16. ቢንያም ውብሸት ፍሰሀ-Biniyam Wubishet  FISSEHA

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ 120 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ከጋዜጠኝነት እስከ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ባለሙያነት የዘለቀው ቢንያም ውብሸት ነው፡፡ ቢንያም፤ በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተደማጭ የነበረ በተለያዩ የወጣቶች ጉዳይ ላይ ያተኮረ "ዳጉ አዲስ" የሚባል በሸገር አዲስ ለአመታት የዘለቀ ፕሮግራም አዘጋጅ፤ አስተባባሪ እና አቅራቢ በመሆንም ሰርቷል፡፡ መንግስታዊ ባልሆኑ የውጭ ድርጅቶች ውስጥ የሰራው ቢንያም በፈጠራ እንዲሁም ለውጥ ላይ ባተኮሩ የሚድያ ስራዎቹ ይታወቃል፡፡ ቢንያም ያለፈበትን መንገድ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

 

              ቸኮለ- ስሙንም ቀየረ

 

1966 . ነው ቢንያም የተወለደው፡፡ እናቱ / አስቴር አባይ ሲባሉ  አባቱ ደግሞ (ድምጻዊ) ውብሸት ፍስሃ ነው፡፡ ቢንያም  በአዲስ አበባ  ነበር የተወለደው፡፡ ከገጠር የመጡ የእናቱ ቤተሰቦች ጥምቀትን ለማክበር ሽር ጉድ ሲሉ ድንገት ስለተወለደ ቤተሰቦቹ ቸኮለ የሚል ስም አውጠለት-አድጎ ቢቀይረውም፡፡ አሁንም ድረስ እናቱን ጨምሮ ያደገበት በቅሎ ቤት አካባቢ ቢንያም ብሎ የሚጠራው ሰው ጥቂት ነው፡፡ ሶስቱም እህቶቹ ዛሬም ድረስ የሚጠሩት ቸኮለን በማቆላመጥ ቼክ እያሉ ነው፡፡

 

                        ገንዘቡን በመጽሀፍ ጨረሰ

 

እንዳሁኑ ቴሌቭዥን፤ ዲሽ እና ጌሞች በሌሉበት ዘመን ለተወለዱ እንደእነ ቢንያም ላሉ ልጆች ብቸኛ መዝናኛቸው ቅዳሜ ከሰአት የኢትዮጵያ ሬድዮ መዝናኛ ፕሮግራም  ነበር፡፡ካልሆነ  ባብዛኛው መጽሃፍ ማንበብ ነበር፡፡ በወቅቱ መጽሃፍ ማንበብ የሚበረታታበት ጊዜ ነበር፡፡ አይኑን መጽሀፍ ላይ ተክሎ የዋለ ለስላሳ ይጋበዛል፡፡ ያስከብራልም፤ ክረምቱ ሲያልፍ ከአስተማሪ ቁጣም የሚገላግል ነው፡፡ ያነበበ ልጅ የሚሸለምበት ጊዜ በመሆኑ መጸሃፍ ማንበብ ግዴታም አስደሳችም ነበር፡፡

 

ኋላ ላይ ይህ መጽሃፍ የማንበብ ልምድ ዳብሮ የቢንያም ዋና ወጪ እና እዳ የመጽኃፍ ዋጋ እንዲሆን አድርጎታል፡፡  በአሉ ግርማ፤ ብርሃኑ ዘርይሁን፤ ስብሃት /እግዚአብሄርን፤  የመሳሰሉ የሚያደንቃቸው ጸሃፊዎች ጋዜጠኛ መሆናቸው፤ ያም ደግሞ ለድርሰታቸው እንደረዳቸው ስላነበበ ሲያድግ ጋዜጠኛ ከተሳካ ደግሞ ደራሲ እሆናለሁ የሚል ምኞት አደረበት፡፡

 

         ስነ-ጽሁፍን መማር

 

የመጀመሪያ ደረጃ የተማረው ከቤቱ በአንድ አፍታ ሩጫ የሚደርስበት ጥበበ ገበያ የሚባል /ቤት ሲሆን 6 ክፍል 98 ፐርሰንታይል በማምጣት 1980 .. ጨርሶ ብሄራዊ /ቤት ደግሞ 7 እና 8  ክፍል የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አብዮት ቅርስ (የቀድሞወ ) /ቤት  (1981-84) ተምሯል፡፡

 

ቢኒያም የመጀመሪያ ዲግሪውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ(1986 .-1992 .) አጠናቋል፡፡ ፡፡  "የለሊት ሰው ነበርኩ" የሚለው ቢንያም የተማረው በማታ የትምህርት ክፍል ሲሆን ለሊቱን ደግሞ ትምህርቱን እና ህይወቱን ለመደጎም  በኮንኮርድ የምሸት ክበብ በዲጄነት ይሰራ ነበር፡፡ የዲጄነት ህይወቱም በብዙ ገጠመኞች የተሞላ ከት/ቤት በላይ ስለህይወት የተማርኩበት ቦታ ነው ይላል፡፡

 

      ደሞዝ ቀንሶ ሄራልድን ተቀላቀለ

 

የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጠኛ ሲሆን በዲጄነት ከሚያገኘው ገቢ 3 እጥፍ ባነሰ ደመወዝ ነበር የተቀጠረው፡፡ ይህ ከፍተኛ የገቢ ቅናሽ የሚወደውን እና የሚፈልገውን ስራ ደስተኛ ሆኖ ከመስራት ግን አላገደውም ነበር፡፡ ሰው የሚወደውን ነገር ሲሰራ ቢቸገርም እርካታው ዋና ክፍያው ነው ይላል፡፡

 

የስድስት አመት የጋዜጠኝነት ሙያው ኢትዮጵያን ከአዲስ አበባ ውጪ ምን እንደሆነች በተግባር አሳይቶታል፡፡ ጋዜጠኝነቱን እየሰራ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን የማስተርስ ዲግሪውን (1996 .-1998 .) ሰራ፡፡  ከአርሶ አደር እስከ የሃገር መሪዎች፤ ከታዋቂ ሰዎች እስከ አዋቂ ሰዎች፤ ከወጣት እስከ አረጋዊያን፤ ከችግረኞች እስከ ባለሃበቶች ወዘተቃለ-መጠይቅ አድርጓል፡፡ በስራ ዘመኑ 500 በላይ ዜና እና አርቲክሎችን ሰርቷል፡፡  በጋዜጠኝነት ቆይታው በጣም ቀላል የሆኑ ለምሳሌ እጅን በአግባቡ መታጠብ፤ ልጅ ሲታመም በፍጥነት ወደጤና ተቋም መውሰድ፤ ልጅን ማስከተብ፤ የኤች አይ መከላከያ ዘዴዎችን መተግበር፤ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት አደጋ ላይ እንደጣለ ተረዳ፡፡ እንደ ህዝብ በከንቱ የምንከፍለው የህይወት ዋጋ ያሳስበው ገባ፡፡

 

ከእርሱ ቀድመው የኮሚኒኬሽን/የተግባቦት ስራ ላይ የተሰማሩ ጓደኞቹ "ታዲያ ለምን የባህሪ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎች ላይ አትሳተፍም?" ብለው አበረታቱት፡፡

 

      የኮሚኒኬሽን ባለሙያው

 

ቢኒያም፤ የባህሪ ለውጥ ተግባቦትን/ኮሚኒኬሽን መርህ እና ስነ-ጥበብን በማዋሃድ ላለፉት 15 አመታት የጤና፤ የስርአተ ጾታ፤ የግብርና ምርት እና ምርታማነት፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋሙ ተቋማት ግንባታ፤ የማህበራዊ ተጠያቂነት መልእክቶችን አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ በእነዚህም ጊዜያት በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ፤ ዳንያ ኢንተርናሽናል፤ የአለም ጤና ድርጅት እንዲሁም .ኤን. ኢንተርናሽናል የሚባሉ መንግስታዊ ያልሆኑ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የተግባቦት ባለሙያ ሆኖ አገልግሏል፡፡

 

ከጋዜጠኝነት እንደወጣ የመጀመሪያ የባህሪ ለውጥ የተግባቦት ሰራ የጀመረው በጆንስ ሆፕኪንስ ዩንቨርስቲ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩንቨርስቲ በጤናው ዘርፍ በተለይም ደግሞ በህብረተሰብ ጤና በአለም ደረጃ ስመ ጥር ሲሆን ብዙ ምርምሮች የሚሰሩበት ተቋም ነው፡፡ ቢኒያም በዚህ ድርጅት ውስጥ የባህሪ ለውጥ የሚያመጡ ተከታታይ የህትመት ድራማዎች ጸሃፊ በመሆን ተቀጠረ፡፡

 

ከዚህ በፊት አንድም ድራማ ጽፎ ለማያውቀው ጋዜጠኛ ከታወቁ ጸሃፊያን ጋር ስራ መጀመሩ ፈተናም፤ ታላቅ እድልም ነበር፡፡ በባህሪይ ለውጥ ተግባቦት እና በምስል ከሳች አጻጻፍ ስመ- ጥር በሆኑ ባለሙያዎች ያገኘው ተጨማሪ ስልጠና የጤና እና መሰል ማህበራዊ ጉዳዮችን በተጠና እና በተቀናጀ እንዲሁም ጥበባዊ በሆነ መልክ ለመስራት አግዞታል፡፡

 

ባህሪይ በጊዜ ሂደት የሚዳብር እንደሆነ ሁሉ ሰዎች ምንም እንኳን ባህሪያቸው መቀየር እንዳለበት ቢያምኑም ባህሪ በአንድ ጀንበር አይቀየርም፡፡ የባህሪይ ለውጥ ስራዎችም ታዲያ ይሄንን ሳይንሳዊ እውነታ ይዘው ነው የሚሰሩት፡፡ ስለሆነም የባህሪ ለውጥ ላይ የሚቀረጹ ገጸ- ባህሪዎች እንደእውነታው አለም ያን ባህሪ ለመላቀቅ የሚያሰናክላቸውን እውነታ መሰረት አድርጎ ነው የሚሰራው፡፡

 

"በዚህ ስራ አንዱ እና ትልቁ ተግዳሮት ጥበብን እና የባህሪ ሳይንስን አስታርቆ መሄድ ነው፡፡ ለድራማው ጥሩ ነው ብለን የምንሰራው ነገር በፕሮግራም ሃላፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል፡፡ የፕሮግራም ሃላፊዎቸን ሃሳብ በሙሉ ተቀብለን ስናካትት ደግሞ ደረቅ እና እንጨት እንጨት የሚል ታሪክ ይሆንብናል፡፡ ይህንን ሚዛን ለመጠበቅ እና የተሟላ ለማድረግ ታዲያ ምጥ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ነው የፈጠራን (ክሬቲቪቲን) አቅም የምናየው" ይላል ቢንያም፡፡

 

ከዚህ በፊት ከሰራነው በተለየ እንዴት እንስራ? ስራችን በቀላሉ ተገማች እንዳይሆን ምን እናድርግ? ምን ቢመቻች የተሻለ ውጤታማ እንሆናለን? ምን አዲስ ነገር ማድረግ እንችላለን? በማለት ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ሃሳብ በመለዋወጥ የሚመጡ አስተያየቶችን ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ነው ብሎ ያምናል፡፡ "በቀላሉ ስብሰባ የምናደርግበትን ቦታ፤ ሰአት፤ መንገድ በመቀየር ብቻ ስራችን ላይ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ችለናል፡፡" ይላል፡፡

 

     ብትሰራም የሚያዝናናህን መርጠህ ነው

 

"የሚወዱትን ከሚሰሩ ከታደሉ ሰዎች እንደ አንዱ አድርጌ ራሴን እቆጥራለሁ፡፡ ለእኔ ስራ መሄድ መዝናኛ እንደመሄድ ነው፡፡" ይላል ቢንያም፡፡ ባለቤቱ እና 3 ልጆቹ እናት ደጋግማ "አንተ ምን ችግር አለብህ?  ብትማርም፤ ብትሰራም የሚያዝናናህን መርጠህ ነው፡፡" ትለዋለች፡፡

 

ለአዲስ አበባ ዩንቨርሰቲ "ላይፍ 101" ለመከላከያ "ጥቋቁር ነብሮች" ለፌዴራል ፖሊስ ደግሞ "ተወርዋሪ ከዋክብት" የሚባሉ የህትመት ድራማዎችን በመጻፍ፤ በማስተባበር ሰርቷል፡፡ ሶስቱም የህትመት ድራማዎች 30 በላይ ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን እያዝናኑ እያጫወቱ ለታለመላቸው ተደራሲያን ራሳቸውን ከኤች አይ ስርጭት እንዲከላከሉ፤ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ደግሞ እንዴት ጤናማ አኗኗር መኖር እንደሚችሉ እና የጸረ-ኤች አይ መድሃኒት ጠቀሜታ እና አወሳሰድ ላይ ያተኮሩ ናችው፡፡

 

በቡድን የሚሰሩ ስራዎችን አስቸጋሪ የሚያደርገው አንዱ ነገር ከሌሎች የተሰጡ አስተያየትን በቀላሉ ተቀብሎ ማስተካከል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም አስተያየት በሚሰጥ ጊዜ መተነካኮስ፤ ሌላውን ማሳጣት፤ መናቆር፤ አጉል አልሸነፍም ባይነት ይታያል፡፡ በዚህ ጊዜ ቢንያም ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ አስተያየቶች በቀና መንፈስ እንዲታዩ ነገሮችን በማለሳለስ ደግሞም ትኩረቱ እና ማእከላዊው ነገር የስራዎቹ የተሻሉ ሆኖ መቅረብ መሆኑ እንዳይሳት ይሰራል፡፡

 

"ስራችን እዚህ ያለነውን ካላሳመነ እና ትንሽም ቢሆን ቅሬታ/ ግርታ ከፈጠረ ሲወጣም ሺህዎችን ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርገን ይህን ስጋት እንቅረፍ ነው ዋናው ትኩረታችን መሆን ያለበት፡፡ አለመስማማት ለስራችን መሻሻል እና ነገሮችን ከሌላ አንጻር ለማየት መልካም ናቸው፡፡" በማለት ጉዳዩ ከሰዎች ይልቅ ርእሰጉዳዩ ላይ እንዲሆን ይጥራል፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ ይሳካለታል፡፡

 

                     "ዳጉ አዲስ"

 

በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተደማጭ የነበረ በተለያዩ የወጣቶች ጉዳይ ላይ ያተኮረ "ዳጉ አዲስ" የሚባል በሸገር አዲስ ለአመታት የዘለቀ ፕሮግራም አዘጋጅ፤ አስተባባሪ እና አቅራቢ በመሆንም ሰርቷል፡፡ የአቻ ግፊትን መቋቋም፤ ስርአተ ጾታ፤ ኤች አይ ኤይድስ፤ ግልጽ ውይይት እና የህይወት ክሀሎትን ዋና ጉዳዮችን ዋና ጉዳይ ያደረገው ይህ የሬድዮ ፕሮግራም የሬድዮ መጽሄት ቅርጽን የተከተለ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ወጣቶች ስለወሲብ፤ የፍቅር ግንኙነት፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሰላላቸው ግንኙነት በግልጽ ስለሚያወሩ እጅግ ተደማጭ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ፕሮግራም ነበር፡፡

 

የቢኒያም አንዱ ተግባር ታዲያ ለአመት የሚበቃ የፕሮግራም ርእሰ- ጉዳዮች ቀድመው እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው፡፡ በባህሪይ ለውጥ ፕሮግራሞች ጋዜጠኞች ብቻቸው ተሰብስበው ፕሮግራሙን አይወስኑም፡፡ የወጣቶች ፕሮግራም እንደመሆኑ ርእሰ- ጉዳይ መረጣው ላይ ወጣቶች ራሳቸው እንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊም፤ ግዴታም ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ከተለያዩ /ቤት የተውጣጡ ተማሪዎችን፤ የማይማሩ ወጣቶች፤ አስተማሪዎች፤ የስነ-ልቦና ባለሙያ እና ወላጅ ያካተተ ቡድን ነው ለሳምንታት አብሮ በመምከር ርእሶችን የሚመርጡት፡፡ ርእስ ብቻ ሳይሆነ ወጣቶቹ ምን ማወቅ እንደሚፈልጉም፤ ለመስማት የሚፈልጉት ጉዳይ፤ የወጣቶች ተግዳሮት፤  ፕሮግራሙ ላይ ማን መካተት እንዳለበት …. አብረው ይወስናሉ፡፡ የስነ -ልቦና ባለሙያዎቹም ፕሮግራሙ በሚሰራ ጊዜ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች እንዲያብራሩ የሚገባቸውን ሃሳቦችም ያነሳሉ፡፡ ወላጆችም ወጣቶች እንዲረዱ የሚፈልጉትን ነገር ከወላጆች አንጻር ያስረዳሉ፡፡ ያንን እንደዋና መነሻ በማድረግ ነው የጋዜጠኞቹ ቡድን አመቱን ሙሉ የሚሰራው፡፡ በዚህ ወቅት ፕሮግራሙን በመምራት፤ የወጣቶቹ ሃሳብ በአግባቡ መካተቱን፤ ጋዜጠኞች ለስራቸው በቂ መነሻ መያዛቸውን ማረጋገጥ የስራው ዋና አካል ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት ጥሩ ታሪክ ከተገኘም እዛው የመስራትን ሁኔታም ያመቻቻል፡፡

 

ቢኒያም ለሶስት አመታት የዘለቀ እርካብ (አማርኛ) ተርካንፊ (ኦሮምኛ) ርኻብ (በትግርኛ) የሚባሉ ድራማ እና እውነተኛ ታሪኮችን አቀናጅተው የሚያቀርቡ የሬድዮ ፕሮግራሞች ላይም ተሳትፏል፡፡፡ ፕሮግራሞቹ ሳይቁረጡ በአማራ መገናኛ ብዙሃን፡ በድምጸ ወያኔ ኤፍ ኤም እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ እንዲሁም በተለያዩ ማህበረሰብ ሬድዮዎችነ ላይ ተላልፈዋል፡፡ በአንዲት የገጠር መንደር ላይ መቼቱን ያደረገው ድራማ ላይ በመመስረት ተዛማጅ ታሪኮችን መስክ ድረስ በመሄድ የአርሶ አደሮችን እውነተኛ ታሪክ አዋዝቶ የሚያቀርብ ፕሮግራም ነው፡፡ ረጅሙን ጊዜ የእውነተኛ ታሪኮቹ አስተባባሪ እና አርታኢ ሆኖ ሲያገለግል ለአንድ አመት ያህል ደግሞ የድራማው ክፍል አስተባባሪ፤ የድራማው ጽሁፍ አርታኢ እንዲሁም የሬድዮ የድራማዎቹ ዳይሬክተር በመሆን ሰርቷል፡፡

 

ቢኒያም ከዚህም በተጨማሪ በስርአተ ጾታ፤  በወባ፤ በኮቪድ፤ በምርጥዘር አጠቃቀም፤ በስርአተ ምግብ ላይ 150 በላይ ስፖቶችን (ማስታወቂያዎችን) በመጻፍ እና ብዙዎቹም ላይ በመተወን ተሳትፏል፡፡

 

ቢንያም የባህሪ ለውጥ ተግባቦት አሁንም ገና እንዳልተነካ፤ ብዙ ልንሰራበት የሚገባ ወሳኝ የሙያ ዘርፍ እንደሆነ አበክሮ ያምናል፡፡

 

  ቤተሰባዊ ህይወትና የህይወት ምልከታ

 

   ቢንያም ውብሸት  ከወይዘሮ ዲና አሰፋ ጋር ጋብቻ መስርቶ 3 ልጆች አፍርቷል፡፡

 

  ቢንያም እንዲህ የሚል ምልከታ አለው ‹‹…..ነገ ላንኖር እንደምንችል እናስብ:: ላለን ነገር እውቅና እና ዋጋ እንስጥ:: በትህትና' በፍቅር' በይቅርታ' በመቀባበል በመኖር ለሰውም'ለፈጣሪም ለራሳችንም ምቹ እንሁን:: ፉክክራችን ሁልጊዜም ከራሳችን ጋር ይሁን::›› ይላል ቢንያም

 

መዝጊያ ... ቢንያም ውብሸት በተለይ በአንባቢነቱ  ይታወቃል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ 1990 . ቢንያምን 20 በላይ መጽሀፍትን አሸናፊ መጽሀፍ መደብር ከሚባል መሸጫ ገዝቶ ሲሄድ በተደጋጋሚ አስተውሎታል፡፡ ይህ የቢንያምን የንባብ ፍቅር በግልጽ የሚያመለክት ነው፡፡ ቢንያም በዛ ጀምሮ በንባብ ያዳበረውን እውቀት ወደ ተግባር ቀይሮ በሀገራችን የሚድያ ስራ ውስጥ የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡ በተለይ በጤና እና በወጣቶች  ብሎም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ቢንያም ተመስክሮለታል፡፡ ድራማዎች ይጽፋል፡፡ አጫጭር ማስተማሪያ ስፖቶችን ይጽፋል፡፡ በዚህም ከቅርብ አለቆቹ ምስጋና ተቸሮታል፡፡ ቢንያም በልዩ ትህትናው ይታወቃል፡፡ ቢንያም ትጉህ ነው፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት እንደ ቢንያም አይነት በአለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የሚድያ ባለሙያዎች ሚናቸው በቀላሉ አይታይም፡፡ የሚያካፍሉት የህይወት ልምድም ለብዙዎች ይጠቅማል፡፡ የቢንያምን ታሪክ በዚህ ዊኪፒዲያ ላይ ስናስቀምጥ ለአዲሱ ትውልድ የሚያስተምረው ነገር እንዳለ ስለምናምን ነው፡፡ /ይህ ጽሁፍ ከቢንያም ውብሸት የተገኘውን ታሪክ መሰረት በማድረግ የተሰናዳ ሲሆን ጽሁፉም የተጻፈው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ መስከረም 21 2014 በተወዳጅ ሚድያ የፌስቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ላይ የወጣ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት ይወጣል፡፡

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች