48.Ellene
Mocria Weldeselassie
የመጀመሪያዋ
ሴት ቲቪ
አቅራቢ
እሌኒ መኩሪያ ወልደስላሴ - Ellene Mocria Weldeselassie
- ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ ለወጣት ለአዛውንት የሚመቹ ደግ እናት፡፡ በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ ስም ያተረፉ፡፡ ለምርምር የማይደክሙ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እነሆ ታሪካቸውን አቀረበ፡፡ ጋዜጠኛዋ በ79 አመታቸው ሀምሌ 14 2013 ህይወታቸው አልፏል፡፡ ታሪካቸው ግን አለ፡፡
የልጅነት
ዘመናቸው በደስታ የተሞላ
ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ በ1934 አመተ ምህረት ከአባታቸው ከአቶ መኩሪያ ወልደስላሴ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሶስና ወርቅነህ ተወለዱ፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ሶስና ወርቅነህ የሀኪም ወርቅነህ እሸቴ ልጅ ናቸው፡፡ ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሳንፎርድ ተማሪ ቤት ነበር የተከታተሉት፡፡ ወይዘሮ እሌኒ ያደጉት ካዛንቺስ አካባቢ ሲሆን የልጅነት ዘመናቸው በደስታ የተሞላ ነበር፡፡ በተለይ በሳንፎርድ ተማሪ ቤት ጥሩ የእንግሊዝኛ ችሎታቸውን ከማዳበራቸው በላይ ደስ የሚል የመዝናኛ ጊዜን አሳለፈው ነበር፡፡ ቴኒስ መጫወት ፤ ዋና መዋኘት ፣ ቴአትር ማየት እና መተወን ደስ ይላቸው ነበር፡፡ እንዲያውም ለልኡል መኮንን ሆስፒታል ማሰሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ቴአትር መስራታቸውን ወይዘሮ እሌኒ በህይወት በነበሩ ጊዜ ተናግረዋል፡፡ በተለይ አያታቸው ክቡር ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ ዳንስ ያለማምዷቸው እንደነበር አይዘነጉትም፡፡
ብስራተ
ወንጌል ሬድዮ
ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ ፣ ማህበራዊ ሳይንስ የማጥናት ግብ ቢኖራቸውም ቤሩት የነጻ የትምህርት እድል አግኝተው ወደዚያ በ1951 ግድም ያቀናሉ፡፡ ነገር ግን የነርስነትን ትምህርት ቢጀምሩም አቋርጠው ወደ እናት ሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ በመቀጠልም ወደ ብስራተ ወንጌል ሬድዮ በማቅናት በእንግሊዝኛው ክፍል ተቀጠሩ፡፡ ያኔ በሬድዮ ከወይዘሮ እሌኒ ጋር ይሰሩ ከነበሩት ባለሙያዎች መካከልም ጋዜጠኛ ልኡልሰገድ ኩምሳ ይጠቀሳል፡፡ ወይዘሮ እሌኒና ጋዜጠኛ ልኡልሰገድ ዜና ሲያቀርቡ ያለበት ቪድዮ ከዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ዘንድ ይገኛል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር በግንቦት 18 1955 ሲፈረም ጋዜጠኛ ከነበሩት መካከል ወይዘሮ እሌኒ ይጠቀሳሉ፡፡ በወቅቱ ገና የ21 አመት ወጣት የነበሩት ወይዘሮ እሌኒ መሪዎች ሲመጡ የተደረገውን ታሪካዊ አቀባበል በፍጹም አይዘነጉትም፡፡
ቲቪ
ቲቪ በ1950ዎቹ እንደ ብርቅ በሚታይበት ዘመን በ1957 አ.ም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተከፈተ፡፡ ታዲያ የመጀመሪያዋ የቲቪ ሴት አንባቢ የነበሩት ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ ወልደስላሴ ነበሩ፡፡ ይህ ለወይዘሮ እሌኒ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ በወቅቱ ሳሙኤል ፈረንጅ አንዱ ወንድ ተናጋሪ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ በጋዜጠኝነቱና በህዝብ ግንኙነት ሙያ ያገለገሉት ወይዘሮ እሌኒ ከሰው ጋር በቀላሉ የሚግባቡ ተወዳጅ ደግ እናት ነበሩ፡፡ በበጎ አድራጎት ምግባራቸው በስፋት የሚታወቁት ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ ወልደስላሴ የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ማህበሩን ረድተዋል፡፡ በተጨማሪም በአንሚ ሬድዮ ከ20 አመት በፊት ያገለገሉት ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ ወልደስላሴ ከአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት ነበራቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ወደ ሀገራችን በሚመጡበት ጊዜ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ስራ ላይ ትልቅ ሚና አበርክተዋል፡፡
ለዛፎች ልዩ ፍቅር ያላቸው
ቤታቸው ሲኬድ ሁልጊዜም ከአረንጓዴ ተክል ጋር የማይታጡት ወይዘሮ እሌኒ ነፋሻማ ቦታ ልዩ ትርጉም ይሰጣቸዋል፡፡ አንድ ከዛፍ ጋር በተያያዘ በፎቶግራፍ የታገዘ መጽሀፍም ለህትመት አብቅተዋል፡፡ በዚህም መጽሀፍ አማካይነት ስለ ሀገራችን ዛፎች በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ወይዘሮ እሌኒ መኩሪያ የተለያዩ ሀገሮችን ቴምብሮችን ያሰባስባሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ለታሪክ ልዩ ፍቅር ያላቸው ወይዘሮ እሌኒ የጡረታ ጊዜያቸውን በማንበብ እና በምርምር ያሳልፉ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር ተመስርቶ በእግሩ እንዲቆም ካደረጉ የሀገር ባለውለታዎች አንዷም ወይዘሮ እሌኒ ነበሩ፡፡ ወይዘሮ እሌኒ በ1959 አመተ ምህረት ከኢንጂነር ሰይፉ ለማ ጋር ጋብቻን መስርተው 3 ሴት ልጆችን ወልደው አንድ ልጅ ደግሞ አሳድገዋል፡፡ ወይዘሮ እሌኒ በተወለዱ በ79 አመታቸው ሮብ ሀምሌ 14 2013 ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የቀብር ስነስርአታቸውም ሀሙስ ሀምሌ 15 2013 ከቀኑ በ6 ሰአት በየካ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ