11.  ጌታቸው   ሀይለማሪያም -GETACHEW HAILEMARIAM                   

 

                     ጌታቸው  ኃይለማሪያም -ታላቁ ጋዜጠኛ

 

ዜና ፋይልን 1979 የፈጠረ፡፡ ጎበዝ አሰልጣኝ፡፡ ጥሩ የዘጋቢ ፊልም ባለሙያ ነው፡፡  የቲቪ ሰብእና ያዳበረ ታላቅ ሰው፡፡ መጽሀፍን ያነባል፡፡ ድምጹ ይማርካል፡፡ 24 አመት በላይ በሙያው አገለገለ፡፡ 49 አመቱ ህይወቱ አለፈ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሰርተው ያለፉ ሰዎችን ያከብራል፡፡ ታሪካቸውን ለአለም ያቀርባል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያም  ታሪኩ ሲቀርብ ይህን ይመስላል፡፡

 

                   የጅማው ጌታቸው

 

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያም 1938 . ነበር የተወለደው፡፡ አባቱ አቶ ኃይለማሪያም ባህሩ  ሲባሉ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ በላይነሽ ታደሰ ናቸው፡፡ የተወለደውም በከፋ ክፍለ- ሀገር  ቦንጋ ከተማ ነው፡፡ ጌታቸው ገና በልጅነቱ በጅማ መድሀኒአለም መዘምራን በመሆን ያገለግል ነበር፡፡

 

የአንደኛ እና 2 ደረጃ ትምህርቱን በጅማ ሚያዝያ 27 ተማሪ ቤት ተከታትሏል፡፡ አብሮ አደጉ የሆኑት የቀድሞ ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር እንደሚናገሩት ጌታቸው በሚያዝያ 27 ይማር በነበረበት ጊዜ ‹‹የሚያዝያ ፋና›› የተሰኘ ጋዜጣ ከአቶ ተክሉ ጋር  አብረው ያዘጋጁ ነበር፡፡ አቶ ተክሉ ታቦር በሚድያው ዘርፍ በአንጋፋነት ከሚጠቀሱት መካከል ነበሩ፡፡ ጌታቸው ኃይለማሪያም   በመቀጠልም ፤መምህር ለመሆን የሚሰጠውን ኮርስ ከወሰደ በኋላ ኮርሱን ሲያጠናቅቅ በዳውሮ ዞን በመምህርነት ተመድቦ ሄደ ፡፡ እዚያም ለአንድ አመት ያህል ካስተማረ በኋላ 1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ብስራተ- ወንጌል የሬድዮ ጣቢያን ተቀላቀለ፡፡ በዚህም የሬድዮ ጣቢያ 5 አመታት ማገልገሉን የቀድሞ ባልደረባው አቶ ዘሪሁን ብርሀኔ ነግረውናል፡፡ 1962 ግድምም ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተዛወረ፡፡

 

      በወጉ የተሞረደ ድምጽ

 

ጌታቸው፣ የኢቲቪ ባልደረባ ከሆነ በኋላ በዚያ ሞገስ ባለው ድምጹና የቲቪ ማንነት በተላበሰ ሰብዕናው በጊዜው የነበሩ ተመልካቾችን አስደምሟል፡፡ በዚህ ልዩ ክህሎቱም ብዙዎች ይደነቁ ነበር፡፡ ጌታቸውም የሚወደውን ሙያው ያገኘ በመሆኑ ደስ ብሎት አቅሙን ሳይቆጥብ ይሰራ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ዜና ሲነበብ የዜና አንባቢዎች ከዳይሬክተሮች ጋር የሚግባቡበትን የቴክኖሎጂ ስልት በመፍጠሩ ጌታቸው ዛሬ ድረስ ምስጋና ይቸረዋል፡፡ እንዳሁኑ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር በስፋት ባልነበረበት ጊዜ እንደ ጌታቸው አይነት ድንቅ አእምሮ ያለው ሰው የግድ ያስፈልግ ነበር፡፡

 

1960ዎቹና 1970ዎቹ ወቅታዊ እና አልፎ አልፎም ዘጋቢ ፊልሞችን በዚያ አስደማሚ ድምጹ ሲያነብ የማይደሰት ተመልካች አልነበረም፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ያነጋገራቸው የቀድሞ የቲቪ ተመልካቾች እንደሚናገሩት ጌታቸው በብዙ ተመልካቾች ዘንድ የሚታወቅና ገና ስሙ ሲጠራ ደግሞ ዛሬ ምን ሊያነብ ይሆን? የሚል ጥያቄ እንዲፈጠር የሚያደርግ ጋዜጠኛ ነበር ብለዋል፡፡














 

       በፕሮፌሽናሊዝም የተቃኘ ፍልስፍና

 

ይህ የዊኪፒዲያ ታሪክ ሲሰራ ባህር ማዶ ሆነው ቃለ-መጠይቅ የሰጡት አቶ ተክሉ ታቦር ጌታቸውን ገና ከልጅነት ያውቁት ስለነበር በየጊዜው ያሳየውን ጥረት በቅርበት የመከታተል እድል ነበራቸው፡፡ በአቶ ተክሉ አነጋገር ጌታቸው በፕሮፌሽናሊዝም የተቃኘ ፍልስፍናን ያራምዳል፡፡ ታዲያ ጌታቸው የባለሙያነትን እሳቤ ሲያራምድ ራሱ ባለሙያው ቀድሞ መገኘትና ማወቅ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ይህን እምነቱንም ተግባራዊ ለማድረግ ጥልቅ ንባብ ያካሂዳል፡፡ አንድ ሰው ጌታቸውን ከውጭ ሀገር ምን ስጦታ ላምጣልህ? ብሎ ከጠየቀው መጽሀፍ ማለቱ አይቀርም፡፡ ራሱም ባህር ማዶ በሄደበት ጊዜ በርካታ መጽሀፍትን ሸምቶ ሀገር ቤት ይገባል፡፡ ይህ ጥልቅ የንባብ ህይወቱ ነገሮችን በምሁራዊ እይታ እንዲመለከትና በጋዜጠኝነት ሙያውም ላይ ከፍ ወዳለ ስፍራ እንዲሄድ አስችሎታል፡፡

 

ጌታቸው ሀይለማሪያም ፤በቀና መንገድ ለቀረበው ሰው ሙያውን አንዳችም ሳይቆጥብ ለማስተማር ወደ ኋላ አይልም፡፡ነገር ግን አንዳንዶች በትእቢትና በኩራት ከቀረቡት እነርሱን ለመቀበል ይቸግረዋል፡፡ አይቶ እንዳላየ ማለፍን ይመርጣል፡፡

 

        አዛሪያ ኪሮስና  ጌታቸው

 

ጌታቸው ቲቪ ይሰራ በነበረበት ጊዜ አየር ላይ ካዋላቸው ፕሮግራሞች አንዱ ከጋዜጠኛ አዛሪያ ኪሮስ ጋር አዘጋጅቶ አየር ላይ ያዋለው ዘጋቢ ፊልም አይረሴ ነበር፡፡ዘጋቢ ፊልሙ በቪየትናም ጦርነት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ይህ 20-25 ደቂቃ ይወስድ የነበረ ዶክመንተሪ ከለንደን የሚላክ ነበር፡፡ ጌታቸው ኃይለማሪያምና አዛሪያ ኪሮስ ታዲያ ይህን ዶክመንተሪ ለተመልካች በሚመጥን መልኩ አየር ላይ ሲያውሉት ብዙዎች ልባዊ አድናቆታቸውን ሰጥተዋቸው ነበር፡፡

 

                   አለም እንዴት ሰነበተች?

 

ጌታቸው ቲቪ በነበረበት ጊዜ ያዘጋጃቸው ከነበሩ ፕሮግራሞች አንዱ ዓለም እንዴት ሰነበተች? የሚለው ይጠቀሳል፡፡ይህ ተተርጎሞ የሚሰራ እና የውጭ ሀገር ጉዳዮች የሚቀርቡበት ዝግጅት በጌታቸው ሲሰናዳ ሰው ሰው የሚል ሆኖ አየር ላይ ይውላል፡፡ ጌታቸው ዓለም እንዴት ሰነበተችን ሲያቀርብ  ቦታው የሄደ እስኪመስል ድረስ ምስል የመከሰት አቅም ነበረው፡፡ በተጨማሪም አልፎ አልፎም ቢሆን ከኢዜአ( ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ) የሚላኩ በወጉ ያልተቃ የውጭ ዜናዎችን መልክ እንዲይዙ በማድረግ ለዓለም እንዴት ሰነበተች ብቁ ያደርጋቸው ነበር፡፡ በዚህም የጌታቸውን አርትኦት የማድረግ ልዩ ክህሎት ማወቅ እንችላለን፡፡ ስለዓለም እንዴት ሰነበተች  ሲነሳ ትዝታውን ያወጋን  በአሁኑ ሰአት ስዊድን ሀገር የሚገኘው ዳንኤል አያሌው፡፡ ዳንኤል በኢትዮጵያ ሬድዮ የቅዳሜ መዝናኛ ላይ 1982-1993 ያገለገለ ሲሆን ጌታቸውን በዓለም እንዴት ሰነበተች? ያስታውሰዋል፡፡ ዳንኤል እንደሚያስታውሰው፣ ያኔ ዓለም እንዴት ሰነበተች? ሲቀርብ ዓለም እንዴት ሰነበተች እስኪእንጠይቃት በተሰኘው የአባባ ተስፋዬ ሙዚቃ  ይጀምር ነበር፡፡ ዳንኤል የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቆ ኢትዮጵያ ሬድዮ ሲመደብ 6 ወር ስልጠና ከሰጡት አንዱ ጌታቸው ኀይለማሪያም ነበር፡፡  ዳንኤል ያኔ ይሰጥ የነበረው ስልጠና መሰረታዊ እንደነበር ዳንኤል ያስታውሳል፡፡ በተለይ ጋሽ ጌታቸው ጥሩ አንባቢ እንሆን ዘንድ ፑሽ አፕ  በሚገባ ያሰራን ነበር ሲል የጌታቸውን ልዩ የማሰልጠን ብቃት የጠቀመው መሆኑን ይናገራል፡፡

 

           ተጨማሪ እውነታዎች ስለጌታቸው

 

የጌታቸው 4 ታናሽ እህቱ ወይዘሮ ውዴ ኃይለማሪያም  ስለ ጌታቸው ተናገሪ ስትባል እንባ ቀድሞ ይተናነቃታል፡፡ በተለይ ወንድሙዋ ገና በወጣትነቱ ወንድም እህቶቹን ለመርዳት በሚል ቀን ከሌት ሲሰራ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ሰኞ ሀምሌ 19 2013 ከዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ጋር ቃለ-መጠይቅ ያደረገችው ወይዘሮ ውዴ ወንድሟ 1987 መስከረም 7 ያረፈ እለት አጠገቡ ነበረች፡፡ እናም የጌታቸው ምስል አሁን ራሱ ፊቴ ድቅን ይላል በጣም ነው የምፈራው ይገስጸኝ ነበር ስትል እንደ ታላቅ ወንድም ጋሻ መሆኑን ትመሰክራለች፡፡ ጌታቸው በህይወት በነበረበት ጊዜ ሬንጅ ሮቨር መኪና ይነዳ ነበር፡፡ ወይዘሮ ውዴ ጌታቸውን በተመለከተ ወደ 11 ዶክመንቶችን የሰጠችን ሲሆን በተለይ ሞገድ ጋዜጣ 1986 አመተምህረት ስለጌታቸው በውስጥ ገጹ ያወጣ ሲሆን አእምሮ ጋዜጣ ደግሞ በመስከረም 14 1987 እትሙ የጌታቸውን የህልፈት ዜና ዘግቦት ነበር፡፡ በወቅቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን  ለጌታቸው የህልፈት ዜና ሽፋን ያልሰጡት ሲሆን ከዚያ በኋላም ለረጅም አመታት ስለ ጌታቸው ብዙም አይነገርም ነበር፡፡ ጌታቸው ኃይለማሪያም ለክልል የኢዜአ ሪፖርተሮችም ቀን ያወጣ ሰው ሲሆን በተለይ ከክልል ሆነው ዘገባቸውን ከእነ ስማቸው እንዲያቀርቡ ያደረገ ባለውለታ ነው፡፡ ቲቪም ላይ ቢሆን ጋዜጠኞች ካሉበት ሆነው ለምሳሌ ዘጋቢው ጌታቸው አሰፋ ከሆነ ጌታቸው አሰፋ ነኝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንዲቀርብ የአሰራር ማሻሻያውን ያደረገው ጌታቸው ነው፡፡

 

   የሙያ

 

           አባት -ጌታቸው

 

ጌታቸውኃ ይለማሪያም አብዛኛውን የሙያ ቆይታውን ያደረገው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው፡፡ በትንሹ 15 አመት ያህል በኢቲቪ አገልግሏል፡፡ ቲቪ በሰራባቸው ጊዜያትም በርካታ ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡ እንደ አለቃ ብቻ ሳይሆን እንደ ባልንጀር መጋቢ/ ሜንተር/ ስመ-ጥሮች ወደ ሙያው እንዲመጡ አድርጓል፡፡

 

ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን 1976 የተቀላቀለችው ሚሊዮን ተረፈ ጌታቸው ኃይለማሪያምን እንደ አለቃዋ ብቻ ሳይሆን እንደ መምህሯ ትመለከተዋለች፡፡ ሚሊዮን የጌታቸውን የፕሮዳክሽን ችሎታ ታደንቃለች፡፡ ጌታቸው አንድ ፕሮዳክሽን ሲሰራ ልብ ብላ የምታየው ሚሊዮን እንደ ጌታቸው አይነት ክህሎት ያለው ባለሙያ በጊዜው በጣት የሚቆጠር ነበር ስትል የጌታቸውን ሙያዊ ልህቀት ከፍ ያለ እንደነበር ትናገራለች፡፡

 

ሚሊዮን፣ ቲቪ በሰራችባቸው ዘመናት ጌታቸው የሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ድርጊቶች የሚያስተምሩ ነበሩ ትላለች፡፡ ጌታቸው ዜና ለማንበብ ወደ ስቱዲዮ ሲገባ ተመልካቹን ያስባል፡፡ በተቻለ አቅም ስርዓቱን በልክ አድርጎ አቀማመጡን አስተካክሎ ወደ ተመልካች ይቀርባል፡፡ ከዚህ በላይ ተመልካችን ማክበር ከወደየትም አይገኝ፡፡ ጌታቸው ይህን መልካም ልማድ ሲከውን ከስር ያሉት አንዳች ትምህርት ያገኛሉ፡፡ ከዚህ በላይ የእውቀት አባት ከወደየት ሊገኝ ይሆን? ለዚያውም ሰርቶ የሚያሰራ አለቃ፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም እንደ አንዳንድ አለቆች የሚኮፈስ አልነበረም፡፡ ቀርቦ ለማስረዳት የሚቀል ሰብእና ነበረው፡፡ ሚሊዮን ይህን መልካም ሰብእናውን ዘልቃ ያየች በመሆኑ ታናናሾችን ለማበረታታት ወደ ኋላ የማይል ነው ስትል እንደ ጌታቸው አይነት የሚድያ ሰዎች ዛሬም ያስፈልጋሉ ስትል ትናገራለች፡፡

 

ጋዜጠኛ ሀይለልኡል ይልማ 1968 . በዜና ክፍል ባልደረባነት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ሲቀላቀል ነበር ጌታቸው ኃይለማሪያምን የመተዋወቅ እድል የነበረው፡፡ጋዜጠኛ ሀይለልኡል የጌታቸው ኃይለማሪያምን ልዩ ችሎታ በተለይ ቲቪ በሚገባ በሁሉም ሰው ዘንድ የተመሰከረ ነበር ይላል፡፡ እንደ ጌታቸው ኃይለማሪያምና ልኡልሰገድ ኩምሳን የመሰሉ ሰዎችን ዳግም ማግኘት አዳጋች ነው ሲል ሀይለልኡል ይናገራል፡፡

 

የመንግስቱ ኃይለማሪያምን ትዝታ በመጽሀፍ ያወጣችው ደራሲ ገነት አየለ 1977 ኮንቲኒቲ አናውንሰር ወይም አስተዋዋቂ ሆና በሰራችባቸው አመታት የቲቪ ሰብእናን በሚገባ እንድታውቅ ስልጠና የሰጣት ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበር፡፡ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ቲቪ ላይ ስትወጣ ተፈራ አስማረ እና ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበሩ ጥሩ ብርታት የሰጡዋት፡፡ጌታቸው አዲስ ነገር እንድንፈጥር ጥርትና የተስተካከለ ቋንቋ እንድንናገር ያደርግ ነበር ትላለች ገነት፡፡ የጋዜጠኝነትን ሀሁ የተማርኩት ከጌታቸው ነበር የምትለው ገነት አየለ ያኔ የወሰደችው ስልጠና በሚድያ ስራ ለመቀጠል አይኗን እንደከፈተላት ታስረዳለች፡፡ ገነት ትዝ እንደሚላት በዜና ሰአት ጌታቸው ኃይለማሪያም ብዙውን ጊዜ ስቱዲዮ ይቀመጥ ነበር፡፡ ስህተት ካየ ተመልክቶ ከመናገር ወደ ኋላ አይልም፡፡ እንደ ጌታቸው አይነት ሰዎች ለኢትዮጵያ ሚድያ ትልቅ ውለታ የዋሉ ናቸው የምትለው ገነት ታሪኩ ለአዲሱ ትውልድ መቅረቡ አስተማሪ ነገር አለው ስትልም ሀሳቧን ትሰነዝራለች፡፡

 

ጸጋ ቁምላቸው፣ 1970ዎቹ አንስቶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በስፖርት ክፍል ያገለገለ ሲሆን ጌታቸው ሀይለማሪያም ጋር 6 አመት በላይ ለሚሆን ጊዜ አብሮ ሰርቷል፡፡ በተለይ የመጀመሪያው የስፖርት የቲቪ ጋዜጠኛ የነበረው ሰለሞን ተሰማ የጌታቸው ኃይለማሪያም የቅርብ ወዳጅ ነበር፡፡ ጸጋ እንደሚያስታውሰው፣ ጌታቸው ኃይለማሪያም ህዝብ በጉጉት የሚጠብቃቸውን የስፖርት መሰናዶዎች ቀድሞ ሲያስተዋውቅ ልዩ ክህሎት ነበረው፡፡ በተለይ ደግሞ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከስፖርት ጋዜጠኞች ጋር ያደርጉት የነበረውን በጉጉት የሚጠበቅ መሰናዶ ጌታቸው ሲያስተዋውቀው ልዩ መልክ ይሰጠው ነበር፡፡ ጸጋ ቁምላቸው፣ ጌታቸው ኃይለማሪያም ከለገሰው ምክር የማይረሳው የቲቪ ጋዜጠኛ በየጊዜው ስለሚታይ የራሱን ክብርና ሰብእና መጠበቅ አለበት ሲል መክሮት ነበር፡፡ ይህም ሲባል ሰው ሊጋብዛችሁ እና መጠቀሚያ ሊያደርጋችሁ ስለሚችል ለሙያው ትልቅ ክብር መስጠት አለባችሁ ነው የሚለው ምክሩ ሲጠቃለል፡፡

 

1974 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሪፖርተርነት የተቀጠረው ጌታቸው አሰፋ ሞክሼው አለቃውን ጌታቸው ሀይለማሪያምን በፍጹም አይዘነጋውም፡፡ ስራ ያለማመደኝ ባለውለታዬ ነው፤ ነጥሬ እንድወጣም መልካሙን የተመኘልኝ ነው ሲልም 30 አመት ወደ ኋላ ተጉዞ ስለጌታቸው ያወራል፡፡ሊቀመንበር መንግስቱ በሚገኙባቸው ቦታዎች ለዘገባ አምኖብኝ ይልከኝ የነበረው ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበር ሲል ትዝታውን አውግቶናል፡፡ጌታቸው የቲቪን ዜና ክፍል ይመራ በነበረበት ጊዜ በክፍሉ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል ገነት ምትኬ፤ ሀብታሙ በቀለ፣ዬ በላቸው፣ሀይለልኡል ይልማ ፣ህሊና ተፈራ አስቻለው ደምሴ ሚሊዮን ተፈራ አስፋው ኢዶሳ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ ታዲያ ጌታቸው ሁሉንም እንደአቅማቸው ወደ ስራ በማሰማራት ኃፊነቱን በብቃት ይወጣ ነበር፡፡ ጌታቸው አሰፋ እንደሚናገረው ቀደም ሲል ስማቸው የተነሳ የዜና ክፍል አባላት የጌታቸው ኃለማሪያም ግርፎች ወይም የእርሱ አዎንታዊ ተጽእኖ ያደረባቸው ነበሩ፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም፣ በየሳምንቱ ቅዳሜ የክፍሉን ልጆች ይሰበስብ ነበር፡፡ እናም ስለ አንድ ሰው ወይም ሪፖርተር መስጠት ያለበትን አስተያየት ያለ አንዳች ማመንታት ሀሳቡን በነጻነት ይሰጣል፡፡ ማደግ ሊገኝ የሚችለው ሀሳብን በመቀበል ነው ብሎም ያምን ስለነበር የሚሰሩ ዜናዎችን በንቃት ይከታተል ነበር፡፡

 

1969 ግድም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና ክፍልን የተቀላቀለው ሳሙኤል ማሞ የኢቲቪ ትዝታው ብዙ ነው፡፡ በኢቲቪ የማይረሱ 5 አመታትን ያሳለፈው ሳሙኤል ዛሬ በግል ንግድ ስራ ላይ ቢሰማራም 5ቱን አመታት እንደወርቃማ ዘመናት ይቆጥራቸዋል፡፡ ታዲያ በእነዚህ ወርቃማ ዘመናት አስደናቂ ክህሎት የነበረውን ጌታቸው ኃይለማሪያምን በፍጹም አልረሳውም ሲል ሳሙኤል 43 አመት ወደ ኋላ ይጓዛል፡፡ ሳሙኤል በአንድ ወቅት አንድ ዜና ትልቅ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ዜናውን ተርጉሞ እንዲነበብ ያደረገው ደግሞ ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበር፡፡ በጊዜው ሳሙኤል ዜናውን ሲያነብ የአሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቼስተር ክሮገር አዲስ አበባ ሊገቡ ነው ብሎ አነበበ፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያ ከምእራባዊያን ጋር ግንኙነቷ ብዙም አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ታዲያ ገና ስልጣን ላይ ከወጣ 1 አመት ያላስቆጠረው ደርግ ተደናግጦ እንዴት ይህ አይነት ዜና ሊተላለፍ ቻለ ?ሲል የቲቪ ሰዎችን አስጠራ፡፡ በጊዜው የጣቢያው መምሪያ ሃላፊ የነበረው አቶ አዛሪያ ኪሮስም ተጠራ፡፡ ሳሙኤል እንደሚያስታውሰው ጌታቸው ኃይለማሪያም 15 ቀን ደሞዙን ሲቀጣ ሳሙኤል ደግሞ 15 ቀናት ስክሪን ላይ እንዳይቀርብ ተደረገ፡፡ ይህን ትዝታ ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ያስረዳው የድሮ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ማሞ ጌታቸው ኃይለማሪያም ጋዜጠኝነትን ከልቤ እንድወደው ያደረገኝ ሰው ነው ብሏል፡፡

 

ዜና ፋይል

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እስከ 1979 . ከሰራ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ እንዲዛወር ተደረገ፡፡ ይህም ሆነ ተብሎ ጌታቸውን ዝቅ ለማድረግ/ዲሞ/ ታስቦ ነበር፡፡ ጌታቸው ግን ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ‹‹ዜና ፋይል›› የተሰኘውን አዲስ ፎርማት ለመቅረጽ ቻለ፡፡ለጀርመን ድምጽ የሚሰራው ነጋሽ መሀመድ፣ ጌታቸው በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያኖረ ታላቅ ባለውለታ ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ነጋሽ የጌታቸውን ችሎታ አብሮት የሰራ በመሆኑ ለመመስከር ይችላል፡፡ የጌታቸው የአሰለጣጠን ሂደት ብዙ አስተምሮኛል ሲልም ያለውን አክብሮትና ፍቅር ተናግሯል፡፡

 

ጌታቸው በበላይ አለቆች ሴራ ቢጎነጎንበትም፣በኢትዮጵያ ሬድዮ የዜና አቀራረብ ላይ አንዳች መሰረታዊ እና አዲስ ለውጥ ለማድረግ ለራሱ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ጌታቸው ይህን ለውጥ ከማድረጉ በፊት የቢቢሲን የዜና አቀራረብ ዘዬ ልብ ብሎ ያጤን ነበር፡፡ 1979 ቀደም ብሎ የአንድን ዜና ዝርዝር ዜና አንባቢው ብቻ ነበር ያነብ የነበረው፡፡ ጌታቸው በፈጠረው የዜና ፋይል ፎርማት ግን ጋዜጠኛው ከሄደበት ሲመለስ በራሱ ድምጽ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህም ዛሬ ድረስ መዝለቅ የቻለውን ዜና ፋይልን መፍጠር የቻለ ነው፡፡

 

ዜና ፋይል በይፋ 1979 ፎርማቱ በወጉ ከተቀረጸ በኋላ ጌታቸው ባለሙያ ማፈላለጉ ቀላል እንዳልሆነ ግንዛቤ አግኝቶ ነበር፡፡ ጌታቸው ይህን የዜና ፋይል ፎርማት ቀርጾ ገቢራዊ ሲያደርግ ከበላይ አለቆቹ ብዙም እክል አልገጠመውም፡፡ ከስር ከየዩኒቨርሲቲው ተመርቀው ይመጡ የነበሩ ወጣቶችም አዲስ ነገርን ለመማር የተዘጋጁ ስለነበሩ ይህም የጌታቸውን እቅድ ያሳካ ህልሙንም እውን ያደረገበት መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡

 

የጌታቸውን ውለታ ከማይዘነጉት ሰዎች አንዱ አለምነህ ዋሴ ነው፡፡ አለምነህ ገና 20 አመት ወጣት ሆኖ የኢትዮጵያ ሬድዮን ሲቀላቀል ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበር የገጠመው፡፡ ታዲያ አለምነህ ስለ ጋዜጠኝነት ህይወቱ መለስ ብሎ ቅኝት ሲያደርግ ዜና ፋይል በሚገባ ቀርጾኛል ብሎ ያስባል፡፡ ከዜና ፋይል ጎንና ጀርባ ደግሞ ጌታቸው ኃይለማሪያም አለ፡፡ እና አለምነህ ጌታቸውን ይወደዋል፡፡ ጌታቸውም አለምነህን ይወደዋል፡፡ አለምነህ እንደጌታቸው እያስመሰለ ሲያወራ ቁጭ ነው፡፡ ነጋሽ መሀመድ ደግሞ የዜና አጻጻፍን የተማርኩት ከጌታቸው ነው ይላል፡፡

 

በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን በዜና ፋይል ዝግጅት ከሪፖርተር እስከ ዋና የስራ መሪነት የደረሰችው ጋዜጠኛ ብርቱካን ሀረገወይን ጌታቸውን የዜና ቀማሪ ነው ስትል ትገልጸዋለች፡፡ ብርቱካን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን 1982 ከሩሲያ በፖለቲካል ሳይንስ አጠናቅቃ ስትመጣ አንድ ብላ ስራ የጀመረችው በኢትዮጵያ ሬድዮ ነበር፡፡ ጌታቸው ደግሞ የዜና ፋይል አባት ስለነበር አዳዲስ ወጣቶች ሲመጡ ብቁ ሆነው እንዲገኙ ያሰለጥን ነበር፡፡ የመሰልጠን እድሉን ካገኙት መካከልም ብርቱካን ሀረገወይን በቀዳሚነት ትነሳለች፡፡ ብርቱካን ከጌታቸው ከተማረችው ነገር አንዱ ከዜና ውስጥ ተስማሚ ርእስን ማውጣትን ነው፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም አንድ ዜተጽፎ ተንብቦ እስከሚቀረጽ ድረስ እስከመጨረሻው ድረስ ተከታትሎ የመቆየት ልማድ ነበረው፡፡ ይህ ልማድ ዛሬ ባሉት የዜና አርታኢዎች ዘንድ ይታያል ወይ? ቢባል የሚያጠያይቅ ነው፡፡

 

ላለፉት 35 አመታት በሬድዮ ጋዜጠኝነት የዘለቀችው ጸሀይ ተፈረደኝም የጌታቸው ውለታ በቀላሉ የሚረሳ አይደለም፡፡  ጸሀይ ረጅም ጊዜዋን ዜና ክፍል ውስጥ ባትሰራም የጌታቸውን እውቀት የመካፈል እድል ገጥሟት ነበር፡፡ ዛሬ 30 አመት አልፎትም እንኳን የጌታቸው ስልጠኛ ውስጤ አለ የምትለው ጸሀይ ታሪኩ በተለይ ለአዳዲስ የሚድያ ሰዎች የሚስተምር ነገር አለው ስትል ያላትን ልባዊ አክብሮት ገልጻለች፡፡

 

             ድምጽና -ጌታቸው

 

ጌታቸው ጥሩ የአነባበብ ክህሎት የታደለ ነበር፡፡ ይህንኑ ለማጤን የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች 30 አመት በፊት ጌታቸው የሰራቸውን ዘገባዎችንና መግለጫዎች ስናዳምጥ ሰውየው ከፈጣሪ የተቸረው ልዩ ድምጽ ከእነ ሙሉ ክብሩ ተሰጥቶታል እንላለን፡፡ ታዲያ ይህ ድምጽ በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ጌታቸውም ሲያነብ በቂ የሆነ የስነ-ልቦና ዝግጅት ስለሚያደርግ ተሳክቶለታል፡፡ ወፍራም እና አጽንኦት ሰጪ የሆነው የጌታቸው ድምጽ ከእዝነ-ህሊና የሚጠፋ አልነበረም፡፡

 

ብርቱካን የአነባበብ ቴክኒክን ጥሩ አድርጎ ያስተማረኝ ጌታቸው ነው ትላለች፡፡ ንባብ ላይ ድምጽን ከውስጥ ማውጣት የመሳሰሉት ቴክኒኮችን በዝርዝር የነገራት ጌታቸው ነው፡፡ ብርቱካን፣ጌታቸው ጋር አብራ የሰራችው 5 ወራት ቢሆንም በእነዚህ ወራት ቁልፍ ጉዳዮችን እንድትጨብጥ አድርጓታል፡፡ 

 

የሙያ ከፍታ

 

በርካታ ባለሙያዎች፤ ጌታቸው የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት ደረጃ በብዙ እርከን ከፍ አድርጎታል ብለው ያምናሉ፡፡ በተለይም እርሱ የኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ላይ 20 አመት በላይ እንደመስራቱ በሙያው ላይ ዛሬ ጎልተው ለታዩት ለውጦች እጁ አለበት፡፡ አብረውት የሰሩትም በሙሉ አንደበት ጌታቸው ያልተነገረለት ነገር ግን ስራው ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ሲለፋ የኖረ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡

 

ጋዜጠኛ ሀይሉ ወልደጻድቅ ጌታቸውን ከብስራተ ወንጌል ሬድዮ አንስቶ ያውቀዋል፡፡ጌታቸው ከአማርኛ ዜና አንባቢነቱ ባሻገርም እንግሊዝኛ አንባቢ ቢሆን እንኳን አቅም የነበረው ሰው ነበር ሲል ጋዜጠኛ ሀይሉ ሀሳቡን ይሰነዝራል፡፡ ይህ የእንግሊዝኛ ክህሎት የዳበረው ደግሞ የቢቢሲ ሬድዮን በንቃት በመከታተሉ ምክንያት ነው ይላል፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያምን በጊዜው ከነበሩት ጋዜጠኞች ለየት ብሎ እንዲታወቅና እንዲከበር ያደረገው ከድምጹ ማማር ባሻገር የሚሰጣቸው ጥልቅ ትንታኔዎች ነበሩ፡፡ ከመጽሀፍ ጋር ውሎ የሚያድረው ጌታቸው ማንበቡ ለሙያው ትልቅ እገዛ አድርጎለታል፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም አድማጭ/ ተመልካች ጥልቀት ያለው መረጃ ሊያገኝ ይገባል የሚል እምነት አለው፡፡ ለዚህም ሲል ነበር እንደ ዜና ፋይል ያሉ ፎርማቶች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አምኖ ገቢራዊ ያደረጋቸው፡፡

 

ጋዜጠኛ ሀይሉ ወልደጻዲቅ የፕሮግራም ሃላፊ ሆኖ ጌታቸው ደግሞ የዜና ሃላፊ ሆኖ ሁለቱም በአንድ አይነት ኤዲቶሪያል ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ታዲያ በኤዲቶሪያሎች ላይ ጌታቸው ሀሳብ እንዲሰጥ ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ ጥልቀት ያለው አስተያየት ይሰጣል፡፡ነገር ግን ካልተጠየቀ ብዙውን ጊዜ ቆጠብ ማለትን ምርጫው ያደርጋል፡፡

 

‹‹……… ስለ ጌታቸው ምን ትዝ ይልሀል? ተብዬ ብጠየቅ ትህትናው ይጎላብኛል፡፡በሰው መስመር ሰተት ብሎ መግባት ምርጫው አይደለም፡፡የራሱን ስራ ብቻ ሰርቶ መሄድን የሚመርጥ ነው›› ሲል ጋዜጠኛ ሀይሉ ስለ ጌታቸው የሚያስታውሰውን አጫውቶናል፡፡

 

            ኦሮማይ ጌታቸውና ዘሪሁን

 

በአሉ ግርማ በጻፈው ኦሮማይ ልቦለድ ድርሰት ውስጥ የዋና ገጸ-ባህሪውን የጸጋዬ ኃይለማሪያምን ባህሪይ ያነበበ ይህ ሰው ጌታቸው ኃይለማሪያም ነው እንዴ ?ማለቱ አይቅርም፡፡ በእርግጥም በመጽሀፉ ላይ ያለው ጸጋዬ ዜና ፋይል ካለው ጸጋዬ ጋር በከፊል ይመሳሰሉ ነበር፡፡

 

በአሉ ግርማ 1975 ግድም የቀይ ኮከብ ጥሪ ዘመቻ ላይ 2 የሚድያ ሰዎችን አብሮ ይዞ ሄዶ ነበር፡፡ ጌታቸው ኃይለማሪያምንና አቶ ዘሪሁን ብርሀኔን፡፡ ሁለቱም በኦሮማይ ላይ በገጸ-ባህሪይነት የተሳሉ ሲሆኑ አቶ ዘሪሁን ፍሬው ዘሪሁን በሚል ስማቸው ተለውጦ በመጽሀፉ ላይ በከፊል ታሪካቸው ቀርቧል፡፡

 

መንጌና ጌታቸው

 

አቶ ዘሪሁን ብርሀኔ 50 አመት በፊት ገና ብስራተ ወንጌል ሳሉ ከጌታቸው ሀይለማሪያም ጋር ትውውቅ ነበራቸው፡፡በብስራተ- ወንጌል ይሰሩ በነበረበት ጊዜም በኒያላ ሆቴል ጌታቸው እና አቶ ዘሪሁን አብረው ይኖሩ ነበር፡፡

 

ያኔ ብስራተ- ወንጌል ከጌታቸው ጋር አብረው ይሰሩ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል ዘውዱ ታደሰ እና አማኑኤል በረከት ይጠቀሳሉ፡፡ጌታቸው ከእነዚህ የቀድሞ የሚድያ ሰዎች ጋር ብዙ ትዝታዎችን አሳልፏል፡፡

 

ለረጅም ጊዜ የቅርቤ ሰው ስለነበር በጥልቀት አውቀዋለሁ፡ የሚሉት አቶ ዘሪሁን ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እንደተናገሩት ጌታቸው የያዘውን ነገር ዘላቂና ትልቅ ማድረግን ተክኖበታል፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማሪያም እና ጌታቸው ኃይለማሪያም ወዳጅ ናቸው እያሉ ወሬ ቢያናፍሱም ይህ ግን ከእውነታው የራቀ ነበር፡፡ ጌታቸው ኃይለማሪያም ሙያውን በጥልቀት እያሳደገ ከመስራት በዘለለ የተለየ ቀረቤታ ከሊቀመንበሩ ጋር እንዳልነበረው አቶ ዘሪሁን መስክረዋል፡፡

 

ጌታቸው ጨዋታና ሳቅ ይወዳል፡፡ነገር ግን ሲጫወት ሰው ይመርጣል፡፡ አንዳንዶች ኩራተኛ ነው ቢሉትም ኩራትን ጌታቸውን አያውቀውም፡፡         

 

ጎበዝ የፕሮዳክሽን ሰው

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም፣ ኢቲቪ በነበረ ጊዜ ጎበዝ የፕሮዳክሽን ሰው እንደነበር ይነገርለታል፡፡ አንድ ካሜራማን ጥሩ አድርጎ ካላነሳለት፡ይናደዳል፡፡ አንዳንዴ ራሴ ካሜራውን ልያዘው የሚልበት ጊዜ ነበር፡፡ በቼክ ሪፐብሊክ ስለ ቪድዮ ቀረጻ ተምሮ ከመጣ በኋላ ለተወሰኑ ጊዜያት ራሱ መቅረጽ ጀምሮ ነበር፡፡

 

በኢትዮጵያ ቲቪ የፕሮዳክሽን ክፍል ሃላፊ የነበሩት አቶ ጅብሪል አባዋሪ ጌታቸው ከተፈጥሮው ለፕሮዳክሽን የተፈጠረ ሰው ነው ይላሉ፡፡ከእርሱ ጋር በመስራቴ ሁልጊዜም ደስታዬ ወደር የለውም ሲሉ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቴክኒክ ክፍል 30 አመት በላይ ያገለገሉት አቶ ንጉሴ ሶሪ ደግሞ፣ ጌታቸው ጋዜጠኛውን የቴክኒክ ሰዎችንና የካሜራ ሰዎችን ሲያስተባብር ይችልበት እንደነበር መስክረዋል፡፡

 

ድምጻዊት ነጻነት መለሰ ኧረ ምን ሆነሀል? የተሰኘውን የሙዚቃ ክሊፕ በሰራችበት ጊዜ በወቅቱ የቀረጻው ሙሉ ፕሮዳክሽን የተሰራው በኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ስቱዲዮ ነበር፡፡ እንደ ዳይሬክተር ኃላፊነቱን የተወጣው ደግሞ ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበር፡፡በጊዜው ጌታቸው ይህን ስራ በጥሩ መልኩ ለማከናወን ምን ያህል ይጨነቅ ይጠበብ እንደነበር በጊዜው የነበሩ የሚያስታውሱት ሀቅ ነው፡፡

 

የእንግሊዝኛ ዜና አንባቢ የነበረው ልኡልሰገድ ኩምሳና ጌታቸው ኃይለማሪያም ልዩ ቀረቤታ ነበራቸው፡፡ ሲቀራረቡም ወግና ስርአት ባለው መልኩ ነበር፡፡ ታዲያ ልኡልሰገድ ወደ ስቱዲዮ ዜና ለማንበብ ሲገባ እንዲህ ብትለብስ ይህን ብታደርግ እያለ ምክር ሲለግስ የነበረው ጌታቸው ኃይለማሪያም ነበር፡፡

 

በዚያን ዘመን ስመጥሩ ከነበሩ የቲቪ ዜና አንባቢዎች መካከል አዛሪያ ኪሮስ፤ ተፈራ ግዛውና ጌታቸው ኃይለማሪያም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

 

      የጌታቸው ድምጽ

 

1981 ጳግሜን ወር ላይ በሀገራችን በሰሜኑ አካባቢ ተከስቶ የነበረው ያለመረጋጋት እልባት እንዲያገኝ በአሜሪካ መንግስት አንድ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ በአትላንታ ተደርጎ የነበረው ውይይት በካርተር ማእከል አስተባባሪነት የተከናወነ ነበር፡፡ በዚያው ሰሞን በጓድ አሻግሬ ይግለጡ ይመራ የነበረው የልኡካን ቡድን ከተቃዋሚው የሻእቢያ ወገን ጋር ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ ይህን የአትላንታውን ዘገባ አስመልክቶ ጌታቸው ሀይለማሪያም አቅርቦት የነበረውን ዘገባ በቅርቡ በተወዳጅ ሚድያ ቲዩብ ላይ ስለምንጭነው አጠቃላይ የጌታቸውን ታሪክ 90 ደቂቃ በዶክመንተሪ መልክ ስለሚቀርብ ይከታተሉ ዘንድ እንጋብዛለን፡፡

 

የጌታቸው ኃይለማሪያም ድምጽ ሞገስ ያለው ነበር፡፡ መግለጫዎችን ሲያነብ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ብዙዎችም የጌታቸው ኃይለማሪያም ተጽእኖ ያደረባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ አለምነህ ዋሴ ነው፡፡ አለምነህ ዋሴ የጌታቸው ታሪክ ትውልድ መሻገር አለበት ብሎ ያምናል፡፡ በተለይ ደግሞ ስለ ጌታቸው ሀይለማሪያም በዘጋቢ ፊልም በመጽሀፍ መውጣት አለበት ብሎ ያምናል፡፡

 

ቤተሰባዊ ህይወት

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም 1968 መስከረምወር ላይ ከወይዘሮ ገነት ታደሰ ጋር ጋብቻ መስርቶ ሀና ጌታቸውና ባያብል ጌታቸው የተሰኙ ልጆችን አፍርቷል፡፡ ጌታቸውና ወይዘሮ ገነት የጋብቻ ስነ-ስርአታቸውን የቅርብ ወዳጆቻቸው በታደሙበት በግዮን ሆቴል አከናውነው ነበር፡፡

 

ወይዘሮ ገነት ታደሰ ባለቤቷ ጥልቅ አንባቢና ልዩ የፈጠራ ክህሎት ያለው መሆኑን ትናገራለች፡፡ በየጊዜው ባህርማዶ እየሄደ ይወስዳቸው የነበሩት ስልጠናዎችም ጠቅመውታል ትላለች፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም ተዘራ ሀይለማሪያም የተባለ ታናሽ ወንድምና ውዴ ኃይለማሪያም የተባለች እህት አለችው፡፡ እህቱን ወይዘሮ ውዴ እንዳገኘናት ተጨማሪ መረጃዎችን በዚህ ዊኪፒዲያ ላይ እናክላለን፡፡

 

በአሁኑ ሰአት በባህር ማዶ መኖሪያውን ያደረገው የጌታቸው ኃይለማሪያም 2 ወንድ ልጅ ባያብል ጌታቸው አባቱ እርሱንና እህቱን በቃሊቲ የመዝናኛ ስፍራ ይወስዳቸው እንደነበር ነግሮናል፡፡

 

1983 የደርግ መንግስት ወድቆ የኢህአዴግ መንግስት በተተካ ጊዜ ሰኔ 27 1983 ከስራ ስንብት ከደረሳቸው 52 የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረቦች አንዱ ጌታቸው ሀኃይለማሪያም ነበር፡፡ ጌታቸው በጊዜው በተደረገ ስብሰባ ከእውነታ የራቁ ክሶች ቀርበውበት 45 አመቱ ከስራ ተሰናብቷል፡፡

 

ጌታቸው ወዲያው አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ወደ መሰረቱት አንበሳ የማስታወቂያ ድርጅት በማቅናት አብረው ሆነው ሲሰሩ ነበር፡፡ ጌታቸውም በግሉ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን እና ዶክመንተሪዎች በመስራት በሙያው አቅሙን ለማሳየት ሞክሮ ነበር፡፡

 

ጌታቸው ኃይለማሪያም ፣በድንገተኛ ህመም 49 አመት እድሜው መስከረም 7 1987 . ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ብዙ ሊሰራ በሚችልበት እድሜ ህይወቱ ማለፉን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

 

ምስጋና:ይህን በጌታቸው ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጽሁፍ እንድንሰራ ለፈቀዱልንና ጠቃሚ ምስሎችን ለሰጡን የጌታቸው ኃይለማሪያም ባለቤት ወይዘሮ ገነት ታደሰ፣ ልጆቻቸው ሀና ጌታቸው እና ባያብል ጌታቸውን ከልብ ማመስገን እንፈልጋለን፡፡ በተጨማሪም ብሩክ ተስፋዬ 4 አመት በፊት በጌታቸው ኃይለማሪያም ላይ የሰራው ዶክመንተሪ ጥሩ መነሳሳት ፈጥሮልናል፡፡ ከዚህ ባሻገር የጌታቸው ኃይለማሪያም የቅርብ ባልደረቦችን ሁሉ ማመስገን እንወዳለን፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮ የስራ ሃላፊዎችም ተመስገኑ፡፡ እንደዚሁም ይህ ጽሁፍ ዊኪፒዲያ ላይ ሲወጡ ያሉ ስህተቶችን በቅንነት በማረም የረዳንን ስለሺ ሽብሩን ማመስገን እንወዳለን፡፡ ታምራት ሀይሉ እና አለምነህ ዋሴም ስራው በቶሎ እንዲያልቅና ለሰጣችሁትም ማበረታቻ ምስጋናችን ትልቅ ነው፡፡ ወይዘሮ ውዴ ሀይለማሪያምም የጌታቸውን ምስሎች ስለሰጠችን ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡ አሁንም ስለጌታቸው መጨመር አለበት የምትሉ ካላችሁ ባካችሁ ወደ ኋላ አትበሉ/

 

መዝጊያ : ጌታቸው በስጋ የለም፡፡ ተማሪዎቹ ግን አሉ፡፡ ጌታቸውን በአካል ባናገኘውም ያስቀመጣቸው መሰረታዊ እውቀቶች ወደታች እየወረዱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ ጌታቸው ሀይለማሪያም በህይወት ሳለ የሚወደውን ነበር የሰራው፡፡ ስለሚወደውም ተወዳጅ ባለሙያ ሆነ፡፡ ተከታይ አፈራ፡፡ በስራው ተከበረ፡፡ 1983 ምንም እንዳልሰራ ሰው ተቆጥሮ ቢሰናበትም የተከለው ስርአት ግን 30 አመት በላይ ዘልቋል፡፡ ኢትዮጵያ ውለታ የዋሉላትን ትበላለች እንዲሉ ጌታቸው መስራት በሚችልበት እድሜው ተበላ፡፡ ግን አልሞተም፡፡ ለጊዜው ተቀበረ እንጂ ለጊዜው ተረሳ እንጂ እንዲህ አይነት የድንቅ አእምሮ ባለቤት ሊዘነጋ አይችልም፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲያድግ ሌሎችን አስተባብሮ አንድ ነገር ፈጠረ፡፡ ድምጹን የማይዘነጋ አድርጎ ትቶልን አለፈ፡፡ አንዳንዶች እንድንረሳው ቢያረሳሱንም ታሪክ ይቀበራል እንጂ አንድ ቀን መውጣቱ ስለማይቀር የጌታቸውም ታሪክ ወጣ፡፡ ምስሉም ታየ፡፡ ድምጹም ተሰማ፡፡ ሁሉም ተነቃቃ፡፡ በህይወት የሌለ ሰው በህይወት ያለን ሰው ሲያነቃቃ አየን፡፡ ጌታቸው ሞቶ በለጣቸው፡፡ ታሪክ የማይወዱ ባለውለታ የማይወዱ ታሪክ ዝንተ-አለም አያነሳቸውም፡፡ ጌታቸው ግን ገና መጽሀፍ ይጻፍለታል፡፡ ይህን 2800 ቃላት የተሰናዳ ጽሁፍ በወጉ አንድ ብለን ከመጀመራችን በፊት መረጃ የሚሰጠን ሰው ፍለጋ በትንሹም ቢሆን ተቸግረን ነበር፡፡ አሁን ይህን ጽሁፍ አዳብሮ ለማውጣት ሲባል 13 በላይ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ የደበዘዘው የጌታቸው ታሪክ ደምቆ እንዲታይ ያደርጋል፡፡ ገና ወደፊት በዚህ ጽሁፍ ላይ አክለን መጽሀፍ ማድረጋችን ከውሳኔ ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች የጌታቸውን ታሪክ በሙሉ ፍቅር እና በቶሎ እንድናወጣ ያደረገን ቁጭት ነው፡፡ ሰው እንዴት በራሱ ሀገር ይደበዝዛል? ለዚያውም ብዙ በደከመበት እና አሻራ ባኖረበት ሀገር፡፡ ጌታቸው ሀይለማሪያም እንደ በጎ አርአያ የሚቆጠር‹‹አይከን›› ነው፡፡ ይህ ሰው በመጪው ትውልድ ይታወስ ዘንድ ታሪኩን እነሆ አቀረብን፡፡ በዚህ ብቻ አንወሰንም የጌታቸውን የህልፈት ቀን መስከረም 7 ምክንያት በማድረግ ጌታቸውን በድምጽ ዘጋቢ ስራ ንዘክረዋለን/ የዚህ ጽሁፍ ሙሉ የቃለ-መጠይቅ፤ የምርምር እና የአርትኦት ስራ የተከናወነው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡/











አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች