9.  ህሊና ተፈራ መኮንን- Helina Teferra Mekonnen

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለፉት 4 ወራት 120 በላይ የሚድያ እና የጥበብ ሰዎችን ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ገጽ  ላይ ሲያወጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡

 

አሁንም ይህን ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል የሚድያ ባለሙያን ህሊና ተፈራን እናስተዋውቃለን፡፡ ህሊና ተፈራ በኢቲቪ 1970ዎቹ በደርግ .ቤት  በዶክመንቴሽን ክፍል እንዲሁም በሚድሮክ ጥረት መጽሄት በማዘጋጀት ትታወቃለች፡፡ ከዚህም ባሻገር ተፈራ መኮንን በተሰኘው ድርጅቷ አማካይነት በርካታ ለሀገር የሚጠቅሙ ተግባራትን አከናውናለች፡፡ በአሁኑ ሰአት በባህር ማዶ ቼዝ ዘድሪም በተሰኘ ድርጅቷ አማካይነት ሀገሯንና አህጉሯን እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡ ህሊና ጠንካራ ፤በጽናቷ ብዙዎች የሚያደንቋት ስትሆን ታሪኳን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡

 

          ህሊና በልጅነት-የአባት ሚና 

 

ትውልዷ አዲስ አበባ 1954 አፍንጮ በር ነው፡፡

 

ህሊና ተፈራ፣  እስከ 10 አመቷ ድረስ አያቶቿ ጋር ካዛንቺስ መናኸሪያ ያደገች ሲሆን ረጅም የልጅነትና የወጣትነት ጊዜዋን ያሳለፈችው ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚገኘው ቤተሰቦቿ በሰሩት ቤት ነው፡፡

 

ወላጅ እናቷ ወይዘሮ አለምፀሃይ ወርቄ በመባል ይታወቃሉ፡፡በድሮው ምርጫ ቦርድ በፀሃፊነት ለተወሰኑ አመታት ያገለግሉ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በግል ድርጅት ውስጥ በገንዘብ ያዥነት ሰርተዋል፡፡

 

ወላጅ አባቷ፣  ሙዚቀኛ ተፈራ መኮንን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ቀደምት ኢትዮጵያዊ ፒያኒስቶች አንዱ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም በደብል ቤዝ ተጫዋችነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ሙዚቀኛ ተፈራ መኮንን በኦስትሪያ እና በሩሲያ የሙዚቃ ባለሙያዎች አማካይነት ትምህርት የቀሰሙ ነበሩ፡፡ በጊዜው ንጉስ ሀይለስላሴ ፈረንጆቹ በኢትዮጵያውያን  እንዲተኩ ስለፈለጉ እንደ ሙዚቀኛ ተፈራ መኮንን ያሉ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች  ፍራንስ ዙልቬከርን በመሰሉ ሰዎች  እንዲሰለጥኑ አድርገው ነበር፡፡

 

ተፈራ መኮንን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ለማኖር የቻሉ ነበሩ፡፡  ከፒያኖ ተጫዋችነታቸው ባለፈ መሪ ሙዚቀኛ ነበሩ፡፡

 

በግላቸው እንዲሁም በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርትን በመስጠት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን ሰጥተዋል፡

 

ህሊና ተፈራ፣ ስለ አባቷ ስታነሳ ‹‹ከጊዜው ቀድሞ የነቃ አባት ነው.›› ስትል ትገልጻቸዋለች፡፡ የአባትነት ብቻ ሳይሆን የእናትነት ሚናንም በቤተሰቡ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ አባት መሆናቸውን በጉልህ ታወሳለች፡፡

 

የሚድያ ዝንባሌ ገና በልጅነት

 

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በጀርመን ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ነበር የተከታተለችው፡፡ በዛም የጀርመንኛ ቋንቋን ተምራለች፡፡ ህሊና ትምህርቷን የጀመረችው 4 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር፡፡

 

በጀርመን ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት እስከ 11 ክፍል ድረስ ትምህርቷን የተከታተለችው ህሊና ተፈራ አሁን ላለችበት ማንነት በዚህ ትምህርት ቤት መማሯ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳበረከተላት ደጋግማ ታነሳለች፡፡

 

ጋዜጠኛ የመሆን ዝንባሌዋ ከልጅነቷ የጀመረ መሆኑን የምትገልፀው ህሊና ተፈራ ወላጅ አባቷ ሙዚቀኛ ተፈራ መኮንን ሬዲዮ እንድታደምጥ ያበረታቷት ነበር፡፡

 

በትምህርት ቤቷ  ጭምርም ከፍተኛ ድጋፍ መደረጉ የበለጠ በዝንባሌዋ እንድትቀጥል ያደረጋት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም ስነ- ፅሁፍ የማቅረብ መድረክ የመምራት ክህሎቷን ማዳበር ጀምራ ነበር፡፡  የክፍል ጓደኞቿ እና አስተማሪዎቿም ይህንን ጥረቷን ያደንቁ ነበር፡፡

 

  ትምክህት ተፈራ ስለ እህቷ

 

  ትምክህት ተፈራ የህሊና ተፈራ ታናሽ እህት ናት፡፡ በአሁኑ ሰአት በባህር ማዶ ስትኖር የሙዚቃ ባለሙያም ነች፡፡ ትምክህት  ስለ ህሊና የልጅነት ጊዜ ስታስብ ብዙ ትዝታዎችን አቅፎ የያዘ ነው ትላለች፡፡ ‹‹ ሁላችንም በፍቅር እና በመተሳሰብ ነበር ያደግነው ›› ስትል የቤተሰቡን ታሪክ ማውሳት ትጀምራለች፡፡ በተለይ ወላጆቻቸው በእነርሱ እድገት ላይ አዎንታዊ ሚና መጫወታቸውን ታነሳለች፡፡ ጥሩ ትምህርት ቤት መማራቸውንም እንደ አንድ በጎ ነገር ትቆጥረዋለች፡፡

 

ትምክህት ስትናገር ‹‹….ህሊና በልጅነት በጣም ፈጣን ነበረች፡፡ ገና በልጅነት ከጓደኞቿ ጋር የነበራት ግንኙነት በጣም ደስ የሚል  ነበር፡፡ ህሊና የሚድያ ዝንባሌ ያደረባት ገና በልጅነት ነበር፡፡ ያኔ አባታችን ፒያኖ ቢያስተምረንም የህሊና ተፈራ ልብ ግን ወደ ጋዜጠኝነቱ የተወሰደ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ብትማርም ውስጧ ያለው ፍል አምሮት ወይም ፓሽን ታሪክ አልነበረም፡፡ በወቅቱ በነበረው እድል 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ኢቲቪ ገባች፡፡ ህሊና አያታችን ቤት ነበር ያደገችው፡፡ የእናቴ እናት ቤት፡፡ እርሷ የመጀመሪያ እኔ ደግሞ ተከታይ ልጅ ስለነበርን ግንኙነታችን የጠበቀ ነበር፡፡ በየጊዜው እኔም አያታችን ቤት ስለምሄድ ጥሩ ጥሩ ትዝታዎችን አሳልፈናል፡፡ ›› ስትል ትምክህት ተፈራ እነዚያን ጣፋጭ የልጅነት ጊዜያቶች ታስታውሳለች፡፡

 

ህሊና ወደ ሚድያው አለም ስትገባ  ቤተሰቡ በጣም ተገርሞ ነበር፡፡ ህሊና ራሷ ደስ ከመሰኘቷ ባሻገር ለእንቅልፍ ራሱ ጊዜ አልነበራትም፡፡

 

‹‹ ……የእርሷ በቲቪ መታየት ለእኛ እንደ አንድ ትልቅ ኩራት ነበር፡፡  ስለምትሰራው ፕሮግራም ቀድማ ትነግረናለች፡፡ ቲቪ ላይ የምትወጣ ከሆነ ልትለብሳቸው ስላሰበቻቸው ልብሶች ትነግረናለች፡፡ ሁሉ ጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ነበረች፡፡ በምታቀርባቸው ዝግጅቶች ላይ የአነጋገር ስልቷ በጣም ይደንቀኝ ነበር፡፡ በራሷ ላይ ያላት መተማመን ራሱ በጣም ደስ ያሰኘኝ ነበር፡፡  የቲቪ መሰናዶዎቿ በጣም ሳቢ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙ አድናቂ ወይም ተመልካች ለማግኘት ችላለች፡፡በእኔ አመለካከት ያኔ ይቀርቡ በነበሩ የቲቪ መሰናዶዎች ውበት እንዲላበሱና ኪነጥበባዊ ለዛ እንዲኖራቸው የራሷን ግላዊ ጥረት ጨምራ አሻራ አኑራለች ብዬ አስባለሁ፡፡በእርግጥ ብቻዋንም ሳይሆን አብረዋት የነበሩ ባለሙያዎችም ትልቅ እገዛ አድርገውላታል፡፡ ከየአቅጣጫው ህብረትርኢት ላይ ዜና በማንበብም  የነበራት ተሳትፎ ትልቅ ነበር፡፡››  በማለት የህሊና ታናሽ እህት ሀሳቧን ገልጻለች፡፡

 

ህሊና የደርግ /ቤት ውስጥ ስትሰራ ማረፍ የምትችልበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ስራው ራሱ ፋታ የማይሰጥ ስለነበር ህሊና ምንም እንኳን በዚህ ስራ አማካይነት  ብዙ እውቀት የቃረመች ቢሆንም ፖለቲካ የሚባለው ነገር ምን ያህል እኩይ ነገር እንደሆነና በመጠላለፍ የተሞላ መሆኑን አስተውላለች፡፡

 

ትምክህት ስታስታውስ ‹‹ ህሊና በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን የተሰጣትን ሃላፊነት በአግባቡ ትወጣ ነበር፡፡ አንድም ቀን ወደ ኋላ አላለችም፡፡ ከእርሷ ጥንካሬን መማር ይቻላል፡፡ ህሊና ጽድት ያለ ውጤት የምታገኝበትን ስራ ነው የምትሰራው፡፡  አንድ ነገር በከፍተኛ ደረጃ ስኬትን እንዲያመጣ አድርጋ ነው የምታቅደው፡፡ የስራ ዲሲፕሊኗ  ለብዙዎች ያስተምራል፡፡ ህሊና የጽናት ተምሳሌት ናት፡፡ ሁልጊዜ አታቋርጥም፡፡ ለወደደችውና ላመነችበት ነገር በትጋት ትሮጣለች፡፡ አእምሮዋ አዲስ ነገር ለማፍለቅ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ይህ ህሊን ልዩ ያደርጋታል፡፡ይህ ሙያ ፍል አምሮት ወይም ፓሽን ይጠይቃል፡፡ ህሊናም በዚህ ፍል አምሮቷ ተጠቅማ ባለችበት ሙያ አንድ ትልቅ አሻራ ለማስቀመጥ ትልቅ ሙከራ አድርጋለች፡፡›› ብላ ነበር፡፡

 

ትምክህት ስለ ህሊና ስታስብ ያላትን የግጥም የስነጽሁፍ እና የመድረክ ላይ ተናጋሪነት ችሎታ ታደንቃለች፡፡ በተጨማሪም  ጎበዝ ኤዲተር መሆኗን ማንሳት ትሻለች፡፡ህሊና ለሙዚቃም የተለየ ፍቅር  አላት፡፡ ስታዳምጥ ደግሞ በደንብ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ግጥሙን የዜማ አወቃቀሩን ቅንብሩን ሁሉ ለማጣጣም ትሞክራለች፡፡ ትምክህት ሀሳቧን ስትቋጭም ‹‹ ለህሊና መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡ ›› ብላለች፡፡  ትምክህት አሁን ህሊና እየሰራችው ስላለው ስራ ስታስብ ትደነቃለች፡፡ በተለይ ቼዝ ዘድሪም የተሰኘው የህሊና ኩባንያ በጥቁር ህዝቦች ላይ ያተኮሩ መድረኮችን ያዘጋጃል፡፡ ታዲያ ህሊና እዚህ ጋር የጥቁር ህዝቦችን ታሪክ ለማስተዋወቅ ታደርግ የነበረው ጥረት ፍጹም የሚደነቅ ነበር፡፡ ትምክህት ህሊና በዚህ ረገድ ህሊና በምታደርገው ጥረት ትደሰታለች፡፡ እህቴም ይህን እውን በማድረጓ እኮራባታለሁ ትላለች፡፡

 

           ወደ ቲቪ ጉዞ  አቶ ፈቃደስላሴ ስለ ህሊና

 

ህሊና ተፈራ፣ 11 ክፍል ሳለች  በወቅቱ በነበረው መንግስት እና በትምህርት ቤቱ አስተዳደሮች በነበረው አለመግባባት ምክንያት ትምህርት ቤቱ በመንግስተ እንዲወረስ ተደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርት ቤቱ ሊዘጋ ቻለ፡፡

 

ከዚህ በኋላ ህሊና ሰባ ደረጃ አካባቢ  ወደ ሚገኘው ናዝሬት ስኩል የሴቶች ትምህርት ቤትን መቀላቀል ችላለች፡፡ አንድ አመት ናዝሬት ተማሪ ቤት ተምራለች፡፡

 

12 ክፍል ትምህርቷን በየካቲት 12 ትምህርት ቤት 1972 . አጠናቀቀች፡፡ በዚህ ወቅትም 18 ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡

 

በዚህ መሃልም በመነን ትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት የፍሪላንሰርነት ቅጥርን ሞክራ የልጅ ፊት ነው ያለሽ በመባል ስራውን ሳታገኝ ቀርታ ነበር፡፡

 

አቶ ፈቃደስላሴ ፍቅሬ  የህሊና የአጎት ልጅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት የሚኖረው ዛምብያ ሲሆን ህሊና የማከብራት እና አብረን ያደግን ታናሽ እህቴ ናት ሲል አድናቆቱን በመግለጽ ሀሳቡን መስጠት ጀመረ፡፡

 

‹‹….. በተለይ በቀድሞው የጀርመን ተማሪ ቤት አብረን በምንማርበት ወቅት ቅርበታችን ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከረ ሄደ፡፡  እጅግ የምወደውና የምቀርበው አጎቴ ጋሽ ተፈራ መኮንን ይህንን ቅርበታችንን አይቶ ህሊናን እንድጠብቃት ሃላፊነት ሰጠኝ፡፡ አደራ ብሎም እንደታላቅ ወንድም አስፈላጊውን እገዛ እንዳደርግ ሃላፊነቱን አስረክቦኝ ነበር፡፡ይህም ላለን እጅግ የጠበቀ ግንኙነት መሰረት የሆነ ይመስለኛል፡፡ህሊና በቅድሚያ በግል ልታደርግ ያሰበችውን ነገር ሁሉ በቅድሚያ የምታማክረው እኔን ነበር፡፡ ህሊና በጀርመን ተማሪ ቤት እንማር በነበረበት ጊዜ በተማሪዎችና በአስተማሪዎች ዘንድ በጣም የምትከበር የምትወደድ እንደነበረች አልረሳውም፡፡ በትምህርቷ በሙዚቃ ጎበዝ ነበረች፡፡ የቋንቋ ችሎታዋም ልዩ ነበር፡፡ ገና በልጅነቷ በአነጋገሯም ረጋ ያለች ነበረች፡፡ ይህም ከሌሎች ተማሪዎች ለየት ብላ እንድትገኝ የሚያደርጋት ነበር፡፡ በልጅነቷ ማንበብ የምትወድ ወደ ስነግጥም እና ስነ-ጽሁፍ ታዘነብል  የነበረች ልጅ ነበረች፡፡ ጋዜጠኛ ልትሆን እንደምትችል ያኔ ገና ታስታውቅ ነበር፡፡ በልጅነቷ መስተዋት ፊት ቆማ ጋዜጣ ይዛ ቲቪ ላይ እንዳየቻቸው ዜና አንባቢዎች እያስመሰለች ስታነብ አስታውሳለሁ፡፡ ይህ የልጅነት ጥረቷ  የሚድያ ሰው ልትሆን እንደምትችል ትልቅ ፍንጭ የሚሰጥ ነበር፡፡ በዚህ ጥረቷም ቀጥላበት በሚድያው ታላቅ ሰው ለመሆን በቅታለች፡፡

 

ህሊና ተፈራን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ሳያት እጅግ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ያኔ ቲቪ ስታመለከት እድሜሽ ገና ነው ተብላ ነበር፡፡  ወዲያውኑ መቀጠር አልቻለችም፡፡   ፍላጎቱ ስለነበራትም መታገስ ነበረባት፡፡ በኋላም ህልሟን ለማሳካት ችላለች፡፡ ህሊና በኢቲቪ ተመልካችን የሚስቡ ብዙ ፕሮግራሞችን ሰርታለች፡፡ ብቃት ያላት ስለነበረችም ነበር በደርግ /ቤት በህዝብ ግንኙነትና ዶክመንቴሽን ውስጥ እንድትሰራ የተደረገው፡፡ ህሊና፣ ያላት ሰብእና በጣም ደስ የሚል ስለነበርና አገሯን የማገልገል ልዩ ፍላጎት ስለነበራት 7 አመታት ትልቅ የመንግስት ሃላፊነትን ወስዳ መስራት ጀመረች፡፡ ወደዚህ /.ቤት ለመግባት ባሳበችበት ጊዜ በእርሷ ላይ ትልቅ እምነት ስለነበረኝ ሁሉ ነገር እንደማያስቸግራት ያለኝን እርግጠኝነት ገለጽኩላት፡፡ እንዳሰብነውም ህሊና ሃላፊነቷን መወጣት ችላለች፡፡ ህሊና 1985 ጀምሮ  ደግሞ በሚድሮክ ውስጥ ወሳኝ ሰው በመሆን ገጽታ ግንባታ ላይ የማይናቅ ስራ ያከናወነች ጠንካራ ባለሙያ ነች፡፡ህሊና ‹‹ክብር ለጥበብ›› በሚል ለባለሙያዎች እውቅና በመስጠቷም ትታወቃለች፡፡ ህሊና፣ በህይወቷ ላይ የሚመጡትን እንቅፋቶች በማሸነፍ  በአሁን ሰአት ‹‹ቼዝ ዘድሪም›› የተባለውን ድርጅት አቋቁማ የምትወደውን ስራ እያከናወነች ትገኛለች፡፡

 

       ዜና በማንበብ በወር 700ብር

 

ህሊና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እየተማረች ሳለች በድጋሚ በወጣው ማስታወቂያ ምክንያት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 1972. የመጠራት ዕድል አገኘች፡፡

 

በወቅቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የታሪክ ጥናት ትምህርቷን እየተከታተለች 1972 . መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መቀላቀል ቻለች፡፡

 

ስራ ከመጀመሯ በፊትም በአቶ ጌታቸው ሀይለማሪያም አማካኝነት ብዙ ስልጠናዎችን ታገኝ ነበር፡፡ ዛሬ ድረስ፣ህሊና አቶ ጌታቸው ሀይለማሪያምን ታመሰግነዋለች፡፡ ጥሩ ጋዜጠኛ እንድሆን አድርጓል ስትልም ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

 

በወቅቱም ህሊና የተቀጠረችበት ገንዘብ በሰዓት 10 እስከ 15 ብር ይደርስ ነበር፡፡

 

ህሊና አማርኛ ዜናዎችን ከማንበብ ባለፈም የእንግሊዝኛ ዜናዎችን እንዲሁም የሪፖርተርነት ስራን እንዲሁም በፕሮግራም አስተዋዋቂነት  በተጨማሪነት ትሰራ ነበር፡፡

 

በዚህ ወቅትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ጥናት ትምህርቷንም ከስራዋ ጎን ለጎን ታስኬድ ነበር፡፡

 

የዜና ሪፖርት ስራዎችን በብዛት እና በጥራት ትሰራ የነበረው ህሊና ተፈራ የመጀመሪያ ስራዋን የጀመረችው ስለ አቶ ወሌ ቸኮል የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ በመዘገብ ነበር፡፡ ተሳትፏቸውንም አስመልክቶ ወደ ሀገር ተመልሰው የሰጡትን መግለጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበችው ህሊና ነበረች፡፡

 

የአማርኛና የእንግሊዝኛ ዜናዎችን እንደ ዜና አንከር በብዛት ታነብ ነበር፡፡ በዚህም በወር እስከ 700 ብር ታገኝ ነበር፡፡ ይህም በጊዜው ቀላል የሚባል ክፍያ አልነበረም፡፡

 

ህሊና በማህበራዊ በኢኮኖሚ በኪነጥበብ ላይ ትኩረት ያደረጉ  መሰናዶዎችን ስታቀርብ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ማትረፍ ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አርካይቭ ውስጥ ቢፈለግ ህሊና የሰራቻቸው እጅግ መሳጭ እና አስተማሪ ፕሮግራሞችን ማግኘት ይቻላል፡፡

 

1974 .  በጊዜው የነበሩ የቲቪ ተመልካቾች እንደሚያስታውሱት ህሊና አንድ መሰናዶ አየር ላይ አውላ ነበር፡፡  ቃለ-መጠይቁ ተክሉ ደስታ በሚባል ህንፃ ላይ ነበር የተቀረጸው፡፡ ከየአቅጣጫው በተባለው ዝግጅት  ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመጀመሪያውን ቃለ -መጠይቅ ያደረገው ከህሊና ተፈራ ጋር ነበር፡፡

 

ህሊና ኩኩ ሰብስቤንም በመኖሪያ ቤቷ  ጭምር በመሄድ ቃለ- መጠይቅ አድርጋ  ሰርታለች፡፡በዚሁ በእሷ አዘጋጅነት እንዲሁም አስተዋዋቂነት ዘወትር አርብ የሚቀርበው ‹‹ከየአቅጣጫው›› የተሰኘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም  በተመልካቾች ዘንድ ለመወደድ የቻለ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ እንዲወደድ ካደረጉት ባለሙያዎች መካከል ደግሞ ህሊና ተፈራ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡

 

     ህሊና ተፈራ በአቶ ሀብቴ ገመዳ እይታ

 

ህሊና ተፈራ ጎበዝ ጋዜጠኛ መሆኗን አቶ ሀብቴ ገመዳ ይመሰክራል፡፡ በጊዜው አቶ ሀብቴ  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮዳክሽን ክፍል ሱፐርቫይዘር በመሆን  ይሰራ ነበር፡፡ አቶ ሀብቴ በጊዜው ህሊና ታሳየው የነበረውን የሙያ ቅልጥፍና ከብቃት ጋር የተዋሀደ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ‹‹ህሊና፣ ፈጣን ቅን ልብ የነበራትና ከሁሉም ጋር የምትግባባ ነበረች ሲል አድናቆት ይቸራታል፡፡ ህሊና ከባልደረቦቿ ጋር ብቻ ሳይሆን በጊዜው ታዋቂ ከነበሩ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ጋር የነበራት ግብብነት ሙያዋን ቀለል ብሏት እንድትሰራ እገዛ አድርጎላታል ሲል አቶ ሀብቴ የህሊናን ሁለገብነት አጉልቶ ያስቀምጠዋል፡፡

 

ህሊና፣ 1974 ግድም ህብረትርኢትን ከሰለሞን ክፍሌ ጋር ስታዘጋጅ ሁለቱም ተመልካችን ደስ ለማሰኘት የተቻላቸውን ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በተለይ  አንድ ወቅት የሙዚቃ እጥረት ባጋጠመ ጊዜ ሰለሞን ክፍሌና  ህሊና ተፈራ ‹‹ሁዴ ናና›› የተሰኘውን ሙዚቃ በህብረ-ትርኢት ክፍለ-ጊዜ  እየተቀባበሉ መዝፈናቸውን አቶ ሀብቴ ያስታውሳል፡፡

 

ህሊና፣ በጊዜው የነበራት ቅልጥፍና ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ክህሎቷም ጎልቶ  የወጣ ነበር፡፡ በተለይ ቃለ-መጠይቆችን የምታደርግበትን ስፍራ በመምረጥ እንደዚሁም ጥሩ የሆነ የዳይሬክቲንግ ክህሎት የተላበሰች ነበረች፡፡ በጊዜው የነበሩት የፕሮግራም  ዳይሬክተሮችም ለህሊና አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛ በመስጠት ነጻ ሆና ትሰራ ዘንድ መንገዱን ምቹ ያደርጉላት ነበር፡፡ ይህ አይነቱ የመቀባበል መንፈስ ህሊና ውስጧ  ያለውን ሃሳብ ያለ አንዳች መከልከል እንድታወጣ አግዟታል በማለት አቶ ሀብቴ ትዝታውን ያነሳል፡፡

 

አቶ ሀብቴ፣ ህሊና ጀርመን ተማሪ ቤት መማሯ ለቋንቋ የተለየ ፍቅር እንዲኖራት ያደረገ ይመስለኛል ሲል ህሊና በጊዜው ከነበሩ የሚድያ ሰዎች በእንግሊዝኛም ሆነ በጀርመንኛ  ችሎታዋ የተሻለ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ እንደ ህሊና አይነት ሰዎች ደግሞ በጊዜው ደርግ /ቤት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ ማስፈለጋቸው አልቀረም፤ ስለሆነም የህሊና  ከኢቲቪ ወደ ደርግ /ቤት መዛወር ትልቅ ትምህርት እንድታገኝና እርሷም አንዳች አስተዋጽኦ እንድታበረክት እንደረዳት አቶ ሀብቴ ያምናል፡፡

 

‹‹….. እኔ ህጻን ስለነበረች ጩጬ ነበር የምላት፡፡ እርሷ ግን ማንነቷን አስመስክራ ፤ችሎታ የተቸረች መሆኑን አሳይታ አደራዋን የተወጣች ናት ›› ሲል አቶ ሀብቴ ህሊና ያለፈችበት መንገድ ለብዙዎች  አስተማሪ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ‹‹…በተለይ አንዳንድ የሚድያ ሰዎች  ዛሬ ድረስ ፊታችሁ የልጅ ነው ተብለው  በኋላ በሂደት አቅማቸውን አውጥተው ሲታዩ አስደነቂ ሆነው የተገኙ ነበሩበት፡፡ ህሊናም ተስፋ ሳትቆርጥ ጠንክራ በመስራቷ ለትልቅ ደረጃ መብቃቷን አቶ ሀብቴ ይመሰክራል፡፡

 

‹‹ …..ህሊና ሁሉን አንቱ ብላ የምትጠራ በስርአት ያደገች ልጅ ናት፡፡ መጀመሪያ አንቱ ብላ ቀርባ ከዚያም ከተግባባች በኋላ አንተ በማለት የወዳጅነት ስሜትን የምታሳይ ትሁት ልጅ/ እናት ነች፡፡ ህሊና እኮ ገጽታ ገንቢያችን ነበረች፡፡ ብራንዳችን ነበረች፡፡ በተለይ ደርግ /ቤት ሳለች የእኛ ብራንድ ነበረች፡፡ ህሊና ትሰራ በነበረበት ጊዜ  እንደ ታደሰ ተስፋዬ አፈወርቅ ማና ፤አብርሀም ሳሙኤል የመሰሉ በሳል ክህሎትን የታደሉ ዳይሬክተሮችም ከጎንና ከጀርባ ሆነው ለህሊና ልዩ እገዛ ይሰጡ ነበር፡፡›› ሲል አቶ ሀብቴ ይናገራል፡፡

 

ህሊና፣ ኢቲቪ ትሰራ በነበረበት ጊዜ የራሴ የምትለው ቡድን አልነበራትም፡፡ ከሁሉም ጋር ትግባባለች፡፡ ከላይ ማኔጅመንት እስከ ታች ድረስ ለህሊና የተለየ አክብሮት ነበራቸው፡፡ ሰዎችን አስተባብራ አግባብታ የመስራት ችሎታን በሚገባ የታደለች ስለነበረች ሰው ከህሊና ጋር ለመስራት አያዳግተውም፡፡

 

‹…….‹ህሊና  ወደ ቀረጻ ከመሄዷ ቀደም ብሎ ለካሜራ ባለሙያው እንዲቀረጽላት ስለምትፈልገው ነገር ትናገራለች፡፡ የት ቦታ በምን አይነት መንገድ ቀረጻው እንደሚከናወን ቀድማ ታዘጋጃለች፡፡ ይህም ለካሜራ ባለሙያው ቀላል ይሆንለታል፡፡ ለካሜራ ባለሙያውም ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ታደርገዋለች፡፡ አውቆት እና ደስ ብሎት ፈጠራዊ ክህሎት እንዲጨምርበትም የተቻላትን ታላቅ ጥረት ታደርጋለች፡፡  በዚህ ክህሎቷ ምንጊዜም ትመሰገናለች፡፡ ህሊና፣ ሚድሮክ ከገባች በኋላ የኢትዮጵያ ቲቪ ማስታወቂያ ስፖንሰር እንዲያገኝ ትልቅ እገዛ አድርጋለች፡፡ መዝናኛውን በስፖንሰር እንድናሳድግ ህሊና ቀኝ እጃችን በመሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን አግዛለች፡፡  በእኔ እምነት ህሊና ገጽታ ገንቢ ናት፡፡ ተሰጥኦ ስለነበራት በገባችበት ቦታ ሁሉ ይሳካላታል፡፡ ይህ ስኬቷ ደግሞ በሁሉም ሰዎች ዘንድ ሊስተዋል የሚችልና የሚታይ ለውጥ ነው ያመጣችው፡፡ መጀመሪያ የኢቲቪን ገጽታ ገነባች፡፡ በመልካም አሻራዋም ስሟን አስጠራች፡፡ ከዚያም ደርግ /ቤት ገብታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቅም አሳየች፡፡ ቀጥላም ሚድሮክ ገብታ የአንድን ተቋም ገጽታ በበቂ ሁኔታ መገንባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳየች፡፡ ከዚያ ደግሞ በኪነጥበቡ እና በሚድያው ስራ ላይ ተሰማርታ ድንቅ እናት መሆኗን አስመሰከረች፡፡ አሁንም በዚህ ትጋቷ ቀጥላበታለች፡፡ መልካም እድል እንዲገጥማት እመኛለሁ›› ሲል አቶ ሀብቴ ስለ ህሊና የሰጠውን ሀሳብ ቋጭቷል፡፡

 

              ህሊና ቲቪ ላይ አየር ላይ ያዋለቻቸው መሰናዶዎች

 

ህሊና፣ እጅግ ተወዳጅነት ካተረፉላት ስራዎቿ መካከልም አንደኛው የጡት ካንሰርን በተመለከተ የሰራችው ነው፡፡ ህሊና፣  ጥቁር አንበሳ ውስጥ የሰልጣኞች እና የኦፕሬሽን ማድረጊያ ክፍል ውስጥ ተገኝታ ነበር የቃለ-ምልልስ ስራውን ያከናወነችው፡፡  በጊዜው  ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጋር  ነበር  ቃለ-ምልልሱን ያደረገችው፡፡ አንድ የጡት ካንሰር ታካሚ የነበሩ እናትንም በማነጋገር  የሰራችው መሰናዶ በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅነትን ያተረፈላት ነበር፡፡

 

የዚሁ ዝግጅት ተከታይ ክፍል፣ ከሁለት ወር በኋላ ከታካሚዋ መልካም የጤና ለውጥን በመከታተል ቀጣይነት ያለው ዝግጅትም ለተመልካች አቅርባለች፡፡

 

ከብዙዎች ህሊና የማይጠፋው የህሊና የቲቪ መሰናዶ   ደግሞ ከባዕድ አምልኮ ጋር በተገናኘ አባኮራን ሰፈር ውስጥ ውሾችን በማርባት የአካባቢን ጽዳት ጭምር ይበክሉ ስለነበሩት ግለሰብ የሰራችው ነው፡፡

 

ሌላው   በከተማ ውስጥ ለብዙዎች የእንቅልፍ መድሃኒት ስለሚሰጠው ሰው የሰራችው መሰናዶ ነው፡፡  ይህ ሰው ብዙዎችን ገንዘብ እና ወርቅ ጭምር ይሰርቅ የነበረ ወጣት ሲሆን ስለዚህ ሰው አየር ላይ ያዋለችው መሰናዶ በርካታ ተመልካች ያስገኘላት ነበር፡፡

 

ህሊና፣ በወቅቱም አብረዋት ይሰሩት ለነበሩት ከስራ ሰዓት ውጪ ጭምር በማምሸት በማደር እንዲሁም አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፈል ይተጉ ለነበሩት ባልደረባዋ የካሜራ ባለሙያ ኢሳያስ ለማ  ምንግዚም አድናቆቷን መለገስ ትፈልጋለች፡፡ ለእርሳቸው የነበራት ክብር እና አድናቆትም በእጅጉ ከፍ ያለ ነበር፡፡

 

በወቅቱም ‹‹ከየአቅጣጫው›› የተሰኘው የቴሌቪዥን ዝግጅት በብዙ ተመልካቾች ዘንድ እጅግ ተወዳጅነትን  እንዲያገኝ የህሊና እና የጓደኞቿ ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡

 

ህሊና ተፈራ፣ ሙዚቃዎችን ዳይሬክት በማድረግም  ትታወቅ ነበር፡፡ ለዚህ ማሳያ የሆነው ስራዋም የመልካሙ ተበጀ ስራ ‹‹ደህና ሁኚ›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡

 

በወቅቱ የነበሩት ባልደረባዎቿም የወቅቱ አለቃቸው ጌታቸው /ማርያም የዜና መዋዕለ ክፍል ሃላፊ በምክትል ሃላፊነት ፀሃዬ ደባልቀው ሰለሞን ክፍሌ  ዜናነህ መኮንን ስዩም መንግስቱ አስቻለው ደምሴ በየነ ብርሃነ ልዑልሰገድ ኩምሳ ሚሊዮን ተረፈ ተፈራ አስማረ አስፋው ኢዶሳ ሃብቴ ገመዳ ንጉሴ ሶሪ ወርቅነህ ክፍሌ አለሙ ቶሎሳ አምሳለገነት ይመር ብዙ ወንድምአገኝ ተገኝ  አንግዳዘር ነጋ ከብዙ በጥቂቶቹ የሚነሱ  ናቸው፡፡ ህሊና በተለይ ከሰለሞን ክፍሌ እና ታደሰ  ተስፋዬ ጋር የበለጠ ትቀራረብ ነበር፡፡ ታደሰ ተስፋዬ እና ሰለሞን ክፍሌ በህብረ-ትርኢት ዝግጅት የሚታወቁ የህሊና ባልደረቦች ነበሩ፡፡ ታደሰ ተስፋዬ የህብረ-ትርኢት የጀርባ አጥንት በመሆን ያገለግል የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ደግሞ ዳላስ ቴክሳስ ውስጥ መኖሪያውን ያደረገ ባለሙያ ነው፡፡

 

3 አመት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቆይታዋ በወጣትነት ዕድሜዋ ብዙ ስራዎችን መስራት የቻለች ጎበዝ እጅግ ታታሪና ተወዳጅ ጋዜጠኛም ጭምር ነች ህሊና ተፈራ፡፡

 

ለሚዲያ ስራዎች ማለትም በብሮድካስት ዘርፍ ለቴሌቪዥን እና ለራዲዮ እንዲሁም ደግሞ ለህትመት የሚዲያ ስራ ጭምር ያላት ከፍተኛ ፍላጎት እና የስራ ተነሳሽነቷ የህሊና ተፈራ መለያዋ ነው፡፡

 

  ህሊና  በደርግ /ቤት

 

ህሊና 1975 መጨረሻ ላይ ከኢትዮጵያ ቲቪ ለቅቃ ደርግ ጽህፈት ቤት የዶክመንቴሽን እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ ተቀላቅላለች፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የህሊና ስራ ዝርዝር ቃለ-ጉባኤዎችን መያዝ የሀገሪቱን ዝርዝር ክንውኖች ሰንዶ ማቅረብ  ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በሀገሪቱ የነበረውን ውጣ ውረድ፤ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ስብሰባዎችን ሁሉ ወረቀት ላይ አስፍሮ ዶክመንት የማድረግ ትልቅ ሃላፊነት የተጣለው በህሊና ላይ  ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት የአምባሳደሮች አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎች ሁሉ  ላይ በመካፈል የመሰነድ ስራዎችን ገና 22 አመቷ ታከናውን ነበር፡፡ ህሊና በደርግ ጽህፈት ቤት ስትሰራ ቦታው ፈታኝ ብሎም አስጨናቂ ሁኔታ ቢፈጥርባትም ትልቅ እውቀት መቅሰም የቻለችበት አጋጣሚ ነበር፡፡

 

ህሊና በደርግ ጽህፈት ቤት  ስትሰራ ብዙ የህይወት እና የስራ ልምዶች ቀስማለች፡፡ ስለ ሀገራችን የወቅቱ ሁኔታም በቂ እውቀት ገብይታለች፡፡ ሀገሯን ከጫፍ ጫፍ ጎብኝታለች ስለ ስራ ፕሮቶኮል ስለ ቋንቋ አጠቃቀም ስነ- ስርዓት በንግግርና በፅሁፍ ወቅት ሀገርን የማስተዳደር እና የመምራት ጥበብን የመሳሰሉ የህይወት ልምዶችን ማግኘቷን በግልፅ ትናገራለች፡፡ ይህም አሁን ላለችበት ደረጃ ብቃትን እንድትላበስ አስችሏታል፡፡

 

ህሊና ተፈራ በብዙዎች ዘንድ የተለየ ችሎታዋ የሚባልላትም የጊዜ አጠቃቀሟ ነው፡፡ ስራን በቶሎ ማስረከብ አምጪ ጨረሽ ወይ? ተብላ ከመጠየቋ አስቀድሞ ስራውን በአግባቡ እና በጥራት ጨርሳ ለአስፈላጊው ተግባር ከአስፈላጊው ጊዜ በፊት ቀድማ ሰርታ ታስረክባለች፡፡

 

የዩኒቨርሲቲ የታሪክ ጥናት ትምህርቷንም 2 ዓመት በላይ በወቅቱ ከነበራት  የስራ ሃላፊነት ጋር መቀጠል አልቻለችም ፡፡

 

ህሊና፣ በህይወቷ ውስጥ ባለፉት  አጋጣሚዎች እና ሁኔታዎች ሁሉ  ማማረር እና መቆጨት  አትፈልግም፡፡ ከሁሉ ነገር መማር እንደሚቻል ታምናለች፡፡

 

   የትዳር ህይወት ሚድሮክ -ከዛም የራስ ስራ

 

ታህሳስ 29 1983 . የገና በዓል ወቅት ላይ ነበር ትዳሯን የመሰረችው፡፡

 

    1983 ግንቦት 20 የመንግስት ለውጥ በተደረገበት ጊዜ ህሊና 4 ወር ነፍሰ- ጡር ነበረች፡፡   ያለችበት ስራ ፈታኝ ሆኖ ቢገኝም የወቅቱ አስፈሪ ሀገራዊ ሁኔታ ሳይበግራት በሀገሯ ቆይታ ትዳር እና ህይወቷን በፈተና ውስጥ መርታለች፡፡

 

ከባለቤቷ  ከአቶ ሳህሉ ወልደ ልዑል ጋር ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቀጥራ በምትስራበት ወቅት ነበር የተዋወቀቺው፡፡ ከትዳር በፊትም በጓደኝነት ረዥም ጊዜያትን  ማሳለፍ ችለዋል፡፡

 

ህሊና ከመንግስት መቀየር በኋላ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ከታምራት ላይኔ ጋር ተመድባ የምትሰራበት ዕድል እንዳለ በጭምጭምታ ሰማች፡፡ ምንም አይነት የመንግስት ስራን መስራት እንደማትፈልግ ገልፃ ሁለት ልጆቿን ብቻ ለማሳደግ በቤቷ ያለስራ ለመቀመጥ ተገደደች፡፡

 

ሁለት ልጆቿን ከወለደች በኋላም ሼህ መሃመድ አሊሙዲን ድርጅት  ውስጥ 3 ዓመታት ያህል  ተቀጥራ መስራት ጀምራለች፡፡

 

በመቀጠልም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ውስጥ በማናጀርነት፣ የህዝብ ግንኙነት ማናጀር፣ እንዲሁም ሚድሮክ ኮርፖሬት ኦዲዮ ቪዥዋልን በማቋቋም እና በመስራት፣ እንዲሁም  በሁለት ቋንቋዎች ይታተም የነበረውን ‹‹ጥረት›› መፅሄትን መመስረት ችላለች፡፡  በየስድስት ወሩ  አንድ ጊዜ ለንባብ የሚበቃውን ጥረት መፅሄትን ደረጃውን ጠብቆ እንዲወጣ በማድረግ  የተቋሙን ገፅታ  ለመገንባት ችላለች፡፡

 

በነፃ ለአንባቢያን ይታደል የነበረው ‹‹ጥረት›› መፅሄት ብዙ ሰዎች ስለ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በብዙ እንዲረዱና እንዲያውቁ ያደረጋቸው ነበር፡፡ በመጽሄቱ ላይ ያላቸውንም አስተያየት በተለያዩ መንገዶች ይገልፁ ነበር፡፡ ይህም የተቋሙ አንዱ የስኬት መንገድ ነበር፡፡

 

ህሊና ተፈራ  ፣ለ6 ዓመትም በሚድሮክ ኢንቨስትመት ግሩፕ ውስጥ አገልግላለች፡፡

 

         አቶ አስፋው መንግስቱ ስለህሊና

 

አቶ አስፋው መንግስቱ ካሳ፣ ህሊና ጋር ሚድሮክ አብረው ይሰሩ ነበር፡፡ በአሁኑም ሰአት መኖሪያቸውን በአሜሪካን ሀገር ያደረጉ ናቸው፡፡ አቶ አስፋው በሚድሮክ የድርጅቱ ጉዳይ  ፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ ህሊና ደግሞ የድርጅቱ /ቤት ሃላፊና የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሆና ትሰራ ነበር፡፡

 

አቶ አስፋው፣ ህሊና ሚድሮክ በነበረች ጊዜ ታሳየው የነበረውን ጥረት ሲገልጹ‹‹…. ህሊና የድርጅቱን ገጽታ በጥሩ መልኩ ለመገንባት የተቻላትን ያህል ጥረት አድርጋለች፡፡ ዋናው ስራዋም ይሄው ስለነበር በዚህ ረገድ ጠንካራ ባለሙያ ነበረች፡፡ ይህን ሀሳቧን ደግሞ የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ ‹‹ጥረት›› የተሰኘውን መጽሄት በማሳተም የተሰጣትን ሙያዊ ሃላፊነት ከጥሩ ብቃት ጋር ለመወጣት ሞክራለች፡፡ በተቻላት  መጠን ጥሩ ቃለ-ጉባኤዎችን በማሰናዳት ድንቅ ስራ ሰርታለች፡፡  ህሊና ድንቅ የስነ-ጽሁፍ ችሎታ አላት፡፡ ሙዚቃንም ደህና አድርጎ የማጣጣም ክህሎትን ታድላለች፡፡ ከባልደረቦቿ ጋር ያላት ግንኙነት ደግሞ መልካም በመሆኑ ሰዎች በጣም አክብሮት ይለግሷት ነበር፡፡ ወይዘሮ ህሊና የተሰጣትን ስራ አክብራ የኖረች ሰው ናት፡፡ 1985 ጀምሮ 15 አመት ስለማውቃት ይህን ጥረቷን በቀላሉ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ በአንድ ቢሮ ውስጥ እንሰራ ስለነበርም ብዙ ሀሳቦችን እንለዋወጥ ነበር፡፡ በቅርብም በስራ እንገናኝ ነበር፡፡ እና ጠንካራ ሰው መሆኗን መመስከር እችላለሁ›› በማለት አቶ አስፋው ስለ ህሊና ተፈራ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

 

                                ተፈራ  ፕሮሞሽን

 

በመቀጠልም 1992 . ቦሌ መድሃኒአለም ኣካባቢ ተፈራ ፕሮሞሽንን በራሷ ጥረት ማቋቋም ቻለች፡፡

 

በተፈራ ፕሮሞሽን ድርጅቷ አማካኝነት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዩኤንዲፒ እና ከኢትዮጵያ ቴሌ ኮሚዩኑኬሽን ጋር የስራ ዕድል ቀረበላት፡፡

 

በኢትዮጵያ ቴሌ ኮሚዩኑኬሽን ውስጥም ያስገቡት ካርድ አገልግሎት ላይ አልዋለም …… የሚለው ድምፅን ጨምሮ ሌሎች የቴሌ የኦፕሬተርነት ድምፅን በሁሉም ኢትዮጵያዊ ስልክ ውስጥ የሚደመጠውን መስራት ቻለች፡፡

 

የተፈራ ፕሮሞሽን የመጀመሪያ ስራም ይሄው ነበር፡፡

 

ከቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ጋርም አምስት ያህል የፕሮጀክት ስራዎችን ጨምሮ ከዩኤንዲፒ፣ ከዩኤስአይዲ፣ ከሴቭ ችልድረን ጋር ጭምር የመስራት ዕድሎች በተፈራ ፕሮሞሽን አማካኝነት ተፈጥረውላት ነበር፡፡

 

የተለያዩ ኮንፍረንሶችን በማዘጋጀት የህትመት የቪዲዮና  የወርክ ሾፕ ስራዎች ከእነዚሁ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር  በመሆን ሰፊ  ተግባራትን ማከናወን ችላለች፡፡

 

ከእነዚህ ስራዎቿ ጋር ተያይዞ የመጣው ትልቁ የስራ ዕድል ከአለም አቀፉ ድርጅት አይ ኤል ጋር በመሆን  የሰራችው ነበር፡፡ በሴቶች የንግድ ዘርፍ ላይ ትኩረቱን ያደረገ  የንግድ የሬዲዮ ፕሮግራም በኤፍ ኤም 97.1 ላይ ታዘጋጅ ነበር፡፡ በዚህም ትልቅ ከበሬታን ማግኘት የቻለች ሰው ናት፡፡

 

ፕሮግራሙም፣ በንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሴት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች አራት የአፍሪካ ሀገራት ሴቶችን ተሳታፊ ያደረገ  ትልቅ የሬዲዮ ፕሮግራም ነበር፡፡

 

            ኤፍሬም እንዳለ ስለ ህሊና ተፈራ

 

    ጋዜጠኛ እና የመጽሀፍ ደራሲ ኤፍሬም እንዳለ፣  ብዙ ጊዜ ስለ ሰዎች ሀሳብ ሲሰጥ አናየውም፡፡ የራሱ አሳማኝ ምክንያት ይኖረዋል፡፡  ህሊናን በተመለከተ ግን ጥቂት ቃላት ቢናገር እንደሚፈልግ ነገረን፡፡ አንድም ህሊና  ምሳሌ ልትሆን ስለምትችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሥራ ጋር በተያያዘ እሷ ላይ ኤፍሬም ይመለከታቸው የነበሩ ክህሎቶች  ብዙዎች ላይ እያየ ስለማይመስለው ሀሳቡን እንደሚከተለው ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ልኳል፡፡

 

‹‹……ከህሊና ጋር የተዋወቅነው እሷ ሚድሮክ በነበረችበት ጊዜ ነው፡፡ በእርግጥ ከዛ በፊትም በአካል ተገናኝተን ባናውቅም በርቀት አውቃት ነበር፡፡ ህሊና እጅግ ጠንካሮች ከሚመስሉኝ ባህሪዎቿ አንዱ የሥራ ፍላጎቷና ትጋቷ ነው፡፡ ለሥራ የምትሰጠው ግነት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ምንም አደናቃፊ ነገር ጣልቃ እንዲገባ እንደማትፈቅድ አጠገብ ሆኜ ያየሁላት ክህሎት ነው፡፡ በተጨማሪ አንድ ሥራ ቀንም ሌትም ተግታ ፍጻሜው ካደረሰችው የልቧ  የሚደርስላት አይደለችም፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ በግሌ የማደንቅላት ሌላው ባህሪይ ለሥራ ጥራት የምትሰጠው ትኩረት ነው፡፡

 

የህሊና የፈጠራ ችሎታ ፈጠራ ውስጥ አለሁ ለሚለው ሰው  የሚያስደምም ነው፡፡  የምታመጣቸው የሥራ ሀሳቦች፣ ወይንም በተለምዶ እንደሚባለው ፕሮጀክትሀሳቦች የታሰበባቸው፣ የተደከመባቸውና ለእያንዳንዷ ነጥብ ሙሉ ትኩረት የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ በኪነጥበብና በባህል ዘርፉ አስባቸውና በተግባር ማዋል ጀምራቸው የነበሩ ሀሳቦች ድግምግሞሽ የሌለባቸውና እንዳሰበችው ብዙ እርቀት ሄደው ቢሆን ኖሮ ያለማጋነን የራሳቸው ተጽእኖ ይኖራቸው ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ለብዙ የኪነ- ጥበብ  ባለሙያዎች መድረኩን ላላገኙ ወጣቶች ከህዝብ መተዋወቂያ የሚሆንም ነበር፡፡ ለጊዜዋ፣ ለጉልበቷና ለገንዘቧ ሳትሰስት እስከመጨረሻው ለመሄድ የሞከረችበትን ትእግስት መጥቀስ ይኖርብኛል፡፡ ግን...አዳዲስና ለረጅም ጊዜ የሚታቀዱ ሀሳቦች በቀላሉ ወደ ተግባር የሚለወጡበት ማህበረሰብ ባለመሆናችን  ያሰበችውን ያህል ርቀት አለመሄዱ ያሳዝነኛል፡፡

 

በዚህ ሁሉ መሀል ግን እንደ እኛ ባለ ብዙ ነገሮች በተጠላለፉበት ማህበረሰብ ውስጥ ህሊና ለነገሮች ያላትን አዎንታዊ (‘ፖዘቲቭእንዲሉ) አመለካከት መጥቀስ ይኖርብኛል...ጨለምተኝነት ብዙ ነገሮችን በሚያጨልምበት ዘመን አዎንታዊ መሆን የሚያስመሰግን ክህሎት ነውና!>>   በማለት ኤፍሬም እንዳለ ስለ ህሊና ተፈራ እንዲነግረን በጠየቅነው መሰረት ሀሳቡን ለግሶናል፡፡

 

         ጉዞ ወደ አሜሪካ

 

የተፈራ ፕሮሞሽንን 8 ዓመታት ስራ በኋላ በመዝጋት ወደ አሜሪካ ማቅናት ቻለች፡፡

 

ለልጆቿ የትምህርት ህይወት ስትልም ነበር ወደ አሜሪካ ያቀናችበት ምክንያት፡፡

 

በአሜሪካም ልጆቿ የኮሌጅ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የራሳቸውን ህይወት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

ሴት ልጇ ምርጫዬ ሳህሉ ሁለቱንም ዲግሪዋን በቴሌቪዥን ብሮድካስቲንግ እና ፐብሊክ ሚዲያ  ያገኘች ሲሆን  ወንዱ ልጇ ደግሞ በጆርናሊዝም እና በፊልም ትምህርት ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

 

ሁለቱም ተመርቀው ስራ እየሰሩና የራሳቸውን ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ፡፡

 

የራስን ህልም መከተል ህልምን እውን ለማድረግ መጣር እና አስፈላጊውን እርቀት ተጉዞ መስዋእትነት በመክፈል እና ሕልምን በመኖር በጉልህ የምታምነው ህሊና ተፈራ ይሄንኑ ተግባሯን የሚያሳየው ‹‹ቼዝ ድሪም›› የተሰኘውን ድርጅት መመስረት ችላለች፡፡

 

በድርጅቷም በባህል በኪነ-ጥበብ በስነ- ውበት ዙሪያ የሚያተኩር chase the dream culture at the beauty የሚል ድርጅትን ከአፍሪካ አሜሪካ ጓደኛዋ ጋር በመሆን በየ 6 ወሩ ለንባብ የሚበቃ የኦንላይን መፅሄት) እንዲሁም በተጨማሪነት evening of cultures የተሰኘ አመታዊ የፓናል ዝግጅት በማሰናዳት እየሰራች ትገኛለች፡፡

 

በተጨማሪነትም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ስለ አሜሪካ እንዲያውቅ የተመለከተቻቸውን ትዝብቶቿን በመጣጥፍ መልክ በማዘጋጀት በመጽሃፍ መልክ ለማሳተም አዘጋጅታ ጨርሳለች፡፡፡

 

ከዚህ ባለፈም  ከባልደረባዋ ሰለሞን ክፍሌ ጋር በመጪው የፈረንጆቹ ኦክቶበር ወር ላይ  አንድ አዲስ ነገር ለመስራት መሰናዶዋን አጠናቅቃለች፤፡

 

በተጨማሪነትም በአባቷ ስም የተሰየመው እና በወንድ ልጇ አማካኝነት የተቋቋመውን ተፈራ ፋውንዴሽንንም ለመመስረት ሙሉ ዝግጅቷን ጨርሳለች፡፡

 

‹‹ክብር ለጥበብ›› የተሰኘ ፕሮጀክትንም ጭምር ለአባቷ ታሳቢነት በማድረግ በጊዮን አዳራሽ ለብዙ ኪነጥበብ ሰዎች ትልቅ ግብዣ በማድረግ ሰርታለች፡፡

 

ህሊና ተፈራ ከጋዜጠኝነት ሙያዋ በማይተናነስ መልኩ ለኪነ- ጥበብ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር እና ስሜት አላት፡፡ ያንን ለማድረግም ብዙ የኪነ ጥበብ ሰዎችን እውቅና እንዲሰጣቸው የማድረግ እንዲሁም የኪነ- ጥበብ ችሎታቸው እና ስራቸው ከሀገራቸው ተሻግሮ እንዲታወቅ ለማድረግ በርካታ የግል ጥረቶችን በማድረግም በስፋት ትታወቃለች፡፡

 

       የህሊና ልጅ ምርጫዬ ስለ እናቷ

 

ምርጫዬ ሳህሉ የህሊና ተፈራ ልጅ ስትሆን ስለ እናቷ የሰጠቺን ምስክርነት እንደሚከተለው ይቅርባል፡፡

 

እናቴ ለእኔ ትልቅ መነቃቃት የምትፈጥርልኝ ናት፡፡ ሁል ጊዜ የምታከናውነውን በማየት ነበር ያደግኩት፡፡ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለማጥናት የወሰንኩት በእርሷ ምክንያት ነው፡፡ ገና 19 አመት ወጣት ሳለች ጀምሮ በኢትዮጵያ ቲቪ ስትሰራ ታደርግ የነበረውን ጥረት እሰማ ነበር፡፡ በሳል ፕሮግራሞችን አየር ላይ ታውል ነበር፡፡ ስለ ጡት ካንሰር 1970ዎቹ አጋማሽ ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙም አይወራም ነበር፡፡ ህሊና ግን ባለሙያ አነጋግራ ሀኪም ቤት ድረስ ሄዳ የቲቪ መሰናዶ ሰርታ ለእይታ አብቅታለች፡፡

 

እናቴ የሴቶች ድምጽ እንዲሰማ ጠንክራ ትታገል ነበር፡፡ ራሷ ችላ በመገኘትም እንደ አርአያ በመሆን ለብዙዎች ተምሳሌት ሆናለች፡፡

 

ተፈራ ፕሮሞሽንን በከፈተችበት ጊዜ በጣም ለሀገር የሚበጁ ስራዎችን አከናውናለች፡፡  ለአለም አቀፍ የስራ ድርጅት / አይኤልኦ / ጋርም በትብብር ትሰራ በነበረበት ጊዜ ምን ያህል ስራዋን በብቃት ታከናውን እንደነበር አልዘነጋውም፡፡

 

‹‹ሴቶች በንግድ አምባ›› የተሰኘውን የሬድዮ ፕሮግራም በምትሰራበት ወቅትም  አልፎ አልፎ ቃለ-መጠይቆችን ስታከናውን አብሬአት የሆንኩበትን ጊዜ አልዘነጋውም፡፡

 

እናቴ ለስራዋ የነበራትን ታላቅ ጉጉት በፍጹም አልዘነጋውም፡፡ መጻፍ ትወዳለች፤ አዲስ ነገር መፍጠርም ያስደስታታል፡፡

 

የሚድያ ሰው ህሊናን እንደ እናት ስገልጻት ደግሞ  በጣም ተንከባካቢ የፍቅር ሰው፤ዘና የማታደርግ ጥሩ አድርጋ ሰዎችን የምታደምጥ ናት፡፡ እናት ህይወትን ጥሩ አድርጎ ማጣጣምን ታውቅበታለች፡፡ ደስ የሚላትን ልብስ ትለብስና ሞገስ ይፈስባታል፡፡ ቤቷ ውስጥ ሰዎችን ስትጋብዝ ደስ ይላታል፡፡ የምግብ ማብሰል ችሎታዋን ብዙዎች ይወዱላታል፡፡ መሳቅ መጫወት ከምንም በላይ ርካታን ይፈጥርላታል፡፡

 

ልጅ በነበረን ጊዜ ጥናታችን  ላይ ትኩረት እንድናደርግ ታበረታታን ነበር፡፡ ተማሪ ቤት የሚሰጠንን የቤት ስራ በአግባቡ እንድንሰራ ምክር ትለግሰን ነበር፡፡  የወግ ጽሁፎች እንድንጽፍ የቤት ስራ ሲሰጠንም በማረም አስፈላጊውን ርዳታ ታደርግልን ነበር፡፡ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በዚህ መልኩ ልዩ እገዛ ስታደርግልን ኖራለች፡፡ እኛ አሁን ላለንበት ስኬት የበቃነው በእርሷ ምክንያት ነው፡፡

 

እናቴ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ እያበረከተች ያለችውን አስተዋጽኦ በግልጽ መመስከር እችላለሁ፡፡ ክብር ለጥበብ ላይ እዚህ አሜሪካን ሀገር የምታዘጋጃቸው አፍሪካን ለቀሪው አለም የሚያስተዋወቁ መሰናዶዎች አስተዋጽኦዋቸው ትልቅ ነው፡፡

 

እናቴ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ መሸነፍን ፍጹም ሳትቀበል እነሆ ዛሬም ውስጡዋ ያለውን ሙያ ታወጣለች፡፡ በዚህም ለምንም በላይ ደስተኛ ናት፡፡ በምንም ነገር ተስፋ የማትቆርጠው እናቴ ለእኔና ለወንድሜም ይህንኑ ታላቅ ጽናት አውርሳናለች፡፡ 

 

ከዚህ ባለፈም አፍሪካውያን እርስ በራሳቸው በጥበቡም ከዛም ባለፉ ግንኙነቶች በመፍጠር የግል ጥቅማቸውን እንደ አፍሪካ እንዲያስከብሩ ብዙ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በርካታ ስራዎችንም እየሰራች ትገኛለች፡፡

 

ለዚህ ማሳያዋ ደግሞ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳ በኮራ ውድድር ላይ እንዲወዳደር ደቡብ አፍሪካ ድረስ ይዛው ማቅናት ችላለች::

 

ይህን ሁሉ ስራዎችን ስትሰራ ግን ምንም አይነት ድጋፍ ያልተደረገላት ህሊና ተፈራ ብዙ በጥበብ ነክ ጉዳይ በሀገሯ ኢትዮጵያ በማዕከል ደረጃ በመስራት ትልቋ ህልሟ ነው፡፡

 

        የእህትማማችነት ሀይል መጽሀፍ /the power of sisterhood /

 

ይህ መጽሀፍ ከሰሞኑ ለህትመትና ለምረቃ የበቃ  መጽሀፍ ሲሆን ‹‹ሲስተርስ ፎር ሲስተርስ›› በተሰኘ ተቋም አማካይነት የታተመ መጽሀፍ ነው፡፡ በዚህ  መጽሀፍ ውስጥ ህሊናን ጨምሮ ቁጥራቸው 29 በላይ የሚጠጋ አፍሮ አሜሪካውያን ሴቶች ልምዳቸውን በጽሁፍ አካፍለዋል፡፡  ህሊና ኔትወርኪንግ ወይም ትውውቅ መፍጠር የሚለው ሀሳብ ትልቅ መሆኑን ስለምታውቅ በዚህ መጽሀፍ ላይ ልምዷን አካፍላለች፡፡ 29 ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እድል የተሰጣቸው ሴቶች እያንዳንዱ 1700 ቃላት እንዲጽፉ እድል የተሰጣቸው ሲሆን ህሊና ከእነዚህ አንዷ ሆና በመጽሀፉ ላይ መጣጥፏን አበርክታለች፡፡

 

መዝጊያ ህሊና ተፈራ መኮንን ከጊዜ ጋር እየሮጠች ያለች ሁለገብ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ናት፡፡ ገና 19 አመቷ አንድ ብላ የጀመረችውን የሚድያ ስራ ዛሬ ላይ ከእነ ሙሉ ክብሩ ጠብቃ እያከናወነችው ትገኛለች፡፡ ህሊና ተፈራ ተሰጥኦ የታደለች ወይም ተሰጥኦዋን አውቃ እየተጋች ያለች ብርቱ ባለሙያ ነች፡፡ ኢትዮጵያዊ ትህትናን እንደተላበሰች የምትወደውን ሙያ ዛሬም በምድረ አሜሪካ እየሰራች ትገኛለች፡፡ የህሊና ታሪክ ብዙ ነገሮችን ያስተምራል፡፡ ህሊና ሚድያ ላይ መግባት ትፈልግ ነበር-ግን በቀላሉ አላገኘችውም፡፡ ጠብቂ ተብላ መጠበቅ ነበረባት፡፡ ታግሳ የምትሻውን አገኘች፡፡ እዚህ ጋር የሚፈልጉትን ለማግኘት መታገስ ጥቅም እንዳለሁ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ህሊና ቲቪ ከገባች በኋላ የምትወደውን በመስራቷ ስኬታማ ሆነች፡፡ ቲቪ ላይ በቆየችባቸው 3 አመታት በአጭር ጊዜ ስመ-ጥሩ ሆነች፡፡ ቀልጣፋ እና ከሁሉ ጋር ተግባቢ ስለነበረች የምታቀርበው ሁሉ ያምርላት ነበር፡፡  ስለዚህ የሰው ልጅ የሚወደውን እና የሚችለውን ሲሰራ ይጣፍጥለታል፡፡ ህሊና ለኪነጥበብ በተለይም ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ስለነበራት ህይወትን የምታይበት ጎን በበጎ የተሞላ ነበር፡፡ ህሊና በተለይ አባቷ ሙዚቀኛ ስለነበሩ ለጥበብ ሩቅ እንዳትሆን አድርገዋታል፡፡ ህሊና የልጅነት ህልሟን እየኖረች ስለሆነ ከዚህ በላይ ምን ደስታ ሊገኝ ይችላል እያለች በሀሴት ኑሮን እያጣጣመች ትገኛለች፡፡ ህሊና ቲቪ በነበረች ጊዜ፤ ደርግ /ቤት  ባገለገለችበት ወቅት ሚድሮክ በሰራችባቸው 7 አመታት ውስጥ ትጋት ሁነኛ መለያዋ ነው፡፡ ይህን አብረዋት የሰሩ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ ተፈራ ፕሮሞሽን የተሰኘውን ድርጅት ከፍታ በሰራችባቸው ጊዜያትም የትጋት ተምሳሌት ነበረች፡፡ ክብር ለጥበብ ብላ የሰሩ ሰዎችን ስታመሰግን እርሷም እየተመረቀች ነበር፡፡ ህሊና በሁሉም መስክ ጥረትን ያሳየች በመሆኑ ውጤቱ ስኬት መሆኑ አልቀረም፡፡ በሀገራችን ጠንካራ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ብዙም ባልበዛበት በዚህ ጊዜ የህሊና የስራ ተሞክሮ ብዙዎችን ያነቃቃል፡፡ ሀገር ቤት የነበረውን ስራ ባህር ማዶ ወስዳ ‹‹ቼዝ ዘድሪም›› ስትል ህልሟ ለአለም አንድ ትርፍ ሊያስገኝ እንደሚችል ወጠነች፡፡ ይህ ውጥኗ ገና ከዚህ በላይ ማደግ የሚችል ነው፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ህሊና ለአዲሱ ትውልድ  የሚያስተምር አንድ ጥሩ ተሞክሮ ያላት ነች፡፡ ይህ ታሪኳ ደግሞ ተሰንዶ ቢቀመጥ ብዙዎችን የማነቃቃት ሀይል አለው ብለን እናምናለን፡፡ ይህን እምነታችንን አጽንኦት ለመስጠት የህሊናን ታሪክ በዚህ መልኩ አሰናድተን አቅርበናል፡፡/ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ አቤል እንዳቅሙና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተጽፎ የተሰናዳ ነው፡፡ ዛሬ መስከረም 16 2014 በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ   በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ ይህ ጽሁፍ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው ይወጣል፡፡

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች