20  አብርሃም ፀሐዬ ግርማይ ABREHAM TSEHAYE GIRMAYE

 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ 130 በላይ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል መምህርና የሚድያ ሰው የኢካሽ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ማእከል መስራች አብርሀም ፀሐዬ ግርማይ  ነው፡፡ አብርሀም ማነው? የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ረዳት ኤክስፐርት አማረ ደገፋው ተሾመ   የአብርሀምን ታሪክ እንደሚከተለው አጠናክሮታል፡፡

 

            'ሀገር በጋዜጠኝነት ይገነባል

 

አንድ ወዳጁ ስለእርሱ ሲናገር "ከዋናው አብርሃም ቀጥሎ ያለ አብርሃም ነው" ይለዋል። በእርግጥም የበርካታ ሀገር ገንቢዎች አባት መሆን ችሏል፤ አብርሃም ፀሐዬ። 'ሀገር በጋዜጠኝነት ይገነባል' የሚል ፅኑ እምነቱን በተግባር የገለጠበት የጋዜጠኝነት ማሠልጠኛ ተቋም አቁሞ በአጫጭር ሥልጠናዎች ሀገር ገንቢ ጋዜጠኞችን እያፈራ ይገኛል።

 

የቱ ጋር ጋዜጠኝነትን እንደወደደ አያስታውስም፤ መቼ በጋዜጠኝነት እንደተሳበ አያውቅም፤ እንዴት ጋዜጠኝነት እንደማረከው ልብ አላለም። ሲገምት ግን 'ምን አልባት አብዝቼ ስከታተለው ሳላውቀውም ማርኮኝ ይሆናል።' ይላል። አሁንም ድረስ የጋዜጣ፣ መጽሔትና ሬድዮ ቀበኛ ነው።

 

        ለማንበብ የበዛ ክብር አለው

 

ማንበብ ነፍሱ ነውና ለህትመት ሚዲያው ያደላል። ገና በለጋ እድሜው ከቦሌ ማተሚያ ቤት በብልሽት ምክንያት ወደሚኖርበት ግቢ በየቀኑ ይመጡ በነበሩ ቁርጥራጭ የሕትመት ውጤቶች ማንበብን አሃዱ ያለው አብርሃም አሁን ላይ አብልጦ የሚችለው ነገር ማንበብ የማይችለው ደግሞ አለማንበብ ሆኗል። ለማንበብ የበዛ ክብር አለው።

 

የሰላሳዎቹን ዕድሜ እያጋመሰ ያለው አብርሃም "እህ..." ብለው የወለዱት እናቱ / አምሣለ መብራቴ ለንባብ ህይወቱ ከፍ ያለውን ድርሻ እንደሚወስዱ ይናገራል። ሹፌር የሆኑት አባቱ አቶ ፀሐዬም ህይወቱ ላይ ሌላ አሻራ አላቸው። "በትምህርት ካልሆነ በስተቀር ሰው አትሆንም!" የሚለውን መሪ ቃል አስጨብጠውታል። በጋዜጠኝነት ዓለም ሊኖር የሚገባውን ሚዛናዊነት በተግባር ቀድመው ያስተማሩት አባቱ ናቸው። 'የከተማና የክፍለሀገር ኑሮን በሚዛናዊ ዓይን እንዳይ ያደረገኝ የሹፌሩ አባቴ ውሳኔ ነው' ይላል። እንደማሳያ ከመሃል አዲስ አበባ አንስተው በሥራ ያወቋት አሰላ ከተማን እንዲቀምስ ያደረጉበት የአፍላነት ዘመኑ ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው በውለታነት ይጠቅሳል። አዲስ መንገድ፣ አዲስ ዕይታ፣ አዲስ ማኅበረሰብ፣ ከሁሉም ጋር አብሮ የመኖርና የሰከነ ሕይወትን ያየበት ተከታታይ የስድስት ዓመታት ሕይወቱ መጨረሻ ላይ በስንብት ቢጠናቀቅም የተለየና የማይለቅ የሕይወት ማኅተም እንዳስቀረለት ያምናል።

 

     የካምፕ ህይወትን አጣጣምኩ ንባቤንም አበረታሁ

 

ጎጃም በረንዳ አባኮራን ሠፈር ከቦሌ ማተሚያ ቤት በሚመጣ የሕትመት ተረፈ ምርት የተጀመረው የንባብ ሩጫው መርቲ ላይ ሲደርስ ዙሩ ከረረ። 'ሌላኛዋ የኔ ውብ የፍቅር መንደር' የሚላት መርቲ የሥራ ሕይወቱን የጀመረባት ናት። ከየትኛውም የኮሌጅ ሕይወቱ 'አንደኛዬ ትምህርት ቤት' ከሚለው ተግባረ ዕድ በጥሩ ውጤት በጄኔራል መካኒክስ ከተመረቀ በኋላ ነው መርቲን የረገጠው። በላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንደስትሪ /ቤት ስር በሚገኘው ፋብሪካ በጄኔራል ሱፐርቫይዘርነት በሰራባቸው ዓመታት 'የካምፕ ህይወትን አጣጣምኩ ንባቤንም አበረታሁ' ይላል። ሳምንታዊ ጋዜጦችን ማሳደድ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መከታተል፣ መጻሕፍትን ማንበብ... በመርቲ ቆይታው እንደመብላትና መጠጣት ለአፍታም ዝንፍ ያላሉ ተግባራቱ ነበሩ።

 

የበዛ ትርፍ ጊዜው የህትመት ሚዲያውን ይበልጥ እንዲወድ አደረገው እንጂ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያውም ላይ የዋዛ አይደለም። መስሪያ ቤቱ ውስጥ የምርትና ሰራተኛ ቁጥጥር ላይ ከመሥራቱ ጋር ተያይዞ የተግባቦት ክህሎቱን አሳድጎለታል። በዕድሜና በስራ ልምድ ከእሱ የተሻሉ ሰዎችን ለማግኘት ቀላል የሆነለት የሥራ ሕይወቱ የማያውቀውን ነገር እንደገለጸለትና ክፍተቱን እንደተመለከተበት ያስታውሳል። ሠራተኝነቱ ሁሉንም ፍላጎት ለማሟላት ከበቂ በላይ እንዲሆን ቢያስችለውም እርካታ ግን ሊሰጠው አልቻለም። ድርጅቱ ለሠራተኞች በነጻ የሚያቀርበው መኖርያ ቤት፣ መብራትና ውሃ እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ የሚዘጋጀው ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ጨምሮ አብሮ ለመኖር ተስማሚ የሆነው ሰራተኛና የአካባቢው ነዋሪ ኑሮውን ቀላልና ተስማሚ አድርጎለታል።

 

ይህ ግን አልቀጠለም። ምቹ አኗኗሩ አዘናግቶ ቢያቆየውም የሥራ ዓለሙን ተሰናበተ። ከመርቲ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ አከታትሎ ከተማራቸው ትምህርቶች አንዱ ብሮድካስት ጆርናሊዝም ነው።

 

       መማር መማር

 

የትምህርት ቤት ህይወቱ ያስገርማል፤ ከሮያል ኮሌጅ ማርኬቲንግን፣ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ደግሞ እንግሊዝኛ ቋንቋን ጎን ለጎን አጥንቶ ሁለቱም በከፍተኛ ውጤት ሲያጠናቅቅ፤ ኮተቤዎች አንድ ያጣላል ብለው በውጭ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጡትና እዚያው ቀጠለ። ይህ ደግነታቸው የመጣው በእንግሊዘኛ ቋንቋ የትምህርት ውጤቱ የዋንጫ ባለቤት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነው። የአንድ ያጣላል ህጉ በራሱ መንገድ ቀጠለና ለሮያል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅም ሰራ። 'ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን' እዚያው ደገመ። ትምህርቶቹን መሳ ለመሳ ያስኬዳቸው ጀመር። የሚናፍቀውን የብሮድካስት ጆርናሊዝም ትምህርቱንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወሰደ። አሁንም ውጤቱ አስመስጋኝ ስለነበር እጅግ በጣም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል።

 

እንዲህ በንባብም በትምህርትም ዕውቀትን ሲቃርም የኖረው አብርሃም 'ንቃት በመፍጠር ትልቅ የማኅበረሰብ ግንባታ ማካሄድ ያስፈልጋል' የሚል ሐሳብ ውስጡ ሰርፆ እንደቀረ ያምናል። ለእነዚህ የማኅረሰብ ግንባታዎች ደግሞ ትምህርትና ሚዲያ ወሳኝ መሆናቸውን ያሰምርበታል። ከእነዚህ ሁለቱ ፈጣኑና ቀላሉ መንገድ ጋዜጠኝነት ነው የሚል አቋም አለው። ይህን እምነት ይዞ ወደ ሚዲያው ለመጠጋት ባደረገው ጥረት የመግቢያ በሩን ጥበት፣ የሚዲያውን አጥር ርዝመት ታዝቧል። በቀድሞው ዛሚ ኤፍ ኤም ላይ ፀዳል ሚዲያና ኢንተርቴይመንት ያዘጋጅ የነበረው "ጤና ይስጥልኝ" የተሰኘ ዝግጅት ላይ እጁን ይዞ የወሰደው ታጠቅ ተክለዮሃንስ የተባለ ወዳጁን ዛሬም ድረስ 'ባለውለታዬ' ይለዋል። ይህን ተንተርሶ ሰዎች ለሰዎች ካልተረዳዱ ቀላሉ መንገድ ይወሳሰባል፤ መረጃ ከማቀበል አንስቶ ሁሉም ለሁሉም የሚችለውን ለማድረግ በቀናነት ቢጥር ሕይወት ይቀላል የሚል ዕምነት እንዲያሳደር አድርጎታል።

 

     ጉዞ ወደ ማሰልጠን

 

የታጠቅ ባለውለታነት ወደሚፈልገው ሚዲያ ስላስጠጋው ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኝነት በአጫጭር ስልጠና መሰጠት እንደሚቻል ሃሳብና ጥቂት የተግባር ልምድ ስለሰጠውም ጭምር እንጂ። ይህን ጅምር ሃሳብ ይዞ በሁለት ዓላማዎች የስልጠና ማዕከሉን አፀና። የእውቀት መተላለፊያ ነው ብሎ የሚያምነው ጋዜጠኝነት 'በታዳጊ ሀገር ሲሆን ፈተናው ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ያለ ነው' የሚለው አብርሃም እንዲህ ያለውን ፈታኝ ስራ መሰራት ያለበት በፍላጎት ነው ሲል መፍትሄውን ያስቀምጣል። ሀገራችን ሰው የሚፈልገውን እንዲማር የሚፈቅድ አቅም ላይ ስላልደረሰች ጋዜጠኝነትን በፅኑ እየፈለጉ በሌላ መስክ የሚለፉ ብዙዎችን ጥቂት ስልጠና በመስጠት ወደ ሚዲያው ጠጋ እንዲሉ ማድረግን የመጀመሪያ ዓላማው አድርጎ ረጅም የሥልጠና ጉዞውን በትጋት ጀመረ።

 

ፍላጎት ብቻውን እንዳይሆን ስልጠናውን ለመስጠት በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ አጋዥ ባለሙያዎች እና ጋዜጠኞች ጋር ዕውቀትን ለማቀበል ድልድይ መሆኑንም ቀጠለ። ጋዜጠኝነት ካለበት ኃላፊነት አንጻር ስነ ምግባር እጅግ ወሳኝ መሆኑን ለመግለጽ "ዕውቀት የትም የሚያደርስ ፈረስ ነው፤ ስነ ምግባር ግን ልጓሙ ነው።" በሚለው ብሂል ያጠናክረዋል። አብርሃም ስለማሰልጠኛው እውን መሆን ከወጣቶቹ ጋዜጠኛ ብሩክ ያሬድና ካሳ አያሌው ካሳ ከአንጋፋዎቹ ደግሞ አቶ ታዬ በላቸውን ያመሠግናል። ስነ ምግባርን በዋነኝነት ማስተላለፍ ዓላማው ነበርና ፍላጎትና ዕውቀቱን ይዘው በስነ ምግባር የሚራመዱ ሰዎችን ለመገናኛ ብዙኃኑ በግብዓትነት በማቅረብ ማኅበረሰብ የማንቃት ይህንንም ተከትሎ ለሀገር መገንባት ሂደቱ የመረጃ ጠጠር የሚያቀብሉ ፅኑ አላማን ያነገቡ የጋዜጠኝነት ሰልጣኞችን ማበርከት ሥራዬ ብሎ እያስቀጠለው ይገኛል።

 

እነዚህን ሁለት ዓላማዎች ይዞ በተለይም በተጠናከረ ሁኔታ ከሰባት ዓመታት በላይ በዘለቀ የማሰልጠኛ ተቋሙ ጉዞ ወደ አንድ ሺህ ሰልጣኞችን አስመርቋል። ወዳጆቹ እንደሚናገሩት "የአብርሽ ተማሪ የሌለበት የቴሌቭዥንና ሬዲዮ ጣቢያ የለም።" እርሱ ራሱ ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቅ 'እርግጥ ብዙ ጣቢያዎች ላይ ሰልጣኞቼ አሉ፤ ይሄን ግን ማሻሻጫ ማድረግ አልፈልግም' ይላል። ተቋሙ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በደብረ ዘይት፣ ፍቼ፣ ደብረ ብርሃን ስልጠናዎችን ሰጥቷል።

 

25ኛው ዙር ስልጠና በኋላ ከአጫጭር ስልጠናዎች ያለፈ ህልምን አንግቦ ከወዳጁ ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋና ከባልደረቦቹ ጋር በመመካከር የአብረን እንስራ ጥያቄ ዕቅድ አቅርቦ 'ኢካሽ' በሚል ስም ለመጣመር የጋራ እቅድ ጸንሶ ተነሳ። አሳዛኝ አጋጣሚ ተከስቶ የካሳሁን ሕይወት በድንገት አለፈ። 'መልካም ስሙ ግን በስልጠናችን ውስጥ አለ' ይላል አብርሃም። ይህን ውጥን ለማስቀጠል የበኩሉን በመጣር ላይ እንደሚገኝም ይገልጻል። ማሰልጠኛውን ወደ ትልቅ ተቋምነት ከፍ የማድረግ ህልሙ ጋዜጠኝነቱ ላይ ብቻ የሙጥኝ በማለት ሳይሆን ዘርፉን በማስፋት መሠረታዊ ስነ ጽሑፍ፣ ህዝብ ግንኙነት፣ ማስታወቂያ እና የሚዲያ ቴክኖሎጂን አካቶ መበርታትን ያስባል።

 

ለጋዜጠኝነት ጀርባዋን የሰጠች ሀገር ውስጥ ስለጋዜጠኝነት እየለፋ እንደሆነ ራሱም ያውቀዋል። 'ጋዜጠኝነት ከፍሎኝ አያውቅም' እያለ በተለያዩ መጽሔቶች ላይ ጋዜጠኝነትና ልዩ ልዩ አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይፅፋል። መጣጥፍቹ ፖለቲካ፣ ቢዝነስ፣ ምጣኔ ሃብትና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይመላለሳሉ። አሁን ላይ በአዋሽ ኤፍ ኤም 90.7 በሳምንት ለአራት ሰዓታት አየር ላይ የሚውል "ስድስት ማዕዘን" የተሰኘ ፕሮግራም ያሰናዳል። ዓለም አቀፍ፣ ቢዝነስ፣ ስነ ልቦና፣ ባህል፣ ታሪክ እና ጤና ስድስቱ የስድስት ማዕዘን መሠናዶ ምሰሶዎች ናቸው።

 

'እንደመታደል ሆኖ ህዝቡ ሚዲያን ያከብራል፤ ያምናል። በምላሹ ደግሞ በሚዲያ የሚነገርላቸው ልሂቃን ስለህዝቡ ሲሉ ሚዲያውን ማክበር አለባቸው' ይላል ደጋግሞ። የስልጠና ግስጋሴው 30 ዙር ላይ ደርሷል። ፍላጎቱ ላላቸው በበረሃ መካከል ድንገት እንደተገኘች ጠብታ ውሃ ፍቱን ነው፤ እንደጋዜጠኝነት ደግሞ የሀገር ግንባታ ላይ በፍላጎት ለመሠማራት የሚሹ በስነ ምግባር የተገሩ ብርቱ የሚዲያ ሠራዊቶችን እንደማዝመት።

 

መዝጊያ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡

 

ከላይ ታሪኩን ያቀረብንላችሁ ሰው አብርሀም በስልጠና የሚያምን እውቀትን በማስረጽ ጽኑ አቋም  ያለው  ነው፡፡ ባለፉት 7 አመታት ጋዜጠኝነትን በአጫጭር የስልጠና ኮርሶች በመስጠት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሙያውን አክብረው እንዲሰሩ የረዳ ታላቅ  ሰው ነው፡፡ አብርሀም ያሰለጥናል ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኝነት ፍቅር ሰው ላይ ያሰርጻል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ በእውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲሰራ አብርሀም ዘወትር ተግቷል፡፡ አብርሀም መምህር ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ማእከልን  መስርቶ ይመራል፡፡ ሰልጣኝ ይመዘግባል-ያስተምራል-እውቀት ይመግባል-ያስመርቃል-ወደ ስራ ያሰማራል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ሚድያ ቀላል ውለታ አይባልም፡፡ በየቦታው የስነ-ጽሁፍ እና የጋዜጠኝነት ፍላጎት ኖሯቸው ነገር ግን የስልጠና እድል ለሚያስፈልጋቸው አብርሀም ሁነኛ ብልሀት ዘይዷል፡፡ የሚድያ ፍቅር  ያላቸውን ሰዎች አንድ ላይ አሰባስቦ ስለ ጋዜጠኝነት ማውራት ሙያውን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

 

በቀደሙት ጊዜያት አንጋፋዎቹ የሚድያ ሰዎች ለዋቢነት ብርሀኑ ዘሪሁን በአሉ ግርማ ሙሉጌታ ሉሌ ጳውሎስ ኞኞ እና የመሳሰሉት ያለፉበትን መንገድ ማስተማር ትልቅ መሰጠትን ይጠይቃል፡፡ አብርሀም ኢካሽ በተሰኘ ተቋሙ በዋናነት ተግባር ተኮር ጋዜጠኝነት  እንዲሰፍን ስለሚሻ በስራቸው የተመሰከረላቸው ትጉ የሚድያ ሰዎችን እየጋበዘ ልምድና እውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ያደርጋል፡፡ ሰልጣኞቹም የበለጠ እንዲነቃቁ እድሉን ያመቻቻል፡፡ እንደሚታወቀው የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት እምብዛም ባልተስፋፋበት በዚህ ጊዜ  የኢካሽ መኖር ትልቅ ክፍተት መሙላቱ እሙን ነው፡፡ አብርሀም እንዲሁም በህይወት የሌለው ወዳጁ ካሳሁን አሰፋ ለዚህ ክሬዲቱን/ የሚና ድርሻ/ ይወስዳሉ፡፡

 

አብርሀም ጋር የሰለጠኑና እየሰለጠኑ ያሉ ሰዎችን ልብ ብለን ስናጤናቸው  ለአንድ ሚድያ የሚመጥን   ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ቁመና ላይ የተገኙ ናቸው፡፡ ሙያውን ወደውት የሚሰሩ ናቸው፡፡ ሌላ ምንም አይሹም፡፡ ሙያው ላይ እድል የሚሰጣቸው ተቋም ይሻሉ፡፡ ይህ አይነቱ የሙያ ስነ-ምግባር ውስጣቸው እንዲኖር የመምህራቸው ሚና  ቀላል አይሆንም፡፡ይህ መምህር ደግሞ አብርሀም ነው፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት  እንደ አብርሀም አይነት በስልጠና ላይ አተኩረው ብዙዎችን እያፈሩ ያሉ ሰዎች ታሪካቸው ሊዘከር ይገባል፡፡ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በጣም ከባድ እና ትልቅ ሃላፊነት እየተወጡ ስለሆነ መንግስትም ሊጎበኛቸው ይገባል፡፡ ጋዜጠኝነትን ሙያዊ ማድረግ ከተፈለገ ሰልጣኙን መርዳት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ኢካሽ አይነት በሚጥሩ ሰዎች የተመሰረቱ ማሰልጠኛዎች በሁሉም መስክ መታገዝ አለባቸው፡፡ 31ዙር ድረስ ሰልጣኝን እየተቀበሉ ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ መታደል ነው፡፡ ይህ ዊኪፒዲያ የተዘጋጀው እንደ እነ አብርሀም አይነት ሰዎችን ለመዘከር ነው፡፡ የሰሩ ግን ብዙ ያልተባለላቸው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ ድርጅት እንደ ኢካሽ አይነት ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት  ዝግጁ ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ መስራች ከኢካሽ አሰልጣኞች አንዱ እንደመሆኑ የተማሪዎቹን ውስጣዊ ስሜት ዘልቆ ለመረዳት ችሏል፡፡ እናም አብርሀም በዚህ ስራው ጠንክሮ መዝለቀ አለበት፡፡ ነገ አዲሱ ትውልድ ይህን የአብርሀምን ታሪክ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያነበዋል፡፡ እስከዚያ ግን ይህ ታሪክ ተሰንዶ ይቆያል፡፡ / ይህ ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ረዳት ኤክስፐርት አማረ ደገፋው ተሾመ  የተጻፈ ነው፡፡ የመዝጊያው ሀሳብ ደግሞ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተሰናዳ፡፡ ይህ አጭር ግለ-ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽና  በዊኪፒዲያ ላይ ዛሬ እሁድ ህዳር 26 2014 ከማታው 12:36 ላይ የተጫነ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው እንዲጫን ይደረጋል፡፡

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች