13 ደረጀ /ማርያም ለገሰ  DEREJE GEBREMARIAM LEGESSE

 

ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ' በሙያቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱና እያበረከቱ የሚገኙ በርካታ ግለሰቦችን የህይወት ታሪክ፣ በህይወት ዘመናቸው ያሳለፉትን ውጣ ውረድ እንዲሁም ልምድና ተሞክሯቸውን በማዘጋጀት ለትውልድ የሚተላለፍ መረጃ በማስቀመጥ ላይ ይገኛል፡፡

 

ለዛሬም የጋዜጠኛ ኢንስፔክተር ደረጀ /ማርያም ለገሠ የህይወት ጉዞ፣ ልምድና ተሞክሮ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ ደረጀ /ማርያም በፖሊስና ህብረተሰብ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በጋዜጠኝነት ከሁለት አስርተ- አመታት በላይ ያገለገለ ሲሆን በተጨማሪም በፌደራል ፖሊስ ትራፊክ የመንገድ ላይ ትራፊክ ተቆጣጣሪና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖሊስ አድቫይዘር በመሆን ደቡብ ሱዳን ውስጥ ተመድቦ መንግስትና ህዝብ የጣሉበትን ከፍተኛ ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 

            ልደት፣ እድገትና ትምህርት፡-

 

ዛሬም ድረስ በህይወት ያሉና እንደልጃቸው ያሳደጉት ጎረቤቶቹ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ደረጀ /ማርያም ለገሠ ሲወለድ ጀምሮ እንደሌሎቹ ህፃናት የሚነጫነጭና የሚያለቅስ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ከሁሉም ትዝ የሚላቸው ደረጀ ዝምተኛ የመሆኑ መንስኤ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወላጅ እናቱ እቅፍ ላይ ሆኖ ወደላይ አንጋጦ ሲመለከት በአርምሞ ውስጥ ሆኖ ይህቺን አለም የሚታዘብ ካህን ይመስል ነበር ይላሉ፡፡ ለዚያም ይመስላል በጨቅላነት እድሜው ያሳይ የነበረው ባህሪይ አብሮት አድጎ አሁን ላይ ለተላበሰው ስብእና፣ ጨዋነት፣ ሰው አክባሪነቱና ሀይማኖቱን አጥባቂ ሊሆን የቻለው ሲሉ ትናንትን ከዛሬ ጋር አነፃፅረው የሚያውቁት መስክረውለታል፡፡

 

አዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ ከፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ጀርባ በተለምዶው ቢሪሞ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተወለደው የዛሬው የፖሊስ መኮንንና ጋዜጠኛ ኢንስፔክተር ደረጀ /ማርያም ለገሠ ወላጆቹ አሥር አለቃ /ማርያም ለገሠና እናቱ ወይዘሮ አበራሽ ደርሰህ ካፈሯቸው 7 ልጆች መካከል የመጨረሻውና ታናሽ ብላቴና ነው፡፡የደረጀ ወላጆች ካላቸው ጥብቅ የሆነ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይነት አኳያ 'ዛሬ ድረስ እያገለገለባት ከምትገኘው የማህደረ- ስብሐት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ነው እንደታላላቆቹ ሁሉ ክርስትና የተነሳው፡፡

 

የደረጀ ቤተሰቦች እንደማንኛውም ሀገርኛ ነዋሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆኑ የህይወት ፈተናን ፊት ለፊት መጋፈጥ የጀመረው ገና በልጅነት እድሜው 11 አመት ልጅ ሳለ ነው፡፡የዛን ጊዜም እነዚህኑ ቤተሰቦቹን ለመርዳት ያለው ፍላጎቱ በማየሉ ለገሀር አካባቢ በሚገኘው በየነ መርእድ (እድገት በህብረት) አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግማሽ ቀን እየተማረ ግማሽ ቀን ደግሞ ልደታ እና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኙ ጋራዦች ውስጥ በሙያ ረዳት ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡በቀረው የምሽት ክፍለ ጊዜ ደግሞ ማህደረ- ስብሀት ቅድስት ልደታ እና ደብረ መድሀኒት መድሀኒአለም ቤተክርስቲያን ውስጥ ወንበር ዘርግቶ ከመምህር ተክለማርያምና ከንስሀ አባቱ ከመምሬ ሽፈራው ለድቁና ማዕረግ የሚያበቃውን የቤተክህነት ትምህርት ሲማር ቆይቷል፡፡

 

ከቤተ ክህነቱ ትምህርት ጎን ለጎን ደረጀ ለአስኳላ ትምህርት ካለው ፍላጎት የተነሳ እንዲሁም ዛሬ ድረስ ለታሪክ ካስቀመጣቸው የትምህርት ማስረጃዎቹ ለመረዳት እንደተቻለው 1 እስከ 8 ክፍል ድረስ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመውጣት የወደፊት ተስፋ ተጥሎበት ታላላቆቹንና ወላጆቹን ያስደስት እንደነበር ወንድምና እህቶቹ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና በዚህ የትምህርት ሂደት ውስጥ ተስፋ አስቆርጦት የነበረውና በህይወት ዘመኑ የማይረሳው ገጠመኝ እንዳለው ደረጀ እራሱ ይገልፃል፡፡

 

ደረጀ 1977 / የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ትክክለኛ ጊዜውን በማያስታውሰው አንድ ቀን እንደተለመደው ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ትምህርት ቤት እየጠጓዘ ሳለ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ሲደርስ አንድ ጎልማሳ ሰው ቀረብ ይለውና ’’ ማሙሽዬ አንድ ነገር ልትታዘዘኝ ትችላለህ ’’ ይለዋል፡፡ ለወላጆቹና ላደገበት ማህበረሰብ ሲታዘዝ ያደገው ደረጀም ’’ ጋሼ ምን ገዶኝ የማልታዘዝህ; ’’ ብሎ ሲመልስለት ግለሰቡም ’’ የያዝከውን ደብተርና ቦርሳ ለእኔ ስጠኝና (በጣቱ በርቀት እያመላከተ) እዛ ልደታ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ከሚገኘው አትክልት ቤት አንድ ኪሎሙዝ ግዛልኝ ’’ ይለውና ሰባ አምስት ሳንቲም ይሰጠዋል፡፡

 

በሶስት ስሙኒዎች ብቻ አንድ ኪሎ ሙዝ መግዛት እንደማይቻል ያልተረዳው ደረጀ ከድንኳን መስሪያ ሸራ የተበጀችውን አሮጌ ቦርሳውን ከውስጡ ካሉት የመማሪያ መፃህፍትና ደብተሮች ጭምር ለሰውዬው አስረክቦ የተባለውን ሙዝ ለመግዛት ወደ ልደታ ሩጫውን ይያያዘዋል፤ ሲደርስም አንድ ኪሎ ሙዝ በሰባ አምስት ሳንቲም እንደማይሸጥ ሲነገረው ሁሉን ይተውና ወደ ላከው ሰውዬ ሲመለስ የጠበቀው ሌላ ሆኖ ቀረ፡፡ ግለሰቡ ለካ በከተማው እየተዘዋወረ ታዳጊ ተማሪዎችን በማታለል የመማሪያ መፅሀፍትንና ደብተሮችን እየሰረቀ እብስ በማለት ለተቀባዮቹ የሚሸጥ ወሮበላ መሆኑ ታወቀ፡፡ ታዳጊው ደረጀም ወላጆቹ በችግር የገዙለትን ደብተርና መፅሀፍት ለቀማኛ ማስረከቡን ሲረዳ ለትምህርት ያለው ፍላጎቱ ቀንሶ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት የህፃን እንባውን እያዘራ ወደወላጆቹ መኖሪያ ይመለሳል፡፡ አድጎ ተምሮ ወላጆቹንና ሀገሩን ለመርዳት ሩቅ አስቦ የነበረው ታዳጊ ይህ ያላሰበው ነገር ሲገጥመው በወቅቱ የወደፊት ሀሳቡ መክኖ በትምህርቱ የነበረው ተስፋ ተሟጦ እንደነበር ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስታውሰው ሌሎች እንደእርሱ በችግር እየተማሩ ያሉ ህፃናት መሰል ችግር እንዳይገጥማቸው የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ በአንደበቱ ይገልፃል፡፡

 

ይህንን ሁሉ ችግር ተቋቁሞ በአካልም በአእምሮም እያደገ የመጣው ደረጀ /ማርያም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በዚህ መልኩ ካጠናቀቀ በኋላ የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት አምጥቶ ወደዘጠነኛ ክፍል ተዛውሮ በቅሎ ቤትና ቄራ መካከል በሚገኘው GCA ወይም በተለምዶ አብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዲስ መንፈስ ትምህርቱን መቀጠል ጀመረ፡፡

 

ኢህአዴግ እና ግንቦት 20/1983 /ም፡-

 

ያኔ ግንቦት ወር 1983 / ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ ሁለት ወራት አስቀድሞ በወቅቱ የነበረው የኮሎኔል መንግስቱ /ማርያም አስተዳደር በረሀ ላይ እየተዋጉ ሰቅዘው ይዘውት ለነበሩ ህወሃቶች በርካታ ስሞችን ሰይሞላቸው ነበር፡፡ እንዲያውም በሀገሪቱ ብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጭምር እነዚህ ድልድይ አፍራሾች፣ ተገንጣይ ወንበዴዎች፣ ነፍሰ- ገዳዮች፣ ደም የጠማቸው ዲያቢሎሶች፣ የውጪ ቅጥረኞች ብቻ ምኑ ቅጡ በየቀኑ በሚተላለፉ የፕሮፖጋንዳ ወሬዎች ሲያብጠለጥሏቸው ይከርማል፡፡

 

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች የደርግን የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ወደራሳቸው በመተርጎም ምናልባትም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ወላጆች ልጆቻቸው ከቤት ሲወጡ እንዳይገደሉባቸው በማሰብ ወያኔዎች ነፍሰ-ገዳዮችና ሰይጣኖች ስለሆኑ ከቤት ብትወጡ ያልቅላችኋል በማለት ከማስፈራሪያ ጭምር ታዳጊ ልጆቻቸውን ይመክሩ ነበር፡፡ ደረጀም እንደሌሎቹ ልጆች ይህ ማስፈራሪያ ከወላጆቹ ስለደረሰው ለጥቂት ጊዜያት ከቤቱ ሳይወጣ ከወላጆቹ ጋር የቁም እስረኛ ሆኖ ለመቆየት ተገደደ፡፡ እንዲህ እያለ ቀናቶች ሲቆጠሩ በደርግ የመገናኛ ብዙሀን ሲለፈፍ የነበረው ወደተግባር ተለውጦ ኢህአዲግ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር በሚል ራሱን ሰይሞ ግንቦት 20 ቀን 1983 / አዲስ አበባ ከተማን ይቆጣጠራል፡፡

 

ዲያቢሎስና ነፍሰ-ገዳዮች የተባሉት በድል አድራጊነት አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ይህ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው የአዲስ አበባ ነዋሪ ኑሮውን በስጋት እየመራ ባለበት ሁኔታ አንድ ነገር ተነግሮት ምንነቱን ሳያረጋግጥና መጨረሻውን ሳያውቅ እረፍት የማይሰማው ታዳጊው ደረጀ /ማርያም እነዛ ዲያቢሎስና ነፍሰ-ገዳይ ተብለው የተሰየሙት ፍጡራን ምን እንደሚመስሉ ለማየት ከራሱ ጋር ይማከርና የወላጆቹን ማስፈራሪያና ምክር ወደጎን በማለት አንድ ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡ 

 

እለቱ ግንቦት 24 ቀን 1983 / ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ከሚኖርበት የፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ጀርባ ከሚገኘው የትውልድ መንደሩ ወላጆቹ ሳያዩት ማንንም ሳያስከትል ተደብቆ በመውጣት ጉዞውን ወደ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ያደርጋል፡፡ እንደደረሰም አካባቢውን ሲቃኝ በአደባባዩ ዙሪያ የተለያዩ የጦር ተሸከርካሪዎች፣ ከባድ የቡድን መሳሪያዎች የተጠመዱባቸው ተሸከርካሪዎች፣ ታንኮችና እንዲሁም የላስስቲክ ጫማ የተጫሙ፣ ካኪ ቁምጣ ሱሪ ያደረጉ፣ በአንገታቸው ዙሪያ ሽርጥ አገልድመው ኤኬ 47 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ የታጠቁ ባለጨበሬ ፀጉራም የሆኑ ታጋዮች ወዲህና ወዲያ ሲንከላወሱ ተመለከተ፡፡ ነገር ግን ወላጆቹ ሲያስፈራሩበት የነበረውና በህሊናው ስሎት የነበረውን ነፍሰ -ገዳይ ዲያቢሎስ የተባለውን ፍጡር ማየት አልቻለም፡፡

 

ይህንን ጉዳይ እያወጣና እያወረደ አደባባዩን ሲዞር ሜክሲኮ ካፌ ፊት ለፊት ካለው የመብራት ሀይል ዋናው መስሪያ ቤት አጥር ጥግ ድንገት ያስደነገጠውን ነገር ተመለከተ፡፡ 3 ሜትር ርቀት ላይ በግምት እድሜያቸው 35 እስከ 40 የሆነ ሁለት ሰዎች አስከሬን ተጋድሟል፣ ጠጋ ብሎ ሲመለከት በአንደኛው ላይ በግንባሩ እና በአንገቱ በኩል በጥይት የተመታበት ስርጉድ ሲኖር በሌላኛው ላይ ደግሞ በግልፅ ተለይቶ በማይታይ ቦታ ላይ ደረቱ አካባቢ በጥይት ተመትቶ ሊሆን ይችላል የለበሰው አዳፋ ሸሚዝ በደም ተነክሮ ተዘርሯል፡፡ ደረጀ ይህን ሁኔታ ሲመለከት ማመን አቃተው፡፡ በህልሜ ነው እንዳይል በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስከሬኖቹን በቆረጣ እየተመለከቱ ሲያልፉ አረጋግጧል፡፡በወቅቱም ወላጆቹም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያስፈራሩበትና ለህወሃት ታጋዮች ደርግ ከሰየመላቸው ቅፅል የፕሮፖጋንዳ ስሞች መካከል ዲያቢሎስ ወይም ነፍሰ- ገዳይ የሚለውን ሰይጣን  በአካል ተገልፆ ማየት  ባይችልም በኢህአዴግ ወታደሮች በኩል በተግባር ተመልክቻለሁ ሲል ይናገራል ደረጀ ስለጉዳዩ ጨዋታ ከተነሳ፡፡

 

ኢህአዴግ በወቅቱ በሚቆጣጠራቸው የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ተግባራትን ያከናውን እንደነበር ከጊዜ በኋላ ቀን ጠብቆ ይፋ ወጣ፡፡ይህንን የሚያደርገው ደግሞ በየትኛውም አካባቢ ማንኛውም አይነት ህዝባዊ አመፅ እንዳይነሳ ህዝቡም መሰል እንቅስቃሴ ቢያደርግ ሊወሰድበት የሚችለው እርምጃ ሞት ብቻ መሆኑን ለማሳየት የቀየሰው ዘዴ እንደሆነ ከበርካታ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ከሠራዊቱ በጡረታ የተገለሉ አባላቱ ነግረውኛል ይላል ደረጀ፡፡

 

የበቅሎ ቤቱ ፍንዳታና ፍቅር፡-

 

የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ አንድ ሳምንት በኋላ ማለትም ግንቦት 27 ቀን 1983 / ከሌሊቱ አስር ሰአት አካባቢ ለሰዓታት የዘለቀና አዲስ አበባ ከተማን ከዳር እስከዳር በድምፅ ያናወጠ የበቅሎ ቤቱ የደርግ የመሳሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤት ፍንዳታ ነበር፡፡ ደረጀ የዚያን ጊዜ 10 ክፍል ተማሪ ሲሆን የበቅሎ ቤት ፍንዳታው ከተከሰተበት ወታደራዊ ካምፕ አጠገብ ከሚገኘው GCA ወይም አብዮት ቅርስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይማር ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ በፍንዳታው ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ ቆየ፤ በኋላም የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ ከሁለት ወር በኋላ ተማሪዎቹ ትምህርት እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ይሁንና ትምህርቱን ለማስቀጠል የማያስችል መሰናክል የሆነ ሌላ ችግር ተከሰተ፤ ይኸውም በበቅሎ ቤቱ ፍንዳታ አማካኝነት ከመሳሪያ ግምጃ ቤቱ የተፈናጠሩ ተቀጣጣይ ነገሮች በትምህርት ቤቱ ቅፅር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ ረጃጅም ቄጤማ ሳሮች ውስጥ ተሰግስገው ስለነበር በፀሀዩ ሙቀትም ይሁን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በድንገት እየፈነዱ የመማር ማስተማሩን ሂደት ያስተጓጉሉ ጀመር፡፡

 

ይሄ ወቅት ደግሞ ደረጀ /ማርያም የፍቅርን ሀሁ የጀመረበት ጊዜ ስለነበር ከአንዲት አብራው ከምትማር ወጣት ጋር የአይን ፍቅር ይይዘዋል፡፡ፍቅሩን ለመግለፅም በፃፋት የመጀመሪያ የፍቅር ደብዳቤ አማካኝነት መቀራረቡ  ከአይን ፍቅር ይዘልና የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ያጠናክረዋል፡፡

 

በተለይ በትምህርት የእረፍት ሰአት ላይ ሁለቱ ፍቅረኛሞች ቁጭ ብለው የሚያወጉበትን ቦታ ሲፈልጉ እነዛ ቅፅር ግቢ ውስጥ የበቀሉት ረጃጅም ቄጤማዎች አመቺ በመሆናቸው ዘወትር እንደሚያደርጉት ሳሮቹ ላይ አረፍ ይላሉ፡፡ እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነበር በሞቀ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረው ፍቅር ከአንድ አመት በላይ ሳይዘልቅ በድንገት የተቋጨው፡፡ እንደወትሮው እነዛ እረጃጅም ሳሮች ላይ ተቀምጠው ስለቀጣይ የህይወት ቆይታቸው፣ ስለነገው ኑሮአቸው እየተወያዩ ባለበት ቅፅበት ፍቅረኛሞቹ ከተቀመጡበት በግምት ሀያ ሜትር ርቀት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ፍንዳታ ይሰማል፤ በአካባቢው የሚገኙ ተማሪዎች ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ ደረጀ ግን ካለበት ቦታ ሆኖ በፍጥነት ፍቅረኛውን አቅፎ መሬቱ ላይ ለጥ ይላል፡፡ (ደረጀ ስለዚህ ሁኔታ ሲያስረዳ ይህን ራስን የመከላከል ዘዴ ከየት እንደመጣለት እንኳን እስከዛሬ ድረስ እንደማያውቅ ነው የሚናገረው) ትረፊ ያላት ነፍስ ሆነችና ሁለቱም ምንም ሳይሆኑ ከተጋደሙበት ሳር ላይ ተነስተው ወደመማሪያ ክፍላቸው ያመራሉ፡፡

 

እንግዲህ ከዛ በኋላ ነው በፍንዳታው ድንጋጤ ይሁን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከፍቅረኛው ጋር የተለያየው፡፡ደረጀ ያፈቀራትንና ወደፊት አብሯት ለመኖር ያሰባትን ልጅ በድንገት ቢለያትም ሁሌም

 

   ’’ ቦንቡ ፍቅርሽ ቢፈነዳ ላንቺ ብዬ ገባሁ እዳ ’’

 

የሚለውን ቆየት ያለ ሙዚቃ ሲያዳምጥ ሁሌም የፍቅር ጅማሬው የሆነችውን ጉብል እያስታወሰ በትዝታ ወደኋላ እየተጓዘ የልጅነት ፍቅሩን ያስታውሳል፡፡

 

ቤተ ክህነት፡-

 

ደረጀ እንደ ወላጆቹ እምነቱን አክባሪ፣ ለታላላቆቹ ታዛዥና በስነምግባር ታንፆ ለማደጉ ትልቁን ሚና የተጫወተለት የቤተክህነት ቆይታው ነው፤ ቤተሰቦቹ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ቤተክርስቲያን አዘውታሪ ነበሩ፡፡ በተለይ የደረጀ ታላቅ እህት በየሳምንቱ እሁድ ታዳጊውን ቤተክርስቲያን ትወስደውና ያስቀድሱ ስለነበር ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልደታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሌሎች የእድሜ እኩዮቹ ጋር የቤተክህነቱነ ትምህርት ለመማር ሁኔታዎች ተመቻቹለት፡፡

 

ደረጀ በዚህ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማዕረገ ድቁና የሚያበቃውን ትምህርት በአግባቡ ከቀሰመ በኋላ ሀምሌ 24 ቀን 1987 / ደብረሊባኖስ ገዳም ገብቶ በወቅቱ ከነበሩት የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ማትያስ ዘንድ የድቁና ማዕረግ ከተቀበለ በኋላ ጎንደር አካባቢ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሲያገለግል ቆይቶ አስቀድሞ ትምህርቱን ከተማረበት አዲስ አበባ ከሚገኘው የልደታና የመድሀኒአለም ቤተክርስቲያን ውስጥ በተሰጠው ፀጋ ለማገልገል በቃ፡፡

 

ደረጀ ፌደራል ፖሊስ ከተቀጠረ በኋላም ቤተክርስቲያንን ማገልገሉን አላቋረጠም ነበር፤ በቤተክህነት ቆይታው የወቅቱ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር የመተዋወቅ አልፎም አብሮ የማገልገል እድሉ ገጥሞት ነበር፡፡

 

ከእለታት በአንዱ ቀን የጥቅምት መድሀኒአለም ዓመታዊ ንግስ ላይ ፓትሪያርኩ ለአገልግሎት መድኃኒአለም ቤተክርስቲያን ሲመጡ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ደረጀም ተረኛ አገልጋይ ሆኖ ሁለቱም ቤተመቅደስ ውስጥ ይገናኙና ከሌሎች ልዑካን ጋር የቅዳሴ አገልግሎቱ ይጀመርና በሰላም ይጠናቀቃል፤ የዚህን ጊዜ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያንን ዲያቆን ጥሩልኝ ብለው ካህናቱን ይልካሉ፤ ደረጀም መልእክቱን ተቀብሎ ወደፓትርያርኩ ይቀርባል፤ ከዚያምካልተሳሳትኩ ድምፅህን ስሰማ በፖሊስ ቴሌቪዥን የማየውን ጋዜጠኛ መሰልከኝ አንተው ነህ ወይ? ” ብለው ይጠይቁታል፤ ደረጀም ቀልጠፍ ብሎ ጋዜጠኛው እራሱ እንደሆነ ያረጋግጥላቸዋል፤ ከዚያም ዘወትር እለተ ሰንበት የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የፖሊስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም እከታተላለሁ፡፡ እናም እዚያ ላይ አይሀለሁ ረጋ ያልክ ልጅ እንደሆንክ አስተውያለሁ፤ ከዚያ ባለፈም ፖሊስ ሆነህ ቤተክርስቲያንህን በማገልገልህ ኮርቼብሀለሁ ስለዚህ ’’ ዲያቆን ወፖሊስ ’’ ብዬሀለሁ ያሉትን አይረሳውም፡፡ እንደውም የሀይማኖት አባቶች የአዲስ ዓመትም ይሁን ሌሎች መልእክቶች በሚዲያ ሲተላለፉ ደረጀ ለሀይማኖቱ ካለው ቅርበት አኳያ ለዘገባ የሚላከው እርሱ ስለሆነ በፓትርያርኩ የመባረክ እድሉ ይገጥመው ነበር፡፡

 

ደረጀ መለዮ ለባሽ ሆኖ እንዴት ሀይማኖቱን ያራምዳል; ሀይማኖትና መንግስት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን ይህ እያከናወነ ያለው ተግባር እርስ በእርሱ አይጋጭበትም ወይ; የሚሉ አስተያየቶች በተለያ አጋጣሚ ይደርሱታል፤ ደረጀ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ የሚከተለውን ብሏል፡፡

 

’’ በእርግጥ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 11 መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ሀይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም ተብሎ ተፅፏል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ የማይገባ ሀይማኖትም ጣልቃ እንዲገባበት የማይፈቅድ ስርዓት ነው። መንግስትና ሀይማኖት  በየቅጥራቸው ራሳቸውን ችለው ይሰራሉ፡ ከዚህ በመነሳትም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም አንዱ የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ መጠን በማንኛውም ኃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ተቋሙም ይሁን አባላቶቹ ጣልቃ እንዲገቡ አይፈቅድም፤ ነገር ግን የሰራዊቱ አባላት የግል ሀይማኖታቸውን እንዳይከተሉ የሚከለክል ደንብም ሆነ መመሪያ አላስቀመጠም፤ ጥፋት የሚሆነው ማንኛውም መለዮ ለባሽ የስራ የደንብ ልብሱን ለብሶ ማንኛውንም ሀይማኖታዊ እንቅስቃሴ ሲያከናውን የተገኘ እንደሆነ ነው፤ እኔ ደግሞ የቤተክርስቲያን አገልግሎቴን የማከናውነው የተቋሙን ህግና ደንብ በሚፃረር መልኩ ሳይሆን ከስራ ሰዓት ውጪ በትርፍ ጊዜ በመሆኑ የሚያስጠይቀኝ ምንም አይነት ጉዳይ ሊኖር አይችልም፤ እንደማንኛውም ዜጋ የግል እምነቴን የማራመድ ነፃነት አለኝ፤ ወደ መፅሀፍ ቅዱሱ ስንመለከት ደግሞ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፀም እምነትህንና የልብ ንፅህናህን ነው እንጂ የሚፈልገው ሙያህን ወይም ስራህን ተመልክቶ አይደለም፤ በቅዱስ ቃሉ ላይ እንደተፃፈው ክርስቶስ ምድር ላይ በስጋ በሚመላለስበት ወቅት በጊዜው የነበረ አንድ የፖሊስ ሀላፊ መቶ አለቃ አገልጋዩ በንዳድ ታሞበት ሊሞትበት እንደሆነ በመግለፅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲፈውስለት ይጠይቀዋል፤ ጌታችንም እንደሚፈውስለት ነግሮት ወደ መኖሪያ ቤቱ እንዲሄዱ ይጠይቃል፤ መቶ አለቃውም ጌታ ሆይ አንተ የእኔ የበደለኛው ቤት ጣሪያ ስር እንድትገባ አልሻም፡፡ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ ሎሌዬን ዳን በለው እርሱም ይፈወሳል ብሎ በመናገሩ ምክንያት ጌታችንም በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት አላየሁም ሲል መስክሮለታል ፡፡ስለዚህ እግዚአብሔር አንተነትህን ነው የሚፈልገው እንጂ ያንተን ሙያ ወይም ያለህን ስራ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የእኔንም የልብ መሻት ወዶ ልጁ አድርጎኛልና ከአለማዊ ስራዬ ጋር በማይጋጭ መልኩ እምነቴን እስከመጨረሻው አፅንቼ እይዛለሁ፤’’ የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡

 

ደረጀ /ማርያም በቤተ ክህነት ቆይታው ከቅዳሴና ከስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ጎን ለጎን ባለው ስእል የመሳል ችሎታው የቅዱሳንን ስዕል እየሳለ ለቤተክርስቲያን ካህናት ይሰጥ እንደነበር ያስታውሰዋል፤ ይህን የስእል ችሎታውን ለማሳደግ የስእል ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር ቢያስብም ጊዜ በማጣት ምክንያት ሳይሳካለት እንደቀረና ወደፊት ግን የስእል ትምህርት ለመማር እቅድ እንዳለው ተናግሯል፡፡

 

ፖሊስነት፡-

 

ከላይ እንደተገለፀው ደረጀ /ማርያም 12ተኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ከግለሰብ ስራ ይልቅ የመንግስት ስራ ነፃነቱ የበዛ መሆኑን ስለተረዳ ለጊዜው እንደ አማራጭ አድርጎ የመረጠው ወላጅ አባቱ ይሰሩበት የነበረውን የፖሊስ ተቋም መቀላቀል ነበር፤ ይህንን እቅዱን ለማሳካት 1990 / በወጣው ማስታወቅያ መሰረት በፌደራል ፖሊስነት ተቀጥሮ የመጀመሪያ ስራውን ፍልውሀ አካባቢ በሚገኘው የፖሊስ ጋራዥ ውስጥ አደረገ፡፡

 

እስከዛሬ ድረስ በዘለቀው የፖሊስ ቤት ቆይታው ሰራዊቱን በቅንነትና በታማኝነት ያለአድልዎ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

 

በዚህ አገልግሎቱም በአለቆቹና በማህበረሱ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎለታል፤ በፖሊስ ቤት የጋዜጠኝነት ቆይታውም በርካታ ጥሩና መጥፎ አጋጣሚዎችን አስተናግዷል፡፡

 

ህዳር ወር 2005 / ጀሞ ኮንዲሚኒየም አካባቢ በአንድ የቻይና መንገድ ስራ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሙስና መንሰራፋቱ፣ ከሰራተኞቹ ደሞዝ ላይ ለመንግስት ታክስ እንደማይከፈል፣ የአስፋልት ስራ መገልገያ ማሽነሪዎች የስራና ከተማ ልማት ሰሌዳዎችን ሳያወጡ ከሁለት  አመታት በላይ ለመንግስት የሚገባ ገቢ እንዳስቀሩ፤ ከመካኒሳ ሚካኤል እስከ ጀሞ ኮንዲሚኒየም ድረስ የመንገድ አካፋይ ደሴት ላይ 200 በላይ ከባድ ገልባጭ መኪናዎችና ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች ለአመታት ያለአገልግሎት መቆማቸው ሀገር ወዳድ ከሆኑ የድርጅቱ ሰራተኞች ጥቆማ ይደርሰዋል፡፡ ደረጀም ' ሁሌ እንደሚያደርገው ጉዳዩን በሚዲያ ለመዘገብ ቦታው ላይ ደርሶ ከቀረፃ በፊት የሚደረግ መረጃ የማሰባሰብ ስራውን ይጀምራል፡፡ ትንሽ እንደቆየም በወቅቱ ከነበረ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ክትትል ኃላፊ ስልክ ይደወልለትና  መረጃ የማሰባሰብ ስራውን እንዲያቆም አለያ ግን ሊከተል የሚችለውን ነገር ማወቅ እንዳለበት ከማስፈራሪያ ጭምር  ይገለፅለታል፡፡ የደረጀ ምላሽ የነበረው ግን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ወንጀል እየተፈፀመ ዝም ብዬ ቆሜ የምመለከትበት ምክንያት የለም፤ ስለዚህ የጀመርኩትን መረጃ የማሰባሰብ ስራ እቀጥልበታለሁ የሚል ነበር፡፡

 

ይህ ከሆነ ከሁለት ቀናት በኋላ ደረጀ በወንጀል መከሰሱን የሚገልፅ መጥሪያ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ይደርሰዋል፡፡ ከዚያም ህጉን አክብሮ የጣቢያው ምርመራ ክፍል እንደደረሰ በሀሰት በተቀነባበረ መንገድ የጠበቀው ክስ መረጃዎችን ሲያሰባስብበት የነበረውን የቻይና መንገድ ስራ ድርጅት ፀሀፊዎችን በሽጉጥ አስፈራርተሀል የሚል ነበር፡፡ ደረጀ እዛው ጣቢያ አድሮ በንጋታው ፍርድ ቤት ቀርቦ ለተሰየሙት ዳኛ ስለተከሰሰበት ጉዳይ ምንም አይነት ጉዳይ እንደማያውቅና እንደውም የተባለው ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ወንጀል መፈፀሙን እሱን አጣርቶ በሚዲያ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከዛም ይህን ስራውን እንዲያቆም ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደደረሰው ሁሉንም በማስረጃ አስደግፎ ይናገራል፡፡ ዳኞቹም በሁኔታው በመገረም ሀገርን ለማዳን እየሰራ ያለ ጋዜጠኛ በሀሰት መከሰሱን አረጋግጠው በነፃ ያሰናብቱታል፡

 

ደረጀም' የጀመረውን ስራ ለመቀጠል ወደ ቦታው ሲያመራ ከመካኒሳ ሚካኤል እስከ ጀሞ ድረስ ተደርድረው የነበሩ ከባድ ተሸከርካሪዎች በሙሉ በአንድ ለሊት ተነስተው ቦታው ባዶ መሆኑን ይመለከታል፡፡ ደረጀም መረጃውን ሳይንቅ በማስታወሻ ደብተሩ መዝግቦ ወደቢሮው ይመለሳል፡፡

 

ከዚህ በኋላ ነበር ደረጀ ለምን እንደዚህ አይነት ስራ ትሰራለህ ባሉ ለጊዜው ስማቸውን መግለፅ ባልፈለጋቸው በወቅቱ አለቃው በነበሩ ሁለት የፖሊስ አመራሮች ጥርስ ውስጥ የገባው፡፡ይህ በዚህ ሁኔታ እንዳለ ወራቶች ተቆጥረው ነሐሴ 24/2004 / በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በይፋ የተገለፀው፡፡ እናም እነዚሁ አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በመንግስት ሳይገለፅ ፌስቡክ ላይ መረጃውን አስቀድሞ ያወጣው ደረጀ /ማርያም ስለሆነ በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሊጠየቅ ይገባል ሲሉ ግምገማ ያካሂዱበታል፡፡

 

በእርግጥም ደረጀ የተባለውን ጉዳይ አድርጎ ከሆነ ግምገማው የተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልፈተ ህይወት በሚዲያ ከተገለፀ በኋላ በመሆኑ ሊያስጠይቀው እንደማይገባ ከገምጋሚዎቹ ግማሾቹ በመናገራቸው በዚህም ነፃ ይወጣል፡፡

 

ደረጀ' ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ከእለታት አንድ ቀን ግን በመላ ሀገሪቱ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ ያደርግ ነበር እንዳሰበውም ሀገራዊ ለውጡ የዶክተር አብይ አህመድን አመራር ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ላይ ይፋ ሆነ፡፡ ዛሬ ላይ እነዛ ደረጀን ሲያንገላቱት ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውን እንቅፋት ሲሆኑበት የነበሩት ሰዎች አንደኛው ሰራዊቱን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅ ሌላኛዋ ደግሞ በወቅቱ ሀገራዊ ጉዳይ መነሻነት ለጊዜው መኖሪያ ቤቷ እንድትቆይ ተደርጋለች፡፡

 

አሁን ላይ ደረጀ ፖሊሳዊ ስራውን ያለማንም ጫና እና ተፅእኖ በአግባቡ እያከናወነ ይገኛል፡፡ 

 

የጋዜጠኝነት ጅማሮ፡-

 

ደረጀ ዛሬ ለደረሰበት የጋዜጠኝነት ሙያ ጥንስሱ የተፈጥሮ ስጦታ መሆኑን ያምንበታል፤ ምክንያቱ ደግሞ ገና ትምህርትን ብሎ ሲጀምር መሆኑን ያስታውሳል፡፡በ1973 / በየነ መርእድ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለ በትምህርት ቤቱ አንድ የስነፅሁፍ ውድድር ይካሄዳል በወቅቱ ደግሞ በውድድሩ አሸናፊ የሆነው የስነፅሁፍ ስራ በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ ላይ ሰንደቃላማ ከተሰቀለ በኋላ በተማሪዎቹ ፊት ይቀርባል፤ደረጀም በዚህ የስነፅሁፍ ውድድር ላይ ለውድድር የሚያቀርባቸው የፅሁፍ ስራዎች እየተመረጡለት በህፃን አንደበቱ በሚኒ ሚዲያ ያቀርባቸው ነበር፡፡

 

በትምህርት ቤት የተጀመረው የስነ-ፅሁፍ ሙያ አድጎና ጎልብቶ በሰማንያዎቹ አካባቢ የፕሬስ ነፃነት በሚል የተለያዩ የህትመት ውጤቶች እንደ አሸን በፈሉበት ወቅት ደረጀም የተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ የፅሁፍ ስራዎችን ለህትመት ያበቃ ጀመር፤ በወቅቱ ይታተሙ ከነበሩት ጋዜጦችና መፅሄቶች መካከል በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አማካኝነት በሚታተሙ ጋዜጦች እንዲሁም በምኒሊክ፣ ክብሪት፣ ትኩሳት፣ ማዶና እና ቃልኪዳን መፅሄቶች ላይ ያለምንም ክፍያ አምደኛ ሆኖ ይሳተፍ ነበር፡፡ ወደ ፖሊስ ሚዲያዎች ለመምጣቱ መሰረቱ ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ጋዜጦችና መፅሔቶች ለህትመት ያበቃቸው የነበሩ ስራዎቹ እንደጠቀሙት ይናገራል፡፡

 

1991 / ሠራዊቱ ውስጥ የውስጥ የስራ ማስታወቂያ ይወጣል፤ ይኸውም የስነፅሁፍ ችሎታ ያላቸውን አባላት በማወዳደር በፖሊስ ሚዲያዎች እንዲሰሩ ማድረግን አላማ ያደረገ ማስታወቂያ ላይ ደረጀ /ማርያም ተመዝግቦ ለፈተና ይቀርባል፡፡ በፈተናው ላይ ተሳትፈው የነበሩት አባላት 27 ሲሆኑ ፈታኝ የነበሩትም ታዋቂው ጋዜጠኛ ሻምበል ግዛው ዳኜ፣ አቶ ካሳሁን ገርማሞ (የታዋቂው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ወላጅ አባት) ታዋቂዋ ጋዜጠኛ ኮማንደር ብርቄ /ገብርኤል ነበሩ፡፡

 

ፈተናው የተሰጠው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የድሮው የፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ ሲሆን በወቅቱ በፈተናው ከተሳተፉት አባላት መካከል አንድ ሴትና ስድስት ወንዶች ብቻ ሲያልፉ በእድሜ ትንሹ የነበረው ደረጀ /ማርያም በመካከላቸው ይገኛል፡፡

 

ደረጀ በፖሊስና ህብረተሰብ ሬዲዮ ፕሮግራም የመጀመሪያ ስራው ከቴዲ አፍሮ አባት ከካሳሁን ገርማሞ ጋር ዜና በማቅረብ ነበር፤ የዚህን ጊዜ ታዲያ አለቆቹ የሆኑት አንጋፋ ጋዜጠኞች ያበረታቱት እንደነበር እና የበለጠ ስራ መስራት የሚችልበትን መንገድ ያስተምሩት ነበር፡፡ ቀስ በቀስም ከዜና አቅራቢነት ሙሉ ፕሮግራም ወደ ማስተዋወቅ ተሸጋገረ፡፡ በፖሊስ ሬዲዮ ቆይታው በርካታ ገጠመኞችን ያስተናገደው ደረጀ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን እንዲህ ይገልፀዋል፡፡

 

ጊዘው መስከረም ወር 1992 / አካባቢ ጅማ በር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ውስጥ ተረኛ አስፈፃሚ ሆኖ በሳምንት አንድ ጊዜ በሚቀርበው የፖሊስና ህብረተሰብ የሬዲዮ ፕሮግራም ዜና አንባቢ ነበር፤ ዜናው ደግሞ ’’ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ገንጂ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ አንድ የኤሌክትሪክ ምሶሶ በዝናብ አማካኝነት ወድቆ እሳት በማስነሳቱ የአካባቢው ነዋሪም እሳቱን ለማጥፋት ባደረገው ሙከራ የአንዲት ወይዘሮ ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፤ የወይዘሮዋ ህይወት ያለፈው በእርጥብ እንጨት እሳቱን ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርጉ ኤሌክትሪክ ይዟቸው መሞታቸው ታውቋል ይላል፡፡’’  ይሄን ዜና አንብቦ ፕሮግራሙ ተጠናቆ ሜክሲኮ አደባባይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ያመራል፤ እንደደረሰም ወላጅ አባቱ ሲያለቅሱ ይመለከታል ምን እንደተፈጠረ ግራ የተጋባው ደረጀ አባቱ ለምን እያለቀሱ እንዳለ ሲጠይቃቸው ቀደም ብሎ ያቀረበውን ዜና እየሰሙት እንደነበርና በዜናው ላይ በኤሌክትሪክ ተይዘው ህይወታቸው ያለፈው ወይዘሮ የወላጅ አባቱ የቅርብ ዘመድ እንደሆኑ ይነግሩታል፤ ደረጀ ምንም እንኳን ሴትየዋን ባያውቃቸውም በነገሩ መደናገጡ አልቀረም ይሁንና የራሱን ዘመድ ህልፈተ ህይወት በሬዲዮ ያረዳ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ በመሆኑ ይህ ዜና ትዝ ሲለኝ ሁል ጊዜም ሲገርመኝ ይኖራል ሲል ተናግሯል፡፡

 

በዚህ ሁኔታ እስከ ነሀሴ 1992 / በሬዲዮ ጋዜጠኝነት የዘለቀው ደረጀ በሻምበል ግዛው ዳኜ እና በካሳሁን ገርማሞ ተከታታይ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ወደ ፖሊስ ቴሌቪዥን ተዛውሮ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ በወቅቱም የፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በጣም ተወዳጅና ተመራጭ በመሆኑ በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች በተመልካች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ነበር፡፡ ደረጀም በስክሪን የማቅረብ ፈተናውን ተፈትኖ በማለፉ ወደቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት እንደተዛወረ በቀጥታ በዜና አቅራቢነትና በፕሮግራም አዘጋጅነት ላይ ነው የተሰማራው፡፡

 

በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ቆይታው አምባሳደር አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ስቱዲዮ ውስጥ በርካታ ፕሮግራሞችን ያቀረበ ሲሆን ካቀረባቸው መካከል የማይረሳቸው እንዳሉ ይገልፃል፡፡

 

ከእነዚህ መካከል ነቀምት ከተማ ተጉዞ የሰራውን የወንጀል ዘገባ መቼም ሲያስታውሰው ይኖራል፡፡ ወንጀሉ የተፈፀመው ነቀምት ከተማ ውስጥ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው ወይዘሮና የሁለት ልጆች እናት ከትዳሯ ውጨ ከአንድ ጎረምሳ ጋር ፍቅር ይይዛታል፤ ውሎ ሲያድር ፍቅራቸው እስከ ወሲብ ግንኙነት ደርሶ በየእለቱ መገናኘት በመጀመራቸው አብረው ለመኖር ይስማማሉ፤ አብረው ለመኖር ደግሞ ህጋዊ ባሏ መወገድ እንዳለበት ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው የልጆቿን አባት ከውሽማዋ ጋር ተባብራ አፍነው በመግደል ከቤቷ በረንዳ ስር ቆፍረው ይቀብሩታል፤ ጉዳዩ እንዳይነቃባትም ለጎረቤቶቿም ባለቤቷ ለስራ አረብ ሀገር ሄዷል ብላ ማስወራት ጀመረች፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ 12 ዓመት ሴት ልጇ ሁሉንም ትመለከት ነበር፡፡ ቀን ቀንን አመት አመታትን እየተካ ሲሄድ ወይዘሮዋ ከውሽማዋ ጋር ፍቅሯን መኮምኮም ትጀምራለች፤ በዚህ መሀል ሁለቱም የፈፀሙት የግድያ ወንጀል እንዳይደረስባቸው ከዚህ በፊት ባሏን ገድለው ከቀበሩበት በረንዳ አፅሙን በማውጣት በመኖረያ ቤቷ ግድግዳ ላይ በምሶሶና በማገር መካከል ከቀረቀሩ በኋላ በጭቃ በመለሰን ደብዛው እንዲጠፋ ያደርጋሉ፡፡

 

አባቷ ሲገደልባት በአይኗ የተመለከተችው ታዳጊ ህፃንነት ይዟት በወቅት ምን ማድረግ እንዳለባት ስላላወቀች ከአራት አመታት በላይ ጉዳዩን በውስጧ ይዛ ለማንም ሳትናገር አስራ ስድስት አመት ሞላት፤ በዚህን ጊዜ ነበር ድፍረቱን አግኝታ የአባቷን ገዳዮች ለህግ ለማቅረብ የወሰነችው፤ እናቷ ውሽማ መያዟንና ከውሽማዋ ጋር ተባብረው አባቷን ገድለው በረንዳ ስር መቅበራቸውን በአካባቢው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዳለች፤ የመረጃ ትንሽ የለውምና ፖሊስ ከታዳጊዋ የደረሰውን ጥቆማ ተቀብሎ የተባለውን ጉዳይ ለማጣራት ወደ ወይዘሮዋ መኖሪያ ያመራና በረንዳውን ያስቆፍራል፤ ሲቆፈር ግን ምንም አይነት ነገር አልተገኘም፤ ፖሊስ ምርመራውን በማስፋት ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር በማዋል በመስቀለኛ ጥያቄዎች ሲያጣራ ወንጀሉ እንዳይደረስባቸው የሟችን አፅም በመኖሪያ ቤቷ ግድግዳ ላይ እንደማገር ሰግስገው ጭቃ እንደለሰኑበት ያብራራሉ፤ ፖሊስም በድጋሚ ወደ መኖሪያ ቤቱ አምርቶ ግድግዳውን ሲያስፈርስ የሟችን እያንዳንዱን የሰውነት ክፍል አጥንት ካወጣ በኋ ለምርመራ አዲስ አበባ ምኒሊክ ሆስፒታል ተልኮ ውጤቱ ሲደርሰው ምርመራውን አጠናቆ ፍርድ ቤት በማቅረቡ ወንጀለኞቹ እያንዳንዳቸው 18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ይላል ዘገባው፡፡

 

ደረጀ በጋዜጠኝነት ቆይታው መልካምና መጥፎ ገጠመኞችን ማስተናገዱ አልቀረም፡፡ ጊዜው 1997 / በመላ ሀገሪቱ በመንግስትና በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል በሚነሱ ግጭቶች ሳቢያ ከፀጥታ አካሉም ይሁን ከተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ህይወት ይጠፋ ነበር፤ መሰል ሁኔታዎችም በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ይስተዋል ስለነበር ይህን ሁኔታ ለመዘገብና ለሚዲያ ለማብቃት የፌደራል ፖሊስ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ እና ጅግጅጋ አካባቢ በማምራት የተለያዩ ዘገባዎችን በማጠናቀር ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ፡፡ ከዚህ የጋዜጠኞች ቡድን ውስጥ ደረጀ /ማርያም የሚገኝበት ሲሆን ስራቸውን ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ሲያመሩ ሜኤሶ የተባለ አካባቢ ሲደርሱ የገጠማቸውንና ህይወት እስከሚያሳጣ ያደረሳቸውን ጉዳይ ያስታውሳል፡፡

 

በወቅቱም ጋዜጠኞቹ ሚኒባስ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተጠቀወመው ጉዟቸውን ጀምረዋል፤፡ ሰዓቱ ደግሞ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ስለሆነ መንገድ ላይ ላለማደርና አዲስ አበባ በቶሎ ለመድረስ ያሰበው ሹፌር በፍጥነት እያሽከረከረ እያለ ሜኤሶ አካባቢ ሲደርስ አንዲት ፍየል ዋናው መንገድ ላይ ትገባበትና ይገጫታል ይሄን ተከትሎም ከፍተኛ የሆነ የተኩስ እሩምታ መኪናዋ ላይ ይወርዳል ሁሉም ጋዜጠኞች እራሳቸውን መከላከያ ሽጉጥ ያላቸው ቢሆንም በወቅቱ አማራጭ ያሉት በአስቸኳይ ከተኩሱ አካባቢ መራቅ ስለሆነ አሽከርካሪው የተቻለውን ያህል እንዲያደርግ ሁሉም ጮኸበት አሽከርካሪውም የተባለውን ተቀብሎ ነፍሱ የመራውን ያህል ተጉዞ አዋሽ 40 ፍተሻ ኬላ ላይ ሲደርስ የፌደራል ፖሊስ አባላት ያሉበት አካባቢ በመቆም ጉዳዩን ያስረዳሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ግን መኪናዋ በግምት 160 ጥይት በላይ ተተኩሶ የመኪናው አካል ወንፊት ቢሆንም ሹፌሩን ጨምሮ በተሸከርካሪው ውስጥ የነበሩት ስምንት ሰዎች ምንም አይነት ጭረት እንኳን ሳይደርስባቸው በህይወት መገኘታቸው ነው፡፡

 

ማስታወቂያ ሚኒስቴርና አቶ በረከት ስምኦን፡-

 

ደረጀ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት በሳምንት ቢያንስ 3 ጊዜ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቅፅር ግቢ መገኘት ግድ ይለዋል፤ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ጋር የህንፃው መወጣጫ አሳንሰር ፊት ለፊት ሁለቱም ሊፍት ይጠባበቃሉ፤ በነገራችን ላይ አቶ በረከት ስምኦንን ከሌሎች ባለስልጣናት የሚለያቸው ነገር ቢኖር ለምን እንደሆነ ባይታወቅም በአብዛኛው ያለ አካል ጠባቂ ወይም አጃቢ መንቀሳቀሳቸው ነው፤ የዛን ጊዜም ሊፍት ሲጠብቁ በነበረበት ወቅት ምንም አይነት አጃቢ አጠገባቸው አልነበረም፤ ሊፍቱ 13 ፎቅ ወደምድር ቤት ወርዶ ሲቆም አቶ በረከት ደረጀና ሌላ አንድ ጋዜጠኛ ብቻ ሊፍቱን ተጠቅመው ወደላይ መውጣት ይጀምራሉ፤ በመሀል ደረጀ የፖሊስ የደንብ ልብስ መልበሱን ያስተዋሉት ሚኒስትሩ ’’ እንዴት ነህ ስራ እንዴት ነው;’’  ብለው ይጠይቁታል፡፡ ደረጀም ’’በጣም ጥሩ ነው’’  ብሎ አፀፋዊ ምላሽ ከሰጠ በኋላ አስከትሎ ’’ እንዴት ነህ አንተስ ስራውን ለመድከው መቼስ ከጅማ በር ስቱዲዮ እዚህ ያለው ስቱዲዮ ጥራት ያለው ይመስለኛል;’’  ሲል አቶ በረከት ስሞንን ይጠይቃቸዋል፤ በጥያቄው ግርምታ ውስጥ የገቡ የሚመስሉት ሚኒስትሩ ’’ እውነትህን ነው የቴሌቪዥን ጣቢያው ስቱዲዮ ይሻላል’’  ብለው በፈገግታ ምላሽ ይሰጡታል ደረጀም መውረጃው ላይ ሲደርስ አቶ በረከትን ’’ በል እንግዲህ ጠንክረህ ስራ በርታ’’  ብሎ ከሊፍቱ ሲወርድ አብሮት የነበረው ጋዜጠኛም ተከትሎት ከሊፍቱ ይወጣና ደረጀን አስቁሞ ’’ ደሬ ለመሆኑ አሁን ማንን እንዳናገርክ አላወክም እንዴ ክቡር ሚኒስትር በረከት ስምኦን ናቸው እኮ’’  ሲለው ደረጀ ባለበት ድርቅ ብሎ ቀረ ሚኒስትሩን እንዳላወቃቸውና በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ ስላገኛቸው ያንን ሁሉ ጥያቄና መልስ ሲያወጋቸው የነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መስለውት ስለነበር ነው፡፡

 

እሳቸውም ቢሆኑ በቃላት ልውውጡ ወቅት ደረጀ እንዳላስተዋላቸው በመረዳታቸው ፈገግታ እያሳዩት ነበር ሲያናግሩት የነበረው፡፡ ደረጀ ሚኒስትርን የሚያክል ያውም የሀገሪቱን ዋና ሰው እንደ ተራ ጋዜጠኛ ስራውን ለመድከው እያለ ማዋራቱ በወቅቱ ቢያስደነግጠውም ዛሬ ላይ ግን ያደረገው ድርጊት ፈገግ አሰኝቶት ለባልንጀሮቹ የሚያጫውተው ወግ ሆኖ ቀርቷል፡፡

 

መቼም አቶ በረከት ስምኦንም ማስተዋሉን ከሰጣቸው ይህንን ገጠመኝ ባሉበት ቦታ ሆነው ማስታወሳቸው አይቀርም፡፡

 

ደረጀ በጋዜጠኝነት ህይወቱ ውስጥ እጅግ የሚያደንቃቸው ጋዜጠኞች በርካታ ቢሆኑም ዳሪዎስ ሞዲ፣ አለምነህ ዋሴ፣ የኔነህ ከበደ፣ ግዛው ዳኜ፣ ብርቄ /ገብርኤል፣ ሙሉዬ ፋንታሁን፣ ብርትኳን ሀረገወይን፣ ዘላለም ቱሉ እና ለሌሎችም ከፍተኛ አድናቆት እንዳለው ይናገራል፡፡

 

ሙዚቃ ህይወቴ፡-

 

ሙዚቃ ድምጸቱ ልዩ ዉበት ያለውና በስው ልቡና ውስጥ ሰርስሮ ሊገባ የሚችል ኃይል አለው። ሙዚቃን አላዳምጥም የሚል ሰው ምናልባትም በከፍተኛ ደረጃ መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ የገባ ሊሆን ይችላል፡፡ነገር ግን ሙዚቃ እንኳንስ ሰብአዊ ፍጡርን ይቅርና ምንም የማያውቁትን እንስሳት እንኳን የማነቃቃት ሀይል አለው፡፡ደረጀም ለሙዚቃ ትልቅ አክብሮት አለው በሙዚቃ ፍቅርን መግለፅ፣ ተሞክሮን ማስተላለፍ፣ ስሜትን መግለፅ፣ የሀገር አንድነትንና ፍቅርን መስበክ ብቻ ምኑ ቅጡ ሁሉንም ነገር መግለፅ ይቻላል ብሎ ያምናል ፡፡ ታዲያ ሙዚቃ ሲባል በአንድ ሳምንት ውስጥ የይድረስ ይድረስ ተውተፍትፎ ተሰርቶ በሁለት ቀናት ውስጥ የሚሰለቹትን ሳይሆን በጥናትና በጥራት ተደግፈው ታስቦባቸው ከአንድ አመት በላይ ታሽተው ለተሰሩ ቆየት ላሉ ሙዚቃዎች ቦታ ይሰጣል፡፡

 

በተለይ እስከ 70 / ድረስ ለተሰሩ ቆየት ላሉ የእንግሊዝኛም ሆነ የአማርኛ ሙዚቃዎ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ስላለው የተለያዩ በርካታ የቪዲዮ እና የኦዲዮ መረጃዎችን እስከማስቀመጥ ደረጃ የደረሰው ደረጀ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ የተለያዩ የጥንት ድምፃውያንን አፈላልጎ በማግኛት ኢንተርቪው አድርጎ ታሪካቸውን ህዝብ እንዲያውቀው አድርጓል፡፡ከእነዚህ ውስጥ ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ፣ ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ፣ግርማ ነጋሽ፣ ታደለ በቀለ፣ ቱቱ ለማ፣መለሰ ቦንገርና ለጊዜው የማያስታውሳቸውን የጥበብ ሰዎች በቴሌቪዥን ጭምር ታሪካቸውን አስተዋውቋል፡፡

 

ደረጀ እነዚህን ሁሉ ተግባራት ቢያከናውንም በተለየ ሁኔታ ግን ልዩ ቦታ የሚሰጠው ለድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ነው፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ አርቲስቱ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቁን ስፍራ የያዘና በርካታ የማይሰለቹ ዘመን ተሸጋሪ ስራዎችን በመስራቱ ነው፤ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ በበርካታ የኪነ ጥበብ አፍቃሪዎች ብዙ የተባለለት ቢሆንም ደረጀም ድምፃዊውን ለማስተዋወቅ ቃለምልልስ አድርጎ የተለያዩ የህትመት ስራዎች ላይ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

 

በአንድ ወቅት የድምፃዊው እግር ከመቆረጡ በፊት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የእግሩ መቆረጥ ወሬ በአሉባልታ መልኩ መዛመቱን የተመለከተው ደረጀ በጉዳዩ በመቆጨት አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ ወደሚገኘው የድምፃዊው ነዳጅ ማደያ ድረስ በመሄድ ወቅታዊ ቃለምልልስ በማድረግ በጊዜው ይታተሙ በነበሩ ጋዜጦች ላይ እውነታውን በማውጣት ይወራ ለነበረው አሉባልታ ትክክለኛውን መረጃ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

 

ሌላው ይቅርና የፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲተላለፍ የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ከተለቀቀ የእለቱ የፕሮግራም መሪ ደረጀ /ማርያም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለጥላሁን ገሠሠ ካለው ፍቅር የተነሳም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴያትር የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ሲያከብር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቀርጾ የተቀመጠውን አይከዳሽም ልቤ የተሰኘውን ሙዚቃ ቪዲዮ በመውሰድ ይኸው ሙዚቃ 1966 ዓም በድምፅ ብቻ ተቀርፆ ላይብረሪ ውስጥ በመቀመጡ ይህንን ድምፅ ብሄራዊ ቴያትር ከተቀረፀው ምስል ጋር ለዛውም በአናሎግ ሲስተም ሊፕ ሲንኩን በመጠበቅ ቆየት ባለው ጊዜ የተዘፈነ እንዲመስል አድርጎ ኤዲቲንጉን ጨርሶ ሙዚቃውን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድምፅ ወምስል ላይብረሪ በማስረከቡ በወቅቱ ከነበሩት የስራ ሀላፊዎች አድናቆትና ምስጋና ተችሮታል፡፡ ሙዚቃው አሁንም በቴሌቪዥን ጣቢያው እየተለቀቀ ይገኛል፡፡

 

ደረጀ /ማርያም ለድምፃዊው ያለውን ክብር ለመግለፅም ጥላሁን ገሠሠ ከማረፉ አንድ አመት አስቀድሞ ድምፃዊውን የሚያሞግስ ግጥም በመፃፍና ዜማውን ሌላ ሰው እንዲያዘጋጅለት እንዲሁም የስራ ባልደረባው ድምፃዊ ዳንኤል ዳምጠው ሙዚቃውን እንዲጫወተው በማድረግ በኢቲቪ የድምፅ ላይብረሪ ውስጥ በክብር እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡

 

የፌደራል ፖሊስ ትራፊክ፡-

 

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በመላ ሀገሪቱ እየደረሰ ያለው የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ስላሳሰበው ይህንን አደጋ ለመከላከልም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የትራፊክ ዲቪዥን በመቋቋም ከሰራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች 53 አባላትን በመመልመል በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ወራት ስልጠና በመስጠት አስመርቆ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

 

2006 / በተሰጠው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩት አባላት መካከልም / ደረጀ /ማርያም አንዱ ስለነበር ከጋዜጠኝነቱ ሙያ ጎን ለጎን የትራፊክ ቁጥጥር ስራውን በኃላፊነት ቦታ ላይ ተመድቦ መስራት ይጀምራል፡፡

 

የፌደራል ፖሊስ ትራፊክ ከተቋቋመበት አላማ አንፃር በሀገሪቱ በሚገኙ የፌደራል ዋና ዋና መንገዶች ላይ የትራፊክ አደጋ ምርመራና ቁጥጥር ማድረግ ስለሆነ አባላቱ በተመረቁ ማግስት ነው በዘመናዊ የትራፊክ ተሽከርካሪዎችና በዘመናዊ የፍጥነት መቆጣጠሪያና የአልኮል መፈተሻ መሳሪያዎች በመታገዝ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ደረጀም የትራፊክ ቁጥጥር ተሽከርካሪ በመረከብ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አምስቱም መውጫ በሮች ላይ የቁጥጥር ስራውን ይሰራ ነበር፡፡

 

በትራፊክ ክፍል ቆይታውም በአገሪቱ የሚገኙ ትራፊኮችን የሙያ ክህሎት ለማሳደግ በተለይ በፍጥነት የሚያሽከረክሩትንና ጠጥተው የሚያሽከረክሩትን ለመቆጣጠር የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር እና የአልኮል መጠጥ መፈተሻ መሳሪያዎች አጠቃቀምን በተመለከተ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅና በደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች በመጓዝ ለትራፊክ አባላት ስልጠና የሰጠበት ሁኔታ አለ፤

 

እንዲሁም በአፍ ኤም አዲስ 97.1 አውቶሞቲቭ የመንገድ ደህንነት የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የፌደራል ፖሊስ ተቋምን በመወከል ለተከታታይ አምስት አመታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በቀጥታ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፤

 

ከዛ በኋላ ባለው ጊዜም በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን አገልግሏል፤

 

ደረጀ /ማርያም በትምህርት አለም ቆይታውን ከዩኒቲ ዪኒቨርስቲ በህግ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ ሲሆን ከዛ በሁዋላ ግን ፕሮፌሽናል ፖሊስ ሆኖ ለማገልገል ካለው ፍላጎት በመነሳት ለአራት አመታት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ በፖሊስ ሳይንስ CRIME PREVENTION የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

 

ኢንስፔክተር ደረጀ /ማርያም በአሁኑ ወቅትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን በመወከል  መንግስትና ህዝብ የጣሉበትን ሀገራዊ ኃላፊነቶች ለመወጣት ደቡብ ሱዳን ውስጥ በፖሊስ አድቫይዘርነት እያገለገለ ይገኛል፡፡

 

መዝጊያ፤ ደረጀ ገብረማሪያም በአንድ በኩል ፖሊስ ነው፡፡ በሌላ ደግሞ ጋዜጠኛ ፡፡ 50 አመት በላይ የዘለለ ታሪክ ያለው የሀገራችን የፖሊስ ጋዜጠኞች ታሪክ በርካታዎችን አፍርቷል፡፡ ፈታኝ በሆነው በዚህ ሙያ ውስጥ ህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደ ግዛው ዳኜ፤ ካሳሁን ገርማሞ፤ የምወድሽ በቀለ ብርቄ ወልደገብርኤል የመሳሰሉትን የመሰሉ ባለሙያዎች ብቅ ብለዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ደረጀ ገብረማሪያም ነው፡፡ ደረጀ ከላይ ከተጠቀሱት ባለሙያ በእድሜ አነስተኛ ግን ተከታይ ሆኖ ሙያውን ያሳደገ በመሆኑ የሚኖረው ታሪክ ጉልህ ነው፡፡ ደረጀ ገና በወጣትነቱ የሚድያ ፍቅር ያደረበት በመሆኑ ይህን ፍላጎቱን አሳካ፡፡ በሀገራችን ፖሊስና ርምጃው ጋዜጣ ፖሊስና ህብረተሰብ የቲቪ መሰናዶ ለህብረተሰቡ ትልቅ ሚና ማበርከታቸው አይቀርም፡፡ በተለይ ህዝቡ ከወንጀል እንዲጠበቅ ለማድረግና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ደረጀ በሙያው ትልቅ ስራ አከናውኗል፡፡ የሚከበር ሙያ ነው-

 

ፖሊስነት፡፡ ደረጀም ይህን ክቡር ሙያ ይዞ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ታሪኩን አንብበን እንደምንረዳው በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ ይገኛል፡፡ ከደረጀ ቀደም ብለው የፖሊስ ጋዜጠኝነት ስራን አሀዱ ያሉት ታሪካቸው የምንሰራላቸው ሆኖ ደረጀም በህዝብ እንዲታወቅ እንሻለን፡፡ አንድ ታሪክ አይቷል፡፡ ብዙ ሰው ሊያይ የማይችለውን ነገር አይቷል፡፡ በምርመራ ስራውም ብዙ የሀገራችን ሰዎች የፈጸሙትን ታዝቧል፡፡ ይህ ታሪክ ነው፡፡ ነገ ሲነበብ የኢትዮጵያ ፖሊስ ጋዜጠኞች ታሪክ ተብሎ በሰፊው ይወሳል፡፡ ደረጀ ታሪኩ በዚህ ብቻ አያቆምም፡፡ ገና ብዙ ከሀገሩ ያበረክታል፡፡ ሀገሩን በጣም የሚወደው ደረጀ ከዚህ በላይ ለሀገሩ ማበርከት ይፈልጋል፡፡

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች