3.  ቤርሳቤህ ጌቴ /Berssabeh Gete

 

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ በማስታወቂያ ዘርፍ በሚድያ ዘርፍ 1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ tewedajemedia gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ 7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ታሪኳ የሚዘከርላት ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ናት፡፡

 

               ትውልድና ልጅነት

 

ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ከአባቷ ከአቶ ጌቴ በላይ እና ከእናትዋ / ብርሀን ካሳ በሀረር ነበር የተወለደችው። ወላጆችዋ የስራ ስፍራቸው ወደ አዲስ አበባ በመቀየሩም 4 አመትዋ አዲስ አበባ በመምጣት በሚስስ ፎርድ አፀደ ህፃናት የትምህርትን ሀሁ መቁጠር ጀመረች። ቤርሳቤህ ጌቴ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በመካነ ኢየሱስ የመጀመሪያ ደረጃ /ቤት 2 ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በምስካየ ህዙናን መድኃኔዓለም ገዳም /ቤት ተከታትላለች፡፡

 

         የዩኒቨርሲቲ ቆይታ

 

2001 . ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋና ስነ-ጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው ቤርሳቤህ ጌቴ በተጨማሪም አረብኛን ማይነር በማድረግ ተምራለች፡፡ በምልክት ቋንቋ ሰርተፍኬት በስነ-መለኮት ዲፕሎማ እና በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪዋን የተቀበለች ሲሆን የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችንም እንዲሁ ለመከታተል ጥረት አድርጋለች፡፡ ሀሴት አካዳሚ የመጀመሪያ የስራ አለምን የተቀላቀለችበት ጅማሮዋ ሲሆን 3 ወራት በላይ ግን አልዘለቀችም፡፡

 

          ሚድያ

 

 የቤርሳቤህ የውስጥ ፍላጎቷ ጋዜጠኝነት ነበርና 2002 የየካ ክፍለ -ከተማ ኮሚኒኬሽን /ቤት ባወጣው የቅጥር ማስታወቂያ በመጠቀም በሪፖርተርነት ስራ ጀምራለች። በኮምዩኒኬሽን /ቤት 2 አመት ቆይታዋ ለአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ ዜናዎችን አጠናቅሮ መላክ ዋንኛ ስራዋ ሲሆን ለአብነትም በክ/ከተማው ስር የሚከናወን በጎ ስራ የነበረውን የመቄዶንያ የአረጋውያንና የበጎ አድራጎት ማህበር ጅምር ስራን 2003 . ቀድሞ በመዘገብ ሙያዊ ግዴታዋን እንደተወጣች የሚታወስ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የክ/ከተማውን ወርሀዊ መፅሄቶች፣ብሮሸሮች፣ፕሬስ ሪሊዞች፣አመታዊ የህትመት ውጤቶችን፣የሬድዮ ፕሮዳክሽኖችንና የቴሌቪዥን ዶክመንተሪዎችን ከማዘጋጀትዋም በላይ ከተቋማት ጋር በሚሰሩ መፅሄቶች ላይ የሌይአውት ንድፍ በማውጣትም ጭምር የተሰጣትን ሀላፊነቶች መወጣት እንደቻለች ስራዎችዋ ምስክር ይበልጥ በሚድያ ሙያ መዝለቅ ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ በሚያዝያ 2004 ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ስትቀላቀል በከፍተኛ ሪፖርተርነት ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስራዋም መለኛ የተሰኘ በሱሰኝነት ችግሮቹ ላይ ያተኮረ ሳምንታዊ መሰናዶ ነበር። በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 9 ዓመት ቆይታዋ በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች በተለይም ማህበራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በርካታ መሰናዶዎችን አየር ላይ አውላለች። በተለይ ደግሞ ዘጋቢ ዶክመንተሪዎች በጥራት በመስራት ትታወቃለች። ዶክመንተሪ ስትሰራም በበቂ ዝግጅትና ስክሪፕቷንም በወጉ አጣጥማ እንደሆነም በብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ ለአየር የበቁትን ድክመንተሪዎችዋን በጥሞና በማድመጥም ምስክርነቱን ማረጋገጥ የሚቻል ነው። የአባይ ሙግት ጥንታዊ ቤቶች ፣ምድረ ቀደምት ሰንደቅ አላማ ፤ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፤የኦሮሞ ገዳ ስርአት ሀገር ማለት የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ቤተ-መጽሀፍና ሙዚየም፣የህፃናት ምገባ፣የህፃናት እና ወጣቶች ቲአትር፣የአይምሮ ጤና፣ፓይለቲቭ ኬር፣የሸክላ ስራ በኢትዮጵያ፣አድዋ፣የሀገር ባህል ልብሶች፣ማህበራዊ ሀላፊነት እና የመሳሰሉት ከዶክመንተሪዎችዋ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በጎ ተፅዕኖን በመፍጠር ረገድም በተለይም የአዕምሮ ጤና ላይ በሚያተኩረው ብዙዬ በተሰኘው የሬድዮ ዶክመንተሪ ዝግጅቷ ላይ የተጠቀሰው ቦርን አጌን የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት በበጎ ፈቃደኝነት የአዕምሮ ህሙማኑን ከጎዳና እያነሳ የሚደግፍ ነበርና ድርጅቱ በራሱ ሊታገዝ እንደሚገባው በዝግጅቷ ገልፃ ነበር ታድያ ይሄንን ዶክመንተሪ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስትር የነበሩት ዶክተር አሚር አማን በሬድዮ ለማድመጥ እድሉን በማግኘታቸው የበጎ-አድራጎት ማህበሩ ከአማኑኤል ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች እና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተደርጓል ይህም አንደኛው የስራዋ ስኬት እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ በቅርብ ሰዎቿ እንደተመሰከረላት ዶክመንተሪን ለማንበብ የሚመጥን ቆንጆ ድምጽ በተፈጥሮ የተቸራት ሲሆን ይህን በተፈጥሮ ያገኘችውን ድምጽ በየጊዜው እየገራች በአሁኑ ሰአት በጣም ጥሩ እና ተመራጭ ድምጽ ካላቸው ጋዜጠኞች አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡ በቃ-ለምልልስ፣በትምህርታዊ እና መዝናኛ ዝግጅቶች ላይ ያተኮሩ መሰናዶዎችን በቅንብር እና በቀጥታ ስርጭት በማስተላለፍም ዕውቀቷን ለማዳበር የቻለችው ቤርሳቤህ ከቃለ-ምልልስ ስራዎችዋ የአቶ አሰፋ አደፍርስ ስፖርተኛ ንጉሴ ገብሬ ደራሲ ገስጥ ተጫኔ ፣አቶ ቴዎድሮስውህድ ማንነት፣ዶ/ ኤርሲዶ ለንደቦ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለስራ ሁል ጊዜም ከመታተር ወደ ኋላ የማትለው ይህች ጋዜጠኛ ለዶክመንተሪ የተለየ ፍቅር እንዳላት ግን አዘውትራ ትናገራለች፡፡ ጋዜጠኛዋ አንድን ስራ ከመስራት በፊት ቅድመ-ዝግጅት ማለቅ አለበት ብላ የምታምን በመሆኑ የምትሰራው ስራ ደረጃውን የጠበቀ ለመሆን ችሏል፤ስራዎችዋን ስትሰራም፣ ዋና ትኩረቷ አድማጮቿ ላይ ነው፡፡ አድማጭ ምን ያህል በምሰራው ስራ ይደሰታል ብላ በጥንቃቄ ለመስራት ትተጋለች በዚህም መሰናዶዎቿ የአድማጭን ስሜት የማርካት አቅማቸው ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ጋዜጠኛዋ ከአዲስ አበባ ውጭ በመስክ ስራ በርካታ የሀገሪቱን ክፍሎች ተዟዙራ በመመልከቷ ስለሀገሯ ያላትን እውቀት ከፍ እንዲል አድርጎታል፤ለስራዋም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተላት ታምናለች። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው በሚመቻቹ የስልጠና እድሎች ላይ በመሳተፍ በነበራት እውቀት ላይ አዲስ እውቀት ለማከል በእጅጉ ትተጋለች፡

 

ሃላፊነት አደራን መወጣት

 

ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ በፋና ብሮድካስቲንግ ስትቀጠር በከፍተኛ ሪፖርተርነት ቢሆንም በየጊዜው ታሳየው የነበረው ጥረት ግምት ውስጥ ገብቶ 2011 በተቀጠረች 7 አመቱ የኤዲተርነት የስራሃላፊነትን በመረከብ የበርካታ ጋዜጠኞችን ስራ የአርትኦት ወይም የኢዲቲንግ ስራ በማከናወን ልዩ ብቃቷን አስመስክራለች ፡፡ የሬድዮ መዝናኛ መሰናዶዎች አየር ላይ ከመዋላቸው በፊት ቀድማ የምታይ በመሆኗ ጣቢያውን የሚመጥን መሰናዶ አየር ላይ እንዲውል ሀላፊነቷን በትጋት ተወጥታለች፡፡ ጋዜጠኛዋ እንደ ስራ አስተባባሪ ብቻ ሳይሆን እንደጋዜጠኛም መቅረጸ -ድምጽ ይዛ በመውጣት የጋዜጠኝነት ፍቅሯን ስትወጣ ቆይታለች፡፡ ሰው እንዴት ይቀመጣል የሚል ጽኑ እምነት ስላላትም መስራቱን ትመርጣለች ከመደበኛ የሬድዮ ስራዋ በተደራቢነት የቴሌቪዥን ውይይቶች እና ፕሮዳክሽኖችን በመቀበል መስራቷም የዚሁ ማሳያ ነው ከዚህም በዘለለ በግል የሚሰሩ የፅሁፍ ስራዎችን፣መድረኮችንና የአርትኦት ስራዎችን በመስራት ለማደግ ትጥራለች፡፡ አንድ ጊዜ ለስራ ከተቀመጠች ማንንም ባታነጋግር ምርጫዋ ነው፡፡ ትኩረቴን ይወስደዋል ስለምትል አንድ ስራ ላይ ካተኮረች ሳትጨርስ ንቅንቅ የለም ፡፡ ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ባለትዳርና 2 ልጆች እናት ሆና የቤተሰቡንም ሃላፊነት እንዲሁም ስራውን በእኩል ደረጃ ሚዛኑን አስጠብቃ ለመሄድ ትሞክራለች፡፡ 2013 ፋና ብሮድስካቲንግ በሰጣት እድገትም የምክትል ዋና አዘጋጅነትን ደረጃ ያገኘች ሲሆን ይህም በጣቢያው ውስጥ ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ በሳል ሴት አርታኢያን መካከል አንዷ ያደርጋታል፡፡

 

አቅምን አጎልብቶ ማውጣት

 

ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ከመደበኛ ስራዋ ባሻገር ለሀገር አስተዋጽኦ ያበረክታል ብላ በምታምንባቸው የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ትታወቃለች፡፡በተለይም በቀጨኔ የህፃናት ማሳደጊያ የሜንቶርሺፕ አገልግሎት በመስጠት የምትሳተፍ ሲሆን ከውድ አረጋውያን ማህበር እና ከሜሪጆይ የልማት ማህበር ጋር በመተባበር የግል አስተዋፅኦዋን ለማበርከት ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ከመደበኛ ስራዎችዋ ለጎን በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ተለያዩ የስራ ድርሻዎች ላይ በመሳተፍ አቅሟን ያሳየች ሲሆን በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን የሚያወሱ የሲዲ እና ሌሎች የህትመት ስራዎች ታትመው እንዲወጡ ምክንያት ሆናለች፡፡

 

ድርጅቱ ዶክመንተሪ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ትኩረት እንደመስጠቱ የቤርሳቤህ ዋና ስራ የማማከር የአርትኦት ፤እና መድረኮችን የመምራት፣ የማስተባበር ስራ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በድርጅቱ የምክትልነት ሀላፊነትን ተቀብላ የሚመጡ ስራዎች በጥራት እንዲሰሩ የግል አስተዋፅኦዋን አበርክታለች። በቤርሳቤህ ጌቴ ኤዲት ተደርገው ከወጡ ስራዎች መካከልም የደበበ ሰይፉ ታሪክ የኢንጂነር በትሩ አድማሴ ታሪክ የኤርትራ ጉዳይ የአሰብ ወደብ ስራ ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የላሞች የጡት ወተት በሽታ ወይም ማስታይቲስ የተሰኘው ከኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተሰራውን ዶክመንተሪ ለዛ ባለው ድምጹዋ ያነበበችው ቤርሳቤህ ነበረች ብሎም የአቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ታሪክ ምረቃን የእንስሳት ህክምና ታሪክ 100 አመት አገልግሎትን እንዲሁም የዶክተር ጌታቸው ተድላን ዲቪዲ ምረቃዎች በዋና የመድረክ መሪነት ሙያዊ ክህሎቷን ያሳየች ሲሆን በዚህም ታላላቅ ሰዎች ሳይቀሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ዘመነኞቹ ባለታሪኮችን ሚና በዊኪፒድያ የመሰነድ ፕሮጀክት ላይ ደግሞ እየሰራች ትገኛለች፡፡ የምታምንበትን ሀሳብ ያለ አንዳች ፍራቻ በመግለጽም የምትታወቀው ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ተወዳጅ ሚድያ በታህሳስ 6 /2013 ያበረከተላትን ተወዳጅ አዋርድ የተቀበለች ሲሆን ወደ ፊት በልዩ ልዩ ጉዳዮች መጽሀፎችን አሳትሞ የማቅረብ ሀሳብም እንዳላት ስትናገር ይሰማል። ቤርሳቤህ ከዚህ በላይ በሙያዋ ሀገሯን የመርዳት ግብ የሰነቀች ሲሆን ይህም ግቧም እንደሚሳካ በእግዚአብሄር ትታመናለች፡፡

https://youtu.be/71iXQ5qUXWE

https://youtu.be/cThrIqK4rtA

https://www.youtube.com/watch?v=bxvnjVkndgk

https://youtu.be/Ydp_EmD01X

https://www.youtube.com/watch?v=iE5wn1SO17M

https://www.youtube.com/watch?v=K9luaLiPFJg

https://www.youtube.com/watch?v=K9luaLiPFJg

https://youtu.be/PZLWR_ARdF8

https://www.youtube.com/watch?v=gcyQF3Fhojo

https://youtu.be/FQoTawycCrw

https://youtu.be/Qb_K8idX64A


አስተያየቶች

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች