ ዜናዎችና ልቦለዶችን ለአንባብያን አድርሳለች። በመቀጠል በሽግግር መንግስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና መረጃ ዳይሬክተር ሁና ለአራት አመታት ካገለገለች በኋላ የቢሮክራሲ ስራ ለእርሷ እንደማይሆን ወዳጆቿ ጠቁመዋት እርሷም ገብቷት ስራ አቆመች።
በዚህ መሃል የወቅቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ ፈቃዱ እምሩ ለአበበ ባልቻ(የመዓዛ ባለቤት) ኤፍ ኤም አዲስ ላይ የአየር ሰዓት ወስዶ ስራ እንዲጀምር ሃሳብ ያቀርቡለታል። ይሄ ሃሳብ የጨዋታ ፕሮግራም ጥንስስ ሆነ፡፡ መዓዛና ተፈሪ አለሙ በኋላም ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ብርሃኑ ድጋፌ፣ ግሩም ዘነበና ደረጀ ሃይሌ ተቀላቅለው ጨዋታ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አየር ላይ መጫወት ያዘ።
እንደ መጽሔት ያለ ቅርፅ የያዘው ጨዋታ ፕሮግራም ለሸገር ኤፍ ኤም እንደ መንደርደሪያ ሆኖ አገልግሏል። መንግስት ለግል የሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ እንደሚሰጥ ሲያስነግር ጋሽ አቤ እድሉን መጠቀም እንዳለባቸው ቢያምንም መዓዛ "ፈቃዱን ብናገኝ ምኑን ከምኑ እናረገዋለን... ጥቂት እንቆይ" አለች፤ ተሟገቱ፤ ለሁለተኛ ጊዜ እንኳንም ተሸነፈች የሚያስብል ሽንፈት ተሸነፈች። ከተፈሪ ዓለሙ ጋር ሆነው አመለከቱ፤ እርሷ እንደምትል ከብዙ ውጣ ውረድ በኃላ ፈቃድ ተሰጣቸው።
የ'ምኑን ከምኑ ልናደርገው ነው' ፍርሃቷ ጨምሮ "ውድድራችን እኮ ከ90 ዓመት አንጋፋው ኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር ነው" ማለቷን ታስታውሳለች። ፍርሃቷ ግን ይበልጥ ትጉ እንድትሆን ያደረጋት ይመስላል። መስከረም
25 ቀን 2000 ዓ.ም ወደ አድማጮቹ መድረስ የጀመረው ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 በሚያስታውቅ መለየት ዓመታትን ዘልቋል። ከእሁድ ጧት አጭር ጭውውት የተነሳ የሬዲዮ ዘመኗን ስታስታውስ "እኔና ተፈሪ ሰው ጆሮ ላይ ነው ያደግነው" ትላለች።
ሸገር ሲቆም ጨዋታ ፕሮግራምን ተደግፎ ነው። ከጨዋታ ፈገግታዎች አንዱ ደግሞ መዓዛ የደመቀችበት የጨዋታ እንግዳ። "በሀገራችን ሰዎች የነበሩበትን፣ ያለፉበትን ጥሩ አድርገው አይፅፉት" የምትለው መዓዛ 'ባይፅፉት ቢያንስ ይናገሩት' በሚመስል ትጋት በርካቶችን አናግራለች። አደባባይ የማትወደው የጋዜጠኞች ሰማይ ከሀገር እስከ ሃይማኖት መሪ ድረስ አደባባይ አውጥታ የሆዳቸውን እንዲያወሩ አድርጋለች። የአንድ ወቅት እንግዳዋ የነበሩት ዶክተር ጌታቸው ተድላ ስለመዓዛ አጠያየቅ እንዲህ ይላሉ፦
"…ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት፣ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ በሬዲዮ ጣቢያዋ የጨዋታ እንግዳ አድርጋ ጋብዛኝ ነበር፡፡ በአራት ክፍል መድባ ብዙ ሰዓቶች የፈጀ ቃለ መጠይቅና ጨዋታ አድርገናል፡፡ አንድን ነገር ለመጠየቅ ስትፈልግ፣ “ጨዋታን ጨዋታ ያመጣዋልና፣ ይህን ይህ ነገር….” ብላ አሳስቃ በሀገርም ውስጥና በውጭ ዓለምም የነበረውን ክስተት አነሳስታ እኔም ከልቤ አውርቼላታለሁ፡፡ አጠያየቋ ከሳቅና ከርህራሄ ጋር የተዋሀደ ስለሆነ፣ ማንም የጨዋታ እንግዳ ሲወያያት እንደ ቅርብ ጓደኛ እንጅ፣ እንደሚከብዱ አወያዮች አይመለከትም፡፡"
የእርሻ ኢኮኖሚስትና፤ የገጠር ባለሙያና
ደራሲ የሆኑት ዶክተር ጌታቸው ተድላ መአዛን ግለጹ ሲባሉ በጣም ከማደንቃቸው ጥቂት አወያይ ሰዎች አንደኛዋ ነች ሲሉ ሀሳባቸውን
አብራርተው ገልጸዋል፡፡
‹‹…….ጥቂት ምርጥ ስብዕና ያለው
ጋዜጠኝነትን ከምትኮርጃቸው ጋዜጠኞች መካከል
ወይዘሮ መዐዛ
አንዷ
ትመስለኛለች።
መዐዛ
ብሩ ከምትሰራቸው
ፕሮግራሞች ምርጥ
ፕሮግራም መስራትንም መኮረጅ ትችላለህ፤ ያው እያየኃትና እየሰማሃት ትማርባታለህ። ደግሞ ሁሌም የጋዜጠኛነት ጉልበቷ
አዲስ ነው፤አታክትም። ለእያንዳንደ ፕሮግራሞቿ
ከዝግጅት እስከ ቀረፃ ያለው ትጋቷ ይገርመኛል።››
ግርማ ፍስሐ
የሸገር 102.1 ፕሮግራም ሃላፊ
ማህሌት ሰለሞን
የቴአትር መምህር እና የፊልም ባለሙያ ናት፡፡ ስለ መአዛ ብሩ አሰብ
ስታደርግ ለስራ ያላት ቁርጠኛ ፍቅር ትውስ ይላታል፡፡ በዚህም ምክንያት መአዛ ለእኔ እንደ አርአያ ወይም አይከን አድርጌ ቆጥራታለሁ ትላለች ማህሌት፡፡
ማህሌት የረጅም ጊዜ የሸገር አድማጭ እንደመሆኗ ሁለ-ገብ የሆነውን የመአዛን እውቀት ታደንቃለች፡፡
‹‹… መአዛ
በሚድያ ስራ የካበተ ልምድ ያደበረች ናት፡፡ ያንን ልምዷን ከቃለ-መጠይቋ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ የመአዛ እውቀት ከንባብ የመጣ
ነው፡፡ ይህም በየጊዜው የዳበረና ክህሎቷን ጨምራ ያካበተችው ነው፡፡ እኔ ሸገር ካፌንም ጨዋታ መሰናዶንም በንቃት አደምጣለሁ፡፡
የእንግዳ እና የርእሰ-ጉዳይ ምርጫዎቿ ይደንቁኛል፡፡ ያላት አቀራረብ ፤ ቁጥብነቷ፤ አድማጭን የሚጋብዝ ነው፡፡ ርጋታዋ ይስበኛል፡፡
መአዛ ቃለ-መጠይቋ የሚጠገብ አይደለም፡፡ የመአዛን ቃለ-መጠይቅ አንዳንድ ጊዜ እየደጋገምኩ የማደምጥበት ጊዜ አለ፡፡ የመአዛ ድምጸት
ወይም ቶን ውስጥ ማንነቱዋን በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡ እናም ጨዋነት ወይም መረጋጋት ድምጹዋ ውስጥ አገኛለሁ፡፡›› ስትል የቴአትር
ባለሙያዋ ማህሌት ሰለሞን ሀሳቧን ሰጥታለች፡፡
መአዛ ብሩ በማህሌት
እይታ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ የመጣች ባለሙያ ነች፡፡ ‹‹ከሸገር
ጥንካሬ ጀርባ ያለች ዋና ሰው ማለት መአዛ ነች ›› ስትል ማህሌት የመአዛ ጥረት ለብዙዎች ተምሳሌት እንደሚሆን ታሰምርበታለች፡፡
የተማረ የሰው ሀይል በሌለበት በብዙ ትግል ሸገር ጣቢያን ለ14 አመታት
በስኬት ማማ ላይ ማቆም መአዛን የሚያስከብራት ነው ስትል ማህሌት ሀሳቡዋን ትሰጣለች፡፡
‹‹… መአዛ ፕሮግራሞቿን ተጨንቃ የምታቀርብ በመሆኑ
በአድማጭ መከበርና መወደድ ችላለች፡፡ የምትሰራቸው ፕሮግራሞች አየር ላይ ከመዋላቸው በፊት በቂ ጥናት እንደተደረገባቸው ያስታውቃሉ፡፡
የጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም 20ኛ አመትን አስመልክቶ መዓዚን በአጭሩ ያነጋገረቻት የሸገር ባልደረባ ህይወት ፍሬስብሀት እንዴት ለቃለ መጠይቅ እንዳቀረበቻት ስትናገር "ተጋፍቻት ነው" ትላለች። አስከትላ "የጨዋታ ዝግጅትን ከነ ሙሉ ክብሩ 20 ዓመት ማቆየት እንዴት ተቻለሽ?" ብላ ስትጠይቃት "የምትሰሪውን መውደድ፤ የምትወጅውን ለመስራት ሁል ጊዜ አዳዲስ መላዎችን መፈለግ" ትላለች።
በትክክልም የምትሰራውን እንደምትወድ ያስታውቃል። ልቅም ያሉት የጨዋታ እንግዳና የሸገር ካፌ ዝግጅቶቿ ያሳብቃሉ። የሬዲዮ ስራ በተለየ ጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት ስታስረዳ "...በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው ጋር ስለምንደርስ ብዙ ሰው እናሳስታለን፤ በአዋቂዎች ትዝብት ውስጥም እንገባለን" ትላለች። ይህ ጥንቃቄዋና ብቃቷ የሚያስገርመው ባልደረባዋ ዘካርያ መሃመድም ይላል፦
"ዜና አትሠራም፤ ነገር ግን ዜናዎች እንዴት እና በምን ማዕዘን መሠራት እንዳለባቸው ስትነግርህ በዚህ ረገድ ያላት ብቃት ያስገርምሃል፡፡"
የጨዋታ እንግዳ ዝግጅት ላይ የቀረቡ እንግዶቿን የፆታ ምጣኔ ሰርታ የሴቶችን ጥቂትነት ስትታዘብ እንደሚያሳፍራት ትናገራለች። "ተጨማሪ ፈተና አለው" የምትለው ኢትዮጵያዊ ሴትነት በአካላዊ ውበት ብቻ መገለጡን አትወድም። የሴቶች ብስለት የሚጎላበት ዘመን እንደሚመጣም ተስፋ ታደርጋለች።
የንግድ ሳይሆን የህዝብ ሚዲያ ዓይነት አወቃቀር እንዳለው የምትገልፀው ሸገር ሬዲዮ በልዩ መታወቂያው ዓመታትን ሲገልጥ ቀላል የማይባሉ ተፅዕኖዎች እንደነበሩት መዓዛ ትናገራለች። ነገር ግን በርካታ መስዋዕትነት በተከፈለባት ሃገር የነበሩ ተፅዕኖዎችን እንደጀብዱ ቆጥሮ እንዲህ ተደርገን ነበር ብሎ ማውራት ተገቢ እንዳልሆነ ታስረዳለች።
በደረሰችበት ከፍታ ረክታ መቆም የማታውቀው መዓዛ ፣ "በምሰራው ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም" የምትለው መዓዛ፣ "የፊት የፊቴን መኖር እንጂ አርቆ ማቀድ ብዙም አለመደብኝ" የምትለው መዓዛ... ሸገር ወደፊት ቴሌቭዥንም ሲኒማም ቢሆን ህልሟ ነው፡፡ ህልሟ እውን ሁኖ በቴሌቭዥን ሌላ አሻራዋን ስታሳርፍ ማየት ደግሞ የኛ ህልም፡፡
መዝጊያ ፤ ይህ የመዝጊያ ሀሳብ የተወዳጅ
ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የግለ-ታሪክ ዝግጅት ክፍል አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
የሚድያ ሰው
መአዛ ብሩ ገብረወልድ ለሬድዮ የተፈጠረች፤ ይህን መክሊቷንም አውቃ
በምትወደው ሙያ የተሰማራች ታላቅ ሰው ነች፡፡ መአዛ ባለፉት 40 አመታት ከሚድያው ገጽ ላይ ጠፍታ አታውቅም፡፡ ለሙያው ትልቅ ከበሬታ
ስላላትም ከሚድያ ውጭ ዝንፍ ብላ አታውቅም፡፡ ከመታየት ይልቅ መስራትን አስቀድማ የሙያውን ህግ ተከትላ አመታት ዘልቃለች፡፡ በተለይ
ደግሞ ከ 22 አመት ወዲህ የቅዳሜ ጨዋታን አንድ ብላ ከጀመረችበት ዘመን አንስቶ የአድማጭን ቀልብ ለመሳብ ችላለች፡፡ ይህ ክህሎቷ
በተፈጥሮ የተገኘ ቢሆንም በንባብ እና በጥረት የካበተ ልምዷን በመጠቀም አንድ አሻራ ለማሳረፍ ችላለች፡፡ በቃለ-መጠይቅ ባለፉት
20 አመታት ከታዩ የሚድያ ሰዎች መካከል መአዛን የሚፎካከር ማግኘት ያዳግታል፡፡ የሚድያ ሰው መአዛ ብሩ ስለ ራሷ ብዙ አትናገር
እንጂ ስራዋ ግን ብዙ ይናገራል፡፡ የፈጠረችው ድንቅ ተጽእኖ ዝም አያሰኝም፡፡ በተለይ ሬድዮ ሲነሳ መአዛን መዘንጋት አይቻልም፡፡
ሸገር 102 ነጥብ 1 ሲነሳ መአዛ ብሩን በቀዳሚነት ከከፍታ ላይ አለማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ይህን የምንጸፈው መአዛ አድማጭ ላይ ተጽእኖ
ስለፈጠረችና አዲሱ ትውልድ ታሪኩ ሊሰነድለት የሚገባውን ሰው እንዲያከብር ስለምንሻ ነው፡፡ መአዛ በአንድ በኩል የመጀመሪያውን የግል
የሬድዮ ጣቢያ የከፈተች በሚል ግለ-ታሪኳ በጥሩ ብእር መጻፍ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ሁለተኛ እንደ ሚድያ ሰው ደግሞ አየር ላይ የምታውላቸውን መሰናዶዎች በማድመጥ ለወጣቱ እንደ ትልቅ አርአያ
የምትቆጠር ነች፡፡
ኢትዮጵያ አይከን
ወይም አርአያ አላት፡፡ ነገር ግን አይከኖቹዋ ወይ በሌላ ሰው ይሸፈናሉ አሊያ ምን ሰራሁ በሚል ራሳቸውን ሎው ፕሮፋይል በሚል ይደብቃሉ፡፡
በእኛ ታሪክ ሰናጆች እምነት ግን የሰራ ታሪኩ ይውጣ ያልሰራ ይደበቅ የሚለውን ታላቅ መርህ አጉልተን ሰው ልብ ውስጥ ማኖር እንሻለን፡፡
ተወዳጅ ሚድያ
እና ኮሚኒኬሽን ግለ- ታሪክ ላይ የስነዳ ስራ የሚያከናውን ድርጅት እንደመሆኑ ብዙ ሰዎችን የማድመጥ የማነጋገር ልዩ እድል አግኝቷል፡፡
አሁንም ትልቁ ግባችን በህይወት እያለን 5 ገጽ እንኳን ጽፈን ያሳለፍነውን እንተርከው የሚል ነው፡፡
ሁላችንም በሙያዋ
የምናከብራት መአዛ ብሩ የሌሎችን ታሪክ በድምጽ እንዳስቀረችው ሁሉ የእርሷም ታሪክ እንዲሰነድ ማድረግ አለባት፡፡ በእርግጥ ተምሳሌት
መጽሀፍ ላይ የወጣው እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ሀሳቦች ከመአዛ እንፈልጋለን፡፡ መአዛ ብሩ ዛሬም በሙያዋ የክብር ቦታ ላይ ሆና ትተጋለች፡፡
እንዲህ ቀን ተሌት የሚተጉ ሰዎችን ግለ-ታሪክ ማንበብ ደግሞ ደስ ይላል-መአዛ ደግሞ ይህን ጽሁፍ አንባብ ተጨማሪ ሀሳቦችን ስታክልበት
የበለጠ አሪፍ ይሆናል፡፡እናከብረሻለን መአዛ ብሩ፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና በአማረ ደገፋው የተዘጋጀ ሲሆን የመአዛ
ብሩን በ100 የሚቆጠሩ አየር ላይ የዋሉ መሰናዶዎች በወጉ በማድመጥና በማጥናት የተመሰረተ ነው፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መሳካት ጠበቃ አበበ ባልቻ ትብብር ያሳየን በመሆኑ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ከነሀሴ 2013-የካቲት
2014 በተደረገ ጥናት የተሰናዳ ነው፡፡ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 6 2014 ይህ የመአዛ ብሩ ግለ-ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የግለ-ታሪክ
ገጽና የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ወጣ፡፡ ጽሁፉ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው ተሻሽሎ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
Meazi
ምላሽ ይስጡሰርዝ