84. ጎበዜ ሲሳይ  ዘገዬ  -Gobeze Sisay Zegeye

          የኢሳቱ ጎበዜ ሲሳይ

 የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፣ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 10 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል

ጎበዜ ሲሳይ  ዘገዬ ይጠቀሳል፡፡ ጎበዜ በዚህ 5 አመት ውስጥ ተስፋ የሚጣልበትን ተግባር ያከናወነ በመሆኑ ባኖረው አሻራ ልክ ታሪኩ ለሌሎች አስተማሪ ስለሆነ እነሆ ሰንደነዋል፡፡

                     ትውልድ እና እድገት

ጎበዜ ሲሳይ  ዘገዬ   ተወልዶ ያደገው በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ጎብዬ በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው። የትውልድ ጊዜውም  ግንቦት 3 1977 ነው፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም ወላጆቹ ወደ ትምህርት ቤት ሳይሆን ወደ ከብት እረኝነት ነበር የላኩት፡፡

አባቱ  በአካባቢው የታወቁ ጎበዝ ገበሬ ነበሩ ።  ከእርሻ ስራ በተጨማሪ ከብት እና ፍየል እርባታ ስለሚያረቡ  የበኩር ልጃቸውን  ወደ ትምህርት ቤት መላክ ሳይሆን  ከብቶቻቸውን   በመጠበቅ  እንዲያግዛቸው ነው የፈለጉት ።

  ከጥቂት አመታት በኋላ ታናሽ ወንድሙ በጎበዜ እግር  የእረኝነቱን ቦታ ተክቶ አባቱን የሚያግዝበት እድሜ ላይ ሲደርስ  ጎበዜ የመማር እድሉን አገኘ።

               ትምህርት  

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን  በጎብዬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ የ2ኛ ደረጃን ደግሞ በወልዲያ አጠቃላይ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  አጠናቋል። በወልዲያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማር  ወላጆቹ በየ3 ቀኑ ስንቅ ቋጥረው  ገበያ ለሚሄድ ሰው ፈልገው ይልኩለታል። ይሁን እንጂ  ስንቁ በወቅቱ   ስለማይደርስ  አብዛኛውን ጊዜ  ምግብ  ሳያገኝ ውሎ የሚያድርበት ቀን ይበዛል።

አፋር ክልል በሚገኘው  በገዋኔ ግብርና ኮሌጅ  በእንስሳት ሳይንስ ዲፕሎማ አግኝቷል። በዓለም  ዝቅተኛ እና  ረባዳማ  መሬት  በሆነው  ዳሎል  የእንስሣት ሀብት እርባታ መለስተኛ ኤክስፐርት ሆኖ ለ4 አመታት ያህል  አገልግሏል።  ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  በየጊዜው ፈተና የሚሆንበት  “ለእንስሳቶቹ  በቂ መኖ እንዴት ማግኘት ይቻላል ? ”  የሚል ነው ። ይህንን ለመቅረፍ የተለያዩ የመኖ ዘሮችን በአካባቢው በማላመድ አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። በዚህም የአርብቶ አደሩን ህይወት ከቀየሩ እና የላቀ ስራ ላከናወኑ  የግብርና ባለሙያዎች  የሚያገኙትን ሽልማት አንደኛ በመውጣት በ2002 ዓ/ም ከቀድሞው  ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  የሜዳልያ  ሽልማት ተቀብሏል። 

                 የጋዜጠኝነት ፍቅር………

ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው የጋዜጠኝነት ፍቅር ዳሎል ሆኖም ሊለቀው  አልቻለም ። በአርብቶ አደሩ ሰፈር ሲንቀሳቀስ እና  ስራውን ሲከውን ሬድዮ አይለየውም ። ሁሌም ለመረጃ ቅርብ ነው ።  ከግብርና ስራው ጎን ለጎንም  ከአፋር ክልል ዳሎል  ተነስቶ ባህርዳር  ዩኒቨርስቲ ( ከ1200ኪ.ሜበላይ  በየሴሚስተሩ በመመላለስ  ) በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት  የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

 በ2008 ዓ/ም የአፋር ክልልን በመልቀቅ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ጉባላፍቶ  እና ራያ ቆቦ የግብርና ባለሙያ ሆኖ ሰርቷል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የሕወሓት  አፈና ጫፍ የደረሰበት ወቅት  ነበር ።

ተቀጥሮ በሚሰራበት አካባቢ የሴፍትኔት ተጠቃሚዎች ከአለም ለጋሽ  አገራት ተሰብስቦ በስማቸው የመጣውን እና  ያለወለድ በብድር መልክ እንዲወስዱ የቀረበውን ገንዘብ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም  ( አብቁተ )  ወደ ራሱ ፋይናንስ ሥርዓት አስገብቶ በ16 በመቶ ወለድ እያበደረ መሆኑን ሲረዳ “ ይህ መሆን የለበትም ። የመጣው ለደሀ ደሀ ገበሬዎች በመሆኑ ያለብድር ሊሰጣቸው ይገባል ። ወለድ መክፈል የለባቸውም ”  በሚል በወቅቱ ከነበሩት  የብአዴን ካድሬዎች ጋር ዐይን እና ናጫ መሆን ይጀምራል ። ብአዴን  በአርሶ አደሩ ላይ የሚፈጽመውን ብዝበዛ እና ብልሹ አሰራር  ጎበዜ  በግልጽ  መሞገት ሲጀምር  ይህንን  ድርጊቱን እንዲያቆም  በቤተሰቦቹ  እና በቅርብ የስራ ባልደረቦቹ  ሽምግልና ይላክበታል።  እርሱ  “ ግን ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ  ልጅ ” ይላል።  በብአዴን አመራሮች  ጥርስ መግባት ጀምሯል። ሰበብ ፈልገው እስር ቤት ሊያስገቡት  እንደሆነም ከአመራሮቹ ውስጥ አንድ የቅርብ ሰው ሹክ ይለዋል።

ስራውን እና ቤተሰቡን ጥሎ ራያ ቆቦን በሌሊት ተሰናብቶ በሱዳን በኩል  ሰሀራ በረሀን አቋርጦ  በአስራ አራተኛው ቀን  ግብጽ ይገባል። በግብጽ ከሁለት አመት የስደት ቆይታው  በኃላ የሕወሓት መገርሰስ እውን ሲሆን ወደ አገሩ ተመልሷል።

               ኢሳት እና ጎበዜ ሲሳይ 

ከለውጡ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የገባው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን እና ራዲዮ (ኢሳት )ን በመቀላቀል  የሚወደውን  የጋዜጠኝነት ስራ  ይጀምራል።

ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ  በርካታ ስራዎችን አከናውኗል። በተለይ በቀድሞው ገቢዎች እና ጉምሩክ ሚኒስቴር የሰራተኞች የሥነ- ምግባር እና ደንብ መመሪያ  መሰረት ሰራተኞቹ የሥነ- ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ዳይሬክተሩ ጥርጣሬ ካደረበት ከስራ ማሰናበት እንደሚችል ይገልጻል። ከስራ የተሰናበተው ሰራተኛ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ቢሄድ እንኳ ወደ ስራው መመለስ እንደማይችል ይደነግጋል።

ይህ የዜጎችን ዳኝነት የማግኘት መብት በገሀድ የነፈገውን  መመሪያ ትኩረት በመስጠት በመመሪያው የተባረሩ ሰራተኞችን ከያሉበት በማሰባሰብ እና የህግ ባለሙያዎችን በመጠየቅ  የተቋሙን የህግ ክፍል ዳይሬክተር በመሞገት የምርመራ ዘገባዎችን በሰነድ አስደግፎ  አጋልጧል። ከአራት መቶ በላይ ሰራተኞች የተባረሩበት ይህ ህገ- ደንብ የወጣው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን ከ8 አመት በላይ ስራ ላይ ውሏል። ይሁን እንጅ  በምርመራ ዘገባው  የተቋሙ የሥነ ስርዓት ህገ ደንቡ   ህገ መንግስቱን በግልጽ የሚጻረር መሆኑን ከዘገባው የተረዳው  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህግ ደንቡ ስራ ላይ እንዳይውል   በግልጽ አግዶታል።

ሌላው ጥቅምት 24 /2013 ዓ/ም  በምዕራብ ወለጋ  ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀንቃ ቀበሌ  ታጣቂዎች  በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ዜጎች በአንድ ቀን ሌሊት ተግድለው አድረዋል። https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1321875481507253&id=100010544402822 ታጣቂዎቹ ከሞት የተረፉ የቀበሌዋ ነዋሪዎችን  ለማጥቃት ወደ ሌላ ቀበሌ ሲንቀሳቀሱ  ጎበዜ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች  እና የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በደረቅ ሌሊት  ስልክ በመደውል  እየሆነ ያለውን ድርጊት አስረድቶ  ባለስልጣናቱ የጸጥታ ሀይሎችን በመላክ  በጫካ የተደበቁ ነዋሪዎችን  ከሞት ታድገዋቸዋል። በወቅቱ  የተፈጠረውን አሰቃቂ የጅምላ ግድያ በግል የፌስ ቡክ ገጹ  ግድያውን ማጋለጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች  የሀዘን መግለጫ  አውጥተዋል ።  በተመሳሳይ በምስራቅ ወለጋ አንገር ጉትን አካባቢ የታጠቁ ሀይሎች ዜጎችን ለማጥቃት ወደ የቀበሌው ሲንቀስቀሱ ከነዋሪዎቹ   የደረሰውን መረጃ ከዜና ባለፈ ለጸጥታ ሀይሎች በመጠቆም ሊደርሱ የነበሩ  አስቃቂ የጅምላ ግዳያዎችን ታድጓል ።https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1429743094053824&id=100010544402822

ከዚህ በተጨማሪም  ብዙ የምርመራ ዘገባዎችን በመስራት ተቋማት የራሳቸውን የርምት እርምጃ ወስደው አስተካክለዋል። https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1446514729043327&id=100010544402822 በተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች  የታዘበውን እና ማስረጃ ባገኘባቸው  እውነተኛ  ዘገባዎችንም  ጎን ለጎን  ለአንባቢያን አድርሷል።

በተመሳሳይ የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ መንገድ ላይ መታገታቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያጋለጠው ይሄው ተስፋ የተጣለበት ወጣት ጋዜጠኛ ነው ።

የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል እየፈጸሙት ያለውን ድርጊት በማጋለጥ ታጣቂ ቡድኑ  በሽብርተኝነት እንዲፈረጅም የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  በተፈጠረ የጸጥታ መደፍረስ  ምክንያት አጣዬ ከተማ ሙሉ በሙሉ ከከተማነት ወደ ፍርስራሽ መቀየሯን በስፍራው ተገኝቶ በዘጋቢ ፊልም ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳይቷል።

  በኢትዮጵያ አንድ ጠንካራ የጋዜጠኞች ማህበር ባለመኖሩ ሁሌም ይከነክነዋል። ጋዜጠኛ ለራሱ የሚሆን ጊዜ ስለሌለው ለራሱ የሚቆምለትን  ጠንካራ አንድ ማህበር  ባለመኖሩ መታሰሩን የምንሰማው በውጭ አገር ባሉ የጋዜጠኞች ማህበር አማካኝነት ነው ይላል ጎበዜ ።

 ይህ ችግር ሊፈታ የሚችለው አንድ ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆነ ማህበር ሲመሰረት እንደሆነ  በማመኑ አራት  የሙያ አጋሮቹን በማስተባበር  የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ማህበርን እንዲመሰረት አድርጓል። በዚያው ማህበር ውስጥም  የህግ ክፍል ሀላፊ ሆኖ አገልግሏል።

ጎበዜ አንድ የህይወቴ መርህ ነው የሚለው “ ለምወደው  እና ለገባሁበት ሙያ እስከ ቀራኒዮ ድረስ መጓዝ አለብኝ ” የሚል ነው ።

“ በሰራኋቸው ዜናዎች ወይም የምርመራ ዘገባዎች ምክኒያት  ሰዎች ፍትህ ሲያገኙ ከዚህ በላይ ለእኔ የሚያስደስተኝ ነገር የለም ” ይላል ጎበዜ ።

“ ራሴን እንደወታደር ነው የማየው ። ሁሌ ለዜና ዝግጁ ነኝ ።ዜና ሳልሰራ ከዋልኩ ድብርት ውስጥ እገባለሁ። ሰዎች ቡና ወይም ሌላ ነገር ወስደው ለስራ እንደሚነቃቁት ሁሉ እኔ ደግሞ  ዜና ሳገኝ ነው የምነቃው ” ይላል ጎበዜ ስለ ስራ ባህሪው ሲገልጽ።  ጎበዜ እዚህ ጋር አንድን ሰው ማመስገን ይፈልጋል፡፡ ግብጽ በስደት ላይ ሳለ የተዋወቃትና የወደፊት የትዳር አጋሩ/ እጮኛውን/ አስቴር ገብሬን ማመስገን ይፈልጋል፡፡  

በ3 አመት ውስጥ በዜና አንባቢነት ፤ በሪፖርተርነት እና  በርካታ ፕሮግራምሞችን  አዘጋጅቶ አቅርቧል ።  የተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞችን በማዘጋጀትም  ለታዳሚው አድርሷል። ጎበዜ አቅምን እስከመጨረሻው ድረስ አሟጦ በመጠቀም ያምናል፡፡ ወደፊት እድልና ሁኔታዎች ከተመቻቹ ከዚህ በላይ ሰርቶ ሀገሩን የመቀየር ግብ ሰንቋል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች