14 ዳግማዊ አሰፋ    Dagmawi Assefa

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የባለሙያዎችን  ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ በዚህ የዊኪፒዲያ ገጽ እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ባለሙያ እና ፀሀፊው ዳግማዊ አሰፋ ይጠቀሳል፡፡ ዳግማዊ የደረሰበትን ትልቅ ፈተና ተቋቁሞ የጽናት ተምሳሌት መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡ ግለ-ታሪኩ ለብዙዎች አስተማሪ በመሆኑ ታነቡት ዘንድ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ቤርሳቤህ ጌቴ ትጋብዛለች፡፡

 

         የልጅነት ደማቁ ትዝታ

 

ዳግማዊ አሰፋ ዴቢሶ፣ በቀድሞ አርሲ ክፍለ ሀገር በሚባለው አሰላ ከተማ ጥር 11/1981 . ተወለደ፡፡

 

አባቱ የመንግስት ሰራተኛ ከባድ መኪና አሽከርካሪ ሲሆኑ እናቱም የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ከቤተሰቡ  አምስት ልጆች  ሁለተኛ ልጅ ነው፡፡

 

እስከ 10 ዓመቱ ድረስ እንደማንኛውም ልጅ በጨዋታና በቡረቃ ቢያድግም 10 ዓመቱ በኋላ ግን ጨዋታውን ገታ በማድረግ ወደ ቤተክርስቲያን መሄዱን አዘነበለ።

 

ወደ ቤተ እምነቱ ሲወሰድ በድቁና እንዲያገለግል ታስቦ ይሁን እንጂ እርሱ ግን ወደ ዝማሬውና ቃሉን ወደማንበብ አደላ፡፡ በዛው ደግሞ በድራማ ማገልገል ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በመጽሀፍ ቅዱስ ንባብና በስብከት አገልግሎት እራሱን አሳደገ። የልጅነት ደማቁ ትዝታው ይህ የአገልግሎት ጊዜው ነበር።

 

              ህግ ለመማር መረጠ

 

በህፃን እድሜው ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ከአሰላ ወደ ሀዋሳ በመምጣቱ መደበኛ የቀለም ትምህርቱን በዛው በሀዋሳ አድቬንቲስት /ቤት ነበር የጀመረው ፡፡በመቀጠል በማውንቶሊቭ  /ቤት 5 እስከ 8 ተማረ፡፡ 8 ሚኒስትሪ ውጤቱ 99.86 ነበረ።

 

9 ክፍል እስከ 12 ክፍል ያለውን የትምህርት ጊዜውን ደግሞ በታቦር መካነኢየሱስ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። የዩንቨርስቲ ትምህርቱን ህግ ለማጥናት ነበረ ፍላጎቱ። ''ቀድሜም ሶሻል ተማሪ ለመሆን የመረጥኩት ህግ ለመማር ነበር፡፡ ከዛ ህግ መረጥኩ፡፡ የመረጥኩት መቀሌ ዩንቨርስቲ ነበር፣ ቀጥሎ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መቀሌን አይቼው ነበር፡፡ መቀሌ በጣም ጥሩ አለማቀፋዊ አቋም ያየሁበት ስለነበር ነው የመረጥኩት፡፡ የደረሰኝ ግን ዲላ ዩንቨርስቲ ነበር፡፡ የመረጥኩት ትምህርት ህግ ነው፡፡ ህግ ተሰጥቶኛል፡፡ ቀጥታ ህግ ትምህርት ለመማር ዲላ ገባሁ'' ይለናል፡፡

 

          በጥሩ ውጤት ተጠናቀቀ

 

ከዲላ ዩኒቨርስቲ ወደ ሀዋሳ ለመቀየር ይፈልግ ነበረና መንገዶችን ሲፈልግ ውጤቱ 3.25 በላይ የሆነን ተማሪ ብቻ እንደሚቀበሉና ፈቃደኛ ከሆኑ ብቻ እድሉ እንደሚኖረው ተረዳ፡፡ በትጋት ማጥናት ነበረበት፡፡ ይህንንም አደረገው፡፡ 2 ሴሚስተር ሲጠናቀቅ 3.6 GPA በማምጣት ያሰበው ተሳካ፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲንም ተቀላቀለ፡፡ 5ዓመቱ ቆይታም 3.6 ውጤት ተጠናቀቀ።

 

''እርግጥ እስከ 7 ክፍል ድረስ መካከለኛ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ምክንያቴ የነበረው አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ቸርች ነበር፡፡ ሌላ ቦታ  ተልኬ እራሱ ሳላውቀው ወደቸርች እግሬ ያቀና ነበር፡፡ አባቴ በጣም ይቆጣኝ ነበር፡፡ 8 ክፍል ስገባ ከአባቴ ጭቅጭቅ መላቀቅ ስለፈለግኩ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ 9 ክፍል 6 ስወጣ አባቴ በቃ ከዛ በኋላ ተወኝ፡፡ አይተኸዋል መስራት እንደምትችል፤ አሁን የራስህ ምርጫ ነው ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ስለትምህርት አናወራም በማለት ተወኝ፡፡ እኔም ትምህርቴን አጥብቄ መያዝ ቀጠልኩ''፡፡

 

የእርሱ አርአያ አባቱ ናቸው መኪናቸውን እያሽከረከሩ ሲመጡ ጥሩንባ ሲያጮሁ ልጆቹን ሁሉ ወስደው ሲያዝናኑ በቃ ሁሉ ነገራቸው ይማርከው ነበረ፡፡ እናም ልጆች ሁሉ ዶክተር ኢንጂነር እያሉ የወደፊታቸውን በምኞት በሚያስቀምጡበት እድሜ እርሱ ግን ሾፌር መሆንን ይሻ ነበር፡፡ ይህ ምኞቱ በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም ለእርሱ ግን የስራዎች ሁሉ ጥግ ሹፍርና ይመስለው ነበረ፡፡ ሆኖም ይህ መሻቱ በአንድ አጋጣሚ ተቀየረ፡፡ በአካባቢያቸው የተከሰተ የወንጀል ድርጊትን ተከትሎ በፍርድ ስርዓቱ የመታደም እድል የገጠመው ዕለት የልጅነት ምኞቱን የቀየረ ሌላ ፍቅር አሳደረበት። አንድም የፈጣሪ ያህል የሚፈሩት ዳኞች እንዲሁም ወንጀሉ ተፈፅሟል እና አልተፈፀመም የሚለው እውነት የመሰሉ የክርክር ነጥቦች እውነትን የመግለጥ ፍላጎት አሳደረበት፡፡ እናም በዛ በለጋ እድሜው ህግ አዋቂ የመሆን  መሻቱን አንድ ብሎ ጀመረ።

 

  የበጎ አድራጎት አገልግሎት

 

የዩኒቨርስቲ ህይወቱ ብዙም ፈታኝ እንዳልሆነበት የሚያነሳው  ዳግማዊ አሰፋ             በማንበብና ነገሮችን ቀድሞ ለማገናዘብ በመቻሉ ብዙ ወጣቶች የሚፈተኑበትና ለመውደቅ ምክንያት የሚሆናቸው የሱሰኝነትም ሆነ የተቃራኒ ፆታ ጉዳይ ለእርሱ ችግር አልነበሩም። በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የታዳጊነት ህይወቱን ቢያሳልፍም ይከተለው የነበረው መርህ ግን ''ሁሉ አቀፍ መሆን'' የሚል ነበረና በብዙ ነገሮች ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ በተለይ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ኳስ፣ዋና፣ ግራውንድ ቴኒስና  ቴብል ቴኒስ ጨዋታ ላይ አዘውትሮ ይሳተፋል ፤ሞተር ሳይክልና መኪና ያሽከረክራል፡፡ የሀገሪቱን  የፓለቲካ እንቅስቃሴም በንቃት ይከታተላል። በዩኒቨርስቲ እራሱን እንዲገራ ያደረገው በአገልግሎቶች ላይ መሳተፉም እንደነበረ ያምናል።''ቸርች አለ፣ ፀበል አለ እዛ ሄዳለሁ፡፡ እዚህ የሚያውቁኝ ሰዎች ለዲላ ቤተክርስቲያን ነግረው ነበረና ቤተክርስቲያን ጉባኤ ማገልገል ጀመርኩ፡፡ በቤተክርስቲያን አገለግል ነበር፡፡ ሀዋሳ ከገባሁ በኋላ ዩንቨርስቲው ለማህበረሰቡ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ከክላስ ውጭ በሳምንት 3 ቀን ነፃ የህግ ድጋፍ እሰጥ ነበር፡፡ ከዛ ደግሞ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲም ነፃ የህግ ድጋፍ ከፈተ፡፡ እዛም ሄጄ ተቀላቀልኩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ  በሳምንት 2 ቀን ነፃ የህግ ድጋፍ እሰጥ ነበር፡፡ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ነበሩ የሚሰሩት፡፡ እኔ ፈልጌ ጊዜዬን ሁሉ እነሱ ላይ አጠፋ ነበር፡፡ ሌላም አብሮኝ የሚሰራ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ አመቱ ሲጨረስ ወደ 2 የሚጠጋ ሰው በነፃ እንዲለቀቅ ረድተን፣ ከአስር በላይ ሰው ቅጣት እንዲቀንስላቸው አግዘን፣ ከቤተሰብ ተገናኝተው የማያውቁትን ከቤተሰብ እንዲገናኙ አግዘን እንደነበረ አስታውሳለሁ''፡፡  ይላል፡፡

 

በተማሪነት ጊዜው በበጎ ፍቃድ ሲሰራ እና ጥቂት ለማይባሉት ሞያዊ ድጋፍ ሲያበረክት የነበረው  ዳግማዊ  ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ስራው አለም ሲቀላቀል ግን አንዳንድ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚያያቸው ያልተገባ ድርጊትና የፓለቲካ ተፅእኖ በፍርድ ቤቶችም ላይ ተጭኖ ሲያገኘው ወደኋላ ማለትን መረጠ፡፡ ይልቁን እንደ አርአያ ከሚያየው የተወደደ ጓደኛው ዳንኤል ዋለልኝ ጋር በመሆን ስራ ቢጀምርም ወደ አስተማሪነት እና ወደ ጥብቅናው እንደሚያደላ ግን ያውቀው ነበረ ፡፡በኋላም በተማሪነት ግዜው የጀመረውን የህግ ድጋፍ መስጠት እና አነቃቂ ንግግሮችን በተለይ ደግሞ በቀና ስነልቦና ዙሪያ አስተማሪ ተሞክሮዎችን በማቅረብ ለብዙዎች በፅናት መቆም አጋዥ መሆኑን አጠናክሮ ቀጠለ።

 

          ከባዱ ፈተና

 

በህይወቱ ላይ የገጠመው ነገር ለማመን የሚከብድ እጅግም አሳዛኝ ጉዳይ ነበረ፡፡ ለእውነት እና ለሙያቸው ታማኝ ሊሆኑ የቆረጡት ሁለቱ ጠበቃዎች( ጓደኛው ዳንኤል ዋለልኝ እና ዳግማዊ) በማጭበርበር እና በወንጀል በገነነ ግለሰብ አማካኝነት ከጉዟቸው ተሰናከሉ። የጉዳዩ መነሻ ኢቭኒንግ ስታር የተባለ ሆቴል ሽያጭ ነው። 35 ሚሊየን ብር የተሸጠው የዚህ ሆቴል ሻጭ እና ገዢ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሻጭ ለመንግስት ሊያስገባ የተገባውን ብር አልከፍልም በሚል ገዢን ባለእዳ በማድረጉ ፍትህ ፍለጋ ጠበቃ ያነጋግራል ፡፡እነ ዳንኤልም ጉዳዩን ተቀብለው በሚያጣሩ ግዜ ግለሰቡ ከዚህ በፊት የመንግስትን ግብር ባለመክፈል ወንጀል ተጠይቆ 12 ዓመት እስር ተፈርዶበታል፡፡ ነገር ግን ሳይያዝ በከተማው ውስጥ በነፃነት ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ዳንኤል እና ዳግማዊ በያዙት ጉዳይ መሰረት የፍትሀብሄር ተጠያቂነት እንደሚነሳበት ያረጋግጣሉ ፡፡ታድያ ይህ ሲረጋገጥ ግለሰቡ 500 ሺህ ብር ጉቦ ከፍሎ ጉዳዩን እንዲዘጉት ይጠይቃል ይለምናል ፡፡በእንቢታቸው ሲፀኑም ወደዛቻ ተሻገረ፡፡

 

ይህም አልሆን ሲለው በመስከረም 28/2007 . ከጠዋቱ 2:30 ሊይ በስራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ በቅድሚያ ዳንኤል ዋለልኝን ተኩሶ ከገደለ በኋላ ዳግማዊ እየተከተለው መሆኑን ሲመለከት እርሱንም አንገቱ ላይ ተኮሰበት ወደቀም  የገጠመው ጉዳት ከሞት አፋፍ አደረሰው፡፡ በብዙ ስቃይ ተረፈ ሆኖም ለአካል ጉዳት ግን ዳረገው። ለእውነት የቆሙት ሁለቱ ሀቀኛ ጠበቆች ለቆሙለት እውነት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ሞት እና የአካል ጉዳት። ዳግማዊ ይህ ለማመን የሚከብድ ገጠመኝ ግን ከስራው አላስቆመውም እንዲያውም አጠናክሮ ቀጠለበት ቢሮ ከፍቶ ለተጎዱት መቆምን እንዲመርጥ ሆነ እንጂ ጉዳቱ ለእውነት ጀርባ እንዲሰጥ አላደረገውም።

 

     ዳግማዊ የጽናት ተምሳሌት

 

ከራሱ ህይወት ተሞክሮ እና መሰናክሎች በመነሳትም መጽሀፍ ለማዘጋጀት የበቃው  ጠበቃ እና ፀሀፊ ዳግማዊ አሰፋ 2012 . አዲስ ህይወትን 2013 ደግሞ ከማዕዘኑ ወዲያ የተሰኘ እውነተኛ ታሪክን መሰረት ያደረገ መፅሀፍ ነው ለንባብ ያበቃው። ከዚህ በተጨማሪ በህግ ስራው ከራሱ ውጪ 2 ሰዎች የስራ ዕድል በመፍጠር ፣የማማከር ስራ፤ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ እንዲሁም ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎም ለፍርድ ቤት፣ለኤንባሲ የልደት፣ ከወንጀል ነፃ፣ የጋብቻና መሰል ዶክመንቶችን ይተረጉማሉ፡፡

 

''አሁን በጣም ወደ ጽሁፍ ስራዎች ላይ የመስራት ሀሳብ ነው ያለኝ፡፡ 2ቱን መፅሐፍ ከፃፍኩ በኋላ ያየሁት ነገር ሰው ከተሞክሮ በጣም ይማራል፡፡ ስለሆነም ወደዛ እንዳዘነብል አድርጎኛል፡፡ በራሴ የህይወት ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ህይወት መነሻ በማድረግ እፅፋለሁ፡፡  የይቅርታ ሰዎች አሉና የእነሱን ሰዎች ታሪክ መፅሐፍ በማድረግ የማውጣት እቅድ አለኝ፡፡ የይቅርታ አርዓያ እንዲኖሩን የማድረግ ሀሳብ በውስጤ አለ''፡፡

 

ወንጀል ነክ ልብወለድ የመፃፍ፣  ረቂቅ የወንጀል ድርሰቶችን መፃፍ አሳብ አለኝ፣ ህይወት ላይ መስራት የወደፊት እቅዶቹ ናቸው። በህግ ድጋፍ በተይለም ገንዘብ የሌላቸውን የማማከር ስራው የሚቀጥል ነው፡፡

 

መዝጊያ፣ ይህ የመዝጊያ ሀሳብ የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላትን ሀሳብ የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

 

ዳግማዊ አሰፋ ገና በወጣትነቱ ታላቅ ህልም የሰነቀ ነበር፡፡ በልጅነቱ ጎበዝ ተማሪ ስለነበር ውጤትን በቀላሉ ነበር ያገኝ የነበረው፡፡ ዳግማዊ አሰፋ ህግ ለመማር ሲያስብ አንድ ለውጥ ለማምጣት በማለም ነበር፡፡ በተለይ ፍትህ ለማስፈንና እውነተኛ የህግ አገልግሎት በመስጠት ራእይ ሰንቆ ነበር፡፡ ዳግማዊ፣ 7 አመት በፊት በአንዲት ቀን በአጋጣሚ በተተኮሰበት ጥይት ለትልቅ አደጋ ተጋለጠ፡፡ አደጋው ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር፡፡ የዳግማዊ አሰፋ ቤተሰቦች ተደናገጡ፡፡ ዳግማዊም ከትልቅ ህልሙ ወደ ኋላ የቀረ መስሎት ነበር፡፡ መጀመሪያ አካባቢ አዘነ፡፡ ነገር ግን በማዘን የሚመጣ ነገር እንደማይኖር ሲረዳ ራሱን ለማጽናት ታላቅ ጀግና ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ፡፡ እንዳሰበውም የጽናት ተምሳሌት ለመሆን  ተነሳ፡፡ የደረሰበትን ችግር ረስቶ ሌሎችን ማነቃቃት የእርሱ አይነት ተመሳሳይ ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳት ጀመረ፡፡ ይህን በማድረጉ ዳግማዊ ይደሰታል፡፡ ምናልባት ፈጣሪ ያተረፈኝ ለዚህ አላማ እንደሆነስ ምን ይታወቃል ብሎ ያስባል፡፡ ዳግማዊን የጽናት ተምሳሌት ልንለው እንደፍራለን ፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች በጽናት ቆመው አንድ ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉ ሰዎችን ያበረታታል፡፡ ታሪካቸው ከአዲሱ ትውልድ መዝገብ ላይም መስፈር አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ዳግማዊ ከዚህ ታላቅ መዝገብ ላይ ታሪኩ መስፈሩ ስለሚገባው ነው፡፡ መጽናት ለተሳናቸው ታሪኩ ብዙ ያስተምራል፡፡/ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ተሰናድቶ የቀረበ ነው፡፡ ህይወት ተረፈ ደግሞ ለዚህ ጽሁፍ መሳካት ትልቅ እገዛ አድርጋለች፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የፌስ ቡክ ገጽ  ላይና የዊኪፒዲያ ገጽ  ላይ ዛሬ ጥቅምት 24 2014 ፖስት የተደረገ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት  ፖስት ይደረጋል፡፡

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች