89. ማርታ ደጀኔ -Martha Dejene 

         የማትበገረው ማርታ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት አመታት  በታላቅ ጽናት ከሰሩት መሀል የአራት ኪሎዋ ማርታ ደጀኔ ትነሳለች፡፡ ማርታ ማናት?

   የልጅነት ጊዜና የትምህርት ሁኔታ

እዚሁ አዲስ አበባ ልዩ ስሙ “አራት ኪሎ”ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔ ገና የ2 ዓመት ህጻን እያለች ነው በፖሊዮ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ የሆነችው፡፡ ቤተሰቦቿ “ትድናለች”በሚል ብዙ ሙከራ ቢያደርጉላትም ሊሳካ አልቻለም፡፡ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ ከመንፈሳዊ እስከ የባዕድ አምልኮ ሁሉንም ሞክረውላታል፡፡ 

ለአካል ጉዳተኝነት በወቅቱ ይሰጥ የነበረው አመለካከት የተዛባ በመሆኑና የማርታ ቤተሰቦች እንድትድን ካላቸው ጉጉት የተነሳ በነበረው ውጣ ውረድ ማርታ ቶሎ ወደ ት/ቤት አልተቀላቀለችም፡፡ ነገር ግን ከልጅነቷ ጀምሮ ብልህ የነበረችው ማርታ እቤት ውስጥ ፊደል መቁጠር፣ መጻፍና ማንበብን ጠንቅቃ ለማወቅ ጊዜ አልፈጀባትም፡፡ የእህትና ወንድሞቿን መጻህፍትን በማንበብ ከወንድሞቿ ሁሉ ልቃ መገኘቷን የተመለከቱት ቤተሰቦቿ መጻህፍት እየገዙ ያቀርቡላት ነበር፡፡ሌላው ቀርቶ ዕቃ ሲገዛ የተጠቀለለበት ጋዜጣን እንኳ “ቆይ እሷ ትየው!”ይባልና ይቀመጥ ነበር፡፡ ት/ቤት ውለው ከሚመጡትና ክፍል ከሚቆጥሩት እህት ወንድሞቿ ማርታ በብዙ እጥፍ የተሻለ የመቀበል ፍጥነት ነበራት፡፡ አንዳንድ ጊዜም ወንድም እህቶቿ የቤት ሥራ ሲሰጣቸው የማርታን እገዛ የሚፈልጉበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ እ ሷም የመማር መብቷን ደጋግማ የመጠየቅ፣ ቤተሰቦቿም ድና እንደእኩዮቿ ውላ ትገባለች የሚለው ውጤት አልባ ድካማቸው ተስፋ ስላስቆረጣቸው ማርታ ት/ቤት እንድትገባ ውሳኔ ላይ የደረሱት፡፡በዚህ ላይ ደግሞ ማርታ የንቁ አዕምሮ ባለቤት መሆኗ ት/ቤት ብትገባ ደግሞ የበለጠ እንደሚሆን ሲያስቡት የባከነው ጊዜ ሳይቆጫቸው አልቀረም፡፡ እናም ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ እንድትጠቀም ሆኖ በአፄ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በዳግማዊ ሚኒሊክ ት/ቤት ተከታተለች፡፡









የሚዲያ ተሳትፎና የጋዜጠኝነት ጅማሮ

አካል ጉዳተኝነቷ እንደልብ አባሮሹንና ድብብቆሹን ከዕድሜ እኩዮቿ ጋር ሊያሳትፋት ባለመቻሉ ያላት አማራጭ በማንበብ ጊዜዋን ማሳለፍ ብቻ ነበር፡፡ በማንበብ ፍቅር ታንጻ ያደገችው ማርታ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ለገዳዲ እና ፋና ላይ የሚተላለፉ ዜናና ፕሮግራሞችን በትኩረት ከመከታተል ባሻገርም በጠቅላላ እውቀት ብርቱ ተሳታፊም ነበረች፡፡“ማርታ ደጀኔ ከ4ኪሎ”የሚለው ስም በብዙ የሬዲዮ አድማጮች ዘንድ ጎልቶ ታወቀ፡፡“ማን ትሆን?”የሚለውን የአድማጮችን ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ዘንድም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከታሜሶል ኮሚኒኬሽን ጋር በትብብር በሚያቀርበው የሐሙስ ማታ የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተወዳድራ በማሸነፍ ማንነቷን ለማስተዋወቅ ተጠቅማበታለች፡፡ ሁለተኛው ውድድር ላይ ስትሳተፍ ግን ማርታ ዓላማ ነበራት፡፡ 12ኛ ክፍል አጠናቅቃ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባትን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እያለች ለወራት ያለሥራ መቀመጥ አልፈለገችም፡፡ እናም የግል ጋዜጣ ጀምራ ለመስራት ፍላጎት አደረባት፤ ግን ገንዘብም ሆነ ሥራውን ለመስራት የሚያስችሏት ቁሳቁሶች አልነበራትም፡፡ ፈቃድ ለማግኘት ደግሞ በባንክ አካውንቷ ብር 10,000 የተሟላ ቢሮ ኮምፒውተርን ጨምሮ /በወቅቱ ኮምፒውተር ውድም ብርቅም ነበር/ ማሟላት ግዴታዋ ነበር፡፡ ገንዘቡን ከማይክሮ ፋይናንስ በብድር ስታገኝ፣ በጠቅላላ እውቀት ተሳትፎ ደግሞ ኮምፒውተሩን አሸንፋ የጋዜጣ ማሳተም ህልሟን እውን አደረገች፡፡ የጋዜጣውም ስም “እውን” ተባለና በሥነ-ጽሑፍ የምታውቃቸው ጓደኞቿን በማሰባሰብ በተከራየቻት አንዲት ጠባብ ቢሮ ውስጥ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ ነገር ግን የተበደረችውም ገንዘብ ሲያልቅ ‹‹እውን›› ጋዜጣ በዚያው ቆመች፡፡ የማርታ የጋዜጠኝነት ፍቅር ግን አልቀነሰም፤ ጥረቷንም አላቋረጠችም፡፡ የከፍተኛ ተቋም መግቢያ ውጤትም ይፋ ሆነና ማርታ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለች፡፡ የ2ኛ ዓመት ተማሪ እያለች በዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም ላይ ተወዳድራ በመግባት ለ4 ዓመታት በጋዜጠኝነት አገልግላለች፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋንም አገኘች፡፡

በወሊድ ምክንያት በዛሚ ኤፍ ኤም የነበራትን የጋዜጠኝነት ሥራዋን ብታቆምም ከቆይታ በኋላ “እውን የማስታወቂያ ሕትመትና ፕሮሞሽን ሥራ ድርጅት”ን በ2000 ዓ.ም በማቋቋም ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በአካል ጉዳተኝነት ላይ ትኩረት ያደረገ “ማዕዶት”የተሰኘ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለ5 ዓመታት ያህል ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ ከመደበኛ ፕሮግራሟ ባሻገር ሃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላትን የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት በመውሰድ ማስታወቂያ የሚያስነግሩና ስፖንሰሮችን በማሳተፍ አዝናኝ ፕሮግራሞችን በመሥራት ትታወቃለች፡፡ከፕሮግራሙ አዝናኝነት ባሻገር የአካል ጉዳተኝነትን ጉዳይ በማካተት ፕሮግራሙ እያዝናና የሚያስተምረበትን ይዘት /Format/ በመቅረፅ ረገድ ብርቱ ጥረት አድርጋለች፡፡ የአካል ጉዳተኞች ዘመናዊ ዳንስና ባህላዊ ውዝዋዜን በፕሮግራሙ መካከል በማስገባት አድማጭ ተመልካቹ ስለአካል ጉዳተኞች የተሻለ ዕይታ እንዲኖረው ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህም ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከተው በሃገራችን የአካል ጉዳተኞችን ውዝዋዜ በማሰልጠን ፈር ቀዳጅ የሆነው የዳንስ ባለሙያ (ኬሮግራፈር)ታደሰ ገብሬ (ጃክሰን) በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ አካል ጉዳተኛ የሆኑ ወጣቶችም ሳይሸማቀቁ ችሎታቸውን በመድረክ በማሳየት ረገድ ለፕሮግራሙ መሳካት የላቀ ሚና ነበራቸው፡፡ማርታ ከዚህ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጎን ለጎንም“ተምሳሌት”እና “ጠብታ”የተሰኙ መጽሔቶችንም በማሳተም ለአንባብያን በነጻ በማድረስ ላይ ነች፡፡ ተምሳሌት መጽሔት በማስታወቂያ ድርጅቷ አማካይነት የሚታተም ሲሆን፤ አካል ጉዳተኝነታቸውን በምክንያትነት ሳያስቀምጡ ችሎታቸውን አውጥተው ከራሳቸው አልፈው ለሌላውም መትረፍ የቻሉ በሀገር ውስጥም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸራቸውን ምሳሌ የሆኑ ግለሰቦች የሕይወት ተሞክሮ የሚስተናገድበት ነው፡፡ ጠብታ መጽሔት Ewin Charitable Associationሥር የሚታተምና የማኅበሩ ልሳን ሲሆን፤ በየዓመቱ ህዳር ወር ላይ ተከብሮ የሚውለውን ዓለም አቀፉን የአካል ጉዳተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚታተም ዓመታዊ መጽሔት ነው፡፡

        በግብረ-ሠናይ ሥራ መሠማራት

እሷ ካለፈችበት የአካል ጉዳተኝነት ሲደመር የሴትነት የሕይወት ውጣ ውረድ እንዲሁም በሙያዋ ከገጠሟት በመነሳት“እውን የበጎ አድራጎት ማኅበርን”በማቋቋም አካል ጉዳተኞች በእጅጉ የሚቸገሩበትን ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ (ዊልቸር) ሀገር ውስጥ በመገጣጠም ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን በማዳን ረገድ አስተዋጽኦ የሚኖረውን የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይም ሴት አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖና ይልቁንም በጤናና ሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ ያልተዳሰሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የድርሻዋን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለት ድርጅቶችን በማስተዳደር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛ ማርታ የሁለቱም ድርጅቶቿ መጠሪያ“እውን”ይባል እንጂ ሁለቱም ተግባራቸው ለየቅል ነው፡፡ ስሙንም የመረጠችበት ምክንያትም የጋዜጠኝነት ፍላጎቷን እውን በመሆኑ የተሠየመ መሆኑን ትናገራለች፡፡ በአንደኛው የማስታወቂያና ሕትመቱን ስታከናውንበት ሁለተኛውን ደግሞ የግብረ-ሠናይ ድርጅቱንም ይዞ ከተነሳው ዓላማና ራዕይ ለማሳካት  በዋና ሥራ አስኪያጅነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡

  የሕይወት ተግዳሮት

ዛሬ ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ መጠነኛ የአመለካከት ለውጥ መታየት ይጀምር እንጂ ቀደም ሲል የነበረው ለአካል ጉዳተኞቸ የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛና የተዛባ ነው፡፡ በዚህ ላይ የነበረው የመሠረተ- ልማት ችግር (መንገድ፣ ት/ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች ወዘተ.) ደግሞ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው ባለመገንባታቸው እንደሌላው ውሎ ለመግባት አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ማርታም የዚህ ማኅበራዊ ችግር ቀማሽ ሆና አልፋዋለች፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያም ለአካል ጉዳተኞች የማይሆን እንደሆነና ፈጽሞ ይህንን ሥራ እንዳትሞክረውም ተነግሯት በጽናት ተወጥታዋለች፡፡ አካል ጉዳተኞች ትዳር መመሥረት፣ ልጆችን መውለድና ቤተሰብ ማፍራት ከባድ ስለሆነ እንዲህ አይነት ሐሳብ ካላት ቢቀርባት መልካም እንደሆነ የተነገራትም ብዙ ጊዜ ነበር፡፡ መልካም የትዳር አጋርነቷን፣ በፈጣሪ የተቸራትን የእናትነት ጸጋዋን ከላይ ከሚታየው የአካል ጉዳት ሁኔታዋ ጋር እያስተያዩ በጎ ያልሆነ አስተያየት የሰጧትም ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ጋዜጣ በምታሳትመበት ወቅትም ይሁን የቴሌቪዥን ፕሮግራሟን ስታዘጋጅ “የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ እኔንም ይመለከተኛል!!” ባይ ተቆርቋሪ አለመኖሩና የሚደገግፋት ማጣቷ አሳዝኗትም ያውቃል፡፡ ነገር ግን በመሞከር የምታምንና ጥንካሬን ተቸረች በመሆኗ ሁሉንም ታግላ አሸንፋለች፡፡

ቤተሰባዊ ሁኔታ

ከባለቤቷ ከአቶ ዮሐንስ አለማየሁ ጋር በትዳር ከተጣመሩ 13 ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን የ3 ልጆች እናትም ናት፡፡ በበርካታ ቤተሰቦች መካከል የምትገኘው ጋዜጠኛ ማርታ እርሷም ቤተሰባዊ ኃላፊነቷን ጠንቅቃ የምታውቅና ይህንንም አቅም በፈቀደ መጠን ለመወጣትና ሁሉንም ለማስደሰት የምትታገል ጠንካራ ሴት ናት፡፡

 ግለ-ባህርይ

አካል ጉዳተኝነቷ እና ሴትነቷ ተደማምረው በህይወቷ በርካታ ተግዳሮቶችን ያለፈችው ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔ የመንፈስ ጥንካሬ የሚንጸባረቅባት፣ ጽናትን የታደለችና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትኩረት የምትሰጥ ናት፡፡ ደጋግሞ በመሞከር የምታምን ትዕግሥትን የተላበሰች፣ ባልተሳካው ጉዳይ ፀፀትና ቁጭት የማታዘወትር ስትሆን ማኅበራዊ ሕይወት በመሳተፍም ረገድ የተሳካላት ናት፡፡ ብዙ ጊዜ በሠርግም ይሁን በለቅሶ እና በመሳሰሉት የማኅበራዊ ሕይወት ዘርፎች ላይ አካል ጉዳተኞች ሲሳተፉ “አሁን አንቺን ማን ያማል? . . . ” የሚሉትንግግሮችበማርታ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፤ ብለዋትም አያውቁም፡፡ ይልቁንም በደረሰባቸው ሀዘን ይሁን ደስታ ተካፋይ ካልሆነች ብዙዎቹ ቅር ይሰኙባታል እንጂ፡፡  

ምሥጋና

ከሁሉ በፊት የፍጥረታት ባለቤት የሆነው፣ በቸርነቱና በዘለዓለማዊ ምሕረቱ የጠበቃትን፣ በመልካም ቤተሰባዊ ፍቅር የባረካትን ልዑል እግዚአብሔርን እናቱን ድንግል ማርያምን ከማመስገን ቸል ብላ የማታውቀው ማርታ በሕይወቷ ውስጥ ትልቁን ሚና የተጫወቱትን እናቷ ወ/ሮ አበራሽ ኃይሌ፣ የምትወዳቸው እህት ወንድሞቿ እንዲሁም ልጆቿ በተለየ ሁኔታ ደግሞ ለዛሬው ማንነቷ ትልቁን ድርሻ የተወጡትን አበበች ዘገኑና ፍቅርተ በቀለን እንዲሁም አቶ ተክለሥላሴ ገላንና ቤተሰቦቻቸው በማርታ ልቦና ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸውና ሁሌም ታመሰግናቸዋለች፡፡









አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች