132. ክፍሌ ሙላት
ወልደየስ-KIFLE MULAT WOLDEYES
የአዲስ ዘመን ጋዜጣን አድማስ አምድን በ1970ዎቹ በጥልቀት የሚከታተል ጋሽ ክፍሌ ሙላትን ፍጹም ሊዘነጋ አይችልም፡፡
ጋሽ ክፍሌ አምዱ በጣም ተወዳጅ ስለነበር ብዙዎች መጣጥፍ በመላክ እጃቸውን ያፍታቱበት ባለውለታ አምድ ነው፡፡ በዚህ አምድ በእነዚያ
ወርቃማ ዘመናት በርካታ አስተማሪ ጽሁፎች ታትመው የወጡ ሲሆን ከዚህ ተፈላጊ አምድ ጀርባ ደግሞ አንድ ታላቅ የብእር ሰው አለ፡፡
ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት ወልደየስ፡፡ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበርን በመምራት በ1990ዎቹ የጎላ ድርሻ እንዳበረከተና ለዚህም
ጥረቱ አለም አቀፍ ሽልማት እንዳገኘ የሚነገርለት ጋሽ ክፍሌ በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን በባህር ማዶ ያደረገ ታላቅ ባለውለታ ነው፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገር የሰሩ ሰዎችን በልዩ ልዩ ድረ-ገጾች ላይ እያወጣ ሲሆን ጋሽ ክፍሌም ከእነዚህ ባለውለታዎች
አንዱ በመሆኑ ግለ-ታሪኩ ብዙ ትምህርት ይሰጣል ብለን እናስባለን፡፡
እዝራ እጅጉና አማረ ደገፋው ግለ-ታሪኩን እንደሚተለው አሰናድተውታል፡፡
የኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር 1944 ዓ.ምን ሲቆጥር በሲዳሞ ክፍለ- ሃገር በጌዲዮ አውራጃ ዳማ አንዲዳ በተባለች ቀበሌ ነው ውልደቱ፤ የስለት ልጅ እንደሆነ የሚነገርለት ክፍሌ ሙላት ወልደየስ ፡፡ ወ/ሮ ቦጋለች በሻህና አቶ ሙላት ወልደየስ ለኢትዮጵያ ሚዲያ ያበረከቱት እንቁ ልጅ፡፡
በሃገሪቱ የህትመት ሚዲያ የደመቀ አሻራውን በጉልህ ያኖረው ክፍሌ ሙላት ከፊደል ጋር ቀድሞ የተዋወቀው ከየኔታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ነው፤ በዚያም ዳዊትን እስከመድገም ደርሷል፡፡ የየኔታን እግር ስሞ ከተነሳ በኋላ በዲላ ከተማ አፄ ዳዊት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የመጀመርያ እና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎንም በትምህርት ቤቱ የሚከናወኑ ስፖርታዊ ውድድሮችን በመከታተል በማግስቱ ጠዋት በዜና መልክ በማዘጋጀት ሰልፍ ላይ ለተማሪዎች በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በይርጋለም ከተማ የራስ ደስታ ዳምጠው መርሓ ሙያ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነው የተከታተለው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው ከትምህርት ቤቱ ሁነቶች ባለፈ የሃገሪቷን ፖለቲካ የሚያስቃኙ ዜናዎችን ማቅረብ ጀመረ፡፡ ከዜናዎቹ አለፍ ብሎም ከአስተማሪዎቹ ጋር በመተባባር የተመረጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልን ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ በንባብ መልክ ያቀርብ ነበር፡፡ የሙዚቃና ትያትር ክበባት ውስጥም ተሳትፏል፡፡ ከውጭ ሃገር (የህንድ፣ የፊሊፒንስ፣ የእንግሊዝ) እና የሀገር ውስጥ አስተማሪዎቹ ጋር የቅርብ ትስስር በመፍጠር ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን የተማሪዎች መማክርት(ስቱደንት ካውንስል) አባልም ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን በማቅናት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅን መቀላቀል ችሏል፡፡ በኮሌጅ ቆይታው የእጩ መምህራን ካውንስል ምክትል ፕሬዚደንት በመሆን በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ አመፅ በመምራትና በማስተባባር በሰፊው ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወጣት የቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን የመሪነት ተሰጥኦውን አሳይቷል፡፡
በ1965 ዓ.ም የመምህራን ማሰልጠኛ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በአስተማሪነት ስራውን የጀመረው በኤርትራ ክፍለ- ሀገር ነበር፡፡ ከ1965-67 ዓ.ም ድረስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በመሆን በአዲነአምን መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ፣ በመንደራ ቅዱስ ጊዮርጊስና በአሥመራ ቀ.ኃ.ስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በአስተማሪነት አገልግሏል፡፡
ኤርትራ በነበረው ቆይታም ከአስተማሪነቱ በተጨማሪ አስመራ ላይ ከፍተኛ የሚዲያ ስራ እንቅስቃሴ በፍሪላንሰርነት
በፅሁፍ ስራዎቹ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ በነዚያ ጊዜያት ነው አሁን ድረስ የሙያ አባቴ እያለ የሚጠራውን የቀድሞው የኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሙሉጌታ ሉሌንና የቅርንጫፍ መ/ቤቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ከበደ አኒሳን
ማግኘትና መተዋወቅ የቻለው፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር እና በማስታወቂያ ሚኒስቴር መካከል በተደረገ ስምምነት በወቅቱ በሚታተመው የኢትዮጵያ ጋዜጣ ውስጥ
በሪፖርተርነት እንዲሁም በአማርኛ ይተላለፍ በነበረው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ፅሁፎችን፣ መግለጫዎችን በማንበብ የጋዜጠኝነት ህይወቱን ጀመረ፡፡
በአንድ አጋጣሚ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር የደርግ
ም/ሊቀመንበር የነበሩት ኮሎኔል አጥናፉ አባተ እና የደርግ የማስታወቂያ ከፍል ሃላፊ የነበሩት ዶ/ር ታምራት ፈረደ ወደ ኤርትራ በመጡበት ወቅት ከእነርሱ ጋር በመሆን በተለያዩ አውራጃዎችና የጦር ክፍሎች አብሯቸው በመጓዝ የሪፖርተርነት ስራን ሰርቷል፡፡ ክፍሌ
በዚህ ወቅት ነበር በሁለቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት(በሌ/ኮሎኔል አጥናፉ አባተ፣ ፒ.ኦ ታምራት ፈረደ) እይታ ውስጥ በመግባት ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ተዘዋውሮ ስራውን እንዲሰራ የተደረገው፡፡ በዳህላክ ደሴት ላይ ለሶስት ቀን ስራ በጦር ጀልባ ሄዶ ሶስት ሳምንት በዚያው በዳህላክ ደሴት ቆይታ አድርጎ የተመለሰበትን ወቅት ‹‹የኤርትራ የስራ ህይወቴ አይረሴው አጋጣሚ›› ይለዋል፡፡
በ1969 ዓ.ም መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በቀድሞው አለቃው እና የሙያ አባቴ እያለ በሚጠራው ሙሉጌታ ሉሌ መስካሪነትና ጠቋሚነት እንዲሁም በወቅቱ ቋሚ ተጠሪ በነበሩት በዓሉ ግርማ አማካኝነት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮፖጋንዳ ክፍልን መቀላቀል ቻለ፡፡ የሙያ አባቴ እያለ የሚጠራው ሙሉጌታ ሉሌ ብዙውን ጊዜ ስለ ክፍሌ ሲናገር በተደጋጋሚ
‹‹በተፈጥሮም ጭምር የጋዜጠኝነት ተሰጥኦ አለው›› ይላል፡፡
‹‹የፕሮፓጋንዳ ክፍሉ በወቅቱ በምስራቅና ሰሜን ግንባር ይካሄዱ ለነበሩ
ጦርነቶች በተቀናጀና በማዕከላዊነት ፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ በማድረግ ወሳኝ ተግባር ያከናውን ነበር፡፡ ሀገሪቷ ትመራ የነበረው ከዚሁ ተቋም በሚወጣ ዕቅድ ነበር፡፡ ታሪካዊ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማገዝ በርካታ የፕሮፖጋንዳ ስራዎች እንደ ሃገር ይከወኑ ነበር፡፡ በሶማሊያ ጦርነት በርካታ ወጣቶችን፣ ወታደሩን፣ እንዲሁም ህብረተሰቡን በፕሮፖጋንዳው በማነሳሳት ከፍተኛ ሀገራዊ ድጋፍን እንዲያደርጉ እና ጉልህ አስተዋፅኦን እንዲያበረክቱ በቴሌቪዥንና በራዲዮ በርካታ ስራዎችን ተሰርተዋል፡፡››
በዚህ የፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ ማዕከል በባልደረባነት ንጉሴ ስዩም ፣ ሙጬ አንተነህ ፣ አሃዱ ሳቡሬ እንደነበሩበት ክፍሌ ያስታውሳል፡፡ ከ1970/71 በኋላ የቡድኑ አባላት ወደ ተለያዩ መምሪያዎች ሲዛወሩ ክፍሌም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዛወረ፡፡ በ1970 ዓ.ም ሚኒስቴሩ ሻለቃ ግርማ ይልማ እንደሚፈልጉት በማዕረጉ በዛብህ (የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ) በኩል ተነግሮት ወደ ሚኒስትሩ ቢሮ እንደሄደ ያስታውሳል፡፡ ሚኒስቴሩ ጋር ሲደርስም ከፍተኛ ሃላፊነት እንደሚሰጡት ተናግረው ‹የመላው ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ› ሆኖ እንዲሰራ ወሰኑ፡፡
ለዚህ ያበቃው የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ተቀላቅሎ ሲሰራቸው በነበሩት ጠንካራ እና ጥራት ባላቸው ስራዎች አማካኝነት ነው፡፡ ‹‹የጎፋ አንበሳ ከግዞት መንደር ወደ ህብረተሰባዊ መንደር›› የተሰኘውና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታተሞ በሬዲዮ በተከታታይ የተለቀቀው ጽሑፉ በቀጣይ የሕይወት ምዕራፉ ላይ ደግ ያልሆነ ተጽዕኖ እንደነበረው እስከ አሁን አይዘነጋውም፡፡
የመላው ኢትዮጵያ የገበሬዎች ማህበር የህዝብ ግንኙነት
ሃላፊ ሆኖ ስራውን ከጀመረ በኋላም ‹‹ብሩህ ተስፋ›› የተሰኘ ወርሃዊ ጋዜጣን ማሳተም እና
ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር የሚያደርጉትን ዲስኩር እና የከወኗቸውን ስራዎች የሚገልፁ ጽሑፎች ለህዝቡ የሚቀርቡበት ነበር፡፡ በዚህ ድርጅት ለአምስት አመታት ግልጋሎትን ከሰጡ በኋላ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተመልሶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ
ላይ እንዲሰራ ተደረገ፡፡
በ1976 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በሙሉጌታ ሉሌ (በወቅቱ ፕሬስ ድርጅት ሃላፊ ነበሩ) ከፍተኛ ድጋፍ ‹‹አድማስ ›› የሚል ገፅ ላይ እንዲሰራ ዕድል ተሰጥቶት ለ9 አመታት በዋና አዘጋጅነት መስራት ችሏል፡፡ ‹‹አድማስ›› የተሰኘው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዓምድ በመላው ሀገሪቱ እጅግ ተወዳጅ ዓምድ ነበር፤ ክፍሌንም በህዝብ ዘንድ ታዋቂነት እና ዝናን እንዲያተርፍ መንገዱን ከፍቶለታል፡፡
‹‹አድማስ›› ዓምድ ገጽ ሲዘጋጅ ምንጮቹን ያደርግ የነበረው ራሱ ህዝቡን እንደነበር የሚያነሳው ክፍሌ በጊዜው ለዝግጅት ክፍሉ የሚሆን መረጃ
የሚሰጡ በቀን ከ1000 በላይ ፖስታዎች ይመጡ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የነበረው ክፍሌ እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጋዜጠኝነት ሙያው አገልግሏል፡፡
በሃሪገቱ የመንግስት መቀየርን ተከትሎ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ የሚያነሳው ክፍሌ ከቀድሞው መንግስት ጋር በነበረው ከፍተኛ የስራ ግንኙነት እና በሰራቸው ስራዎች በአዲሱ መንግስት ከባድ ችግርና የስራ ህይወትን እንዳሳለፈ ይገልፃል፡፡
በ1984 ዓ.ም ወደ ታች ሲነበብ ‹‹ትግራይ እስክትለማ ሌላው ሀገር ይድማ›› የተሰኘ ግጥም በመውጣቱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ውስጥ በርካታ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ በውጤቱም በርካታ ሰዎች ከስራቸው እንዲሰናበቱ ሀገራቸውንም ጭምር ለቀው እንዲወጡ ሆኖ ነበር፡፡ ግጥሙ የወጣው ክፍሌ ሙላት አዘጋጅ በነበረበት አድማስ ገጽ ስር ስለነበር የወቅቱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር እርምጃ ሊወስዱበት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ከአንድ ወዳጁ ጥቆማ ተሰጥቶት ለሁለት ሳምንታት ያህል ከአዲስ አበባ በመራቅ ‹‹ሕቡዕ›› መግባቱን በትካዜ ያስታውሳል ፡፡
ከእውቅ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ውስጥ አንዱ የነበረው ክፍሌ ሙላት
በቀጣይ የተወሰደበት እርምጃ ከአዲስ አበባው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባነት ተነስቶ ወደ ደቡብ ማስታወቂያ ክፍል እንዲዘዋወር በማድረግ ነበር፡፡ በዛ ያለው ሃላፊ ግን እንዲህ ያለውን የቀድሞ መንግስት አገልጋይ አልቀበልም በማለቱ ወደ ደቡብ ሳይሄድ ቀረ፡፡ ከጓደኛው ዳኛቸው ይልማ(የማይክሮ ሊንክ መስራች) ጋር በ1984 ‹‹ዜና አድማስ ›› የሚል ጋዜጣን በማቋቋሙ ደስተኛ ያልነበሩት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ወደ ጋምቤላ እንዲያቀና አዘዙት፡፡
ሁኔታዎች እጅግ አደገኛ በመሆናቸው ከመሞት መሰንበት ብሎ ለስራም ለሽሽትም ወደ ጋምቤላ ቢያቀናም በዚያ ህይወት ከባድ ነበር፤ በፅኑ እስከ መታመም ደረሰ፡፡ ከጋምቤላ በመመለስ ዳኛቸው ይልማ ጋር ዜና አድማስ
ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት መስራቱን ቀጠለ፡፡
በ1985 ዓ.ም በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ላይ በሰራው ዜና ምክንያትም ‹‹ዜና አድማስ›› ጋዜጣ ክስ ተመስርቶበት እርሱና ዋና ስራ አስኪያጁ ዳኛቸው ይልማ ታሰሩ፡፡ ‹‹ዳኛቸዉ በዋስ ሲፈታ እኔ ግን በማዕከላዊ ከዚያም በመቀጠል በከርቸሌ እስር ቤት ለ6 ወራት ያህል ታሰርኩ›› ይላል ክፍሌ፡፡
ዳኛቸው ይልማ ፣ ብርቱካን ፣ ቴዎድሮስና ክፍሌ በጋራ ባቆሙት ‹‹ዳብቴክ›› የተሰኘ የህትመት ድርጅት ዜና አድማስ ለአራት አመታት ያህል እየታተመች ለንባብ ትበቃ ነበር፡፡ የድርጅቱን ስም ከባለአክሲዮኖች ስም የመጀመሪያ ፊደላትን ወስዶ መሰየሙን ክፍሌ ዛሬም ያስታውሳል፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ‹‹ዳብቴክ› ሲፈርስ ‹‹ዜና አድማስ›› መታተም አቆመ፡፡
ከዚህ በመቀጠል ክፍሌ ‹‹አዲስ አድማስ›› የተሰኘ ጋዜጣን በ1986 ዓ.ም መጀመር ችሎ የነበረ ቢሆንም የሀገር ውስጥ ግብር ብር 45000 አለበት በሚል ክስ እንደተመሰረተበትና ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ እንዲዘጋ በመደረጉ ቢቆጭም ለአሰፋ ጎሳዬ(አሁን ያለው አዲስ አድማስ ጋዜጣ መስራች) ግን የበዛ ክብር እንዳለው ይናገራል፡፡ አሁን ያለው ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ከእርሱ በኋላ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ፈቃድ ሰጪ ወሳኝነት ስያሜው እንዲሰጠው የተደረገ እንደሆነም ይናገራል፡፡
በዚህ መሃል ህይወቱን ለመምራት ሲል በተለያዩ ቦታዎች ላይ በፍሪላንሰርነት የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ በመሆን አገልግሏል፡፡ በስራ ህይወት አጋጣሚ ባወቀው አንድ ወዳጁ ደጋፊነት ‹‹ኢትዮ ታይምስ›› የተሰኘ ጋዜጣን ማዘጋጀት ጀምሮም ነበር፡፡ ከጋዜጣው አለፍ ብሎ ‹የአስደናቂ ታሪኮች አድማስ› የተባለች አነስተኛ መፅሃፍን አሳትሞ መታሰቢነቱን ፊደል ላስቆጠሩት የኔታና በስራ አጋጣሚ ላወቃቸው ‹የሰበታዎቹ ፈረንጆች› አድርጎታል፡፡
የጋዜጠኞች በማህበር መሰባሰብን በፅኑ የሚደግፈው ክፍሌ ለህትመት ሚዲያው ያበረከተው አስተዋጽዖ በጋዜጠኝነት፣ ዋና አዘጋጅነትና አሳታሚነት ብቻ የተገደበ አልነበረም፤ ‹‹የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር›› መስራች አባል ጭምር ነው፡፡ ማህበሩ የመፍረስ
አደጋ በተጋረጠበት ወቅትም በርካታ ሃላፊነቶችን በመያዝ እንደአዲስ በማደራጀት፤ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራትና አመራራሮች እንዲመረጡ በማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከት ችሏል፡፡ ከሰባት ዓመት በኋላም ማህበሩ ህጋዊ ሰውነት እና እውቅና እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
የኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ማህበርን በመወከል ጋና ላይ በነበረው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ኔትወርክ የመስራች ጉባኤ ላይ በመሳተፍ የአፍሪካ ጋዜጠኞች ኔትወርክ መቀመጫ ቢሮውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን ባይሳካም፡፡
በ1997 ዓ.ም በሀገራችን ላይ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ተፈላጊ በመባል ስሙ በሃገሪቱ የመገናኛ ዘዴዎች ተበትኖ መፈለጉንና
በወቅቱ ህይወት እጅግ ፈታኝ ሆኖበት እንደነበረ ክፍሌ ሙላት በትውስታ መልክ ያነሳል፡፡ በካምፓላ የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የመስራቾች ጉባኤ ላይ ከተሳተፈ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መመለስ አለመቻሉንም በቁጭት ያስታውሳል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለበት እንዲቆይ በማድረግ የማህበሩን ስራ ወደ ኔዘር ላንድ ፣ ፊንላንድ፣ እንግሊዝ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመሄድ እንዲሰራ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባደረገለት ከፍተኛ ድጋፍም ካለበት ካምፓላ ኢንቴቤ ወደ ሀገረ አሜሪካ መግባት ችሏል፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ኑሮውን በዚያው ሀገረ አሜሪካ ነው፡፡ በወጣትነቱ ከጀመረው ትዳር ሶስት ልጆችን ማፍራት ችሏል፤ አንዱአለም ክፍሌ ፣ ወሰን ክፍሌና ማህሌት ክፍሌ፡፡
ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ ጠንቅቆ የሚያውቃት ክፍሌ ሙላት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍለ ሀገራት በመዘዋወር ሰርቷል፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፣ የካቲት መፅሄት ፣ ማርክሳዊ ርዕዮት መፅሄት እና በሌሎች በርካታ የህትመት ፤ የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ላይ እንዲሁም በሌሎች የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች መስራት ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ማህበርን በመወከልም የኢንተርናሽናል ፕሬስ ኢንስቲቲዩት ፣ የፔን ኢንተርናሽናል እና የአምነስቲ ኢንተርናሽል ሽልማትን ጨምሮ
ሌሎች የአለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለው ክፍሌ ዛሬም ያሉ ጋዜጠኞች በአንድ ገዥ ማህበር ታቅፈው ለመብታቸው እንዲታገሉ ይመክራል፡፡ በሀገር ውስጥ በጋዜጠኝነቱ ብቻ
ከአምስት ጊዜ በላይ ለእስር ቢዳረግም፤ ከዚህ በተቃራኒው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደጋጋሚ ሽልማትን ማግኘት የቻለው በመሰረቱት ጠንካራ ድርጅት መሆኑን አውስቶ ‹‹መንግስት ሁሌም መንግስት ነው፤ መብትን ለማስከበርና ሙያንም ለማዳበር ድርጅት ለጋዜጠኞች እጅግ ወሳኝ ነው››
በማለት ምክሩን ይለግሳል፡፡
መዝጊያ.፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንዲሁም የዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጆች አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ጋሽ ክፍሌ ብዙ ያልተነገረለት ነገር ብዙ የተጋ ባለሙያ ነው፡፡ ዛሬም 60ዎቹ እድሜ ላይ ሆኖ ያንን ወርቃማ የጋዜጠኝነት ዘመን ሲያስታውስ አንድ ጉልህ አሻራ ያስቀመጠ መሆኑን ማወቅ ይቻላል፡፡ የእነ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ፤ ጋሽ ማእረጉ በዛብህ ዘመን ሲነሳ የእነርሱ ደቀመዝሙር በመሆን በቀዳሚነት የሚነሳው ጋሽ ክፍሌ ነው፡፡ ጋሽ ክፍሌ ገና በ20ዎቹ እጁን ያፍታታ ነበር፡፡ በዚያ እድሜ በእነ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ እግር ስር ሆኖ እውቀትን ቀሰመ፡፡ ወዲያውም በራሱ ቆሞ ብእርን ከወረቀት አዋህዶ ለሚወደው ነገር ጊዜ ማጥፋቱን ተያያዘው፡፡ በተለይ አድማስ የተሰኘው አምድ ከብዙ ሰዎች ጋር አስተዋወቀው፡፡ ብዙ እንዲያነብ ለአንባቢ ምን ቁምነገር ላቅርብ እንዲልም አስቻለው፡፡ ክፍሌ በዚህ ብቻ አልቆመም ነጻ ፕሬስ በሀገራችን አንድ ተብሎ ሲጀመር በ1984 መሆኑ ነው ጉልህ አሻራ ካኖሩት ውስጥ እንደ አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ጋሽ ክፍሌ ሙላት ዜና አድማስ የተሠኘችውን ጋዜጣ በመመስረት ሙያዊ ፍቅሩን ተወጣ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የህትመት ሚድያ በተለይ ደግሞ አዲስ በነበረው የነጻ ፕሬስ ውልደት ላይ አንድ ጡብ እንደማኖር የሚወሰድ ነው፡፡ ክፍሌ ሙላት ከስመጥር የሚድያ ሰዎች ከእነ ሙሉጌታ ሉሌ ጋር የሰራ በመሆኑ እርሱ ከታላላቆቹ ያገኘውን እውቀት ለታናናሾቹ በማካፈል ሙያዊ አደራውን በሚገባ የተወጣ ታላቅ ሰው ነው፡፡ በተለይ በ1990ዎቹ በነጻ ፕሬስ ላይ ያደረገው አስተዋጽኦ በብዙዎች ጎልቶ የሚነገር ትልቅ አበርክቶው ነው፡፡ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበርን መመስረት ጀምሮ እንደ መሪ ግንባር ቀደም ሚና ሊወጣ የቻለ መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ለእስር የተዳረገ በመሆኑም ጋዜጠኝነት ትልቅ ዋጋ ከከፈሉት ተርታ ይመደባል፡፡ ነገር ግን ምን ያህሎቻችን ጋሽ ክፍሌ ሙላት ያለፈበትን መንገድ እናውቃለን? ግለ-ታሪኩ በወጉ ተሰንዷል ወይ? ይህ ሰው ለኢትዮጵያ ሚድያ አንድ የማይረሳ ውለታ የተወ አሁንም ለሀገሩ መልካሙን የሚመኝ ሀገር ወዳድ ሰው ነው፡፡ ጋሽ ክፍሌ ባህር ማዶ ሆኖ ለዚህ ግለ-ታሪክ ዘጋቢዎች ያለፈበትን መንገድ ሲያጫውተን አንድ ትልቅ አሻራ ማኖሩን ይገነዘባል፡፡ እኛ ለምንሰራው የስነዳ ታሪኮችን ፈልፍሎ የማውጣት ስራ ተባባሪ መሆኑን በግልጽ ነግሮናል፡፡ ጋሽ ክፍሌ ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች ግብአት የሚሆን በርካታ እውቀት ያካበተ ሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን በስደት ላይ ሆኖ ቢገኝም ዛሬም ኢትዮጵያን እየጠራ ይኖራል፡፡ እኛ የጋሽ ክፍሌን ታሪክ በዚህ መልኩ ሰንደን ስናቀርብ ትውልዱ በተለይ በሚድያ ዘርፍ ያለው አንዳች ቁምነገር ሊቀስም እንደሚችል እናምናለን፡፡ እናም ጋሽ ክፍሌ ግለ-ታሪኩን በዚህ መልኩ እንድንሰራ ስለፈቀደልን ብሎም ታላቅ አክብሮትና ቀና ትብብር ስላሳየን በተወዳጅ ሚድያ የግለ-ታሪክ ቦርድ ስም ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ ጋሽ ክፍሌ ባለህበት ስፍራ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን‹፡፡/ ይህ ግለ-ታሪክ ዛሬ ጥር 13 2014 አ.ም በዚህ ድረ-ገጽ እንዲሁም በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ወጣ፡፡ ግለታሪኩ በጋዜጠኛ አማረ ደገፋው እና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገ በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡./
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ