22. ስለሺ ሽብሩ ወርቁ- Sileshi Shibiru worku
ስለሺ ሽብሩ ወርቁ ባለፉት 24 አመታት በኤሌክትሮኒክስ ሚድያ አቅሙን ያሳየ ጠንካራ ባለሙያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአውደሰብ እና በስኬት ዝግጅቱ ከሰው ህሊና አልጠፋም፡፡ የሚድያ ስራ ደሜ ውስጥ ነው የሚለው ስለሺ ሀገሩን በሙያው የማገልገል ከፍተኛ መሻት አለው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ ስለሺ አይነት ሰዎች ታሪካቸው ቢነገር የሚያስተምሩት አንድ ጉዳይ አለ ብሎ ያምናል፡፡ በሚድያ ዘርፍ በብዙ መንገዶች ያለፈው ስለሺ ማነው? ለዝርዝሩ ጽሁፉን ያንብቡ፡፡ ክፍል አንድን እንዲህ አጣጥሙት፡፡
አንድም ቢሆን ሺህ ነው
ዕለተ አርብ ግንቦት 7 ቀን 1962 ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ በሚገኘው የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አንድ ህጻን ይህቺን ምድር ተቀላቀለ ። እናቱ ከዚህ በፊትም በከፍተኛ የህክምና ክትትል እና ቀዶ ህክምና በመውለዳቸው የተነሳ ከዚህ ህጻን በኋላም እርግዝና ቢሞክሩ ለህይወታቸው አስጊ ይሆናል በሚል የሀኪሞች ውሳኔ ዳግም እንዳይወልዱ ተደረጉ። እናም እናቱ ከወለዷቸው 2 ልጆች የመጨረሻ የመሆን እድልን ተጎናጸፈ። ለዚያም ነው ስለሺ የሚል መጠሪያ ስም የተሰጠው ። አንድም ቢሆን ሺህ ነው ለማለት። ስለሺ ሽብሩ ወርቁ።
እናቱ ወይዘሮ ገረሙ ይግለጡ ገብሬ ፣ አባቱ አቶ ሽብሩ ወርቁ ቦሩ ይባላሉ። ትውልዱም ሆነ እድገቱ አቃቂ በሰቃ ነው። ስለሺ በተወለደበትም ሆነ በጎረመሰበት ዘመን አቃቂ በሰቃ ራሷን የቻለች ወረዳ ነበረች፡፡ በመናገሻ አውራጃ ስር ያለች ወረዳ ። ከአዲስ አበባ ጋር ኩታ ገጠም ከመሆኗ ውጭ በአስተዳደር እርከን አትገናኝም ነበር ። እንደውም አቃቂ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ከተሞች በላቀ በቁጥርም በአይነትም የበዙ ፋብሪካዎች ነበሯት ። እነ ስለሺም የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት አቃቂ ናት ይሉ ነበር። ይህ ራስን የመቻልም ሆነ በራስ የመኩራት አባዜ በውስጣቸው የሰረጸው የአቃቂ ልጆች ዛሬም የአዲስ አበባ አንድ ክፍለ ከተማ ሆነው እንኳን አዲስ አባ እንሂድ ወይንም አዲሳባ ውዬ መጣሁ ይላሉ እንጂ ፒያሳ ደርሼ ወይንም መገናኛ አምሽቼ የሚል ቋንቋ ከአፋቸው አይሰማም።
ልጅነት
ክፉ አይታይ ደግ ብቻ
ሁሉ ነገር መጫወቻ
ቂም የለ ብቀላ
ልጅነት ማር ወለላ በአንድ ወቅት ስለሺ ለልጅነት የቋጠራት ስንኝ ናት ።
’ከአፉ ማር ጠብ የሚል
አቃቂ አሁን የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ከተሰራበት አቅራቢያ የጥምቀት በዓል ከሚከበርበት የታቦት ማደሪያ ጀርባ በስተቀኝ የአቃቂ ወንዝን ተዋስኖ በሚገኘው ስፍራ ነው ትውልድ እና እድገቱ።
ልጅ ሆኖ እንደ ልጅ የዋህ ፣ አይነ ግቡ እና ‘’ከአፉ ማር ጠብ የሚል’’ አይነት እንደነበር ጎረቤቶቹ ይመሰክራሉ። ዛሬ ሀምሳንም ደፍኖ እንደ ልጅነት ጊዜው የሚያዩት የሚወዱት እናቶች ብዙ ናቸው። አንገቱ ላይ የማይጠፋው ቃጭል እና ዶቃ ‘’ከሰው አይን ይጠብቀው’’ በሚል የታሰረለት ሲሮጥ ድምጽ ስለሚያሰማ እናቱ ሰምታ እንዳትመልሰው በትናንሽ እጆቹ ጭምቅ አድርጎ መሮጡን ተክኖበት ነበር።
ዛሬም ድረስ የፍቅር መንደር እንደሆነ ያለው የስለሺ ሰፈር ያሉ ጎረቤታሞች ስለሺን በጋራ ነው ያሳደግነው ይላሉ ። የመጨረሻ ልጅ በመሆኑም አምስት አመት ሆኖትም የእናቱን ጡት ይጠባ ነበር ። እናቱ ስራ ላይ ሆነው ጡት አምጪ እያለ ሲያስቸግራቸው ቅርብ ካለችው ጎረቤት ቢላ ይዘህ ናቅ ቆርጬ እሰጥሀለሁ ትለዋለች። ገሚሶቹ ‘’ለጡት ካለው ፍቅር’’ ገሚሶቹም ‘’ከየዋህነት’’ ይሉታል ጎረቤት ሄዶ ቢላ! ይላል ። የቅርቧ ጎረቤት ባምባዬ ትባላለች፡፡ እናቱ ስራ ላይ እንዳለች ስለምትረዳ እርሷ ስራ ከሌላት እዚያው ታቆየዋለች ፣ ስራ ላይ ከሆነችም እኔ ጋ ቢላ የለም በቀሉ ጋ ሂድ ትለዋለች። በቀሉ ጋ ሄዶ ቢላ ይላል ። ያው ኮድ ሆኖ ቀርቷል። እና እሷም ስራ ካላት ወደሚቀጥለው ቤት ትልከዋለች ። እንዲህ እንዲህ እያለ መንደሯን ዞሮ ሲመጣ እናቱ ስራ ጨርሳ ትጠብቀዋለች ። በሰፊው ጡቷን ታጎርሰዋለች ። ዛሬ ድረስ ጤነኛ ለሆነው ጥርሱ ስለሺ ለእናቱ ጡት ምስጋና ያቀርባል።
በዘመኑ እንደነበረ ትምህርት ቄስ ትምህርት ቤት ከመምሬ ግርማ ዘንድ ፊደልን መልዕክተ ዮሐንስን ትንሽም ቢሆን ዳዊትን ደግሟል። እናቱ የነበራቸውን ላሞችም ጠብቋል። በአቃቂ ወንዝም ዋኝቷል። የአቃቂ ወንዝ ክረምቱን አይደፈርም ። እጅግ በጣም ይሞላ እና አካባቢውን በሙሉ ያጥለቀልቃል። በበጋ በተለይ ከጥቅምት ጀምሮ ኩልል ብሎ ያምራል ‘’አጠገቡ በሚገኘው ምቹ ሜዳ እንደልባችን ኳስ እንጫወታለን፡፡
ሲደክመን
ወንዙ
ውስጥ
እንንቦጫረቃለን’’
ይላል
ስለሺ
የልጅነት
ህይወቱን
ሲያወራ
ልክ ዛሬ እንደሆነ ሁሉ በሀሳብ ነጉዶ።
በአንድ ወቅት አንድ የእድሜ እኩያው ውሀ እየዋኘ ሳለ የገባበት ይጠፋል- ወይንም ሰምጦ ቀረ ። ቤተሰቦቻቸው ድሮም እንዲዋኙ አይፈቅዱም ነበር እና በአካባቢው የነበሩ ታዳጊዎች ሁሉ ደንግጠው ወደ የቤታቸው ገቡ ። ሁሉም አድፍጦ የሚሆነውን እና የሚባለውን ይጠብቃል። መንደሩ ጩኸት በጩኸት ይሆናል። ገዛኸኝ ውሀ ውስጥ እንደሰመጠ ሰአታት አለፉ ። የሰፈሩ ልጆች እኩዮቹ ሁሉ ግራ ገባቸው በቤተሰቦች አካባቢ ‘’ሰይጣን ይዞት ነው’’ የሚል ወሬ ተሰማ ። እና ሲባል’’አዋቂ ቤት ተሄዶ ለያዘው ሴይጣን የሚደረገው ተደርጎ ይለቀዋል’’ የሚል ዜና መጣ ። የሰፈሩ ልጆች በሙሉ በመገረም ሁኔታውን በጉጉት መጠበቅ፣ ገዛኸኝን ዳግም አግኝቶ ምን እንደተፈጠረ ከራሱ አፍ መስማት እንዴት እንደጓጉ ዛሬ ድረስ ሲገናኙ የሚያወሩት ነው።
ምን ያደርጋል ከ 2 ቀናት በኋላ አስክሬኑ ነበር የወጣው ። ዛሬ ስለሺ ጎልምሶ ሲያስበው የሚዋኝበት ወንዝ አጠገብ ትልቅ የግራር ዛፍ አለ ። የዚያ ግራር ስር ወንዙ ውስጥ አለ ምናልባት ገዛኸኝ ዳይቭ ሲገባ የግራሩ ስር ይዞ እዚያው አስቀርቶት ሊሆን ይችላል እንጂ ሰይጣን ካላጣው ስፍራ ባህር ውስጥ ገብቶ ምን ያጫናንቀዋል ይላል።
ፊታውራሪ አባይነህ መተኪያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለሺ ለአቅመ አንደኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ከነበሩት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው። አንድ 3 ወይንም 4 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡ ከመኖሪያ ቤታቸው እዚያ ነው አንደኛ ክፍል ተመዝግቦ ትምህርት የጀመረው።
ሉጫ ጸጉሩን እንደ ኤልቪስ ፕሪስሊ እና እንደ አለማየሁ እሸቴ ግራ እና ቀኝ ከፍሎ ትምህርት ቤት የሚመላለሰው ስለሺ መንገድ ላይ የሚያዩት ሁሉ የሚወዱት አይነት ገጸ- ባህሪይ ነበር ይላሉ፡፡ የዕድሜ እና የክፍል ጓደኞቹ። በተለይ ደግሞ ሲናገር ኮልታፋ የሚሉት አይነት ባህሪይ ነበረው ። አረፍተ- ነገር ሲጀምር የመጀመሪያዋን ፊደል ሶስት አራቴ ረግጦ የመጥራት ልማድ ወይም ባህሪይ ነበረው ። የአባቱ እናት እንደሚሉት ድሮ በልጆቻቸው የልጅነት ዘመን እቤታቸው አዘውትረው የሚመጡ የኔ ቢጤ ነበሩ፡፡ እኚህ አዛውንት የኔ ቢጤ ምላሳቸው ኮልታፋ ነበር ። እየተኮላተፉ ሲለምኑ ከልጆቻቸው ሁሉ ተለይተው የስለሺ አባት ሁሌ ይስቁባቸው ነበር። እናም ይላሉ የስለሺ አያት ነፍሳቸውን ይማረው እና እናም የስለሺ አባት በሳቁት ስለሺ ኮልታፋ ሆነ። ይሁን እና ስለሺ አድጎ የብሮድካስት ጋዜጠኛ ሆኖ ድምጹን የሚሰሙ የሰፈሩ ሰዎች ‘’ወይ ጉድ ያ ምላስ ተፈትቶ እንዲህ ይሁንi’’ ማለታቸው አልቀረም።
ስለሺም፣ ለምላሱ መፍታታት ባለ ውለታ የሚላቸው ሰዎች አሉት። በተለይ የ 4ኛ ክፍል ሳይንስ መምህሩ ተመሳሳይ ምላስ ስለነበረው አንድ የውጭ ሀገር ሰው ጫካ ሄዶ ምላሱ ስር ጠጠር በማስቀመጥ በተደጋጋሚ ይጮህ እንደነበር እና ምላሱ እንደ ተፍታታለት ትነግረው ነበር ። ከዚያም አልፎ ድምጽን አውጥቶ ጮክ ብሎ እንዲያነብ ታበረታታው ነበር ። እርሱም ብዙውን ጊዜ ጮክ ብሎ ማንበብ እንዲሁም ለአብሮ አደጎቹ ጭምር መጽሀፍትን ይተርክላቸው እንደነበር ያስታውሳል። በተለይ ጊዜው የመጽሀፍት ዓለም ትረካ የነገሰበት ጊዜ ስለነበር በወቅቱ ይተረክ የነበረውን የገበየሁ አየለን ‘’ጣምራ ጦር’’ ስለሺ ልጆች ሰብስቦ ያነብላቸው እንደነበር አይረሳም ። አድጎ ለአቅመ ስራ በቅቶ ኢትዮጵያ ሬድዮ በፍሪ ላንሰርነት ሲቀጠር የንባብ ልምምድ የሰጠው ቴክኒሻኑ ተካ ወልደ ሀዋሪያትም የእስክሪፕቶ ቀፎ በመንጋጋዎቹ ነክሶ ጮክ ብሎ በማንበብ ምላሱን ማፍታታት እንደሚችል ነግሮት ደጋግሞ ማድረጉን ስለሺ አይረሳም።
የእግዜር ኩርኩም
ፊታውራሪ አባይነህ መተኪያ ትምህርት ቤት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የደረሰበትን እሱ ‘’የእግዜር ኩርኩም’’ የሚለውን አጋጣሚ በህይወቱ ላይ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ስለሺ ያሰምርበታል። ነገሩ እንዲህ ነው። በዚያን ወቅት እርሱም ሆነች እህቱ የከሰዓት ፈረቃ ስለነበሩ ከቤት ቀድመው ይወጣሉ። በመንገዳቸው ያለ ሾላ አፍርቶ በርካታ ወፎች እላዩ ላይ ሰፍረው ይንጫጫሉ ። ስለሺም ሁለት ባላ ባለው ዋርካ በአንዱ ላይ ይወጣል፡፡ የበሰለውን እየቀጠፈም ለእህቱ ይወረውራል፣ እህቱም የበላችውን በልታ ሌላውን በቦርሳዋ ትከታለች። ወፎቹ የማይችሉት ባላጋራ መጥቶባቸው የሾላዋን ዛፍ ለቀው ሄደዋል ። ስለሺ በዚያኛው ባላ ላይ አንዲት የበሰለች ድፍን ሾላን አንዲት የቀረች ወፍ እየበላች ይመለከታል። ይህንን ታሪክ ብዙ ጊዜ ሲያወራ ልክ ዛሬ እንደሆነ ሁሉ ሁሉም ነገር ይታየዋል። ልክ ዛሬ ገበያ ላይ እንደምናየው ቀላ ያለ አፕል የመሰለችዋን በያኔው የእነርሱ አጠራር ድፍን ሾላ ከዚያኛው ባላ ላይ ሄዶ እስከሚያወርደው
ቸኩሎ
ወይንም
ሰስቶ
አጠገቡ
ያለውን
ያልበሰለ
ድፍን
ሾላ ቀንጥሶ ወደ ወፏ ወረወረው። ወፏም ምናልባት ረግማው በረረች ። ስለሺ ከአንድኛው ባላ ወደ ሌላኛው ባላ ለመሸጋገር እንደጀመረ ባፍጢሚ መሬት ተተከለ። ከዚያም በጀርባው ተንሸራቶ ቋጥኝ ተደግፎ ተኛ። እህቱ ደነገጠች ደጋግፋ አንስታው ወደ ትምህርት ቤት ልትወስደው ሞከረች ። ትምህርት ቤት እሄዳለሁ ብሎ መንገድ ለመንገድ የሾላ ፍሬ መልቀምም ሆነ ሌላ ተግባር ላይ መሰማራት በቤታቸው ህግ የሚያስቀጣ ተግባር ነው ። በአንድ በኩል እቤት እንዳይሰማ በመጨነቅ በሌላ በኩል የሚሰማውን ከፍተኛ ህመም አምቆ ትምህርት ቤት የደረሰው ስለሺ ትምህርት ቤት እንደደረሰ የበላው የሾላ ፍሬ ሌላም ነገር ጨምሮ ከሆዱ ወጣ። እናቱም ተጠርታ ወደ ቤት ወሰደችው ። ይህቺ የ 4ኛ ክፍል ኢንሲደንት ወይንም ክስተት ዛሬ ድረስ ስጥ የሚበሉ ወፎችን እንኳን እንዳያባርር አድርጋዋለች ። ከዚህም በላይ እንዳይስገበገብ ፣ ባለው ተመስገን ብሎ እንዲኖር ከፍተኛ ድርሻ እንዳላት ይመሰክራል።
ስምንተኛ ክፍልን አልፎ ዘጠነኛን አቃቂ አድቬንቲስት እስከሚገባ ድረስ እስከ ስድስተኛ በፊታውራሪ 7 እና 8 ደግሞ ድሮ አቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ይባል በነበረው ከመኖሪያ ቤታቸው ማዶ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። አቃቂ በስለሺ ስብዕና እና ስነ ልቦና ውስጥ ትልቅ ቦታ አላት ። የብዙ ፋብሪካዎች እና የብዙ ወዛደሮች ሀገር መሆኗ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ስራ ፍለጋ መጥቶ እንጀራ አግኝቶ ልጅ በልጅ ሆኖ የሚኖርባት መሆኗ አቃቂ ልዩ ናት ። አንዱ የሰፈራቸው ሰው ካገራቸው መጥተው አቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ይገባሉ፡፡ የመጀመሪያው ቀን ወንድ ሁሉ በማሽን ፈትል ሲፈትል ቢያዩ ምነው ሸዋ እንደ ሴት ፈትል ስፈትል አልገኝም ብለው ጥለው ይወጣሉ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ብረታ ብረት ፋብሪካ ገብተው ብረት ማቅለጥ ጀምረዋል።
ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲገናኙ አብዛኛው ተማሪ የወዛደር ልጅ በመሆኑ አባቱ የሚሰጠውን የስራ ልብስ ማሰፊያ ( ቱታ ) ጨርቅ ለልጆቹ ስለሚያሰፋ እንደየ ፋብሪካዎቹ የቱታ ጨርቅ ቀለም ልጆቹም አባቶቻቸው የየትኛው ፋብሪካ ሰራተኞች እንደነበሩ መገመት ለእነ ስለሺ ከባድ አልነበረም ። ለምሳሌ የእርሱ አባት የሚሰሩበት አቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ብዙውን ጊዜ ሰማያዊ የቱታ ጨርቅ ስለሚሰጣቸው ሰማያዊ ኮት እና ሱሬ የሚለብስ ልጅ አባቱ የአጨጨፋ ወዛደር ናቸው ማለት ነው ። አንድ ተማሪ ካኪ ቀላም ያለው ልብስ የሚያዘወትር ከሆነ አባቱ የቃጫ ፋብሪካ ወዛደር ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም ነበር።
እንደ ስለሺ የአጨጨፋ ( የአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ) ወዛደር ልጅ መሆን ብዙ የሚያኮሩ ነገሮች ነበሩት ። አንደኛ አጨጨፋ በመላው ኢትዮጵያ በሰራተኛ ብዛት አቻ አይገኝለትም ። በሶስት ሺፍት የሚሰሩ 6 ሺህ ሰራተኞች አሉት። ሁለተኛ የውጭ ሀገር አብዮታዊ መሪዎች መጥተው የሚጎበኙት እሱኑ ነው ። ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ እና ፊደል ካስትሮ እንኳን አጨጨፋን ነው የጎበኙት። ኬኔት ካውንዳ በሉ ጁሌስ ኔሬሬ ነጭ መሀረባቸውን እንደያዙ አጨጨፋን ጎብኘተዋል ። አረ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ይሁን የሩማኒያ ነው ዩጎዝላቪያ መሪ ቻውቼስኮ ይሁን ብቻ የሆነ ተመሳሳይ ስም ያላቸው መሪዎች አጨጨፋን ሲጎበኙ የእንኳን ደህና መጣችሁን ዝግጅት ስለሺ እና ጓደኞቹ ሰፈራቸው ሆነው ሰምተዋል። ‘’ ጓድ ቻውቼስኮ ኣንኳን ደህና መጡ!! ‘’ ሲል ማይኩን የያዘው ሰው ሰልፈኛው ወዛደር ተቀብሎ ጓድ ቻውቼስኮ እንኳን ደህና መጡ ሲል እንደነበር የልጅነት ጆሮዎቹ ልቅም አድርገው ሰምተዋል ። እንዲያውም አንዳንድ የእድሜ እኩዮቹ አብረው ማለታቸውንም ያስታውሳል። ሌላው የአጨጨፋ ወዛደር ልጅ መሆን የሚያኮራው አጨጨፋ ከፋብሪካነት በላይ የከተማው ሰዓት ነጋሪ መሆኑ ነው ። ማለዳ 12 ሰዓት በረጅሙ የሚለቀቅ ጥሩምባ አለው ። ይህ ለማለዳ ገቢዎች ተዘጋጁ መሆኑ ነው ። ተሜም ለትምህርቷ ትዘጋጅበታለች ። አንድ ሰዓት ሲሆን ደግሞ 2 ጊዜ አጫጭር ጥሩምባዎች ይሰማሉ ። እነዚህ አንደኛው የማለዳ ሽፍት ወዛደሮች ገብተው ማለቃቸውን ፣ አዳሪ ሽፍት ወዛደሮች ደግሞ መውጣት እንደሚችሉ ማሳወቂያ ናቸው። ስድስት ሰዓት ላይ የምሳ እረፍት ማብሰሪያ ሰዓት ይጮሀል። ዘጠኝ ሰዓት ደግሞ የማለዳ ሽፍት ወዛደሮች መውጫ እና ምሽት አምስት ሰዓት ወጪዎች መግቢያ ነው። ምሽት 4 ሰዓት ደግሞ አዳር ሰራተኞች ከቤታችሁ ውጡ የሚል ረጅም ጥሩምባ ይሰማል። ምሽት 5 ሰዓት ልክ እንደ ማለዳው 2 አጫጭር ጥሩምባዎች ይሰማሉ። 9 ሰዓት የገቡት ወደ የቤታቸው ይሄዳሉ አዳሪዎች ቦታውን ይረካባሉ ። ዛሬ እንዲህ አይነት የ 3 ሽፍት ስራ በኢትዮጵያ መኖሩን ያጠራጥራል ። ዛሬ በኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ሰዓት ነጋሪ ፋብሪካ ለምን እንደማይኖር ግራ ይገባኛል ይላል ስለሺ ሽብሩ የድሮውን ትውስታ ለጓደኞቹ ሲያወጋ።
የአቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ለስለሺ ከባቱ ፋብሪካነትም በላይ ነው ። እርሱም ሆኑ የአባቱ ጓደኞች ልጆች ቅዳሜ አንዳንዴም አባቶቻቸው overtime ሲታዘዙ እሁድ እሁድ ምሳ ይዘው ይሄዱ እና የመስሪያ ቤቱ ክበብ የሚያዘጋጀውን በትንሽ ሳንቲም የሚገዛውን ፓስቲ እና ጮርናቄ መብላት የሚወደድ እና የሚናፈቅ ነገር ነው ። ለስለሺ ግን አባቱ የሚሰሩበት ወርክ ሾፕ ውስጥ የቴክኒክ ስራዎችን ማየትም ሆነ መሞከር ከሁሉ በላይ ያስደስተው ነበር። በሌዝ ማሽን ድሪል ማድረግ እና አንዳንድ ቅርጻቅርጾችን ማውጣት ጀምሮ ነበር አልሙኒያም ቆርጦ፣ ሞርዶ እና በስቶ የዶሚኖ ጠጠር ሰርቶ እንደነበርም ያስታውሳል።
አቃቂ አድቬንቲስት እና 3H
ከ 9-12 ያሉትን የትምህርት አመታት በታላቁ የአቃቂ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ነው ስለሺ የተማረው። አቃቂ አድቬንቲስት ስለሺ ዛሬ ድረስ መመሪያ ያደረጋቸውን ብዙ ነገሮች እንደሰጠችው ይናገራል። ትምህርት ቤቷ 3H የሚል ባለ ሶስት መዓዘን ሎጎ አላት ሰው በልጅነቱ በትምህርት ሲታነጽ ሊገነባቸው ይገባል የምትላቸውን head , hand & heart ማለትም አእምሮን ፣ እጅን እና ልብን ወይንም ልቦናን ማነጽ ላይ ማተኮር አለበት ነው መርሁ። ብሩህ አእምሮ፣ የሚሰሩ እጆች እና የሚራራ ልቦና ለማንኛውም ወጣት ያስፈልጋል ነው። ይህን መርህ ተከትሎት የኖረው ስለሺ ከአባቱ የስራ ቦታ የቀሰመው እውቀትም ሆነ የሰጠው ድፍረት እቤቱ ሙሉ የእጅ መሳሪያዎች አሉት ለውሀ መስመር ለኤሌክትሪክ ሶኬትም ሆነ ማብሪያ ማጥፊያ ስራ ሰራተኛ አያስፈልገውም።
ጥልቅ ንባብን የለመደውም ሆነ ከስነ ግጥም ጋር የተቆራኘው በዚያው በአድቬንቲስት ትምህርት ቤት መሆኑን ስለሺ ይናገራል በተለይ በሳድስ ይደፉ የነበሩ የወል ቤትም ሆነ ዘላሰኛ ግጥሞቹን ከሳድስ ጥገኝነት ለማውጣት የአማርኛ አስተማሪዎቹ አንደበቱን እንዳፍታቱለት ይመሰክራል።
የዘመናት የህዝብ ብሶት ወልዶኛል ያለው የህወሃት ሰራዊት ግንቦት 20 አዲስ አበባን ሊቆጣጠር ሚያዚያ ወር ላይ ነበር የነ ስለሺ ዘመን የ 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተናቸውን የወሰዱት ። ጥቅምት ላይ ውጤታቸው ሲገለጽ ስለሺም ለዩኒቨርስቲ መግቢያ የሚሆን ነጥብ አምጥቷል።
ብዙ ጊዜ ዕድለኛ ነኝ የሚለው ስለሺም የመጀመሪያ የዩኒቨርስቲ ምርጫው ተጠብቆለት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6ኪሎ ካምፓስ ይመደባል። 2ተኛ አመት ላይ ቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ የትምህርት ክፍል ይመደባል ። በዚያን ወቅት none teaching በሚል ዘርፍ የጋዜጠኝነት ኮርሶችን መስጠት መጀመሩም መልካም ዕድል ነበር። ጋሽ ማዕረጉ በዛብህን የመሰሉ አንጋፋ ጋዜጠኞች በመምህርነት በመቀላቀላቸው የትምህርት ክፍሉም ሆነ ተማሪዎቹ ተነቃቅተው ነበር። ጋዜጠኝነት በጥቂቱ ውጭ ሀገር ሄደው በሚማሩበት አሊያም ከቤተ ክህነት በሚወረስባት ኢትዮጵያ የተወሰነም ቢሆን የማስተዋወቂያ ትምህርት መስጠቱን እንደ በጎ ጅማሪ ያየዋል ስለሺ ዛሬ ለተፈጠረው የጋዜጠኝነት ዩኒቨርስቲ ያኔ የተጣለው መሰረትም ዋጋ እንደነበረው ያምናል።
ቡትሮስ ጋሊ ይውጣ
በ1985 የያኔው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ግብጻዊው ቡትሮስ ጋሊ የኤርትራን ህዝበ ውሳኔ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመነጋገር አዲስ አበባ ነበሩ ። ተማሪው ይህንን በመቃወም 6ኪሎ በሚገኘው የኳስ ሜዳ ስብሰባ ጀመረ ። ስብሰባው ወደ አመጽ አደገ ። አበበ ገላው ያኔ እጅግ መሳጭ የሆኑ ቀስቃሽ ንግግሮችን ያደርግ ነበር ። ጋሻው ካሴ የሚባል እድሜው ከፍ ያለ ተማሪም የተማሪዎች መማክርት ሊቀመንበር የነበረ እንዲሁ ተቃውሞውን ይመራ ነበር። ስለሺም እጅ ከማውጣት እና ‘’የታጋይ ድምጽ ይጮሃል’’ እያለ ከመዘመር የዘለለ ሚና ባይኖረውም ስብሰባ አለ በተባለበት ይገኝ ነበር።
አንዱን ቀን የአራት ኪሎ እና የአምስት ኪሎ ተማሪዎችን ጨምሮ ፣ አይነ ስውራንም ሆኑ በዊል ቸር የሚጠቀሙም ሆነ ምርኩዝ የሚይዙ ሳይቀር ተሰብስበዋል ። አላማው አፍሪካ ህብረት አካባቢ በመሄድ የመንግስታቱ ድርጅት ኤርትራን ከማስገንጠል ይቆጠብ ለማለት ነው ። ሁሉም ተማሪ ሰላማዊ ነው ። በርካታ ባንዲራ እና መፈክሮችን ይዘው በተደራጀ መልኩ መስመራቸውን ሳይስቱ ጉዞ ጀመሩ ። የፊተኛው ቡድን የ6ኪሎ የሰማዕታት ሀውልትን ሲሻገር የመጨረሻው ሰልፈኛ 6ኪሎ የኒቨርስቲን ለቋል ። ለቆ ሲያበቃ ዋናው በር ተዘጋ ! ከዚያ ተኩስ በተኩስ ሆነ። ስለሺ እንደሚያስታውሰው ብላቴ ገብተው ከውጡት ተማሪዎች በስተቀር ሌሎቹ የተኩስ ልምድ ስለሌላቸው የተተኮሰ ሁሉ ሰው ላይ የሚያርፍ ነበር የሚመስላቸው። ሰልፈኛው ተመልሶ ወደ ዩኒቨርስቲ ሊገባ ቢሞክር ሁሉም በሮች ተዘግተዋል ። የዩኒቨርስቲው የብረት አጥር ደግሞ በጣም ረጅም ለመውጣትም የማይመች ነው ። አንዱ አንዱን እየደገፈ በሚንጣጣ የጥይት ድምጽ መሀል አንዳንዴም የአጥሩ ብረት እና ጥይት ሲገናኝ እየሰሙ ወደ ግቢ ከገቡት ተማሪዎች ውስጥ ነበር ስለሺ።
መንግስት እንደገለጸው አንድ ተማሪ ሞቶ በርካቶች ቆስለው ሰልፉ ተቀለበሰ። በዚያው ሰሞን እንዲሁ አራት ኪሎ ሄደው ግቢ ውስጥ ‘’የታጋይ ድምጽ ይጮሃል’’ ሲሉ ፌደራል ፖሊስ መጥቶ የግቢውን በር ዘግቶ መግባት እንጂ መውጣት አይቻልም ይላል። ተማሪው ዋናው በር ድረስ በመምጣት ድምጹን ከፍ አድርጎ ያሰማል። እየመሸ ሲመጣ ፍርሀት ሁሉም ዘንድ ነገሰ። ከመሸ ለማደር ከጓደኞች ጋር ይታደራል ። ግን ፖሊስ እንደሚገባ እና በተለይ ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ የመጡትን ተማሪዎች እንደማይለቃቸው ሁሉም ገብቶታል።
መላ ሲታሰብ ከ 4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ ከጀርባ አጥሩን የሚያዋስኑ መኖሪያ ቤቶች አሉ ማንንም ሳያስፈቅዱ ስለሺ እና ጓደኞቹ ሰው ግቢ ዘለው ይገባሉ ። በጣም የተደናገጡት የግቢው ባለቤቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከግቢው ያስወጧቸዋል። ስለሺም ቁልቁል ወረድ ብሎ ሺ 80 የሚባለው ሰፈር ያሉ አክስቶቹ ዘንድ ሄዶ አደረ። በዚያ ምሽት 4 ኪሎ የተገኙ ጓደኞቹ ሸዋ ሮቢት ተወስደው የፌደራል ፖሊስን ቅጣት ቀምሰው ፣ ሁለተኛ አይለምደንም ብለው ፈርመው ነው የተለቀቁት።
ስለሺ ሁሌም አጽንኦት እንደሚሰጠው በለውጥ መሀል ያለው የሱ ትውልድ ብዙ መከራን ደርሶበታል። በደርግ ስርዓተ ትምህርት ኢትዮጵያዊነትን በሚያወድስ እና በሚያነግስ ዘመን አድጎ የጎለመሰ ትውልድ የዚህ አስተሳሰቡን የሚቃረን አስተሳሰብ ሲመጣበት ቀጥታ ተላትሟል።
ስንት ነገር መፍጠር ማሰብ እና ማብሰልሰል የሚችሉ ጂኒየስ የዚያን ዘመን ወጣቶች ጊዜያቸውን በሙሉ በትግል አሳልፈዋል። ይህ ስለሺ እንደሚያምነው ትውልዱን ያከሰረ ሀገርም የጎዳ እስካሁንም ያልተፈታ አባዜ ነው።
የጋዜጠኝነት ጉዞ
ኢትዮጵያ ሬድዮ ዜና ፋይል ነበር በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ስራ የጀመረው። ያኔ ዜና ፋይል ዝነኛ ነበር። የጋዜጠኝነት ከባድ ሚዛኖቹ እነ ነጋሽ መሀመድ ፣ ንግስት ሰልፉ ፣ ብርቱካህ ሀረገ ወይን ፣ እሸቱ ገለቱ ፣ ተፈሪ ለገሰ ፣ ሺበሺ ጸጋዬ ዜና ፋይልን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሰውት የነበረው ዘመን ላይ ነበር ስለሺ በሪፖርተርነት የተቀላቀለው ።
የቢቢሲን ዜናዎች የሚቀዳ ትልቅ ናግራ የሚባል ማሽን አለ ። የዜና ሰዓት እየተጠበቀ ድምጹ የቀረጻል ። ምናልባት 10 ሰዓት ላይ የዕለቱ ዋና አዘጋጅ የተቀዳውን ድምጽ እየሰማ ይተረጉማል። ብዙውን ጊዜ ነጋሽ መሀመድ ይሄንን ይሰራል ። ነጋሽ የሚጽፍለት ሰው ይፈልጋል ያ ሰው ስለሺ ሽብሩ ሆኖ ተገኘ ። ምናልባት ልጅነቱ እና የእጅ ጽህፈቱ ጥሩነት በነጋሽ ዘንድ አስመርጦት ይሆናል። ስለሺ ግን እንደ ትልቅ እድል ተጠቀመበት የነጋሽን የአጻጻፍ ስታይል ፣ የአተረጓጎም ጥበብ ልቅም አድርጎ ያዘ። አንዳንዴ ነጋሽ የሚሰማውን እየሰማ ምን ብሎ ይተረጉመው ይሆን ብሎ ይገምታል ። እየቆየ ሲመጣ አብዛኛው ግምቶቹም ትክክል ይሆኑለት ጀመር ። ያኔ በጋዜጠኝነት መንገድ ለመጓዝ መንገዴን ጀመርኩኝ ይላል።
ለዝርዝሩ ስለሺ ሽብሩ
ሺበሺ ጸጋዬ ይሁን እሸቱ ገለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዝርዝሩ ስለሺ ሽብሩ የሚለውን ግጥማዊ የዜና አመራር አየር ላይ ያዋሉት ይላል ስለሺ ። ከዚያ ባሉት የጋዜጠኝነት ህይወቱ እና የዜና ሪፖርት አቀራረቡ ብዙዎቹ ዜና መሪዎች
(Anchr) ለዝርዝሩ
ስለሺ
ሽብሩ
ማለት
ይመቻቸው
ነበር።
የዜናን
ዋጋ በሚገባ ለሚረዳው ስለሺ ግን ዝም ብሎ አውደ ጥናት ተከፈተ ተዘጋ ለሚል ዜና ይሄንን ብራንድ የሆነ አጠራር አታባክኑት ይል ነበር። ይህ አጠራር ከረንቡላ ቤትም ገብቶ ነበር። ጥሩ የመታ ተጫዋች ሲኩራራ ለዝርዝሩ ስለሺ ሽብሩ ይል እንደነበር በዙ ቦታዊች ላይ የታዘቡ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ስኳር
ታህሳስ 18 ወይንም 19 ቀን አመሻሽ ላይ የዜና ፋይል የዕለቱ አዘጋጆችን ያስደነገጠ ወይንም ያስገረመ ዜና ይመጣል ። ታምራት ላይኔ ‘’ቢመክሩኝ ቢመክሩኝ አልሰማ ብዬ’’ ብላ ብላ ብላ ይላል ። ስለሺ እንደሚያምነው ያንን ዜና አብዛኞቹ ሲኒየር ጋዜጠኞች ማንበብ አልፈለጉም ምናልባት ሰውየውን ስለሚያውቋቸው ወይንም ስለሚያከብሯቸው ሊሆን ይችላል። ዜናው ግን በጀማሪ ጋዜጠኛ መነበብ እንዳልነበረበት ዛሬም ድረስ አምናለሁ ይላል። ይሁን እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከውን የቴሌ ፕሪንት ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ እንዳለ ፕሪንቱን አንብብ ብለው ሰጡት።
ያለ ምንም መሸማቀቅ የሚጠብቀውን እያጠበኩኝ የሚረገጠውን እየረገጥኩኝ አነበብኩት ይላ ስለሺ ። የዜና ሰዓት ደርሶ ለዝርዝሩ ስለሺ ሽብሩ ሲባል የአቶ ታምራት ላይኔ የተወካዮች ምክር ቤት ውሎ ተዘረዘረ። እንዲህ እንዲህ እያለ ለተወሰኑ ወራት በዜና ፋይል የቆየው ስለሺ ሰኔ 3 /1989 ለርጅም አመት በቆየበት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በከፍተኛ ሪፖርተርነት ስራ ጀመረ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለሺ እንደሚለው የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነትን በቅጡ የኖረበት ሙያውን ያጣጣመበት እና ከህዝብ ጋር በደንብ ያስተዋወቀው ነው።
ደምበ ገዳሙ
በባድመ ግንባር ገመሀሎ የሚባል ተራራ አቅራቢያ የሚገኝ ቦታ ነው ። የኢትዮጵያ ጦር በባድመ ጦርነት የማዘዣ ጣቢያ አድርጓቸው ከነበሩ ስልታዊ ጠቀሜታ ካላቸው ቦታዎች አንዱ ነው ። ስለሺን ጨምሮ በባድመ ግንባር የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የካሜራ ባለሙያዎች አንዳንዴ በማዘዣ ጣቢያ ባንከር ተብለው የሚጠሩት ምሽጎች ውስጥ ይውላለ ያድራሉ ። ባንከሮች ከባድ መሳሪያንም ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ ቁልቁል እና አግድም ተቆፍረው ድንጋይ ተገንብቶላቸው የሚሰሩ መከላከያ ናቸው።
ግንቦት 16 ቀን 91 ዓመተ ምህረት የኤርትራ መንግስት ሰኞ ባድመ በሚል ከባድ ማጥቃት የሰነዘረበት እለት ነበር ። ግንቦት 16 የኤርትራ መንግስት የነጻነት በዓል ነው። ምናልባትም የነጻነት በዓሉን በድርብ ድል ለማጀብ አስቦ ይሆናል ።የኤርትራ መንግስት ከባድ የተባለ ማጥቃት ለሊቱን ሰንዝሯል። የኢትዮጵያ የጦር ሄሊኮፍተሮችም ጥምር ጥምር እየሆኑ ሲተኩሱ ከደንበ ገዳሙ እነ ስለሺ በቅርብ ርቀት ያያሉ ። ካሜራ ማኖችም የሄሊኮፍተሮቹን ማጥቃት ይቀርጻሉ። በዚህ መሀል አንዲት አጥቂ ሄሊኮፍተር በአየር ላይ ተመትታ በእሳት ትያያዝ እና ቁልቁል ትወርዳለች። ጋዜጠኞችን ጨምሮ ደምበ ገዳሙ አፋፍ ላይ ሆነው ትዕይንቱን የሚመለከቱት ሁሉ በንዴት ጨሱ። እልህ ተጋቡ ። ተንገበገቡ ። ወዲያው ‘’አብራሪው ተርፏል’’ ። ‘’አብራሪው ተርፏል’’ የሚል ዜና ተስተጋባ !! ሲመታ የነበረው ያ ሁሉ ንዴት በርዶ በደስታ መፍነክነክ ሆነ።
አብራሪው በፓራሹት ወርዶ የወገን ጦር ያለበት ስፍራ አርፎ ስለነበር ወዲያው በፒክ አፕ መኪና ይዘውት ደምበ ገዳሙ መጡ። በእሳት የተያያዘ የበረራ ልብሱን አውልቆ በነጭ የውስጥ ልብስ ያለው አብራሪ በእሳት የተለበለቡ እግሮቹን በፋሻ ጠቅልሏቸዋል ። በእጁ ማካሮቭ ሽጉጥ እና የድምጽ መቅረጫ ቴፕ ይዟል። ያንን ቅጽበት ሲያስታውስ ስለሺ ምን አይነት ኢትዮጵያዊነት እንደሆነ ሁሌ ይገርመኛል ይላል። ካፒቴኑ ፊት ላይ ምንም የመረበሽ ስሜት አይታይም ጭራሽ ‘’አይዟችሁ! ልካቸውን አሳይተናቸዋል’’ ! ። ‘’ድል የኛ ነው! ‘’ እያለ በሙሉ ልብ ደምበ ገዳሙ የከበቡትንን ጋዜጠኞችን ያበራታታ ጀመር። ስለሺ እንደሚለው ንዴት ፣ እልህ ፣ ቁጭት ፣ ደስታ እና ፈንጠዝያ በትንሽ ደቂቃ ውስጥ በደንበ ገዳሙ ጉብታ ተትረፈረፈ።
በነገራችን ላይ ስለሺ ታህሳስ መጨረሻ ላይ ተቀይሮ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ አንድ ወር ላይ ጥር መጨረሻ ላይ ህረት በተባለ ቦታ ላይ 2 የቴሌቪዥን ካማራ ቀራጺዎች እና አንድ የፕሬስ ድርጅት ፎቶ ግራፈር ህይወታቸው አልፏል ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ መሀመድም ቆስሎ ተርፏል።
ኢቲቪ በለውጥ ጎዳና
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ በመሆ ያገለገሉት ሶሎሜ ታደሰ ለኢቲቪ በስራ አስኪያጅነት ከተመደቡ በኋላ ኢቲቪ ብዙ ለውጦችን አምጥቷል። በተለይ አዳዲስ የፕሮግራም ፎርማቶች ሲተከሉ ሀሳብ ከማመንጨት ርዕስ ከመሰየም ጀምሮ የፕሮግራሞቹ አዘጋጅ በመሆን ስለሺ በሚገባ ተሳትፏል። ከነዚህ ፕሮግራሞች ስኬት እና አውደ ሰብ በሚባሉት ፕሮግራሞች በርካታ ውጤታማ ግለሰቦችንም ሆነ የተቋሞችን የለውጥ ታሪክ በስኬት ፕሮግራሙ ሰርቷል ። በወቅቱ የነበሩ የኢሀዴግ የሚዲያ ጠርናፊዎች ባይደሰቱበትም የሀገር ባለ ውለታ የሆኑ ትላልቅ ሰዎችንም በአውደ ሰብ ፕሮግራሙ አቅርቧል። እቴጌ ጣይቱ ፣ አሉላ አባ ነጋ ፣ ጅነራል ወልደ ስላሴ በረካ ፣ አበበች ጎበና ፣ ዛሬ የቶቶት ባህላዊ የምግብ አዳራሽ ባለቤት የሆነው ጠንክር ቴኒ ፣ የወርልድ ስፔስ መስራች ኖህ ሳማራ ስለሺ ለአየር ካበቃቸው ታሪኮች የተወሰኑ ናቸው ። እሱ እንደሚለው የመንግስት ሰዎች ፕሮግራሙ መቃብር እየቆፈረ የድሮ ፊውዳሎችን ታሪክ ከሚያወጣ የታጋዮችን እና የገበሬዎችን ታሪክ እንዲሰራ ነበር ፍላጎታቸው።
የነ ተክሌ አመጽ እና የስለሺ ሪፖርት
ተክለ ሚካዔል ሳህለ ማሪያም አበበ ( ልጅ ተክሌ ) አሁን በካናዳ የሚኖር ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጠበቃ ነው ። 3ተኛ ወይንም አራተኛ አመት የህግ ተማሪ እያለ የእርሱ ዘመን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ ያው እንደ የትኛውም ዘመን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥያቄ ብዙ አስተዳደራዊ እና ወሳኝ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አያጣም ።
ስለሺ ሚያዚያ 8 ቀን ከሰዓት በኋላ ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ላይ ናቸው እና ባስቸኳይ እንድትሄዱ ከተባሉት ሪፖርተሮች እና ያካሜራ ባለ ሙያዎች አንዱ ይሆናል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6ኪሎ ዋናው በር ላይ ሲደርሱ ግን ነገሮች ከጠበቋቸው በላይ የከረሩ ነበሩ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው በር ጥርቅም ብሎ ተዘግቷል ። ከውስጥ የነተክሌ ባቾች የተቃውሞ ድምጽ ያስተጋባል። የነ ስለሺን የእንግባ ጥያቄ የበሩ ጠባቂዎች አልተቀበሉትም። ከዋናው በር ማዶ ላይ ድባብ መናፈሻ ደጃፍ ላይ የቆመች ወያኔ መኪና ውስጥ ያለን ጀማል የተባለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ፍቃድ እንዲጠይቁ ጠባቂዎቹ በነገሯቸው መሰረት እነ ስለሺ አቶ ጀማል ዘንድ ይሄዳሉ ።
አቶ ጀማል ‘’ከየት ነው የመጣችሁት’’ ? እነ ስለሺ ‘’ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን’’ ። ስለሺ እንደሚለው አቶ ጀማል መገናኛ ስልካቸውን አውጥተው ወደ ጠባቂዎቹ አለቃ ይደውላሉ ። የቢቢሲን ወኪል ለምንድን ነው ያስገባችኋት ? ይጠይቃሉ አቶ ጀማል ። ያኔ ኒታ ባላ የምትባል የቢቢሲ የአዲስ አበባ ወኪል ገብታ ግጭቱን የተመለከተ ዜና በዌብ ሳይት ለቃ ነበር። በዚህ የተበሳጩት አቶ ጀማል የጠባቂዎቹን አለቃ ከሰደቡ በኋላ ‘’ አሁን የኢቲቪ ሰዎች ስለ መጡ ለማስተባበል እንዲመች አስገቧቸው ። ነገር ግን 205 ህንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ ያለው ደም እንዳይቀረጽ
‘’ የሚል
ቀጭን
ትዕዛዝ
ይሰጧቸዋል
። ትዕዛዙንም ሆነ ኢቲቪ አስተባባይ መባሉን የሰማው ስለሺ አስተባባይ ያለመሆኑን ለማሳየት ቸኩሎ 3ኛ ፎቅ ያለው የተማሪዎች ደም ሳይጠረግ በካሜራው ለማስቀረት ፍጠኑ ብሎ ወደ ዋናው በር ያመራል። ጠባቂዎቹ በሩን ቢከፍቱም አንጀታቸው ያረረው ተማሪዎች የኢቲቪን ጋዜጠኞች አናስገባም አሉ። በዚህን ጊዜ ነበር ስለሺ ተማሪዎቹን ለማለዘብ ከፍ ያለ ቦታ ቆሞ መናገር የጀመረው። ‘’ ይህ መንግስት ነገ ይወድቃል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖ ይቀጥላል። እባካችሁ ደማችሁ ይቀረጽ ! የጥላሁን ግዛው ደም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አርካይቭ ውስጥ አለ የናንተም ደም ዛሬ ባይተላለፍ እንኳን አንድ ቀን ለአየር ይበቃል እባካችሁ ‘’ ገሚሱ ተማሪ ይቀረጽ በማለቱ እነ ስለሺ ካሜራቸውን ይዘው በሚንገበገቡ የተማሪ አይኖች እየተገረፉ ወደ 502 ህንጻ አመሩ በጣም ተደብድበው በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ያሉ ተማሪዎችን ስቃይ እና በተማሪ ደም የቀለሙ ግድግዳዋችን እና ወለሎችን ቀርጸው በካሜራቸው አስቀሩ።
በመቀጠልም ስለሺ በወቅቱ የተማሪዎች ጊዚያዊ ካውንስል አመራር ከነበሩት ፋሲል እና ተክሌ የግጭቱን መንስዔ እና ምክንያት ይጠይቃል ‘’ ተማሪዎች ስብሰባ ላይ እያለን ሁለት ጸጉረ ልውጥ ወጣቶችን ተመለከትን ተማሪ እንዳልሆኑ ስላወቅን መታወቂያ ጠየቅናቸው። የላቸውም ደህንነት መስሪያ ቤቱ እኛን እንዲሰልሉ ያስገባቸው መሆኑን በመጠርጠር ያዝናቸው። ይህንን የሰማው የደህንነት መስሪያ ቤቱ በአካባቢው የነበረን ታጣቂ ሀይል የዩኒቨርስቲውን በር ጥሶ እንዲገባ አደረገ ። ታጣቂው ተማሪዎችን ደበደበ’’ ይህንን ከተማሪዎቹ አመራሮች የወሰደው ስለሺ በወቅቱ የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ወደ ነበሩት ፕሮፌሰር ሞገሴ አሸናፊ ዘንድ ይሄዳል እሳቸውም ‘’ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሳያውቅ የጸጥታ ሀይል በር ጥሶ በመግባት ተማሪዎችን መደብደቡ አግባብ እንዳልሆነ በምስልም በድምጽም ተቀርጸው ተናገሩ። ይሄንን ይዞ ወደ ቢሮ ከተመለሰ ቧላ የትምህርት ሚኒስትሯን ሀሳብ ለማግኘት መደዋወል ጀመረ ። ሚኒስትሯን አግኝቶ ለቃለ መጠይቅ ወደ አራት ኪሎ ያመራል ሚኒስትር ገነት ዘውዴም የጸጥታ ሀይል ያለ ትምህርት ሚኒስቴር ፍቃድ በር ጥሶ መግባቱን አወገዙ ። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር እጅግ ማዘናቸውን ይገልጻሉ ። ስለሺ ዳግም ወደ ቢሮ ተመልሶ የፖሊስ ኮሚሽንን ምላሽ ለማግኘት ሞክሮ አልተሳካለትም ። ዜናውን አጠናቅሮ ለኤዲተሩ ያቀርባል። የዜናው ሊድ ወይንም ርዕስ ‘’የአዲስ አበባ ፖሊስ ያለ ማንም ፍቃድ 6ኪሎ ዩኒቨርስቲ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን ደበደበ’’ የሚል ነበር። የወቅቱ ስራ አስኪያጅ ሶሎሜ ታደሰ የዜናውን ፊልሞች አይታ አንዳንድ የበዛ ደም ያለባቸው ምስሎች እንዲወጡ በማለት ዜናውን አድንቃ እንዲተላለፍ ፈቀደች።
ስለሺ እሱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኖ በነበረው የ1985 ‘’የቡትሮስ ጋሊ ይውጣ’’ ትዕይንት ተደብድቦ አንድ ተማሪም ህይወቱ በጸጥታ ሀይል አልፎ ኢቲቪ የአዲስ አበባ ፖሊስን የተለመደ ተማሪዎችን የሚወነጅል እና የሚያጣጥል መግለጫ ነበር የሚያነበው ። በርሱ የጋዜጠኝነት ዘመን ኢቲቪ እሱ እንደሰራው አይነት ዜና ማስተላለፉ ስለሺ ሁሌም ስራ አስኪያጅ ለነበሩት ሶሎሜ ታደሰ ምስጋናውን ይሰጣል።
ያ ዜና የተላለፈ ምሽትም ሆነ በማግስቱ ነገሮች ተካረሩ ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን የተቃውሞ ትዕይንት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ተቀላቀሉት ። በተለይ ዩኒቨርስቲዎች አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዋነኛ ተዋናዮች ሆኑ ። አምስት ኪሎ የሚገኘው የፈተናዎች ድርጅት ተቃጠል።
ደርግ ያደርግ ከነበረው በምን ይለያል ?
ሚያዚያ 9 ቀን 1993 የኢቲቪ ዜና በተላለፈ በማግስቱ ከሰዓት በኋላ ትምህርት ሚኒስትር ገነት ዘውዴ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ በርካታ የመንግስት እና የፓርቲ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሚኒስትሯ ቢሮ ነበሩ። የሚኒስትሯ ቢሮ ከሚገኘበት 3ኛ ፎቅ ቁልቁል የሰማዕታት ሀውልት ይታያል። ከላይ ከ5ኪሎ በእሳት ተያይዘው ቁልቁል የተለቀቁ የመኪና ጎማዎች ብዙዎቹ ከትምህርት ሚኒስቴር ህንጻ ፊት ለፊት ከሚገኘው የያኔው የደህንነት ህንጻ ጋር ይጋጫሉ። የእነ ስለሺ ካሜራ ከሚኒስትሯ ቢሮ በመስኮት ቁልቁል ትዕይንቱን ይቀርጻል ። በዚህ ጊዜ ሁለት ወጣቶች ሁለት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዘው ይታያሉ ። ሊሎች ተማሪዎችም ወጣቶቹን ከበው ያወራሉ ። ካሜራው እነሱ ላይ ነው ። ወጣቶቹ ክላሹን አስፋልቱ ላይ ፈጠፈጡ ክላሹ ይሰበራል። ወዲያው ከሌላ አቅጣጫ የመጡ ወታደሮች አካባቢውን በተኩስ ያናውጡታል። ቆመጥ የያዙ ወታደሮችም ወጣቶችን አናት አናታቸውን ይሏቸው ጀመር። እነ ስለሺ በንዴትም በቁጭትም ቁልቁል ይቀርጻሉ ሚኒስትሯም እታች ያሉት ደብዳቢዎች ባይሰሟቸውም ለመጻፍ የሚከብድ ነገር ይናገራሉ ። ንግግሩም ካሜራ ውስጥ መግባቱን ስለሺ ይናገራል ።
ሚኒስትሯ ስለሺን ‘’ምነው ልጄ ትላንት አንተ ደም አሳይተህ ጅማ ምግብ አልበላም ብሎ ሲበጠብጥ አደረ ፣ አለማያ እቃ ሲሰባብር አደረ ፣ መቀሌ አንድ ተማሪ ሞተ እንዴት በመንግስት ሚዲያ እንደዛ አይነት ዜና ታስተላልፋለህ’’ የሚል ጥያቄ እና ወቀሳ ያቀርቡለታል።
ስለሺም እሱ ሪፖርተር እንጂ የስራ ሃላፊ አለመሆኑን እንዲተላለፍ ሀላፊነት ያለባቸው የበላይ አለቆቹ መሆናቸውን ። ይህንን ጥያቄም መመለስ ያለባቸው አለቆቹ እነደሆኑ ይገልጽና፣ ነገር ግን ይላል፣ ነገር ግን እነደ ሪፖርተር ሚዲያው የአንድ ወረዳ ታጣቂዎችን ጥፋት እና ስህተት ሲሸፍን መኖር አለበት ብሎ እንደማያምን መንግስት ተማሪዎቹ ላይ ጥቃት የፈጸሙ እና እንዲፈጸም ያዘዙ ሀላፊዎችን መርምሮ እንደሚቀጣ ቢገልጽ ምናልባት እሳቸው ያሏቸው ነገሮች ሊፈጸሙ ይችሉ እንዳልነበር ለማስረዳት ይሞክራል።
መግለጫው እንደተጀመረም ሚኒስትር ገነት ዘውዴ ‘’ ከዛሬ 12 ሰዓት ጀምሮ የፌደራል ጦር ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥተናል ‘’ ይላሉ ጥያቄ ለመጠየቅ የመጀመሪያውን እድል የወሰደው ስለሺ ‘’ይህ ትዕዘዝ ደርግ ያደርገው ከነበረው በምን ይለያል’’ የሚል ጥያቄ ያነሳል። ወይዘሮ ገነትም ‘’ እንዴ ደርግ እኮ አለም ያወቀው ጨቋኝ ነው እንዴት እኛን ከደርግ ጋር ታወዳድራለህ’’
በሚል
ጀምረው
መልስ
ይሰጣሉ።
መግለጫውን
ይዞ ወደ ቢሮ የተመለሰው ስለሺም ‘’ የፌደራል ጦር ወደ ዩኒቨርስቲዎች እንዲገባ የትምህርት ሚኒስትሯ ትዕዛዝ ሰጡ’’ በሚል ሊድ ዜናውን አዋቅሮ ለአየር አበቃው። ምሽትም የሚኒስትር ገነት ዘውዴ መግለጫ ሙሉውን አየር ላይ ዋለ።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተለይም የሶሎሜ አስተዳደር በኢሀዴግ ከፍተኛ ሹመኞች ጥርስ ውስጥ በዚህ አካባቢ ስለ መግባቱ ስለሺ ይስማማል ። በተለይ ለሹመኞቹ ቅርብ ከሆኑ ባልንጀሮቹ ዜናው መሰራት የነበረበት መንግስት መግለጫ ከሰጠ በኋላ ነበር የሚል አስተያየት ደርሶታል።
ኢቲቪ አዲስ ስራ አስኪያጅ ተመደበለት
ወይዘሪት ሶሎሜ 95 መጨረሻ ወይንም 96 መጀመሪያ ላይ ከሀላፊነቷ ተነሳች ። ብዙ የኢቲቪ ባልደረቦች አዘኑ ። ስለሺም አንዱ ነው ። ምክንያት አላቸው ሶሎሜ ስራ ለሚሰራ ባለሙያ እንደ አለቃም እንደ ታላቅ እህትም ነበረች። ብር አዋጥተው የአንገት ሀብል ሸልመው ነበር ሶሎሜን የሸኟት ። በሽኝቱ ላይ ሶሎሜ ‘’ ከልቤ አገለግለዋለሁ ብዬ የመጣሁበት ቤት ነበር ። እናንተን ይዤ እዚህ ሀገር ላይ ለውጥ የሚያመጣ ሚደያ ለመስራት ህልም ነበረኝ። ግን አልሆነም ። ለደሞዝ አልነበረም እዚህ የምሰራው ‘’ አለች እውነትም ያኔ ደሞዟ 2800 ብር ብቻ ነበር ከኢቲቪ ወጥታ ያገኘችው ስራ ከ 2000 ዶላር በላይ ነበር ደሞዝ የሚከፍላት። ምናልባት ስለሺ እንደሚያምነው በ1997 ለሚደረገው ምርጫ ሶሎሜ የምትመራው ሚድያ እንዳሻዬ ለመሆን አይመቸኝም በሚል የገዢው ሹመኞች ጫና በማሳደር ሃላፊነቷን እንድትለቅ ሳይገፏት አይቀሩም።
የእርሷን መልቀቅ ተከትሎ አቶ ብርሃን ሀይሉ የተባሉ ስራ አስኪያጅ እና ከየወረዳው የተወጣጡ የልማት ወኪሎች davolopment agents DA ወጣቶች ሚዲያውን ወረሩት ። ለቴሌቪዥንም በርካቶች ደረሱት ። እነዚህ የልማት አርበኞች ‘’ ቴሌቪዥን የበከተ በረት ነው አጽዱት ‘’ የሚል የስራ መመሪያ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።
በዚህ
መንፈስ
የመጡት
አርበኞች
አንዳንዶቹ
የገጠማቸው
እና የተባሉት እንደተቃረነባቸው
ለስለሺ
ይነግሩት
እንደነበር
ያስታውሳል።
አንድ ቀን አዲሱ ስራ አስኪያጅ ይፈልጋችኋል ተብለው የአማርኛ ማስተባበሪያ ሰራተኞች በቲቪ ላይብረሪ ተሰብስበዋል ። ምክትል ስራ አስኪያጁ አሰፋ በቀለ ‘’ብርሀን ሀይሉ ይባላሉ እስካሁን ያልተዋወቋችሁ በስራ ብዛት ነው’’ የሚል አጭር ማስተዋወቂያ ሰጥተው መድረኩን ለአዲሱ ስራ አስኪያጅ ይሰጣሉ ። አዲሱ ስራ አስኪያጅም በቀጥታ ወደ ጥያቄ ይገባሉ ‘’ የእርስ በርስ ግንኙነታችሁ ምን ይመስላል? ነበር ጥያቄያቸው’’ የሚመልስ ሲጠፋ ማብራራት ጀመሩ ‘’ ሪፖርተሮች ከሹፌሮች ወይንም ከኤዲተሮች ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል ‘’ አሉ። አሁንም ቤቱ ዝም አለ ። በመሀል ሙሉ ጥቁር ሱፍ በቀይ ክራቫት ለብሶ ከፊት ከተቀመጡት ሪፖርተሮች የእድል ስጡኝ እጅ ተነሳ ። ስለሺ ነበር ። ቀጠለ ‘’ የቤቱን ቅዝቃዜ ለማሞቅ እርስዎ የትምህርት ደረጃዎን ፣ የስራ ልምድዎን ቢገልጹልን ወደ ኢቲቪ ሲመጡስ ምን ለማድረግ ምን ለመለወጥ አስበው እንደመጡ ቢነግሩን እኛም ፈታ ብለን እንነጋገራለን’’
ብሎ ይዘጋዋል። ስለሺ እንደሚለው ይህንን ጥያቄ አዲሱ ስራ አስኪያጅ ራሳቸውን ቤተሰባዊ እንዲያደርጉ እድሉን ልስጣቸው በሚል ነው ያቀረበው። የአቶ ብርሀን መልስ ግን የንዴት የድምጻቸው ቶንም የቁጣ ይመስላል። ‘’
የትምህርት
ደረጃ
ላልከው
ለቦታው
ቢኤ ነው ኤም ኤ ነው የሚገባው የሚለውን ከፈለጋችህ ልንወያይበት እንችላለን ። ከአለማያ ዩኒቨርስቲ ቢኤ ዲግሪ አለኝ። የስራ ልምድ ላልከው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ሆኜ ለረጅም ጊዜ ሰርቻለሁ ከግራስ ሩት ሌቭል ጋር የመስራት ጥሩ ልምድ አለኝ። በፌደራል ደረጃ ስመደብ ይህ የመጀመሪያዬ ነው አፍተር ኦል እኔ የመንገስት ሹመኛ ነኝ መንግስት ፖሊሲዬን ያስፈጽምልኛል ብሉ ሾሞኛል ። ይሄው ነው ‘’ ብለው አሳረጉ። ያለ ምንም ውጤት ያ ስብሰባ አለቀ ። ከስብሰባ ሲወጣ አንዳንድ የስለሺ ባልደረቦች ያንን ጥያቄ መጠየቅ እንዳልነበረበት በመግለጽ ‘’ ሰውየው ይጠምድሀል።’’ ብለውታል እሱም ሁሌም በነጻ አዕምሮ ያሰብኩትን ፊት ለፊት የመናገር
መብቴን
መጠቀም
አለብኝ
አለበለዚያ
የኔ መኖር ትርጉም ያጣል’’ ነበር መልሱ ። እንደጠበቀውም ስለሺ ያንን ጥያቄ በማንሳቱ ምንም የደረሰበት ክፉ ነገር የለም እንዲያውም ቲቪ አውጥቶት ለነበረው የምክትል ዋና አዘጋጅ የስራ ቦታ ተወዳድሮ በአቶ ብርሀን ሀይሉ ፊርማ ነው አልፈሀል በከፍተኛ ሀላፊነት ተግባርዎን እንዲወጡ ከአደራ ጋር አሳስባለሁ የሚል የዕድገት ደብዳቤ የደረሰው።
የ97 ምርጫ በሚድያ ሰዎች ላይ ብዙ ጦስ ይዞ መጥቷል ስለሺም የዜና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ ከአንዳንድ ሪፖርተሮች ጋር መጋጨቱ አልቀረም ። ያኔ የምርጫ ክርክር እሁድ ጠዋት በቀጥታ ስርጭት ይተላለፍ ነበር ። ይህንን በቀጥታ የተላለፈ ክርክር ዜና ሊሰሩ የተመደቡ አንዳንድ ሪፖርተሮች ከክርክሩ ይዘት ውጭ የገዢውን ፓርቲ የሚያወድስ ዜና ሰርተው ይመጡ ነበር ። የስለሺ ሙግትም ሰዉ በቀጥታ ስርጭት ሲሰማው የዋለውን እውነት እንዴት እንዲህ አይነት ተራ ፕሮፓጋንዳ ይዛችሁ ትመጣላችሁ የሚል ነበር። እነዚህ ‘’ሪፖርተሮች’’ ገዢው ፓርቲ ላይ የሚሰነዘር ትችት ሁሉ የሚያንገበግባቸው ። በዜናም ሊጠቀስ ይገባዋል ብለው የማያምኑ መሆናቸውን ስለሺ ይመሰክራል።
አንዴ አንድ የትግርኛ ክፍል ባልደረባ ዜና ይወጣ እና ያንን ዜና በአማርኛ ሰርቶት ይመጣል ስለሺ የዕለቱ አዘጋጅ ነበር ። ብዙውን ጊዜ ከሪፖርተሮች የሚመጡ ዜናዎችን ኤዲት ሲያደርግ ስለሺ ድምጽ አውጥቶ ነው የሚያነባቸው ። አንድም ሙሉ ቀልቡን ዜናው ላይ ለማሳረፍ ሁለትም ሪፖርተሩ ሲያነበው ወይንም ድምጹን ሲቀረጽ በአንድ ትንፋሽ ምን ያህል መሄድ ይችላል ብሎ አርፍተ ነገሮችን አጠር አጠር እንዲሉ ለማድረግ ነው ።
ከትግርኛ ክፍል ባልደረባ የመጣውንም ዜና ሌሎች ሪፖርተሮች ባሉበት ልጁም አጠገቡ እያለ አነበበው። ‘’ በህወሃት መካከል የተነሳው አለመግባባት በሰላም ከተፈታ ስለት አስገባለሁ ብለው ያተሳሉ እናት ስለታቸው በመድረሱ አንድ በሬ እና ድፎ ዳቦ አስገቡ ‘’ ይላል ሊዱ። ስለሺ ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ቀና አለ። ቢሮ ውስጥ የነበሩ የአማርኛ ሪፖርተሮች ምን ሊል ነው ብለው አሰፈሰፉ። ስለሺ ኮስተር ብሎ ለትግርኛ ሪፖርተሩ ጥያቄ ማቅረብ ጀመረ ። ‘’በሬው የስንት ብር ነው ? ‘’ ዋ እኔ ምናውቃለሁ ሲያዩት ትልቅ ነው። ዳቦውስ ምን ያህል ኪሎ ዱቄት ፈጀ ? እሱንም አላውቅም ከፈለክ ደውዬ መጠየቅ እችላለሁ። የህወሃት ያለ መግባባት በሰላም ተፈቷል ወይ ? በሰላም መፈታት ማለትስ ምን ማለት ነው ? ሴትየዋስ የየትኛው ወገን ደጋፊ ናቸው ? የአማርና ዜና ክፍል ባልደረቦች ሳቃቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ። ስለሺ ምንም አልሳቀም ለትግርኛው ሪፖርተር አለው ይህ ዜና - ዜና እንዴት እንደማይሰራ ማሳያ ይሆናል ብሎ እንዲህ አይነት ዜናዎችን ጠብቆ ወደሚያስቀምጥበት
ፋይል
አስገባው።
የትግርኛው
ሪፖርተር
ሊሞግት
ሊያስረዳም
ሆነ ሊያስፈራራ ሞከረ ስለሺም የመጨረሻ ቃሉን ነገረው ‘’ ከፈለክ በትግርኛ ዜና ላይ እንደፈለክ አድርገው ይህ የአማርኛ ዜና ነው አዘጋጁም እኔ ስለሺ ነኝ’’ ጠብቅ አሳይሃለሁ እያለ ሪፖርተሩ ወጣ ስለሺም ፈገግታውን ጋብዞ ስራውን ቀጠለ።
ኢቲቪ ደህና ሰንብት
የ97 ምርጫ ክርክር በተጋጋማበት የታህሳስ ወር መጨረሻ በኢቲቪም ሁኔታዎች ጦዘው ነበር ። የግል ጋዜጦችን ይዞ ወደ ቢሮ መግባት አስፈሪ እና አስፈራጅ ሆኖ ነበር ስለሺ ደግሞ መኖሪያ ቤቱ ከነበረው አምባሳደር ሰፈር ሲወጣ ብዙ ጋዜጦችን የያዙ አዟሪዎች ይጠብቁታል ። አንድ ሁለት ሶስቱን ገዝቶ ፖስታ ቤት መግቢያው ላይ ካለችው ካፌ ከአሪፍ ማኪያቶ ጋር ዋና ዋና ዜናዎችን አይቶ ትንታኔዎችን ለማንበብ ወደ ቢሮው መግባት የዘዎትር ተግባሩ ነው። በኢቲቪ ያለው ሁኔታ እንደማያስቀጥለው በተረዳበት ሰዓት ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የእኛ ዘንድ ና ጥሪ ይቀርብለታል። ዋልታ ያኔ ከኦሮምያ ክልል ጋር ከ4ሚሊዮን ብር በሚልቅ ክፍያ ደኩሜንተሪ ሊሰራ ውል ገብቶ ነበር ። እነዚህን ዶክሜንተሪ ፊልሞችን ጥሩ አድርጎ ሊሰራ የሚችል ባለሙያ ሲያፈላልግ ስለሺ ሽብሩ እና ታደሰ በላቸው አይኑ ውስጥ ገብተዋል ። ስለሺን ለኦሮምያ ታደሰን ለደቡብ ያኔ ከፍተኛ በሚባል የደሞዝ ዝውውር አሰፈረማቸው።
ዋልታ በቆየባቸው 3 ዓመታት ስለሺ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሀገሬ በሚል ርዕስ ለአየር የበቁ በርካታ ዶክሜንተሪዎችን ሰርቷል ። በዋናነት ጽሁፍ ዝግጅት ፣ በካሜራ ዳይሬክቲንግ ፣ አንዳንዴም በትረካ የተሳተፈባቸው እነዚህ ደኮሜንታሪ ፊልሞች ዛሬም በዋልታ ቴሌቪዥን የሚተላለፉ ጥሩ ስራዎች ናቸው ።
በተለይ የሶፍ ዑመር ገሞ ላይ የተሰራው ደኩሜንተሪ ስለሺ እንደሚለው መቼም ከአእምሮው አይጠፋም። የአካባቢው ሰዎች ሶፍ ዕመርን ዋሻ አይሉትም ለነርሱ ታላቅ የክብር መሰብሰቢያ ፣ ታላቅ ክብረ በዓል የሚደረግበት ቦታ ፣ የተከበረ ስፍራ ስለሆነ ዋሻ የሚለው የአማርኛ ቃል ያንሰዋል ይላሉ።
የሶፍ ዑመርን ገሞ የዌብ ወንዝ በሚገባበት በአዩ መኮ በኩል ገብቶ ወንዙ በሚወጣበት በሁሉቃ በኩል ሙሉ ፊልም እየሰራ የወጣ የፊልም ቡድን ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላም እንዳልሰማ ስለሺ ይናገራል።
ግርማ የሚባል ጓደኛ ነበረው ሶፍ ኦመርን ለመስራት ዝግጅት ላይ ያለ ሰሞን ። ግርማ የ1967 የእድገት በህብረት ዘማች ነው ። ምድቡም ሶፍ ኦመር ወረዳ ላይ ነበር ። ከጓደኞቹ ጋር ሶፍ ኦመር ውስጥ ገብቶ መጓዝ እስከቻሉ ድረስ ሄደው ስማቸውን ጽፈው መውጣታቸውን ነግሮ አደራ ስሜን ፈልግልኝ ብሎታል።
ከ ሰባቱ የሶፍ ኦመር ወንዝ ማቋረጫዎች ውሰጥ የመጀመሪያው ማቋረጫ ላይ ከለው ቋጥኝ የበርካታ ዘማቾች ስሞች በጥቁር ቀለም ቁልጭ ብለው ይታያሉ። ከ31 አመት በኋላ የዘማች ግርማን እና የጓደኞቹም ስም የፊልሙ አካል ሆኖ ነበር።
በዋልታ የ 3 ዓመት ቆይታው ከሶፍ ኦመር በተጨማሪ የድሬ ሼኽ ሁሴንን ፣ የጉማ ስርዓትን ፣ የኦሮሚያ ደን እና ፏፏቴዎችን ፣ የኦሮሚያ ሀይቆችን ፣ የባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክን ከዲንሾ እስከ ሰናቴ ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የጩምቦ እና አንጮቴን ፣ በኮኮሳ ባህላዊ ሰርግን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊ ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ሁነቶች ላይ መልካም የሚባሉ ደኩሜንተሪዎችን
ሰርቷል።
ከነዚህም
በላይ
ከህንዷ
ሙምባይ
ወደብ
ጅቡቲ
ድረስ
አባይ
ወንዝ
ትባል
በነበረችው
መርከብ
7 ቀን
እና ለሊት በመጓዝ የመርከበኞችን ህይወት እና የመርከብን ስራ እና ኑሮ የሚያሳይ ደኩሜንተሪ ሰርቷል።
ጉድ ባይ ደህና ሁኚ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ መላው የጠፋበት ነበር የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ። የገዢው ፓርቲ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮችም ‘’በትግላችን ያመጣነው ሚሊኒየም’’ በማለት መግለጫ እስከ መስጠት ደፍረው ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የኦዶቪዥዋል ባለ ሙያ እፈልጋለሁ ብሎ ማስታወቂያ ያወጣው። አስፈላጊ መስፈርቶችን አሟልቶ ፣ ቤተሰቡንም ከ6 ወር በኋላ መውሰድ እንደሚችል ተስማምቶ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ወደ ሳዕዲ ዓረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ አመራ። እነደተባለውም ባለቤቱ ሜሮን መክብብ እና ልጁ ኖህ ስለሺ በ6ኛው ወር ተቀላቀሉት ።
በሪያድ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቆይታው የትምህርት ቤቱን ፣ የማህበረሰቡንም ሆነ የኤምባሲውን ስራዎች ቪድዮ መስራት፣ ፎቶ ግራፍ ማንሳት ፣ ስክሪፕት እየጻፉ ኤዲት እያደረጉ ለወላጅም ለትምህርት ቤቱ አርካይቭም ማስቀመጥ አንዳንዴም ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ልኮ እንዲተላለፉ የማድረግ ስራዎችን አከናውኗል። በኋላ ላይም የጀርመን ድምጽ ሬድዮ የሪያድ ወኪል ሆኖ ለ 4 ዓመታት ሰርቷል ። ዶቸ ቨሌ ዋና መስሪያ ቤቱ ያለበት ቦን ወስዶ የ 3 ሳምንት ስልጠና በሬድዮ ጆርናሊዝም ፣ በሞባይል እና ኦንላይን ጆርናሊዝም ስልጠና ሰጥቶታል።
በተለይ በ2008 ህዳር ወር የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ‘’ህገወጥ’’ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ከሀገሬ ውጡልኝ ብሎ በየ ማጎሪያ ካምፕ የጣላቸው ጊዜ የወገኖቹን ሰቆቃ በየ ቦታው እየዞረ ፊልም አድርጓል ። ከስክሪፕት ጋርም አዋህዶ ለሚመለከታቸው አካላት ሰጥቷል ፣ በማህበራዊ ሚዲያም አስተላልፏል፣ ለሰነድም አስቀምጧል። ሳዑዲ አረቢያን ስለሺ ረጅም የጥሞና ጊዜ ያገኘሁበት ሀገር ይለዋል ። ብዙ ያነበበበት ፣ ቴክኒካል የሆኑ የካሜራ እና የኤዲቲንግ እውቀቶችን ያዳበረበት ። ሁለተኛ ልጁን ሆሳዕናና ያገኘበት በርካታ ኢትዮጵያዊያንን የበረሀ ወዳጆች የተዋወቀበት ሀገር ነው ሪያድ ሳዑዲ ዓረቢያ። ከ2009 በኋላ የሳዑዲ ዓረቢያ ኑሮ አስቸጋሪ እየሆነ መጣ ። ኤክስፓት ሌቪ በሚል ስም በነፍስ ወከፍ ግብር ክፈሉ መባሉ ። በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ‘’ውጣ አትበለው ግን እንዲወጣ አድርገው’’ በሚመስል መርህ ሳዑዲ ለውጭ ሀገር ዜጎች ብዙም የማትመች ሀገር ለማድረግ የልዑል መሀመድ ቢን ሰልማን አስተዳደር በርካታ ተግባራትን አከናወነ።
እነደ መታደል ሆኖ ደግሞ በኢትዮጵያ ወያኔ መራሹ መንግስት ከስልጣን መወገዱ በኢትዮጵያም በአንጻራዊነት የመገናኛ ብዙሀን የተሻለ ስራ መስራት መቻላቸው ስለሺን ወደ ሀገሩ ጠቅልሎ እንዲገባ ገፋፋው።
2010 መጀመሪያ ላይም የ9 ዓመት የሳዑዲ ዓረቢያ ኑሮውን አጠናቆ 2 ልጆቹን እና ባለቤቱን ይዞ ወደ ሀገሩ ጠቅልሎ ገባ።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን በአዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ስራ ሲጀምርም ከመጀመሪያዎቹ ስታፎች ስለሺ አንዱ ነበር። ለ 6 ወራት ያህልም በዜና ክፍል አዘጋጅነት ሰርቷል ። ከዚያም በናሁ ቴሌቪዥን በዜና ክፍል ሀላፊነት ከ 2 ዓመት በላይ ቆይቷል። ስለሺ እንደሚያምነው ህይወቱም ኑሮውም ሆነ ስሜቱ ከሚዲያ ጋር የተሸመነ ነው። ሚዲያ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት ዋነኛው መሳሪያ ነው ብሎ ያምናል ። በናሁ ቲቪ ቆይታው ይህንኑ እምነቱን ሊያጠናክር የሚያስችሉ የፕሮግራም ፎርማቶች ላይ ያተኩር ነበር ። በተለይ የስቱዲዮ ውይይቶች ህዝብን የሚያነቁ መብት እና ግዴታውን እንዲያውቅ ፣ በስሜት እንዳይነዳ ፣ እውቀት መር የሆነ አስተሳሰብ ማህበረሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ላማድረግ የበኩሌን ጥረት አድርጌያለሁ ብሎ ያምናል ስለሺ።
የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንቶች እንደሚሉት ትውልድ በእድሜ እርከን በ 3 ይከፈላል። እስከ 33 ያለው ትውልድ የመጀመሪያው ፣ እስከ 66 ያለው ሁለተኛው እና ከ 66 በላይ 3ኛው ትውልድ ይሉታል።
የሁለተኛው ትውልድ አባል የሆነው ስለሺ ከ3ኛው ትውልድ ያገኛቸውን በርካታ ሙያዊ ክህሎቶች ለመጀመሪያው ትውልድ የማስተላለፍ ሀላፊነት እንዳለበት ያምናል። መልካም ስብዕናና ስነ ልቦና ፣ ቅንነት እና መልካምነት ፣ ከመልካም እውቀት እና ልምድ ጋር ቢገናኙ የሚዲያ ሰው ለመሆን ጥሩ ግብዓቶች ናቸው ይላል ስለሺ። አሁንም በፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ጽህፈት ቤት በኮሚኒኬሽን ዳይሬክተርነት በማገልገል ላይ ይገኛል።
መዝጊያ፣ ስለሺ ሽብሩ ለመረጃ ቅርብ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለውም ግንኙነት እጅግ መልካም ነው፡፡ ከአንድ የሚድያ ሰውም እንዲህ መሆን ይጠበቃል፡፡ ስለሺ ግለ-ታሪክ ይወዳል፡፡ አውደ- ሰብ ላይም አሻራውን በማሳረፉ የሰው ታሪክ ጉዳይ ይስበዋል፡፡ ኢቲቪ በሰራባቸው 8 አመታት የስራ መሪ ብቻ ሳይሆን ደፋርም ነበር፡፡ ገና የ2ኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ከእውነት ጋር መጋፈጥ ጀመረና ጋዜጠኛ ሆኖም ይህ ጉዳይ ተከለተው፡፡ ይህም በጣም የሚያስከብረውና ለየት ብሎ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡ በምን አይነት ጥረት እና ልፋት ስራውን አየር ላይ ያውል እንደነበር አብረውት የሰሩ አበጥረው ያውቃሉ፡፡ ስለሺ ባህር ማዶ ወይም ሳኡዲ በነበረ ጊዜም ከሚድያ ብዙም ሳይርቅ ሀገሩን
በብቃት
እና በሙሉ ሃላፊነት ሲያገለግል ነበር፡፡ በቅርባችን ያሉ ሰዎችን ምን ሰሩ ብለን ስለማናይ እንጂ በርካታዎች ድምጻቸውን አጥፍተው ልታወቅ ሳይሉ ሰርተዋል፡፡
ስለሺም
በእኛ
እይታ
ከእንደነዚህ
አይነቶቹ
ሰዎች
ተርታ
ይመደባል፡፡
ይህን
ዊኪፒዲያ
ያዘጋጀን
ሰዎች
ታሪካቸውን
ለምንሰራላቸው
ሰዎች
ሙሉ ሃላፊነት ወስደን መመስከር እንችላለን፡፡ ስለሺ በዘመኑ በወርቃማው የኢቲቪ ቆይታው ጀግኖ የሰራ በመሆኑ ይህን ዊኪፒዲያ የሚያነቡ ሁሉ ያመሰግኑታል፡፡
/ ይህ
ጽሁፍ
95 ከመቶ
ከባለታሪኩ
በተገኘ
እና ቅርጽ በያዘ መልኩ የተሰራ ሲሆን የክትትል እና የአርትኦት ተግባሩ ደግሞ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሀምሌ 6 2013 በውኪፒዲያ ላይ ወጣ ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ