6. መስከረም ጌታቸው አሞኘ- Meskerem Getachew Amogne


ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ 130 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል  መስከረም ጌታቸው ትጠቀሳለች፡፡ መስከረም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ የአመራር ደረጃ የደረሰች ጠንካራ ሴት ስለመሆኗ ይነገራል፡፡ በተለይ በኢቲቪ 2003 ወዲህ ይሰሩ የነበሩ በሳል ዘጋቢ ፊልሞች በእርሷ አማካይነት የሚሰሩ ነበሩ፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ መስራች ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ጥረቷን በማየት ለዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት በማቅረብ ታሪኳ ለትውልዱ አስተማሪ ስለሆነ በሚከተለው መልኩ ግለ-ታሪኳ እንዲጠናከር አድርጓል፡፡

 

                            አንደኛ ደረጃ ሳለች ተሰጥኦዋን አወቀች














 

ቤተሰቡ ከጋዜጠኝነት ውጭ ሌላ ሙያ አታውቁም እንዴ? እስኪባሉ ድረስ ከታላቅ እስከ ታናሽ ሶስቱም ጋዜጠኞች ናቸው። ታላቃቸው ሃይማኖት ጌታቸው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ኪነ-ሂስና የፍቅር ነገር ፕሮግራሞች በወቅቱ ተደማጭነትን አግኝታለች። ኑሮዋን በሀገረ- አሜሪካ ስታደርግ ግን ወደ ጤና ዘርፍ ገባች።ታናሻቸው ይናገር ጌታቸው ደግሞ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ራዲዮ የትዝታን በዜማ አዘጋጅ በመሆን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ላይ አሻራውን እንዳሳረፈ ብዙዎች ይስማማሉ።በኤልያስ መልካ ሕይወት እና ስራዎች ላይ ያተኮረ "የከተማው መናኝ" መጽሐፍንም በመጻፍ የበለጠ እውቅናን አትርፏል።

 

የዛሬ የጋዜጠኝነት ሕይወቷን የምታካፍለን የሚዲያ ባለሙያ በእነዚህ ሁለት ባለሙያዎች መሀል የተገኘች ናት-መስከረም ጌታቸው። "የእህት እና ወንድሜን የጋዜጠኝነት ተሰጥዖ ያወቅኹት ከእኔ በኋላ ነው።የእኔ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የታወቀ ሲሆን የእነሱ 2 ደረጃ ተማሪ እያሉ ነው ተሰጥኦዋቸው የወጣው "ትላለች ትውልዷ እና እድገቷ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ነው። ለቤተሰቧ ሁለተኛ ልጅ ሁና ከአባቷ አቶ ጌታቸው አሞኘ እና ከእናቷ / ይመኙሻል ሙሉ 1977 ሰኔ 16 ተወለደች።መስከረም 1 ቀን ክርስትና በመነሳቷ መስከረም ተባለች።

 

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ፍኖተ-ሰላም ባከል 1 ደረጃ /ቤት 7 እና 8 ፍኖተ ሰላም .. 1 እና መለስተኛ ደረጃ /ቤት 2 ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በዳሞት 2 ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ማስተርስ ደግሞ በፎክሎርና ስነ ጽሑፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጨርሳለች።

 

                                              ሰልፍ ላይ ጠዋት ጠዋት ታነብ ነበር

 

መስከረም ጌታቸው 3 ክፍል ጀምራ የተለያዩ ስነ ጽሑፎችን በመጻፍ እና የሌሎችንም በመሰብሰብ በተማሪዎች ሰልፍ ላይ ጠዋት ጠዋት ታነብ ነበር። በትምህርቷ እስከ 8 ክፍል ድረስ 1 እስከ 3 የምትወጣ የደረጃ ተማሪ  በመሆኗ ከቤተሰብ ብዙም ተፅዕኖ የሚደርስባት አልነበረችም። ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በስነ ጽሑፍ በድራማ እና በሚኒ ሚዲያ እንቅስቃሴዎች በትምህርት ቤቶች መምህሮቿ ላይ ሳይቀር ተጽእኖ መፍጠር ችላለች። ባሳለፈቻቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ በክበባት እንቅስቃሴ ከፊት የምትሆነው መስከረም ይህ አላረካት ቢል ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ‹‹ሕይወት ፋና›› የተባለ ጸረ ኤች አይቪ ኤድስ ክበብ መሰረቱ። በወቅቱም በፍኖተ- ሰላም ከተማ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ነበር። "በተለያዩ ክበባት በሀላፊነት ላይ አገለግል ነበር፤ ሁሉም መምህራንንና ተማሪዎች የሚሰጡኝ ሞራል እና ድጋፍ ለዛሬዋ ማንነቴ ስንቅ ነው"  የምትለው መስከረም "2 ደረጃ ስገባ ግን ብዙ ሰዓቴን ለሚኒ ሚዲያ ስነ ጽሑፍና ድራማ በማዋሌ፣ ሴት በመሆኔም በታዳጊነት እድሜ በየመድረኩ መታየት፣ ለልምምድ ሲባል አምሽቶ መግባት ሲመጣ ቤተሰብ በተለይም እናቴ ቁጥጥሯ ጠበቅ ማድረግ ጀመረች።ነገር ግን በተለያዩ መድረኮች ትልልቅ ሽልማቶችን አገኝ ስለነበር ገመዷን አንዴ ጠበቅ አንዴ ላላ ታደርገው ነበር"

 

       በክፍት መኪና ላይ ሁና የሰራችው ማስታወቂያ

 

አንድ ጊዜ ከምእራብ ጎጃም ዞን ባለስልጣናቱ ይመጡና ለማኅበረሰቡ ስለማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ማስተዋወቅና የደን ጭፍጨፋን መቀነስ አለብን ለዚህ ስራም በከተማው የሚታወቅ ሰው ጠቁሙን ሲባሉ መስከረም ጌታቸው ትመረጣለች።የከተማዋ ኃላፊዎችም ከትምህርት በኋላ ይጠሯትና "ማስታወቂያ ልናሰራሽ ነው" ይሏታል።በሬዲዮ ከመስማት ውጭ እንዴት እንደሚሰራ ባታውቀውም በደስታ "እሽ" አለቻቸው።እናም ከትምህርት ቤታቸው አንዲት ልጅ ተመርጣ እንጀራ በአዲሱ ምድጃ እንጀራ እየጋገረች መስከረም ደግሞ በክፍት መኪና ላይ ሁና ስለማገዶ ቆጣቢነቱ እያስተዋወቀች በፍኖተ ሰላም ከተማና ዙሪያ የወረዳዋ ከተሞች ማስታወቂያውን ሰሩ።ባለስልጣናቱ ሲሄዱ በሙያዋ የመጀመሪያ ክፍያ የሆነውን 50 ብር ሰጧት።"በክፍት መኪና የጌታቸውን ልጅ ተመልከቷት እየተባለ ማስታወቂያ መስራት የሚሰጠው ክብር እንዳለ ሁኖ በወቅቱ 50 ብር በጣም ብዙ ነበር። ለእናቴ ያስተዋወቅሁትን ምድጃ ልግዛልሽ አልኳት።እሷም አልፈልግም አንቺ ደስ ያለሽን ግዥበት አለችኝ።"

 

      በልጅነት የሚድያ ልምምድ

 

ጋዜጠኛ ከመሆን ውጭ ምንም ህልም አልነበራትም።ፍኖተ ሰላም ከተማ በወቅቱ መጽሔት እና ጋዜጣ እንደልብ ማግኘት ስለማይቻል ለመስክ ስራ የሚመላለሱ አባቷን ከባህር ዳር እና አዲስ አበባ ታስገዛ ነበር።በከተማው በቀላሉ የሚገኘውን የበኩር ጋዜጣን ደግሞ ስጋ ግዥ ስትባል ከስጋው ላይ አንስታ ደሙን እያደረቀች አንዴ በዜና አንዴ በትረካ መልክ በንባብ ትለማመዳለች። የራሷን ስነ ጽሑፍ ስራዎችንም በመድብል መልክ በየክረምቱ ታዘጋጃለች። ቤት ውስጥ የዘፈን ካሴቶችን እየፈለገች በድብቅ በመሰረዝ የራሷን ስነ ጽሑፎችና ጋዜጦችን እያነበበች ትቀዳ  ነበር። አንዳንዴም ጓደኞቿን "ለምን ቃለ መጠይቅ አላደርጋችሁም?" እያለች ለምና የከተማው ቀይ መስቀል ቢሮ በማስመሸት እየቀዳችና መልሳ እየሰማች የጋዜጠኝነት ፍቅሯን ታስታግስ ነበር። 11 ክፍል እያለችም በጸረ ኤች አይ ኤድስ የክበባት እንቅስቃሴዋ  ወደ ሞሮኮ ለዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳትፎ ተመርጣ የነበር ቢሆንም ለጊዜው በማታስታውሰው ምክንያት ግን ጉዞ ቀረ።

 

አንድ ቀን እንዲህ ኾነ። በወቅቱ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበርና ለህክምና ወደ /ሰላም ሆስፒታል ትሄዳለች።ካርድ አውጥታ የህክምና ተራዋን ስትጠባበቅ አንድ የሬዲዮ መቅረጸ- ድምጽ የያዘ ሰው ታያለች።ጋዜጠኛ እንደሆነ እርግጠኛ ናት።ህክምናዋን ጥላ ወደ ሰውዬው ሮጠች። ግን አልደረሰችበትም።ስትመለስ ወረፋዋ አልፏታል።"ባገኘው ምን እንደምለው አላውቅም ግን ጋዜጠኛ እንደእኔ ቁሞ እየሄደ ሳይ ማመን አቃተኝ።የሆንኩም መሰለኝ።ያን ቀን አምላኬን ሳመሰግን አደርኩ"

 

                                    ያደረ ዜና

 

በየደረጃው ያሉ መምህራን ለእሷ የነበራቸው ድጋፍና ፍቅር የተለየ ነበር። 11 ክፍል የአማርኛ መምህሯ መምህር ግዛቸው ክፍል ውስጥ ዜና ይዘሽ እየመጣሽ አንብቢ ይሏት ነበርና አንድ ቀን ዝም ብትላቸው አንብቢ ሲሏት "ጋሼ የአደረ ዜና ነው "በማለቷ ተማሪዎቹ ይስቃሉ። የተወሰነ ጊዜም በቅርቦቿ የአደረ ዜና ይሏት ነበር። እሷ ግን የዜናን ትኩስነት በመረዳት ዜና መሆኑ አልፏል ለማለት ነበር የፈለገችው።

 

መስከረም ጌታቸው የመጀመሪያ ድግሪዋን ወዳጠናችበት ጎንደር ዩኒቨርስቲ ያመራቸው 1995 ነው ።የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ባለመኖሩ የስነ ጽሑፍና ቋንቋ ክፍል በመመደቧ በጣም ማልቀሷንና ዩኒቨርሲቲ ለመቀየርም ብዙ እንደጣረች ትገልጻለች። ይህም ጋዜጠኝነት የተማረ ብቻ ጋዜጠኛ ይሆናል የሚል የተሳሳተ አመለካከት ስለነበር ምኞቴ ሁሉ በአጭር ቀረ ከማለት ነበር።

 

  መስከረም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ

 

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በስነ- ጽሑፍ እና ድራማ ስራዎች 3ቱም የዩኒቨርስቲ ግቢዎች በሚዘጋጁ መርሐ ግብራት ታቀርብ ነበር። ማራኪ ካምፓስም ማራኪ ኤፍ ኤም የሚባል ራዲዮ ከመሰሎቿ ጋር ጀምረው አገልግሎት ሰጥተዋል።በቋንቋና ስነ- ጽሑፍ ትምህርት ክፍልም የስነ ጽሑፍ ምሽቶችን እያዘጋጁ ለተማሪዎችና ለመምህራን ያቀርቡ ነበር።በወቅቱ በዚህ እንቅስቃሴዋ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሐልም ነበረች። ከዩኒቨርስቲው ልትመረቅ ስትልም አንዳንድ መምህራን ጠርተው "መመረቂያ ውጤትሽ ጥሩ ነው፤ ለምን እዚሁ አትቀሪም?በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ጉዞ የትም አትደርሽም"አሏት። የእርሷ መልስ ግን "አልፈልግም አንድ ቀን ዜና አንብቤ ልሙት የሚል ነበር።የመመረቂያ ጽሑፏን በግእዝ ቋንቋ ላይ  "The role of Ethiopian orthodox church in preserving and preventing of gee’z language" በሚል ርእስ ነበር የሰራችው። የሚገርመው ግን በወቅቱ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ግእዝን በተመለከተ የሚያማክር መምህር አጥታ ርእስ ቀይሪ ስትባል ፍቃደኛ ባለመሆኗ  አንድ መምህር ነበር በፍቃደኝነት ያማከራት።

 

ሕልሟ እንደሚሳካ በማመንም 12 ክፍል ስትጨርስ ኋላም ከዩኒቨርስቲ ስትጨርስ አድራሻ እንቀያየር ሲሉ  ለጓደኞቿና መምህራን በዚህ ታገኙኛላችሁ በማለት የኢትዮጵያ ሬዲዮን ፖስታ ሳጥን ቁጥር ትሰጥ ነበር።

 

                                ህልም ሲሳካ

 

መስከረም ጌታቸው የዘመናት ህልሟን የሚፈታው ቀን ጥር 14 1999 እውን ሆነ :: በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሪፖርተርነት ተቀጠረች። በወቅቱ እህቷ ሃይማኖትም በኢትዮጵያ ራዲዮ ተቀጠረች። "ፈተናው ብዙ ዙሮች ያሉትና ወራትን የወሰደ ስለነበር ከፍኖተ ሰላም እየመጣሁ ነበር የምፈተነው። የመጨረሻ ማለፌን ስሰማ ውስጤ ተረበሸ።ያ ሁሉ የተመኘሁት፣ ብዙ የለፋሁበት ነገር እንዲህ ይሳካል ብዬ ማመን አቃተኝ።ለጓደኞቼ ለቀድሞ መምህሮቼ ሁሉ ደወልኩ። ሌላ ስራ ብቀጠር አስተማሪዎቼና ጓደኞቼ ራሱ የሚያዝኑብኝ ይመስለኛል። የሚገርመው ለፈተና ስመላለስ ኢቲቪ በር ላይ ፎቶ እነሳ ነበር ካላለፍኩ ደግመው አያስገቡኝም እያልኩ።ግን እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነበርና ከሕልሜ ጋር አገናኜኝ።"በማለት ያችን ቀን ታስታውሳለች። መስከረም ጌታቸው በጋዜጠኝነት ህይወቷ አስቀድማ ካነበቻቸው ዜናዎች አንዱ  በታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራን የሚይዝ ነበር :: ይህም የቅንጅት አመራሮች መፈታት ሰበር ዜና ሲሆን ለወትሮው መሰል ዜናዎች በቆዩና ልምድ ባላቸው ጋዜጠኞች የሚነበብ ቢሆንም ያን ቀን ግን መስከረም ተፈልጋ ተጠራች። የዜና ክፍል ሓላፊው "ይህንን ዜና አንብቢው" አሏት። በአጭር ጊዜ ምን ብሰራ ነው ይህን የመሰለ ዜና የተሰጠኝ ብላ ራሷን ጠየቀች። ዜናው የተፈቱትን ሁሉንም ስም ዝርዝር ያካተተ በመሆኑ በጣም ረጅም ነበር። ከሰራች በኋላ በየቦታው ሰው ቁሞ ሳይቀር ዜናውን ይሰማል።ስማቸውን ስትዘረዝርም እንትና ተፈቷል አልተፈታም ይላል።በሌላ ቀን አለቃዋን ለምን ግን ያን ዜና ሰጣችሁኝ? ብላ ጠየቀችው።መልሱ ዛሬም ድረስ ፈገግ ያስደርጋታል። "ስታነቢ ስለምትፈጥኝ ቶሎ እንድትጨርሽው"የሚል ነበር።

 

በወቅቱ ሁሉም አዲስ ጋዜጠኛ ዜና ክፍል ከተመደበ በኋላ ነበር ፍላጎቱ ታይቶ ወደ ሌላ ክፍል የሚዛወረውና 3 ወራት በኋላ ከዜና መዝናኛ ክፍልን ተቀላቀለች። ገና ተማሪ እያለች ጋዜጠኛ ስሆን እሰራቸዋለሁ ብላ የያዘቻቸውን እቅዶች አስገባች። እነዚህም "የንስር ዓይን ያጣው ቅርስ-ግእዝ" "ጋሽ ጀንበሬ" ምኒሊክ ወስናቸው ሕይወት ላይ፣ የሕሊና ጸሎት፣ታይተው የሚጠፉ የሽልማት ድርጅቶች ጉዳይ ጥቂቶች ናቸው። ተሰርተው አየር ላይ ሲውሉ የተመልካቹ ግብረ መልስ ጋዜጠኝነትን እስትንፋሷ ላደረገች መስከረም ሌላ ዓለም ውስጥ እንደመግባት ነበር።

 

                  መስከረም እና የኢቲቪ ገጠመኝ

 

ጋዜጠኛ የመኾኗን ደስታ አጣጥማ ሳትጨርስ ያልጠበቀችው አሳዛኝ ነገር ተከሰተ። ወቅቱ የፖለቲካ ውጥረቱ ብዙ ያልረገበበት እና በተለይም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወይንም አዲስ ተመራቂዎችን በጥርጣሬ የሚታዩበት ነበርና የሚተላለፈው ሁሉ ለትርጉም የተጋለጠ ኾነ። መስከረምም ይህ አጋጠማት። አንድ ቀን በእለቱ የሚሄዱ ሙዚቃዎችን መምረጥ ተራዋ ነበርና ለራሷ የወደደቻቸውን ሙዚቃዎች መርጣ ለኤዲተሯ አሳየች፡፡ የማስተባበሪያው ሓላፊም ፈረመችበትና ተላለፈ። በሚቀጥለው ቀን ሓላፊዋ ቢሮ ተጠራችና ተልእኮዋ ምን እንደሆነ ተጠየቀች። እሷ ግን እንዳልገባት መልሳ ጠየቀች።"ማታ የተላለፉ ሙዚቃዎች ቅንጅቶች ላይ ደርሷል እየተባለ በአንዳንዶች የሚነገረውን ወሬ የሚያግዝ ነው" አለቻት። የተመረጡት ሙዚቃዎች የዓለማየሁ እሸቴ "አይ ዘመን" እና የክራር ተጫዋቹ ተሾመ ደምሴ "አዳራሹ ቤቴ" የሚለው ነበር። ለማስረዳት ብትሞክርም አልተሳካም። ጉዳዩ አድጎ  የወቅቱ ስራ አስኪያጅ ወደ ኾኑት / ታቦር /መድኅን ትባረር የሚል ምክረ ሃሳብ ቀረበ እሳቸው ግን ገና አዲስን ሰራተኛ ማስተማር ነው ማባረር የሚሻለው በሚል ውድቅ አደረጉት። "በወቅቱ እሳቸውን ክፍል ምረጡ ሲባል ብቻ ነው የማወቃቸው። በእውነት እግዚአብሔር በእሳቸው አድሮ መልካምን አደረገልኝ እንጅ የዓመታት ምኞቴን እንደመንጠቅ ስለሆነ ለእኔ ከባድ ውሳኔ ነበር። የሚገርመው ከቀናት በኋላ ከጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ጋር ተጠራን። ጌጡ የምናከብረው ጋዜጠኛ ከመሆኑ አንፃር ስራ አስኪያጁ ቢሮ ከእርሱ መጠራት ራሱ ለእኔ ክብር ነበር። ከዚያም የምንሰራቸውን ስራዎች አድንቀው አዲስ ፕሮግራም በእኛ መጀመር እንደሚፈልጉ ነገሩን። ይህ ንግግር ከጌጡ ይልቅ ወራትን ላስቆጠርኩት ለእኔ አዲስ ሰራተኛ ትልቅ ሞራል ነበረው።"በማለት አጋጣሚውን ታስታውሳለች።

 

መዝናኛ ክፍል በርካታ ፕሮግራሞችን አቅርባለች። ጀግናው አትሌት ኃይሌ /ሥላሴን ጨምሮ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን የአንድ ለአንድ ቃለ  መጠይቅ አድርጋለች።ወደ አመራርነት በመምጣትም ቡድን መሪነት ሰርታለች።

 

                 አንቺ መስከረም ጌታቸው ነሽ ሌላ

 

አንድ ወቅት ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲዋሀዱ ሲወሰን ቀድሞ በጉጉት ታደምጣቸው  የነበሩ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጠኞች እሷ ካለችበት ክፍል ገቡ።  እነጋሽ ደምሴ ዳምጤ ጋሽ ደጄኔ ጥላሁን ብርቱካን ሐረገ ወይን ወይንሸት አስፋው ፣የእናት ፋንታ ውቤ ፣ዳንኤል ታደሰ እና ሌሎችም። አንድ ቀን ቢሮ አረፍ ባለችበት የምታከብረው ጋዜጠኛ ዳንኤል ታደሰ ወረቀቶችን ይዞ መጣ።"ቆይ አንች ጎጃም ሁነሽ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ልብወለድና ግጥም ትልኪ ነበር?" "አዎ" አለችው። "እነዚህን የላክሽው አንቺ መስከረም ጌታቸው ነሽ ሌላ ብዬ ነው እኮ" ብሎ ተማሪ እያለች ለቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም የላከቻቸውን ልብወለዶች አሳያት።ደነገጠች። አዘጋጆቹን እንዲማርክ ብላ ቃላት የመረጠችውና  ወረቀቱን ለማስዋብ የጣረችው ትዝ አላት። ከየት እንዳገኘው ጠየቀችው። ዳንኤል ታደሰም በወቅቱ የወደዳቸውን ስራዎች ከተላለፉ በኋላ ራሱ በክብር እንደሚያስቀምጣቸው ነገራት። ይህ አጋጣሚ የማይረሳት ሁኖ አለፈ።

 

             የዶክመንተሪ ክፍል ሀላፊ እና ጎበዝ የዘጋቢ ፊልም ባለሙያ

 

  የኋላ ኋላ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ክፍልን ሲያዋቅር በሓላፊነት ተዛወረች። የራሷን ስራዎች ከመስራት ባለፈም አጠቃላይ የዘጋቢ ፊልም ስራዎችን አስተባብራለች፡፡ ለአመታት መርታለች።"በጋዜጠኝነት ሕይወቴ  ዘጋቢ ፊልም ስራ በጣም እወደዋለሁ። ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ እና በየጊዜው ራስህን እንድታሳድግ የሚያስገድድ ነው ።መጀመሪያ ወደ ክፍሉ ስገባ ብቃወምም በኋላ ግን የራሴን አቅም እንድፈትሽ ስላደረገኝ ወድጀዋለሁ" ትላለች። መስከረም በተመልካች ዘንድ በተለይም ብዙ ሴት ጋዜጠኞች በማይታዩበት አስቸጋሪው የዶክመንተሪ ስራ ውስጥ የራሷን አሻራ አሳርፋለች። ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራዎችንም ሰርታለች።ጥቂቶችም -

 

 "እንደገና" የሕዳሴ ግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ በኋላ የመጀመሪያው ዘጋቢ ፊልም ሲሆን የቀደመ ገናና ታሪካችንን ለመመለስ እና መሀል ላይ ከነበረው ጠባሳችን ለመንጻት ያለን እድል ስለመሆኑ የተሰራ እና ብዙዎች ላይ ቁጭት የፈጠረ

 

 "ሐራም" በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛት ላይ የተሰራ

 

 "ደወል" በሕገ ወጥ ስደት ላይ ታንዛኒያ ድረስ በመሄድ የተሰራ

 

 "የጉባ ተጋድሎ" በሕዳሴ ግድቡ ላይ የሰራተኞችን ጥረት እና የሕዝቡን የማያቋርጥ ድጋፍ በተመለከተ የተሰሩት ይገኙበታል።

 

የቀድሞ ሁለቱን ጠቅላይ ሚኒስትሮች (// መለስ ዜናዊ እና // /ማርያም ደሳለኝ)  እና የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊን ባን ሙን ጨምሮ በርካቶችን በተለይም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ቃለ መጥይቅ አድርጋለች። ከዘጋቢ ፊልም ስራዎች ባለፈም የተለያዩ ሀገራዊ መድረኮችን መርታለች።የተወሰኑትም᎓-

 

የቀደሙት // መለስ ዜናዊ እና // /ማርያም ደሳለኝ የተገኙባቸው የሕዳሴ ግድቡን የተመለከቱ የተለያዩ ሕዝባዊ የንቅናቄ ፕሮግራሞች በሚሊኒየም አዳራሽ

 

/ /ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ይፋ የተደረገውን ሀገራዊ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ንቅናቄ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ

 

ከዚህ በተጨማሪም በም// ደመቀ መኮንን የሚመራው ሀገር አቀፍ የሕገ ውጥ ስደት ተከላካይ ግብረ ሐይል ውስጥ አባል በመሆን ሙያዊ እና የዜግነት ግዴታዋን ተወጥታለች።

 

"በጋዜጠኝነት ሕይወቴ በሕዳሴ ግድቡና ሕገ ወጥ ስደትን በተመለከተ ለሰራኋቸው ስራዎች ትልቅ ቦታ አለኝ።እንደ ጣቢያ ሁሉም ባለሙያ ጋር ተናበን በመስራትም በወቅቱ ተጽዕኖ ፈጥረናል ብዬ አምናለሁ። በግሌም ብዙ የለፋሁባቸው በሕገ ወጥ ስደት ስራዎቼም እስከሕይወት መስዋእትነት የሚያደርስ አደጋ የተጋፈጥኩበት ነበር። ከሕገ ወጥ ደላሎች ቤት ከባልደረቦቼ ጋር ራሳችንን ደብቀን ተጓዥ መስለን በመግባት መረጃ ሰብስበናል። እኔን ከለዩኝ በኋላ ግን የስልክ ማስፈራሪያዎች ነበሩ።አዲስ አበባ ተመልሼም በተለያየ መንገድ መረጃዎችን እንዳላወጣ ማስጠንቀቂያ ይላክልኝ ነበር።ታንዛኒያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ፖሊስ ሲያገኛቸው ደላሎች መኪናውን ገልብጠው 40 ሲሞቱ ሂጄ ነበር።በወቅቱ ወደ ደላሎች ሰፈር ያውም በሌሊት ነበር የሄድነው፡፡ ከባድ ስሜት ነበረው።  ግን ይህ አያስፈራህም ምክንያቱም ፈተናዎች የጋዜጠኝነት አንድ ገጽታ ናቸውና።"

 

                        መስከረም እና ስልጠና

 

ጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸው የሙያ ክህሎቷን ለማሳደግ ከምታደርገው ግላዊ ጥረት ባለፈ በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ስልጠናዎችን ተከታትላለች :: ከእነዚህ ውስጥም :-

 

ዮጋንዳ ኢንቴቤ በመሄድ አሜሪካ ኢምባሲ  ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጥምረት ጋር በመሆን ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋዜጠኞች ያዘጋጀው በውሃ ሀብት አጠቃቀምና የተፋሰስ ሀገራት የሚዲያ ስራዎች ትኩረት ምን መሆን አለበት በሚል ጉዳይ ስልጠና ወስዳለች። ይህም የኾነው በሕዳሴ ግድቡ ላይ የሰራቻቸውን ስራዎች በመመልከት ኢምባሲው በራሱ  በላከላት ግብዣ ነው

 

ኬኒያ በመሄድ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኞች ጋር ሴቶች በግጭት አፈታት ያላቸውን ሚና በተመለከተ

 

ቢቢሲ /ኢንተር ኒውስ በተለያየ ጊዜ የሚዲያ ስልጠናዎች

 

የአመራርነት ስልጠና ከተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወስዳለች

 

         አስከሬን መሀል ቁመሽ ስትናገሪ……

 

መስከረም ጌታቸው ለአመነችበት ነገር ደፋር እና በራሷ የምትተማመን ሴት ስለመሆኗ ብዙዎች ይመሰክራሉ። እርሷ  ይህ የአስተዳደጓ ውጤት መሆኑን ትናገራለች። "ቤተሰብ ዝም በይ ብሎ ሳይሆን ተናገሪ ልስማሽ ብሎ ነው ያሳደገኝ በተጨማሪም ከልጅነት ጀምሮ መድረክ ላይ ወጥቶ መናገርን በብዙ ሰው ፊት መቆምን መለማመዴ ጠቅሞኛል "ስትል ትገልጻለች።በጠባይዋ ግልጽና ተግባቢ ናት። እርሷ ግን "አዲስ ሰው ቶሎ መተዋወቅ ላይ አንዳንዴ እቸገራለሁ" ትላለች።መስከረም ጌታቸው ኢትዮጵያን በሙሉ በሚባል ደረጃ በሙያዋ  ዙራለች።አሜሪካ ፣ካናዳ እና ቻይና ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የመሄድ እድል አግኝታለች። ሀገሯን ከቃላት በላይ ትወዳለች፡፡ የተለያዩ የውጭ እድሎች ቢኖሯትም ከቤተሰብ ጀምሮ ግፊት ቢኖርም ለእርሷ ግን የማይታሰብ ነው። ከተማሪነት ጀምሮ  በትምህርቷ ደረጃ በመያዝ በስነ ጽሑፍ ውድድሮች፣በዮኒቨርስቲ ቆይታዋ ከዮኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት እጅና ከሌሎችም ምስክር ወረቀቶችንና መጻሕፍት ፣በኢቲቪ በተለያዩ አመታት  በከፍተኛ አፈጻጸም ተከታታይ ሽልማቶችን ስታገኝ  "ሐራም" በተሰኘው ዘጋቢ ፊልሟ ቢቢሲ ሴቶችና ሕጻናት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞችን ባወዳደረበት ወቅት እጩ ለመሆን ችሎ ነበር። ከጠ/ /ማርያም ደሳለኝ እጅ ሳይቀር ተሸልማለች። ለእሷ ግን ከእነዚህ ኹሉ የሚበልጠው ሌላ ነው "አንድ ቀን መንፈሳዊ ጉዞ አድርገን አንድ ገዳም ገባሁ።ከቅዳሴ በኋላ የግል ጸሎት ሳደርግ አንድ በኑሮ ደከም ያሉ እናት መጥተው ተቀመጡ።ከሁኔታቸው እኔን ማናገር እንደፈለጉ ስለገባኝ እንደጨረስኩ ሰላም አልኳቸው።ደረታቸው እየደቁ አንቺ በዚያ በርሀ ወገኖችሽን ፍለጋ የሄድሽው ነሽ አስከሬን መሀል ቁመሽ ስትናገሪ እያሉ ይደቃሉ።እኔም ሰው እንዳንረብሽ በዐይኔ ብቻ አዎ አልኳቸው። እኔ የምሰጥሽ የለኝም እሷ ትጠብቅሽ ይህንን ጸበል ተቀበይኝ ብለው ጸበል ሰጡኝ ለእኔ ከዚህ በላይ ስጦታ የለም"

 

              መስከረም ጌታቸው የውሳኔ ሰው ናት

 

በስራዋ እልኸኛ ናት የአሰበችው ካልሆነ እንቅልፍ የላትም።አንዴ እንዲህ ኾነ አሟት ወደ ሆስፒታል መሄድ ነበረባት። የጀመረችውን ሳትጨርስ ልትተኛ ነው።ስለሆነም ቢያንስ ቃለ መጠይቆቼን ልጨርስ ብላ ወደ ቦሌ አመራች። ቃለ መጠይቁ ከተማው እንዲታይ በሚል ከረጅም ሕንጻ ቴራስ ጫፍ ላይ ነበር። ቁማ ስትጠይቅ ነበር ከደቂቃዎች በኋላ "ራሴን ያገኘሁት አንድ ክፍል ውስጥ በሰው ተከብቤ የምጠይቃቸው ሰውዬ ክንድ ላይ ነበር። ራሷን ስታ ነው ውሃ እያሉ ይጮሀሉ። ከነበርኩበት ቦታ አንፃር አወዳደቄ ማማሩ እንጅ ከባድ ነበር። እንደዚህ እየጠየቅሁ 2 ጊዜ የወደቅሁበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ።"

 

በርካታ አመታትን በሓላፊነት ስትሰራ ብዙዎች የውሳኔ ሰው ናት ይሏታል።"ይህ ጠባዬ ለአንዳንዶች አይመቻቸውም። ግን እንደሓላፊ ወንበሩ የተሰጠህ ልትጠይቅም ስታጠፋ ደግሞ ልትጠየቅም ነው።በዚህ አልጸጸትም። እኔ ፈጣሪን የሚያስከፋ ነገርን አለማድረጌን ብቻ ነው እርግጠኛ መሆን ምፈልገው። ሓላፊነት በህሊና መኖርን የግድ ይላል። ሕሊናችን ደሞ በምናምነው አምላክ መገዛት አለበት ያኔ ውሳኔዎችህ ትክክል ይሆናሉ"

 

ለዚህ ደረጃዋ አርአያ የምታደርገውን ስትገልጽም "በጋዜጠኝነት ሙያዬ አርአያ የማደርገው ኢትዮጵያ ራዲዮን እንደ ጣቢያ ነው ።ከጠዋት እስከማታ ያሉትን ፕሮግራሞች የሚያዘጋጁት ጋዜጠኞች እንደመክሊታቸው ለእኔ አስተዋጽዖ አድርገዋል።እነሱን ስሰማ ነው ያደኩት፤ ሁሉንም ለመሆን ነው የተመኘሁት።"ትላለች።

 

መስከረም ጌታቸው ሁለተኛ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፎክሎር እና ስነ ጽሑፍ  2007 . የያዘች ሲሆን በመንጃ ጎሳ የማንነት ተረኮች ላይ ነበር ጥናቷን የሰራችው።  2008 መስከረም ወር ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በፍቃደኝነት ከለቀቀች በኋላ መስከረም ጌታቸው መልቲ ሚዲያ የሚል ድርጅት በመክፈት በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችን ለተቋማት ሰርታለች፡፡ ከፋና ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት በመግዛትም አስተላልፋለች።ከእነዚህም መካከል "ሞገደኛው ብእር" በአቤ ጉበኛ ሕይወት ላይ ያጠነጠነ "የምሁራን ጉዞ "በሀገራችን ምሁራን ሀገራዊ አበርክቶ ላይ "የአንድነት መንገድ" በኢትዮጵያዊ አንድነት ምንነት ላይ ያተኮሩ ይገኙበታል። 2012 . በኋላ የግል ስራዋን ለጊዜው በማቆም ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት ዙራለች።በአሁኑ ሰዓትም የማኅበረ ቅዱሳንን ቴሌቪዥን ሓላፊ በመሆን ታገለግላለች።"አስቀድሞ በዚህ ደረጃ ባይሆንም አገልግሎት ውስጥ ነበርኩኝ ነገር ግን ከርቀት ይልቅ ቀርበን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የምናገለግልበት ሰዓት እንደሆነ ስለተሰማኝ የምወደውን ሙያዬን ለጊዜው አቁሜ አዲሱን ሚዲያ ማገዝ እንዳለብኝ አምኜ ነው የገባሁት።በዚህም ከገንዘብ ይልቅ በበረከት እና በሰላም መኖርን አትርፌበታለሁ። መንፈሳዊ ሚዲያን መምራት ከሌላ ሚዲያ ሓላፊነት በጣም ይለያል። በእውቀት እና ጠንካራ አሰራር በመዘርጋት ብቻ ሳይሆን እምነትን አስቀድመህ መምራት ያስፈልጋል። ይህ እድልም ፈተናም ያደርገዋል። "ትላለች። በቀጣይ ግን ወደ ግል ስራዋ በመመለስና መልቲሚዲያዋን በማሳደግ ብዙዎች የሚርቁትን የዘጋቢ ፊልም ዘርፍ በካምፓኒ ደረጃ የማቋቋም ሕልም አላት።

 

መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መስራች ሀሳብ የሚንጸባረቅበት የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት ያመኑበት አቋም ሲሆን የባለታሪኳን አበርክቶ ጨምቀን የምናቀርብበት ነው፡፡

 

መስከረም ጌታቸው   ጥር 14 2014 ሲመጣ ወደ ሚድያ የገባችበትን 15 አመት ታስባለች፡፡ ባለፉት 15 አመታት በሙያዋ አንዳንዴ እንደ አቅሟ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአቅሟ በላይ ሰርታለች፡፡ በተለይ ጠንካራ በሳል የቲቪ ዘጋቢ ፊልሞች ወደ ተመልካች በማድረስ ተመስክሮላታል፡፡ መስከረምን በቅርበት የሚያውቁ አለቃዋ ሆነው የሰሩ እንዲሁም እርሷ አለቃቸው ሆና የመራቻቸው እንደሚናገሩት መስከረም ትጋትን የተላበሰች ብሩህ አእምሮ ያላት ጋዜጠኛ ነች፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ታሪካቸው ሲከተብ ቢያንስ የሚነገር ነገር ስላላቸው ለትውልዱ አንዳች ጠቃሚ ነገር ያስተላልፋሉ፡፡ ዛሬ ጠንክሮ የሰራ ነገ ታሪኩ በደማቅ ብእር ይጻፍለታል፡፡ ያልሰራ ደግሞ ይረሳል፡፡ የዚህ የአማርኛ ዊኪፒዲያ ዋና ግብ የደከሙትን ፤ወይም አንድ ሚና ያበረከቱትን ብቻ ለይቶ በማውጣት ከታሪክ ማህደር ላይ ማስፈር  ነው፡፡ መስከረም ከዚህ የታሪክ ማህደር ውስጥ ታሪኳ እንዲሰፍር በቂ እና አሳማኝ ምክንያቶች አሉን፡፡ አንደኛ ጽናትን በሚጠይቀው የቲቪ ጋዜጠኝነት ውስጥ  ፈታኝ የሆኑ ዘጋቢ ፊልሞች አየር ላይ እንዲውሉ አድርጋለች፡፡  በተጨማሪም ህልሟን ለማሳካት በልጅነት ታደርጋቸው የነበሩትን ጅምሮች አጠናክራ በመቀጠል አቅሟ እምን ድረስ እንደሆነ አሳይታለች፡፡ መሪም ሆና በሰራችባቸው ጊዜያት የለወጠቻቸው ነገሮች አሉ፡፡

 

መስከረም ጌታቸው እስከ 2 ዲግሪ በመማርም በእውቀት ራስን  ማሻሻል እንደሚቻል ታምናለች፡፡ በኢትዮጵያ የሴት ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ  እንደ ብዙወንድማገኝ ተገኝ፤  እንደእነ ሂሩት መንግስቴ ገነት  አሸብር  አይነት  ሰዎች ታሪካቸው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የሴት ጋዜጠኝነት ታሪክ ላይ ምርምር ለማድረግ ከተፈለገ የእነርሱ የስራ ጉዞ ቀዳሚ ምንጭ ይሆናል፡፡ መስከረም ባለፉት 15 አመታት ባለፈችባቸው አመታት ብዙ ሁኔታዎችን ያሳለፈችና የታሪክ ምስክር ስለሆነች ታሪኩዋ ቢሰነድ ምርምር ለሚያደርጉ ለአዲሱ ትውልድም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ትልቅ ሚና ከአሁን በኋላ ያበረክታሉ ብለን ተስፋ ከጣልንባቸው መካከል መስከረም አንዷ ናት፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት እና መስራቾች ሀገሩን የሚወድ ጠንካራ ሰው ወደፊት እንዲመጣ ጽኑ ምኞት አላቸው፡፡ ሰው በህይወት እያለ ታሪኩን በወጉ ቀኖችን በትክክል እየጠቀሰ ማስቀመጥ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ መስከረም ጌታቸው ዛሬ ታሪኳ ሲሰነድ ከእርሷ በኋላ ወደ ሚድያ የመጡ ሰዎች ይነቃቁበታል፡፡ ይማሩበታል፡፡ ዋናው የእኛ ግብም የሚድያን ሙያ ማስከበር የባለሙያዎችን ልምድ ሰንዶ ማስቀመጥ ስለሆነ የመስከረም 15 አመት የሚድያ ልምድም ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ የሚቆጠር ነው፡፡  በመሆኑም ህልሙን ያሳካ ሁሉ የሀገሩን አንድ ክፍተት እንደሞላ ይቆጠራል፡፡ መስከረም ጌታቸውም ህልምን እውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሚድያ ስራን በድል ስላጠናቀቀች የአማርኛ ዊኪፒዲያ ላይ በወርቃማ ብእር ታሪኩን ልንከትበው በቅተናል፡፡/ ይህ አጭር ግለ-ታሪክ ከባለታሪኳ የተገኘን መረጃ መሰረት በማድረግ በቅርብ የሚያውቋትን ባልደረቦች በማነጋገር የተጠናከረ ነው፡፡ በተጨማሪም አየር  ላይ ያዋላቻቸውን መናዶዎች በበቂ ሁኔታ በመመልከት የተሰናዳ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ  እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 9 2014 ከማታው 5 ሰአት 28 ደቂቃ የተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና የአማርኛ ዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች