8. ከፋለ ማሞ አለሜ kefale mammo
aleme
አቶ ከፋለ ማሞ በ83 አመታቸው አረፉ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሸን ለነጻው ፕሬስ እድገት ታላቅ ሚና ያበረከቱት ታላቅ ባለውለታ አቶ ከፋለ ማሞ ህይወታቸው በማለፉ የተሰማውን ታላቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ ታሪካቸውን በዊኪፒዲያ ላይ ለማስፈር ታላቅ መሰናዶ ባደረግንበት ሰአት በድንገት ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡ የቀብር ስነ-ስርአታቸውም በኔዘርላንድ ጥቅምት 9 2014 እንደሚፈጸም ከቤተሰብ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ለቤተሰብ መጽናናትን እየተመኘን ታሪካቸውን በአጭሩ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
አቶ ከፋለ ማሞ አለሜ ' ከአባታቸው ከአቶ ማሞ ዓለሜ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ደስታ በጋሻው በቀድሞ አጠራር ሸዋ ክፍለ ሀገር በሰላሌ አውራጃ ሀምሌ 16 ቀን,1930 ዓ.ም ተወለዱ።እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው አምሃ ደስታ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በታዋቂው በጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ከዛም እንግሊዝ ሃገር በማቅናት በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሎንዶን በፖለቲካል ሳይንስ የማስተርስ
ዲግሪያቸውን
ተቀብለዋል።
አቶ ከፋለ ማሞ ለትምህርት ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ አሜሪካ በሚገኘው
ዩኒቨርስቲ
ኦፍ ዊስኮንሲን ማዲሰን በመሄድ በጋዜጠኝነት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ሃገራቸውን ለማገልገል ባላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አገርቤት ተመልሰው በከፍተኛ ሃላፊነት ቦታዎች በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ኢትዮጵያን በቅንነት አገልግለዋል። በመጀመሪያም በኢትዮጵያ ንጉሰ- ነገስት መንግስት የቀድሞው የባህር ሀይል መምሪያ የአድሚራል እስክንድር ደስታ ልዩ አማካሪ በመሆን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሰጥተዋል። ከዛም በመቀጠል በማስታወቂያ እና መርሃብሄር ሚኒስቴር መስሪያቤት፣ የሬድዮ መምሪያ ሃላፊ በመሆን ለረጅም ዓመታት በመስራት፣በኢትዮጵያ የሚድያ እና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራቸውን አኑረዋል። በዚህ አገልግሎታቸው ወቅት የኢትዮጵያ ሬድዮን በማዘመን፣በሃገራች ን ታዋቂ የሆኑ ጋዜጠኞችን ፣ሙያዊ ክህሎት በማሳደግ ረገድ ያደረጉት አስተዋጽኦ
በነባር
ጋዜጠኞች
ዘንድ
እስካሁን
ሲዘከር
ይኖራል።
ከኢትዮጵያ ሬድዮ የስራ አስኪያጅ ሀላፊነት በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነት በመስራት፣ የሃገራችንን ጋዜጠኝነት ወደ አንድ ከፍታ ካሸጋገሩ ጋዜጠኞች አንዱ በመሆን ገናና ስም አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከታዋቂ ከሙያ አጋሮቻቸው፣ አቶ አሳምነው ገብረወልድ እና አቶ ማእረጉ በዛብህ ጋር በመሆን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ማህበር (ኢጋማ) በመመስረት እና የአመራር አባል በመሆን ለጋዜጠኝነት እድገት የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።
በመቀጠልም ከሃገር እና ከመንግስት በተሰጣቸው ሃላፊነት የአሩሲ ገጠር ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የተለያዩ የመንግስት ልማት ድርጅቶች እና ፋብሪካዎችን ስራ ስኪያጅ በመሆን መርተዋል። እንዲሁም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሆነው ለዓመታት ሃገራቸውን
አገልግለዋል።
የ1983ቱን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ የግል ነጻ ጋዜጣ እና መጽሄት የመስፋፋት አጋጣሚን በመጠቀም በመጀመሪያዎቹ ነጻ ፕሬሶች ላይ በመሳተፍ ለሃገራችን የሚድያ ነጻነት የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በዚህም የሩህ መጽሄት ዋና አዘጋጅ ሆነው የሰሩ ሲሆን፣በተጨማሪም
በሌሎች
ነጻ ጋዜጦች እና መጽሄቶች ላይ በመሳተፍ በሃገራችን ነጻ ሃሳብን ለማሳደግ ጥረት አድርገዋል።
ወደ ስልጣን የመጡት አዲሶቹ የወያኔ መሪዎች በሃገሪቱ እያበበ የመጣውን ነጻ ጋዜጠኝነት ለማፈን በከፈቱት የእመቃ ዘመቻ የተነሳ፣ የጋዜጠኞች መታሰር እና እንግልት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ እንደእነ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ከመሳሰሉ አንጋፋ ጋዜጠኞች እና ከወጣቶች እነ አበበ ገላው ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ)ን በመመስረት፣ አቶ ከፋለ ማሞ የመጀመሪያው ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ሃላፊነታቸው የወያኔ መንግስት በነጻ ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን ወከባ ለዓለም በማሳወቅ የብዙዎችን ህይወት ከአደጋ ታድገዋል። በዚህ እና ሌሎች እንቅስቃሴያቸው የተነሳ ከወያኔ መንግስት የተለያዩ ዛቻዎች እና ወከባዎች ደርሶባቸዋል።
በዚህ ሁኔታ፣ ሃገር ውስጥ መቆየት ለእርሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው የሚያስከትለውን አደጋ በመገንዘብ ወደ አውሮፓ ተሰደው በኔዘርላንድ ሃገር ቀሪ ዘመናቸውን አገራቸውን እያገለገሉ ኖረዋል። በኢትዮጵያ ለሃቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለማስከበር በተደረገው ትግል አቶ ከፋለ ማሞ እና የትግል አጋሮቻቸው የማይናቅ አስተዋጽኦ በታሪክ ምን ግዜም ሲዘከር ይኖራል።
በስደት ሃገራቸውም የኢትዮ ቲቪ ዋና አዘጋጅ በመሆን ወጣት ጋዜጠኞችን በሙያው እያነጹ የሃገር ባለውለታነታቸውን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዢን (ኢሳት) ለመጀመሪያ ግዜ በአምስተርዳም ሲቋቋም ቀዳሚ ጋዜጠኛ በመሆን እና በማማከር ለሚድያው እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። አቶ ከፋለ ማሞ ከጋዜጠኝነቱ ሙያ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አመራርነት የነበራቸው ተሳትፎም የነበራቸው ሁለገብ አበርክቶ ምስክር ነው።
አቶ ከፋለ በስጋ የአንዲት ሴት ልጅ አባት ሲሆኑ፣ ሁለት የልጅ ልጆች አፍርተዋል። ከ50ዓመታት በላይ በቆየ የሙያ አገልግሎታቸው የመንፈስ ልጆችን ለመፍጠር ባላቸው ፍላጎት ብዙ ወጣት ጋዜጠኞችን በማሰልጠን ብቁ ትንታግ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ለሃገራቸው አፍርተዋል። ከማንም እና ከምንም በላይ አገራቸውን ይወዱ የነበሩት አቶ ከፋለ ማሞ፣ ይህንንም የሃገር ፍቅር በታማኝነት እና መስዋዕትነት በመክፈል አረጋግጠው አልፈዋል።
አቶ ከፋለ ማሞ ባደረባቸወ ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ጥቅምት 3 ቀን 2014ዓም በተወለዱ በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ስነ-ስርአታቸውም ማክሰኞ ጥቅምት 9 2014 በአመስተርዳም ይፈጸማል ፡፡
አንተነህ መርእድ ስለ አቶ ከፋለ ማሞ
ታላቁን የኢትዮጵያ ልጅ ከፋለ ማሞን ማረፍ መስማት ሃዘናችንን መራር ያደርገዋል። ጋሽ ከፋለ ማሞ ሃገሩን በብዙ ዘርፍ ያገለገለ ቢሆንም የነጻ ፕሬስ በኢትዮጵያ እንዲያብብ የተጫወተው ሚና ጉልህ ነው። አቶ ከፋለ የመጀመርያውን የጋዜጠኞች ማህበር በፕሬዝደንትነት ከመምራቱም በላይ ህወሃት በነጻ ፕሬስ ላይ የሚያደርሰውን አፈና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጋለጥና ጋዜጠኞችንም ድጋፍ እንዲያገኙ በመርዳት ጋሻችን ነበር። አቶ ከፋለ ማሞና ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ በአፈና ላይ የነበረ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ እንዲያገኝ በነጻ ሚድያ መሰረት በመጣላቸው ስራቸው ህያው ነው። ለመላ ቤተሰቡ መጽናናትን እንዲሰጥ እመኛለሁ።
ገነት አየለ ስለ አቶ ከፋለ ማሞ
የቀድሞው የኢትዮዽያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ)ፕሬዝዳንት አቶ ከፋለ ማሞ ማረፋቸውን ስሰማ በጣም አዘንኩ:: ጋሽ ከፋለ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ክፍሎች በሬድዮና በጋዜጣ ከተራ ጋዜጠኝነት እስከ ከፍተኛ ሃላፊነት በመሥራት ያገለገሉ ምርጥ ባለሙያ ነበሩ:: በተለይም የወያኔ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በሁዋላ ለይስሙላ የፕሬስ ነፃነትን ፈቀድኩ ብሎ የግል ጋዜጠኞችን በእስርና በእንግልት በሚያሰቃይበት በ80ዎቹ ውስጥ ጋሽ ከፋለ የሩህ መጽሔት አዘጋጅ ሆነው ሲሰሩ ወጣት ጋዜጠኞችን በማበረታታት የሚመጣውን ችግር ሁሉ በፅናት ሲጋፈጡ ቆይተዋል:: ያላቸውን ልምድ በማካፈል ለሙያው መዳበር ካደረጉት አስተዋፅኦ ጋር ከአንጋፋ የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ኢነጋማን አቋቁመዋል:: በዚህን ጊዜ ነበር ጋሽ ከፋለን በቅርብ ለማወቅ እድል ያገኘሁት:: የምክርና የማበረታታት ሥራ ከመሥራት ጋር እኔን ጨምሮ ብዙ ጋዜጠኞች በየፖሊስ ጣቢያው ስንጠራ እንግልት እንዳይደርስብን
ራሳቸው
ዋስ በመሆን ወይም ሌሎችን በማፈላለግ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር:: በሁዋላ ራሳቸውም በወያኔ ማሳደድ ለስደት ሲዳረጉና ወደ ሆላንድ ሲሄዱ የነገሩኝን አስታውሳለሁ
" ገኒ
ተስፋ
ሳትቆርጪ
ሥራሽን
ቀጥይ:
: እኔም
ከእንግዲህ
የቀረኝን
ህይወቴን
የፕሬስ
ነፃነት
እንዲያብብ
ትግሌን
እቀጥላለሁ
" ነበር
ያሉኝ::
ጋሽ ከፋለን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁዋቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት አመስተርዳም ከተማ ሄጄ በነበረበት ጊዜ ካሉበት ቦታ ሄጄ በጠየቅሁዋቸው ጊዜ ነበር:: በሠላም እረፉ ብርቱው ታጋይ ድንቅ
ጋዜጠኛ ጋሽ ከፋለ::
ሚሚ ከፋለ ማሞ
አባቴ ነጻ ሆኖ ነው ያሳደገኝ፡፡ አንድ ልጁ ስለሆንኩ የፈለኩትን ያወራኛል፡፡ ጓደኞቹ እነ ጋሽ ማእረጉ በዛብህ ራሳቸው የቅርቤ ነበሩ፡፡ አባቴ ሰው በጣም ያከብራል፡፡ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እንደ ልጅ ከማየት ይልቅ ሀሳቤን አክብሮ ያሰደምጥ ነበር፡፡ በ1970 ዎቹና በ1980ዎቹ የነበሩ ወጣት ጋዜጠኞችም ይህን ለወጣት እድል የመስጠቱን ነገር ያውቁለታል፡፡ አባቴ ትሁት ነው፡፡ በእርግጥ መቆጣት ባለበት ነገር ላይ ይቆጣል፡፡ እኔን ግን ተቆጥቶኝ አያውቅም፡፡ ለስራው ደግሞ ትልቅ አክብሮት አለው፡፡ የሚሰራው ደግሞ እስከሚደክመው ድረስ ነው፡፡ በማኔጅመንት ደግሞ የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ የስራ መሪ በነበረ ጊዜ ልዩ ትጋቱን ማሳየት የቻለ ታላቅ ሰው ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ