24. የሸዋ ማስረሻ Yeshewa Masressha
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 10 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል የሸዋ ማስረሻ ትጠቀሳለች፡፡
ከልጅነት እድሜዋ አንስቶ በምትወደው ሙያ ውስጥ በደስታ መቆየቷን ያዩ ህልሟን የኖረች ሲሉ የሸዋን ይገልጿታል፡፡ ለጋዜጠኝነት ልዩ ፍቅር ያላት የሸዋ ማስረሻ ጋዜጠኝነትን እንጀራዬ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን የማገዝና የመርዳት ሰብአዊ ፍላጎቴን የምወጣበት መሳሪያዬ ጭምር ነው ብላ ታምናለች፡፡ ዘውትር ከአዳዲስ እውቀቶችጋ የሚያገናኘው ጋዜጠኝነት ህይወትን አሰልቺ ከማድረግ የሚታደግም ነውና ሁኔታዎች ቢፈቅዱ ሁሌም ብኖርበት ብላ ትመኛለች፡፡
የህክምና ባለሙያ የሆኑት አባትዋ ማስረሻ አገርግዛት ለስራ ወደ ጎንደር ደብረታቦር አቅንተው በነበረበት ወቅት እዛው የተወለደችዉ የሸዋ በ 6 አመቷ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣችው፡፡ የጋዜጠኝነት ህይወት ጅማሬዋ ብዙ የራቀ አልነበረም፡፡
ትምህርት
ለሴት ልጅ ከሌሎች ጋር ጥሩ መወዳደሪያዋ ትምህርት መሆን አለበት፤ ቤተሰቦቼም በቁስ የሚለካ ሃብትን ሳይሆን ተምሮ መለወጥን ነዉ ያወረሱኝ የምትለው የሸዋ ማስረሻ የትምህርትና የስራ ህይወቷን ጎን ለጎን ማስኬድ የቻለች ናት፡፡
- በአብዮት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሳለች በቴአትርና ስነጽሁፍ ክበብ መሳተፍ የጀመረች ሲሆን ገና በ 14 አመቷ የ 8ኛ ክፍል ተማሪ ሆና በያኔዉ ሬድዮ ፋና "የከርሞ ሰዉ"የልጆች ፕሮግራም ላይ በጋዜጠኝነት ትሠራ ነበር፡፡
- በምስራቅ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ4 አመት ቆይታዋን በሚኒሚዲያ ክለብ ውስጥ በሃላፊነት ስትሠራ ቆይታ ኮከብ ጋዜጠኛ በመሆን ተሸልማ ነው ያጠናቀቀችው፡፡
- የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአ.አ.ዩ በስነጽሁፍና ቋንቋ ስትከታተል ከባህል ማዕከል የስነ-ጽሁፍ ምሽት ተሳትፎዋ በተጨማሪ በለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ በአንባቢነት ሰርታለች፡፡
- የሁለተኛ ዲግሪዋን (ማስተርሷን) በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ያጠናቀቀችውም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስራ ላይ ሆና ነበር፡፡ የ2ኛ ዲግሪዋ የመመረቂያ ወረቀት ርእስ የደቡብ ሱዳንን ግጭት ሚድያዎች እንዴት ዘገቡት የሚል ነበር፡፡
የስራ ህይወት
የሸዋ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ሆና መስራት የጀመረችዉ በዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም በ1998 ዓ.ም ላይ ነበር፡፡ በጣቢያው እስከ ኤዲተርነት ደረጃ ያገለገለች ሲሆን ዛሚ ከፍተኛ የጋዜጠኝነትን ልምድ የቀሰመችበት፣ከአድማጮች ጋር የተዋወቀችበትና የማህበረሰቡን ችግር በቻሉት የመቅረፍን እድል ያገኘችበት ቤቷ ነበር፡፡ እዚህ ጋር ለጣቢያዉ መስራችና ባለቤት ለጋዜጠኛ ሚሚ ስብሐቱ ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡ ዛሚ በመስራቷ ከ2002ዓ.ም አንስቶ እስካሁን እየሰራችበት የምትገኘዉን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስትቀላቀልም በጥሩ ብቃት ስራዋን ለመቀጠል አላዳገታትም፡፡
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከ7 አመታት በላይ በሬድዮ ጋዜጠኝነት ከሰራች በኃላ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲከፈት ወደዛው ተዘዋውራለች፡፡ 7 አመታት በሬድዮ ጋዜጠኝነት በሰራችባቸው ጊዜያት ከጣቢያው ጋር በትብብር የሚሰሩ ፕሮግራሞችን በጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመስራት ትታወቃለች፡፡በሴቶች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ መሰናዶዎች፤ማህበራዊ ዋስትና በሚል ርእስም ለዘመታት የቆየ ፕሮግራምን አየር ላይ በማዋል ትታወቃለች፡፡ በሬድዮ ጋዜጠኝነት ቆይታዋ አዘውትራ ከምትሰራቸው ዜናና ፕሮግራሞች በተጨማሪ “120 ደቂቃ"ን የመሣሠሉ የሬድዮ ቀጥታ ስርጭቶችን የመራች ሲሆን በተለይም “እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?"
በተሰኘው
አሳታፊ
የቀጥታ
የስልክ
ዉይይት
ፕሮግራም
በበሣልና
ሚዛናዊ
አወያይነቷ
ብዙዎች
ያውቋታል፡፡
በአሁኑ ወቅት “በፋና 90" አዘጋጅነትና አቅራቢነት እና በዜና አንባቢነት እየሰራች የምትገኘዉ የሸዋ ለዜናና ፕሮግራም ሊሆኑ ይችላሉ ተብለዉ የማይታሰቡ ጉዳዮችን በማንሳትና በልዩ አቀራረብ ጭምር ለተመልካች በማቅረብ ትታወቃለች፡፡እሷም “ለሰዉ ቅርብ የሆኑ ጉዳዮችን ማቅረብ እወዳለሁ" ትላለች፡፡ በጣቢያዉ ከከፍተኛ ሪፖርተርነት ተነስታ ረዳት ዋና አዘጋጅ የስራ መደብ ላይ የደረሰችዉ የሸዋ በፋና ሬድዮ ይተላለፍ በነበረዉ ትናንሽ ጸሀዮች (እማማ ጨቤ) ድራማ ላይ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም “ቃልዬ" የተባለችዉን ገጸ ባህሪ ወክላ በመተወን አድንቆትን አትርፋለች እንዲሁም አጭር የቴሌቪዥን ድራማ ላይም ተሳትፋለች፡፡ ጋዜጠኝነትና ትወና እምብዛም አብረው ስለማይሄዱ በትወናው ብዙም ያልገፋችበት የሸዋ በተለይ ከሙያዋጋ የተያያዘና ጠንካራ ሴት ገጸ ባህሪ የምትወክልበት ፊልም ካገኘሁ ግን የመስራት ፍላጎት አለኝ ትላለች፡፡ የሸዋ ማስረሻ እንደ ሬድዮ ጋዜጠኛ ለሬድዮ የሚመጥን ድምጽ በተፈጥሮ የተቸረች በመሆኑ ይህንንም በሚገባ ጥቅም ላይ አውላዋለች፡፡ ለቲቪ የሚሆን ሰብእና የተላበሰች በመሆኑም 90 ደቂቃን ስትመራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ስለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
የመድረክ መሪነት ስራ
መድረክ መሪነት(Master of Ceremony) የየሸዋ ማስረሻ ሌላኛዉ መገለጫዋ ነው፡፡ ከስራዋ ጎን ለጎን በርካታ ትላልቅ መድረኮችን በብቃትና በእውቀት ላይ በተመሰረተ አቀራረብ መርታለች፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ፡-
- በ UNDP አዘጋጅነት በሞያሌ ድንበር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያለመ፣ የኬንያና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሃላፊዎች የተገኙበት (Regional Conference on Sustainable Peace for the Cross
border Communities of Moyale) መድረክ
- የሲቪክ ማህበራት ላይ ያተኮረ (National Civic engagement policy validation workshop)
- ለ3 ተከታታይ አመታት በዋልታ ኢንፎርሜሽን የተዘጋጁ ብሄራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን (በአ.አ ስታዲየም)
- በአፋር ሰመራና በአ/አ ከተማ በፌደሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት የተዘጋጀ የብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች በዐላት ይገኙበታል፡፡
ዝንባሌዎች
የሸዋ ከሌሎች ህዝቦች ባህልና እሴቶችጋ የሚያስተዋውቁ ጉብኝቶችን ትወዳለች፡፡“ከመልክአ ምድርና ሰው ሰራሽ ግንባታዎች የበለጠ የሰዎች አኗኗርና ባህል የበለጠ ይስበኛል"
ትላለች፡፡
በስራ
አጋጣሚ
በአብዛኛዉ
የአገሯ
ክፍል
የመገኘት
እድል
ገጥሟታል፡፡
ተራራ
መውጣትን
(Hiking) የመሳሰሉ
እንቅስቃሴዎች
ላይ መሳተፍ ትወዳለች፡፡ ደም መለገስን በመሳሰሉት በጎ ተግባሮች የምትሳተፈው የሸዋ “የበጎ አድራጎት ስራ የሁሌም ዝንባሌዬ የሆነ ግን ደግሞ ያሰብኩትን ያህል ያልተራመድኩበት ዝንባሌዬ ነዉና ትልቁ የቤት ስራዬ ነዉ" ትላለች፡፡
እንደማጠቃለያ
ባለትዳርና የመንታ(ሴትና ወንድ) እናት የሆነችው የሸዋ ማስረሻ ካላት የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ አንጻር በርካቶች ከጋዜጠኝነት ውጪ ብትሰማራ የተሻለ ገቢን እንደምታገኝ በመንገር ቢሞግቷትም፣ የአገሪቱ የፕሬስ ነጻነት ነገርም ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ቢኖሩትም ቢሳካላት እስከመጨረሻዉ በሙያዉ ውስጥ መቆየትን ትመርጣለች፡፡ በሙያዋ ጥሩ ስምን መትከልና ሌሎችንም ማገዝ የምትፈልገዉ የሸዋ ይህ የዊኪፒዲያ ገጽ ጨምሮ ለታሪክ የሚበቃ የሚነገርልኝ የምረካበት ስራ ገና አልሰራሁም ብላ ታምናለች፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ