5. ዜናነህ መኮንን
-ZENANEH MEKONEN
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ130 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ጋዜጠኛ እና ዜናነህ መኮንን ይነሳል፡፡
አሁን ታሪኩን የምናቀርብላችሁ ሰው ጋዜጠኛ ፤ ደራሲ ፤ ገጣሚ ሀያሲና የዜና አንከር ወይም ስመጥሩ የዜና አቅራቢ ነበር፡፡ ዜናነህ መኮንን፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎችን ታሪክ አሳብስቦ በኢንሳይክሎፒዲያ ቅርጽ ለማሳተም ጉዞ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ እስከ ህትመቱ በዚህ ገጽ ስለ ዜናነህ መኮንን አጭር ግለ-ታሪክ ታውቁ ዘንድይህን ጽፈናል፡፡ የዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጅ የተወዳጅ ሚድያ ከፍተኛ የዊኪፒዲያ ኤክስፐርት የሆነችው ዘቢባ ሁሴን አሊ ናት፡፡ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ በአርትኦት እና መረጃዎችን በማቅረብ እገዛ አቅርቧል፡፡ ታሪኩን በጥሞና ታነቡ ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡
አንጋፋዎቹ መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በ1970ዎቹና 80ዎቹ ሲታወሱ ዛሬም ድረስ ስሙ በጉልህ ይነሳል። የታሪክ ተመራማሪ፣ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ልዩና ተወዳጅ ዘጋቢ ነዉ፡፡ ዜናነህ መኮንን፡፡ ከጋዜጠኛነቱ በተጨማሪ ደራሲ ፣ገጣሚና ሃያሲም ነው። ከግርማ ሞገሱ ጋር ግርማ ሞገስን የሚያላብስ ልብስ ለብሶ በኢትዮጲያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሸቱ ሁለት ላይ “ጤና ይስጥልኝ እንደምን አመሻችሁ ከሰዓቱ ዜና ጋር ዜናነህ መኮንን ነኝ” በማለት እጅ ሲነሳ የብዙዎች ትዝታ ሆኖ አልፏል። በበርካታ የቲቪና የሬድዮ ተከታታዮች ዘንድም የሚወደድ ነው፡፡ የጀርመን ድምጽ (ዶቼ ዌሌ ሬዲዮ) የጣቢያው መክፈቻና መዝጊያ ድምፅ የዚሁ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህ ሰዉ ኑሮውን በእየሩሳሌም ካደረገ ዘመናት ተቆጥረዋል።
ው ልደትና እድገት
ዜናነህ በ1945 ዓ.ም ጎንደር አዘዞ በምትባል ከተማ ውስጥ መስከረም ወር ላይ አደይ አበባና አዲስ አመቱን ተከትሎ ነበር ወደዚህች ምድር የመጣው። ውልደቱ አዘዞ ይሁን እንጂ በቤተሰቦቹ የስራ ጸባይ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የመጣው በልጅነቱ ነበር፡፡ በመቀጠልም ወደ ጂማ ሄዶ “ቆጪ” ሰፊር ይኖሩና ፃዲቁ ዮሀንስ (አሁን የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ሆኗል)ይማር ነበር፡፡ ጂማ እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ ከተማረ በኋላ ወደ ጎንደር በመሄድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ የሁለተኛውንም አጋምሷል። ከዚያም ወደ ድሬዳዋ በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የሙዚቃ ፍቅር ስለነበረው በ60ዎቹ ገደማ ያሬድ ትምህርት ቤት ሙዚቃን ለመማር ገብቶም ነበር። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱንም የጨረሰው እየሠራ በመማር ነበር።
የጋዜጠኝነት ሕይወት
ዜናነህ፣ በጄኔራል ዊንጌት የሁለተኛው ዙር የፖለቲካ ተማሪ ሳለ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ፓለቲካን የተለማመደው። በዚሁ አጋጣሚ በጣም ተከራካሪና ላመነበት ሟች መሆኑን ያዩ ወዳጆቹ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲቀጠር ይገፋፉት ነበር። ከዚያ 1968 ገደማ በሬዲዮ ሪፓርተርነት ተቀጠረ። የመጀመሪያው ንባቡ ‹‹የአብዮት መድረክ›› የሚባል የኢህአፓና የሜኤሶን የግጭት ሁኔታ የሚገልፅ በርካታ አድማጮች የነበሩት መሰናዶ ነበር።
እነ አሳምነው ገብረ ወልድ፣ እነ ዘውዱ ታደሠ፣ እነ መሀመድ እንድሪስ፣ እነ ንጉሴ ተፈራና እነ አብዱ ሙዘይን በኢትዮጲያ ሚዲያ ላይ ትልቅ አበርክቶ ያደረጉና የእኔም ሞዴል የምላቸው ናቸው ሲል በተለያዩ ሚዲያዎች ቃለ- መጠይቅ ሲያደርግ ይደመጣል።
በዋነኛነት ግን ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ እንዲገባ አርአያ የሆነው አሳምነው ገብረወልድ እንደሆነ ይናገራል። ሌላዉ ደግሞ ጎንደር ትምህርት ላይ እያለ ሰኞ ሰኞ የጀርመን ራዲዮ ድምፅን አዘውትሮ ያደምጥ ስለነበር ያን ይዞ ሰልፍ ላይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ለመላ ተማሪዎቹ ያነብ ነበር። ይህም በኋላ ለነገሰበት የጋዜጠኝነት ሞያ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይናገራል።
ለመጀመሪያ ግዜ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩት አቶ ማዕረጉ በዛብህ ግጥሞቹን በጋዜጣ ላይ ያወጡለት አጋጣሚ ጥሩ መነቃቃትና የእችላለሁ መንፈስ እንዲያድርበትም ያደረገው እንደነበር ይናገራል፡፡
አንዳንዴም ስምን መልዐክ ያወጣዋል እንዲሉ ዜናነህ ዜናን ሲያነብ አድማጮቹን የሚያከብር ፤ለማህበረሰቡ ቅርብ የሆኑ ጉዳዮችን አድኖ የሚዘግብ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነበር። መንግስትን የሚቃወሙና በመንግስት ያኮረፉ ሰዎች የዜናነህን ዜና አድማጮች ነበሩ፡፡ የዜና አቀራረቡ፣ አከፋፈትና አዘጋጉ ላይ የሚያሳየው ትህትና ዜናነህን አይረሴ አድርገውታል።
የማስታወቂያ ሚኒስተር ዉስጥ ሲቀጠር ዘመኑ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ይካሄድ የነበረበት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከራዲዮ ወደ ቴሌቪዥን ገብቶ ዜናንና ከየአቅጣጫው የሚባል ፕሮግራም ተሰጠው፡፡ ይህ ወቅት ጥሩ መለማመጃ ሆኖለትም አለፈ። በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ታሪክ ለ7 ዓመታት ያህል እንቁጣጣሽን አንባቢ የነበረውም ይሄው ዜናነህ ነበር። በጊዜው በነበረው ትእዛዝ መሰረት የቲቪ ወይም የሬድዮ አንከሮች እንኳን አደረሳችሁ ማለት አይፈቀድላቸውም
ነበር፡፡
ይልቁንም
እንኳን
ደረሳችሁ
ብቻ እንዲሉ ይገደዱ ስለነበር ነው፡፡ ምክንያቱም ያኔ የነበረው የሶሻሊዝም አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መኖር ወይም ሀይማኖት ላይ ጥብቅ ተቃውሞ ስለነበረው ነው፡፡ ዜናነህ ግን አልፎ አልፎ አውቆ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ተመልካችን ሰላም የሚልበት ጊዜ ነበር፡፡
አንድ ወቅት ጄኔራልን ኮሎኔል ብሎ ዘግቦ በመሪዎች ዘንድ በእኩይ አይን ታይቶ እንደነበር ያታወሳል፡፡ ዜናነህ ዜና ማንበብ ሲጀምር "ይህ የኢትዮጵያ ድምፅ ነው" ብሎ መጀመሩን ሳይቀር እንዲያቆም የተከለከለበት አጋጣሚም ነበር። ዜናነህ በሃላፊው ተፈርሞ ያልተሰጠውንና እርሱ ያላመነበትን ጉዳይ የማይዘግብ፤ የራሱን ስሜት፣ አመለካከትና አተያይ በፍፁም በሚያነበው ዜና ውስጥ ጨምሮ አድማጭን የማያደናግር ሰዉ ነበር፡፡
በ1967 ዓ.ም በማስታወቂያ መምሪያ ጋዜጠኝነትን “ሀ” ብሎ የጀመረው ባለ ነጎድጓዳማው ድምፁ አንጋፋው ጋዜጠኛ ዜናነህ ሃሳቡን ያለ ይሉኝታና ፍርሃት በነፃነት መግለፅ መቻል ባህሪው ነው። ይህንንም የማይወዱለት ታዲያ ብዙ ዋጋን አስከፍለውታል። በደርግ ግዜ ከ1969-1971 ለ2 አመት በሙያው ብቻ የታሰረ ጋዜጠኛ ጥቀሱ ቢባል ዜናነህ ነበር። የኢህአፓ አባል ነህ በሚል የክስ ጭብጥ አስረውት ይህ አላስኬድ ሲላቸው ደግሞ የልዑል መኮንን ልጅ ነው በሚሉ አሉባልታዎች ከከፍተኛ አንድ ማዕከላዊ እስከ ዓለም በቃኝ ድረስ እሥር ቤቶቹን አፈራርቋል፡፡ ከእስሩ ሲፈታ ለሶስት ዓመት ያህል ያለ ኪራይ ከመምሪያው ሀላፊ ጎን ብስራተ ወንጌል ውስጥ ቤት ተሰጥቶት በነፃ እንዲኖር በማድረግ የሞራል ካሳም ተከፍሎት ነበር፡፡
ሁሌም ሽክ እና በሱፍ ግርማ ሞገስን ተላብሶ የሚታየው ዜናነህ ቡና የሚጠጣው እንኳን ቦታዎችን መርጦ ነበር። በተለይ የኢትዮጵያ ሆቴል ቡና ነፍሱ ነች፡፡ ይህ የሚያስቀናቸው ሰዎች ደግሞ ጠላቶቹ ሆኑ፡፡ “ቅናት የሚባለው ነገር የእውነት ደምና አጥንት እንዳለው የተረዳሁት ያኔ ነበር” የሚለው ዜናነህ ከዚህም ተነስቶ ነበር ‹‹ነፃነት›› የሚለውን የመጀመሪያ መጽሀፉን የፃፈው። “ትምህርት ከድል በኋላ” የሚለውን አባባል እና አመለካከት አጥብቆም ይቃወም ነበር፡፡ ይህ ልዩነት አሁንም ድረስ አብሮት ዘልቋል።
አበርክቶ
ዜናነህ፣ በሙያው በትላልቆቹ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያገኘ ሰው ነው፡፡ አብዬ መንግሥቱ ለማ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሲያስተምሩ “ዜና ዜናነህ አነበበ ሲባል ዘመዳዊ ተሳቢ ነው” እያሉ ስሙን ይጠሩትና ያደንቁትም ነበር፡፡
ዜናነህ “ነፃነት” የተሰኘ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ጦርነት የኢትዮጵያ ጀግኖች የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚዘክር ታሪካዊ ልቦለድና በአዲስ አበባ ህይወት ላይ የሚያጠነጥን የመሀበረሰቡን አኗኗር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ “ከጣሪያው ስር” የተሰኘ ልቦለድን ለአንባቢያን እንካችሁ ብሏል። በ1999ዎቹ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ማለት ነው አሜሪካን ሀገር ያሳተመውና ወደ 30 የግጥም ስብስብን የያዘ “በረከተ መርገም”ን የሚሞግት “በረከተ ራዕይ” በሚል ርዕስ የግጥም ሲዲ አውጥቷል፡፡
"የመንገድ
ላይ ወግ" ኢትዮጲያን ወደ ኋላ ከሚጎትቷት ባሀርያት መካከል ቅናት ላይ የተሰራ ትያትርም ፅፏል። ዜናነህ በድርሰቶቹ ሀይማኖታዊ ፖለቲካዊና የፍትህ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡ ብዙዎቹ ስራዎችህ እንጉርጉሮ ይበዛባቸዋል ብለው ሲጠይቁት የኔ ስራዎች የማህበረሰቡ ቅጂዎች ናቸው
"ኑሮ
ካሉት
መቃብርም
ይሞቃል"
ከሚል
ማህበረሰብ
ወጥቼ
ከዚህ
የተለየ
ልፅፍ
አልችልም
ሲልም
ይደመጣል።
በ1975 ላይ ቤተሰብ ለመጠየቅ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ተጉዞ ነበርና የተወለደባት አዘዞ መብራት ስላልነበራት በወቅቱ ከነበሩ ሺህ አለቃ መላኩ ተፈራ ጋር ተነጋግሮ መብራትም አስበርቶ ዜናነህ መብራት አስበራልንም ተብሎ ይነገር ነበር። ዓለም በቃኝ በእስር ላይ እያለም ስፖርቱ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴዎች ያደርግ ነበር።
የትዳር ህይወት
ዜናነህ ትዳር የመሠረተው ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ነው። ከወይዘሮ አልማዝ ጥላሁን ጋር ትዳር መሰረተ፡፡ ገና ሚስት ሳያገባ ልጆች ብወልድ ስማቸውንም “ቢታንያ (ከሞት መዳን) እና ነፃነት (የመፀሀፌን ስያሜ) ለልጆቼ እሰጣቸዋለሁ ብሎ ያልም የነበረውን ለልጆቹ ስያሜ አድርጓል፡፡ አሁን ላይ የሦስት ሴት ልጆች አባት ሲሆን የመጀመሪያ ልጁ ቢታንያ 37 አመቷ የታሪክ ምሩቅ ነች፡፡ የ30 ዓመቷ ነጻነት ደግሞ ጎበዝ ተዋናይት ነች። ሶስተኛዋ ከፈረንጅ ሴት የተወለደችው የሩሲያ ዜግነት ያላት “ሩኒያ” ትባላለች፡፡
ከትዳር አጋሩ ጋር ለ5 ዓመት ያህል አብረው ከቆዩ በኋላ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ አሜሪካ ሄዳ እንድትኖር አደረገ። ከባለቤቱ ጋርም ርቀት ለያያቸው። በአንድ ሰው ደመወዝ የልጆችን ፍላጎት አሟልቶ ማስተማሩ እየከበደው ሲመጣ ከሀገር መውጣት ግዴታ ሆነበት፡፡ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ቦታውን ሲቆጣጠረው ወደ እስራኤል ሀገር ሄደ። ልጆቹ ገና የ2 እና የ3 ዓመት ህፃን ሳሉ ነበር እናታቸው ጥላቸው የሄደችው። እነርሱ ዛሬ የደረሱበት እንዲደርሱ ትልቅ ስራ ነበረበት፡፡
ዜናነህ አሜሪካን ሀገር ፣ጀርመን ከዚያም ወደ ስዊድን፣ ኖርዌይ ተዘዋውሯል፡፡ ኖርዌይ በነበረበት ጊዜም ሊደርሺፕን ተምሯል፡፡ ልጆቹንም በእነዚህ ሀገራት ልኮ ማስተማር ይችል ነበር፡፡ ስብእናቸው ላይ መስራትና በእንክብካቤው ስር እንዲያድጉ በመፈለጉ ነበር በእስራኤል እንዲያድጉ የወደደው።
ዜናነህ፤ ትምህርት ቤቱን ብቻ አምኖ የሚተው አባት ሳይሆን የልጆቹን የቀን ተቀን ህይወት የሚከታተልና ስለ ልጆቹም አብዝቶ የሚጨነቅ አባት ነበር። በጣም አስቸጋሪ የፈተና ግዜንም አሳልፏል። ልጆችን ያለ እናት ብቻውን የማሳደጉ ሀላፊነትም በጫንቃው ላይ አርፏል። ሌላ ማግባት ሳያምረው ልጆቹን በኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር አንፆ ያሳደገ እና የልጅ ልጅ ለማየትም የበቃ ጠንካራ ኢትዮጲያዊ አባትም ነው።
ህይወት ከሃገር ዉጭ
“አንተ ከአገርህ ልትወጣ ትችላለህ። አገር ግን ካንተ ውስጥ አትወጣም! ... እናም ኢትዮጵያ፤ አገሬ ሳልገባ አምላክ አይግደለኝ! “ሲል ይደመጣል፡፡ ዜናነህ መኮንን ከሀገሩ ወጥቶ ወደ እስራኤል ሃገር የተጓዘው በ1984 ዓ.ም አጋማሽ ነበር፡፡
ወደ እስራኤል ሀገር ከሄደ በኋላ ትምህርታዊ የሆኑ ፊልሞችን ዳይሬክት በማድረግ ሰርቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የ24 ሰዓት የግል ሬዲዮ ጣቢያ መስርቶ ይሰራ ነበር። በርካታ ሬዲዮ ጣቢያዎችን በማቋቋምና ወጣቶችን በማሰልጠን ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ወጣቶችንም ማፍራት ችሏል።
በኋላም በ1991 አካባቢ ወደ አሜሪካም አቅንቶ ነበር። አሜሪካንም እንዳሰበውና እንደጠበቀው ስላላገኘው 9ወር አካባቢ እንደተቀመጠ ወደ ኖርዌይ ሄዶ በሊደር ሺፕ ተምሮ ተመርቋል። ከዚያ ወደ ልጆቹ ወደ እስራኤል ሀገር ተመልሷል። እስራኤል ሀገርም በርካታ ኮርሶችን ወስዷል።
እስራኤል ሀገር መኖሬ ምርጫ ሳይሆን የፈጣሪ ፍቃድ ነው ብሎ ያምናል። እስራኤል የአለም ማእከል ነችና በየግዜው ህይወት አለ ፤ዜና አለ ፤የፈጣሪን መኖር እንዳረጋግጥ አድርጎኛልና እስራኤል ለእኔ መማሪያ ትምህርት ቤቴ ነች ይላል።
እስራኤል ሀገር ከገባ በኋላ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ አካዳሚክ የሆኑና የፍልስፍና መፀሃፍትን ማንበቡን የሚያስታውሰው ዜናነህ በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜን ጠብቆ ከልጆቹ ጋር የሚወያይበትና መፀሀፍ ቅዱስን የሚያነብላቸው ቀን እንዳለው ይናገራል፡፡
ዜናነህ በዚህ በ30 ዓመት ጉዞ ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በርካታ የራዲዮና የቴሌቪዥን አስተማሪ ፕሮግራሞችን መስራት የቻለ ጠንካራና ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነው።
“ጋዜጠኛ ጡረታ አይወጣም” በሚል ንግግሩ የሚታወቀው ዜናነህ አሁንም የጀርመን ራዲዮ ጣቢያ (ዶቼዌሌ) የመካከለኛው ምስራቅ ዘጋቢ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ሶስት መንግስታትን በጋዜጠኝነት ህይወት የኖረዉ ዜናነህ አሁን ሀገራችን ያለችበትን ለውጥ ይደግፋል፡፡ ነገር ግን ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድታድግ ማህበረሰቡ እንደገና መወለድ አለበት የሚል እምነትም አለው። ወደ ፊት ሀገሩ ትልቅ ተስፋ እንዳላት አድርጎ ያስባል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ትክክለኛነትን የሚያሳዩ ሞዴል የሚሆኑ ባለሙያዎችም እንደሚያስፈልጓት ይናገራል፡፡አሁንም ኑሮውን በእስራኤል አድርጎ በሶሻል ሚዲያ ላይ ድምፅ ላነሳቸው ድምፅ እየሆነም ይገኛል።
የዜናነህ አንዳንድ ትዝታዎች
ዜና ነህ መኮንን እንደሚያስታውሰው ማእከላዊ እስር ቤት ሳለ ደርግ እነ ሃይሌፊዳ ዶ/ር ንግስት አዳነን በህይወት እንደሌሉ እየታወቀ ለምርመራ ስማቸውን ሲጠራ ይገርመው ነበር፡፡ እነ ሀይሌ እና ንግስት ተገድለው ሳለ ነገር ግን ይህ በደርጎች ሳይታወቅ ስማቸው ይጠራ ነበር፡፡
ታዲያ በዚያን ጊዜ ዜናነህ ደርጎች ያሰሩትን አያውቁም እንዴ ?ያለ በት ጊዜ ነበር፡፡
የኢህአፓው ብርሃነ መስቀልም እዛው ማእከላዊ ታስሮ ነበር ትዝ ይለዋል፡፡
ዜናነህ ኩላሊት ባይኖረኝም ለሃገሬ የምሰጣት ልብ አለኝ ይላል፡፡ ይህን ከአንድ ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለመጠየቅ የተናገረው ነው፡፡
አንድ ወቅት ዜናነህ ኖርዌይ ሳለ መፅሀፍ መሸጫ ገብቶ አንዳንድ ኖት ይወስዳል፡፡ ታድያ ኦስሎ መፅሃፍት መሸጫ ገብቶ እያነበበ ማስታወሻ ሲፅፍ ወደ 7 ፖሊሶች ከበቡት፡፡ ምን ወንጀል ሰራሁ ሲል መፅሃፍ እያነበብክ ማስታወሻ መያዝህ ነው አሉት፡፡ እሺ ብሎ ይቅርታ ያደርጉልኛል ሲል አላደረጉለትም፡፡
ዜናነህ
ስለዚህ
ጉዳይ
ሲያስታውስ
‹‹ ከዚህ
በፊት
የነበረ
ማስታወሻ
የያዝኩትን
ሁሉ ከዚህ መፅሃፍት መደብር አለመሆኑን እየነገርኳቸው ማስታወሻዬን ወረሱት፡፡ ስፍራው የሰላም የኖቤል ሽልማት ከሚሰጥበት ኦስሎ ከተማ ህንፃ ፊት ለፊት ከፓርላማው አጠገብ ነው›› ብሎ ትዝታውን አውግቶናል፡፡
መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
ዜናነህ መኮንን በዚያ ሞገስ ባለው ድምጹ መረጃ ሲያቀብል ከብዙዎች ከበሬታን ማትረፍ ችሏል፡፡ ዜናነህ ዜና አንባቢ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ጉዳዮች ላይ መጽሀፍትን የሚያነብ በሳል ነው፡፡ ዜናነህ ከማንበቡ በፊት ጉዳዩ ላይ ቀድሞ ጥልቅ ግንዛቤ ይይዛል፡፡ ከዚያም በሚነበበው ጉዳይ ላይ ነፍስ ይዘራበታል፡፡ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ የነበርን የቲቪ እና የሬድዮ ዜና አድማጭ ተመልካቾች ዜናነህ ልንረሳው አንችልም፡፡ ዘመኑን ሊከስትልን በሚችል መልኩ አንድ ትዝታ አእምሯን ላይ ጥሎ ነበር፡፡ ዜናነህ እንዲሁ አንብብ የተባለውን ዜና የሚያነብ ሳይሆን ይልቁንም ካላመነበት እንዲህ ተብሎ መነበብ የለበትም ብሎ ክርክር የሚገጥም በሳል አንባቢ መሆኑ በብዙዎች ይመሰከርለታል፡፡ይህ ጠያቂነቱና በምክንያት ማመኑ ገና በወጣትነቱ የጀመረ ነበር፡፡ ላመነበት ነገር ፊት ለፊት ይገጥማል፡፡ ያላመነበት ነገርን ደግሞ እንደዋዛ የሚቀበል ሰው አልነበረም፡፡ ዜና ነህ በኢትዮጵያ የዜና አንከሮች ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያስቀመጠ መሆኑ ይመሰከርለታል፡፡
እርሱ
በእውቀት
ላይ ተመስርቶ ስለሚሰራ የሚያነባቸው ዜናዎች ወደ እውነት የተቃረቡ ነበሩ፡፡ ዜናነህ ጎበዝ አንባቢ ስለነበር፤ ያነበበውን ደግሞ ስለሚያካፍል ይህም ትልቅ ርካታ ይሰጠዋል፡፡ ለህትመት ያበቃቸው መጽሀፎቹ ጥልቅ አንባቢነቱን የሚነግሩን ናቸው፡፡ ዜናነህ ለሀገሩ ያለውም ፍቅር ጥልቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ አይተን ይህ ጠንካራ ሰው ለትውልዱ ታሪኩ ያስተምራል ብለን ስላመንን እነሆ ዜናነህን እናውቀው ዘንድ ሰንደነዋል፡፡ ዜናነህ ዛሬም ከሚኖርበት እስራኤል ሆኖ ብዙ ሀሳቦችን ያካፍላል፡፡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ መደረግ አለበት ብሎ በሚያምነው ነጥብ ላይ ቃለ-ምልልሶችን ይሰጣል፡፡ በዚህም ለሀገሩ ያለውን ተቆርቋሪነት በአቅሙ ያሳያል፡፡ ዜናነህ መኮንን ለኢትዮጵያ ሚድያ ለዋልከው ውለታ እናመሰግናለን፡፡
መልካም
የስራ
ዘመን
ብለን
አክብሮታችንን
መግለጽ
እንወዳለን፡፡/
ይህ የዊኪፒዲያ ግለ-ታሪክ በዘቢባ ሁሴን እና በእዝራ እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን ዛሬ ህዳር 28
2014 በተወዳጅ
ሚድያ
የፌስ
ቡክ ገጽ እና በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም
በየጊዜው
ይወጣል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ