95. ንግስት ሰልፉ - NIGIST SELFU
ንግስት በ2012
ከዕለታት በአንዱ ቀን ንፋስ ስልክ ውስጥ
ንግስት ሰልፉ ታዋቂ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበረች ናት፡፡
ንግስት ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል በአዘጋጅነት ፣ በአቅራቢነት ፣ በኤዲተርነት እና በኋላም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሀላፊነት ቦታ ሰርታለች፡፡
ንግስት ሰልፉ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከተች ናት፡፡ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ ንግስት
አይነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎችን ታሪክ በልዩ ልዮ ድረ-ገጾች መሰነድ ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ አሁንም ንግስት ሰልፉ ያለፈችበትን
የህይወት እና የስራ መንገድ ታነቡ ዘንድ ጋብዘናል፡፡
👇
ዛርብሩከን፣ ጀርመን ለተለያየ ትምህርት ከሄዱ ኢትዮጵያዊያን ጋር በ1987 ዓ.ም
1. የልጅነት ህይወት
ንግስት ሰልፉ የተወለደችው የኢትዮጵያ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ንፋስ ስልክ ስብስቴ ለጋሲዮን ይባል የነበረው ትምህርት ቤት አጠገብ እሁድ መስከረም 24 ፣ 1957 ዓ.ም ነው፡፡
አባቷ አቶ ሰልፉ ወርቁ እናቷ ደግሞ ወ/ሮ አታክልት ገሰሰ ይባላሉ፡፡ ወላጅ አባቷ የተወለዱት የቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር ስላሴ አውራጃ ሲሆን ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያሉ በዚያኔው አጠራር ባሌ ጎባ ጠቅላይ ግዛት በሚባል ወደሚታወቀው ቦታ ከወላጆቻቸው እና ከቤተዘመዶቻቸው ጋር ሄደው መኖር ጀመሩ። የንግስት የአባቷ በኩል ቤተዘመዶች አሁንም እዚያው ባሌ ነዋሪ ናቸው::እናቷ ወ/ሮ አታክልት ገሰሰ የተወለዱት ጣና ሀይቅ ላይ ባህር ዳር አቅራቢያ በሚገኘው ወንድዮ በሚባል አካባቢ ነው፡፡
ንግስት ለእናት እና አባቷ የመጀመሪያ ልጅ ናት። አባቷ በመንገድ ኮንስትራክሽን ሙያ ላይ የተሰማሩ ስለነበሩ ከተወለደችበት ቦታ በሁለት አመቷ ተነስተው ወደ ምዕራቡ የሀገራችን ክፍል አጋሮ፤ ከፋ ጠቅላይ ግዛት ይዘዋት ሄዱ፡፡ አራት አመት ሳይሞላት ተመልሰው አ.አ ገቡ፡፡
ከዚያም ያኔ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ስር ወደነበረችው ውልባረግ ከተማ ገቡ። እዚያም አምስት አመቷ ላይትምህርት ጀመረች። ሶስተኛ ክፍል እያለች ቤተሰቡ በቅርብ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ሆሳዕና ከተማ ተዘዋወረ፡፡
ሶስተኛ ክፍልን በሚሲዮናዊያን ትምህርት ቤት፤ አራተኛ እና አምስተኛ ክፍል አጋማሽ ደግሞ በራስ አባተ ቧያለው ት/ቤት ተምራለች ፡፡
የተቀረውን የአምስተኛ ክፍል የትምህርት ጊዜ በቀድሞ መንዝና ግሼ አውራጃ ባሸ በምትባል የገጠር ከተማ፤ሰባተኛ እና ስምንተኛ አጋማሽ ደረስ ደግሞ እዚያው አውራጃ ሞላሌ ከተማ ነው የተማረቺው ፡፡
ሆሳዕና ከተማ እያለች ትምህርት ቤቷ ከቤቷ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ስለነበረው ምሳ እየያዘች በመመላለስ በኋላም መንዝ ውስጥ ሞላሌ ከተማ ከባሸ 26 ኪ.ሜ ርቀት ስለምትርቅ ወላጆቿ ያፈሯቸውአንዲት የባዳ ዘመድ ጋ ተቀምጣ ነው የተማረችው።ከዚያም በ1969 መጋቢት ወር ላይ ወላጆቿ እሷንና ሶስት ታናናሾቿን ይዘው ወደ አምቦ ከተማ ሲዛወሩ ንግስት የአስራ ሁለት አመት ልጅና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። በየጊዜው የሚቀያየረው አካባቢዋ በትምህርት ውጤቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም አልነበረውም። በየገባችበት ክፍል ሁሉ በጣም ጎበዝ ተማሪ (ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የምትወጣ) ነበረች።
ንግስት አምቦ ከተማ በሚገኘው በቀድሞ ስሙ መስከረም ሁለት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት ቤት አጠናቅቃ ማትሪክን በ1973 ዓ.ም በመውሰድ ከትምህርት ቤቱ ለዲግሪ ለሚያበቃ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለመማር ካለፉ 42 ተማሪዎች መካከል ብቸኛዋ ሴት ነች፡፡
2. የግል
ህይወት
ንግስት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትማር በነበረበት “BLACK DIAMOND(ጥቁር እንቁ)” የሚል ቅፅል ስም እንደነበራት በዚያን ዘመን ስድስት ኪሎ ግቢ ውስጥ የተማሩ ያስታውሳሉ፡፡
ንግስት በ1980 ዓ.ም ከአሁኑ ባለቤቷ ዶክተር አሸናፊ ጐሳዬ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀምረው ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ወደ ሄደበት ቫይማር (Weimar) የምትባል የጀርመን ከተማ ጋብዟት በሄደችበት ጊዜ ቀለበትአሰሩ፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በሰኔ 12፤ 1986 የጋብቻ ስነ ስርአታቸውን በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ፈፀሙ፡፡ ንግስት ሰርግ ስታደርግ የመጀመሪያ ልጃቸው እምነት አሸናፊ የሶስት ወር ህፃን ነበር፡፡ ልክ በሁለትአመቱ በመጋቢት 1988 ሁለተኛዋን ልጃቸውን ቃልኪዳን አሸናፊን ወለደች፡፡
3. ትምህርት
በ1974 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በ1978 ዓ.ም በውጭ ቋንቋዎች እና ስነ - ፅሁፍ (እንግሊዘኛ) የባችለር ዲግሪ አግኝታለች።
ንግስት ከብዙ አመታት በኋላ በ1997 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ በስርዓተ- ጾታ ጥናት(Gender Studies) የድህረ- ምረቃ ፕሮግራም አጠናቃ በ1999 ዓ.ም ማገባደጃ ለይ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡
አሜሪካ ከሄደች በኋላም ወደ ስመ -ጥሩው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዘርን ካሊፎርኒያ (University of Southern California) በመግባት በሶሻል ዎርክ ሌላ የማሰተርስ ዲግሪ (Master in Social Work)ተቀብላለች፡፡ ንግሰት ሰልፉ በአሁኑ ወቅት Licensed Independent Clinical Social Worker ነች፡፡
4. የሙያ ህይወት
ንግስት ሰልፉ ከዩኒቨርሲቲ እንደጨረሰች ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ የገባቺው በ1979 ዓ.ም ነው፡፡
ስለ ሬዲዮ የስራ ዘመኗ ስትጠየቅ በአጭሩ “እንደተመኘኋት አገኘኋት” ነው ትላለች።
ያን ግዜ ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ወደ መንግስት መስሪያ ቤቶች ይመድብ የነበረው በአብዛኛው ማዕከላዊ ዘመቻ መምሪያ ይባል
የነበረው መስሪያ ቤት ነበር፡፡ ንግስት በተለያየ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን ላይ በሰጠችው ቃለምልልስ እንደገለፀችው የኢትዮጵያ ሬዲዮ
አንድትመደብ አስቀድማ አመቻችታለች ፡፡ በራዲዮ ጣቢያው የፕሮግራም መምሪያ ሀላፊ የነበሩት በታዋቂው ጋዜጠኛ አቶ ታደሰ ሙሉነህ
በፅሁፍ እና የድምፅ ብቃቷ ከተፈተነች በኋላ “ከመደቡሽ እንቀበላለን” የሚል እሺታን ማግኘቷን ተከትሎ ወደዚያው ተመድባለች፡፡
በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ደማቅ አስተዋፅኦ አንዳላቸው ከሚታመንባቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዷ የሆነችው ንግስት የቃላት አመራረጧ፣ አጫጭር አረፍተ- ነገሮች አጠቃቀሟ፣ የድምጽ ቅላፄዋ እና ከእሷ በፊት ያልተለመደ የአነባበብ ዘይቤዋ ለየት አድርጎ አጉልቷታል፡፡ ንግስት ረጅም አረፍተ ነገር ለሬዲዮ እንደማይገባ ስትገልፅ “ሬዲዮ ቃላት መደረት አይወድም" ትላለች፡፡
ንግስት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከ1979- 89 ዓ.ም ለአስር አመታት ነው በሙያው ላይ ያሳረፈችው አሻራ ከጋዜጠኝነት ሙያ
ከራቀች ከብዙ አመታት በኋላ አልደበዘዘም፡፡ በእሷ የተጀመረው የአፃፃፍ እና አቀራረብ ዘይቤ በኋላ በኋላ ወደ ሙያው በገቡ ጋዜጠኞች
የተለመደ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮ ስራ አቋርጣ ወደ ኖርዌይ ሄዳ እንደተመለሰች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሶስት አመታት ተኩል ሰርታለች፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት በሪፖርተርነት እና በዜና አዘጋጅነት ሲሆን የቀረው ጊዜ ደግሞ በአማርኛ ፕሮግራም ክፍል መሪነት ነው፡፡
ንግስት የ1997 ሀገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሁኔታ የጋዜጠኝነት ስራ
ከምንጊዜውም ይበልጥ ህሊናን የሚፈትን ሆኖ ስላገኘችው፤ በተለይም በነበረችበት የሐላፊነት ቦታ መቀጠል ለአገዛዙ ወንጀል
ተባባሪ መሆን ነው ብላ ስለወሰነች ስራዋን በገዛ ፍቃዷ ለቃለች።
በጊዜው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ምክትል ስራ አስኪያጅ የነበረው ሃላፊ ወደ ግል ስልኳ ደውሎ ወደቦታዋ አንድትመለስ
ለማግባባት ሲሞክር ምላሿ “እንኳን ፆሜን የማላድር ሆኜ ቀርቶ፤ ደሞዝ ስለቀረ የምበላው እና የማርፍበት የሚቸግረኝ ቢሆን እንኳን
ለህሊናዬ መገዛትን ስለምመርጥ አልመለስም” እንዳለች ይነገራል፡፡
ንግስት ከሀገር ከወጣች በኋላም ከጋዜጠኝነት ሙያ ላለመራቅ ሞክራለች:: ከዚህም ውስጥ በጉልህነት የሚጠቀሱት በኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮ ቴሌቪዥን (ኢሳት) አልፎ አልፎ የምታቀርበው ሪፖርት እና KLFE1590 ይባል በነበረ አንድ የሲያትል ራዲዮ ጣቢያ ታቀርብ የነበረው በራሷ ስም ተሰይሞ የነበረው NigistSelfu Radio Show ነው፡፡ የሬዲዮ ዝግጅቱ በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ አመሻሽ አንድ አንደ ሰዓት ለአንድ አመት ተኩል ያህል ይተላለፍ ነበር፡፡ ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደዚሁም በአሜሪካ ነዋሪ ኢትዮያጵዊያን ህይወት ላይ የሚያተኩር ነበር። KLFE 1590 ፎርማቱን ቀይሮ የአየር ሰዓቱን ለተለያዩ ዝግጅት አቅራቢዎች ከማከራየት ይልቅ የ Conservative Talk Radio ራዲዮ ፎርማት ለመከተል ሲወስን የንግስት ሰልፉ ሬዲዮ ሾው ዝግጅትም ድንገት ተቋረጠ፡፡
ንግስትም በዚህ አጋጣሚ በማዘን ጋዜጠኝነትን ለጊዜው ለመተው በመወሰን ወደ ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም
ገባች፡፡
ንግስት ሰልፉ በአሁኑ ወቅት በሲያትል ከተማ በ University of Washington Medicine ስር በሚገኘው Harborview Medical Center ውስጥ Medical Social Worker ሆና በመስራት ላይ ነች::
5. ጉብኝት እና የስራ ቦታ
ንግስት ሰልፉ በስልጠና፣ በስራ ምክንያት እና በግል ከአውሮፓ ( እንግሊዝ፣ ጣሊያን ፣ ስዊድን ፣ ኖርዌይ ፣ጀርመን)
ከአፍሪካ (ግብፅ፣ ቱኑዚያ ፣ ሱዳን ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ፣ ሞዛምቢክ ፣ ዚምባብዌ ፣ናይጄሪያ እና ቡርኪናፋሶ
እና ሴኔጋል) እንዲሁም ከመካከለኛው እና ሩቅ ምስራቅ ( የተባበሩት ኤሚሬቶች ፣ቻይና እና ጃፓንን) የመጎብኘት እድል አግኝታለች፡፡
ባለቤቷ የዶክትሬት ዲግሪ (PhD) በተቀበለበት በኖርዌይ፣ ትሮንድሀይም ከተማ ከ1997 -2001 ኖራለች፡፡
ወደ አሜሪካ የሄደችው በ2000 ዓ.ም ሲሆን አሁን የምትኖረው በሰሜናዊ ምዕራብ ጠርዝ ላይ በምትገኘው ሲያትል ከተማ
ነው፡፡
ንግስት ወደ አሜሪካ የሄደችው መስከረም 24፣ 2000 የ43ኛ አመት የልደት በዓሏ ቀን ነበር። አሜሪካየሄደችው ከባለቤቷ
እና ያኔ የ13 እና የ11 ዓመት ከነበሩት ሁለት ልጆቿ ጋር ባለቤቷ ዝነኛውን ፉልብራይት ስኮላርሺፕ (Fulbright
Scholarship) ማግኘቱን ተከትሎ ነው፡፡
6. የበጎ ፍቃደኝነት ተሳትፎ
ንግስት ሰልፉ ሲያትል ውስጥ በፀረ ወያኔ ትግል በአሜሪካ ውስጥ ጉልህ ሚና ከነበራቸው መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያውያን
ህዝባዊ ፎረም በሲያትል (Ethiopian public forum in Seattle) መስራቾች አንዷ ናት፡፡
የኢትዮጵያ የሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከተቋቋመ ጀምሮ የድጋፍ ኮሚቴን ለበርካታ አመታት መርታለች። ኮሚቴው ለኢሳት ወደ ግማሽ ሚሊየን ዶላር በማሰባሰብ በአለም ላይ ካሉ የኢሳት ደጋፊ ከተሞች የቀዳሚነቱን ቦታ ይይዛል ፡፡ የኢሳት የድጋፍ አለም አቀፍ ኮሚቴም አባል ነች፡፡ በተጨማሪም በምዕራባዊው ክፍለ- ግዛት የሚካሄዱ እና ኢሳት ላይ ሊቀርቡ የሚገባቸውን ክንውኖች ለኢሳት ዘግባለች፡፡
የምትኖርበት ሲያትል ከተማ እ.ኤ.አ በ2017 ባዘጋጀው Poetry on Buses ፕሮጀክት ላይ ግጥሞች በኢትዮጵያ በሚነገሩ ቋንቋዎች ከ 20 በላይ ግጥሞች አስችላለች፡፡
ንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ትኖር በነበረበትም ጊዜ በተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ስር በሚንቀሳቀሰው WASH Ethiopia ብሄራዊ ኮሚቴ አባል ነበረች:: WASH Movement ኢትዮጵያን በመወከል በሴናጋል ፣ በናይኖቢ እና ኡጋንዳ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርባለች፡፡
ሁለተኛ ደረጃ የተማረችበት መስከረም ሁለት ት/ቤት ሀምሳኛ አመት በአሉን ሲያከበር በሀገር ውስጥና በውጪም ያሉ የቀድሞ
ተማሪዎችን በማሰባሰብ ት/ቤቱን ለመደገፍ በተቋቋመ ኮሚቴ በአባልነት አገልግላለች፡፡
7. የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ
በተገኘው ጊዜ እና አመቺ አጋጣሚ ሁሉ በተለያዩ በምትኖርበት ከተማ አካባቢ ውጪ ያሉ ቦታዎችን መጎብኘት እንደሚያስደስታት
የሚያውቋት ይናገራሉ፡፡
ንግስት የተፈጥሮ በተለይም ወንዝ፣ ሃይቅም ይሁን ውቅያኖስ የውሃ አፍቃሪ ነች።
ለቅርብ ቤተሰቦቿ እና ዘመዶቿ ያላትቅርበትና ፍቅር የሚያስገርም ነው ይባላል፡፡
መዝጊያ ፤ ይህ
መዝጊያ የዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጆችን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
ንግስት ሰልፉ በተለይ ስመ-ጥር በነበረችባቸው በ1980ዎቹ ጊዜያት ሙሉ አቅሟን አውጥታ ስትሰራ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ እነ ጌታቸው ሀይለማሪያም ዜና ፋይልን በጀመሩበት ጊዜ ንግስት ሰልፉ ዜና በመስራት ብቻ ሳይሆን ዜናን ለማቅረብ በሚመጥን አስገራሚ ድምፁዋ ታላላቅ ዜናዎችን አየር ላይ ስታውል ነበር፡፡ ይህ የ30 አመት ትዝታን የሚያመጣ የእነ ንግስት ዘመን ምናልባትም ወርቃማው ዘመን ሊባል ይችላል፡፡ እናም ንግስት በዚህ ወርቃማ ዘመን ውስጥ እንደማለፏ አብረዋት ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ ከተቀለቀሉ ባለሙያዎች ጋር ሆና ለኢትዮጵያ የሬድዮ ጋዜጠኝነት እድገት የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ንግስት ለ10 አመታት በዚህ እጅግ በምታከብረው ሙያ ላይ ስታገለግል መስራት ከሚጠብቅባት በላይ ሰርታ ሀገሯን ማገልገል ትመኝ ነበር፡፡ እርግጥም በቆየችባቸው ጊዜያት የራሷን አሻራ ስለማኖሯ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ንግስት በ2000 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የዛሬ 14 አመት ወደ ባህር ማዶ ካቀናችም በኋላ የሚድያ ፍቅሯን ለመወጣት የተቻላትን ታላቅ ጥረት አድርጋለች፡፡ በባህር ማዶ እንደ አንድ የሚድያ ባለሙያ የሚጠበቅባትን በማከናወን አንድ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሏ ለራሱዋ ትልቅ ርካታን የሚያስገኝላት ነው፡፡ በተለይ በኢሳት ቲቪ ምስረታና መጠናከር ላይ ትልቅ ሙያዊ እገዛ በማድረግ ንግስት የማይዘነጋ ትልቅ ሚና ነበራት፡፡ ስለሆነም በዚህ ጥረቷ መመስገን እንዳለባት እናምናለን፡፡ ንግስት በአሁኑ ሰአት የማህበራዊ ጥናት ባለሙያ ሆና እያገለገለች አንድ ነገር ለኢትዮጵያ ለመስራት እየተጣጣረች እንደሆነ እናምናለን፡፡ ይህንን የንግስት ሰልፉን ታሪክ ያቀናበርነው አዲሱ ትውልድ ያለፈችበትን መንገድ እንዲያውቅ በመሻት ነው፡፡ ንግስት ሰልፉ የ1980ዎቹን የዜና ፋይል ታሪክ በወጉ የምታውቅ የራሷ ጉልህ አሻራ ያኖረች በመሆኑ ልናመሰግናት እንወዳለን፡፡
ሲያትል የንግስት ሠልፉ የሬዲዮ ዝግጅት ይተላለፍበት በነበረበት ስቱዲዮ በ2002 ዓ.ም
በ1989 መስከረም ወር ላይ ዋሽንግተን ዲሲ በ VOA ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደ ስልጠና ላይ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ