7. መኩሪያ መካሻ /ረዳት ፕሮፌሰር/ Mekuria Mekasha
/(Assistant Professor)
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ120 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ
ሊያሳትም
እንደሆነ
ይታወቃል፡፡
እስከዚያ
ድረስ
ታሪካቸው
በዚህ
ዊኪፒዲያ
እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል የጋዜጠኝነት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ነው፡፡
ረ /ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ከ40 ዓመታት በላይ በሙያው ያገለገለ ሲሆን፡የሰው ልጅ ሰብዕና የሚገነባው በሦስት ሙያዊ መሰረቶች ላይ ነው ይላል፤በውትደርና፣በጋዜጠኝነት
እና በመምህርነት ሙያ እሱ ደግሞ በሁሉም ያለፈ ነው፡፡
ከመነሻው ጀምሮ አሁን እስከ ደረሰበትያለው ታሪኩ በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡
የሊሙ ገነቱ መኩሪያ
መኩሪያ መካሻ በቀድሞ አጠራር በከፋ ክፍለ ሀገር ሊሙ ገነት ከተማ በእርሻ ስራ ይተዳደሩ ከነበሩት ከአባቱ አቶ መካሻ ወልዴ እና ከእናቱ ወ/ሮ ንጋቷ በየነ በታህሳስ 1951 ነበር የተወለደው፡፡
በኋላም ቤተሰቦቹ ወደ አትናጎ ስለተዘዋወሩ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በዚያው ተምሯል፡፡
በቡና ተክል በተከበበችው እና በተወለደባት አረንጓዴያማዋ ሊሙ ገነት ተመልሶ የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን
ተምሯል፤ከአውራጃውም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ጅማ ሚያዝያ 27 ትምህርት ቤት በመዘዋወር ቀጣይ ትምህርቱን በዚያው ቀጠለ፡፡
ሆኖም ወቅቱ የአብዮት ማዕበል በጅማ አካባቢ የኢህአፓ እንቅስቃሴ የተስፋፋበት፣የሶማሊያ ጦርነትና የኤርትራ አማጺያን ሀገሪቱን ወጥረው የያዙበት ወቅት ነበርና ትምህርቱን ሊጨርስ ጥቂት ሲቀረው ገነት ጦር ትምህርት ቤትን ተቀላቅሎ በእጩ መኮንንነት በ1970 ዓ.ም በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተመረቀ፡፡
በ20 አመቱ ጉዞ ወደ ራሺያ
ከስልጠናውም በኋላ ያኔ አዲስ በተቋቋመው የበታች ሹማምንቶች አካዳሚ የአሁኑ አዋሽ አርባ ላይ የሚገኘው ተቋም ውስጥ በሜካናይዝድ ክፍል አሰልጣኝ መምህር ሆኖ ተመደበ፡፡በጊዜው የተለያዩ ተግባራትን ከከወነ በኋላ በ1972 ወደ ራሽያ የፓርቲ አመሰራረት (party construction) ለመማር ተላከ፡፡
ለ6 ወራት ይህንኑ ትምህርት ተከታትሎ ከተመለሰ በኋላም ምፅዋ 6ኛ ነበልባል ክ/ጦር ተመደበ፡፡በዚያም ጦሩ የፖለቲካ ዕውቀት እና ብስለት እንዲኖረው፣ለዓላማ እንዲዋጋ በማድረግ ስራን ጨምሮ እስከ 1974 ድረስ ሰሜን ዕዝ መምሪያ አስመራ ቆየ፡፡ከዚያም 22 ተራራ ክ/ጦር ጋር በቀይ ኮከብ ዘመቻ አፍእቤት-ባሸሬ ግንባር ተሰልፎ እናት ሀገሩን አገለገለ፡፡ለአገልግሎቱም
የዘማች
አርማ
ተሸላሚ
ሁኗል፡፡
ለጋዜጠኝነት ትምህርት ዳግሞ ወደ ራሺያ
መኩሪያ መካሻ ፣ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ የቲአትር ባለሙያ የመሆን ፍላጎት ነበረው፤በተለይ በመምህሩ አበራ የዕብዩ አማካይነት በሚፃፉት ቲአትሮች ላይ ትልልቅ ገፀ-ባህርያትን ወክሎ መሳተፍ ለዚህ መነሻው ነበር፤በኋላ በውትድርና ወቅትም ረዥሙን ጊዜ በማንበብ እናበማስተማር ያሳለፈ እና የተለያዩ ቦታዎች ላይ ለስራ ይንቀሳቀስ ስለነበረ ለስነፅሁፍ የበለጠ እንዲቀርብ እና እንዲያሳድገውም ረድቶታል፡፡
በቀይ ኮከብ ጥሪ ዘመቻ ላይም በፕሮፖጋንዳ እና ፅሁፍ ዝግጅቶች ላይ ሲሳተፍ እና ሲያሰለጥን ከቆየ በኋላ በ1975 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የጋዜጠኝነት የትምህርት እድል መጥቶ መኩሪያ ከክፍሉ እና ከሰሜን ዕዝ ተመርጦ ወደ አዲስአበባ በመምጣት በመስከረም
1976 ዓ.ም ለዚሁ ትምህርት ወደራሽያ አመራ፡፡
መኩሪያ ‹‹…የሩሲያ ሕዝብ ለአገሩ ያለው ፍቅር የተለየ ነው፤ እኔም በዛው በነበረኝ ቆይታ ማንኛውም እረፍቴ ላይ የተለያዩ የየሀገራቸውን ክፍሎች ተዘዋውሬ አይቻለሁ ይላል፤በቆይታውም እነሌኒንግራንድን፣በዓለማችን ታዋቂውን የባህል ማዕከል እና ሙዚየም የሆነውን ኤርሚታዥን፣ሚኒስክርን እና ኦዴሳን ጨምሮ የሐገሪቱን አብዛኛውን ክፍል ጎብኝቷል፡፡
እንደ ሁለተኛ ሐገሬ ነው የማያት በሚላት እና በሚወዳት ሩሲያ በ1981 ዓ.ም ከተማረበት የሎዎቭ የጋዜጠኝነት ት/ቤት በፓለቲካዊ፣ወታደራዊ ጋዜጠኝነት ትምህርት በማስተርስ ዲግሪ ተምሮ አጠናቆ ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡
ታጠቅና መኩሪያ
ከራሺያ ከተመለሰም በኋላ በመከላከያ የመጽሄት እና የጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በታጠቅ መጽሄት እና ጋዜጣ አርታኢነት፣የተለያዩ ፊቸር ፅሁፎችን በመጻፍ፣በጋዜጣው ላይ ደግሞ እንደ አምደኛ በአንድ አፍታ አምድ ስር ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ትችትንም ጭምር ይጽፍ ነበር፡፡
በ1983 ዓ.ም ከኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣት ጋር በተገናኘ ለ14 ዓመታት ካገለገለበት መከላከያና ከታጠቅ መጽሄት እናጋዜጣ ስራውን አቆመ፤ለስድስት
ወራትም
ተሀድሶ
ተብሎ
በሁርሶ
ታስሮ
ከቆየ
በኋላ
ስር አጥ ሆነ፡፡
እፎይታ እና መኩሪያ ለ10 አመት
መኩሪያ በጊዜው ስራ ስላልነበረው የተለያዩ ጓደኞቹ ቤት ይኖር የነበረ ቢሆንም መሐመድ ዑመር የተባለ ጅማ ይኖር የነበረ ሰው ቤት ቆይቶ ነበር፡፡ በጊዜው ህይወቴን ለወጠው ከሚልለት ሄራልድ እና አዲስዘመን ይሰራ ከነበረው እንዲሁም ቀድሞ ከሚያውቀው ከጋዜጠኛ አረፍዐይኔ ሐጎስ ጋር ተገናኘ፡፡አዲስ
ህይወት
ተጀመረ፡፡እፎይታ
በተሰኘው
እነሱ
በጀመሩት
መጽሄት
ላይ እንዲሰራ ባቀረቡለት ጥያቄ መሰረት በ1985 ዓ.ም ስራውን ጀመረ፡፡
እፎይታን የለወጠ ጀግና
በእፎይታ መፅሄት በቆየባቸው አስር ዓመታት መፅሄቱ እንዴት ተወዳጅ መሆን አለበት ሽፋኑስ ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ፤ መጽሄቱ ከግርግር እና ውዝግብ ማረፊያ ሆኖ ሰዎች የሚዝናኑበት እንዲሆን የተለያዩ አጫጭር ፅሁፎችን፣ወጎች እና የተለያዩ የራሽያ ትርጉሞች እንዲወጡ ያደርግ ነበር፤:
ሌላው እነጌጡተመስገን፣ነፃነትሰለሞን፣ፍሬዘውድ ተሾመ ፣ኤርሚያስ ስዩም እና ሌሎችም በርካታ ወጣት ልጆች ወደ ሙያው እንዲመጡ እና እንዲያልፉ ማድረግ ችሏል፡፡በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ልሳን የሆነው አዲስ ልሳን ጋዜጣ ሲቋቋም ከመስራቾቹ አንዱ ነበር፡፡
በ1990 ዓ.ም ከእፎይታ መጽሄት ባሻገርሳምንታዊ ጋዜጣን ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር እንዲጀመር አደረገ፡፡ጋዜጣው
ሲጀምርም
ከፊት
እና ከኋላ ገጹ ጀምሮ አዲስነገርን ይዞ የመጣ እና ተቀባይነትንም ያገኘ ነበር፡፡ጋዜጣው
በተለይ
ጀማሪ
ወጣት
ጸሀፍያን
እጃቸውን
እንዲያፍታቱ፣
የስነጽሁፍ
ችሎታቸውን
በተግባር
እንዲያስመሰክሩ
በር የከፈተ ነበር፡፡
ከእፎይታ ወደ እፍታ
መኩሪያ በዚህ ሂደት ብዙ እድገቶችን ከእፎይታ ጋር ያሳለፈ ሲሆን ከህትመቱን ማዘመን ባሻገር ወደ እፍታ መጽሃፍ እና ብሮድካስት ማምጣት ፍላጎትም ነበር፡፡ እፍታ መፅሀፍ ዝግጅት እንዲደረግና ወጣት ደራሲያን እንዲበረታቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡በኋላ ተቋሙ ሲዘጋም ለ6 ወራት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይም አምድ በመያዝ በኮንትራት መስራት ችሏል፡፡
ከጋዜጠኝነት ወደ መምህርነት ቀጥሎም መጽሀፍ ማሳተም
ከእነዚህ ጉዞዎች በኋላ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ኢንስቲትዩት ማስታወቂያ ሲያወጣ ተወዳድሮ ሌላኛው ትልቅ አስተዋጽኦ ያሳረፈበትን ስራውን በ1993 ዓ.ም ጀመረ፡፡
በዚህም ሙያው በርካቶችን በማፍራት ብዙዎችን ብቁ ማድረግ ችሏል፤ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማትም ጥናት በማድረግ እንዲሻሻሉ ከፍተኛ ሙያዊ አስተዋፅኦው የሚዘነጋ አይደለም፡፡
በመፅሀፉም ዘርፍ ኮዞኖስትራ የተሰኘውን የማፊያ ታሪክን የያዘን መጽሀፍ አጠር አድርጎ ከማሳተም በተጨማሪም የሩስያ ስነጽሁፍ እና የራሱን የግል ወጎች፣የጉዞ ማስታወሻዎችን እና ከቤተመንግስት ዶሴ የብላቴን ጌታ ወልደማርያም አየለ ታሪክንም ጨምሮ ሌሎችንምመጽሀፎች አሳትሟል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ከ30 በላይ የስልጠና ማኑዋሎችንና የጥናት ወረቀቶችን ያሰናዳ ሲሆን ከ16 በላይ የትርጉም ስራዎችን እንደሰራ ካሪኩለም ሲቪው ላይ ሰፍሯል፡፡9 አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችም ላይም በመሳተፍ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ለሚድያው እድገት የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡
በሚድያው ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የሚድያና የኮሚኒኬሽን ፖሊሲ በዩኤንዲፒ ድጋፍ ከአንድ የውጭ ሀገር ኤክስፐርት ጋር ሰርቶ ለመንግስት አስረክቧል፡፡ መንግስትም ይህን ፖሊስ አጽድቆ ጥቅም ላይ አውሎታል፡፡ለዚህም ከኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከነበሩት ካሳሁን ጎፌ የምስጅር ወረቀት ሊያገኝ ችሏል፡፡
በአርትኦትም ከበርካቶች ጋር የሰራ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች(አዲስ ዘመን፣ሄራልድ፣ፎርቹን፣አዲስ ነገር፣አዲስ ዜና፣ኢትዮጵስ፣አዲስ አድማስ) መጣጥፎችን፣አርቲክሎችን በማሳተም ለአንባቢው እንዲደርስ አድርጓል፡፡
የሚያነባቸውን መጽሀፍም በመገምገም በተለያዩ የማቅረቢያ መንገዶች የሚያደርስ ሲሆን ይህም ከክፍል ውስጥ መምህርነት ባሻገር የእርሱን ችሎታም የሚያሳይነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ወደ አሜሪካ፣ደቡብ አፍሪካ(ቶምሰን ፋውንዴሽን በሮይተርስ ማእከል)፣እስራኤል በመጓዝ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ሙያውን አዳብሯል፡፡አልፎ ተርፎም በጣልያን በኮሙኒኬሽንና በባህላዊ(ሓሪሶት) ፖሊሲ ማናጅመንት ሁለተኛ ደረጃ ማስተርስ ተቀዳጅቷል፡፡
የሚዲያ ኢንዱስትሪው እንዲጎለብትም በፕሬስ ፣በኢዜአ የቦርድ አባል በመሆን አገልግሏል ፡፡እያገለገለም ይገኛል፡፡በተጨማሪም የሃገራችን ሥነ ጥበብና ባህል እንዲጎለብት ከወዳጆቹ ጋር ተደራጅተው ታዛ የተሰኘ መጽሄት በማሳተም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለጥበብ ብልፅግና እየሰራ ይገኛል፡፡
በቅርቡ 105 ጋዜጠኞች በጋራ በመሰርቱ ዋርካ ሚዲያ ላይም በሰብሳቢነት በማገልገልም ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደፊትም ወደራዲዮና ሌላ የብሮድካስት አማራጭ የማስፋት ሃሳብ አለው፡፡አብረው ከተሰለፉ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆንም ኤፍ ኤም 104.1የሬዲዮ ጣቢያ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡
የረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ምኞት
የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት በሙያና በገንቢ ጋዜጠኝነት እንዲመራ ምኞቴ ነው።ከአዝማሪነት መውጣት አለበት።ጋዜጠኞቻችን የሰከኑና ደርዝ ያላቸው እንዲሆኑ ምኞቴ ነው።ከለብ ለብና ከእሳት አደጋ አሰራር መውጣት አለባቸው።የኛ ጋዜጠኝነት መሪ አላገኘም፣ከዚህ ዕውር ድንብር መውጣት አለበት።መሪዎቹ
በቴክኒክ
ክህሎትና
ዕውቀት
የበለጸጉ፣ሰውን
የመምራት
ጥበብ
ያላቸው
የሰከኑ
እንዲሆኑ
እመኛለሁ።
ቤተሰብ
መኩሪያ መካሻ ቤተሰብ የመሰረተው እፎይታ መጽሄት በነበረበት ወቅት በ1987 አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ልጆች አሉት፡፡ሴት ልጁ በቅርቡ ከአ.አ.ዩ ጥቁር አንበሳ ኮሌጅ በሕክምና የተመረቀች ስትሆን ታናሽየው ደግሞ በኢንቴርየር ዲዛይነር ትምህርት በስኮላርሺፕ በጣልያኑ ፔሩጃ ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ ይገኛል፡፡
አረፍ አይኔ ሃጎስ ስለ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ
አረፍአይኔ ሀጎስ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በጋዜጠኝነት ብሎም በመጽሀፍ ደራሲነት ያገለገለ ሲሆን መኩሪያን ከ30 አመት በላይ ያውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አሁኑ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ በነበረችበትና በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጐች ሕይወት ላይ ጭፍንና የጅምላ ውሳኔዎች ይሰጡ በነበረበት ጊዜ ነበር ከመኩሪያ መካሻ ጋር የተዋወቅነው። መኩሪያ ከሰለባዎቹ አንዱ ነበር። በወቅቱ የእፎይታ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ስለነበርኩ ከእኛ ዘንድ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸልኝ። ጥቂት ጥያቄዎችን ካቀረብኩለት በኋላ ከአሥር ዓመታት በላይ በሙያው ውስጥ ያለፈችው ነፍሴ በጎውን ስላመላከተችኝ ከእኛ ጋር ተቀላቀለ።
ብዙም ሳይቆይ በራሱ ጥረትና ሥልታዊ አካሂድ፤ ችሎታም ተጨምሮበት፣ ብቃቱን ማሳየት ጀመረ። በመሆኑም ከመጽሔት ዝግጅት ክፍሉ ከወጣሁ በኋላ ምክትል ዋና አዘጋጅ ለመሆን በቃ። በነዚያ ጊዜያት ጠቃሚ ጽሁፎችን ከማበርከቱም በተጨማሪ የመጽሔቱ ዲዛይነር በመሆን ሰርቷል። ከመኩሪያ ጋር ከዚያን በፊትም ክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮ ይባል በነበረው ተቋም አብረን አገልግለናል።
መኩሪያ ባህርዩ የማይለዋወጥ፣ የሰከነ ፣ ትሁትና በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸ ሰው ነው። እናም እነሆ በመጨረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ለመሆን በቅቷል። እኔም በዚያ ተቋም ለአጭር ጊዜ በመምህርነት ባገለገልሁበት ጊዜ በእውቀቱና በሥነ ምግባሩ በተማሪዎቹ ዘንድ ከበሬታን ያተረፈ እንደነበረ መመሥከር እችላለሁ።
ራሄል አበበ ስለ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ
ራሄል አበበ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዋና አዘጋጅነት እያገለገለች ስትሆን ስለመምህሯ የሚከተለውን ሀሳብ አስፍራለች፡፡
ተወዳዳሪ የሌለው መምህር
በመጀመሪያ ትልልቅ ባለሙያዎች እያሉ እኔ ስለማደንቀው መምህሬ ጥቂትም ቢሆን ምስክርነት ለመስጠት ዕድሉን በማግኘቴ የተሰማኝ ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ያለማጋነን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ፋኩሊቲ የወጣ ተማሪ ሁሉ የሚያውቀው፤ በተለይም በፊቸር አርቲክል አጻጻፍና በህትመት ሌይአውትና ዲዛይን ኮርሶች ተወዳዳሪ የሌለው መምህር ስለመሆኑ እኔን ጨምሮ በብዙዎች የሚመሰክርለት ነው።
ጋዜጠኞችን በመደገፍና በመቅረጽ ላይ ይገኛል
ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገር ራሱ የጻፋቸውንና የተረጎማቸውን ጽሁፎች ደጋግሜ አንብቤያለሁ፤ በእነርሱም ጭምር ብዙ ተምሬያለሁ። ፊቸር ለመጻፍ ስሞክር ቀድመው ወደ አእምሮዬ የሚመጡትም እንዴት መጻፍ እንዳለበት የሚያሳዩት የእርሱ ጽሁፎች ናቸው። በሌይአውትና ዲዛይንም እንዲሁ ክህሎቱን ለሌሎች በማስተላለፍ በርካቶችን የቀረጸ ነው፡፡ በትምህርት ቤት ከምናገኘው ዕውቀት በተጨማሪ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ ባለው አበርክቶም ብዙ ጋዜጠኞችን በመደገፍና በመቅረጽ ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በኢትዮጰያ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳረፈ እና አሁንም እያሳረፈ ያለ ወደፊትም በሚፈጠረው የሚዲያ ምህዳር ትልቅ ሚና የሚኖረው ታላቅ ባለሙያ ነው።
ጌጡ ተመስገን ስለ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ
ጌጡ ተመስገን ከ2ሚልዮን በላይ ተከታይ ያለውን የራሱ የፌስ ቡክ ገጽ ያለውና በሚድያ ስራ ከ20 አመት በላይ የዘለቀ ሲሆን ስለ ጋዜጠኛ መኩሪያ ይህን አሰፈረ፡፡
ቆንጥጦ ያሳደገኝ
በጋዜጠኝነት ሙያ በተግባር ፊደል ያስቆጠሩኝ ባለውለታዎቼ እጅ የምነሳቸው የኔታዎቼ (Mentors) የትየለሌ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህሬ (ረቡኒ) ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በሙያው
‹‹ቆንጥጦ
የማሳደግ››
ያህል
ትልቅ
ድርሻ
አለው።
እድለኛ
ሆኜ በሥራ ዓለምም አለቃዬ ሆኖ ተገናኝተናል። ምክር እና ተግሳፁን ማውሳት እፈልጋለሁ። አትርሱ! ...
በሙያችሁ
ሕዝባዊ
አመኔታ
እና ሕዝባዊ ከበሬታን ለማግኘት በሥራ መታተር አለባችሁ። ወገንተኝነታችሁ
ለአገርና
ለሕዝብ
ይሁን!
... አንድ
ዘገባ
(ለአንባቢ፣
ለአድማጭና
ለተመልካች)
ከመቅረቡ
በፊት
- ከርዕሰ-
ጉዳይ
መረጣ
ጀምሮ የመረጃ አሰባሰብ፣ የመረጃ አደረጃጀት እና የመረጃ እና ማስረጃ ትንተና ላይ ጥልቀት እና ጥንቃቄ አድርጉ። ምክንያቱም ጋዜጠኝነት ለአገር እና ለሕዝብ ዘብ የቆመ፤ ብእር የጨበጠ ወታደር ማለት ነው። ከሕግ አውጪ፣ ከሕግ ተርጓሚ እና ከሕግ አስፈፃሚ ቀጥሎ አራተኛ መንግሥት ሆኖ የሚሰራ፤ የታላቅ ሙያ ባለቤት ነዉ። ጆሮ ያለው ይስማ! - በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ የሚያነውራችሁን (ሂስ የሚሰጣችሁን) አክብሩ። በሙያችሁ ተጠያቂነት እና ግልጽነት ( Accountability & Transparency ) አሠራር ውስጥ መሥራት (መኖር)ን አትዘንጉ - እያለ የሙያ ልጆቹን በከፍታ (በላቀ ደረጃ) አሳድጎናል። መምህር ሆይ! - ልጆችህ እዚህ ደርሰናል። እጅ ነስተናል - ክብር እና ምስጋናውን ውሰድ።
አይናለም ሀድራ ማእሩፍ ስለ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ
ጋዜጠኛ አይናለም ሀድራ በኤንቢሲ ቲቪ ማኔጀር ስትሆን ስለ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ያላትን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ጋዜጠኝነትን በጽንሰ- ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ኖሮት የሚያስተምር ባለሙያ ነው፡፡ በተማሪነተ ቆይታዬ የሰጠኝን ኮርሶች ከጽንሰ ሃሳቡ ባለፈ ተጨባጭ ተግባራዊ ምሳሌዎችን ያውም ሃገራዊ እውነታዎችን እያጣቀሰ ያቀርብ ነበርና ይሄን አካሄዱን እጅግ አደንቅለታለሁ- ተጠቅሜበታለሁም፡፡
እንደ ብቁ መምህር የተማሪዎቹን አቅም በቅጡ ለይቶ የሚያውቅ የሚያበረታታ ብርቱ መምህር ነው፡፡
ከትምህርት ቤት ቆይታዬ በኋላም በተለያዩ አጋጣሚዎች ሙያዊ ምክርና ድጋፍ ሲያስፈልገኝ በመተማመን ከምሄድባቸው ሰዎች ቀዳሚው ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ‹‹እውቀትህን አካፍለሀል፤ አክብረህ ሙያዊ እርዳታህን /ምክርህን አልነፈግከንምና እናመሰግናለን፡፡
ከመምህርነተ ባለፈ የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣል፤ ለሚዲያ ኢንደስትሪው እጅግ ጠቃሚ ጥናቶችን ያጠናል፡፡ ረ/ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ለኢትዮጲያ የሚዲያ ኢንደስትሪ መልካም ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡
እኛም ተማሪዎቹ የእርሱን እግር እንከተላለን፡፡
እናመሰግናለን፡፡
ሲሳይ ገብረማሪያም ስለ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ
ሲሳይ ገብረማሪያም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የመዝናኛ ዘርፍ ምክትል አዘጋጅ ሲሆን ስ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ይህን ምስክርነት እነሆ ብሏል፡፡
የእውቀት
አባታችን
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዲግሪዬን ስማር አስተምሮኛል፡፡
በተለይ
ደግሞ
በሌይ
አውት
ንድፍ
ትምህርት፤
በፊቸር
ጽሁፍ
በቂ እውቀት እንድንቀስም የረዳን ድንቅ መምህራችን ነው፡፡በዚህም ሁላችንም ተማሪዎች የእውቀት አባታችን ነው ብንለው የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡በአሁኑ
ሰአት
በተለያዩ
መገናኛ
ብዙሀን
በተለያዩ
የሃላፊነት
ደረጃዎች
እያገለገሉ
ያሉ የሚድያ ሰዎች ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ያስተማራቸው ናቸው፡፡
የገዘፈ ሰብእና
ይህ በብዙዎች የሚመሰገን መምህር የገዘፈ ሰብእና ነው ያለው፡፡ ብዙ ተማሪዎች በእርሱ የማስተማር ክፍለ-ጊዜ ደስ ብሏቸው ይማራሉ፡፡ የማስተማር ዘዴው በቀላሉ ግልጽ የሆነና በተግባራዊ ማሳያዎች የታጀበ ነው፡፡ እኔ በግሌ ባለሁበት የመዝናኛ ዘርፍ ላይ ከጋዜጠኝነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ስደርስ ከረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ያገኘሁት እውቀት ጠቅሞኛል፡፡ ፊቸር እንዴት መጻፍ እንዳለበት በበቂ ሁኔታ ተንትኖ ስላስረዳኝ በተግባር እርሱ ያስተማረኝን መሰረት በማድረግ ጥሩ ስራ መስራት ችያለሁ፡፡
በህትመት ዘርፍ ላይ እንደመማሬ ጋዜጣ ላይ መጻፍ እንድችል የዚህ ታላቅ መምህር አስተዋጽኦ ቀላል አይባልም፡፡ ያስተማሩኝ መምህራን ሁሉም እውቀት እንዳገኝ የረዱኝ ቢሆንም የረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ግን በልዩነት በጣት ከሚቆጠሩ ካስተማሩኝ ምርጥ መምህራን ምናልባትም ብቸኛው ነው፡፡
እጄን በሚገባ አፍታትቻለሁ
እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በያዝኩበት ጊዜ በጋዜጠኝነት ተማሪ ቤት ትታተም በነበረችው ሃሌታ ጋዜጣ ላይ እጄን በሚገባ አፍታትቻለሁ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ በእንግሊዝኛም በአማርኛም እንድንጽፍ እያደረገ በጽንሰ-ሀሳብ የተማርነውን በተግባር ማየት እንድንችል አድርጎናል፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት የተቀናጀ የቤተሰብ ቅንጅት በተሰኘው አንድ ፕሮጀክት ውስጥ ለ 6 አመት በፍሪላንስ መጻፍ የቻልኩት ከመምህሬ መኩሪያ ባገኘሁት ታላቅ እውቀት ነው፡፡
ፈታ
ያለ
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መምህር ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ተርጓሚና ጸሀፊ ፤ የጥናት ወረቀት አቅራቢም ነው፡፡ እርሱ የጻፋቸውን መጣጥፎች ይመስጣሉ፡፡ እንዲህ ነው የሚጻፈው ከማለት በዘለለ ራሱ ጽፎ ስለሚያሳይ የተግባር መምህር ልለው እችላለሁ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ፈታ ያለ ብዙ የማያጨናንቅ ግን ብዙ እውቀት የሚያስጨብጥ ታላቅ ሰው ነው፡፡ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ በተለይ ባለፉት 21 አመታት ጋዜጠኞች ብቁ አድርጎ በማፍራት መምህሩ መኩሪያ ትልቅ አሻራ ማሳረፉን ሁላችንም የምንስተው አይመስለኝም፡፡ ለሰጠኝ እውቀት ምስጋናች ላቅ ያለ ነው፡፡ እኛም ከእርሱ የቃረምነውን እውቀት ይዘን በፕሮፌሽናሊዝም የተቃኘ ጋዜጠኝነትን ማስፈን አንደምንችል አንዳችም ጥርጥር የለኝም፡፡
መዝጊያ ፣ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መስራች አቋም የሚንጸባረቅበትና የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት ያመኑበት ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ በውትድርና በጋዜጠኝነት እንዲሁም በመምህርነት ያለፈ በመሆኑ ጠንካራ ሰብእናን ለመላበስ የቻለ ነው፡፡ ወታደር ነው ብለን ስናበቃ ደግሞ በአንደኛው እጁ ብእር ይይዛል፡፡ ብእር ይዞ ደግሞ ከወረቀት ያዋህዳል፡፡ ወታደር እና ጋዜጠኛ ሆኖ ካየነው በኋላ ደግሞ ጠመኔ ይዞ ከተማሪዎቹ ጋር ይገኛል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለፈው መኩሪያ ህይወትን እያነበበ፤ ከህይወት ጨልፎ እየተማረ ደግሞ ኑሮን እየጻፋት ከዚያ ጥበብን እያካፈለ በእርካታ ያሳልፋል፡፡እፎይታ
መጽሄት
እና ጋዜጣ ላይ በሰራባቸው ጊዜያት እንደ ኤዲተር ብቻ ሳይሆን እንደ ብእረኛ ከአንባቢ ጋር ተዋውቋል፡፡ ከሚድያ ውጭ ወጥቶ በሌላ ሙያ መሰማራት ስለማይሆንለት ደስ በሚለው ሙያ ሀገሩን ያገለግላል፡፡ፕሮፌሽናሊዝም እንዲሰፍንም ይታገላል፡፡ ትግሉ እንዲሳካም ያስተምራል፤ የምርምር ወረቀት ያቀርባል፤ ፖሊሲ ሲዘጋጅ አቅሙን ያወጣል፡፡ በሚድያ ላይ ሊሰሩ በታቀዱ በጎ ጅምሮች ላይ ሁሉ አሻራውን ለማሳረፍ እጁን ይዘረጋል፡፡ መኩሪያ በሚድያ አለም በተለይ ከ1985 ጀምሮ በቆየባቸው አመታት የአቅሙን ያህል ህግና ስርአትን የጠበቀ የጋዜጠኝነት ባህል እንዲኖር የተቻለውን አድርጓል፡፡ ራሱን ከንባብ ጋር እያቆራኘ እውቀትን ሲቀስም ስለኖረ በብዙዎች የሚመሰገን መሆን ቻለ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር
መኩሪያ
መካሻ
የጋዜጠኞች
አባት
የተባለው
ሁሉም በእውቀት የተሞሉ እንዲሆኑ ስለረዳ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚድያ ፕሮፌሽናሊዝምን አክብሮ ከሰራ እና የመኩሪያ ተማሪ ከሆነ መኩሪያ ውጤታማ ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ዊኪፒዲያ ስንል ያነጋገርናቸው በርካታ ከመኩሪያ እውቀት የቀሰሙቱ በአንድ ድምጽ እንዳሉት መምህሩ ከልቡ ያሳተምራል-የተከተለው አድጎ ይገኛል፡፡
እንደ መኩሪያ አይነት ሰዎች ታሪካቸው ዊኪፒዲያ ላይ ቢሰነድ ምናለበት ስንል ከአክብሮት ጋር ታሪኩን ለመጪው ትውልድ ሰንደናል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም ወደ ኋላ ተመልሶ ያለፈበትን እንዲያስታውስ ጋዜጠኛውን መምህሩን መኩሪያ እነሆ ከአንባቢው ጋር አስተዋውቀናል፡፡ የሰሩ ሰዎች ታሪካቸው እንዲሰነድ ስንሻ ሌሎችም በመኩሪያ ደረጃ ያሉ ታሪካቸው ያልተሰነደ ሰዎች ቢመጡ ደስታችን ሀያል ነው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ይህን የዊኪፒዲያ ታሪክ በጻፈውና በመሰረተው ሰው እይታ ሲታይ ሌሎችን የሚያበረታታ ድንቅ ሰው ነው፡፡ ከ23 አመት በፊት የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ መኩሪያን እንደማወቁ ይህ በ2230 ቃላት የተሰነደ
አጭር
ግለ-ታሪክ ሲያንስበት እንጂ ከዚህ በላይ ሊጻፍለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ተማሪ ቤት በሀገራችን የ20 አመት ታሪክ ያለው ሲሆን ለተማሪ ቤቱ ማደግ ደግሞ የረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ አሻራ ትልቅ መሆኑን ሀገር እንዲያውቅልን እንሻለን፡፡ /
ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ ቅድስት ወልዴና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰናዳ ሲሆን የአርትኦትና የመዝጊያው
ጽሁፍ
ደግሞ
በጋዜጠኛ
እዝራ
እጅጉ
የተዘጋጀ
ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ ዛሬ መስከረም 18
2014 በተወዳጅ
ሚድያ
የፌስ
ቡክ ገጽ እና በዊኪፒዲያ ላይ ፖስት የተደረገ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተጨመረበት በየጊዜው ይቀርባል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ