21. ይምበርበሩ ምትኬ ገብረጻድቅ  YIMBERBERU MITIKE GEBRETSADIK

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ የብዙዎችን ታሪክ እያሰባሰበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ወደፊትም የባለሙያዎች ታሪክ ራሱን ችሎ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ  በሆነ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊታተም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል  የስፖርት ጋዜጠኛው ጋሽ ይምበርበሩ ምትኬ ይጠቀሳል፡፡

 

ጋሽ ይምበርበሩ ምትኬ ፕላዛ ሆቴል አካባቢ በሚገኘው ቤቱ የጡረታ እድሜውን እያሳለፈ ይገኛል፡፡  ጋሽ ይምበርበሩ ሊረሳ የማይገባ ጋዜጠኛ የብዙዎች ባለውለታ መሆኑን  እንመሰክራለን፡፡ በኦን ላይን ሚድያ ለመጀመሪያ በሚባል መልኩ የጋሽ ይምንበርበሩን ታሪክ አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ጋሽ ይምበርበሩን ለማስታወስ ምክንያት የሆኑን አቶ ሀይሉ ወልደጻድቅና  ልጃቸው እመቤትን ማመስገን  እንወዳለን፡፡ በተለይ ጎግል ፎቶዎች ላይ የጋሽ ይንበርበሩን አንድም ምስል አላገኘንም ነበር፡፡ አሁን ከዚህ ጽሁፍ ጋር የጋሽ ይምበርበሩን የሚድያ ጉዞ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን  ወጥተዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ላልተነገረላቸው እንቁም ላልተዘመረለት እንዘምር፤ የሰሩ ይታወቁ የሚል መርሁን ተግባራዊ ለማድረግ እነሆ የጋሽ ይንበርበሩን ታሪክ ታነቡ ዘንድ ጋበዝን፡፡

 

                     ልጅነት

 

በስፖርት ጋዜጠኝነቱ ሁላችንም የምናደንቀው ጋሽ ይምበርበሩ ምትኬ  ዘንድሮ 81 አመቱ ላይ ሆኖ  ያሳለፈውን ወርቃማ ጊዜ ያስታውሳል፡፡ ጋሽ ይንበርበሩ በሰሜን ሸዋ በመርሀቤቴ ወረዳ በቡርቃቶ ገበሬ ማህበር 1932 የተወለደ ሲሆን  በአካባቢው በነበረው ባህል መሰረትም  ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደልን ቆጥሯል፡፡ ወላጅ አባቱ አቶ ምትኬ ገብረጻድቅ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ በስሙ ተስፋ ይባላሉ፡፡

 

ታዳጊው ይምበርበሩ ምትኬ 9 አመት ሲሆነው 1941 መሆኑ ነው የእናቱ ታናሽ ወንድም ዘንድ አዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ መጥቶም በቅዱስ ዮሀንስ ቤተ-ክርስቲያን ንባብ እየተማረ ሳለ  በአመቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ወደምታስተዳድረው ኮልፌ ሰዋስው ብርሀን ተማሪ ቤት በአዳሪነት ገባ፡፡ እዚያም መደበኛ ትምህርትን ተከታትሎ 5 ክፍልን ጨረሰ፡፡ 1947 መስከረም ወር ላይ ሲዳሞ ክፍለሀገር በይርጋለም ከተማ በኖርዌጅያን ሚሲዮን መምህራን ማሰልጠኛ 2 አመት ተምሮ ተመርቋል፡፡ በጋሞጎፋ ክፍለሀገር በኮንሶ ወረዳ ሚሲዮን በሚያስተዳድረው /ቤት ለአንድ አመት አስተምሯል፡፡

 

    ትምህርትና ስራ

 

ይምበርበሩ ምትኬ ከፍተኛ የትምህርት ጥማት ስለነበረውም 1949 መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ  በመድሀኒአለም ባላባት ተማሪ ቤት 8 -12 ክፍል አጠናቅቋል፡፡ 1956 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ፋክልቲ ለአንድ አመት ከቆየ በኋላ  ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ የኢትዮጵያ መካነ-ኢየሱስ  ቤተ-ክርስቲያን ታስተዳድረው በነበረው የምስራች ድምጽ ሬድዮ  በልጆች ክፍለ-ጊዜ አዘጋጅነት ተቀጠረ፡፡  በዚያ መስሪያ ቤት በልጆች ፕሮግራም አዘጋጅነቱ ሳይወሰን በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ  እስከ 1966 ድረስ ሰርቷል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎቱን ለመቀጠል እንዲያመቸውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች አስተዳደር ክፍል ለአንድ አመት ተኩል አገልግሏል፡፡

 

ወደ ሚድያ አለም፡፡

 

1967 ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር  ተዛውሮ በሬድዮ መምሪያ በጡረታ እስከተገለለበት  እስከ 1986 ድረስ በስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅነት አገልግሏል፡፡ የተመደበበትን ስራ በብቃት መወጣት ይችል ዘንድም  1960 በሬድዮ ፕሮግራሞች አጻጻፍ ስልት በናይሮቢ ኦል አፍሪካን ቸርችስ 4 ወራት ተከታትሎ  ሰርተፊኬት አግኝቷል፡፡ 1977 ደግሞ በቼኮዝሎቫኪያ ጋዜጠኝነትን በተመለከተ ተምሮ ዲፕሎማ ሊያገኝ ችሏል፡፡

 

ጋሽ ይምበርበሩ አጠቃላይ በሚድያ ስራ 29 አመት በላይ ያገለገለ ሲሆን  19 አመቱን በስፖርት ጋዜጠኝነት አገልግሏል፡፡ እንደ ደምሴ ዳምጤ  ያሉ ጋዜጠኝነት ሙያ እንዲመጡ ትልቁን ድርሻ የተወጣው ጋሽ ይምበርበሩ ነበር፡፡  10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር 1968 ሲከናወን የውድድር ዝግጅቱ የተቃና እንዲሆን ጋሽ ይምበርበሩ የጎላ ሚና ነበረው፡፡ ለዚህም አስተዋጽኦው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ፊርማ ያረፈበት  የምስጋና የምስክር ወረቀት  ተበርክቶለታል፡፡ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የአለም እግር ኳስ ውድድር ተከናውኖ እንዳበቃ  መግለጫ ወይም በጨዋታው ላይ የእንዴት ነበር ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ትንታኔ ላይ ጋሽ ይምበርበሩ ምትኬ በመታደም ስለ ጨዋታው አስፈላጊ እና ወሳኝ ጥያቄዎችን ያቀርብ ነበር፡፡

 

አደራ ተቀባዩ ጋሽ ይንበርበሩ

 

ወይዘሮ መንበረ ግርማ  ከጋሽ ይምንበርበሩ ጋር የቅርብ ዘመድ ናቸው፡፡ ይንበርበሩ ትልቅ ውለታ የዋለልኝ  ድንቅ ሰው ነው የሚሉት ወይዘሮ መንበር ልጄን ወልጄ 8 ወሯ ጀምሮ አሳድጎ ለቁምነገር ያበቃልኝ ነው፡፡ ለዚህ ውለታውም ዝንተ-አለም አመሰግነዋለሁ ሲሉ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

 

ወይዘሮ መንበረ ጋሽ ይንበርበሩን ሲገልጹት ‹‹ እጅግ ቆፍጣና ብሎም ቆጠብ  ያለ ይሉታል፡፡ ጋሽ ይንበርበሩ ሰው  ሲያዝን ደራሽ ነው፤ ሰው ህመም ሲገጥመው ቀድሞ ተገኝቶ መላ ያበጃል፡፡ በዚህ ባህሪው በብዙዎች የተወደደ እንደሆነ ወይዘሮ መንበረ ይናገራሉ፡፡

 

  የግንባር ስጋ

 

የቀድሞ ጋዜጠኛ እና ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ ደግሞ  1968 ግድም ጋሽ ይንበርበሩ ጋር መተዋወቁን ይናገራል፡፡ ከዚያም 1972 የኢትዮጵያ ሬድዮን ስፖርት ክፍልን ሲቀላቀል ዋና አዘጋጆ ይንበርበሩ ምትኬ ነበር፡፡

 

‹‹ ጋሽ ይምርበሩ ሁላችንንም ስነ-ምግባር ያስተማረን ሀቀኛ ጋዜጠኛ ›› ሲል ግርማ ነጋሽ  ለቀድሞ አለቃው ያለውን አድናቆት ይገልጻል፡፡

 

ግርማ እንደሚናገረው ይንበርበሩ ኳስ ሲዘግብ የተመለከተውን ነገር   ብቻ ይዘግባል፡፡ ለእውነት የቆመ የስፖርት ጋዜጠኛ መሆኑን ብዙዎቹ ያውቃሉ፡፡ አለባብሶ ማለፍ የሚባል ነገር ይንበርበሩ ጋር አይሰራም፡፡ ብዙዎች በዚህ ባህሪው የግንባር ስጋ ሲሉ ስም ያወጡለታል፡፡

 

ጋሽ ይምበርበሩ ስራውን ካከናወነ በኋላ ቀጥታ ወደ ቤቱ ነው፡፡ ግርማ እንደሚያስታወሰው ‹‹ ይንበርበሩ ጭምት ነው፤ ቆጠብ ያለ ነበረ፡፡ ቀልድና ጨዋታ ጀምረን ከሆነ እርሱ ሲመጣ በዝምታ እንሞላለን፡፡ ከአክብሮት ጋር፡፡ ጋሽ ይንበርበሩ ቆጠብ ያለና ብዙም ቀልድ ነገሮችን የማይወድ በሚሰራው ስራ ላይ ብቻ አጽንኦት የሚሰጥ ሰው ነው ›› ሲል ግርማ  ነጋሽ ይገልጸዋል፡፡

 

ምሩጽ ይፍጠር በሞስኮ ኦሎምፒክ ባሸነፈ ጊዜ ዘገባውን ያስተላለፈው  ጋሽ ይምበርበሩ ምትኬ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ካኖሩት ውስጥ አንዱ ነው፡፡  ጋሽ ይንበርበሩ የተከበረ ታላቅ ሰው፡፡

 

መዝጊያ    ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበትና የተወዳጅ ዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት ከስምምነት የደረሱበት ነው፡፡

 

ኢትዮጵያ የሚከበሩ ሰዎች እያሏት ሰው ማክበር አታውቅም፡፡  በቀጥታ የሚድያ ሰዎች የተረሳን ከማስታወስ ይልቅ የታወቀን ያሳውቃሉ፡፡ ታዋቂዎች ብቻ የሚድያ ሽፋን ያገኛሉ፡፡ የሰሩቱ ግን ስለተደበቁ ወይም የሰሩ ስለማይመስል ታሪካቸው ወጥቶ መማማሪያ አይሆንም፡፡ ባለውለታ መዘንጋት ልማዳችን እየሆነ ከመጣ ሰነበተ፡፡ ጋሽ ይንበርበሩ መዘከር ያለበት ሰው ነው፡፡ ታሪኩ መጻፍ ያለበት ሰው ነው፡፡ እነ ደምሴ ዳምጤ ይንበርበሩ ነው ለዚህ ደረጃ ያበቃን ሲሉ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ፡፡ ግን እንዴት የጋሽ ይንበርበሩን ታሪክ በትንሹ ማውጣት ሳይቻል ቀረ? ጋሽ ይንበርበሩ ድንቅ ሰው ነው፡፡ ታሪኩን በማውጣት በኩል የቅርብ ቤተሰብ ትልቅ ሃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ግለ-ታሪክን ቆፍረው የሚያወጡ አዳኝ የግለ-ታሪክ አጥኚዎች የግድ ያስፈልጋሉ፡፡እነዚህ የግለ-ታሪክ አጥኒዎች በብዙ ቁጥር በየጓዳው ያሉ ለሀገር የደከሙ ሰዎች ወደ መድረኩ ብቅ በማለት ልምዳቸውን ማካፈል ይጀምራሉ፡፡ ለጋሽ ይንበርበሩ መልካም ጤንነት እየተመኘን ወደ ፊትም ሰፋ ያለ መጣጥፍ ይዘን እንደምንቀርብ ቃል እንገባለን፡፡/ ይህ ጽሁፍ የምርምር የቃለ-መጠይቅ እና የአርትኦት ስራው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ መስከረም 23 2014 በዊኪፒዲያ ላይ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ወጣ፡፡/

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች