1. ታዬ በላቸው መልካ-TAYE BELACHEW MELKA
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ130 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ጋዜጠኛ እና የህግ ባለሙያ ታዬ በላቸው መልካ ይነሳል፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ በወር 285 (በሁለት መቶ ሰማንያ አምስት ብር) እየተከፈለው "ከየአቅጣጫው" ፤ “ዓለም እንዴት ሰነበተች?” ፤“ቲቪ መስተዋት” የሚባሉ ፕሮግራሞችን ያዘጋጅ ነበር፡፡ በኋላም እያደገ መጥቶ የዜና ዋና አዘጋጅ መሆን ችሏል። ኢህአዴግ እስኪገባ ድረስ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ (ዘጠኝ) ኣመታት ቆይታ ከሺህ በላይ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን በአድማጭ ተመልካቹ ልብ ውስጥ እና የቴሌቪዥን አርካይቭ ላይ ማስቀመጥ የቻለ ሰው ነው። የቤተመንግስት ሪፖርተር በመሆንም በፓርላማ የሚካሄዱ ሁነቶችን ወደ ህዝቡ ያደርስም ነበር፡፡ጋዜጠኛ በመሆኑና እውነታውን በመፃፉ ብቻ ከአስር ጊዜ በላይ ለእስር ተዳርጓል። ጋዜጠኛ ታዬ በላቸው መልካ
ው ልደት እድገትና ትምህርት
ጋዜጠኛ እና የህግ ባለሙያ ታዬ መጋቢት 30 ቀን 1949 ዓ.ም በድሬዳዋ ልዩ ስሙ አዲስ ከተማ በሚባል አካባቢ ተወለደ። እናትና አባቱ በድሬዳዋ ረጅም ዘመናትን ያሳለፉ ሲሆን በተለይ የእናቱ ሙሉ ቤተሰቦች ሀረርን እና ድሬዳዋን የመሠረቱ ሰዎች እንደሆኑ ይነገራል። አባቱ አቶ በላቸው መልካ(በላቸው ቅመሙ) ድሬዳዋ ቀፊራ በሚባለው አካባቢ በእህል ንግድ በኦጋዴን ደግሞ በሸቀጥ ንግድ ላይ ለዘመናት የተሰማሩ ነበሩ። ከሰባት ልጆች መካከል ታዬ የቤቱ 3ኛው ልጅ ነው።
ታዬ በላቸው አሸዋ ሚካኤል የቄስ ትምህርትን ተምሮ አንደኛ ክፍልን በዚያው በድሬዳዋ ልኡል መኮንን ትምህርት ቤት ጀመረ። በኋላም ከአያቱ ጋር ወደ አለማያ(ሀሮማያ) ሄዶም ተምሯል፡፡ ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የተማረው ደግሞ ጂግጅጋ ነዉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀዉ በትውልድ መንደሩ በድሬዳዋ ልኡል መኮንን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። በትምህርት ቤት ቆይታው የሚኒ ሚዲያ አባል በመሆን ሰኞ ሰኞ የሳምንቱን ዋና ዋና ዜናዎች ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ከስፖርት ጋዜጠኛው ደምሴ ዳምጤ ጋር በመሆን ለተማሪዎች ያቀርቡ ነበር።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነበር በኋላ ለገነነበት የጋዜጠኝነት ሙያው መሠረትን የጣለው። “አቶ መኮንን ሸገኔ” በወቅቱ የነበሩ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በትምህርት ቤት ውስጥ ካቋቋሟቸው በርካታ ክበቦች መካከል ታዬም የጂኦግራፊ ክበብ አባል በመሆን የተለያዩ ጉዞዎች በሚደረጉበት ወቅት ፎቶግራፍ አንሺ እና ታሪክ ዘጋቢ እንዲሆን ተመረጠ፡፡ ታዬም በከፍተኛ የደስታ ስሜት መስራት ጀመረ፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በወቅቱ በድሬዳዋ ከተማ የሚኖሩ ባለሀብቶችን በማስተባበር እርዳታ በማሰባሰብ የመጀመሪያውን በእርዳታ የተገኘ ገንዘብ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሚገኙ የኢትዮጲያ ጠቅላይ ግዛት ይባሉ የነበሩትን በርካታ ባህላዊ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ስፍራዎችን መጎብኘት የቻለው በ17 ዓመቱ ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ ታዬ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ፅሁፎችን እና ፎቶግራፎችን በመሰብሰብ በኤግዚቢሽን እንዲጎበኝ አድርጓል። ታዬ፣ 12ኛ ክፍል እንደደረሰ ማትሪክ ለመፈተን በተዘጋጀበት ወቅት በ1966 ማለት ነው አብዮቱ ፈነዳ። በዚህ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ለሁለት ተከፈለ። ፈተናውን እንፈተን እና አንፈተን በሚል ውዝግብ ተፈጠረ። የተወሰኑት ተፈተኑ ሌሎች ደግሞ አለፋቸው ታዬም ካልተፈተኑት መካከል ነበር፡፡
ከጃንሆይ መንግስት ለውጥ በኋላ
መንግስት ተቀየረ፡፡ የጃንሆይ መንግስት ወድቆ ግዜያዊ የደርግ አስተዳደር ተመሠረተ። በዚህ ወቅት ታዬ ኦጋዴን ስለኖረና ሶማሌኛ ቋንቋም ስለሚናገር በቀብሪዳሀር አውራጃ “ሸኮች” በምትባል የገጠር ከተማ በመንቀሳቀስ በእድገት በህብረት የእውቀትና የስራ ዘመቻ አባል ሆኖ ሳይማር ያስተማረውን ማህበረሰብ ማስተማር ጀመረ።ይህ ወቅት ደግሞ ሶማሊያ ኦጋዴንን ለመውረር እየተንቀሳቀሰች ያለችበትና አካባቢው በረሀብ ቸነፈር የተገረፈበት መጥፎ አጋጣሚ ነበር። አሁን ታዬና ጓደኞቹ ፊደል ማስቆጠሩን ትተው ስለጤና እና ስለ እርሻ ትምህርት መስጠት ጀመሩ። ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ወቅትም ሆነ።
1967 እንዲህ አልፎ 1968 ዓ.ም ገባ። ይህ ወቅት ደግሞ የሀገራችን ፖለቲካ እጅግ የጦዘበት የኢህአፓና ሜኤሶን እንቅስቃሴም የተፋፋመበት በመሆኑ በነበረው ስሜት ስራን መስራት ያልቻለው ታዬ በላቸው ካምፑን ለቆ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሠ። ወደ ቤተሰቦቹ ሲመለስ ግን ሁሉም ነገር ተለዋውጦ ጠበቀው። ሶማሊያ ያደገበትን አካባቢ ወራ ብዙ የእድገት በህብረት አባላት ተሰውተውና በጎርፍ ተወስደዉ ጠበቁት፡፡
1969 ዓ.ም ግን በህይወቱ ብርሀን የፈነጠቀበት ዘመን ሆነ። በተለይ በ1996 በለውጡ ምክንያት ከትምህርታቸው የተሰናከሉ ተማሪዎች ተፈቅዶላቸው ማትሪክ እንዲፈተኑ ሆነ፡፡ ታዬም፣ የዚህ እድል ተጠቃሚ ነበርና ውጤት መጥቶለት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ። ባዮሎጂን ሜጀር ኬሚስትሪን ማይነር አድርጎ መማር ጀመረ። በዚህ ወቅት ግን ፖለቲካው የተጧጧፈበት ዘመን በመሆኑ ማን እንደሚገድል እንኳ ሳይታወቅ በየመንገዱ ወጣቱ ወድቆ የሚገኝበት ጊዜ ነበረ። ታዬ፣ በስጋት እስከ ጥር ከተማረ በኋላ የመማሩ ዋስትና አደጋ ላይ በመውደቁ ትምህርቱን አቋርጦ እህቱ ጋር ወደ ሀረር ተመለሰ።
በወቅቱ፣ በሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት ስር የነበሩ በርካታ መምህራን በነበረው ጦርነት ምክንያት ለቅቀው ስለነበር የ1ኛ ደረጃ መምህራንን መቅጠር እንደሚፈልግ የሚገልፅ ማስታወቂያ ወጣና ተፈትኖ አልፎ በምዕራብ ሀረርጌ "መጣቀሻ" በምትባል ትንሽ ከተማ ማስተማር ጀመረ። በወቅቱ የየሀባ እንቅስቃሴ በአካባቢው ነግሶ ስለነበረ መሳሪያዎች ይዘረፋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በአካባቢው የሚገኙ መምህራን ሳይቀሩ ተለቅመው እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ ታዬም “ኢህአፓና ቅጥር ነብሰ ገዳይ ነህ” በሚል ምክንያት ያለምንም ጥያቄና ምስክር አሰበ ተፈሪ ጭሮ ማረሚያ ቤት ለአንድ ዓመት ያህል ታሰረ። እስር ቤት እያለም አብዮቱን በድላችኋል እና መካስ ስላለባችሁ ለእናት ሀገር ጥሪ ድራማ ስሩ ተብሎ ታዞም ድራማን ሰርቷል።
በመጨረሻም በነፃ ተለቅቆ፣ በ1970 ዓ.ም ወደ ትምህርቱ ተመለሰና ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተመርቆ `ደበሶ” በምትባል ትንሽ ከተማ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር በመሆን መስራት ጀመረ። እያስተማረ እያለ ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩና ያቋረጡ ተማሪዎች መልሰው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ ተሰጠ። ታዬም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆኖ በ1972 ዓም ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ትምህርቱን ቀጠለ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የነበረውን የስነፅሁፍ እውቀት ተጠቅሞ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አርቲክሎችን ይፅፍ ነበር።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የጋዜጠኝነት ቆይታ
በ1974 ዓ.ም ታዬ የመጨረሻ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮግራም አስፈፃሚነት የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ። በወቅቱም ወደ 500 ሰዎች ተወዳድረው ታዬን ጨምሮ 5 ሰዎች አለፉ፡፡ በወር 285(በሁለት መቶ ሰማንያ አምስት ብር) እየተከፈለው በኮንትራት ሰራተኝነት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቀጠረ። ታዬ "ከየ አቅጣጫው"
የተሰኘ
ፕሮግራምን
ጨምሮ
የተለያዩ
ዜናዎችን
ሰርቷል።
ሳምንታዊ
ፕሮግራምም
ነበረው፡፡
አንድ
ወቅት
ከየአቅጣጫው
በተሰኘ
ፕሮግራሙ
ላይ
"በውሀ
መሀል
ተከባ
ውሀ የተጠማች ሀገር"
በማለት
በወቅቱ
በቢሾፍቱ
አካባቢ
የነበረውን
የውሀ
ችግር
እስፍራው
ድረስ
በመሄድ
በተንቀሳቃሽ
ምስል
አስደግፎ
ያቀረበው
ፕሮግራም
እጅግ
አነጋጋሪ
ከመሆኑም
በላይ
አብዮቱን
የሚቀለብስ
አስተሳሰብ
ያለው
ጋዜጠኛ
ነው ይሰቀላል ይገደላል ተባለ፡፡ አቶ ሀይለማርያም ጎሹ በሚባሉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሀላፊ በነበሩ ጠንካራ ሰው አማካይነት ነገሮች ተፈትተው የታሰበለት ሳይሆን ጠንካራና ላመነበት ሟች መሆኑን ያስመሰከረበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
ታዬ “ዓለም እንዴት ሰነበተች?” የሚል ፕሮግራም አስተባባሪ ሆኖም ሰርቷል። “ቲቪ መስተዋት” የሚባል ፕሮግራምም እንዲሁ ያዘጋጅ ነበር፡፡ በኋላም እያደገ መጥቶ የዜና ዋና አዘጋጅ መሆን ቻለ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለ6 ዓመታት ድረስ በኮንትራት ከሰራ በኋላ በ1979 ዓ.ም ቋሚ መሆንም ችሎ ነበር። ቋሚ ሲሆን ይከፈለው የነበረ ደመወዝም አድጎ 347 ብር ደርሶ ነበር። ይህ ክፍያ ደግሞ በዘመኑ የጋዜጠኝነት ታሪክ ትልቅ የሚባለው ነበር።
ታዬ፣ በዘመኑ አመራሮች ዘንድ በነበረው ተቀባይነት ከፍ እያለ በመምጣቱና ለስራ ባለው ተነሳሽነትና ፍጥነትም ስለሚደመሙ ኢሰፓኮ ሲመሠረት ሙሉ ዝግጅቱን በቤተ- መንግስት ተገኝቶ የሠራውም እርሱ ነበር። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የማዘጋጃ ቤት ቆይታው ከነ ሀብታሙ በቀለ፣ ከነ የሺጥላ እና አሰፋ በቀለ ጋር የጠበቀ ጓደኝነት ነበረው። እንደ ተወርዋሪ ኮከብ እያበራ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሏል። ኡጋዴን አካባቢ በነበረው ጦርነት እና በ1977 በነበረው ድርቅ የተጎዱ ወገኖቹን ለማቋቋም በነበረው ሂደት ታዬ በሙያው ትልቅ ተሳትፎን አድርጓል።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በነበረው የ (ዘጠኝ) ዓመት ጉዞ ወደ ሀሰብ፣ ወደ ትግራይና ወደ ኤርትራ እንዲሁም በደቡቡ የሀገራችን ክፍል በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በመዘዋወር የተለያዩ መድረኮችን ያዘጋጅ ነበር። በውጭ ሀገር ሳይቀር እየተንቀሳቀሰ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነው። ኢህአዴግ እስኪገባ ድረስ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታው ከሺህ በላይ የሚሆኑ ዜናና ፕሮግራሞችን በአድማጭ ተመልካቹ ልብ ውስጥ እና የቴሌቪዥን አርካይቭ ላይ ማስቀመጥ የቻለ ሰው ነው። የቤተመንግስት ሪፖርተርም በመሆን በፓርላማ የሚካሄዱ ሁነቶችን ወደ ህዝቡ የሚያደርስ ነበር። የቤተመንግስት ጉዳዮች ዘጋቢነት የስራ ግዜው አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ስፍራው ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ በመሆኑ ታዬም በአንድ ወቅት ካሜራ ማኑ የፈጠረውን የምስል መበላሸት ቆርጦ ለማውጣት ሲል የጓድ መንግስቱ ሀይለማርያምን ንግግር ቆርጦ በመግጠሙ እርሱ (50)ሀምሳ ብር የቅርብ አለቃው የነበረው አስቻለው ደምሴ ደግም (100)መቶ ብር እንዲቀጡ ተደርገዋል።
በ1957 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተመሠረተበትን 25ኛውን የብር ኢዩቤልዩ በዓል ሲከበር ሲጀመር ጀምሮ የነበሩትን ትላልቅ ሰራተኞች አግኝቶ በማነጋገር ጣቢያው ሲጀመር ምን ይመስል እንደነበርና በ25 ዓመታት ውስጥ ያሳየውን ለውጥ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ትልቅ መፅሄት አዘጋጅቶም ነበር። በዘመኑ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ከተለያየ የሀገራችን ክፍሎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ከእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በመሆን የማስፈርና የማቋቋም ስራዎችን የሠራበትን አጋጣሚ ታዬ በላቸው አለቃ በነበረበት ወቅት በስሩ የሚገኙ ጋዜጠኞችን የሚያግዝ አዳዲስ ጋዜጠኞች ሲቀጠሩ ሙያዊ ድጋፎችን ይሰጥ የነበረ እና ጎበዝ ጋዜጠኞችን አፍርቻለሁ ይህንንም ዛሬ ላይ ስመለከት እኮራበታለሁ ይላል።
የጋምቤላ ባሮ ድልድይ ሲመረቅ፤ የአሰብ መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን፤ የአሰብ ኤርፖርት ሲመረቅ፤ አየር ሀይል እና ባህር ሀይል ሲመረቅ ሁሉ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየተንቀሳቀሰ ዘግቧል። ታዬ በላቸው፣ በዚያን ዘመን live/ ቀጥታ ስርጭት/ የሚያቀርብ ደፋር ጋዜጠኛም ነበር። በውጥረት ውስጥ ስራዎችን በፍጥነት በመስራት የሚታወቅ በመሆኑ በጣቢያው የሚሰጠው የስራ አፈፃፀም ውጤት ጥሩ ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከጀርመን ሀገር ጋር በነበረው መልካም ግንኙነት ስኮላር ሺፕ ይሰጥ ነበርና ታዬም በበርሊን ተገኝቶ የጋዜጠኝነት ሙያ ስልጠናን ማግኘት ችሏል። በራሺያ በእንግሊዝና በጀርመን ወታደሮች ይጠበቅ የነበረው የበርሊን ግምብ ሲፈርስ እና ሁለቱ የጀርመን ሀገሮች ተዋህደዉ ጀርመን አንድ ስትሆን የተመለከተ ፤ በስፍራው ስለነበረ ለዘመናት ተራርቀው የነበሩ ቤተሰቦች ሲገናኙ የነበረውን ስሜት የተጋራ የአይን እማኝም ነበር
ከደርግ መንግስት መውደቅ በኋላ
ኢህአዴግ እንደገባ ግንቦት 19 ቀን1983 ማለት ነዉ የምሽቱ የጣቢያው አስፈፃሚ ከነበሩት አንዱ ታዬ በላቸው ነበር። ሀገር ቀልጧል በየቦታው የሚሰማው የጥይት ድምፅ ነው፡፡ ግንቦት 20 ቀን ኢህአዴግ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ታዬ ለ3ቀን ያህል ከቤተሰቦቹ ጋር ሳይገናኝ የቆየበት አጋጣሚ ነበር። ከሳምንት በኋላ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ተሰጣቸውና ተመለሱ። በወቅቱ የቡርቃ ዝምታ መፅሀፍ ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ሀላፊ ሆኖ ነበር። ከአንድ ሳምንት ስራ በኋላ ከሰኔ 24 ሽግግር መንግስት በፊት መሆኑ ነው “አማረ አረጋዊ፣ በረከት ስምኦንና ተስፋዬ ገብረአብ” የሚመሩት ትልቅ ስብሰባ ተካሂዶ ለደርግ መንግስት በጣም የሰሩ ጋዜጠኞች ከስራ ገበታቸው እንዲታገዱ ስማቸው ከተዘረዘሩት መካከል አንዱ ታዬ ነበር። ታዬና ወደ 14 የሚደርሱ ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው ተባረሩ። ከፕሬስ እነ “ሙሉጌታ ሉሌ” ከራዲዮ እነ “ሀይሉ ወልደፃዲቅን” ጨምሮ ወደ 64 የሚሆኑ ሰዎች በወቅቱ ከስራ ተባረዉ ነበርና ምን እናድርግ? በሚል መሰባሰብ እና መመካከር ጀመሩ። በኋላ አራት ኪሎ ባለው “ሲፒኤ” ክስ አቀረቡ። ከብዙ ምልልስና ክርክር በኋላ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ተወሰነላቸው። ነገር ግን አብሮ መሰራቱ የህይወት ማጣት ዋጋን ሊያስከፍል ስለሚችል የፖለቲካ ውሳኔ ተሰጥቷቸው ጡረታው የደረሰ ጡረታው እንዲከበርለት መስራት የሚችለው ደግሞ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ውጭ በየትኛውም ቦታ ገብተው መስራት ይችላሉ የሚል ደብዳቤ ተሰጣቸው። ከዚህ በኋላ ግን ታዬ በላቸው በኢትዮጸጵያ ቴሌቪዥን የነበረው ህይወት አከተመለት።
በጦቢያ መጽሄት ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት
ከኢትዮጲያ ቴሌቪዥን መባረር በኋላ፣ ታላላቅ የሚባሉ ባለሞያዎች ተሰባስበው “ጦቢያ” የምትባል መፅሄትን ማዘጋጀት ጀመሩ። ጊዜውም 1984
ነበር፡፡
ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ታዬን ጨምሮ በርካታ ከስራ ተሰናባቾች የተካተቱባት በሳምንት ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ ኮፒ የሚታተምላት “ጦቢያ” የምትባል ብዙ አንባቢያንን መያዝ የቻለች መፅሄት ማሳተም ቻሉ። ግና አልተኛ ባሉት ጠላቶቻቸው
"ጦቢያ"
የሚለው
መጠሪያ
"ጦሩ
ቢዋጋ
ያሸንፋል"
የሚል
ትርጓሜ
የያዘ
ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ ተከፍቶባቸውም ነበር። ያም ሆኖ ታዬ በላቸው በጦቢያ መፅሄት ታሪክ ከሪፖርተርነት ጀምሮ እስከ ዋና አዘጋጅ በኋላም እስከ ቡድን መሪነት ለዘጠኝ አመታት ሰርቷል። በዚህ የ9 ዓመት ቆይታውም ወደ አራት ያህል ጊዜ ታስሮ ተፈቷል። ታዬ በፊት መፅሄት የነበረችና በኋላም ጋዜጣ መሆን በቻለችው ጦቢያ ላይ የመፅሄቷ አዘጋጅ ሆኖም ታላላቅ የሚባሉ ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስ በማድረግ ይፅፍ ነበር። ኤችአይቪ ኤድስ መከላከልን በተመለከተ ህይወት እንታደግ የሚል ፕሮጀክት ቀርፀው የዚህ አምድ አዘጋጅ በመሆንም ሰርቷል። የስፖርትና የህግ ነክ ፅሁፎች ከመውጣታቸው በፊት የማየቱን ስራም ይሰራ ነበር።
በ1987 ዓ.ም በሙባረክ ግድያ ዙሪያ በፃፈው ፅሁፍ ማእከላዊ ታስሯል። ሀሰተኛ ዜና ፅፈሀል በሚል ጥቅማቸው የተነካ ሰዎች በሙሽርነት ጊዜው ሳይቀር የጫጉላ ግዜውን ሀዋሳ በክስ ላይ እንዲያሳልፍ አድርገውታል። “ኤርትራና ትግራይ ከኢትዮጵያ ቢገነጠሉ ካንሰር ናቸው አያስፈልጉም” የሚል መንፈስ ያለው በፕሮፌሰር ይልማ የተፃፈን የእንግሊዝኛ ፅሁፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማቅረቡ ካንሰር ብሎ ተሳድቧል ተብሎ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ለሶስት ወራት ታስሮም በ5000 ብር ዋስ የተፈታበት አጋጣሚ ነበር። ለመጨረሻ ግዜ በ1990 ዓ.ም አካባቢ ኢሲኤ በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስጊ ስለሆነ ለሰራተኞቹ ከቤታችሁ እንዳትወጡ ነገሮች ከከፉ ወደመጣችሁበት እንመልሳችኋለን በማለት ከአዲስ አበባ ከተማ እንዳይወጡ የሚያሳስብ ማስጠንቀቂያ የሰጠበትን መግለጫ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማቅረቡ ህዝቡን አሸበረ ተብሎ ከከፍተኛ ድብደባና ስቃይ ጋር ለሶስት ወር ማእላዊ ለአራት ወራት ደግሞ ማረሚያ ቤት ታስሯል።
ታዬ ጋዜጠኛ በመሆኑና እውነታውን በመፃፉ ብቻ በተለያዩ ግዜያት ከአስር ጊዜ በላይ ታስሯል። እስሩ ሲበዛበት ይበልጥ እንደ ብረት እያጠነከረው ይመጣል እንጂ በህይወቱ ተስፋ የቆረጠበት ግዜን አያስታውስም። በማያውቀውና እርሱን ተጠያቂ በማያደርገው ሁሉ ቡድኖች ተደራጅተው ሲያጠቁት እጅ ከመስጠት ይልቅ ያለ ጠበቃ የመመከት አቅሙን ለማጎልበት ህግን ተምሮ በዲግሪ ተመርቋል፡፡ በጀርመን ከተማረው ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ፕሪንቲንግ ሚዲያን ተምሮ ዲግሪውንም ይዟል።
በ1993 አካባቢ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ከጦቢያ ለቀቀና ከሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን እያንዳንዳቸው አምስት ሺህ ብር በማዋጣት ልሳነ ህዝብ መፅሄትና ጋዜጣን ማሳተም ጀመሩ። መፅሄቷ እስከ 1997 ድረስ ከታተመች በኋላ የ97 ምርጫ ሲደርስ እንዳይታተሙ ለብርሀንና ሰላም ከተፃፈባቸው መፅሄቶች አንዷ በመሆኗ እንዲቆም ተደረገ።
ከዚህ በኋላ ግን ታታሪውና ለሞያው ብዙ ዋጋን የከፈለው ጋዜጠኛ ታዬ በላቸው የጋዜጠኝነት ስራ በቃኝ ብሎ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ስኮላር ሺፕ አግኝቶ መማር ጀመረ። ግና ጋዜጠኝነት ከህይወቱ ጋር የተጋመደው ታዬ በመማር ላይ ሳለ “ሪሊያንስ አፍሪካ” የሚባል ፕሮጀክት መጥቶ ፕሮጀክቱ በሚያሳትመው ጋዜጣ ላይ “ፍሊራንሰር” ሆኖ መስራት ጀመረ። እየሰራ የተማረውን ትምህርቱን ሲጨርስ ጎበዝ ተማሪም ስለነበር በከፍተኛ ማእረግ ተመርቆ ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያን ያጠለቀ ጀግና ነበር። ዩኒቨርሲቲው ወደ ሼር ካምፖኒ ሲቀየር በተማሪዎች ተወክሎ የቦርድ ፀሀፊም ሆኖ አገልግሏል።
የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በወር የሚታተም ጋዜጣ ላይ የታክስ ነክ ጉዳዮች ላይ አርቲክሎችን በመፃፍ ለአምስት ዓመት ያህል ሰርቷል። የግል ኢንዱስትሪዎች ማህበር ደግሞ በየ ሁለት ወር የሚታተም አምራች ኢንዱስትሪው የሚል መፅሄትና ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖም ሰርቷል።
በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ በህትመቱም ሆነ በኤሌክትሮኒክሱ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን የሠራና ዛሬም በመስራት ላይ የሚገኘው ታዬ በነፃው ፕሬስ የ30 ዓመት ታሪክ ጉዞው ውስጥ “የሰላም ጋዜጠኝነት” የሚባል ተልእኮ ከተሰጣቸው አንዱ ሆኖ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ጦርነት እንዲቆም ትልቅ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ በመቅረቱ ግን ለዘመናት ሲቆጭ እንደነበረ ይናገራል።ዛሬ ለውጡ ይዞት ከመጣው አንዱ የኤርትራና የኢትዮጵያ እርቅ መሆኑ ደግሞ ያስደስተዋል።
ከኢህአዴግ መንግስት መዉደቅ በኋላ
ታዬ በላቸዉ ከለውጡ በኋላም በሞያዉ የተለያዩ የኮሚቴ እና የግል ስራዎችን በመስራት ሀገሩ በፈለገችበት ሁሉ በመሰማራት ላይ ይገኛል፡፡ ከ2010 ለውጥ በኋላ የሚዲያ አሳሪ ህጉ እንዲሻሻል በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በኮሚቴነት ከተዋቀሩት አንዱ ሆኖ በህግም በጋዜጠኝነትም ሞያህ ሀገርህ ትፈልግሀለች ተብሎ ስለታመነበት ያለምንም ክፍያ ለ11 ወር ከግብረ ሀይሉ ጋር በመሆን በተለይ የመገናኛ ብዙሀን አዋጅን አራት ቦታ ከፋፍሎ የማስቀመጥ ስራዎችን ሰርቷል።
ታዬ በሲዳማ ሪፈረንደም ወቅት ታዛቢ በመሆንና በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ተንቀሳቃሽና ተቀማጭ ታዛቢ በመሆን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደ 2.7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የምርጫ ስነምግባር ስልጠናን ሰጥቷል።
አሁን ላይ የተለያዩ የህግ ጉዳዮችን በማማከርና በጋዜጠኝነት ሞያ ላይም የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት እና በማስተማር ስራ ላይ ይገኛል። ወደ NGO ገብቶ
“vision Ethiopian Congress Democratic
Party” በሚባል
የሲቪክ
ድርጅት
ውስጥ
የተመራቂ
ተማሪዎች
መፅሄትን
በማዘጋጀት፤
ህግ ነክ የሆኑ አጫጭር ኮርሶችን በመስጠትና የፀረሙስናና የስነምግባር መኮንንም ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል ። ታዬ ህግና ጋዜጠኝነትን እያጣጣመ አሁን በስራ ላይ አርባ ዓመታት ሞላው፡፡
የትዳር ህይወት
ታዬ ትዳር የመሠረተው በ1987 ዓ.ም ሲሆን ከዛሬዋ የትዳር አጋሩ ወ/ሮ አበራሽ ጋር የተዋወቁት በ1981 ነበር። በወላጅ እናቱ ከፍተኛ ግፊት እርሱ ሳያውቅ ሙሉ የጥሎሽ ወጪውን ሸፍነውና ጓደኞቹ እነ ሙሉጌታ ሉሌ እቁብ ሰብስበው የቤት እቃ አሟልተው ሞቅ ባለ ሰርግ ነበር ትዳር እንዲመሰርት ያደረጉት።
በትዳር በቆየባቸዉ የ27 ዓመታት እድሜ አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆችን ማፍራት ችለዋል፡፡ ሴት ልጁ ምልክት ታዬ ማስተርሷን እየተማረች ሲሆን በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የኮምፒውተር አሲስታንት መምህር ነች።
መዝጊያ ፣ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ