10. ጌትነት ይግዛው Getnet Yigzaw
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ120 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል አቶ ጌትነት ይግዛው አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ጌትነት ከቱሪዝምና ሚድያ ጋር በተያያዘ ለሀገራቸው አንድ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡ ታሪካቸውን ቤርሳቤህ ጌቴ እንደሚከተለው አጠናክራዋለች፡፡
ከቱሪዝምና ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ረዥም የህይወት ዘመንን አሳልፈዋል። ዘርፉን በአጋጣሚ ቢቀላቀሉትም ለመነጠል እስኪቸገሩ ድረስ በአብሮነት ዘልቀዋል። ታድያ መዝለቅ ብቻ አይደለም በተሰማሩበት የስራ መስክ በውጤታማነታቸው ከፍ ያለ ከበሬታን አስገኝቶላቸዋል። አቶ ጌትነት ይግዛው ንጉሴ፡፡
ልጅነት
ትውልዳቸው በጎንደር ከተማ በጣልያን ወረራ ወቅት ቸቸላ በመባል ስያሜ ከተሰጣት አካባቢ ነው። ቸቸላ ጥሩ ትዝታ ያለባት የጎንደር ከተማ አካል ስትሆን አሁንም በመንደሯ ተወልደው ያደጉ ልጆች በተለያየ ምክንያት በመሰደድ እስከ አሜሪካ ድረስ የዘለቀ የቸቸላ ሰፈር ተወላጆች ማህበር መስርተው የጋራ አብሮነት የሚያጠናክሩበትና
እንደ
አንድ
ቤተሰብ
ከሚተያይ
ማህበረሰብ
ውስጥ
ነው የወጡት።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በድሮ አጠራሩ ልዕልት ተናኘወርቅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በደርግ ዘመነ መንግሥት ስሙ ተቀይሮ ህብረት በተባለው የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ከ1ኛ-6 ኛ ክፍል ተምረው ያጠናቀቁ ሲሆን ቀጣዩን ከ7-12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በፋሲለደስ ት/ቤት ተከታትለዋል ።
በወቅቱ በፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበራቸው የመማር ማስተማር ሂደት መሰረት ከ8ኛ-12ኛ ክፍል የምርት ቴክኖሎጂ ተማሪ በመሆን በብረትና በንድፍ ሥራ በተግባር የተፈተነ ትምህርት በመከታተል በወቅቱ ከአዲስ አበባ የተግባረዕድ የሙያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ጋር አቻ የሆነ የዲፕሎማ ሰርትፍኬት አግኝተዋል፡፡ በዚህ የሙያ ትምህርታቸው ዘመንም የተለያዩ የቤት ቁሳቁስና መሰል የብረትና እንጨት ውጤቶች ያመርቱም እንደነበር ከተማሪነት ትዝታቸው አንዱ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ወጣትነት ስራና ትምህርት
የወጣትነት ዘመናቸው መግቢያ ላይ
አገራችን ውስጥ በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት በወቅቱ አጠራር ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር በመባል በሚታወቀው ጭንቅ የደርግ ሥርዓት ውስጥ የወደቀበት ግዜ ነበረና ጅምር የወጣትነት ዘመን በምጥ ያለፈ ነው ለማለት ያስችላል።
የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት እ.ኢ.አ በ1975 ዓ.ም ሲሆን ከዚህ በኋላ የውጭ ትምህርት ዕድል በማግኘታቸው ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ቡልጋሪያ በማምራት የቋንቋ ትምህርታቸውን በሲሊቨን ከተማ በማጠናቀቅ የትምህርትና የሥራ ዘመናቸውን ለመቀጠል ወደ ተደለደሉበት ከጥቁር ባህር ጥግ ወደምትገኘው የቱሪስት መናኸሪያ የቡርጋስ ከተማ በመሄድ በጀኔራል ኢቫን ቪናሮብ በመባል በተሰየመ ተንቀሳቃሽ የባህር ላይ ጋራዥና ግዙፍ የመርከብ ማምረቻ ፋብሪካ ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የትምህርትና የመስክ ስልጠና ሲወስዱ ቆይተዋል። በቡልጋሪያ በዚህ የትምህርት መስክ ለሦስት ዓመት ተኩል ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ እ.ኢ.አ በ1977 ዓ.ም አገራችን ውስጥ በነበረውና እልፍ አዕላፍ የሰው ህይወት ባጠፋው የድርቅና የርሃብ ወቅት በቡልጋሪያ የነበረው ቆይታ ከባድ ጊዜ ሲሆንባቸው ትምህርቱን ሳያጠናቅቁ አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲመጡ አስገድዷቸዋል።
ህይወትን ለመምራት ሥራ ማፈላለግ የግድ በመሆኑ የስራ ፍለጋው ምቹነት ታድያ ከእናታቸው ጉያ ሳይርቁ ሊሆን እንደሚገባ የሚያጠያይቅ አልነበረም፡፡ ምክኒያቱም የቡልጋሪያ ቆይታቸውና ትምህርቱ የተቋረጠውም በዚሁ ምክንያት ነበረና። ከተወሰነ ከቆይታ በኋላ የቴሌኮምዩኒኬሽን በአየር ትራፊክነት ባወጣው የሥራ ማስታዎቂያ መሰረት ተቀጣሪ ለመሆን መንገድ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በቅጥር ውድድሩ በአንደኛነት ደረጃ ቢያልፉም የቅጥር ሂደቱ ከ6 ወር በላይ ይፈጅ ነበረና መጠበቁን በመሰልቸት የጎንደር ከተማ ባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መ/ቤት ባወጣው የአብያተ-መንግሥታቱ አስጎብኚነት ስራ ለመቀጠል ወሰኑ።
በጊዜው ለሥራ ቅጥሩ እንደዋነኛ መስፈርት የተወሰደው ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ውጪ ተጨማሪ ቋንቋን የሚችል ሰው ይፈልጉ ነበረና ከቡልጋሪያ ባገኙት የቋንቋ ትምህርት እውቀት መስፈርቱን በማሟላታቸው ቀዳሚ ሆነው ሊመረጡ ችለዋል። እ.ኢ.አ በ1982 የጎንደር አብያተ መንግስታት አስጎብኚ ሆነውም ተቀጠሩ። ስራ የጀመሩበትን የመጀመሪያ ወራቶችን ልዩ የሚያደርጋቸው ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያም ጎንደር ተመርጣ በአይነቱ ትልቅና ታሪካዊ የሆነ “የዓለም አቀፍ ቅርሶችን የመንከባከብና መጠበቅ መርህ” በሚል አጀንዳ ዓለም-አቀፍ ጉባኤ ለመምራት የፈረንሳይ ዜግነት ያላቸው የወቅቱ የዩኔስኮ ጀነራል ሴክሬታሪ የነበሩት ሚስተር ፌዴሪኮ ማዮር በቁጥር በርካታ የውጭ ዜጎች ጭምር የታደሙበት በጎንደር ከተማ ተገኝተው ነበረና ደማቅ የስራ ጅማሮ እንዳደረገላቸው ይገልፃሉ።
ትውውቅ ከቱሪዝም ጋር
አቶ ጌትነት ይግዛው በተለያዩ ጊዜያት ከቱሪዝም፣ ከቅርስ ጥበቃና ከታሪክ ገላጭነት ዘርፍ ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎችን በመስራት በፊልም ጭምር የተደገፈ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። በተለይ በአገር ውስጥ ከተሰሩት ታዋቂው “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀዳማዊ ስልጣኔ” ዶክሜንተሪ ፊልም ተጠቃሽ ነው ፣ በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን፣ በፋና ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በሌሎች የግል ሚዲያዎች በርካታ የዶክመንተሪ ሥራዎችን ለትውልድ ያበረከቱ ሲሆን እንዲሁም ከስመ ገናና ታላላቅ የውጭ ሚዲያዎች ጋር(ቢቢሲ፣ ዶቼቬሌ፣ ቪኦኤ እና ዲኤስቲቪ...)
የዶኪሜንተሪ
እና የጉዞ ምክር ፊልሞችን አብሮ ለመስራት በቅተዋል።
በአስጎብኝነት ዘመናቸው የውጭና የአገር ውስጥ መሪዎችን፣ ታላላቅ ክብር ያላቸውን ሰዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና የጉዞ ዘጋቢዎችን፣አንባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን በማስጎብኘት አድናቆትን አትርፈዋል፡፡
ማንኛውም ስራ እውቀትን መሰረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባዋል ብለው የሚያምኑት አቶ ጌትነት ለዚህም ሲሉ ለሚሰሩት ስራ እንዲያግዛቸው ቀጥተኛ የትምህርት ዘርፍን መርጠው ተምረዋል። አዲስ አበባ ከቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የመጀመሪያው የቱሪስት አስጎብኝነት ሥልጠና በመውሰድ ለሁለት ጊዜ የአስጎብኝነት ሰርትፍኬት አግኝተዋል፡፡ ለንደን አገር በሚገኘው ካምብሪጅ ቱቶሪያል ኮሌጅ በቱሪዝምና ትራቭል ኤጀንት ማኔጅመንት ሥልጠና በብር ዲፕሎማ ደረጃ የተቀበሉ ሲሆን ከጎንደር ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ሰልጣኝ በመሆን በቱሪዝም አስተዳደር የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያዙ፡፡ የትምህርቱ ትግል በዚህ ሳያቆም በመቀጠል በዛው የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ባገኙበት በጎንደር ዩንቨርስቲ የመጀመሪያው ባች በመሆን በቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደር ሁለተኛ ድግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ በሥራ ዘመናቸው በተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር ዓቀፍ አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ በቁጥር በርካታ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል ።
የጎንደር ፋሲለደስ ቤተመንግስታት አስጎብኚ በመሆን የተጀመረው ሥራ ጊዜውንና እድገቱን ጠብቆ የዓለም አቀፍ ቅርሱን በአስተዳዳሪነትና በዩኔስኮ የቅርሱ ተጠሪ እስከመሆን የዘለቀ ሀላፊነትን ተቀብለው እየሰሩ ቆይተዋል። በአገራችን የሚገኙት የዓለም አቀፍ ቅርሶች አብዛኛዎቹ በ1970ዎች የተመዘገቡት የአስተዳደር እቅድና ዓለም-አቀፍ ዶሴ የሌላቸው በመሆኑ የዓለም አቀፉ ቅርስ ድርጅት ዩኔስኮ አፍሪካ 2009 በሚል ኬኒያ ናይሮቢ ላይ በተደረገው ጉባኤ በመሳተፍ ሁሉም ቅርሶች የተሟላ ዶሴ እንዲኖራቸው ሥራ ከፍተኛውን ቦታ በመያዝ የማይናቅ አበርክቶ አድርገዋል፡፡ የማኔጅመንት ፕላን ተዘጋጅቶላቸው የተሟሉ የዓለም አቀፍ ቅርስ እንዲሆኑ ከሰሩት መካከል አቶ ጌትነት ይግዛው በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ጥምቀት ዩኔስኮ ላይ እንዲመዘገብ የጣሩ
በቱሪዝም ዘርፍ ሀገሪቱ ተገቢ ጥቅምን እንድታገኝ በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል ሲከበር በካርኒቫል (በጎዳና ላይ ትርኢት) ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን እንዲደምቅና ከሀይማኖታዊው አቋም ባልተዛነፈ መልኩ ባህላዊው ስርዓት ተጠብቆ እንዲከበር ብዙ ሰርተዋል፡፡ በብዙ ውጣ ውረድም ሀሳቡ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በውጤቱም “ጥምቀትን በጎንደር መታደም ማለት መታደል ነው፡፡ ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን” በሚለው መሪ ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በጎንደር ጥምቀት ሲታደም ዘለግ ያለ ቆይታ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ በመላው ዓለም የሚኖር የሰው ዘር በቀጥታ በቴሌቪዥን መስኮት እንዲከታተለውም ተደርጓል። በውጤቱም በዓለ- ጥምቀት ሀገርን የሚያኮራውና የዓለም አቀፍ ቅርስ እንዲሆንልን ተፅዕኖ ለማሳደር እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ተግባር ሆኖ ይቆጠራል። ከሁሉም የቅርስና ቱሪዝም ዘርፉ ሰራተኞች ጋር በማበር ጥምቀት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ አቶ ጌትነት ይግዛውም እንደ ቱሪዝምና ቅርስ ከፍተኛ ባለሙያ ሰው የድርሻቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል።
የጎንደር ቤተመንግስት አስተዳዳሪ በነበሩ ወቅት ከጥገና ፣ጥበቃ እና እድሳት ስራ ጋር በተያያዘ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለአሥራ ዘጠኝ ዓመት መንግስትና ህጉ የሚፈቅድላቸውን የዓመት እረፍትና የእረፍት ጊዜአቸውን በመሰዋት ብዙ መድከማቸው ይነገርላቸዋል። ቅርሱ ከቀደመው ይዘቱ እንዳይዛነፍም በጥንቃቄ ለመስራት መትጋት ነበረባቸውና ይህንም አድርገውታል።
የፈረሳይዋ ታሪካዊ ከተማ ከቨንሰንት ከተማ ጋር ጎንደርን እህታማች ከተማ ለማድረግ ለስምንት ወራት የደከሙበት ፕሮጀክት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ፕሮጀክቱን እውን በማድረግ የከተማዋ ቅርሶችን ለማስጠበቅና በመጠገን ለቱሪስት እይታ ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል ድጋፍን ለማስገኘት ሰርተዋል፡፡ ተሳክቶላቸውማል።
በዚህም
መሰረት
የፀደቀው
ፕሮጀክትም
በጎንደር
ከተማ
ፋይናንስ
በኩል
12 ሚሊየን
ብር የገንዘብ ፈንድ ገቢ እንዲደረግና የራስ ግንብ ጥገናና ልማት እንዲከናወን የደከሙበት ስራቸው ምስክር ነው።
ከቤተ-መንግስቱ ሁለት ኮሎሜትር እርቀት ላይ የሚገኘው የፋሲል መዋኛ ገንዳን ለማስጠገን ከኖርዌይ መንግሥት ድጋፍ 6.6 ሚሊየን ብር በላይ የተገኘው በአቶ ጌትነት ይግዛው የግል ጥረት ነበር፡፡ ሆኖም ይሄንን እና መሰል ጠቃሚ እድሎችን እንደ አይናቸው ብሌን ለሚሳሱለት ዓለም አቀፍ ቅርስም ሆነ ለጎንደር ከተማ ጥቅም ሲሉ በብዙ ድካም ሃብት ቢያመጡም በውስጥ የአሰራር ችግር እና የተሳሰረ ሙስና ምክንያት
በእጃቸው
የነበሩ
ብዙ እድሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርገዋል፡፡ አልፎም በተቀናጀ መልኩ የግድያ ሙከራ እስኪደረግባቸው ዋጋ የከፈሉበት ስራ እንደነበረ የሚዘነጋ አደለም።
በ1982 መጨረሻ ላይ የነበራቸውን ታሪካዊ የሥራ ገጠመኝ እንዲህ ያስታውሱናል።
''ፊልም
ለመስራት
የተገኙ
የእንግሊዙ
ታዋቂ
ቴሌቪዥን
(ቢቢሲ)
የዶኪሜንተሬ
ፊልም
ሥራ ባልደረቦች የከተማችን የቱሪስት ጉብኝት ሥርዓት አካል የሆነውን የቅዳሜ ገበያን ለማስጓብኘት በጊዜው የአካባቢው የጋሪ መጓጓዣ በመጠቀም የፊልም ባለሞያዎችን በምወስድበት ወቅት በአጋጣሚ የአንዱ ጋሪ ፈረስ ጀርባው የቆሰለ ስለነበር በገጣባ ፈረስ ላይ ተቀምጣ የምትጓዘው አንዷ ባለሙያ ጩኸቷን ለቀቀችው፡፡ በጣም እንዳዘነችብኝ ነገረችኝ፡፡ እኔም ምክንያቱ ግልፅ ስለአልነበረልኝ
ምን እንደሆነች ስጠይቃት ለእንሰሳ ይቆረቆሩ የነበሩ እንደ ፃድቁ ዮሀንስ አይነት ንጉሶች ነበሩ ብለህ ተርከህልን ስታበቃ እንዴት ጀርባው በቆሰለ ገጣባ ፈረስ ላይ ትጭነናለህ በማለት ጠየቀችኝ፡፡ እኔ ሌላኛው ጋሪ ላይ ነበርኩና አላስተዋልኩም ነበር በዚህ ክስተት ያዘነው ቡድን ወደ አገሩ ተመልሶ ጎንደርን በሁለት አይነት ክስ በለንደን ከተማ ከሰሱ፡፡
አንደኛው በገጣባ ፈረስ ላይ መጫን ሰብአዊነት የጎደለው ነው በማለት እና ሁለተኛው ክስ ደግሞ በፋሲል አውደግቢ በሚገኘው የአንበሳ ማጎሪያ ይኖር የነበረን የአራዊት ሁሉ ንጉሥ አንበሳን፣ በቀን 5 ኪሎ ሜትር መሯሯጥ የተፈጥሮ ግዴታ ያለበትን እንስሳ የተፈጥሮ ስጦታውን በመገደብ በትንሽ ሳጥን ውስጥ በማስቀመጥ በሚል ክስ ተመሰረተብን፡፡ እንደሚታወቀው እንግሊዞች የእንሰሳ መብት ተቆርቋሪና ተሟጋቾች ናቸውና የአያያዝ ችግር እንዳለብን ከተጠይቀንበት በኋላ በሁለተኛ ዓመቱ በባህርዳር ከተማ ባለጋማ ከብት እንስሳ መብት ተሟጋች ቢሮ ለመክፈት ችለዋል። በአሁኑ ጊዜም በአገራችን መዲና አዲስ አበባ ተጨማሪ ቢሮ በመክፈት ዓመታዊ የባለጋማ እንስሳት መታሰቢያ በዓል ለማክበር የቻሉ ሲሆን ይሄንን ታሪካዊ ገጠመኝ አልረሳውም'' ብለውናል።
ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ከቢቢሲ ሚድያ ጋር በነበረ የስራ ቆይታ ደግሞ ለ30 ደቂቃ የሚቆይ ከጫፍ ጫፍ (Pole to Pole) ሲሪየስ ፊልም ጌትነት ይግዛው የማስጎብኘት ስራቸውንና ተሳትፏቸውን ተወጥተው ባገኙት ገንዘብ በጎንደር ከተማ በግዜው የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ መኪና የገዛ ተብሎ የተደነቀበትና የላቡ ዋጋ የሆነችው መኪናው እስከአሁንም ትታወሳለች።
አቶ ጌትነት ይግዛው ከጎንደር ቤተመንግስት አስተዳዳሪነት በኋላ በቤተሰብ ምክኒያት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመጀመሪያ በባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር የቱሪስት ፋሲሊቲ ከፍተኛ ባለሙያና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ፣ በኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን፣ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም እና በኢትዮጵያ በቱሪዝም ድርጅት በህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርነት ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በቱሪዝም ኢትዮጵያ የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ ጌትነት ባለትዳር እና የልጆች አባት ናቸው።
መዝጊያ ….. ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንን አቋም የሚያንጸባርቅ የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት ያመኑበት ነው፡፡
አቶ ጌትነት ይግዛው ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በተባለው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ አተኩረው በተለይ ቱሪዝምን በሚድያ በማስተዋወቅ የበኩላቸውን የተወጡ ታላቅ ባለሙያ ናቸው፡፡ ይህን ሙያቸውን ከልብ እንደሚወዱት ታሪካቸው ይናገራል፡፡ ልምዳቸው ደግሞ በዘመናዊ የቱሪዝም ትምህርት የታገዘ ስለሆነ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ሚና ማበርከታቸው አልቀረም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን ባህላዊ ገጽታ ብሎም እሴት ለቀሪው የአለም ማህበረሰብ በማሳወቅ የአቶ ጌትነት አስተዋጽኦ ታሪክ ሊመዘግበው ይገባል፡፡ እንደ አቶ ጌትነት አይነት ሰዎች በተሰማሩበት ሙያ አንድ አሻራ ለማኖር ሌት ተቀን ይለፋሉ፡፡ ሙያውን በትጋት ለማሳደግ ላይ ታች ይላሉ፡፡ ነገር ግን የሄዱበት መንገድ ወይም አጭር ግለ-ታሪክ ተጽፎ አይገኝም፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች የአቶ ጌትነት ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ አንድ የሚያስተምረው ነገር አለ ብለን እናምናለን፡፡ ሀገር ተረካቢው ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ የቀድሞ ታሪክ ማወቅ ከፈለገና ባህል እሴቶችን ማብላላት ከመረጠ የእነ አቶ ጌትነት ሙከራዎች መነሻ ይሆኑታል፡፡ አቶ ጌትነት ይግዛው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቱሪዝም ዘርፍ የሰሩ ናቸው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ምንጊዜም የማትዘነጋቸው ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ አቶ ጌትነትን እናከብራቸዋለን፡፡ ስለምናከብራቸውም ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንደነዋል፡፡
/ ይህ የዊኪፒዲያ ግለ-ታሪክ የቃለ-መጠይቅና የቅንብር ስራ የተከናወነው በጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ሲሆን ዛሬ ጥቅምት 3
2014 አ.ም በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ይህ ጽሁፍ በየጊዜው አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት ይወጣል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ