2.   ነቢዩ ባዬ ንጋቱ / ረዳት ፕሮፌሰር/   NEBIYOU BAYE NIGATU /Assistant professor

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የቴአትር ሰዎችን ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ የብዙዎችን ታሪክ እያሰባሰበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ወደፊትም የቴአትር እና የስነ-ጽሁፍ ባለሙያዎችን ታሪክ ራሱን ችሎ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ  በሆነ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊታተም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ይገኝበታል፡፡

 

ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ለመስራት የማይደክመው ነው፡፡ብዙዎች በተሰጠው መክሊት ይደመማሉ፡፡ አቅሙ ትጉህነቱ፣ ጥንካሬው የሚጀምረው ገና በለጋነቱ ነው፡፡ አንደበተ- ርቱዕ እና የነካኸው ሁሉ ይስመር የተባለለት አይነት ሰው ነው፡፡ ባለ ብዙ መክሊትና  የበርካታ ስኬቶችም ምክንያት በመሆን ዛሬም ለሃገሩ እየተጋ ይገኛል፡፡ የለውጡ ሞተር ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፡፡ ታሪኩን ጋዜጠኛ ዘቢባ ሁሴን አሊና እዝራ እጅጉ እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡

 

             ውልደት እና እድገት

 

ነብዩ ባዬ   ጥር 12 ቀን 1972 . በጎንደር ከተማ ተወልዶ 6 ወር እድሜው ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ በኩል 50 . ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ አለም ከተማ አድጓል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በታላቁ የቋንቋ ሊቅ በተሰየመው በአለቃ ኪዳነ ወልድ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ነብዩ ገና 2 ክፍል ተማሪ እያለ ነበር ወደ ጥበብ የተጠራው፡፡ በዚያን ዘመን በትምህርት ቤቱ የትያትርና የስነ-ጽሁፍ ክበብ አባል በመሆን  በተማሪዎች ፊት ቆሞ ዜናዎችን፤ ግጥሞችንና የስፖርት ዘገባዎችን ሲያቀርብ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ መምህራኖቹ ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ ይነግሩት ነበር፡፡እኔ የወላጅ አባቴ ቅጂ ነኝየሚለው ነብዩ ወላጅ አባቱ ከድርሰት እና ከስነ-ግጥም ጋር ቅርበት ያላቸው መሆኑና መጽሃፍትን እስከማሳተም የደረሱ በመሆናቸው ይህንኑ እየተመለከተና በዚህም እየታነጸ ማደጉ አሁን ላለበት ደረጃ ትልቅ አሻራ ጥሎልኝ አልፏል ይላል፡፡

 

ነብዩ ባዬ፣ 1984 . 12 ዓመቱ እዝያዉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ትምህርት ቤት እያለ ነበር አንድ ጀግና ህጻንን ወክሎ የመጀመሪያውን ትያትር የተጫወተው፡፡ ከዚያ በኋላማ የተለያዩ ትምህርታዊ ይዘት ያላቸውን አጫጭር ድራማዎችን ጥሩ አድርጎ መስራት ጀመረ፡፡

 

         ነብዩና የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ቆይታ

 

ነብዩ ዘጠነኛ ክፍልን እንደጨረሰ ያደገባት አዲስ አለም ከተማን ተሰናብቶ ወደ አዲስ አበባ መጣ ፡፡ በአዲስ አበባ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ገብቶም ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡ ገና በለጋነት እድሜው የተለከፈበት የትያትር ፍቅርን ችላ ማለት ግን አልተቻለውም፡፡ በትምህርት ቤቱ የትያትርና ስነ-ፅሁፍ ክበብ ውስጥ ስሙ በጉልህ የሚጻፍ ተሳታፊ ሆነ፡፡ 11 ክፍል ተማሪ ሳለ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለክበባቸውዲምፕልየሚባል ስያሜን ሰጥተውም ነበር፡፡

 

ነብዩ ትያትር መክሊቴ ነዉ ብሎ እንዲያምን ያደረገዉ አጋጣሚ የተከሰተውም 1988 .  በዚሁ 11 ክፍል ተማሪ ሳለ  ነበር - “Young Reporters competition” ቢቢሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፅሁፍ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች እንዲወዳደሩበት የፈጠረው እድል ነው ፡፡ ነብዩም ከእነዚህ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ በመሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ  የጦርነት አስከፊነትን ለወጣቶች መስበክላይ ትኩረቱን ያደረገ አንድ ገፅ ከግማሽ ወረቀት በመጻፍ አንደኛ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሪትሽ ካውንስል በዘመኑ ትላልቅ የሚባሉ ሽልማቶች ተበርክተውለታል፡፡ 12 ክፍል ሲደርስ ደግሞየትእቢት አክሊልየተሰኘ ትያትርን በመሪ ተዋናይነት ከበርካታ አማተር ተዋንያን ጋር በመሆን መርካቶ አካባቢ በነበረው መስታወት የትያትር ክበብ እና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ለእይታ አብቅቷል፡፡ ነብዩ ከትምህርት ቤት ውጭም ፒያሳ ገዳም ሰፈር 08 ቀበሌ አዳራሽ ከነ ተፈራ ወርቁ፣ ደምሴ በየነ፣ ቴዎድሮስ ለገሰ እና ሌሎችም አማተር ተዋንያን ጋር የመስራት እድል ነበረው፡፡

 

       ሕይወት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪነት እስከ መምህርነት

 

ነብዩ ባዬ 1990 . አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪነት ተቀላቀለ፡፡ ነቢዩ ባዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ በበርካታ ቴአትሮች ላይ  ተውኗል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ‹‹አማጭ›› የተሰኘው ቴአትር ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ቴአትር ላይ እንደ አለምጸሀይ በቀለ፤ ደበሽ ተመስገን፤ ደረጀ ደመቀ ያሉ ተዋንያን የተወኑ ሲሆን ነቢዩም ከእነዚህ የጥበብ ሰዎች ጋር የመተወን እድሉን ያገኘ ነበር፡፡ በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ የቆየውና ‹‹የቀን ቅኝት›› በሚል ስያሜ በሚታወቅ ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ላይ ከእነ ሽመልስ አበራ ወለላ አሰፋ እና ከመሳሰሉት ጋር ተውኗል፡፡ ነቢዩ 1993 /  በከፍተኛ ማእረግ ተመርቆ እዚያው በረዳት መምህርነት ተቀጠረ፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ሳያስተምር ከተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ እና ከበላይነህ አቡኔ ጋር የማስተማር ስነ-ዘዴዎችንና የትወና ስልቶችን ሲመለከትና ሲያጠና ቆይቶ 1994 . በተቀጠረ በሁለተኛ ዓመቱ የሚወደው የመምህርነት ሙያ ውስጥ ደስ እያለው ገብቶ ማስተማር ጀመረ፡፡ በአዲስ  አበባ ዩኒቨርሲቲ  በተማሪነት ዘመኑም በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት 'አማጭ' የሚሰኝ ትያትርን መጫወት ችሎ ስለነበር ከቀደሙ የቴአትር ባለሙያዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት ችሎ ነበር፡፡

 

ወቅቱ በኢትዮጵያ የትያትር ታሪክ ውስጥ የተማረ እና ያልተማረ የሚል ልዩነት የተፈጠረበት ነበር፡፡ ነብዩ ይህን ልዩነት ለማጥበብ ቆርጦ በመነሳት 1994 .  በመጀመሪያ አመት የመምህርነት ጊዜው  ላይ እያለ ውጤት ኖሯቸው ለትያትር የተሰጡና በቀን የመማር እድሉን ላላገኙ  አማተር ተዋንያን  በማታው መርሀ ግብር የመማር እድሉን እንዲያገኙ ከባልደረባው በላይነህ አቡኔ ጋር በመሆን የዳሰሳ ጥናት አቅርበው ካሪኩለሙ ተቀርፆ ትምህርቱን አስጀምሯል። ይህ የትያትር ትምህርት በማታው መርሀ ግብር ከዲፕሎማ ጀምሮ እስከ ዲግሪ የደረሰውም በነብዩ ዘመን ነበር።

 

ነብዩ ዛሬ ለሚታየው የትያትር እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ያሉ እነ እመቤት /ገብርኤልን፣ እነ ተስፋዬ /ሃና፣ እነ አስቴር በዳኔንና እነ ትእግስት አለሙን በማስተማር ‹‹›› ብሎ የጀመረው የትያትር መምህርነት ሙያው ዛሬም ድረስ በርካቶችን እያፈራበት የሚገኝ በተማሪዎቹ እጅግ የሚወደድ እና የሚከበር መምህር ነው።

 

2001 . መገባደጃ ጀምሮ የትምህርት ክፍሉን በኃላፊነትም መርቷል።  በዚህ ወቅት ደግሞ የማስተርስ መርሀ ግብር አስከፍቷል፡፡ ነብዩ በዩኒቨርሲቲው ሲቀጠር እርሱ ለትምህርት ክፍሉ ሰባተኛ መምህር ሲሆን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ሲሆን ደግሞ የመምህራንን ቁጥር ከፍ በማድረግ ስምንት ተጨማሪ መምህራን እንዲቀጠሩ አድርጓል። የትያትር ትምህርት ክፍል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተመራጭና ተወዳጅ እንዲሆንም ትልቅ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ነቢዩ ካከናወናቸው ትልቅ አስተዋጽኦዎች አንዱ 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የቴአትር ፊስቲቫል እንዲደረግ ሚና ማበርከቱ ነው፡፡ ይህ ፌስቲቫል 11 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር፡፡ ይህን በፋና ወጊነቱ የተመሰከረለትን ፌስቲቫል በሴክሬተሪ ጀነራልነት የመራው ነቢዩ ነበር፡፡ ነቢዩ ባዬ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ህግ ሲወጣ  አባል በመሆን የራሱን ድርሻ የተወጣ ትጉህ ሰው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ‹‹የሀገር ብሌን›› የተሰኘ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ታሪክ የሚዘክር ሙዚቃዊ ተውኔትን በመስራት እና በማስተባበር የማይዘነጋ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ነቢዩ ይህን ሁሉ የሚያከናውነው ከማስተማር ስራው ጎን ለጎን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የድራማ እና የፊልም ካውንስል ውስጥ በአባልነት በማገልገል የራሱን ድርሻ የተወጣ ባለሙያ ነው፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ውስጥም 6 አመታት ለማገልገል ችሎ ነበር፡፡

 

                                       ተጨማሪ አስተዋጽኦዎች

 

ነቢዩ ባዬ  ትወናን ከማስተማሩ በዘለለ በመተወንም አቅሙን ያስመሰከረ ነው፡፡ ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ ፎዚያ ላይ ተውኗል፡፡ የፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ስራ በሆነው ጤዛ ፊልምም ላይ ነቢዩ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በኤምኔት የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ የተሰራው ‹‹አባትየው›› ወይም ዘፋዘር በተሰኘው ፊልም ላይ መተወን ችሏል፡፡ ነቢዩ የአዲስ አበባ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ሓላፊ በነበረ ጊዜም ቅድመ-ምርመራን ወይም ሳንሱርን እንዲቆም አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እድሳት እንዲከናወን የማስፋፊያ ስራው እንዲከናወን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን የራስ ቴአትር ቤት ፈርሶ ተለዋጭ 5000 ካሬሜትር ተሰጥቶት እንዲገነባ ነቢዩ ባዬ የራሱን ጉልህ ሚና ለመወጣት ችሏል፡፡

 

ከዚህም ባሻገር ፒያሳ ማዘጋጃ ቤት ታጥሮ የነበረው ስፍራ ታሪካዊ ዳራውን በማመልከት በተለይ በወቅቱ ለነበሩት ከንቲባ ታከለ ኡማ በማስረዳት ቦታው የአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እንዲሆን አድርጓል፡፡ ነቢዩ ባዬ በነበረው የመንግስት የስራ ኃላፊነት በተለይ በባህል እና ማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ ትልቅ የመዋቅር ለውጥ እንዲደረግ ሚና ያበረከተ ባለውለታ ነው፡፡   ነብዩ የሀሳብ ሀብታም ነው፡፡ በአንድ ወቅት ክቡር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሳሉ ዛሬ ለበርካታ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች እፎይታ የፈጠረውን የተማሪ ምገባ እና ደንብ ልብስ ማልበስ ላይ የማማከር አገልግሎት ውስጥም ነበረበት። ታሪካዊው የሰይጣን ቤት እንዲፈርስ ሲወሰንበትም ይሄው የሀገር ተቆርቋሪ መምህር ለሚመለከተው አካል ጮሆ ነበር፡፡ ቅርሱ ዛሬም ተጠብቆ እንዲቆይ የሆነው፡፡

 

                          የትዳር አለም

 

ነብዩ ባዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከነበረች / የሸዋዘርፍ አዛናው ጋር የነበረው የፍቅር ህይወት ወደ ትዳር አድጓ ከሚወዳትና ከሚያከብራት  ባለቤቱ ጋር 11 (አስራ አንድ) ዓመታትን  አብረው በመዝለቅ 3 ልጆችንም አፍርተዋል።ልጆቹም አማናዊት ነቢዩ፤ ቃናልኡል ነቢዩና ሆህተ ነቢዩ ይባላሉ፡፡

 

                     የኃላፊነት ዘመን 

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የትያትር ትምህርት ክፍል  ሃላፊ   በመሆን 2    አመት

 

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የትያትርና ስነጥበብ ኮሌጅ  ዲን  በመሆን 6 ዓመት

 

ብሄራዊ  ትያትርን  በሃላፊነት) ለአምስት ወር

 

የባህልና  ቱሪዝም ቢሮ  ሃላፊ በመሆን አንድ አመት  ከአምስት ወር 

 

              አሁን በሃላፊነት

 

የአዲስ ሚዲያ ኔትወርከ ቦርድ ሰብሳቢ

 

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል

 

የወወክማ ቦርድ አባል 

 

በፍል ውሀ አገልግሎት ድርጅትም እንዲሁ ቦርድ አባል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።   

 

ነብዩ አሁንም በዚሁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የትያትር ምህርነቱን እንደቀጠለ ነው። የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግንም እንዲሁ አግኝቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፒ.ኤች. ትምህርቱንም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በቅርቡም አራዳ ክፋለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲን ወክሎ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን ምርጫውንም ማሸነፉና የምክር ቤት አባል መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

         ስለ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ  የሚያውቁት ምን ይላሉ?

 

ወይዘሮ የሸዋዘርፍ  አዛናው የነቢዩ ባዬ ባለቤት ስትሆን ባለቤቷን እንደ ባል እና እንደ  መምህር ስትገልጸው ከዚህ በታች ያለውን ሀሳብ ሰንዝራ ነበር፡፡

 

‹‹..ከነቢዩ ጋር የተዋወቅነው 1999 ነው፡፡ ቴአትር ስንማር ጎበዝ ከሚባሉ መምህራን አንዱ ነው፡፡ ተዘጋጅቶ የሚመጣ መምህር ስለነበር በእርሱ የማስተማር ክፍለ-ጊዜ  የሚቀር ተማሪ አልነበረም፡፡አልፎ አልፎ በተለያየ ምክንያት ይቀር በነበረበት ጊዜ ተማሪው ይናደዳል፡፡አንድ ጊዜ የማስታውሰው እንዲያውም ቀርቶ  መምህር አሰፋ ወርቁ ጋር ልንከሰው ሄደን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እርሱ ቢያስተምረን ይሻላል በሚል እሳቤ ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ለነቢዩ ያለንን ፍቅር ነበር፡፡ ነቢዩ በባህሪው ይቀርባል፡፡እናም ከእኔም ጋር መጀመሪያ በጓደኝነት ተቀራረብን፤ ከዚያም ከጥቂት አመት ቆይታ በኋላ ለመጋባት ቻልን፡፡ነቢዩ ለእኔ በጣም የሚደንቀኝ ሰው ነው፡፡ብዙ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ አስታራቂ ሽማግሌ ይሆናሌ፡፡ ጋብቻ ላይ እንደ ሽማግሌ ሆኖ የሚሄደው እርሱ ነው፡፡ ሰዎች በሚጋጩበት ጊዜ የሚያስታርቀው ነቢዩ ነው፡፡ በፍቅር ያምናል፡፡ ነቢዩ ሁሌ ጊዜ ከሰዎች ጥሩ ነገር ከመጠበቅ ቀድሞ ያለ አንዳች ቅድመ-ሁኔታ ጥሩ ነገር ማድረግ ያስፈልጋል ብሎ ያምናል፡፡ባለቤቴ ስለሆነ ሳይሆን ነባ ልቡ ንጹህ ነው፡፡ ለእኔ በአንድ በኩል ወንድሜ ይመስለኛል፡፡ በሌላ ደግሞ የልጆቼ አባት ባለቤቴ ይሆናል፡፡ ሁሉን ነገር በፍቅር እና በሰላም በመፍታት ያምናል፡፡ ለልጆቹ በመጣበት ሰአት ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ በንባብ ጊዜውን በማሳለፍ ንባብ ምሉእ ሰው እንደሚያደርግ በተግባር ለልጆቹ ያሳያቸዋል፡፡ ይህ ትልቅ ስራ ነው፡፡ ነባ ለእኔ ጎበዝ አስተማሪ ነው፡፡ በየጊዜው ለሀገሩ የሚሰራውን በጎ ነገር አውቃለሁ፡፡ መድረሻውም ስለሚታየኝ ትልቅ ነገር ለሀገሩ  እንደሚሰራ አልጠረጥርም፡፡ እንደ ባል ምርጥ ባል እንደ አባት ተወዳጅ አባት እንደ መምህር ደግሞ ብስል መምህር ነው፡፡ እግዚአብሄር  መልካሙን ሁሉ እንዲገጥመው እመኛለሁ፡፡

 

  የነቢዩ ባዬ እናት  ሲስተር አዜብ አድማሱ ስለ ልጃቸው

 

ነቢዩ ገና በልጅነት ሰላማዊ ልጅ ነበር፡፡ ብዙም አላስቸገረኝም፡፡ ልጅ ሆኖ ልጆች ሲጣሉ ያስታርቅ ነበር፡፡ አዲስ አለም ያድግ በነበረበት ጊዜ ልጆች በኳስ ምክንያት  ሲጋጩ ያጠፋውን ለይቶ ዳኝነት የሚሰጠው  ብላቴናው ነቢዩ ነበር፡፡ ይህ ሰላም ወዳድነቱ አሁን ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡ እኔ መጀመሪያ ቴአትር ለመማር መወሰኑን ሳውቅ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡‹‹ እንዴት ለፍቼ ለፍቼ ልጄ ቴአትር ይማራል›› አልኩ፡፡ አባቱ ግን እንዲገፋበት መከረው፡፡ አባቱ ራሱ ከጥበብ ጋር የተቆራኘ ልምድ ያካበተ በመሆኑ የነቢዩን ዝንባሌ አውቆለት ነበር፡፡ በኋላ 1993  በማእረግ ሲመረቅ ቴአትር ሙያ ለካ እንዲህ አይነት ታላቅ ሙያ ነው ስል በቂ ግንዛቤ አገኘሁ፡፡ አሁን ይህ ሙያ በጣም የተከበረ መሆኑን በነቢዩ አይቻለሁ፡፡ በየቦታው ትልቅ ክብር እያገኘ መሆኑን ሳውቅ ደግሞ እንኳንም ቴአትር ተማረ አልኩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምክር ሲሰጠኝ ታላቅ ወንድሜ ይመስለኛል፡፡ ፈጣሪ የባረከው ልጅ ነው፡፡ አንገቱን ደፍቶ በትህትና ሲያወራ የልጅነቱ ነቢዩ ይታወሰኛል፡፡ አባቱ ድሮ‹‹…. ይህ ልጅ የኢትዮጵያ ልጅ ነው ለሀገር ሰጥቸዋለሁ ›› ሲል የወደፊቱን ተናግሮ ነበር፡፡ እውነትም  ይህ ልጅ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ነቢዩ መልካም ልጅ ነው፡፡ በአል ሲመጣ በግ ይዞ ይመጣል፡፡ ያጫውተናል፡፡ እርሱ ሰላም ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ ከእነ መላ ቤተሰቡ ለልጄ መልካም የስራ ዘመን እመኝለታለሁ፡፡

 

         የአገኘሁ አዳነ አስተያየት ስለ ነቢዩ ባዬ

 

አገኘሁ አዳነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የስነ-ጥበብእና ዲዛይን ተማሪ ቤት ዳይሬክተር ነው፡፡ የስነ-ጽሁፍ ባለሙያም ነው፡፡

 

‹‹ የነቢዩን የሰአት አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉንም በአግባቡ ያከናውን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በጣም በተጣበበ ሰአት ነበር የሚሰራው፡፡የስነ-ጥባባት ኮሌጁ ዲን በነበረበት ጊዜ የሀሳብ ልዩነቶችን የሚያስታርቅበት መንገድ በጣም ይደንቀኝ ነበር፡፡ ግጭት ይፈታበት የነበረበትን መንገድ ሁላችንም እናደንቅ ነበር፡፡በጣም ሆደ-ሰፊነት አይበታለሁ፡፡ የሰዎችን ልዩ ክህሎት አይቶ እንዲያወጡት የማስተባበር ድንቅ ብቃት አለው፡፡ ጫናዎች በሚፈጠሩበት ሰአት እርሱ ያረግባቸዋል፡፡የእርሱ በጣም የተለየ፡፡ ጎበዝ ነው፡፡ ለሚፈልገው ጉዳይ ሰዎችን ማስተባበር ይችላል፡፡ ተናደህ አንድ ጉዳይ ከባድ ሆኖብህ ነባን ስታገኘው ቀላል እንዲሆን ያደርግልሀል፡፡ ይህ ችሎታው ነው፡፡ በኮሌጅ  ቆይታው ደግሞ ያስተማራቸው ጎበዝ መምህርነቱን ይመሰክራሉ፡፡ ሌላው ስለ ነቢዩ የሚገርመኝ  በስራ በተወጠረበት ጊዜ  ስትነግረው የማይሰማህ ሊመስልህ  እርሱ ግን ጉዳዩን አሳጥሮ ሲነግርህ ትደነቃለህ፡፡ የኮሌጁ ዲን በነበረበት ጊዜ እነዚህ ጠንካራ ባህሪያት አይቼበታለሁ፡፡ ወደፊትም ብዙ ሊሰራ የሚችል ሰው ነው፡፡

 

                 የትእግስት አለማየሁ    አስተያየት

 

ትእግስት አለማየሁ የቴአትር እና ጥበባት መምህርት ስትሆን በአሁኑ ሰአት የፒኤችዲ ትምህርቷን እየተማረች ትገኛለች፡፡

 

ነብዩ ባዬ ከማውቃቸው በጣም ብሩህ አእምሮ ካላቸው ሰዎች አንዱ ነው፡፡  ይህንን ያልኩበት ምክንያትም  ነገሮችን በተገቢው ቦታና ጊዜ በተገቢ ሁኔታ በእውቀት እና በጥበብ፤ ከቅንነት እና ከመልካም ስነ ምግባር ጋር ማድረግ የሚችል ምሁር ስለሆነ ነው፡፡  እርሱ ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች የሚፈልገው እውቀት እና  ክህሎታቸውን ብቻ ነው፡፡ ስለቀደመ ትውውቁ ወይም ዝምድናው አያስብም፡፡ ለሚያስተምረው እና ለሚመራው ተቋምም አዳዲስ ነገሮችን በማስጀመር የሚቀድመው የለም፡፡ ጊዜውን በተገቢው ሁኔታ ይጠቀማል፡፡ ያስተምራል፣ ይተውናል፣ ቴአትር ያዘጋጃል የዶክትሬት ዲግሪውን ይማራል፣ በአመራርነት ይሳተፋል፣ ሰዎችን በተቻለው መጠን ይረዳል፣ ከሚበልጡት ይማራል፣ የቀደሙትን ያከብራል፣ እንቅፋት የሚሆኑበትን እንዳላየ ያልፋቸዋል በሀይማኖቱ ይተጋል፣ ማህበራዊ ህይዎትም ላይ አይሰንፍም፡፡

 

                                የዘካርያስ ብርሃኑ አስተያየት

 

ዘካሪያስ ብርሀኑ የቲያትር፣የስነጽሁፍና የሚዲያ ባለሙያ ሲሆን በሚድያ ስራ 14 አመት በላይ የዘለቀ ብቁ ባለሙያ ነው፡፡

 

/ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህሬ ነበር።ከማልረሳቸው፣ትርጉም ያለው ዕውቀትና ሀሳብ ከሰጡኝ መምህራን አንዱና ዋነኛው ነው።እርሱ የሚሰጠውን ኮርስ እና የሚገባበትን ክፍለ ጊዜ በምን ያህል ጉጉትና ናፍቆት እንጠብቅ እንደነበረ አልረሳውም።

 

ነብዩ፤ በተለይ የሁለት ነገር ፀጋ አብዝቶ እንደተሰጠው አምናለሁ።የማስተማር እና የመተወን።በሁለቱም ግን የጠገብነው አይመስለኝም።በማስተማሩ ይሻላል ብዙዎቻችንን አፍርቷል።በትወናው ግን ተመልካቾች ተበድለዋል።"አማጭ" በተሰኝው ፋርስ ተውኔት የነብዩን አስገራሚ ትወና የተመለከተ አቻ የሆነን ተሰጥኦ ሲፈልግ እስከዛሬ በአምሮት ኖሯል።

 

ነብዩ አንደበተ ርቱዕ ነው።በሁሌም ንግግሩ ለአድማጩ የሚሰጠው አክብሮትና ትህትና ይገርመኛል።ከባባድ ሀሳቦችን በቀለለና በወዝ ለበስ አገላለጽ የሚያቀርብበት መንገድ ምንጊዜም ይደንቀኛል።

 

       የተስፋዬ ማሞ አስተያየት

 

ተስፋዬ ማሞ የፊልም የስነ-ጽሁፍ እና የቴአትር ባለሙያ ሲሆን በሸገር ሬድዮ የጥበብ መንገድ የተሰኘ የሬድዮ መሰነዶ  አየር ላይ የሚያውል ዘርፈብዙ ባለሙያ ነው፡፡

 

ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬን ‹‹አባትየው›› የተሰኘው ፊልም ላይ አብረን ስንሰራ አውቀዋለሁ፡፡ ነቢዩን ሳውቀው ጀምሮ በትጋቱ ነው፡፡ በተለይ የጊዜ አጠቃቀሙ ለብዙዎች የሚደንቅ ይመስለኛል፡፡ ነቢዩ ከእኔ ጋር የጥበብ መንገድ በተሰኘው ሳምንታዊ መሰናዶ ላይ ሲሰራ ለሁሉ ነገር የሚሰጠውን ጊዜ አይቻለሁ፡፡ 2004-2010 የጥበብ መንገድ ላይ አብረን በሰራንባቸው ጊዜያት በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበብ ጉዳዮች አየር ላይ ሽፋን እንዲያገኙ የተቻለውን ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ነቢዩ ጊዜ አጠቃቀም ላይ በጣም የተካነ ነው፡፡ ለሁሉ ጊዜ አለው፡፡ የትኛው ጉዳይ ቅድሚያ ማግኘት አለበት የሚለውም ላይ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚሰራ ብዙ ጉዳዮችን ያሳካል፡፡ በአንድ በኩል ያስተምራል፡፡ ደግሞ በሌላ ቴአትር ያዘጋጃል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባል ስለሆነ ደግሞ እዚያም ተገኝቶ የበኩሉን ይወጣል፡፡ እነዚህን ሁሉ አስማምቶ አንዱ ከአንዱ ጋር እንዳይጣረስ የሚያደርገው ጥረት ለብዙዎቻችን ሊያስተምር የሚችል ነው፡፡ በተሰማራበት ሁሉ እንዲቀናው እመኛለሁ፡፡

 

መምህር ቻላቸው ፈረጅ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዳይሬክቲንግና የተውኔት መምህር ነው፡፡

 

ነባ 2002 ጀምሮ አስተምሮኛል፡፡ ብዙ ጊዜ የምንለው ነገር አለ፡፡ተማሪዎች  ከሌላ መምህር 10 ክፍለጊዜ ከሚማሩ የነቢዩ ባዬን አንድ ክላስ ቢማሩ  ምርጥ ነው የሚል ብሂል አለ፡፡ ምን ማለት ነቢዩ ከሌሎቹ መምህራን በጥሩ የማስተማር ስነዘዴ ተሸሎ በመገኘቱ ነው፡፡ ይህንን ሁሉም ተማሪ ሊመሰክረው የሚችለው ትልቅ ሀቅ ነው፡፡ነቢዩ ይዘትን በሚገባ ቀለል አድርጎ የማቅረብ ድንቅ ብቃትን የተቸረ ነው፡፡ የሚያስተምረው እንዲገባን አድርጎ  ተግባራዊ እውቀትን አክሎ ነው፡፡ በተለይ ሙዚቃዊ ድራማ ሲያስተምር ወደር አይገኝለትም፡፡ነቢዩ በሁሉ የእውቀት ዘርፎች ሁሉ እውቀትን የተካነ ነው፡፡ሁሉ ቦታ ላይ አታጣውም፡፡ ነቢዩ መኮፈስ የሚባል ነገር አይነካካውም፡፡ወደታች ወርዶ በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለማነጋገር ወይም እንደወዳጅ ለማጫወት አይቸግረውም፡፡ አልፎ አልፎ እንጦጦ አካባቢ የሚገኙ ነዳያንን ሲረዳ አብሯቸው አሹቅ ሲበላ አስታውሳለሁ፡፡ ነቢዩ ሰዎች ወደ አንድ እድገት እንዲቃረቡ እንጂ በሰው መስመር አይገባም፡፡እኔ አሁን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መምህር ሆኛለሁ፡፡ እንደ መልካም አርአያ አድርጌ የምቆጥረው ነቢዩን ነው፡፡ እንደ ወንድም ቀርቦ ለመምከር ራሱን ያሰናዳ ነው፡፡  ደግሞም ፈሪሀ-እግዚአብሄርን የታደለ ታላቅ ሰው ነው፡፡ ነባ በሄደበት ሁሉ መልካም እድል እንዲገጥመው ምኞቴ ነው፡፡

 

መዝጊያ፤  ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበትና የተወዳጅ ዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት ከስምምነት የደረሱበት ነው፡፡

 

  ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ገና 41 አመት ጎልማሳ ሆኖ/2014/ ለሀገሩ እና በሙያው ትልቅ አበርክቶ የሰጠ ነው፡፡ በዚህም በዘመናችን ያሉ ሁሉ አክብሮታቸውን ይቸሩታል፡፡ ነቢዩን ብዙዎች ነባ እያሉ በፍቅርና በአክብሮት ይጠሩታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ለግንኙነት የተመቸ ሰብእና ስላለው  ቀለል ብሏቸው ይቀርቡታል፡፡ ነቢዩ ለሀገር ያበረከተውን ሚና 6 ከፍለን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በቴአትር መምህርነት ያበረከተውን ጉልህ ሚና ነው፡፡ ነቢዩ፣ ያስተማራቸው በግልጽ እንደሚመሰክሩት ጥልቅ የሆነ ግንዛቤ የያዘ መምህር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ያወቀውን በማሳወቁ ግቡን በሚገባ ሊያሳካ ችሏል ማለት ያስደፍራል፡፡ በሁለተኛነት ነቢዩ በትወና ላይ አቅሙን አሳይቷል፡፡ ‹‹አማጭ›› ከተሰኘው ቴአትር ጀምሮ አባትየው  ፊልም ድረስ ነቢዩ ውስጡ ያለውን አቅም አሳይቷል፡፡letters from the red sea  በተሰኘው ፊልም ላይም ነቢዩን እናገኘዋለን፡፡

 

ይህ ፊልም በፈረንሳይ ባለሙያዎች ባለቤትነት የተያዘ ሲሆን ነቢዩም አሻራውን ለማኖር የቻለበት ነው፡፡ ሶስተኛው ነቢዩን እንድናደንቅ የሚያስገድደን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አዳዲስ የትምህርት መርሀ-ግብሮች እንዲጀመሩ ያደረገው ጥረት ነው፡፡ በተለይ ቴአትር በማታ እንዲከፈት ያደረገውን ጥረት እዚህ ጋር ማንሳት እንችላለን፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ነቢዩ ቴአትር ያዘጋጃል ሙዚቃዊ ተውኔቶችን እውን ያደርጋል፡፡ ነቢዩ በአንድ በኩል ደግሞ ያማክራል፤ በሚድያዎች ላይ መግለጫ ይሰጣል፤ የጥናት ወረቀቶችን ያቀርባል፡፡ በተለይ የመንግስት የስራ ሃላፊ በነበረ ጊዜ የአቅሙን ያህል ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ያደርጋል፡፡ ሙያውን ተጠቅሞ የባህል የኪነ-ጥበብ መድረኮች እንዲዘጋጁ ያስተባብራል፡፡ በተለይ ደግሞ በሙዚቃዊ ተውኔቶቹ ይመሰገናል፡፡ በሁሉም ይሳካለታል፡፡ ማህበራዊ ግዴታውንም በወጎ በወጣት የሚታገዙትን በሚችለው አቅም ያግዛል፡፡ ይህ እንግዲህ የቴአትር መምህር ከሆነ በኋላ ባለፉት 20 አመታት ያከናወናቸው ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ያልተጠቀሱ ብዙ ናቸው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ በሚያዝያ 2010 የደበበ ሰይፉን የሙት አመት ማስታወሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማእከል ባዘጋጀ ጊዜ በወቅቱ 3 ቀን ያለ አንዳች ቢሮክራሲ ፕሮግራሙ እንዲሳካ የረዳው ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ነው፡፡ በመጋቢት 2013 የተፈሪ  አለሙ ልደት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር በተከበረ ጊዜ አንዱ ተናጋሪ በመሆን የተወዳጅ ሚድያን ሀሳብ የደገፈው ነቢዩ ነው፡፡ እኛም ለችሎታው ምስክር መሆናችንን ለመግለጽ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ እና ነቢዩ ትውውቃቸው የሚጀመረው 1988 ነበር፡፡ ነቢዩ የየካቲት 12 ተማሪ ሆኖ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር ባዘጋጀው መሰናዶ እና ቢቢሲ ባዘጋጀው  የስልጠና መርሀግብር ላይ ሚኒሚድያውን ወክሎ ተገኝቶ ነበር፡፡ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እዝራም ቦሌ ሀይስኩልን ወክሎ 11 ክፍል ሆኖ ከነቢዩ ጋር በአንድ የስልጠና ማእድ ተቀምጦ ነበር፡፡ ነቢዩ ከያኔ ጀምሮ በጥበቡ አለም የመዝለቅ ህልም ነበረው፡፡ ይህን ህልሙን በሚገባ ከማሳካቱ ባሻገር ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ችሏል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ የቦርድ አባላትና አዘጋጆች እንደሚያምኑት እንዲህ አይነት ግለ-ታሪኮች መሰነዳቸው ፋይዳቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ከዚህ በላይ ለሀገሩ ድንቅ ነገር ማበርከቱ የማይቀር ሆኖ እስካሁን በሰራው ግን ሊጻፍለት የሚገባው ታላቅ ሰው ነው፡፡ አጠገባችን ያለውን የአንድ ድንቅ ሰው ታሪክ በወጉ ከሰነድን ታሪክ አለን ማለት ነው፡፡ ነቢዩ በሙያው ባለው ሃላፊነት በጠንካራ ጎኑ እየቀጠለ ደካማ ጎኑን እያረመ ይቀጥላል፡፡ ያሰባቸውን የጥናት ወረቀቶች ለህትመት ያበቃል፡፡ በውስጡ ያሉ የጥበብ ስራዎችም ይወጣሉ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ይህንን 2671 ቃላት የተሰናዳ የነቢዩ ባዬን ታሪክ እናነባለን፡፡ ነባ እንወድሀለን …… ከታላቅ አክብሮት ጋር/ የዚህ ጽሁፍ የምርምርና የቃለ -መጠይቅ ስራ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በዘቢባ ሁሴን አሊ የተከናወነ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ መስከረም 23 2014 Tewedaje media የፌስ ቡክ ገጽና የአማርኛ ዊኪፒዲያ ላይ የተጫነ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው የሚሰራ ይሆናል፡፡

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች