23. ያሬድ ብርሃኑ ጌታሁን  Yared Berehanu Getahun

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ትርጉም ያለው ለውጥ  ያመጡ ሰዎችን ታሪክ በመሰነድ ላይ  ይገኛል፡፡ያሬድ ብርሀኑ በሚድያው ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የራሱን አሻራ ከማሳረፍ በዘለለ የበጎ አድራጎት ማህበርንም ለማቋቋም የቻለ ነው፡፡ በጥረት  አንድ ቦታ መድረስ እንደሚቻል ስላስመሰከረው ያሬድ ብርሀኑ ቤርሳቤህ ጌቴ ያሰናዳችው የግለ-ታሪክ ጽሁፍ እናንብብ፡፡

 

መምህር ያሬድ ብርሃኑ ጌታሁን ይባላል፡፡ በሐምሌ 24 1979 . ነበር በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ አዲሱ ገበያ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን  አካባቢ የተወለደው፡፡

 

1979 . ሐምሌ 24 ቀን ለወይዘሮ ጠጅነሽ ፈታኝ ምጥን አስከትሎ ነበር ይህችን አለም የተቀላቀለው።ለቤተሰቡ ብቸኛ ወንድ ልጅ ሲሆን ሁለት እህቶችም አሉት፡፡ የቅዱስ ያሬድን ስም በማግኘቱ ይኮራል ''እንኳንም እነሱ አስቀድሞ ገብቷቸው ያሬድ አሉኝ እንጂ እኔም ከያሬድ ውጪ መጠሪያ ስሜ እንዲሆን ባለመፍቀድ ሌላ ስም ሰጥተውኝ ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያው ሥራዬ የማደርገው ስሜን በፍርድ ቤት ማስቀየር ነበረ'' ብሎናል፡፡

 

ልጅነቱ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ የጨዋታ የቡረቃ ግዜ ነበር። በተለይ እግር ኳስ ጨዋታ በጣም ይወድ ስለነበር የእግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አሳድሮበት ነበረ።

 

መምህር ያሬድ የፊደል ቆጠራን የጀመረው ከየኔታ ዘንድ ሲሆን እስከ መልክተ- ዮሐንስ ከደረሰ በኋላ 1987 . በላይ ዘለቀ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመደበኛ ትምህርት ጀመረ።በላይ ዘለቀ በኢኮኖሚ አነስተኛ አቅም ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች ወይም የደሀ ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበር የያሬድም ቤተሰቦች ተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነበሩና እዛ እንዲማር አድርገውታል፡፡

 

         በላይ ዘለቀ በያሬድ ትውስታ እንዲህ ይገለፃል:-

 

'' በላይ ዘለቀ ጥቂት የነጠቁ እና የመጠቁ ጀግና ተማሪዎች የሚወጡበት የድሆች መማርያ በልዩ ስሙ ወልዶ መጣያ ይባል ነበረ፡፡ በኔ ዘመን ዙሪያውን አጥር የለውም ወና ነበር ወደቤት ለመሄድ ከፈለጋችሁ አስተማሪ ማስፈቀድ አይጠበቅባችሁም የልብ ፈቃድ በቂ ነው ተነስታችሁ እብስ ነው፡፡ የትሄዳችሁ የሚል አስተማሪ  ያለ መስሏችሁ 110 በክፍል ውስጥ ታጭቀን እየተማርን በአመቱም አስተማሪው ካወቋችሁ እናንተ ቀለሜ ተማሪ ናችሁ ማለት ነው፡፡

 

በቃ በላይ ዘለቀ ነጻ የሆነ ምድረ በዳ ነው ኮርኒስ የሌላቸው በቦንዳ ጣሪያቸው የታሰረ በብሎኬት የተሰራ ግድግዳ የተቦረቦረ ወይም ቀዳዳ ያለው ብርድ የሚያስገባ መስኮት እና ብሎኬት ማየት የተለመደ ነው ተጽፎ የማያልቅበት ጥቁር ሰሌዳ ላይ ገብቶ የሚለቀልቅ አስተማሪ ከመገልበጥ ይልቅ በቅጡ ሳንረዳ የተማርን ይሁን የተመላለስን ዛሬ ሳስበው ይገርመኛል፡፡በእረፍት ሰዓት ውኃ ለመጠጣት በቂ ባለመሆኑ ወደ መንደር ውስጥ እየገባን ሁሉ ከጓደኞቼ ጋር ከሰው ቤት ለምነን እንጠጣ ነበር፡፡ የማረሳው አጋጣሚም ውኃ ለመጠጣት ብዬ ከጓደኛዬ ጋር ወደ አንድ ግቢ ስንገባ ውሻ አባሮኝ የሳማ ቅጠል ውስጥ የገባሁበትን አጋጣሚ እና በሳማ የተለበለብኩበትን ታሪክ ያስታውሰኛል'' ሲል የልጅነት ትዝታውን አጫውቶናል፡፡

 

በአንደኛ ደረጃ ትምህርቱ ከማይረሳቸው ትምህርቶች መካከል እርሻ ኑሮ በዘዴ እና እጅ ስራ የሚባሉ ትምህርቶችን ሲሆን በበላይ ዘለቀ በነበረው 8 ዓመት ቆይታ ኳስ ተጨዋች ለመሆን የነበረውን ፍላጎት ለማሳካት የትምህርት ቤቱም ሜዳ ሰፊ ነበረና  ኳስ አብዝቶ እንዲጫወት እድል ፈጥሮለታ ነገር ግን የትምህርት ግዜውን እስኪሻማበት አድርሶት እንደነበረ አይዘነጋውም።

 

''ለዘመኑ ልጆች በረባሶ የሚባል ከመኪና ጎማ የሚሰራ 50 ሳንቲም ጀምሮ እስከ 2.50 ብር 1-7 ክፍል ያደረኩት ጫማ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሸራ ጫማ ያደረኩት እና ፎቅ ላይ የወጣሁት ከተጫወትንበት ሜዳ ላይ መሬቱ ተቀንሶ በተሰራው ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃ ነው፡፡ ያኔ የነበረኝ ፍርሀት  ፎቢያ ዛሬም በድልድይ ላይ መሻገር አልወድም ፡፡ሁለተኛው በልጅነት አእምሮዬ ከኛ በክፍል የሚበልጡን ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በእርሻ ትምህርት የሚተክሏቸው ጎመን እና ካሮት  አሁን ላይ ጎመን ለመውደዴ መነሻ ሳይሆኑ አይቀሩም ''፡፡

 

በትምህርቱ መካከለኛ የሚባል ተማሪ የነበርው ያሬድ ብርሀኑ በተለይ እንግሊዝኛ ሂሳብ የማይወዳቸው የትምህርት አይነቶች እንደነበሩ ያስታውሳል። ሆኖም ለታሪክ እና ለጆግራፊ ትምህርት ልዩ ፍቅር ነበረው። የስምንተኛ ክፍል (ሚንስትሪ) 1993 . ወስዶ ወደ 9 ከፍል በማለፍ ድል በር የተባለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቷል። ድል በር 1994 . ነበር የተከፈተው።

 

የድል በር /ቤት እንደቀድሞ የተንጣለለ ሜዳ ያለበት ሳይሆን ዘመናዊ እና የተዋበ ህንጻ ያለበት መሆኑ  ኳስ ተጨዋች የመሆን ፍላጎቱን በመቀየር ወደ ሚኒ ሚዲያ እንዲገባ ገፍቶታል። ''ከበላይ ዘለቀ አብሮኝ የመጣው የክፍላችን ጎበዙ ተማሪ በረፍት ሰዓት ስንገናኝ የነሱ ስም ጠሪ ነበረ እና የሚኒ ሚዲያው ተወካይ ተሰጦዖ ላላቸው ልጆች ንገሩ ያላቸው ጓደኛዬ መጥቶ አንተ ልጅ የተደበቀ የጋዜጠኝነት ዝንባሌ አለህ ብሉ የተደበቀውን የጥበብ ፍላጎቴን ቀሰቀሰብኝ እና ተመዘገብኩ''፡፡ በዛን ወቅት ሀሙስን ላንዳፍታ የሚል ፕሮራም በማቅረብ በውስጡ የነበረውን የጋዜጠኝነት ፍላጎት እንዳገኘው ያምናል።  ''

 

የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎች በመውሰድ እውቀቱን እንዳዳበረው የሚናገረው ያሬድ  በዚህ መሐል ግን ለትምህርቱ  ትኩረት ባለመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ 9 ክፍልን ደግሞ እንዲማር ሆነ ''ከዛ በጣም አዘንኩ በሚቀጥለው ዓመት እልህ ይዞኝ 9 ክፍልን 10 ወጥቼ ወደ 10 ክፍል ተሻገርኩ''ይላል፡፡

 

አስረኛ ክፍል ያመጣው ውጤት ለቴክኒክና ሙያ የሚያስገባ ሲሆን የጋዜጠኝነት ፍላጎቱን ለማርካት በግሉ የጋዜጠኝነት ትምህርት ለመማር ኢዛ የጋዜጠኝነት እና የሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋማ በመግባት ጋዜጠኝነትን በሠርተፍኬት ተማረ። ጎን ለጎንም  በአዲስ አበባ የመገነናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ለአንድ ዓመት በተለማማጅ ጋዜጠኝነት እየሰራ ቆየ። 10 ክፍል ውጤቱን ለማሻሻል  ደግሞ በግል ኮሌጅ በመግባት ህግ በመማር ከፕሪቶር ሕግ የኮሌጅ 2002 . በዲፕሎማ ተመረቅኩ፡፡ በዛው ዓመት እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ደግሞ የሙዚቃ ትምህርት በመጀመር በሙዚቃ ዲፕሎማ ተመረቀ፡፡ በጋዜጠኝነቱ ሙያ ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ በኋላ ወደ ዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 በመሻገር ለአንድ ዓመት ጤና ይስጥልኝ የተባለ የጤና ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ በመሆን ሰርቷል፡፡ በመቀጠል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኀበር የገንዘብ ድጋፍ ፍጥጫ የተባለ የወጣቶች የሬድዮ ፕሮግራም 5 ወር በኢትዮጵያ ሬድዮ በዋና አዘጋጅነት ያቀርብ ነበር በፋና ሬድዮ( 98.1 ) ፍጥጫን ስሙን ማለዳ ብሎ በመቀየር በፋና 98.1 ዘወትር ሀሙስ ከረፋዱ 400 ጀምሮ 2 ዓመት እያዘጋጀ አቅርቧል።

 

በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኀበር በየ ሶስት ወሩ የሚዘጋጅ ‹‹ጸዳል›› የተሰኘ የወጣቶች ጋዜጣ 8 ዕትም በዋና አዘጋጅነት የሰራው ያሬድ ብርሀኑ ፡ወርልድ ዋይድ ኦርፋንስ ፋውንዴሽን የተባለ ድርጅት 4 ዓመት በትርፍ ጊዜ ሥራ በህጻናት ፕሮጀክታቸው ላይ በኮርድኔተርነት በወር 500 ብር እየተከፈለው መስራቱን አይዘነጋውም፡፡ 'ከዛ' በመቀጠል ወደ መንፈሳዊው መንገድ በመመለስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ 2005 እስከ 2008 . ድረስ 4 ዓመት በቀን የትምህርት መርሐ ግብር በስነ-መለኮት ትምህርት በመማር 2008 . በዲግሪ ተመርቄያለሁ''፡፡  በመንፈሳዊው አገልግሎት  በክራር ከዛማሪያን ጋር በአዲስ አበባም ሆነ በክፍለ ሀገር እየተዘዋወረ የሚያገለግለው መምህር ያሬድ 2007 . በጀመረው የብርሃን ልጆች የተሰኘ የፌስ ቡክ መጽሔት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ይሰራ ነበር ለአብነት ያክል 2008 . ከስነ-መለኮት ትምህርት እንደተመረቀ በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ለሚገኙ 50 ህጻናት ቦርሳና አንድ ደርዘን ደብተር 20 አረጋውያን ብርድ ልብስ 10 አረጋውያን ጋቢ

 

በመስጠት በምርቃቱ ቀን 80 ሰዎች ድጋፍ በማድረግ የጀመረውን የበጎ ስራ  ከጊዜ ወደጊዜ እያሳደገ የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃን በድጋፍ እና የልደት(ገና) በዓልን 2009 . በሬ በማረድ የምሳ መርሐ ግብር በመዘጋጀት ከነሱ ጋር የማሳለፍ ልምድ ነበረው፡፡ በመቀጠል በጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ለዳግማ ትንሳኤ በዓል ድጋፍ በማሰባሰብ 32 ፍራሾችን በማሰራት እና የምሳ ግብዣ በማድረግ በጣም የተሳካ ጊዜ አሳልፏል፡፡ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ ለሀዋሳ የአረጋውያን መንደር የሚውል 13 ፍራሽ እና 657 መጽሐፍም አበርክቷል፡፡ በሜሪ ጆይ ኢትጵያ ህዝብ ግንኙነት ሆኖ በተቀጠረበት 1 ዓመት ቆይታ  ዶክመንታሪዎችን የቴሌቪዥን ፕሮግራም እና ማስታወቂያዎችን በመስራት ስራውን በሙያው ደግፏል፡፡

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት በተባባሪ ፕሮግራም አቅራቢነት በፕሮፖዛል ተወዳድሮ በማሸነፍ 2012 ታህሳስ 05 እስከ ግንቦት 30/2012 ድረስ 6 ወር ዘወትር እሁድ ከረፋዱ 500 እስከ 600 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የአንድ ሰዓት የቴሌቪዥን ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብር በዋና አዘጋጅነት ሲሰራም ቆይቷል፡፡

 

መዝጊያ

 

የብርሃን ልጆች የህጻናት እና የአረጋውያን መንደር የተሰኘ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሀምሌ 03/11/2012 . ጀምሮ በማቋቋም በመስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅነት እየሰራሁ የሚገኘው መምህር ያሬድ ብርሀኑ ዘንድሮ በመስከረም 29/01/2014 . ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በድግሪ ተመርቋል።በጥር ወር  ጋብቻ ለመፈጸምም በዝግጅት ላይ ይገኛል።

 

ጉዞ ይቀጥላል…..የብርሃን ልጆች የቴሌቪዥን ጣቢያየብርሃን ልጆች ሁሉን አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት…..የብርሃን ልጆች መንፈሳዊ እና ስነ-ልቦናዊ የጋብቻ የማማከር አገልግሎት ድርጅት በቀሪው ዘመኑ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማሳካት የሚፈልጋቸው ዕቅዶቹ ናቸው፡፡

 

ያሬድ ብርሀኑ ወጣት ነው፡፡ በዚህ የወጣትነት እድሜው  በሚድያ ሙያ አንድ ሚና አበርክቶ ለማለፍ የራሱን ትልቅ ጥረት ያደርጋል፡፡

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች