91. የማማ በሰማይና የቶፓዝ ተርጓሚ

   ጌታነህ አንተነህ ካሣ -Getaneh Anteneh Kassa 

የማይዘነጉ ባለውለታዎች››  ለወጣቱ ትውልድ  አርአያ የሚሆኑና መንገድ አመላካች ናቸው

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1970ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡  ይህ አጭር ግለ-ታሪክ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አቶ ጌታነህ አንተነህ ካሳ በትርጉም እና በድርሰት ስራቸው በተለይ በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዝኛ ክህሎታቸው ይታወቃሉ፡፡ ማማ በሰማይ እና ቶፓዝ ቴአትር የሚጠቀሱ ስራዎቻቸው ናቸው፡፡ አቶ ጌታነህ ለእናት ሀገራቸው ካበረከቱት አንጻር አንቱታ ቢያንሳቸውም ራሳቸው በፈቀዱት መሰረት አንተ በሚል በአክብሮት እና በቀረቤታ ታሪካቸው እናቀርባለን፡፡    

1. ትውልድና ትምህርት

በአማራ ክልል፣ በምዕራብ ጐጃም ዞን፣ በደንበጫ ወረዳ፣ በደንበጫ ከተማ፣ መስከረም 19 ቀን፣ 1946 ዓ.ም. ተወለደ፡፡ በዚያው ከተማ እስከ 8ኛ ክፍል ትምህረቱን ተከታትሎ ሲያበቃ፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በምሥራቅ ጐጃም ዞን፣ በጎዛምን ወረዳ፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ፣ በንጉሥ ተክለ- ሃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት (በኋላ ድብዛ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት) እስከ 11ኛ ክፍል ተከታተለ፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የልዑል በዕደ- ማርያም ላቦራቶሪ ት/ቤት (Prince Bede Mariam Laboratory School) በማጠናቀቅ በ1964 ዓ.ም. በ4 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በፊዚካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል በ1ኛ ዓመት ተማሪነት ተመዘገበ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ትምህርት መስክ አልገፋበትም፤ በ1965 ዓ.ም. በፈረንሳይኛ ማሠልጠኛ ኮሌጅ (Ecole Normale Supérieure) ገባና የ4 ዓመታት የፈረንሳይኛ ቋንቋ፣ የአማርኛ ቋንቋ እንዲሁም የቋንቋ ማስተማር ጥበብ (Pedagogy) በመከታተል በ1970 ዓ.ም. በቢ.ኤ. ዲግሪ ተመረቀ፡፡ በመሃሉ በዕድገት በሕብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ ተሳትፏል፡፡ በ1993 ዓ.ም. Open University of Business School (UK) እየተዘጋጀ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ አማካይነት ይሰጥ የነበረውን Professional Diploma in Business Management ኣግኝቷል፡፡

2.ሥራ

ሀ. መምህር - በመስከረም 1971 ዓ.ም. በምዕራብ ጐጃም ዞን፣ በባሕር ዳር ከተማ በአፄ ሠርፀ ድንግል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የፈረንሣይኛና የአማርኛ ቋንቋዎች መምህር በመሆን ሥራ ጀመረ፡፡ ሆኖም በዚያው ዓመት አጋማሽ የፈረንሣይኛ ቋንቋ ትምህርት ከሥርዓተ ትምህርቱ እንዲወጣ ስለተደረገ፣ ሙሉ በሙሉ ወደአማርኛ መምህርነቱ ተጠቃለለ፡፡

ለ. ርዕሰ- መምህር - በ1974 ዓ.ም. አጋማሽ በምሥራቅ ጐጃም ዞን፣ በደጀን ከተማ፣ በጐጃም በር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በርዕሰ መምህርነት ተመደበ፤ በ1976 ዓ.ም. በምዕራብ ጐጃም ዞን በፍኖተ ሠላም ከተማ ወደሚገኘው ወደዳሞት አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውሮ የርዕሰ- መምህርነት ሥራውን ቀጠለ፡፡

ሐ. የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር - በ1977 ዓ.ም. ወደሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት ተዛውሮ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ሆነ፡፡ በዚሁ መርሀ ግብር በ1978 ዓ.ም. ወደፈረንሣይ አገር ተልኮ፡-

1 በሶርቦን ዩኒቨርሲቲ (Université de la Sorbonne, Paris III) ቋንቋን ላዋቆች በማስተማር ጥበብ - Certificat de Spécialisation፣

2 በ Centre de Recherche et d’Etudes pour la Diffusion du Français (CREDIF)፣ Rouen (France) የፈረንሣይኛ መምህርነት ከፍተኛ ሠርቲፊኬት ፣

3 በ Centre International d’Etudes Pédagogiques de Sèvres (Paris, France) የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት ታዳጊዎችን በተለይ የንባብ ክሕሎት የማሳደግን ልዩ ትምህርት ቀስሞ ተመለሰ፡፡

በሊሴ ገ/ማርያም ከሚሠራው ሥራ በተጓዳኝና ከዚያም በኋላ በአዲስ አበባው Alliance Ethio-Française እስከ1987 ዓም. ድረስ በፈረንሣይኛ መምህርነት ሠራ፡፡ በጥር 1980 ዓ.ም በቀድሞው International Livestock Centre for Africa (ILCA), ባሁኑ International Livestock Research Institute (ILRI) በትርጉም ክፍሉ አሐድ ውስጥ ተቀጥሮ እስከ ሰኔ 1985 ዓ.ም. ድረስ ሠራ፡፡ በሐምሌ ወር 1985 ዓ.ም. የAlliance Ethio-Française ትምህርት ክፍል አስተባባሪ በመሆን እየሠራ ሳለ ለተጨማሪ የሥነ ትምህርት ሥልጠና ዳግመኛ ወደፈረንሣይ አገር ለሁለት ወራት ተላከ፡፡ በዚያ ቆይታው ወቅትም በፈረንሣይ ት/ሚኒስቴር በ Bureau d’Etudes pour les Langues et les Cultures (BELC) መምህራንን በማሠልጠንና በቋንቋ ትምህርት ቅበላ ንድፈ ሐሳብ ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት ለማድረግ ዕድል ኣገኘ፡፡

4. በፈረንሣይ ሥልጠናውን አጠናቆ እንደተመለሰ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የቋንቋ ትምህርት ክፍል የፈረንሣይኛው ዘርፍ አስተባባሪ በመሆን የመቀጠር ዕድል አገኘና የዓለም አቀፉ ሲቪል ሰርቪስ አባል ሆነ፡፡ በኮሚሽኑ ከቋንቋ ክፍል አስተባባሪነቱ በተጨማሪ የሥራ አፈጻጸም ብቃት ማበልጸጊያና ምዘና ክፍል ተጠሪ (ፎካል ፖይንት) እንዲሁም የሥራ ዕድልን በማሳደግ (Career Develoment) ዘርፍ አሠልጣኝና ኮች (Coach) በመሆን እስከ መስከረም 2008 ዓ.ም. ድረስ ሲሠራ ቆይቶ በ62 ዓመት ዕድሜው ጡረታ ወጣ፡፡

5. ትርጉም፣ ድርሰት - አቶ ጌታነህ በILRI የትርጉም ሥራ አሐድ በሠራባቸው አምስት ተኩል ዓመታት ራሱ ተርጓሚ ያልነበረ ቢሆንም፣ ለተርጓሚዎቹ ቴክኒካዊ ቃላትን (አቻዎችን) እየፈለገ በማቅረብ ፈታኝና አታካች ሥራ በተሰማራበት ጊዜ ስለአተረጓጎም ጥበብም እጅግ ከፍተኛ ትምህርት ገብይቷል፡፡ በILRI ይሠራ በነበረበት ወቅትም ቶፓዝ የተባለውን የማርሴል ፓኞልን ተውኔት የመጀመሪያ ረቂቅ ትርጉም ሠራ፡፡ በዚሁ የትርጉም ሥራው በመግፋትም በርከት ያሉ ሥነ ጽሑፋዊና ጥናታዊ ሥራዎችን ተርጉሞ የተወሰኑትን ለመድረክም፣ ለሕትመትም ለማብቃት ቻለ፡፡

ባሁኑ ወቅት አቶ ጌታነህ በትርጉም ሥራው ቀጥሎበታል፡፡ በሠንጠረዦቹ ላይ የተመለከቱትን መጽሐፎችና ሠነዶች በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ (ካንዱ ወደሌላው) ተርጉሞ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ወደፊት አቅም በፈቀደ ጊዜ ለሕትመት የማብቃት፣ ሌሎችንም ሥራዎች የመጨመር ተስፋ አለው፡፡

አቶ ጌታነህ አንተነህ የ4 ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት፣ የሦስት ሴቶችና የሁለት ወንዶች፣ በድምሩ የአምስት ልጆች አያት ናቸው፡፡

አድራሻ፡- አዲስ አበባ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 7፣ የቤት ቁጥር 1537

ኢሜይል - 4getaneh@gmail.com

ስ.ቁ. - +251910017632

የመ.ሣ.ቁ - 60245








አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች