94 . አብይ ኤፍሬም ሞትባይኖር Abiy Ephrem Motbaynor
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ማእከል ለሀገራቸው የሰሩ ግለሰቦችን አጭር ግለ-ታሪክ በዊኪፒዲያ ላይ እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ‹‹ሰው በህይወት ሳለ ታሪኩን ሰንዶ ለትውልድ ያስቀምጥ›› የሚለውን ግባችንን ደግፈው በርካታ ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን እንድንጽፈው እየፈቀዱ ናቸው፡፡ ታሪካቸው እንዲጻፍ የምንሻቸው ሰዎች ከሁሉም የሙያ መስክ ቢውጣጡ ደስ ይለናል፡፡ ለዛሬ ታሪካቸው እንዲሰነድ ፈቃዳቸውን የሰጡን የመንግስት የስራ ሃላፊ አቶ አብይ ኤፍሬም ናቸው፡፡ እኒህ ለሚድያ ቅርብ የሆኑ ሰው ሚድያን ያጠኑ ሚድያም ላይ የሰሩ ናቸው፡፡ አቶ አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በመዛወር የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን በኃላፊነት የመምራት ዕድል የገጠማቸው ሲሆን በአሁኑ ሰአትም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።ሀገር የምታልፈበት ታሪክ በስራ መሪዎቿ ግለ-ታሪክ ሊታይ ይችላልና የእኒህ ሰው የህይወት ተሞክሮ ለብዙዎች ያስተምራል ብለን በማሰባችን የህይወት ገጻቸውን ማሳየት እንጀምራለን፡፡ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፤ ሚኒስትሮች ፤ ሚኒስትር ዴኤታዎችም በቅርቡ ጎራ ስለምንል ብእር ከወረቀት አዋህዳችሁ ቁዩን፡፡ ይህ የአቶ አብይ ኤፍሬም ታሪክ የተሰጡ ምስክርነቶችን ጨምሮ በጋዜጠኛ ጸጋ ታሪኩ እና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰናዳ ሲሆን ጥሞና ሰጥተው እንዲያነቡትም ተጋብዘዋል፡፡
"የሠላ ወታደራዊ ሠላምታ"
ገና በማለዳው ነፍሱ ለውትድርና ሙያ ልዩ ስፍራ ነበራት፡፡ "የሠላ ወታደራዊ ሠላምታ" ሲመለከት ለጋ ነፍሱ በሃሴት ትደምቃለች፡፡ በአጋጣሚ ወታደራዊ ሠላምታው ተቋዳሽ የመሆን ዕድል ሲገጥመ ደግሞ ደስታው ድንገት ሽቅብ ይወነጨፋል፡፡
ወላጅ አባቱ አቶ ኤፍሬም ሞትባይኖር በደርግ ዘመን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊ ነበሩ፡፡ በዘመኑ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንንኖች ለወላጅ አባቱ የሚሰጡት የሰላ ወታደራዊ ሰላምታን ተከትሎ በእምቡጥ አእምሮው ውስጥ ወፍራም ትዝታን አትሟል፡፡
በደርግ ዘመን አጐቶቹም በባህር-ኃይል፣ በምድር ጦር እና በአየር ኃይል ውስጥ በተለያየ ወታደራዊ ማዕረግ ሃገራቸውን ያገለግሉ ስለነበር ነፍሱ ለውትድርና ሙያ በጥብቅ እንድታደላ አድርጓታል፡፡
በተለይ “ወታደራዊ ሠላምታ” እንደ አባቱ የመቀበል ክብር፣ አልያም እንደአጐቶቹ በቆፍጣና ተክለሰውነት ሰላምታ የመስጠት ዕድል ባለቤት የመሆን ፍላጐቱ ከለጋ ዕድሜው ነበር ውስጡ የተጠነሰሰው፡፡
“በወታደራዊ ሙያ ስልጠና አልፌ የክብር መለዬ ደፍቼ ሃገሬን ማገልገል ባልችልም፤ አሁን ባለሁበት የሙያ መስክ እና የሥራ ኃላፊነት የሰላ ወታደራዊ ሠላምታ ሰርክ የመቀበል እና የማየት ዕድል አግኝቼያለሁ፡፡ በከፊልም ቢሆን ምኞቴ የተሳካ ይመስለኛል፤ አሁንም ድረስ ውስጤ በሃሴት እንዲደምቅ እና ሥራዬን ለመከወን ብርታት ይቸረኛል፡፡” ይላል፡፡
ውልደት እና የለጋ ዕድሜ ጉዞ
ከመንግስት ሠራተኛ ቤተሰብ የተገኘው አብይ ኤፍሬም ሕይወቱን በመንግስት ሥራ ላይ አድርጐ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ውልደቱ 1974 ዓ.ም ነው፡፡ ከወላጅ አባቱ ከአቶ ኤፍሬም ሞትባይኖር እና ከእናቱ ከወ/ሮ አሰለፍ ተሰማ በመዲናችን አዲስ አበባ ነሐሴ በገባ በ29ኛው ቀን በንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ይህችን ዓለም ተቀላቀለ፡፡
የወላጆቹ አምሮት ገና ከጅምሩ አገሩንና ወገኑን የሚያስጠራ ትልቅ ሰው ሆኖ ማየት ነበር፡፡ ለበኩር ወንድ ልጃቸው መጠሪያ ስሙን አብይ ብለው አወጡለት፡፡ ብቸኛውን ወንድ ልጃቸውን ለስሙ እንዲመጥን በጠንካራ ሥነ-ምግባር እንዲታነፅ ይደክሙ ያዙ፡፡
ወላጅ አባቱ በደርግ ዘመን በከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነት እናት ሃገራቸውን ለማገልገል የተለያዩ ክፍለ ሃገራት ይዘዋወሩ ነበር፡፡ ሆለታ፣ ሸዋሮቢት፣ ሻሸመኔ፣ መቂ እና ዝዋይ ቤተሰቡን ይዞ በመዟዟር ከባድ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ለእናት ሃገር ማገልገል ታላቅ ክብር ቢሆንም የተረጋጋ የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት በመንግስት ደሞዝ ህይወት አልጋ ባልጋ እንዳልነበረች አብይ ያስታውሳል፡፡
እድሜው ለመደበኛ ትምህርት እስኪደርስ ድረስ ከወላጁቹ በተጨማሪ በመልካም ግብረገብ ተኮትኩቶ እንዲያድግ በዙሪያው ከህሊና ሰሌዳው ታትመው የዘለቁ ባለውለታዎቹን እስከዛሬ በክብር ያነሳቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዕድሜው ለደረሰባቸው ሴት አያቶቹ ልዩ አክብሮት እና ደማቅ ትውስታውን በምልሰት ያወሳል።
የወላጅ አባቱ እናት (አያቱ) ወ/ሮ ዝይን ንጉሴ ለአብይ ያላቸው ስስት እና ፍቅር ልዩ ነበር፡፡ ለቤተሰብ ጥየቃ በሄዱ ቁጥር ከአጠገባቸው እንዲርቅ አይፈልጉም፡፡ አንድ ቀን ግን የልጅ ነገር ሆነና ወ/ሮ ዝይን በለጋው አብይ ክፉኛ ተበሳጩ፡፡ በተደጋጋሚ ቢያዙት ውስጡ ለጨዋታ እያደላ ትዕዛዛቸውን ከመጤፍ አልቆጠረውም፡፡ ቁጣ በተቀላቀለበት ስሜት ጠሩት፡፡ አብይም የአያቱ ቁጣ እንግዳ ከመሆኑ ባሻገር ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስበው እርጉዝ የሚያስጨነግፍ ይመስል እንደነበር በህሊናው አቅቦ ይዞታል፡፡
ወ/ሮ ዝይን ንዴታቸው እየተጋፋቸው “እኔ የማዝነው ባንተ ስንፍና ሳይሆን ልጅሽ (አቶ ኤፍሬም) ሰነፍ ልጅ አለው መባሌ ነው!” ብለው አንባረቁበት፡፡ ከስነ-ምግባር ውኃ ልክ ወርዶ መገኘት ለቤተሰብ የመርህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ክብርን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ህጸጽ መሆኑን በስውር ነገሩት፡፡ ከዛች መራር ክስተት በኋላ አያቱን ለማስደሰት ብቻ ሳይሆን ልጇ (ወላጅ አባቱ) ሰነፍ ልጅ አለው ተብላ ሰው እንደይዘባበትባት በሚል ቅን ስሜት አብይ ታዛዥነቱን በተግባር እያፀና ዘለቀ፡፡
የወላጅ እናቱ እናት ወ/ሮ በርኸ ጣሴ እንዲሁ በአብይ መልካም ሰብዕና ግንባታ በጐ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ማለዳ ተነስተው የዘወትር ፀሎታቸውን ሲቋጩ፤ “ የወለድነውን፤ የወደድነውን ጠብቅልን!“ ብለው የማሳረግ ልማድ ነበራቸው፡፡ ከስራቸው የማይጠፋው ልጅ አብይ የአያቱን የፀሎት ማሳረጊያ ሀረግ በቃሉ ሸምድዷት ኖሯል፡፡
አንድ ማለዳ ጠብቆ “ትርጉሙ ምን ማለት ነው” ብሎ አያቱን ጠየቀ፡፡ “የወለድነው ማለት የእኛን ቤተሰብ ፈጣሪ ከክፉ እንዲጠብቅልን ነው፤ የወደድነውን ማለት ደግሞ ከቤተሰብ ውጭ በዘር፣ በሃይማኖት የማይመስሉንን በዙሪያችን ያሉ ጐረቤቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ሜዳ እየሄድክ አብረህ ምትጫወታቸው ባልንጀሮችህን በሙሉ ችግር እንዳይደርስባቸው ፈጣሪ እንዲጠብቃቸው ነው፡፡" ብለው በሚገበው ቋንቋ አስረዱት፡፡ ከአያቱ ማብራሪያ በኋላ ከቤተሰቡ ውጪ ያሉ ጎረቤቶቹ፣ ባልንጀሮቹ እና ከማህበረሰቡ ጋር በፍቅር እና በአክብሮት ወዶ-ተዋዶ ለመኖር የህይወት ልምምድ መሰረት እንደጣሉለትና በአሁን ማንነቱ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በኩራት ይመሰክራል፡፡
"መቂ አንድ እንጀራ በቂ!"
የአብይን የልጅነትና ጉርምስና ታሪክ መቼት በመሪነት የተጋራችው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የመቂ ከተማ ናት፡፡ ሸገርን ለለመደ ሰው መቂ ጠባብ ከተማ ናት፡፡ (የቀድሞ መጠሪያዋ ዱቢሳ ነበር) ሁሉ ነገሯ የተጠጋጋ ነው፡፡ ታዳጊዋ የመቂ ከተማ በታዳጊው አብይ የሕይወት ፍኖት ደማቅ አሻራዋን አሳርፋለች፡፡
በወላጅ አባቱ የሥራ ጠባይ ምክንያት ከመቂ ከተማ ጋር ሕብረት የፈፀመው በ-1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት የቄስ ትምህርት ቤት በመግባት እንደመሰሎቹ መደብ ላይ ተቀምጦ ፈደል እና ቁጥር በፍጥነት እንዲለይ አግዞታል፡፡
በ-1981 ዓ.ም ጀምሮ በመቂ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተከታትሏል፡፡ የደርግ መንግስትን ውድቀት ተከትሎ ሕይወት የነበራትን መልክ እና ቀለም ይዛ መቀጠል አልቻለችም፡፡ ወላጅ አባቱ በመንግስት መውደቂያ ዋዜማ ጫፍ በምክትል አውራጃ አስተዳዳሪነት ተሹመው ወደ ጐጃም ተዛውረው ሄዱ።እንደቀደሙት ጊዜያት ቤተሰብ ይዞ ለመጓዝ የሃገሪቱ ፖለቲካው ድባብ ጋባዥ አልነበረም፡፡
ወዲያው የኢህአዴግ ጦር ወደ መሃል አገር እየገሰገሰ የነበረበት ወቅት ስለነበር ቤተሰቡ የመበታተን አደጋ ተጋርጠበት፡፡ አዲሱ መንግስት እግሩን እስኪተክል እና የሃገሪቱ ሠላም እስኪረጋጋ ከወላጅ እናቱ እና ከታናሽ እህቱ ረቂቅ ኤፍሬም ጋር የኑሮን ዱብዳ እዛው መቂ ከተማ የባዳ ዘመድ ጋር ተጠግቶ ለማሳለፍ እንደተገደደ አብይ ይናገራል፡፡
ሃገር ተረጋግቶ ወላጅ አባቱ እንደሌሎች የደርግ ሹማምንት የመታሰር ዕጣ ሳይገጥማቸው ወደ መቂ ወረዳ አስተዳደር ምክር ቤት በአማካሪ ባለሙያነት መደበኛ ሕይወታቸውን ቀጠሉ፡፡ የተበታተነው ቤተሰብ ዳግም ተዋህዶ ሰላማዊ ኑሮ መኖር ተጀመረ።
በነዚያ የፈተና ጊዜያት መላ ቤተሰቡ የባይተዋርነት ስሜት ሳይፈጠርበት በማስጠለልና በመደገፍ የመቂ ከተማ ድፍን ነዋሪ በሙሉ ውለታውን ለማመስገን ከቃል በላይ መሆኑን ይስረዳል፡፡
“መቂ አንድ እንጀራ በቂ!” የሚለው ተለምዳዊ አገላለጽ ከዕውነት በላይ መሆኑን ለመቂ ከተማ እና ነዋሪ ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ ሁነኛ ህያው አማኝ እሱ እና ቤተሰቦቹ ስለመሆናቸውን በኩራት ይገልፃል፡፡
የሚቻለውን ብቻ ሳይሆን የማይቻለው የኑሮ ገፅ
ወላጆቹ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ ብቻ ነው የነበራቸው፡፡ ሁለቱምንም ልጆች በትምህርትታቸው ውጤታማ እና በግብረገብ የታነፁ ሆነው እንዲያድጉ የሚችሉትን ብቻ ሳይሆን የማይችሉትንም ሁሉ ከመሞከር ወደኋላ እንዳላሉ - አብይ ይናገራል፡፡
በጊዜው የመንግስት ሰራተኛ ወር ደሞዝ ጠብቆ ኑሮን መምራት አስቸጋሪ ስለነበር ጎን ለጎን ተጨማሪ ገቢ አማራጭ ለማስፋት የከብት እርባታ እና የግብርና ሥራዎች ላይ ድፍን ቤተሰቡ ለመሰማራት የነበረው ምርጫ ከዛ ያለፈ አልነበረም፡፡
ቤተሰቡ በመረጠው አማራጭ የገቢ ማስገኛ ዘርፍ ራሱን የቻለ ዕውቀት እና ፅናት ይጠይቅ ነበር፡፡ ይህ ተልዕኮ የኑሮ ዘይቤ ለውጥ ማምጣቱ የግድ ቢሆንም እንደመደበኛው የከተማ ነዋሪ ዝቅ ብሎ ከፍ የሚያደርግ ሥራ ውስጥ መሰማራት መቻሉ እንደትልቅ ዕድል ተወስዷል፡፡
በተለይ የግብርናው ዘርፍ ኑሮን ከመደጎሙ በላይ የገአርሶ አደሩን እና የመደበኛውን ነዋሪ ዝቅተኛ ኑሮ ገጽታ በርቀት ሳይሆን በቅርበት፤ በማየት ሳይሆን በመሆን፤ የመቂ ከተማ የታዳጊነት ዕድሜው የሕይወት መልመጃ ደብተር በመሆን እንዳገለገለችው ውለታዋን በታላቅ አክብሮት ያስታውሳል፡፡
በመቂ ከተማ እና አጎራባች ገጠር ቀበሌዎች በብዛት የኦሮሞ ማህበረሰብ በስፋት የሚኖርበት ሲሆን፤ ከህብረተሰቡ ጋር ባለው የደረጀ መስተጋብር የኦሮሞን ባህል ለመረዳት እና ቋንቋውን ከአማርኛ ቀጥሎ በመግባቢነት ለመልመድ ምቹ አውድ ፈጥሮለታል፡፡
አብይ ለትምህርት ልዩ ትኩረት እና ክብደት ይሰጥ ስለነበር በ-1985 ዓ.ም ወደ መቂ ካቶሊክ ት/ቤት የመግቢያ ፈተናውን በመውሰድ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የ5ተኛ ክፍል ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
መቂ ካቶሊክ ትምህርት ቤት በከተማው እስከ 12ተኛ ክፍል ድረስ ትምህርት የሚሰጥበት ብቸኛ የትምህርት ተቋም ከመሆኑ በላይ በፈረንጆች የሚመራ ስመ-ጥር እና በትምህርት አሰጣጡ አዲስ አበባ ከሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት ጋር በአንጻራዊነት በዘመናዊነቱ የሚቀራረብ እንደነበር ይነገራል፡፡
በት/ቤት ተሳትፎ የደረጃ እና የከፍተኛ ማዕረግ ተማሪ ከመሆን ባሻገር ለስነ-ፅሁፍ ከነበረው የጠና ዝንባሌ አንፃር በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተወዳደረ የስነ-ጽሑፍ ስራዎቹን በማቅረብ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡
የሥነ-ጽሑፍ ልክፍት ጅማሬ
በአብይ የሥነ-ጽሑፍ ልክፍት ውስጥ የአባቱ ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ አቶ አፍሬም ብርቱ አንባቢ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ መንፈሳዊ ድርሳናትን ሲተረጉሙ ብላቴናው አብይ ከጎናቸው ሆኖ ብዙ ተምሯል፡፡ ለአድቬንቲስት ሰባተኛ ቤተክርስቲያን አማኞች የሕይወት ክህሎት ማበልፀጊያ በርካታ መፀሃፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በትርጉም ሲመልሱም በለጋ አዕምሮው የሚችለውን ሁሉ ቀስሟል፡፡ በአባቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃት የተሳበው አብይ የፅሁፍ ሥራ የሕይወት ፍኖት ማጀቢያው መሆኑን የተረዳው በዛ ጊዜ መሆኑን ያስታውሳል፡፡
የአባቱን ዳና እየተከተለ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ አጫጭር ታሪኮችን የመጻፍ ልምምድ ውስጥ ተጠመደ፡፡ በሂደት የቋንቋ አቀባበሉ እየዳበረ በመምጣቱ በት/ቤት ውስጠ በመድረክ መሪነት፣ በአስተርጓሚነት እና በስነ-ፅሁፍ ሥራዎቹ ተሳትፎውን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ አደረገ፡፡
ከትምህርት ሰዓት ውጪ ቤተሰቡን በጉልበት ከመደገፍ ከሚያደርገው ተሳትፎ ጐን ለጐን ለእርሻ ሥራ ጊራባ ጀዌ በሚባል በከተማዋ አጐራባች ቀበሌ ገበሬ ማህበር በሚያደርገው ምልልስ የሚታዘበውን በወረቀት ላይ እየከተበ በድርሰት መልክ ለክፍል ጓደኞቹ በማንበብ ውዳሴ (አድናቆት) መሰብሰቡን ገፋበት፡፡
በንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል መሃል አዲስ አበባ እትብቱ የተቀበረው አብይ፤ ከከተሜነት ይልቅ ነፍሱ እና የሕይወት ልምምዱ ለገጠሩ ኑሮ ብሎም ለግብርና ዘርፍ ያደሉ ይመስላል፡፡
ጉርምስና ሲጫጫነው አጥንቱ ሲጠና በሬ ጠምዶ ማረስ፤ መሬት አለስልሶ ማዘጋጀት፤ ዘር መርጦ መዝራት፤ ጉልጓሎ፣ በምርት አጭዶ እና አፍሶ ጐተራ እስከማድረስ ሂደት የመሳተፍ ዕድል ማግኘቱን በስሜት ያወጋል፡፡
“የአንድ ኢትዮጵያዊ የሕይወት ሰም እና ወርቅ በተግባር የሚፈታው በግብርና ዘርፍ መሳተፍ ሲችል ነው” ይላል አብይ፡፡ ብዙ ወዳጃቹ ለግብርና ሕይወት የራቁና ከተሜነት የዋጣቸው ናቸው፡፡ "የኔን የህይወት ልምድ ሳስበው ብዙ ነገር እንደጐደለባቸው ይሰማኛል፡፡ በተለይ ዛሬ ላይ ባለንበት የሥራ ኃላፊነት ስለገበሬው ህይወት ዕድል እና ተስፋ፣ ፈተና እና ስጋት ኖረን ካላየነው በንድፈ ሃሳብ ብቻ እንወጣለን ማለት አዳጋች ነው፡፡ የምንደግፈውን ወገን የህይወት ገጾች ቀርበን መረዳት ይገባናል፡፡" ይላል፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ጉዞ
በ1992 ዓ.ም የወሰደው የማትሪክ ፈተና ውጤቱ ለመምህራን ኮሌጅ የሚያበቃው ነበር፡፡ የልጅነት ህልሙ በባሌም ሆነ በቦሌ ስድስት ኪሎ ወደ የሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መግባት ሲሆን ወላጆቹም የበኩር ልጃቸውን ፍላጎት ለማሟላት በማታው መርሃ ግብር አስመዘገቡት፡፡ በ1993 ዓ.ም አዲስ አበባ ቀበና በሚገኘው አክስቱ ቤት ሆኖ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል የዲግሪው ትምህርቱን በማታው መርሃግብር መማር ቀጠለ፡፡
ጎረምሳው አብይ እትብቱ ከተቀበረበት መዲና ጋር ዳግም መገናኘቱ አዲስ የህይወት ገጽ ገልጦለታል፡፡ ከዩኒቨርስቲ ትምህርቱ ጎን ለጎን የማትሪክ ውጤቱን ለማሻሻል ቀን ቀን በቁጭት ዝግጅቱን አጠናክሮ ገፋበት፡፡ የማትሪክ ውጤቱን አሻሽሎ መስከረም 1994 ዓ.ም በቀድሞ የኢትዮጵያ መገኛኛ ብዙሃን ኢንስቲትዩት በግል ተወዳድሮ በህትመት ጋዜጠኝነት ለሁለት ዓመታት የዲፕሎማ ትምህርቱን ተከታትሎ በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ፡፡
በዘመኑ የኢትዮጵያ መገኛኛ ብዙሃን ኢንስቲትዩት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት እና የማስታወቂያ ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በዲፕሎማ መርሃ-ግብር ስልጠና የሚሰጥበት ተቋም ነበር፡፡ በዘመኑ ኢንስቲትዩቱ ለግል ተማሪዎች ቁጥሩ ውስን የሆነ ዕድል ያመቻች ነበር። አብይ የመግቢያ ፈተናውን በብቃት በማለፍ የመጻፍ ክህሎት አምሮቱን በዕውቀት የሚያስደግፍበት አውድ ተፈጠረለት፡፡
ዲፕሎማውን እንዳጠናቀቀ በግሉ የሚዲያ ዘርፍ The Sun በተሰኘች ሳምንታዊ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት ተቀጠረ፡፡ ለአንድ መንፈቅ በሚሆን ዕድሜ ዜና የማምረት ልምምዱን አጠናክሮ ገፋበት፡፡ ወርሃዊ ደሞዙ ከትራንስፖርት ወጪ በላይ አትሸፍንም ነበር፡፡ እሷም ብትሆን ወር ሲሞላ በጉጉት ጠብቆ ሳይከፈለው ወሮቹ ይደራረቡ ጀመር፡፡ ይሄን ጊዜ ከራሱ ጋር መከረ፡፡
የግሉ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ታዳጊ በመሆኑ የተመነደገ ደሞዝ አያስመኝም፡፡ ባጋጣሚ የኢትዮጵያ መገኛኛ ብዙሃን ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ተካቶ በዲግሪ ትምህርት ለመስጠት ለግል ተማሪዎች የሰጠውን ዕድል ተወዳድሮ ፈተናውን አለፈ፡፡ የትምህርት ደረጃን ማሻሻል ቢያንስ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሞራል ስንቅ እንደሚሆነው ከራሱ ጋር ተማክሮ ወሰነ፡፡
በ-1995 አጋማሽ ላይ በዩኒቨርስቲው መደበኛ የቀን ተማሪ በመሆን የጋዜጠኝነት ትምህርቱን መማር ጀመረ፡፡ በተመሳሳይ ዩኒቨርስቲ በማታው መርሃ-ግብር የሚከታተለውን የቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ትምህርቱን ጊዜውን አጣጥሞ ቀጠለ፡፡
እርግጥ ነው! በቤተሰብ ምጥን ድጎማ ሁለት ዲግሪ በተመሳሳይ ጊዜ በመደበኛ እና በኤክስቴንሽን መርሃ ግብር መከታተል ቅንጦት ቢመስልም፤ ጊዜ እና ጉልበቱን አጣጥሞ ውጥኑን ከዳር ለማድረስ እየተጋ ተስፋ ሳይቆርጥ ተጨማሪ የገንዘብ ማግኛ መንገዶችን ማፈላለግ ጀመረ፡፡
እንደአጋጣሚ ሆኖ በርካታ የግል ህትመት ሚዲያዎች በቁጥር እየበዙ የመጡበት ወቅት ነበር፡፡ ለተለያዩ ጋዜጦች ለአምዶቻቸው መሸፈኛ የሚሆኑ መጣጥፎች፣ ዜና ትንታኔዎች እና የትርጉም ታሪኮችን በመጻፍ ውስን ገንዘብ ማግኘት በመቻሉ የዕለት ወጪ ጫናዎቹን ከማስታገስ ባሻገር በየሴሚሰተሩ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ የበለጠ ብርታት አጎናፀፈው፡፡
የልጅነት ጥንስስ ህልም እና የተግባር ፊቺ
ከትምህርት ህይወት ጎን ለጎን ከግሉ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ተዋንያን ጋር የፈጠረው ግንኙነት ቀስ በቀስ የተሻሉ ሃሳቦችን በመድፈር ግንዛቤ እና የመፈፀም ብቃቱን እንዲያጎለብት አግዘውታል፡፡ በወርሃ ሐምሌ-1996 ዓ.ም ናሽናል ኮንስትራክሽን ለተሰኘ የግል ወርሃዊ መጽሄት ላይ በዋና አዘጋጅነት ጠቀም ባለ ደሞዝ በመደራደር ተቀጥሮ ስራውን ጀመረ፡፡ ግልጽ የጊዜ ዕቅድ በመንደፍ የተቀጠረበትን የስራ ሃላፊነት ሳይሸራርፍ ሁለቱንም የዲግሪ ትምህርቶቹን በመከታተል በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ሃምሌ 1998 ዓ.ም ለመመረቅ በቃ፡፡
የጊዜ አጠቃቀም ክህሎቱ እና ያመነበትን የመፈፀም ብቃቱ በተግባር እየተፈተነ እና እያረጋገጠ መምጣቱ . . . ከፊደል ሀ ብሎ ከኑሮ ዋ ብሎ እንዲሉ አድርጎታል። በመቀጠል እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅት በተሰኘ ሃገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ኦፊሰርነት አግልግሏል፡፡
ዳግም ወደ ሚዲያው ተመልሶ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በዌብሳይት እና በእንግሊዘኛ ዜና ዴስክ ኤዲተርነት ከአንድ ኣመት በላይ ካገለገለ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርቱን በመከታተል የማስተርስ ዲግሪውን ሐምሌ 2002 ዓ.ም ይዟል፡፡
የመንግስት ስራ ሃላፊነት ጉዞ
በ2001 - 2007 ዓ.ም ጀምሮ በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን አገልግሏል፡፡ በተቋሙ ተልዕኮ መሰረት የሃገሪቱን ሴቶችና ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በእጅጉ የኮሙኒኬሽን ስራ ማስደገፍ የሚጠይቅበት ዓመታት ነበሩ፡፡ በርካታ ሃገር-አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ተከታታይ የህዝብ ንቅናቄ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በነዚህ የተቋም ቁልፍ ተግባራት በኮሙኒኬሽን ስራ መደገፋቸው ግድ ይሉ ነበር፡፡
ለዓመታት የዘለቁት መድረኮች የአብይን የኮሙኒኬሽን አመራር የጠየቁ ነበሩ፡፡ በትምህርት ዝግጅት እና በልምድ ያካበተውን የኮሙኒኬሽን ዕውቀት በተግባር ለመተርጎም ወርቃማ ዕድል እንደፈጠሩለት አብይ ይናገራል፡፡
በተቋም ውስጥ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬትን በሰው ሃይል፣ በግብዓት እና በአሰራር በማጠናከር፤ በማኔጅመንት ኮሚቴ ውስጥ የነቃ ተሳትፎን በማጎልበት፣ ከሚዲያ ተቋማት ጋር ትርጉም-አዘል የስራ መስተጋብር በመዘርጋት፤ ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ህብረ-ሃይል በመፍጠር እና የተቋሙን ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ደማቅ አሻራውን እንዳሳረፈ በቅርበት የሚያውቁት ይመሰክሩለታል፡፡
አብይ በነበረው የአገልግሎት ዘመን ሚኒስቴር መ/ቤቱን - ከክልል መዋቅሮች፣ ከልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ ከባለደርሻ አካላት፣ ከፌዴራል ተቋማት፣ ከአለም አቅፍ ተቋማት፣ ከሚዲያ እና ከሰፊው ማህበረሰብ ጋር ድልድይ በመሆን ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ሚናውን እንደተወጣ የቅርብ ስራ ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡
አብይ በሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊነት አገልገሎት ዓመታት ውስጥ ተቋሙ በሃገር አቀፍ ደረጃ ትርጉም ያላቸው ውጤቶች እንዲመዘገቡ ባደረገው ሚና እና በለውጥ ስራ አመራር ብቃቱ ከተቋሙ ሞዴል አመራር መሆን እንዳስቻለው ያስታውሳሉ፡፡
በሃገሪቱ የሕዝብ ግንኙነት ሙያ ተገቢውን ትኩረት እና ዋጋ ባልተሰጠበት ጊዜ፤ መንግስት እና ህዝብን እንደ ድልድይ በመሆን ወቅታዊ መረጃ በመስጠት፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማጐልበት፣ የተቋም እና የሚዲያ አጋርነትን በማጠናከር፣ በተያዩ ማህበራዊ -ፖለቲካዊ ንቅናቄዎችን በመፍጠር፣ ቁልፍ የማህበረሰብ ክንፎችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያጐለብቱ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በመምራት፣ በፌዴራል ተቋማት መካከል የህዝብ ግንኙነት ሥራ ክፍሎችን ህብረት በማጠናከር እና ሙያዊ መስተጋብር በመፍጠር እንዲሁም ተቋም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ህብረ-ሃይል (synergy) በመፍጠር ሙያዊ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡
የተሳትፎ መድረኮች እና ጥናታዊ ጽሁፍ አበርክቶ
ሚዛናዊ የስርዓተ -ፆታ ሥርዓት እና ፍትሃዊ የሚዲያ ተደራሽነት (ሃዋሳ፣ ጥቅምት2003 ዓ.ም.)
የመገናኛ ብዙሃን ሚና ለወጣቶች ልማት (አዲስ አበባ ፣ ጥር 2004 ዓ.ም.)
የሚዲያ አጋርነት ለሁሉ አቀፍ ዕድገት (አዳማ፣ የካቲት 2005 ዓ.ም.)
Elimination and prevention of all forms of violence against Women and girls
(57th CSW-UN New York – USA March 2013)
(Population Council Washington DC USA – Oct.8, 2014)
Enhancing the coordination and influencing capacity of Alliance to end child Marriage/ FGM (Girl’s summit, July 2014 London, UK)
ከመደበኛው ስራ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ አባል በመሆን ተቋሙ ተወዳዳሪነቱን እንዲያሳድግ፣ መልካም ገጽታውን እንዲገነባ፣ የሪፎርም እርምጃ ውስጥ እንዲጓዝ እና አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶችን መሠረት የሚጥሉ ሥራዎችን በመምራት ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡
በዚህ የህይወት መስመር በግል ጥረት የተቆናጠጠው ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊነት የመጨረሻ ግቡ እንዳልሆነ አብይ ያምናል፡፡ ኃላፊነት የሚሸከምበት ትከሻው ከፍታን ብቻ ሳይሆን ክብደት ባለችው የሃገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ከባድ የሥራ አውድ ውስጥ የማለፍ ልምምዱን እንዳዳበረለት ይናገራል፡፡
ከየካቲት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በመዛወር የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን በኃላፊነት መምራት ዕድል የገጠመው ሲሆን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በመሆን እስካሁን በማገልገል ላይ ይገኛል።
በስራ ህይወት ጉዞው ይህ ሃላፊነት የተለየ መሆኑን አብይ ይናገራል፡፡
"በታሪክ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት መረከብ የብቃት ከፍታ መገለጫ ሳይሆን፤ በፍጥነት ከሚለዋወጡ አውዶች ጋር ራስን በአዳጊ ዕውቀት አስማምቶ ለእናት ሃገር በሚበጁ ግዙፍ አጀንዳዎች ዙሪያ ገንቢ እና በጎ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚገጥም በህይወት የማይደገም ልዩ ዕድል ጭምር ነው፡፡"
ቢሮው ከሚከታተላቸው ሃገራዊ ጉዳዮች መካከል የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ብሄራዊ ኮሚቴ የማስተባበር ሚና አንዱ ነው፡፡ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ በቅርበት የመሳተፍ ዕድል ማግኘቱ ለተጨማሪ የማስተርስ ትምህርት እንደገፋፋው አብይ ይናገራል፡፡
በ-2011 ዓ.ም ስፔን ሃገር ከሚገኘው የካሉ ኢንስቲትዩት የሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከል በ-International Cooperation and Humaniterian Aid ሁለተኛ የማስትሬት ዲግሪውን ለሁለት ዓመታት ተከታተሎ አጠናቋል፡፡ የማስተርስ ትምህርቱን መማሩ ተልዕኮውን በተሻለ መረዳት እና ዓለም አቀፋዊ እሴት በሚጨምር አግባብ ለመፈፀም እንዳገዘው ያስረዳል፡፡ አሁንም ሃገር ካለችበት የዘመን መንፈስ ጋር የተናበቡ አጫጭር ጠቃሚ ስልጠናዎችን በመውሰድ፤ በማያቋርጥ ትጋት የመፈፀም አቅሙን እየገነባ የዕለት ስራውን በሃላፊነት ስሜት እየተወጣ ይገኛል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ዘወትር ወደ ቢሮ ሲገባ በልጅነት ነፍሱ ላይ የታተመውን የሰላ ወታደራዊ ሠላምታ የመቀበል አልያም ለከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ሲሰጥ የማየት ዕድል ገጥሞታል፡፡ በከፊልም ቢሆን የልጅነት ምኞቱ እንደተሳካለትና ሁሌም ውስጤ በሃሴት እየደመቀ ስራውን በልዩ ብርታት እየከወነ እንደሚገኝ በደስታ ስሜት ያወሳል።
የቤተሰብ ህይወት
አቢይ ነሐሴ 18፣ 2007 ዓ.ም ትዳር መሰረተ፡፡ ከባለቤቱ ወ/ሮ ትዕግስት ምስጋናው ጋር በትዳር ከተጣመረ በኋላ፤ የአንድ ወንድ እና የሁለት ሴቶች አባት የመሆን ተፈጥሯዊ ክብርን ተጎናጽፏል፡፡ የአብራኩ ክፋዮች ካለን አብይ፣ ሆናልያት አብይ እና ማልዳኪን አብይ ይባላሉ፡፡
አቢይ ቤተሰብ ከመሰረተ በኋላ በህይወቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳመጣለት ይናገራል፡፡ ቀዳሚ ባለድርሻ ተመስጋኝ ሚያደርጋት ደግሞ ባለቤቱን ወ/ሮ ትዕግስት ምስጋናውን ነው፡፡
"ውዷ ባለቤቴ ቲጂዬ ባል እና አባት የመሆን ክብርን ያጎናፀፈችኝ ሚስቴ ብቻ ሳትሆን፤ በዕለት ተዕለት ስራዬ ውስጥ 360º ቀለበታዊ ድጋፏን ማትነፍገኝ ጓደኛዬ ጭምር ናት፡፡ እኔም በሰጠችኝ ፍቅር እና አክብሮት ከፍታ ውሃ-ልኩን ጠብቄ ድርብርብ ሃላፊነቴን ሳልሰለች ለመወጣት (ከፈጣሪ እገዛ ጋር) እተጋለው፡፡" ይላል፡፡
በትዳር ተጣምሮ የመኖር ዘ-ልማዳዊ ክስተት ተደርጎ መወሰድ የለበትም ባይ ነው ~ አብይ። ትዳር በየቀኑ አዲስ እና ጤናማ የጋራ ህይወት ለማጣጣም ህብረ-ብዙ የህይወት ሃላፊነቶችን በጀርባ አደላድሎ በመሸከም፤ መልካም ባል፣ መልካም አባት፣ እንዲሁም መልካም ዜጋ በመሆን ከራስ ጋር የሚደረግ ውድድር ማካሄጃ የህይወት መድረክ መሆኑን ያምናል፡፡
መልካም ምኞት
በምድር ስንኖር በህይወት የምናልፍበትን ሳይሆን በህይወት የምንኖርበትን ቆይታ ለማሳመር መድከም ይኖብናል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ለተፈጠርን ዜጎች ደግሞ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ በተሰማረንበት የሙያ መስክ በጋራ ሊጠቅሙ፣ እሴት ሊያክሉ እና በመሻሻል ቅኝት ለወገን እና ለሃገር ሊያተርፉ በሚችል አስተሳሰብ ላይ ያለንን ጊዜ፣ ጉልበት እና ሃብት በማፍሰስ ለሚከተለው ትውልድ ምቹ መደላድል መፍጠር ይኖብናል፡፡
ፍፁም በማይጠቅሙ እና በሚጎዱ ሃሳቦች ተጠልፈን ተያይዞ ለመውደቅ መባዘን ለራስ፣ ለወገን፣ ለትውልድ እና ለሃገር አትራፊ ስለማያደርግ ከዚህ ማጥ ነቅተን በፍጥነት መሻገር ይገባል፡፡
ዘመን በሚፈልገው አሸናፊ አስተሳሰብ ዙሪያ ዳር ቆሞ መካሪ መሆን ሳይሆን ወደ መሃል ዘልቆ ተግባሪ መሆን ይጠይቀናል፡፡ በእናት ሃገራችን ምድር እንደዜጋ ትርጉም-አዘል ድርሻችንን ከተወጣን ሃገርን ማቅናት እንደሚቻል አምናለሁ፡፡ ደግሞም ይቻላል፡፡
ስለ አቶ አብይ ኤፍሬም የቅርብ ሰዎቻቸው የሰጡት አስተ ያየት
ወ/ሮ ትዕግስት ምስጋናው ~ ባለቤት
አባ ብየ የምጠራው ባለቤቴን የስራ አለቃየ ሆኖ ነው ያወኩት። በስራ ላይ በእጅጉ ኮስታራ ስለነበር ትውውቃችን እዚህ የሚደርስ አይመስልም ነበር። የኋላ ኋላ ተግባቦታችን እየጠነከረ ጥሩ የሚባል ጓደኝነት ፈጠርን። በጊዜ ሂደትም ግንኙነታችን ወደ ፍቅር ተቀይሮ ለትዳር በቃን ።
አብይ ስለ ትዳር የነበረኝን የተወሳሰበ አመለካከት እንድቀይር ያስቻለኝ ባሌ ነው። ኑሮን ቀለል ባለ የህይወት መርህ እንድንመራ፤ የልጆቻችን የወደፊት እጣፈንታ በእኛ ዘላቂ ብርታት ላይ እንደሚመሰረት ሰርክ የሚተጋ ጠንካራ አጋሬ ነው። ባጭሩ አብይ የመውደዴ እና የአክብሮትን ጥግ ያየሁበት ለኔ ባለቤቴ፣ ለልጆቼ ደግሞ መልካም አባት ነው። ስኬታማ የስራ ህይወት እንዲኖረው ከልብ እመኝለታለሁ።
አብይን ከ10 አመት በላይ አውቀዋለሁ:: ለኔ እና ለብዙዎች የማውቃቸው ታማኝ ወዳጅ፣ መሪ፣ አማካሪ እና አርአያ ነው።
በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን የማስተርስ ትምህርት እየተማርን ነበር የተገናኘነው። እያንዳንዱን ኮርስ ባህሪ ጠንቅቆ በመረዳት እና በየደረጃው የበለጠ ለመማር ያለውን ጉጉት ከአብይ ብዙ ተምሬያለሁ።
በወቅቱ ዕውቀትን እና ክህሎትን ለማዳበር ባለው ብርቱ ፍላጎቱ አብረውን የነበሩ ተማሪዎቹን እና አስተማሪዎች ጭምር አስደንቆናል።
በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት በቢሮው ለሁለት ወራት በኢንተርንሺፕ ፕሮግራም በተለማመድኩበት ወቅት ንድፈ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመቀየር ያለውን ችሎታ በሚገባ አስተውያለሁ።
ሁሌም እያነበበ ያለውን አዲስ መጽሃፍ እና ምን እንዳስደነቀው እየነገረን የውይይት ሃሳቦች እየመዘዘ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያጋራን ነበር።
በሚደንቅ አግባብ የአመራር ልምምዶችን በንባቦች እያስደገፈ ክህሎታችንን እንድናጎለብት ያግዘን ነበር።
መጽሐፎች የእርሱ እውነተኛ ጓደኞች ናቸው ማለት እችላለሁ። እንዲሁም የአመራር ጥበቡን እና የሙያ ብስለቱን ያሳደገው በንባብ መሆኑን በእርግጠኝነት መመስከር እችላለሁ።
የአብይ የተግባቦት ችሎታ በፅሁፍም ሆነ በንግግር የፈለገውን መልዕክት በጥራት እና ጥበባዊ በሆነ ስልት ለተደራሲያን ማድረስ ይችልበታል።
የግል ተግባቦት ብቃቱ ማንነቱን ሊገልጽ ይችላል። በኔ እይታ ረዘም ላሉ ዓመታት ውጤታማ የህዝብ ግንኙነት በተግባር የተፈተነ ልምዱ አሁን ለደረሰበት ትልቅ የስራ ሃላፊነት እንዳበቃው መገመት አያዳግትም።
አንድ አመራር የሚፈተነው በስራ እና በተዛማጅ አውዶች ልዩነትን መፍጠር እና ሌሎችን በተጨባጭ ከፍ ማድረግ ሲችል እንደሆነ ከአብይ ጋር በነበረኝ የልምምድ ወራት አረጋግጫለሁ።
በዙሪያው ለነበሩ ባለሙያዎች ዘርፈ ብዙ ክፍተት በመሙላት ለተልዕኮ አሳምኖ የማዘጋጀት አቅም እኔ የማደንቀው አመራር ነው።
በግል ትዝብቴ በማንኛውም ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ የአለቃነት ስሜት ተሰምቶት አያውቅም። ሰዋዊ ባህሪው እጅግ የጎላ በመሆኑ ትንሹንም ትልቁንም በእኩልነት እና በአገልጋይነት ስሜት የስራ አጋር የማድረግ ተሰጥዖ ከሌሎች ልዩ ያደርገዋል።
ብዙዎች በአብይ አካባቢ ቀርበው ካስተዋሉ በቋንቋ ብቃቱ የስነ-ጽሁፍ ውጤቶቹን አለማድነቅ አይችሉም። የቋንቋ አጠቃቀም እና አገላለፅ ከፍታው በዕለት ተለት ስራዎቹ ላይ በስፋት ይንፀባረቃሉ።
ምናልባት ብዙዎች አያውቁም ብዬ ማስበው የግጥም እና የሙዚቃ ድርሰት ስራዎቹን ይመስለኛል። የአብይ ጅምር ጥረቶቹን በማየቴ ወደፊት ለተደራሲያን የሚደርሱበት መንገድ እንደሚፈጠር እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ።
አብይ በሂደት ዓለምአቀፋዊ ግንዛቤው እና ተሳትፎውን እያጎለበተ በመምጣቱ ከፊትለፊት ትልቅ ዕድል እንዳለው ይታየኛል።
በመጨረሻ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጠናዊ አዝማሚያዎችን በመከታተል በትንታኔ ላይ የተመሰረተ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂን የማሳደግ ተስፋው ሰፊ በመሆኑ አብይ ባካበተው የደረጀ ልምድ ህዝብ እና ሃገርን የበለጠ እንደሚያግዝ እተማመናለሁ።
ወ/ሪት ትርሲት ይትባረክ - ወ/ት ትርሲት ይትባረክ /ጂግጂጋ ዩኒቨርስቲ/
2 . አቶ አባይነህ ጥላሁን፣ /የቲቪ ጋዜጠኛ/ ስለ አቶ አቢይ
አብይ ጋር ትውውቃችን የሚጀምረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ዲግሪ ስንማር 1998 ዓ.ም ነው፡፡ በጊዜው አብይ "ሰቃይ" የሚባል ተማሪ ሲሆን ለታናናሾቹ የተማረባቸውን የተለያዩ ኮርስ ማቴርያሎችን ይሰጠን ነበር፡፡
በአጋጣሚ በ2002 ዓ.ም ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አብይ በሃላፊነት በሚመራው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ውስጥ ጀማሪ ባለሙያ ሆኘ ተቀጥሬ አብሬው የመስራት እድል አገኘሁ፡፡
በተቋም ደረጃ አብይ ተወዳጅ እና ልዩነት ፈጣሪ አመራር የነበረ ሲሆን ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች መካከል ሙያውን ጠንቅቆ ማወቁ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴው የጎላ መሆኑ በልዩነት አስታውሰዋለሁ።
የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚስቴር ተቋማዊ ህልውና እና እንቅስቃሴ በህዝብ ዘንድ ጎልቶ ለመታወቅ የበቃው በአብይ የኮሚኒኬሽን አመራር ዘመን እንደሆነ በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡
በተቋም አስተዳደር ብቃቱ፣ ከሚዲያ ጋር ባለው ጠንካራ የስራ ግንኙነት፣ ሃገር አቀፍ ኩነቶችን በመምራት፣ በግለሰባዊ ሰናይ ምግባሩ እንዲሁ ሰርቶ በማሰራት ብቃቱ ረገድ በግሌ ግልፅ እና በጎ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል።
አብይ ከባለሙያዎች እና ከአመራሮች ጋር የነበረው ግንኙነት ሲበዛ ጤናማ እና የማይጎድል ትህትና የተላበሰ ቢሆንም በመደበኛ የተግባር ዑደት ውስጥ ውሳኔ የመስጠት ድፍረቱ እና ብቃቱ ደስ ያሰኘኝ ነበር።
አብይ ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ስታዘብ በትክክል የአቋም እና የመርህ ሰው መሆኑን አረጋግጦልኛል።
በአብይ አመራር ስር ባለሙያ ሆኜ በመስራቴ በግሌ ለነበረኝ የዕውቀት፣ የሙያና የህይወት ክህሎት እንዲሁም የማህበራዊ ግንኙነት ልምምድ ዓይኔን እንድገልጥ እና ራሴን እንድፈትሽ ያገዘኝ ታላቅ ወንድሜ ነው።
በስራ ቆይታዬ በመደበኛ የስራ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት ከሚሰጠን ገንቢ ምክሮች መካከል ከውስጤ ማይጠፋውን እስከዛሬ ድረስ አስታውሳለሁ።
"ማናችንም በኮሙኒኬሽን በቅተን የተወለድን አይደለንም፤ መቼም ቢሆን በአለቃ ቀጭን ትዕዛዝ ወይም በጎ ቸርነት የባለሙያ ብቃት ተገንብቶ አያውቅም። እያንዳንዱን ኩነት ስራችን ብቻ ሳይሆን የኮሙኒኬሽን ሙያ ብቃት ማጎልበቻ መድረካችን መሆኑን መረዳት ይገባናል፤ Please Be Wise።" ይል ነበር።
ጠንካራ የኮሙኒኬሽን መሪ የሚፈጠረው በተግባር ልምምድ መሆኑን በማስረገጥ የሰርክ የተግባቦት ስራችን የወር ደሞዝ የምንጠብቅበት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዷ እርምጃ አቅማችንን ለማሳደግ የምንጠቀምበት መድረክ እንደሆነ በውል አስገንዝቦናል።
አብይ ባለው የሰከነ አስተውሎት እና አዳጊ ብቃት በሂደት ካካበተው ልምድ ጋር ተዳምሮ ሃገራዊ አበርክቶዎቹ በቀጣይ እንደሚሰፉ ጥርጥር የለኝም።
ሁሌም ቢሆን አክባሪው እና የሙያ ደቀመዝሙሩ በመሆኔ እኮራለሁ። በመጨረሻም ስኬታማ የስራ እና የቤተሰብ ህይወት እንዲኖረው እመኝለታለሁ፡፡
ዶ/ር አስናቀ ተስፋዬ / አአዩ/ ( ከልጅነት ጓደኛ) ስለ አቶ አብይ
አቶ አብይ ተማሪ ሆነን ጀምሮ ለሰዎች የሚያዝንና ትሁት ነበር ። በዛ በልጅነት እድሜ የማይጠበቁ ለሌሎች ሰዎች መቆርቆር ሌሎችን ሰዎች የማገዝ ጠባይ የተቸረው ነበር ። ለዚህም ማሳያ የማነሳው ሌሎች ከእድሜው አነስ ያሉ ልጆችን በማስጠናት ያግዝ ነበር ።
በባህሪው ከልጅነታችን ጀምሮ እስካሁንም አብሮት የዘለቀው :- ጥንቁቅ ከሰው ተግባቢ በአለባበስም እራሱን ለሚፈለገው ሥራና ጉዳይ ዝግጁ አርጎ ጥንቅቅ ብሎ የሚገኝ ነው ። ከልጅነቱ የነበረው ይሔ ባህሪው ይመስለኛል በተገኘበት እና በደረሰበት ቦታ ሁሉ የሚፈለገውን ሆኖ ነው የሚገኘው ። ሙሉ ነው ማለት እችላለሁ በብዙ ነገር
ተማሪ እያለን ጀምሮ የስነ - ጽሁፍ ፍቅር ነበረው ።
ትምህርት ቤታችንና ትምህርት ቤቶች በሚያዘጋጁት መድረክ ላይ ግጥሞች መጣጥፎች እና ምክር አዘል አነቃቂ ንግግሮችን ያቀርብ ነበር ። ወደ ጋዜጠኝነትና የኮሚውኒኬሽን ሞያ በኋላ ያዘነበለው እንዳውም ለዛ ይመስለኛል
አዲስ ነገር ለማወቅ ለመለወጥ ያለው ዝግጁነት ሁሌም ይደንቀኛል ። ከልጅነቱ ጀምሮ እንደዚህ ነው ። በአንድ ወቅት ሳገኘው ሁለት ዲግሪ ይማር ነበር ። እንደጨረሰ ወዲያው ነው ሁለተኛ ዲግሪውን የጀመረው ። ሥራም ላይ እንደዛ ነው የተለያዩ ተቋማት ላይ በነበረው ኃላፊነት ሥራን በቅልጥፍና።ተደራራቢ ጫናዎችን በብቃት ስለሚወጣ ነው አሁን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የኮሚውኒኬሽን ከፍተኛ ፕሮቶኮል ኃላፊነት ደረጃ የደረሰው።
አቶ አብይ ኤፍሬም የፖለቲካ ሰው የሚዲያ ባለሙያ እና ቤተሰቦቹን ቤተሰቡንና ጓደኞቹን አብሯደጎቹን የሚወድ የቤተሰብ ሰው ነው።
ዶ/ር አስናቀ ተስፋዬ / አአዩ/ ( ከልጅነት ጓደኛ) ስለ አቶ አብይ
የትናንቱ አብይ ከቤተሰቡ ጋር እኔ ተወልጄ ወዳደኩበት መቂ ከተማ የመጣው ገና በለጋ ዕድሜው ነበር። ከልጅነት እስከእውቀት የነበረውን የህይወት ጉዞ በቅርበት የመታዘብ ዕድል ስለነበረኝ ስለአብይ የሚወሱ ትውስታዎችን ማጋራት በመቻሌ ከልብ ደስተኛ ነኝ።
አብይ በጠባይ ረገድ ቀለል ያለ፣ ተግባቢና ትሁት ሰው ነው፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ
ከነበሩት የክፍል ተማሪዎች በዕድሜ ትንሹ አብይ ሲሆን፤ በብዛት ውሎው ግን ከታላላቆቹ ጋር ነበር፡፡ በዘመኑ በታላላቆቹም ዘንድ ተወዳጅ እና ተደማጭ እንደነበር ሳስብ ሁሌም ይደንቀኛል።
በልጅነት አእምሮ የአብይ ጉልህ መለያዎቹ መካከል የማልረሳው ከእኩዮቹም የቀደመ አስተዋይ ልጅ ስለነበር በተለይ በንጸህናው አጠባበቅ፣ በመልካም ስነ ምግባሩ እንዲሁም ጨዋታ አዋቂነቱ ለራሴ መንፈሳዊ ቅናት ይጭሩብኝ ነበር
በትምህርት አቀባበል እና ትጋት ፈጣን በመሆኑ በመቂ ካቶሊክ ት/ቤት መምህራን እና ተማሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ሲሆን በውጤቱም የከፍተኛ ማዕረግ ተማሪ ነበር።
በት/ቤት ውስጥ በሚኒ ሚዲያ እና ስነ~ፅሁፍ ክበብ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ የነበረው ሲሆን በስነፅሁፋዊ ስራዎች ብቃቱም በየመድረኩ ከታላላቆቹ ጋር ተወዳድሮ ማሸነፍ በመቻሉ በተደጋጋሚ ሲሸለም አስታውሳለሁ።
በዛ ዘመን የነበረው ንቁ ተሳትፎ የፈጠረው ዝንባሌው ይመስለኛል ዛሬ ላይ ወደ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት የሙያ ዘርፍ እንዲያቀላቀል ዝንባሌው የመራውው፡፡
በለጋ እድሜያችን ብዙዎቻችን ጋር የማይስተዋል ነገር ግን በልጅነቱ አብይ ላይ በልዩነት የሚስተዋል አንድ ነገር ላንሳ።
ሁላችንም በሚባል ደረጃ በልጅነት የዕድሜ ዘመን ልብስ ተኩሶ መልበስ ይቅርና፣ በወላጆቻችን አስተኩሰን የመልበስ ግንዛቤውም ሆነ ልምምዱ አልነበረንም።
አብይ ግን . . . ከልጅነቱ ጀምሮ በአለባበሱ እና በንፅህና ጉዳይ ሲበዛ ጠንቃቃ ሲሆን የተማሪ ዩኒፎርሙ ሁሌ እንደተተኮሰ እንዲሁም ጫማው በቀለም ተወልውሎ እያብረቀረቀ ሽክ እንዳለ ነበር ት/ቤት የሚመጣው።
ያደግንባት መቂ ከተማ አቧራ የሚበዛባት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የአብይን የአለባበስ ጥንቃቄ እና ንፅህና አጠባበቅ በወቅቱ ለምንታዘብ የቅርብ ወዳጆቹ በጣም አግራሞት ይፈጥርብን ነበር።
በዚህ የቀደመ ልዩ ሰብዕናው በመቂ ማህበረሰብም ሆነ በትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎች ዘንድ እጅግ የሚወደድና በምሳሌነት የሚጠቀስ ከፍ ያለ ሰብዕና ባለቤት ነው።
በዘመናችን መቂ ካፈራቻቸው እና ለሀገር ከፍተኛ አስተዋዕጾ እያበረከቱ ካሉት ወጣት ምሁራን መካከል በግምባር ቀደም የሚጠቀስ አንዱ አብሮ አደጌ እና ጓደኛዬ አብይ ኤፍሬም ነው ~ ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም።
አብይ ገና ከዚህ በላይ ብዙ ርቀት የሚጓዝ ሁለገብ የተግባቦት፣ የፖለቲካ፣ የልማትና ማህበራዊ ዘርፍ አቅም ያለው ሰው በመሆኑ፤ ወደፊት ሃገር እና ወገኑን በተሻለ መልኩ እንደሚያገለግል ተስፋ አደርጋለሁ፤ ደግሞም አምናለሁ፡፡
እግዚያብሔር ይርዳህ!
ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ስለ አቶ አቢይ
ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች እና ከማስተማር ላይ የመጡ በእድሜ ከሚበልጡት ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ለትምህርት ሲመጣ ነው የማወቀው።
ውጤታማና ጎበዝ ልጅ ነበር በትምህርት ።ከዛ ጊዜ ጀምሮም ይመስለኛል እስካሁን በዕድሜ ከሚበልጡት ጋር አብሮ በብቃት መሥራት የተለማመደው።
ለኔ አብይ ስርአት ያለውና እጅግ ሲበዛ ምስጉን የተባለ ጸባይ ባለቤት ነው ።
ጎበዝ ታታሪ እና አዳዲስ እውቀቶችን ናፋቂ የሆነው አብይ ኤፍሬም ትምህርቱን በከፍተኛ ማእረግ ነው የተመረቀው ። አሁን የደረሰበትን የሥራ ልምድ እና የእውቀት ከፍታን ሳይ ...መምህሩ ስለነበርኩ ና ተማሪዬ ስለነበረ እኮራለሁ፡፡
አቶ ታየ ሙሉጌታ የኢኖሼሽን እና ቴክኖሎጂ የሚኒስትሩ አማካሪ ስለ አቶ አቢይ
ከትውውቅ ግዜ እስከ አሁን እንደ ቅርብ የሙያ ዘርፋ ተከታታይነቴና አንተን በመመልከት አግባብ ሶስት ዋና ዋና መገለጫዎች ላይ ጉልህ ልዮነቶች ተመልክቻለሁ።
1.ለሐላፊነት የመታመን ተሰጥኦ
ከ16 አመት በፊት በነበረኝ የመጀመሪያ የትውውቅ አጋጣሚ አዲስ የኮንስትራክሽን ዘርፍ መፅሔት ህትመትን በዋና አዘጋጅነት ለመምራት በቀረበበት አጋጣሚ ለጀማሪ ሙያተኛ ያልተለመደ እርጋታ :በስራ አመራር ኢዲቶርያል አማካሪዎች የተሰጡ ሙያዊ ምክሮችን መጥጦ የሚያስቀር ጥልቅ አድማጭነት :እንዲሁም ትጉ የአፈፃፀምና የክትትል ስራዎች ትጋቱ አዲስ ነገር ለመትከል ለሚተጋ ሀይል ወጣቱ አብይ ገና ከጠዋቱ ለሀላፊነት የሚታመን ትከሻ እንደነበረው በግሌ ያረጋገጠልኝ ሁነኛ የትውውቅ አጋጣሚ ነበር።
2.ተራማጅ ቁመናን የተላበሰ (progressive posturing )
በአብይ ኤፍሬም የሙያ እድገት ሒደት እንደቅርብ ታዛቢ ጎልቶ የሚታየኝ በተግባቦት ሐላፊነቱ ከአመት ወደ አመት እያደገ የመጣ እና ሙያውን ተመርቆበት ያቆመ ሳይሆን ጥማት እየገፋው ልምምዶቹንና ከፍተኛ እሴት ጨማሪ አጋጣሚዎቹን በፍጥነት ለሙያ እድገቱ በቀጥታ ማዋል በመቻሉ በሙያው አሁንም ድረስ እያደገ ያለ ሰው እንዲሆን አስችሎታል።
በእኔ አስተያየት በተለይ በአገራችን የተግባቦት ሙያ ምስለ ገፅ ውስጥ ሙያተኞች የሚያጋጥማቸው ችግር በተለይ በሚዲያና በማህበራዊ ትስስር ገፆች ባላቸው ቀጥተኛ የተፅእኖ ውጤቶች ተጠልፈው የቆሙና አዳዲስ ሙያዊ ልምምዶች ውስጥ ለመግባት ፈተና አጋጥሟቸው እድገታቸው የተገታ በስም ብቻ የቆሙ በመሆናቸው ለዘርፋ ወይም ለሚያገለግሉት ተቋምና ህዝብ በደረጃና በይዘት ዝቅተኛ አገልግሎት ብቻ በመስጠት የተወረኑ ናቸው።
በዚህ ረገድ አብይ ባለፋት አመታት በተለየ የተግባቦት ዘርፍ,political communication speciality ከመጋረጃ ፊትም ሆነ ጀርባም የሚሰራቸው ስራዎቹ በሚያገለግልባቸው ከፍተኛ ቢሮዎች ውስጥ በቅርብ አመታት የተገኙ ጠንካራ ውጤቶች ምስክሮች ናቸው።
በተለይ ባለፋት አራት አመታት ባጋጠሙ አገራዊ ቀውሶች ውስጥ የቀውስ ተግባቦት ስራዎችን Applied Crisis Communication sበተገቢው ሁኔታ በመምራት አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ሳስብ በእነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሙያውን ማሳደግ መቀጠሉን ያረጋግጥልኛል።
መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ማአከል አቋም የሚንጸባረቅበትነው፡፡ ከላይ ታሪካቸውየተነበበው ሰው ለምን ታሪካቸውን እንደሰራነው እና የእኛንም አጭር ዳሰሳዊ ምልከታ በአቋም የምናስቀምጥበት ነው፡፡
ይህን ታሪክ እንድንሰራ ሙሉ ፈቃደኝነታቸውን የሰጡን አቶ አብይ በመንግስ ት የስራ ሃላፊነት ያሳለፉና አሁንም እያገለገሉ ያሉ ሰው ናቸው፡፡ በአጭር አገላለጽ ከፍተኛ መሪዎቻችን ግለ-ታሪካቸው ምን ይመስላል? የሚኒስተር አማካሪዎች በየት መንገድ ያለፉ ናቸው? የሚለውን በወጉ እንድናውቅ የአቶ አብይ ታሪክ ጥሩ ምስል ይሰጠናል፡፡ የእኛ ዋና ግብ የሰዎችን ታሪክ እንዳለ ማቅረብ ቢሆንም ባቀረብናቸው ሰዎች ላይ ደግሞ የተጠቀለለ ሀሳብ መስጠት እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሀሳባችን በተለይ ሌሎች በመንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች እኔም እኮ ለሀገሬ ሰርቻለሁ ፤ በህይወት እያለሁ ታሪኬ በ10 ገጽ ሊሰነድ ይችላል የሚል መነሳሳት የሚፈጥር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ታሪካቸውን የምናቀርብላቸው ሰዎች ጽሁፉን ፖስት እስካደረግንበት ቀን ድረስ ያለውን አስተዋጽኦዋቸውን በማየት እውቅና ለመስጠትም እናስባለን፡፡
1ኛ አቶ አብይ በኮሚኒኬሽን ሙያቸው በተለይ ከ12 አመት በፊት ብዙዎች ትጋታቸውን መስክረዋል፡፡
2ኛ አቶ አብይ በስራ ሂደት በተከታታይ በሚያሳዩት ከፍተኛ የመፈፀም ብቃት እና ሙያቸውን በአዳጊ ዕውቀት ለማጀብ በሚያደርጉት ያልተቋረጠ ጥረት የመንግስት የስራ ሃላፊነትን መረከብ ችለዋል።
3ኛ ለውሳኔም በጣም የሚሆኑ ፤ በራስ መተማመናቸው የጎላ ሰው ናቸው፡፡
4ኛ ለመደበኛ ትምህርት ያላቸው ጉጉትና ከሁሉም ነገር ለመማር የሚያሳዩት ታላቅ ተነሳሽነት ገራሚ ነው፡፡
እንደ አቶ አቢይ አይነት ሰዎች በቅርብ ሰዎቻቸው እንደተመሰከረው የሚያኮሩ ናቸው፡፡ የሚያኮሩ ሰዎች ደግሞ ለዊኪፒዲያ ይመጥናሉ፡፡
ይመጥናሉ ብቻ ሳይሆን ትውልድ ይማርባቸዋል፡፡ እስከመቼ በፈረንጆች ምሳሌ እንኖራለን፡፡ ኢትዮጵያ በየሙያው የሚሮጡ ግን ልታይ የማይሉ ልጆች አፍርታለች፡፡ ብዙ ሰርተው ገና ይቀረኛል ወይም ይህን ሳሳካ ታሪኬ ይሰነዳል የሚሉ ብርቱዎችን ይዛ ሳታጎላቸው/.ጉልህ ሳታደርጋቸው / በከፍታ ማማ ላይ ሳታኖራቸው ቆይታለች፡፡ አሁን ግን ሁሉ ታሪክ አለው ፤ የሰራ ደግሞ የበለጠ ታሪክ አለው ብለን ስንነሳ እንደ አቶ አብይ አይነት ሰዎች ታሪካቸውን እንድንሰራ ይፈቅዱልን ዘንድ
እንጠይቃለን፡፡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ግለ-ታሪ ክ በሚለው ዘርፍ ስንቱ አስተማሪ ታሪክ ይኖረው ይሆን? ሲጻፍ ወይም በቃል ሲነገር ብቻ ነው የሚታወቀው፡፡ እኛ ግን አዲሱ ትውልድ ወይም ከ50 አመት በኋላ የሚተካን ትውልድ ሲመጣ ማነው አቢይ ኤፍሬም ? ምን ሰርቶ ነበር? ብሎ ቢጠይቀን ይህን በ4293 ቃላት የተሰነደ አጭር ግለ-ታሪክ እናቀብለዋለን፡፡
አስተዋጽኦ ፣ /ይህ ግለ-ታሪክ እንዲሰራ ባለታሪኩ ይገባቸዋል ብለው ሀሳብ የሰጡን የተወዳጅ ሚድያ ዊኪፒዲያ ቦርድ አባላት ጥበቡ በለጠ ፤ አይናለም ሀድራንና ታምራት ሀይሉን ማመስገን እንወዳለን፡፡ የዚህ ግለ-ታሪክ የምርምር ፤ የቃለ-መጠይቅ እና የመዝጊያ ሀሳብ ስነዳ በጋዜጠኛ ጸጋ ታሪኩና በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 19 2014 ፤ ከሌሊቱ 8 ሰአት በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ማእከል የፌስ ቡክ ገጽ እና በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ አስፈላጊወ ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
አስተዋጽኦ ...... ጸጋ ታሪኩ ባለፉት 12 አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ያሳለፈች፤ ከ1000 በላይ የቲቪና የሬድዮ ፕሮግራሞችን አየር ላይ ያዋለች በርካታ የሀገሪቱን ክፍል ዞራ ያየች ብርቱ ጋዜጠኛ ነች፡፡ በ2013 የጣራ አዋርድ እጩ የነበረች ሲሆን በአሁኑ ሰአት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቲቪ ዘርፍ ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን ታገለግላለች፡፡ በተጨማሪም በበጎፈቃደኝነት በተወዳጅ ዊኪፒዲያ በዋና የዊኪፒዲያ አማካሪነት ታገለግላለች፡፡ ጸጋ በማህበራዊ ሚድያ ላይ መጣጥፎቿም ትታወቃለች፡፡
Wow bexam des yemil tarik new. Bizu neger lewexatoch yastemral. Abiyn enem aqewalehu Tihut, sew akbarina tegbabi new.
ምላሽ ይስጡሰርዝ