ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ120 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል በሳሉ ብእረኛ እና የታሪክ ጸሀፊ ጳውሎስ ኞኞ ይጠቀሳል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ራሱን በንባብ ያበለጸገ የሀገሩን ታሪክ በጥልቀት የመረመረ ታላቅ ሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያም ይህን ታላቅ ውለታውን በፍጹም ልትረሳው አትችልም፡፡ ጳውሎስ ፈታ ያለ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በአዲስ ዘመን፤ በኢትዮጵያ ድምጽ ፤ እንዲሁም በሩህ ጋዜጣ ላይ የሰራ የሀገር ባለውለታ ነው፡፡ ህዳር 11 2014 ሲመጣ ጳውሎስ የተወለደበት 88ኛ አመት ይታሰባል፡፡ በእለቱ በማህበራዊ ድረ-ገጾችና በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች ስለ ጳውሎስ መረጃ እስከምንሰነዝር ድረስ ታምሩ ከፈለኝ ስለ ጳውሎስ ኞኞ ያሰናዳልንን ጽሁፍ እናንብብ፡፡
“… ደስ ብሎህ ኑር የምትለኝ ከሆነ አፍንጫዬ ድረስ የሚያጠልቀኝን ሃብት ስጠኝ፡፡ አይ አይሆንም የምትል ከሆነ ግን አለማዊ ምኞት የሚመኘውን ልቤን አብርድልኝና የማላወላውል ባህታዊ አድርገኝ፡፡ አለዚያስ በዚህ ብቅ እንቅ ኑሮ አታታለኝ፡፡ ግን ግደለኝ አልልምና እንዳትጨክን”
የካቲት 25/ 1951 የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ ላይ ለግዜር ፅፎ ካሳተመው ደብዳቤ
ውልደትና
እድገት
ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በህዳር 11፤ 1926 ዓ/ም በምስራቁ የሃገራችን ክፍል ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ ነው የተወለደው፡፡ ውልደቱ ቁልቢ ይሁን እንጂ እድገቱ ድሬዳዋ ነው፡፡ እናቱ ወይዘሮ ትልጫለሽ አንዳርጌ ትባላለች፡፡ አባቱ አቶ ኞኞ ግሪካዊ ነጋዴ ነው፡፡ (አባቱ መርከበኛ ነበር የሚሉም አሉ) ጳውሎስ የመጀመሪያ ስሙ አማረ ነበር፡፡ ለእናቱ የመጀመሪያ ልጅ ነበር፤ የተወለደውም በስለት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሁለተኛው ዙር የኢትዮ ጣልያን ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ጳውሎስ እዛው ድሬዳዋ ውስጥ የቀለም ትምህርቱን ጀመረ፡፡ በትምህርት አቀባበሉ ፈጣንና ጎበዝ ስለነበረ በእጥፍ እያለፈ አራተኛ ክፍል ደረሰ፡፡
በሰአቱ እናትና አባቱ አብረው አይኖሩም ነበር፡፡ እናቱም ችግር ውስጥ ገብተው ስለነበር ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም፡፡ ጳውሎስ ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል አቋረጠ፡፡ እናቱ ወይዘሮ ትበልጫለሽ ምንም አይነት ገቢ ስላልነበራት ትምህርቱን አቋርጦ እናቱን በስራ ለማገዝ ደፋ ቀና ማለት ጀመረ፡፡ ድሬዳዋ ከተማ በተለይም ባቡር ጣቢያ አካባቢ የተቀቀለ እንቁላልና የተለያዩ ስእሎችን እየሳለ መሸጥ ጀመረ፡፡
የእንቁላል ሽያጩ ቀዝቀዝ ሲልበት እንቁላሎቹ ላይ የተለያዩ ቀለም እያደረገ ደንበኞቹን ይስብ ነበር፡፡ የሚስላቸው ስእላትም የመላእክትና የቅዱሳን ስእሎች ነበሩ፡፡ ቆይቶ እሱ ስእሉን እየሳለ ሽያጩን ለሌላ ሰው ሰጠ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ቅመሞችን ጨምሮ በአካባቢው ያልተለመደ አይነት ለስላሳ መጠጦችን ይሸጥ ነበር፡፡
የቅጥር ስራ
ጳውሎስ፣ 17 አመት ሲሆነው በእርሻ ሚኒስቴር ስር ወደ ሃረርጌ ክፍለሃገር ጨርጨር አውራጃ ሄዶ ተቀጠረ፡፡ ስራው በወቅቱ ከብቶች ሲከተቡ የተከተቡትን ካልተከተቡት ለመለየት የጆሯቸው ጫፍ ይቀነጠብ ስለነበር ይህንን ስራ እንዲሰራ ነው፡፡ (በሂደት ወደ ከታቢነት ሳይሸጋገር አይቀርም) ለዚህ ስራውም የሚከፈለው በወር 8 ብር ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ስራው ሶስት አመት አካባቢ ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በፀሃፊነት (በድሬሰርነትና በሂሳብ ሰራተኝነትም ጭምር) ተቀጠረ፡፡ ደሞዙም ወደ 80 ብር አደገለት፡፡
በልጅነቱ ትምህርቱን ያቋረጠው ጳውሎስ በአጭር የትምህርት ቆይታው ግጥሞችን እየጻፈ ትምህርት ቤት ውስጥ ያነብ ነበር፡፡ አዲስ አበባ መጥቶ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ከተቀጠረ በኋላም ይህ የፅሁፍ ስራውን አሳድጎ ፅሁፎችን ለተለያዩ ጋዜጦች መላክ ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ አንዲት ልጅ አይቶ እንደወደዳት ይነገራል፡፡ የልጅቷ ስም ፈለቀች ይባላል፡፡ በጊዜው ፍቅሩን በግልጽ መናገር ስላልቻለ ጋዜጣ ላይ ግጥም ጽፎ ላከ፡፡ የግጥሙ ስንኞች የመጀመሪያ ፊደላት ቁልቁል ሲነበቡ “ፈለቀች ትወደኛለች፤ እኔም እወዳታለሁ” ይላል፡፡ በዚህ መልኩ ግጥም ፅፎ ጓደኞቹን አስደንቋቸዋል፡፡
ጳውሎስ በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል እየሰራ ፅሁፎቹንም በጋዜጣ ማሳተም ከቀጠለ በኋላ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ጠራችው፡፡ ጳውሎስ የድምጽ ጋዜጣን ጥሪ ሳያመነታ ጠቀብሎ ስራውን ጀመረ፡፡ ደሞዙን በ30 ብር ቀንሶ በ50 ብር ደሞዝ ነበር የተቀጠረው፡፡
በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ የጋዜጣዋን ይዘት ቀይሮ በአንባቢ ዘንድ በጉጉት የምትጠበቅ አድርጓታል፡፡ ጋዜጣ አዟሪዎችንም መልምሎ አንድ አይነት የደንብ ልብስ አሰፋላቸው፡፡ እነሱም የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ብቻ አዟሪ እንዲሆኑ አድርጎ ጥሩ የሆነ የገበያ ስርአት ዘረጋ፡፡ በዚህ ሁሉ ስራው በአመት 1000 ጋዜጣ ብቻ ለማሳተም እቅድ የሰነቀችው ድምፅ ጋዜጣ በሂደት እስከ 30000 ጋዜጣ ትታተም ጀመር፡፡
በየሳምንቱ ሃሙስ የምትወጣው ድምጽ የብዙዎችን ቀልብ የሳበች እንድትሆን የጳውሎስ ሚና ከሁሉ የላቀ እንደነበር ይነገራል፡፡ በወቅቱ ጋዜጣዋ በጣም ተወዳጅና ተናፋቂ ሆና ነበር፡፡ ድምጻዊ ተፈራ ካሳም
“የመላው ኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ
ትናፍቂኛለሽ ዜናሽ እስኪወጣ”
ብሎ አቀንቅኖላት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ተወዳጅነት ሌሎች በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር ሆነው የሚታተሙ ጋዜጦች ላይ ተጽእኖ ፈጠረ፡፡ በዚህም ግርማቸው ተክለሃዋርያት (በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩ) አረንጓዴ የደንብ ልብስ ለብሰው የኢትዮጵያ ድምጽን ብቻ የሚያዞሩ ጋዜጣ አዟሪዎችን አሳሰሯቸው፡፡ ጳውሎስ በቀጣዩ ህትመት ላይ “ሚኒስትሮቻችን ጋዜጣ አዟሪዎቻችንን ማሰር ጀመሩ” የሚል ፅሁፍ ይዞ ወጣ፡፡ ይህን ፅሁፍ የያዘው ጋዜጣ ለአንባቢ ሳይደርስ ታፍኖ ቀረ፡፡ የጋዜጣውን ወጪም ጳውሎስ እንዲከፍል ተደረገ፡፡ ከጋዜጣውም ተሰናበተ፡፡ (ጋዜጣዋም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር ሆና መታተም ጀመረች)
ጳውሎስም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ስራ ጀመረ፡፡ ከዛም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዛወረ፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት እንዲሁም ደግሞ የተወሰኑ አምዶችን በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጳውሎስ ያዘጋጀው የነበረው ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› የሚል አምድ ነበረው፡፡ በዚህ አምድ ከተለያዩ አንባቢዎች የሚላኩለትን ጥያቄዎች ይመልስበት ነበር፡፡ በዚህ አምድ ጳውሎስ የሚሰጣቸው ምላሾች አንዳንዶቹ ቀልድ ይመስላሉ፡፡
የተወሰኑትን ጥያቄና መልሶች እንጥቀሳቸው
ጥያቄ፡- ባጠና ባጠና አልገባ አለኝ?
ጳውሎስ፡- ባጠና ካልገባሽ በስንጥር ሞክሪው፡፡
ጥያቄ፡- ሙስሊምና ክርስቲያን ቢጋቡ ምን ችግር አለው?
ጳውሎስ፡- ምንም ችግር የለውም፡፡ ፍቅሩ ከበረታ አንዳቸው ወደአንዳቸው ይጠቃለላሉ፡፡
በዚህኛው መልስ ጃንሆይ ተቆጡ፡፡ ጃንሆይ ቤተመንግስት አስጠሩትና ለምን እንደዚህ አልክ ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም እርስዎ የሙስሊሙም የክርስቲያኑም የሁሉ ንጉስ እንደሆኑት ሁሉ እኔም የሙስሊሙም የክርስቲያኑም ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ አላቸው፡፡ እርሳቸው በጣም ስለተደነቁ ሊሸልሙት ምን እንደሚፈልግ ጠየቁት፡፡ ጃፓን ሃገር ያለ የፅህፈት መሳሪያ እንዲገዛለት ጠየቀ፡፡ ጃንሆይ እንዲገዛለት ሲያዙ እኔ ቢሮክራሲ አልወድምና ገንዘቡ ይሰጠኝ እራሴ እገዛለሁ ብሎ 5000 ብር ተሰጠው፡፡
ደርግ ከገባ በኋላ ጳውሎስ አዲስ ዘመን ላይ ወታደሩን ነቅፈሃል ተብሎ ተሰናበተና ወደ ኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዢን ተዛወረ፡፡ በዛም በመዝናኛ ዝግጅቶች ላይ የተለያዩ መፃህፎቶችን እንዲሁም ዶክመንተሪዎችን ይሰራ ነበር፡፡ ስራዎቹም ተወዳጅ ሆኑለት፡፡
ጳውሎስ በጋዜጠኝነት ህይወቱ ውስጥ ሙያውን ለማዳበር ወደ ተለያዩ ሃገራት ተጉዟል፡፡ ለአብነትም ቼኮዝላቫኪያ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ሃንጋሪ በመሄድ ለህይወት የሚጠቅመውን ልምድ ቀስሞ ተመልሷል፡፡
የታሪክ መፅሃፍቶች
ጳውሎስ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ታሪክ ተመራማሪ ነበር፡፡ የተለያዩ የታሪክ ሰነዶችን ይመረምራል፡፡ ታሪክንም ይከትባል፡፡ በታሪክ ረገድም በርካታ መጽሃፍትን ፅፎ አሳትሟል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት፣ አጤ ሚኒሊክ፣ አጤ ቴዎድሮስ፣ አጤ ሚኒሊክ፣ አጤ ሚኒሊክ ከውጪ ሃገራት ጋር የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ አጤ ሚኒሊክ በሃር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ የአጤ ዮሃንስ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢንሳይክሎፒዲያ የሚባሉትን መፅሃፎቹን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ታትመው ለንባብ ከበቁት የታሪክ መጽሃፎች በተጨማሪም ሳይታተሙ የቀሩ በርካታ መፅሃፎችም ነበሩት፡፡ ምናልባትም ያልታተሙት መፅሃፎቹ የልጅ እያሱ፣ የእቴጌ ጣይቱ፣ የዘውዲቱን ታሪክ ሳይዙ አልቀሩም፡፡
ጳውሎስ በታሪክ አሰናነዱና አዘጋገቡ በጣም ተደናቂ ነበር፡፡ እውቁ የታሪክ ምሁር ተክለፃዲቅ መኩሪያም ምናልባት ይተካኝ ይሆናል ብለው የሚያስቡት እርሱን ነበር፡፡
ስነፅሁፋዊ ስራዎች
ጳውሎስ ከታሪክ ፀሃፊነቱ ባሻገርም ልቦለድም ይጽፍ ነበር፡፡ ያሳተማቸው የልቦለድ መጽሃፎችም አሉት፡፡ የጌታቸው ሚስቶች፣ የኔዎቹ ገረዶች፣ የአራዳው ታደሰ፣ ከሴቶች አንባ፣ እንቆቅልሽ፣ ምስቅልቅል፣ ቅይጥ የሚሉት መጽሃፎቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ሌሎች ኢ-ልቦለድ መፅሃፎችም ነበሩት፡፡
“ችግር ስር ከሰደደ መዘዙ ብዙ ነውና በጋራ ሆነን በእንጭጩ እንቅጨው” የሚል መርህ ያለው ጳውሎስ በልቦለድ ስራዎችም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ያሳይ ነበር፡፡
ሌሎች ሙያዎች
ጳውሎስ ከጋዜጠኝነቱና ደራሲነቱ ባሻገር ሁለገብ ሰው ነበር፡፡ ከአናጢዎቹ ጋር አናፂ ሆኖ ፋስ ያነሳል፡፡ ግንበኞች ቢመጡ ቱንቢውን፤ ቀለም ቀቢዎች ቢመጡ ብሩሹን ይዞ ወደ ስራ ቢገባ የማያሳፍር ሙያ ነበረው፡፡ የቧንቧ ስራና ኤሌክትሪክም ይችል ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ስራ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ በመስራት ክህሎት ያለው መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡
ጳውሎስ ፎቶ ግራፍም ያነሳ ነበር፡፡ በልጅነቱ የጀመረው የስእል ጥበብም አለው፡፡
የትዳር ህይወት
ጳውሎስ ከእናቱ ጋር አራት ኪሎ አካባቢ ይኖር ነበር፡፡ እናቱ በልጅነቱ ከአጠገቧ ሳታርቅ እንዳኖረችው ሁሉ እርሱም ራሱን በቻለ ጊዜ አብሯት ይኖር ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አንዲት ሴት አየ፡፡ ስሟም አዳነች ታደሰ ይባል ነበር፡፡ ጎረቤታሞች ስለነበሩ በቅርብ ይተያያሉ፡፡ ለመገናኘት ግን አልደፈሩም፡፡ አንድ ቀን የአዳነች አባት ሲሞቱ ቤት ድረስ ሄዶ ያስተዛዝናት ጀመር፡፡ በዛው በጣም ተቀራርበው የአይን ፍቅራቸውን አሳድገው ይገናኙ ጀመር፡፡ እንደወጉም ሽማግሌ ተልኮ በ1955 ተጋቡ፡፡
ወይዘሮ አዳነች አመለ ፀባይ ሸጋ ሴት ነበሩ፡፡ ጳውሎስንም በስራ ያግዙት ነበር፡፡ አዳነችና ጳውሎስ አንድ ልጅ ወልደው ስሙንም ሃዋርያው ብለውታል፡፡ ሃዋርያው ጳውሎስ፡፡
ሞት
የ1983ቱ መንግስት ለውጥ እንደመጣ ‹‹ሩህ›› የምትባል የግል መፅሄት ነበረች፡፡ መፅሄቷ እንደተመሰረተች ጳውሎስ ዋና አዘጋጇ ሆነ፡፡ ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ ታመመና አልጋ ላይ ዋለ፡፡ ህመሙን ያዩ ወዳጅና አድናቂዎቹ ገንዘብ አሰባስበው ወደ ጀርመን ላኩትና ታክሞ ተመለሰ፡፡ ነገር ግን ጤናው በዘላቂነት ሊመለስ አልቻለም፡፡ ተመልሶ ሲታመም ሼህ መሃመድ አሊ አላሙዲን ወጪውን ሸፍነውለት አሜሪካ ሄዶ ታከመ፡፡ ነገር ግን ህይወቱ ሊተርፍ አልቻለም፡፡ ግንቦት
29/1984 ዓ/ም ህይወቱ አለፈ፡፡
እንደ
መውጫ
ጳውሎስ ከታመመ በኋላ ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ አብዝቶ ነበር፡፡ በአንድ ቪዲዮ ላይም በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲመሰክር የሃዋርያት ስራ 3፡- 16 ላይ ያለውን “ይህ የምታዩት የምታውቁት ሰው ድኖ የበረታው በኢየሱስ ስም በተገኘው እምነት ነው፡፡” የሚለውን ሲጠቅስ ተሰምቷል፡፡
በእርግጥ ገና በልጅነቱ ጀምሮ እናቱ መፅሃፍ ቅዱስን ታስተምረው ነበር፡፡ ስሙን ከአማረ ወደ ጳውሎስ የቀየረችውም በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ ካለው ጳውሎስ ጋር ባህሪው የተመሳሰለ ስለመሰላት ነበር፡፡
ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ምስክርነቱ ላይ አንዲት በግዝት የቆመች አይጥን ሴቶች ሲገድሉ በመመልከቱ እንቅልፉን አጥቶ ማደሩን ያነሳል፡፡ እባካችሁ በክርስቶስ ገዝታችሁ አስቁማችሁ አትግደሉ እያለ ይመክር ነበር፡፡
ህመም በፀናበት ጊዜ እራሱን ሊያጠፋ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜም ነፍሴን ተቀበላት ብሎ ሲፀልይ እናቱ ሲከፋህ ድንገት መጽሃፍ ቅዱስ ከፍተህ አንብብ፡፡ ያም ቃል ያበረታኃል ያለቺውን አስታውሶ መጽሃፍ ቅዱስ ሲከፍት ያገኘው የዳዊት መዝሙር ቃል ራሱን ከማጥፋት እንደታደገው ይናገራል፡፡ ቃሉም ይህ ነበር፡-
“በትእግስትህ ፀንተህ እግዚያብሄር የሚያደርገውን ለማየት ተጠባበቅ፡፡ መዝ37፡- 7
ስለ ጳውሎስ አብረውት በቅርበት የሰሩ ምን ይላሉ?
‹‹……ጽሁፎቹን አሁንም እወድለታለሁ፡፡ የሚጽፋቸው ቀለል ያሉና ወዝ ያላቸው ናቸው፡፡ አንባቢዎቹን የሚያውቀው ጳውሎስ ቀልድም ሆነ ቁምነገር አስተባብሮ መጻፍ ይችላል፡፡ ከሁሉም ይልቅ ሌሎቻችን ባልለመድነው ሁኔታ በምርምር የተደገፉ ጽሁፎችን ማቅረቡን ባህሉ አድርጎ ይዞታል፡፡
ሙሉጌታ ሉሌ/1933-2008/ በጊዜው የፕሬስ መምሪያ ሃላፊ የነበረ
‹‹……የመጀመሪያውን ረቂቅ ነው የሚሰጠኝ፡፡ እንደምታየው / ጽሁፉን እያሳየኝ/ ስርዝ ድልዝ የለውም፡፡….. እኔ እንዲያውም ከታይፕ ይልቅ እጅ ጽሁፉን እመርጣለሁ፡፡ ከጽሁፉ ላይ ነው ቀጥታ የማነበው፡፡ ለመጻፍ ከፈለገ ይጽፋል፡፡ ጥሩ ስብስብ ያለውም ይመስለኛል፡፡
ታደሰ ሙሉነህ 1938-2004 በወቅቱ ኢትዮጵያ ሬድዮ የነበረ
‹‹….የጋዜጠኝነት ስራ በቡድን የሚሰራ እንደመሆኑ ተግባብቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡ጋሽ ጳውሎስ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ተቀናጅቶ መስራትን ያውቅበታል፡፡››
ነቢዩ ኢያሱ በአሁኑ ሰአት በባህር ማዶ የሚገኝ
የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤ ፤
ደራሲ እና ጋዜጠኛ የጳውሎስ ኞኞ ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት የተፃፃፏቸውን ደብዳቤዎች በመሰብሰብ እና በማሳተም ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ገጥሞት እንደነበር ይነገራል። ለዚህም እንደ ማሳያ፣ ጳውሎስ ኞኞ የሚከተለውን ደብዳቤ ለደርግ አባል ለሆኑት ለተስፋዬ ወልደስላሴ ፅፎ ነበር። ይህ ደብዳቤ በመስከረም 13ቀን 1979 ዓ/ም ተፃፈ።
ለጓድ ተስፋዬ ወልደስላሴ
የኢሠፓ ማእከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ ተለዋጭ አባልና የአገር እና ህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፤
ደብዳቤዬ የህይወት ውሳኔ ጉዳይ ስለሆነ ስራ እንደሚበዛቦት ባውቅም እስከመጨረሻው እንዲያስቡልኝ በታላቅ ትህትና እለምናለሁ።
ዋናው ቁም ነገር፤ አገሬን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ጠልቼ ሳይሆን በደረሰብኝ የግል በደል ከኢትዮጵያ ምድር ለመውጣት ስለፈለኩኝ የመውጫ ፍቃድ እንዲሠጠኝ ለመለመን ነው።
በእኔ እምነት፤ እያወቅሁ በኢትዮጵያ ላይ ክፉ ነገር አልሰራሁም። በአገሬ አስተዳደርም ላይ እያወቅሁ የሰራሁት መጥፎ ስራ የለም። ይሄ እንግዲህ በእኔ እምነት ነው። መጥፎ ነገር ብሰራ ኖሮ መንግስት ከራስ ፀጉሬ አንዲቱን እንኳን ሳይነካ በሰላም እና በክብር አያኖረኝም ነበር።
አሁን ከፋኝ። የከፋኝም በሶስት ነገሮች ነው።
፩ኛ) ለአዲስ አበባ ከተማ መቶኛ አመት መታሰቢያ መጽሀፍ እንዳዘጋጅና ለአንዳንድ ወጪዎች የሚረዳኝ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እርዳታ እንዲያደርግልኝ የዛሬ 4 አመት ጠይቄ አምስት ሺህ ብር እርዳታ ሊሠጠኝ ተዋውለን ገንዘቡን ተቀበልኩ። በውላችን መሰረት የማዘጋጀውን መፃፍ የማሳተሙ ቅድሚያ የማዘጋጃ ቤቱ ሆኖ ማዘጋጃ ቤቱ ባያሳትመው እኔ እንዳሳትመው ተዋውለን ነበር። ስራውን ጨርሼ በውላችን መሰረት እንዲፈፀም ደጋግሜ ለማዘጋጃ ቤት ብፅፍም መልስ አጣሁ። አሁን በመጨረሻው፤ "መፅሃፉ በግለሰብ ስም መታተም አይገባውም ተብሎ ተወሰደብህ" የሚል ወሬ ሰማሁ። ከ 300 ገፆች በላይ የሚሆነውን መፅሃፌን ማን መሆኑን የማላውቀው የበላይ ወርሶኝ ያጠራቀምኳቸውን 500 ያህል ፎቶግራፎቼን ታቅፌ ቀረሁ።
፪ኛ) ቀድም ብሎ በጓድ ፍሰሃ ደስታ፣ በኋላም በጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ ፍቃድ የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ መዝገብ ቤትን እንዳጠና አስፈቅጄ በእረፍት ጊዜዬ እየሰራሁ የዳግማዊ አጤ ምኒሊክን ደብዳቤዎች ገልብጬ ወሰድሁ። ደብዳቤዎቹን ከፋፍዬ የስምና የቦታ ማውጫ ሰርቼ፣ ታይፕ አስመትቼ (2245) ደብዳቤ ያህል ያሉበትን ያንደኛውን መፅሃፌን እንዲታተም ለመነጋገር ለኩራዝ ድርጅት በታህሳስ ወር 1978ዓ/ ም ሰጠሁኝ። በኋላ ምን እንደደረሰ ብጠይቅ
"የበላይ
አካል
ወሰደው"
አሉኝ።
‹‹ማነው
የበላዩ
አካል?››
ብዬ ደጋግሜ ብጠይቅ ታስበላናለህ እና አርፈህ ተቀመጥ እባል ጀመር።
"ንገሩኝና
ልበላ"
ብልም
የሚነግረኝ
አጥቼ
ለፍቼ
ባዶ እጄን ቀረሁ።
፫ኛ) በዚህ ላይ እንዳለሁ አንድ ቀን የማስታወቂያ ሚኒስትራችን ከቢሯቸው ጠርተውኝ "ብዙ የታሪክ ፅሁፎችን፣ ማስረጃዎች እና ደብዳቤዎች አሉዎት?" ቢሉኝ ለስራ የተጠየቅሁ መስሎኝ "አዎን ያቅሜን ያህል ያጠራቀምኳቸው አሉኝ" አልኳቸው። "ያለዎትን ማንኛውንም የታሪክ ማስረጃ ለመንግስት እንዲያስረክቡ ታዘዋል" ቢሉኝ፤ "ማነው ያዘዘው?" አልኳቸው። "የበላይ አካል ስላዘዘ በአስቸኳይ ያስረክቡ" አሉኝ። "ለዚህ ከሆነ የለኝም" ብላቸው፤ "ቤትዎ ይፈተሻል" ብለውኝ እስካሁን ሳላስረክብ አለሁ።
እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበደልበትን ልስራ አላልኩም። ታሪኩን እንዲያውቅ ያቅሜን ያህል እየፈላለግሁ የችሎታዬን ያህል ልስራለት ነው የምለው። አሁንም የጀመርኩት እንደ አልማናክ ወይም እንደ ኢንሳይክሎፒዲያ መሳይ የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሃፍ አለኝ። በስራዬ ተስፋ ባልቆርጥም፤ "ከደሞዜ እየተበደርኩ በከባድ የኑሮ ችግር እየኖርሁ ታይፕ ካስመታሁ በኃላ ያ የማይታወቅ የበላይ አካል ቢወርሰኝስ?" እያልኩ አስባለሁ። ስለዚህ በረጋ ህሊና ስራዬን ለመጨረስ ከኢትዮጵያ ምድር ለመውጣት አሰብሁ።
ከኢትዮጵያ ምድር ልውጣ ስል አገሬን ከድቼ አይደለም። ግን ይሄን እኔ ሳላውቀው የሚወርሰኝን የበላይ አካል የሚባለውን ስም ጠልቼ እና ፈርቼ ነው። ታላላቆቹ የበላዮች ይሄን እንደማይሰሩ አውቃለሁ። በዚህ በኩል ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም። ለዚህም ያለኝ ማስረጃ ታላላቆቹ የበላይ አካሎች በኔ ላይ መጥፎ አስተያየት ቢኖራቸው ኖሮ ለህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አባልነት በበላይ አካል ተመርጬ ባልገባሁ ነበረ። እኔን ግራ ያጋባኝ በበላይ አካል ስም የግል ስራዬን ያውም ድርሰት መወረሴ ነው።
አገሬን ብቻ ሳይሆን መንግስቴንም እወዳለሁ፣ አከብራለሁ። የምወደውና የማከብረውም በአፌ ሳይሆን ከልቤ ነው። ይህም በመሆኑ ነው እንደሌላው ሳልጠፋ በህጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ምድር ለመውጣት የፈለግሁት።
ከኢትዮጵያ ምድር ወጥቼ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። በአሳቤ ያለው የአማርኛ የህትመት ፊደል ካለበት አገር ሄጄ የማውቀውን የኢትዮጵያን ታሪክ እያሳተምሁ ለመኖር ነው። ደግሜ የምናገረው ያደግሁበትንና የኖርኩበትን አገሬን፣ የምወደውንና የሚወደኝን የኢትዮጵያን ህዝብ ከድቼ አይደለም። ስራዬን ከማልወረስበት አገር ሰርቼ ካልሞትሁ ለመቀበር ወደ አገሬ የምመለስ ሰው ነኝ።
እንኳን ከኢትዮጵያ ውጪ ከአዲስ አበባ ደብረ ዘይት የምሄድበት ገንዘብ የለኝም። ጥረቴ መፅሃፍ በመግዛትና ይህን በመሳሰለው ስለነበረ ኑሮዬም የተመሰቃቀለ ነው። ስለዚህ ጓድነትዎን የምለምነው ሶስት ነገሮችን ነው፤
፩ኛ) የሚወዱኝን ኢትዮጵያውያንን የመሳፈሪያ ገንዘብ እንድለምንና እንዳጠራቅም እንዲፈቀድልኝ ነው። ይህን ሳላሳውቅ ልመናዬን በሚሥጥር ባደርገው የመንግስቴን ስም ለማጥፋት የተነሳሁ ስለሚመስልብኝ እንደዚያ አይነቱን ነገር አልፈለግሁም። አላደርገውም። የሚቻል ቢሆን በጋዜጣም ሆነ በቃል ለመለመን እንድችል የፈቃድ ወረቀት እንዲሠጠኝ፣ በወረቀት መፍቀዱ የማይቻል ከሆነ ግን ልመና ለመጀመር መነሳሳቴን መስሪያ ቤቱ አውቆ በቃል እንዲፈቀድልኝ ነው።
፪ኛ) የምሄድበትን አገር ርቀት የሚወስነው በልመና የሚገኘው ገንዘብ ልክ በመሆኑ ልመናዬን ስጨርስ በህጋዊ መንገድ የመውጫ ፍቃድ እንዲሠጠኝ።
፫ኛ) በምወጣበት ጊዜ ያሉኝን የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሃፎቼንና አንዳንድ ጥርቅምቅም ማስረጃዎቼን ይዤ እንድወጣ እንዲፈቀድልኝ በማክበር እለምናለሁ።
ይህን ደብዳቤ ሥጽፍ፤ "ይበላሃል" የሚባለው የማላውቀው የበላይ አካል እንደሚበላኝ እጠረጥራለሁ። አንዳንድ ወዳጆቼም ነገሩን በሚስጥር እንዳደርገው መክረውኝ ነበር። እኔ ግን በአገሬ ላይ የማውቀው ወንጀል ያልሰራሁ ሰው በመሆኔ እንደሌባ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ያልበደለኝም ያገሬን መንግስት ስም ለማሳማት አልፈለግም። በዚህ ምክንያት፤ ያ በይ የተባለው ህቡዕ አካል ቢበላኝም ካለሁበት የብስጭት ኑሮ የማይቀረውን ሞት ብሞት ይሻላል በማለት በግል ውሳኔዬ ይህን ደብዳቤ ፅፌሎታለሁና በሚያደርጉልኝ ከፍተኛ እርዳታ ደስ እንደሚያሰኙኝ ተስፋ አለኝ።
ይህን ደብዳቤዬን ለጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማሪያም አልጻፍኩም። ነገሩን አስቤው ስራ ስለሚበዛባቸው በአንድ ፣መልኩም የግል ጉዳይ አላደክማቸውም በማለት ነው። ግን ለሁለት ሰዎች ያህል እንዲረዱኝ በማለት ግልባጩን መስጠቴን ይወቁልኝ።
ጨርሰው ስላነበቡልኝ እግዚአብሄር ይስጥልኝ። በቅርብ ጊዜ ተስፋ ያለው ደስ የሚያሰኝ መልስዎን እንደማገኝም ተስፋ አለኝ።
ምንጭ:
አጤ ምኒሊክ በአገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች
በጳውሎስ ኞኞ
መዝጊያ፣ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚን አቋም የሚያንጠባርቅና
የተወዳጅ
ሚድያ
የዊኪፒዲያ
ቦርድ
አባላት
ያመኑበት
ነው፡፡
ጳውሎስ ለበርካታ ጸሀፊዎች መሰረት የሆነ ታላቅ ተምሳሌት ነው፡፡ ጳውሎስ ጥሩ አንባቢ ነው፡፡ ገና በልጅነቱ ለእቃ መጠቅለያ የተቀመጠ ጋዜጣን ሲያነብ ያደገ ነው፡፡ ጳውሎስ ጠንክሮ በማንበቡ ምክንያት በመደበኛ ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በሳል የታሪክ እና የስነ-ጽሁፍ ድርሰቶችን አቅርቧል፡፡ ይህም እንደ አርአያ ያስቆጥረዋል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ በብዙዎች የሚታወቅ ስመ-ጥሩ ሰው ነው፡፡ በተለይ አንድ ጥያቄ አለኝ በተሰኘው አዝናኝ አምዱ ለብዙዎች ዘና ማለት ዋና ምክንያት መሆን ችሏል፡፡ ይህ አንጋፋ ደራሲ፤ ጋዜጠኛ እና የታሪክ ተመራማሪ ብዙ ያነበበ በመሆኑ የሚጽፋቸው መጽሀፎች ጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ጳውሎስ በህይወት በኖረባቸው 58 አመታት አንድም ሳይደክመው ጊዜውን በምርምርና በንባብ በመጻፍ ያሳለፈ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የጻፋቸው መጽሀፎች በታሪክ ላይ ያለንን ትልቅ ሀብት ከትቦ ያስቀረ ነው፡፡ ይህ ሰው ገና በልጅነቱ ሚሲዮን ውስጥ ያደገ በመሆኑ መጽሀፍ ቅዱስን ሲያነብ ነው ያደገው፡፡
ጳውሎስ ኞኞ በ1984 ታሞ በነበረበት ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ቃለ-ምልልስ ያደረገለት ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ነበር፡፡ በሰኔ 1984 የወጣው ነጸብራቅ መጽሄት 4 ገጽ የፈጀ ጽሁፍ አውጥቶ ነበር፡፡
ጳውሎስ ኞኞ በገጽ 7 ላይ ለአለምነህ በሰጠው ቃለ-ምልልስ እንዳለው‹‹ …. እኔ ጥሩ ጸሀፊ ነኝ ማለት አይደለም፡፡ ጥሩ የታሪክ ጸሀፊ ነኝ ማለቴም አይደለም፡፡መጽሀፍ ባነበብኩ ቁጥር የትም በሄድኩ ቁጥር የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ ያገኘሁትን ሁሉ ለቃቅሜ በማስታወሻ ይዤው ስለነበር እኔ ብሞት ያ ነገር ብትንትኑ እንደወጣ ይቀራል፡፡ ስለዚህ አሁን እኔ ያለኝን ጥሩም ሆነ መጥፎ ባሳትመው የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ የተሻለ ሲሰራ የታተመውን የበለጠ ያጠራዋል›› ብሎ ነበር፡፡
እኛ ይህን የአማርኛ ዊኪፒዲያ ያሰናዳን ሰዎችም አላማችን ይሄው ነው፡፡ ትናንት እነ ጳውሎስ ደክመው አንድ እውቀት አቀበሉን፡፡ ተቀባዩ ደግሞ የራሱን አክሎበት ለቀጣዩ እንካችሁ ብሎ የማቀበል ሂደቱን ያስቀጥላል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ጳውሎስ ኞኞ ሁሉ ጊዜም ስሙ ከፍ ባለ ደረጃ ሊነሳ የሚገባ ታላቅ የሀገር ዋርካ ነው፡፡ ግንቦት 29 የሞተበት ቀን መታወስ አለበት፡፡ ህዳር 11 የተወለደበት ቀን መዘከር አለበት፡፡ በእነዚህ ቀናታ ከራሳችን የፈለቁ የራሳችን ጀግኖች ማወደስ ካልቻልን የእኛ ያልሆኑ ሰዎች ጀግናችን ሆነው ሳናውቅ ይመጡብናል፡፡ ያ ከመሆኑ በፊት እንደ ጳውሎስ ኞኞ ያሉ ተምሳሌት የሆኑ ብርቆችን በየምክንያቱ እያነሳን አንድ ‹‹አይከን››/ ጀግና / ብናስተዋውቅ በራስ ጌጥ ማጌጥ ይከተላል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለዚህ ነው በትልቅ ፍል አምሮት / ፓሽን/ ይህን የስነዳ ስራ በብቃት እያከናወነ ያለው፡፡ በመሆኑም ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ስለምንዘክር ከሀሳባችን ጋር የምትስማሙ አብራችሁን እንድትቆሙ እንላለን፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ ታምሩ ከፈለኝ የተጻፈ ሲሆን የአርትኦትና ተጨማሪ ሀሳቦች የማከሉ ስራ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተከናውኗል፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ መስከረም 22 2014 በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የፌስ ቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
፡
ለዚህ ፅሁፍ ግብአት የሆኑ፡-
ደረጀ ትእዛዙ፤ ጳውሎስ ኞኞ ግለ-ታሪኩ
ሃብታሙ ግርማ ደምሴ፤ የስነፅሁፍ ሰዎች እና ስራዎቻቸው (2011)
በሸገር ራዲዮ ጳውሎስ ኞኞ የህይወት ታሪክ ላይ የተዘጋጁ ሶስት ተከታታይ ዝግጅቶች (በተፈሪ አለሙ)
በፋና ራዲዮ ስለ ደራሲው ስራ እና ህይወት የተሰራ ፕሮግራም (በቤርሳቤህ ጌቴ )
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ