137. ተፈራ ሻውል - Teferra Shiawl- Kidanekal
አምባሳደር ተፈራ ሻውል
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኑኬሽን ለሀገር ያገለገሉ ሰዎችን ታሪክ እየከተበ ለትውልዱ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ አሁን ታሪካቸው የሚነገርላቸው ሰው በአንድ በኩል በጋዜጠኝነት ያገለገሉ ሲሆን ረጅም ዘመናቸውን ደግሞ በዲፕሎማሲ የሰሩ ናቸው፡፡ ብስራተ ወንጌል ከዛሬ 59 አመት በፊት ሲጀመር ይህ ብስራተ ወንጌል ነው የሚለውን መክፈቻ ያሰሙ ናቸው፡፡ በጀርመን ፤ በካርቱም ፤ እንዲሁም በቼክ ሪፖብሊክ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ለረጅም አመታት የሰሩ ናቸው፡፡ የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻውል፡፡ራሳቸው በአምባሳደርነት ከማገልገላቸው በላይ ልጃቸውም ወደዚህ ክቡር ሙያ እንዲሳብ በር የከፈቱ ናቸው፡፡ ልጃቸው ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በአሁኑ ሰአት በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናቸው፡፡ እነሆ አቶ ተፈራ ሻውልን ታውቁ ዘንድ ይህን ጽፈናል፡፡ ይህንን አጭር ዘገባ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉና አማረ ደገፋው እንደሚከተለው አሰናድተውታል፡:
1
እንደ
ኢትዮጵያ የዘመን ቀመር 1950ዎቹ አጋማሽ.....
በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች
ታሪክ ከማሟሻዎቹ አንዱ የሆነው የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ተመርቆ ስራውን ሲጀምር የተሰማው የመጀመሪያ ድምፅ የእርሳቸው ነው፦ የአምባሳደር
ተፈራ ሻውል። "ይህ የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ
ጣቢያ ነው"። ከግማሽ ከፍለ ዘመን በላይ
ወደ ኋላ መለስ ብለው ወቅቱን ሲያስታውሱ 'ንጉሰ ነገስቱ ብስራተ ወንጌልን ሲመርቁ "ይህ የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ነው" ብዬ መጀመሪያ ቁልፉን ሲጫኑ አናውንስ ያደረኩት እኔ ነኝ' ይላሉ። በዚህ ቀደምትነታቸው ኩራት እንደሚሰማቸውም ይናገራሉ።
አምባሳደር
ዲፕሎማትና የሚድያ ባለሙያ አቶ ተፈራ ሻውል ኪዳነቃል በጥቅምት 6 1936አ.ም በሸዋ ዞን በሆለታ ነበር የተወለዱት፡፡ አለቃ ሻውል ኪዳነቃል ወላጅ አባታቸው
ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ሳሳሁልሽ ኪዳኔ ይባላሉ፡፡ የአንደኛ
ደረጃ ትምህርታቸውን በሆለታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በደብረብርሀን ተከታትለዋል፡፡ በመጨረሻም ወደ ደብረዘይት ተዘዋውረው
ደብረዘይት ወንጌላዊት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡
በሆለታ የንጉሱ የጦር ትምህርት ቤትን የተጎራበተ ልጅነታቸው ብዙ አሳይቷቸዋል... 'ጥይት
ከመተኮስ በስተቀር ወታደሮቹ የሚያደርጉትን
በሙሉ እናደርግ ነበር' ይላሉ
ልጅነታቸውን እያሰቡ።
የመጀመሪያ
ደረጃ ትምህርታቸውን በሆለታ አጠናቀው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረ ብርሃን እንዳጋመሱ... እርሳቸው
እንደሚሉ "በወቅቱ በነበረ ሽግሽግ..." በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት እየተከፈለላቸው ደብረ ዘይት
በሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ በአዳሪነት እየተማሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በደብረ ዘይት የነበራቸውን
ቆይታ እንደሚወዱት ይናገራሉ። ለዚህም በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር መምህራን መማራቸው፣ ከመደበኛው የትምህርት ስርዓቱ ጎን ለጎን
ተጨማሪ ክህሎቶችን መቅሰማቸው፣ በእረፍት ጊዜአቸው በይርጋዓለም ሆስፒታል የሚሰጡት የነጎ ፈቃድ ግልጋሎትና ሌሎችንም በምክንያትነት ያነሳሉ።
የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪ በነበሩበት በአንድኛው ቀን፤ አዲስ ለሚቋቋም አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ለድምፅ ፈተና
የሚሄዱ ጓደኞቻቸውን ያገኟቸውና 'አብሬአችሁ ሄጄ ተፈትናችሁ እስክትወጡ ውጭ እጠብቃችኋለሁ' ብለው በአንድነት ወደ መፈተኛ ቦታው ያቀናሉ። ጓደኞቻቸውን የፈተነው ፈታኝ
አይቷቸው ኖሮ አስገብቶ ፈተናቸውና ከተዘጋጁት ይልቅ ያልተዘጋጁት ተፈራ ሻውልን በአንደኝነት አሳልፎ በትርፍ ሰዓታቸው እንዲሰሩ
ቀጠራቸው። አንዲት አንቀፅ ካነበቡ በኋላ የመጀመሪያ ክፍያቸው 25 ብር እንደነበረ ያስታውሳሉ። የያኔውን 25 ብር ብርታት ለማስረዳት ሲሞክሩ 'ቱሪስት ቡና ቤት ከበር መልስ መጋበዝ የሚያስችል ገንዘብ ነበር' ይላሉ።
ዜና አንባቢም ዜና ተርጓሚም
ሆነው በብስራተ ወንጌል ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ለከፍተኛ ትምርህት ወደ ጀርመን ሲያቀኑ፤ የሬዲዮ ጣቢያን በጋዜጠኝነት ስልጣን ባርኮ
የመክፈት ታሪካቸው በዚያም ተደገመ። የጀርመን ድምፅ ዶቼበሌ
የአማርኛው ክፍል ሲመሰረት አሻራቸው አለበት። "ከ ሀ እስከ ፐ ያልሰራሁት የለም' የሚለው ቃላቸው የአሻራቸውን ድምቀት ይነግረናል።
የጀርመን ቆይታቸውን አጠናቀው
ሲመለሱ የብስራተ ወንጌል ስራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። 'ለሃይማኖታዊ ስብከት ቢቋቋምም ሚዛናዊ ሚዲያ ነበር' ሲሉ በሚገልጡት እናት ቤታቸው በአማርኛና እንግሊዝኛ
ቋንቋዎች ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በድጋሜ ወደ ጀርመን የሚሄዱበት አጋጣሚ
ተፈጠረ።
ጀርመን ፍራንክፈርት ላይ በወንበዴዎች
ቦንብ የተወረወረበት የኢትዮጵያ አውሮፕላን መጠነኛ እክል ገጥሞት ወደ ሃገሩ ከተመለሰ በኋላ የጀርመን ፕሬስ ስለኢትዮጵያ የሚፅፈው
ጥሩ ያልሆነ ጽሑፍ ያሳሰባቸው የወቅቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ከተማ ይፍሩ፤ ችግሩን ለመፍታት በስልክ አስጠርተው 'እዚያው ስለተማርክ
የግርማዊ ንጉሰ ነገስት ልዩ ጸሐፊ ሁነህ ቦን ከተማ ብትሄድ' እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ሀገር ውስጥ የነበራቸውን
ኑሮ 'በጣም የተንደላቀቀ' ብለው የሚገልፁት ተፈራ ሻውል
ይከፈላቸው ከነበረ ደመወዝ ከግማሽ በላይ ለሚቀንስ፣ ከጋዜጠኝነት ወደ አምባሳደርነት ለሚያሻግራቸውና ከእናት ሀገራቸው በአካልም ቢሆን ለሚያርቃቸው
ሀገራዊ ተልእኮ 'ከሀገር በላይ ምንም የለምና' በማለት ይሁንታን ሰጡ። በጀርመን
የተጣለባቸውን ተቀዳሚ ሀገራዊ ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተው የ66ቱ ድርቅ ሲከሰት ለተጎጅዎች እርዳታ እንዲደረግ የበኩላቸውን እንደተወጡ ያስታውሳሉ።
በመቀጠልም ወደ ሱዳን ካርቱም
ተዛውረው ሲሰሩ በሀገር ውስጥ የመንግስት ለውጥ ሁኖ የወቅቱ አለቃቸው ዳዊት አብዲ በደርግ ሲጠሩ አምባሳደር ተፈራ ጉዳይ መፃሚ
ሆነው በዚያው ቆዩ። አስቀድሞ አለቃቸውን የጠራ ደርግ ድጋሜ እርሳቸውንም ጠርቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስ ጉዳይ ሃላፊ አድርጎ
ሾማቸው፤ ቀጥሎ ደግሞ አሰራቸው።
3 ዓመታት ታስረው በተፈቱ በ3ኛው ቀን ጓድ መንግስቱ አስጠርተው
በስህተት ስለመታሰራቸው ይቅርታ ጠይቀው "በምን እንካስህ" ብለው እንደጠየቋቸው ያስታውሳሉ።
'አንድ መሪ ስህተቱን አምኖ ለሀገሬ
እንድሰራ እድል ከሰጠኝ ከዚህ በላይ ካሳ አልፈልግም' ብለው መመለሳቸውን አሁንም ድረስ አይረሱ።
የሰርቶ አደር ጋዜጣ አዘጋጅ
እንዲሆኑ እድል ቢሰጣቸውም ባለመፈለጋቸው የቱሪዝም ኮሚሽን አማካሪ ሆኑ፤ ቀጥሎም የቀይ መስቀል ዋና ፀሐፊ ሆኑና በ77 ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ
አሰባሰቡ።
በድርቁ ወቅት የነበራቸው አስተዋፅኦ
ተቆጥሮ፣ ምስራቅ ጀርመን የነበሩት አምባሳደር የልብ ህክምና ሊያደርጉ
መሆኑ ታስቦ ለ3ኛ ጊዜ ወደ ጀርመን ተላኩና
መሉ አምባሳደር ሆኑ። በዚያ ለስሚንቶ፣ የጨርቃ ጨርቅና ሴራሚክ ፋብሪካዎች መቋቋምና ለበርካታ ተማሪዎች ስኮላርሽፕ መሳካት አብዝተው
ጣሩ።ወደ ችኮዝላቫኪያ ተዛውረው እየሰሩ እያለ ሌላኛው የመንግስት ለውጥ ሆነና ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ተጠሩ።
በርካታ ወዳጆቻቸው እንዲቀሩ
ቢመክሯቸውም ያለምንም ፍርሃት ጓዛቸውን ጠቅለው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ
የወቅቱ ባለስልጣናት 'ከዚህ የበለጠ አርበኝነት የለም' እንዳሏቸው ያስታውሳሉ። ለ3 ዓመታት በአቶ ስዩም መስፍን
ስር ሰርተዋል።
በመቀጠል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ገብተው ለሀገራቸው ሲሰጡት የኖሩትን ግልጋሎት ለዓለም ህዝብ ሁሉ ያለ አድሎ አበርከተዋል። 'የUN ሰራተኛ
መሆን ዓለምን በሚገባ ማወቅ ነው' በማለት በሚገልጹት መስሪያ ቤት አደጋን በመተንበይ ለአመታት ሰርተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአማካሪዎች
መማክርት ጉባኤ አባል ሆነው የሚወዷት ሀገራቸውን
እያገለገሉ ያሉት አምባሳደር ተፈራ 3 ወንድ ልጆችን ስላፈሩበት ትዳር ሲጠየቁ 'ያኔ ደፋር ነበርኩ' ብለው ወደ ሚያስታውሱት የወጣትነት ዘመናቸው በትዝታ ይሄዳሉ።
በአቶ ከተማ ይፍሩ አማካኝነት
ወደ ጀርመን ከማቅናታቸው
ጥቂት ቀደም ብሎ ለሆነ ጋብቻቸው
ሽምግልና የላኩት የወቅቱ አለቃቸው የነበሩ ሻለቃ አሰፋ ለማን ጨምሮ ቢትወደድ አስፍሃ ወልደ ሚካኤል፣ ጀነራል ደረሴ ዱባለና ጀነራል ደበበ ኃይለ ሚካኤልን ነበር።
የክብር ዘበኛ ምክትል የነበሩት ጀነራል ከበደ ዋጋዬ ሽምግልናውን
ተቀብለው ያኔ አዲስ በነበረው ዋቢ ሸበሌ
ሆቴል የተወሰኑ ሰዎችን ያሳተፈ ኮክቴል አድርገው ልጃቸው ወይዘሮ ወይንሸትን ለአምባሳደር ተፈራ ይሰጣሉ። ይህ በሆነ በማግስቱ 'አውሮፕላን ተሳፈርን' ይላሉ አምባሳደር።
በሰርጋቸው ማግስት የተንደላቀቀ
ያሉትን ኑሮ አስትቶ ባህር ያሻገራቸው፤ በስህተት 3 አመት አስሮ በፈታቸው መንግስት ስር ከ10 አመታት በላይ እንዲያገለግሉ ያደረጋቸው፤ ጡረታቸውን ሲቀሙ 'ይሁን ሀገሬን አልከስም' ያስባላቸው፤ የአማካሪዎች መማክርት ጉባኤ አባል እንዲሆኑ ሲጠየቁ በከፍተኛ ደስታና ኩራት እንዲቀበሉት ያስቻላቸው የፀና
የሀገር ፍቅራቸው መሆኑን ይናገራሉ። 'እስር ቤቱ ይረሳል፤ የተደረገብህ ግፍ ይረሳል፤ ከሀገር
የሚበልጥ የለም' ይላሉ።
አባት እና ልጅ አምባሳደር
አቶ ተፈራ በ1950ዎቹ መጨረሻ ጋብቻ የመሰረቱ ሲሆን ሁለተኛው ልጃቸው አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በአሁኑ ሰአት በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናቸው፡፡ ዲፕሎማትነትን ከወላጅ አባቴ ከአቶ ተፈራ እያየሁ አደግኩ የሚሉት የዚህኛው ዘመን ዲፕሎማት ሄኖክ በፈረንሳይ ሀገር የህግ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡
ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ከዚህ ግለ-ታሪክ ዘጋቢ ጋር ከፓሪስ በስልክ እንዳወሩት ከልጅነት ጀምሮ ዲፕሎማትነት ይስባቸው እንደነበር አጫውተውናል፡፡ አባታቸው በበርሊን እንዲሁም በሀንጋሪ አምባሳደር ስለነበሩ ቤት ውስጥ የሚመጡ ሰዎችን በማየት እንዲሁም ደግሞ በሚድያ የሚወራውን በማድመጥ ብዙ ፍላጎት ሊያድርባቸው እንደቻለ ይናገራሉ፡፡
ባለሙሉስልጣን
አምባሳደር አቶ ሄኖክ
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በጀርመን ስለነበር ያኔ ደግሞ በተለይ በ1977 ግድም ስለ ድርቁ የሚወራው ነገር የኢትዮጵያን ገጽታ በአሉታ ጎን የሚያቀርብ ነበር፡፡ ያኔ ገና ታዳጊ የነበረው ሄኖክም የኢትዮጵያን ምስል በእንዴት ያለ መልኩ መቀየር ይቻላል በሚለው ላይ አስቦበት ነበር፡፡ እኔም ሳድግ የኢትዮጵያን ምስል በበጎ ቀይራለሁ የሚል ህልም ሰነቀ፡፡ አለም አቀፍ ህግ የተማርኩት ወደ ዲፕሎማሲው እንዲስበኝ ለማድረግ ነው ይሉ የነበሩት አምባሳደር ሄኖክ እንዳሰቡትም በዲፕሎማሲው መስክ ተሰማርተው ሀገራቸውን መርዳት
ችለዋል፡፡ ይህም ከወላጅ አባታቸው ደስ ብሏቸው የወረሱት በጎ ውርስ ነበር፡፡ ባለሙሉ የስልጣን አምባሳደር ሄኖክ በ1995 አ.ም ከፈረንሳይ ቀጥታ ወደ ውጭ ጉዳይ በመቀላቀል በአፍሪካ ዲፓርትመንት በተለይ የአፍሪካ ህብረት ጉዳይ በአምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ስር በነበረው ክፍል ውስጥ መስራት ጀመሩ፡፡ኋላ ላይ ያሁን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመሩት ክፍል ነበር፡፡
ልጅ አምባሳደር ሄኖክ ከአባት አምባሳደር ተፈራ ሻውል ብዙ ትምህርት ቀስሜአለሁ ይላሉ፡፡
‹‹ አባቴ ከሰው ጋር የመግባባት ልዩ ክህሎቱ ይደንቀኛል፡፡ ይህም ለአንድ ዲፕሎማት የግድ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሌላው አባቴ ሀገሩን ለማገልገል ያለው ፍቅር ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ነው፡፡
ሁለገብ እውቀቱም ለብዙዎች የሚገርም ነው፡፡ ስለ ሀገሩ ብሎም ስለ አካባቢ ሁኔታ ጠንቅቆ አውቆ ነው የሚመራው ፡፡ በመሆኑም ብዙ ነገሮች ይሳኩለታል፡፡ በዚያ ላይ ከጋዜጠኝነት ወደ ዲፕሎማትነት የተሸጋገረ በመሆኑ የተግባቦት ክህሎቱ ልቆ የተገኘ ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ላለሁበት ደረጃ አባቴ ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡ ›› ሲሉ
በአሁኑ ሰአት በፈረንሳይ
በአምባሳደርነት እያገለገሉ ያሉት አምባሳደር ሄኖክ ስለ አቶ ተፈራ ማለትም ስለአባታቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አምባሳደር ተፈራ በአሁኑ ሰአት የ78 አመት
ሰው ሲሆኑ በብዙዎች የሚከበሩ ላገራቸው ጥልቅ ፍቅር ያሳደሩ በወርቃማው ዘመን ሀገራችን ያፈራቻቸው ወርቅ ሰው ናቸው፡፡ መልካሙን ሁሉ ተመኘን፡፡
መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
የቀድሞ ዲፕሎማት አቶ ተፈራ ሻውል ብዙ አልተነገረላቸውም ይሁንና ስራዮ ይናገር ብለው ብዙም ለመታየት የሚጓጉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን በዘመናቸው የሰሩት ድንቅ ስራ ዛሬ በአዲሱ ትውልድ በበጎ ይወሳል፡፡ ዲፕሎማሲ በሀገራችን እንደ ዋና ህልውና በሚታይበት በዛሬ ጊዜ የእነ ዲፕሎማት ተፈራ ግለ-ታሪክ ብዙ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው፡፡ በተለይ ሚድያ እና ዲፕሎማሲን አንድ ላይ አጣምሮ እውቀት ያከማቹ ታላቅ ሰው ስለሆነ ኢትዮጵያ ብትጠቀምባቸው ስንል ታሪካቸውን አጠር ባለ መልኩ አቅርበነዋል፡፡ ስለ እርሳቸው ብዙ ሲወሳ ባለማየታችን እኛ ደግሞ ብእር ከወረቀት አዋህደን እኒህን ባለውለታ ተዋወቁ ማለት እንወዳለን፡፡ የቀድሞ ዲፕሎማት አቶ ተፈራ ራሳቸውን ብቁ ዲፕሎማት ከማድረጋቸው ባሻገር ልጃቸውም የእርሳቸውን አርአያ ተከትሎ እንዲያድግ አድርገዋል፡፡ በዚህ ውጤታማ አባት ሊባሉ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በወርቃማው ዘመን የኖሩ ብርቱዎቿን በወጉ መንከባከብ ፤ ታሪካቸውን በወጉ መዘከር አለባት፡፡ እንደ ዲፕሎማት አቶ ተፈራ ያሉ ሰዎች ተንቀሳቃሽ ቤተ-መጽሀፍት እንደማለት ናቸው፡፡ ምን ያህል ሰው ተንቀሳቅሶ አጠገቡ የመጣለትን ቤተ-መጽሀፍት ይጠቀማል? የሚለው ብዙዎች ከልባቸው የሚጠይቁት ጥያቄ ነው፡፡ ትውልድ የእነ አቶ ተፈራ ሻውልን ታሪክ ሲያነብ ያኔ እንዲህም ነበር እንዴ? ሲል በተመስጦ ይሞላል፡፡ ሀገሩን ያከብራል፡፡ በሀገሩ ሰዎች ይኮራል፡፡ እንዲህ የሚያኮሩ ሰዎች ደግሞ ታሪክ ሲናገሩ ከምንም በላይ ይመስጣሉ››/ ይህ ግለ-ታሪክ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰናዳ ሲሆን በዚህ ድረ-ገጽእና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የሚወጣ ነው፡፡ ይህ ግለ-ታሪክ በየጊዜው ተጨማሪ መረጃዎች የሚታከሉበት ይሆናል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ