17 በአሉ ግርማ-BEALU GIRMA
የመፅሃፍ ሃውልት የቆመለት በአሉ ግርማ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ
ወጣት በሚል ሀሳብ ከ120 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ
ሊያሳትም
እንደሆነ
ይታወቃል፡፡
እስከዚያ
ድረስ
ታሪካቸው
በዚህ
ዊኪፒዲያ
እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ታሪኩን የምናነብለት አንድ .ደራሲና ጋዜጠኛ አለ፡፡ በአሉ ግርማ፡፡ በአሉ ግርማ ማነው? በታምሩ ከፈለኝ የተሰናዳውን ታሪክ እነሆ እንደሚከተለው አሰናድተናል፡፡
ውልደትና እድገት
በአሉ ግርማ ፣ በወርሀ መስከረም በ1929 አመተ ምህረት በኢሉባቡር ከተማ (አሁን ኢሉ አባቦራ) ሱጴ ተብላ በምትጠራ ገጠር ተወለደ። በአሉ በአባቱ ህንዳዊ ሲሆን በእናቱ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የበአሉ እውነተኛ አባት ስም ግርማ ሳይሆን ጂምናዳስ ይባላል፡፡ (ሞልቬር 'ብላክ ላየንስ' በሚለው መጽሐፉ ግርማ የእንጀራ አባቱ እንደሆነ ሲገልጽ እንዳለጌታ ደግሞ 'በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ' በሚለው መጽሐፉ ግርማ አባቱ ሳይሆን በዓሉ ከሱጴ ተነስቶ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ተቀብሎ ያሳደገው ነው ይላል፡፡)
ጂምናዳስ፣ የተወለደው ህንድ ውስጥ ጉጅራት በተባለ ከተማ ነው፡፡ በእዚያ ከተማ ውስጥ ዝርያችን ከኢትዮጵያ ይመዘዛል የሚሉና ራሳቸውን “ሀቢሲስ” ወይም “ሲዲስ” ብለው የሚጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ ሀቢሲስ ማለት ከሃበሻ ሃገር የመጣ ህዝብ ማለት ሲሆን ሲዲስ የሚለው ደግሞ ስድስተኞቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ማለት ነው፡፡
የበአሉ እናት ያደኔ ቲባ የምትባል የሱጴ ቦሩ ተወላጅ ናት፡፡ በጊዜው አባቷ በሚነግዳቸው ንግዶች ስር ትሰራ የነበረ ሲሆን ጂምናዳስ ደጋግሞ በወቀየው ሲያመራ በውበቷ ተማርኮ በወጉ መሰረት ሽማግሌ ልኮ ነበር የተጋቡት፡፡
ጂምናዳስ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረ ጊዜ ከአዲስ አበባ ኢሊባቡር እየተመላለሰ ሸቀጣ ሸቀጥ ይነግድ ነበር፡፡ (ሞልቬር ነጋዴ ሳይሆን አናፂ እንደነበር ነው የፃፈው)
ህንዳዊ አባቱ ለልጁ ያወጣው ስም “ባሉ” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም ከህንድ ቋንቋዎች ባንዱ “እድለኛ” ማለት ነው፡፡
ሰዎች ስያሜው አዲስ ስለሆነባቸው ለአጠራር እንዲቀላቸው በአሉ እያሉ ይጠሩት ጀመር፡፡ ስሙም በዛው ቀጥሎ መደበኛ መጠሪያው ሆነ፡፡ የሚጠራው በወላጅ አባቱ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ነው፡፡
ያደኔ ቲባና ጂምናዳስ በአሉን ብቻ አይደልም የወለዱት፡፡ ከበአሉ ቀጥሎ ሶሎሞን የሚባል ልጅም ወልደው ነበር፡፡ ነገር ግን ሶሎሞን ሁለት አመት ከመንፈቅ እንደሆነው በተነሳው ፈንጣጣ በሽታ ህይወቱ አልፏል፡፡
አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በኢሊባቦር፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከዛም በመቀጠል ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ወደ አሜሪካ በመሄድ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
የስራ ህይወት
በአሉ ትምህርቱን እንደጨረሰ ፣ ስራ የጀመረው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ነበር፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ሳለም ዜና ያነብ ጋዜጣም ያዘጋጅ ነበር፡፡ የ'መነን'ና 'አዲስ ሪፖርተር' መጽሔቶች የ'አዲስ ዘመን'ና 'ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ' አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በእነዚህ ጋዜጦች ላይ ከፍ ያለ ለውጥ እንዳመጣም ይነገርለታል፡፡
በአሉ፣ በጋዜጦቹ ከመንግስት አቋም ውጪ የሆኑ ጽሑፎችን ወይም የዘውድ ስርአቱንና የመንግስት ባለስልጣኖችን የሚተች ጽሑፎችን ያስተናግድ ነበር። በእነዚህም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከመሰጠትና ከሥራ እስከመታገድ ደረጃ ደርሷል፡፡ በግሉም ሌሎች ማለትም እንደ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር እና ሰለሞን ደሬሳ አይነት ተጋባዥ ጸሐፊዎችን እያስተባበረ የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ለማቋቋም ቢፈልግም በመንግስት ክልከላ ይታገድበት ነበር፡፡
ከዚህ ባሻገርም፣ ከአብዮቱ በኋላ የዜና አገልግሎት ኃላፊ፣ በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን አገልግሏል።
ከአብዮቱ በኋላ በአሉ ከመንግስቱ ሃይለማርያም ጋር ጥብቅ ግንኙነት መስርቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ (እራሳቸው ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ለገነት አየለ እንደነገሯት ከሆነ የበአሉ ግርማና የመንግስቱ ትውውቅ ሰባ ደረጃ አካባቢ በሚገኝ አንድ ባር ውስጥ ነው፡፡ በአሉ እዚያ ባር ውስጥ ወዳጁ ከነበረችው ድምጻዊት ብዙነሽ በቀለ ጋር ይመላለስም ነበር፡፡)
በአሉ ከመንግስቱ ጋር በነበረው ጥብቅ ግንኙነት የኤርትራውን የቀይ ኮከብ ዘመቻ አጋዥነት ደርሶም ነበር፡፡ ከዚህ ዘመቻ በፊት የእሱ “የቀይ ከከብ ጥሪ” የሚለው መጽሐፍ ወጥቶ ስለነበር ዘመቻው ጥሪም ከዚህ መጽሐፍ ርእስ እንደተቀዳ ይነገራል፡፡ በዚህ ዘመቻም ሊቀመንበሩ በአሉን ወደ ዘመቻው ይዘውት ሄደው ነበር፡፡ የመጨረሻ የሆነው 'ኦሮማይ' የተሰኘው ልቦለዱን የፃፈው ያንን በ1974 ዓ.ም ኤርትራ ክፍለሀገር የተካሄደውን ዘመቻ መሰረት አድርጎ ነው፡፡
የፍቅር ህይወትና ትዳር
በአሉ ቆንጆ ሴት አይቶ አድናቆቱን ሳይገልፅ የማያልፍ ነበር፡፡ ከተወዳጇ ድምጻዊት ከብዙነሽ በቀለ ጋርም ፍቅር ውስጥ ገብተው እንደነበረም ይነገራል፡፡ ሆኖም ብዙነሽ በቀለና በአሉ ግርማ በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት ተለያዩ፡፡
ከብዙነሽ የተለያየው በአሉ ብዙም ሳቆይ አሜሪካ ሄዶ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ሲጨርስ አልማዝ ከምትባል የካዛንቺስ አካባቢ ልጅ ተወዳጀ፡፡ አልማዝ ቆንጆና ዳንስ የምትወድ ሴትም ነበረች፡፡ (አልማዝ ከበአሉ ጋር የመሰረተችው ትዳር መጀመሪያዋ አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል ከበደ ሃይሌ (የአርበኛው ሃይሌ አባ መርሳ ልጅ) የሚባል ባል ነበራት፡፡ ከከበደ ሀይሌም ልጆች ወልዳ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የወንድሟን አምደሚካኤልን ጓደኛ በአሉን ያገባችው፡፡
በአሉ በትዳራቸው ውስጥም ይሄ የሴት ሙያ ነው ይሄ የወንድ የሚለው ስራ አልነበረውም፡፡ ሲያሻው ወደማእድቤት ገብቶ ምግብ ያበስልም ነበር፡፡
ከአልማዝ ጋር ተጋብቶ ሶስት ልጆችንም ወልዷል፡፡ ከሶስቱ ውስጥ ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ዘላለም በዓሉና ቢኒያም በዓሉ ይባላሉ፡፡ ሴቷ መስከረም በአሉ ትባላለች፡፡
የድርሰት ስራዎቹ
ደራሲ በአሉ ግርማ በአጠቃላይ ስድስት ረጃጅም ልቦለዶች አሉት፡፡ እነሱም 'ከአድማስ ባሻገር'(1962)፣ 'የህሊና ደወል' (1966)፣ 'ደራሲው' (1972)፣ 'ሀዲስ' (1975) እና 'ኦሮማይ' (1975) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስራዎች ውስጥ 'የህሊና ደወል' እና 'ሀዲስ' በመቼት እና በተሳሉ ዋና ገፀባርያት ተመሳሳይነት ቢታይባቸውም በጭብጥ ረገድ ግን ልዩነት እንዳላቸው የስነጽሑፍ ምሑራን ይናገራሉ ፡፡ 'ሀዲስ'፤ በ'ህሊና ደወል' ውስጥ የተነሱ ጉዳዮች ሰፋ ባለ እይታና የተወሰኑ ቅንጭብጭብ ታሪኮችና ገፀባርያት ታክለውበት የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡
በአሉ ከዚህም በተጨማሪ መጀመርያያ በየካቲት መጽሔት(1975)
በኋላ
ደግሞ
'ጭጋግና
ጠል'
በሚል
ርእስ
አንጋፋና
ወጣት
ደራስያን ስራ ይዛ በ1990 ዓ.ም በታተመች መድበል ላይ የታተመ “የፍፃሜው መጀመርያ” የሚል አጭር ትረካ አለው፡፡
በአሉ መጨረሻ መጽሐፉን 'ኦሮማይ'ን ከጻፈ በኋላ ከስራ ታገደ፡፡ የመታገዱ ምክንያትም በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ በሥራ አጋጣሚ እጁ የገቡትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ስም ሳይቀር የሚያጎድፍ ስራ ሰርተሃል የሚል ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት ሹመቱ የታገደው በ1975 ዓ.ም በነሃሴ ወር ነበር፡፡
ሞት
እስከ የካቲት 8: 1976 ዓ.ም ያለስራ የቆየው በዓሉ አንድ ዕለት እንደወጣ ቀረ። ከዛ ምሽት በኋላ በአሉ ወደ ስራ አልተመለሰም፡፡
በአሉ ከጠፋ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደብረዘይት መንገድ ቃሊቲ አካባቢ መኪናው ቆማ የተገኘች ቢሆንም በአሉን የበላ ጅብ ግን ወዲህ ነኝ አላለም ነበር፡፡ መንግስትም በአሉ የኛ ወገን ነበር፤ አሁን ግን ከድቶን ስለጠፋ ያያችሁት አሳውቁኝ የሚል ማስታወቂያ ቢያስነግርም እራሱ መንግስት እንደገደለው ይጠቆማል። እርግጠኛውን የሚጠቁሙ አይደሉም፡፡
በአሉ ከቤት ከወጣባት ጊዜ ጀምሮ ግን እዚህ ቦታ ታይቷል የሚል ሰው ባይገኝም የደራሲ እንዳለጌታ መጽሐፍ በዓሉ በደርግ ደህንነቶች ተይዞ ቤርሙዳ ተብሎ ይጠራ የነበረ ቦታ ታስሮ በመጨረሻም መገደሉን ያትታል፡፡ ሆኖም ሞተ መባሉ ተሰማ እንጂ አስክሬኑ ግን እስከዛሬ አልተገኘም፡፡ እናም ሃገሩን በጋዜጠኝነትም በደራሲነትም ያገለገለው በአሉ ግርማ የቆመለት ሃውልት የለውም፡፡
ስለ በአሉ ግርማ በሃገራችን ብዙ ፀሃፍያን በጋዜጣም በመፅሄትም ብዙ ፅፈዋል፡፡ በራዲዮና በቴሌቪዥን ያልተነሳበት አመትና ወርም የለም (ማለት ይቻላል)፡፡ የደራስያንን ታሪክ የያዙ መጻሕፍት በአሉን በቀጥታም በተዘዋዋሪም አያልፉትም፡፡ የደርግ ባለስልጣኖች በተለያየ ስፍራ ሆነው በሚፅፉት መጽሃፍም በዓሉን ያነሳሱታል፡፡ እንዳለጌታ ከበደ ግን በ2008 አመተምህረት ያሳተመው
"በአሉ
ግርማ
ህይወቱና
ስራዎቹ"
የሚለው
ባለ440
ገፅ መጽሐፍ ከሁሉም የተለየና የደራሲውን ህይወትና ስራዎች" በዝርዝር የተመለከተ ነው፡፡ በዚህም መጽሐፉን "ሃውልት ላልቆመለት ደራሲ የቆመ የመጽሐፍ ሃውልት" የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡
መዝጊያ፣ በአሉ ግርማ ለብዙዎች መነቃቃትን የፈጠረ በሳል ፤ ደፋርና ንቁ ብእረኛ ነው፡፡ በአሉ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳረፈ ፤ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ በሀገራችን የድርሰትና የሚድያ ስራ ውስጥ የጎላ ድርሻ የነበረው ነው፡፡ ዛሬም ግን በአሉ ግርማ በማን ተገደለ ለሚለው መልስ የለም፡፡ ገና የ47 አመት እድሜ ሳለ የተሰወረው በአሉ በድርሰት ስራዎቹ መላ ኢትዮጵያውያን ያነሱታል፡፡ በአጫጭር አረፍተ-ነገሮቹ የስነ-ጽሁፍ ባለሙያዎች ስሙን ከፍ አድርገው ያነሱታል፡፡ በአሉ ግርማ በተለይ ‹‹ኦሮማይ›› በተሰኘ ድርሰቱ በመላ አንባቢያን ለመደነቅ የቻለ ነው፡፡ በስራው ህያው ለመሆን የቻለ ነው፡፡ ይህን የበአሉን የዊኪፒዲያ ታሪክ ያሰናዳን የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አባላት በአሉ በስራው ህያው መሆኑን እናምናለን፡፡ የጻፋቸው ድርሰቶች፤ በሚድያ ዘርፍ ያሳለፋቸው ዘመናት ለአዲሱ ትውልድ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ አዲሱ ትውልድ፤ ደፋር ጸሀፊ እንዲሆን እውነትን አይቶ እንዳያድበሰብስ
የበአሉ
ህይወት
ብዙ ያስተምራል፡፡ አንድ ሰው ስለ በአሉ ማወቅ ቢፈልግ መጠነኛ መረጃ እንዲያገኝ ብለን ይህን ግለ-ታሪኩን ሰንደን አስቀምጠናል፡፡
ከበአሉ
ግርማ
ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መታከል አለበት የሚባሉ መረጃዎችን በtewedajemedia@gmail.com
ልትልኩልን
ትችላላችሁ፡፡
በአሉ
ግርማን
በየጊዜው
የመዘከር
ትውልድ
በወጉ
እንዲያውቀው
የማድረግ
ግብ የሰነቅን ስለሆነ ከዚህ ሀሳባችን ጋር ትብብር ለምታደርጉ ሁሉ በራችን ክፍት ነው፡፡ የበአሉ ምስሎች ፤ ሰነዶች ፤ ድምጾች ማንኛውም በአሉን የሚገልጽ ማስረጃ ያላችሁ ሁሉ ያላችሁን እንካችሁ ብትሉን ደስታችን ወደር የለውም፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ ታምሩ ከፈለኝ የተጻፈ ነው፡፡ የአርትኦት ስራው ደግሞ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው የተከናወነው ፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ መስከረም 17 2014 በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የፌስ ቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ገጽ ላይ ወጣ፡፡
የበአሉ ለዚህ ፅሁፍ በዋቢነት ቀረቡ መፅሃፎች
በአሉ ግርማ ህይወቱና ስራዎቹ፤ እንዳለጌታ ከበደ (2008)
ስብሃት ገብረእግዚያብሄር ህይወቱና ስራዎች፤ በአለማየሁ ገላጋይ
መለያየት ሞት ነው፤ በአለማየሁ ገላጋይ
የመንግስቱ ሀይለማርያም ትዝታዎች፤ በገነት አየለ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ