83. ኢሳያስ ሆርዶፋ ሚጀና- Esyas Hordofa Miijena

                  ኢሳያስ ሆርዶፋ-አንጋፋ የአፋን ኦሮሞ ደራሲና ጋዜጠኛ 

 የማይዘነጉ ባለውለታዎች››  ለወጣቱ ትውልድ  አርአያ የሚሆኑና መንገድ አመላካች ናቸው

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1970ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡  ይህ አጭር ግለ-ታሪክ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አቶ ኢሳያስ ሆርዶፋ በአፋን ኦሮሞ የጋዜጠኝነትና እና የድርሰት ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ሚና ካላቸው ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ዛሬም ከጡረታ እድሜያቸው በኋላ ብእር ከወረቀት አገናኝተው ይጽፋሉ፡፡ ለእናት ሀገራቸው ካበረከቱት አንጻር አንቱታ ቢያንሳቸውም ራሳቸው በፈቀዱት መሰረት አንተ በሚል በአክብሮት እና በቀረቤታ ታሪካቸው እናቀርባለን፡፡  

ኢሳያስ ሆርዶፋ ሚጀና በቀድሞ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ በነቀምቴ በ1945 ዓ.ም ተወለደ፡፡ከ1ኛ  እስከ 3ኛ በሲዊዲን ሚሲዮን ከ3ኛ አጋማሽ እስከ10ኛ ክፍል በቀድሞ ነቀምቴ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ1ኛና 2ኛ ደረጃ ከዚያም በነቀምቴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃት/ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተማረ፡፡

በ1966 ዓ.ም በአሥመራ መምህራን ማሰልጠኛ በመምህርነት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ አለማያ እርሻ ኮሌጅም በአዝርዕት ልማትና ጥበቃ በ1976 ዓ.ም በዲፕሎም ተመርቋል፡፡በ1972 ዓ.ም. በቀድሞዋ ሐንጋሪ ሶሻሊስት ሪፓብሊክ ዋና ከተማ ቡዳፔስት በሚገኘው አለም አቀፍ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ኢኒስቲቲዩት የጋዜጠኝነት ኮርስ ተከታትሏል፡፡ከዚህም  በቀር በሊድ እስታር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በስነ- መለኮት ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል፡፡ 











ኢሳያስ ሆርዶፋ ወደ ሥራ ዓለም ከተሠማራ በኋላ÷

• 1967 አና 1968 ዓ.ም ለሁለት ዓመታት በቀድሞ ወለጋ ክ/ሀገር አርጆ አውራጃ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ ባንዲራ 1ኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ተብሎ በሚጠራው ት/ቤት በመምህርነት&

• በ1969 ዓ.ም.የቀድሞ አብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅ ኦሮምኛ ፕሮግራም በፍሪላንስ በፕሮግራም አዘጋጅነት&

• በ1970 በቀድሞ የወለጋ ክ/ሀገር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወኪል&

• በ1971 በቀድሞ የከፋ ክ/ሀገር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወኪል &

• ከ1971መጨረሻ እስከ 1977 መስከረም ወር በቀድሞ ሐረር ሬዲዮ ኦሮምኛ ፕሮግራም፣በፕሮግራም አዘጋጅነት፣በፕሮግራም ክፍል ኃላፊነትና የሐረርጌ ክ/ሀገር የማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር ቅ/ጽ/ቤቶች የበላይ ኃላፊነት&

• ከ1977 እስከ 1983 ዓ/ም ሰኔ ወር በቀድሞ አብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅ ብሔራዊ አገልግሎት ኦሮምኛ ፕሮግራም በከፍተኛ የፕሮግራም አዘጋጅነትና በፕሮግራም ክፍሉ ተ/ኃላፊነት &

• ከ1983 ሰኔ ወር እስከ 1984 ዓ.ምበቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንበከፍተኛ ፕሮግራም አዘጋጅነት፣

• ከ1984 መጨረሻ እሰከ 1985 ሐምሌ ወር ከሱዳን ዋና ከተማ ከካርቱም ይተላለፍ ለነበረው የኦሮሞ ነፃነት ድምፅ በዋና አዘጋጅነት፣ በአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ኀላፊነትና በሬድዮው ኤዲቶሪያል ቦርድ ም/ሰብሳቢነት

• ከ1987-1989 ዓ.ም.በግል ትራንስፖርት ንግድ ስራ ላይ ቆይቶ   እንደገና ወደ ጋዜጠኛነት ስራው በመመለስ ከ1989 እስከ 2003 ዓ.ም በቀድሞ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኦሮምኛ ፕሮግራም ከከፍተኛ ፕሮግራም አዘጋጅነት እስከ ዋና አዘጋጅነት በአጠቃላይ በመንግስት የመገናኛ ብዙሐን ድርጅቶች ለ30 ዓመታት  በጋዜጠኛነት ሙያ አገልግሎ በ2003 ዓ.ም ጥቅምት ወር ዕድሜው ለጡረታ ሳይደርስ መንግስት  “ቢፒአር“ (BPR)  ብሎ ለሙከራ ባወጣው መመሪያ መሰረት በጡረታ ተገሏል፡፡ይህ  መመሪያ ኢሳያስንና ሌሎች 129 የድርጅቱን ሰራተኞች ከስራ ካፈናቀለ በኋላ“ መመሪያው በትክክል  ሰራተኞችን አይመዝንም “ በማለት ከ2003 ዓ.ም.  በኋላ አልቀጠለም፡፡

በተለይ የያኔውንድርጊት ኢሳያስ ሲያስታውሰው በ2003 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ከድርጅቱ በቢ.ፒ.አር. ለሚሰናበቱት ሰራተኞች  አዲስ  አበባ  እስታዲዮም  ፊት  ለፊት  በሚገኘው  የኢትዮጵያ  መንገድ  ትራንስፖርት  መሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫ  በሰጡበት  ዕለት  ኢሳያሰ በሰጠው አስተያየት  ላይ“...የኢትዮጵያ  ንግድ ባንክ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ ላገለገሉት  ሠራተኞቹ  የወርቅ ቀለበት ሲሸልም እናንተ  ግን ለረዥም ዘመናት አገልግሎታችን  ምክንያት  ፈጥራችሁ በዚህ ሁኔታ እኛን ከስራ   ማፈናቀላችሁ   በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ታሪክ ይቅር የማይላችሁ ድርጊት ነው…“ በማለት ይህን በፈፀሙ በድርጅቱ የወቅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ኦሮምኛ ፕሮግራም ክፍል የኦህዲድ ካድሬዎች ላይ ቅሬታውን ገልጧል፡፤

ጋዜጠኛና ደራሲ  ኢሳያስ  ሆርዶፋ በ1969 ዓ.ም ገና ከ23 ዓመት ወጣትነት እድሜው ጀምሮ በኢ.ዜ.አ. &በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅቶች ለረዥም ዘመን አገልግሎቱ በሽልማት ሳይሆን  ኢ- ዲሞክራሲያዊ በሆነ መመሪያ መሰናበቱ ምን ጊዜም የማይረሳው መጥፎ ትዝታው መሆኑን  ይናገራል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ኢሳያስ ሆርዶፋ ምንም እንኳን በህውሐትና ኦህዲድ ዘንድ በአመለካከት ልዩነት የስራ ትጋቱ ባይደነቅለትም ኢሳያስ ታታሪና በስራው ላይ ጎበዝ ትጉህ መልካም ሥነ ምግባር ያለው በአፋን ኦሮሞ የሬድዮና ቴሌቪዥን አድማጭ ተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው ሲሆን ከኢህአዲግ የጭቆና ዘመን በፊት ለዚህ መልካም ስነ ምግባርና ጎበዝ ጋዜጠኛነቱ በ1972ና 1973 ዓ.ም በወቅቱ የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር ሚኒትር ከነበሩት ሻለቃ ግርማ ይልማ ትጉህ ጋዜጠኛ ሆኖ በመመረጥ የምስክር ወረቀት የተቀበለ ሲሆነ ፤በ1975 ዓም ደግሞ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞ ማህበር ባደረገው ምርጫ አሁንም ምስጉን ጋዜጠኛ ሆኖ በመመረጥ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል፡፡ ኢሳያስ በ1975 ጥቅምት ወር በቀድሞው ሶቭዬት ህብረት ዋና ከተማ ሞስኮ ላይ በተካሄደው አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ጋዜጠኞችን በመወከል በተገኘበት ወቅት በርካታ ልምድ የቀሰመ ሲሆን ከ38 አመት በፊት የተነሳው ምስልም ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ ቀርቧል፡፡

ሌላው  ኢሳያስ  በዘመነ ህውሓትና ኦህዲድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥ ቆይታው የደረሰብኝና የማልረሳው  አሳዛኝ  ትዝታዬ  ነው  ብሎ የሚያነሳው &ከከፍተኛ ፕሮግራም አዘጋጅነት መደብ  ላይ ሆኖ ለዋና  አዘጋጅነት  ደረጃ  ተወዳድሮ ታህሳስ 1 ቀን 1994 ዓ.ም በ2527 ብር የወር  ደመወዝ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሲያገለግል በ1998 ዓ.ም አካባቢ  የኢኮኖሚ  ማሻሻያ በማለት መንግስት  በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ የመንግስት  ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ጭማሪ ባደረገበት ጊዜ ለሁሉም  የድርጅቱ  ሰራተኞች የደመወዝማስተካከያ   ጭማሪ ሲደረግ ለኢሳያስ ግን “ አንተ ጣሪያውን ነክተሃል “ተብሎ  ተከለከለ፡፡ በዚህም ኢሳያስ ተበሳጭቶ ሲ.ፒ.ኤ. ሄዶ አቤቱታ ሲያቀርብ የሲፒኤ “ ይህ ለመላው  የሀገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች የተደረገው  ጭማሪ  የደመወዝ እስኬልን የሚመለከት አይደለም አንተም ልታገኝ ይገባል ፤ ሂድና ጠይቃቸው  “ ብለው ሲመልሱት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴለተቪዥን ድርጅትዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት በኋላ ለአጭር ጊዜ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት( ዛሬ በህይወት በዚህ ዓለም የሉም ) ሲጠይቅ  “ምንም ልረዳህ አልችልም “ በማለት መልስ ሰጡት፡፡  በዚሁ  ኢሳያስ አዝኖ ተመለሰ፡፡

ከሁሉም  የሚገርመው ደግሞ  አዲስ ለክፍሉ  የሚቀጠሩትን ጋዜጠኞች ለመቅጠር  ክፍሉና  የድርጅቱ  አስተዳደር ኢሳያስን  የፈታኞች ኮሚቴ አባልና ፈታኝ  አድርጎ  መርጦ  ተቀጣሪዎችን  የፅሑፍና  የቃለ - መጠይቅ   ፈተና ሰጥቶ  አርሞና  ነጥብ  ሰጥቶ ፈተናውን  ያለፉት ተቀጥረው ኦሮምኛ ክፍል ሲመደቡ የኦህዲድ አባላት በመሆናቸው ብቻ የኢሳያስ አለቃ  ሆነው መሾማቸው ነው፡፡

“ ኑሮ  ባይሳካም ፣ተገፍተን  ጊዜ ቢጥለንም ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ቢኖሩም ፣ የሰራዊት ሁሉ  ጌታ  ልዑል  እግዚአብሔር ከኛ ጋር  ከሆነ  ከፍ እጂ ዝቅ አንልም፤እግዚአብሔር ራስ ያደርገሃል እንጂ ጅራትአያደርግህም(ዘዳግም.28፡14)ታዲያ በደረሰብኝ  በደል ከጓደኞቼ በታች አልሆንኩም፤እግዚአብሄርን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም ተብሎ ተፅፏል፤“  በማለት ደራሲ ኢሳያስ የድሮውን መጥፎ ትዝታዎች በቅሬታ ያስታውሳል፡፡

ኢሳያስ ሆርዶፋ በትራንስፖርት ንግድ ሥራ ላይ

ከላይ ባጭሩ እንደተገለፀው ጋዜጠኛና ደራሲ ኢሳያስ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በኦሮሞ ነፃነት ድምፅ ሬድዮ የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በ1985 እንደ ተመለሰ ወደ ቀድሞ ጋዜጠኛነት ሥራው ለመመለስ አልፈገም፤የራሱ የሆነ የግል ሥራ ለመስራት ፈለገ ፡፡ ግን እንደፈለገው መዘጋጀት ስላልቻለ 1986ዓ.ም ካለምንም ሥራ አሳለፈ፡፡ በ1987ዓ.ም ግን የመድህን ዋስትና ያላትን በታላቅ ወንድሙበአቶ ደመላሽ ሆርዶፋ የግል የቤት መኪና ዋስትና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብር 55,000(ብር ሃምሳ አምስት ሺህ ባገኘው ብድር ላይ ታላቅ ወንድሙ ብር 5ሺህ ጨምረውለት አንድ ሚኒ ባስ በብር 60ሺ ገዝቶ ቀድሞ የነበረውን 2ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ በማድረግ ከሞጆ- አዳማ-ቢሾፍቱ-መቂ- ሻሸመኔ አላባ ቁሊቶ ሾኔ መስመር መሥራት ጀመረ፡፡

በዚህ የሥራ ዘርፍ በተለይ በ1988 ዓ.ም በሻሸመኔ ቆይታው ያጋጠመውን መጥፎ ትዝታውን አይረሳም፡፡ ጥር 3ቀን 1988ዓ.ም.በሻሸመኔ የቀድሞ መናኸሪያ ከንጋቱ 12 ሰዐት በተራው መንገደኞችን ወደ አላባ ቁሊቶ ከተማ አሳፍሮ ለመጓዝ ተራ በመጠበቅ ላይ እያለ አንድ የሃምሳ አለቃ ፖሊስ ትራፊክ አንድ ክላሽንኮቭ ጠብ መንጃ በያዘ ፖሊስ በመታጀብ መጥተው ከነ ሚኒባሴ ሻሸመኔ ወረዳ ፖሊሰ ጣቢያ ወሰዱት፤ከወሰዱት በኋላ የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ ያለው በወቅቱ የወረዳው ጣቢያው አዛዥ …. የሆነ ;አንተ ኦነግ አባል ነህ መኪናዋም የኦነግ ነች ወዘተ በማለት እንድታሰር ትዕዛዝ ሰጠ፡፡በዚሁ መሰረት ምንም መረጃ ሳይኖራቸው አራት ቀናት ካሰሩት በኋላ የም/የመቶ አለቅነት ማዕረግ ያለው ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኀላፊ የነበረ በአጋጣሚ ለቁጥጥር ወደዚህ ፖሊስ ጣቢያ መጥተው የጣቢያውን አዛዥ ሲያነጋግሩ ኢሳያስን ልትጠይቅ ከአዲስ አበባ መጥታ ሁኔታውን ለዚህ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለቁጥጥር ለመጡት ኀላፊ ስለ ኢሳያስ  መታሰር ጉዳይ አስረዳች፡፡

በዚሁ አካሄድ ኀላፊው ኢሳያስን አስጠርተው ሲያዩት የሚያውቁት ጋዜጠኛ ሆኖ አገኙት፡፡ከዚያም አሳሪውን የጣቢያውን አዛዥ በጥያቄ አጣደፉት፤

;ለመሆኑ ጋዜጠኛ ኢሳያስን ለምን አሰራችሁት ?;

;ስለ ጠረጠርነው;

;በምን ጠረጠራችሁት?;

;በኦነግነት;

;ምን ወንጀል ሲፈፅም ?;

;በጥርጣሬ;

;ያገኛሁበት ወንጀል ሳይኖር አንድን ዜጋ በጥርጣሬ ይህን ያህል ቀን ማንገላታችሁ በጣም ያሳዝናል አሁን ፍቱት ከእናንተ ጋር ግን በኋላ ይህንንና ሌላ የስራ አፈፃፀማችሁን  እንገመግማለን; በማለት ከእስር አሰናበቱት፡፡

ደራሲ ኢሳያስ አርብ ዕለት ሲታሰር የተወሰደበትን የመንጃ ፈቃዱን እንዲመልሱለት ሲጠይቅ መንጃ ፈቃዱ ሻሸመኔ ከተማ ኦህዲድ ፅ/ቤት እንደ ተወሰደ ተነገረው፤በዚሁ ተመልሶ ከአዲስ አበባ ለመጡት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ኀላፊ አመለከተ፤ኀላፊውም በድርጊቱ በጣም ተገርመው

;የኦህዲድ ፅ/ቤት ደግሞ ወደ ትራፊክ ፅ/ቤትነት ተዛወረ እንዴ?; በማለት ተሳልቀውበት እንዲመልሱለት አስደረጉ፡፡

በጥቅምት 19 ቀን 1989 ዓ.ም በዚያው ሻሸመኔ ከተማ በቀድሞው የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምትክ አዲስ ተሹሞ የመጣው የጣቢያው አዛዥም መኪናዋን ካለ ቦታ አቆምክ ብሎ ከጎኑ ሽጉጥ አውጥቶ ኢሳያስ ግንባር ላይ ደግኖ; ግንባርህን በዚህ እበትነዋለሁ; በማለት በመስመር ላይ የነበረውን ትራፊክ ፖሊስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ እንዲያስረው አዘዘ፤

የትራፊክ ፖሊሱም በታዘዘው መሰረት ወደ ፖሊስ ጣቢያው ወሰደው፡፡ሲያስረክበውም ;እኔ በዚህ ሾፌር ላይ ምንም የትራፊክ ስነ ስርዐት ደንብ መተላለፍ አላገኘሁበትም፤እኔ አልከሰስኩትም፤ እንዲታስር ያዘዙት የጣቢያው አዛዥ ናቸው; በማለት አስረክቦት ሄደ፡፡የዕለቱ ቃል ተቀባይ ፖሊስ ግን ህግን ባልተከተለ መንገድ ኢሳያስ ዳግም ወደ ፖሊስ ጣቢያው መምጣቱ አሳዝኖት ከሌሎች እስረኞች ጋር ሳይደባልቀው

;እኔ በአንተ ጉዳይ በጣም አዝናለሁ እዚሁ መኪናህ ውስጥ እደር ጧት ያሰረህ አዛዡ እስረኞችን ሲጎበኙ ከእስረኞች ጋር ሆነህ ተታያለህ በማለት መኪናው ውስጥ አሳድሮት ጧት ሊለቀቅ ችሏል፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ይህንንም በሀዘኔታ ያስታውሳል፡፡

ኢሳያስ በዚህ አስቸጋሪ ፈተና የበዛበት የትራንስፖርት ንግዱን ሥራ ሊቀጥልበት አልፈለገም፤ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ከዕለታት አንድ ቀን አቶ ደግፌ ቡላ በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ክፍል ኀላፊ በኋላ አምባሳደር የሆኑት ጋር አንድ ሥፍራ ተገናኝተው ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወደ ቀድሞው የጋዜጠኛነት ሥራው መመለስ ከፈለገ እንደሚችል ገልፀውለት ነሐሴ ወር 1989 ዓ.ም ኢሳያስ ወደ ቀድሞው ስራ ተመልሶ  በጥቅምት ወር 2003ዓ.ም በጡረታ እስከ ተገለለበት ድረስ አገልግሏል፡፡  

ለአፋን ኦሮሞ ስነ ጽሁፍና አርት ዕድገትያበረከተው አስተዋፅኦ

የሬዲዮ ኦሮምኛ ድራማ ከ1976 እስከ 1983 ዓ.ም

“ፎዚያ” በመጀመሪያበ1976 ዓ.ምበሐረር ሬድዮ ጣቢያቀ ጥሎም በ1977 ዓ.ምበኢትዮጵያ ሬድዮ ብሔራዊ አገልግሎት  ኦሮምኛ ፕሮግራም ለአድማጮች የቀረበ የመጀመሪያውረዥምየተባለዘመናዊ ባለ አንድ ሰዓት ድራማ ነው፡፡

“ሀዊ”በ1979 ዓ.ም በቀድሞአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅ ብሔራዊ አገልግሎትየኦሮምኛ ሬድዮመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ለሶስት ወራት  በተከታታይ  የቀረበ  የመጀመሪያው ለአድማጮች የተላለፈ ዘመናዊና ረዥም ባለ ሶስት ሰዓት ድራማ ነው፡፡

ይህ“ሀዊ“የተሰኘው ልበ-ወለድ ድራማ በዚያን ዘመን ለቋንቋው አድማጮች ለመጀመሪያ ጊዜ መተላለፉ ጽሁፎቻቸውን ለህዝብ የሚያቀርቡበት መድረክ አጥተው የተቀመጡትን ብዙ የአፋን ኦሮሞ ልበ-ወለድ ደራሲያንን ያነሳሳና የስነ-ፅሁፍ ስራቸውን ወደ ሬድዮ ጣቢያው የመዝናኛ ፕሮግራም ዝግጅት ክፍል ይዘው እንዲመጡ አርዓያ ለመሆን በቅታለች፡፡ለአብነትምለመጀመሪያ ጊዜ  በ1983 እና 1984 ዓ.ም ተከታታይ ዓመታት በአፋን ኦሮሞ  ታትመው ለአንባቢያን የቀረቡት ድርሰትቶች  በሬድዮ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ 1979 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ለአድማጮች የቀረቡት“ጉራቻ አበያ “ እና“ዋ ለማደቡ ” (ኩሳ  ገዶ )የተሰኙትልበ-ወለድትረካዎች ሀዊ ድራማ በመስከረም ወር 1979 ዓ.ም ለአድማጮች ከቀረበች በኋላ ነው፡፡ሀዊ ከነዚህ  ልበ-ወለድ መፅሐፍት  ዘግይታ  ብትታተምም  ለአፋን ኦሮሞ የሬዲዮአድማጮች ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ  በመቅረብ  ቀዳሚ ናት፡፡

ሀዊ ድራማ በ1995 ዓ.ም በልበ-ወለድ መፅሐፍ በሜጋ መፅሐፍ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት ታትማ ለአፋን ኦሮሞ አንባቢያን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበች ስትሆን ከዚያም ደራሲው በራሱ ወጪ  ስድስት ጊዜ ደጋግሞበማሳተም ለአንባቢያን አቀርቧል፡፡ ሀዊ በአፋን ኦሮሞ አንባቢያን ዘንድ እጅግ ተደናቂና ተወዳጅ መፅሐፍ ስትሆን እስከ 2013 ሰላሳ ሺህ (30‚000 ) ቅጂ ታትማ ለአንባቢያን ቀርባለች፡፡ይህም ቁጥር ከአፋን ኦሮሞ ልበ-ወለድ መፅሐፍት  ቀዳሚያ የሚያደርጋት መሆኑን ያስረዳል፡፡

ደራሲው በአሁኑ ወቅት ይህችን መፅሐፍ ወደ ፊልም ፅሑፍ ቀይሮ ለተመልካቾች ለማቅረብ ለቀረፃውና ለልዩ ልዩ ወጪዎች እሰፖንሰር በማፈላለግ ላይ የሚገኝ ሲሆን የዚህን ተወዳጅና ተደናቂ ልበ- ወለድ መፅሐፍ ፊልም ሥራ በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ እስፖንሰር በማድረግም ሆነ በተባባሪነት ለመስራት ለሚፈልጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በነገራችን ላይ ሀዊ ልቦለድ መጽሀፍ  በመስከረም 2013  በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እና በስሙ ኦድዮ ቡክ ትብብር በኦድዮ ትረካ ሊቀርብ ችሏል፡፡ ትረካውንም አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ሃሊማ መሀመድ አቅርባዋለች፡፡ 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኦሮምኛ ድራማከ 1983 እስከ2003 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኦሮምኛ ታሪክበ1983 ዓ.ም ሐምሌ ወር፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመልካቾች የቀረበችው አጭር ባለ 20 ደቂቃ  “ራጂ ዋቲሌ” የተሰኘችው ድራማ የደራሲ ኢሳያስ የስራ  ውጤት ነች፡፡

በ1984 ዓ.ም ህዳር ወር የዓለም የኤድስ ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መታሰብ የጀመረበት ቀን ለተመልካቾች የቀረበው ረዥም የተባለ የባለ አንድ ሰዓት የቴሌቪዥን ድራማ ”ዱር ሀፌ” የተሰኘውም የዚሁ ደራሲ የስራ ውጤትነው፡፡

ከዚህም  በቀር፣“ዱረ ሃፌ”፣“ራጂ ዋቲሌ”፣“ጉዲ ሰዲ”፣“ወርቄኮ”፣  “ጉያቲ ሰና ”፣ የተሰኙት  ስራዎቹ  በኦሮምኛ  የሬዲዮ ድራማ  ታሪክ  የመጀመሪያዎቹና ለዛሬው  የኦሮምኛ ሬድዮ ድራማ ዕድገት፣ ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡

በተለይ በ1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴለተቪዥን በአማርኛ ስርጭት በጀመረበት በ25ኛውዓመት ላይ የአፋን ኦሮሞ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭት ሲጀመር የቴሌቪዥን ድራማ ለመስራት በአፋን ኦሮሞ የሚተውኑ ተዋንያንን ለማግኘት ከፍተኛ ችግር የሆነበት ወቅት ነበር፡፡ ደራሲ ኢሳያስ ከላይ የተጠቀሰውን“ዱር ሀፌ“ የተሰኘውን ድራማ የዓለም የኤድስ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታስቦ ለሚውልበት ቀን ለተመልካቾች ለማቅረብ በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከነበሩት ትያትር ቤቶች ውስጥ አፋን ኦሮሞ መናገር የሚችሉ አርቲስቶችን በማስፈለግና በማፈላለግ ደራሲ ኢሳያስ ከፍተኛ ጥረትአደረገ፡፡እናም ጥረቱ ከንቱ አልቀረም፡፡ከብዙ ሩጫ በኋላ ማርታ ስለሺ፣ሙሉጌታ ባልቻና ታደሰ ጩቄ የተባሉትን ተዋንያን ከራስ ትያትር ፣ ከኢትዮጵያ ሬድዮ አፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ክፍል ደግሞ ሮማን ሙላቱ የተባለችውን ጋዜጠኛ በመጨመር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አፋን ኦሮሞ ድራማ ታሪክ  የመጀመሪያ የሆነውን በወቅቱ ረዥም የተባለውንይህን የአንድ ሰዓት ድራማ ለተመልካቾች ለማቅረብ ተችሏል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ሳይገለፅ የማይታለፈው ይህ ፅሑፍ እስከተዘጋጀበት ድረስ  ከደራሲው ኢሳያስ ሆርዶፋና አርቲስት ማርታ ስለሺ በስተቀር የተቀሩት በድራማዉ ላይ በተዋናይነት የተሳተፉት ሶስቱ ተዋንያን ማለትም ሙሉጌታ  ባልቻ፣ ታደሰ  ጩቄና ጋዜጠኛ ሮማን ሙላቱ ሪቂቱ ዛሬ በሕይወት አለመኖራቸው ነው፡፡ግን ዛሬ በህይወት ባይኖሩምበአፋን ኦሮሞ ድራማ ታሪክ ውስጥ  ስማቸውና  ስራቸው  ለዘለዓለም ሲዘከር  ይኖራል፡፡

እነዚህ ተዋንያን በአፋን ኦሮሞ የቴሌቪዥን ድራማና አፋን ኦሮሞ ፊልም  አጀማመር ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ “ራጂ ዋቲሌ “ ለተሰኘችው የመጀመሪያዋ አጭር ባለ 20 ደቂቃ ድራማ ላይ የተሳተፉት ተዋንያን ግን በሙያቸው ተዋንያን ሳይሆኑ ደራሲው አደፋፍሮና አለማምዶ  ያሰራቸው ነበሩ፡፡ እነሱም የአፋን ኦሮሞ ድምፃዊ ዳግም መኮንን እና ወ/ሮ ጎበኔ ነመራ ይባላሉ፡፡

ድምፃዊ ዳግም መኮንን ከረዠም ዓመታት በፊት ማለትም ድራማውን በተዋናይነት ከሰራ በኋላ ብዙ ሳይቆይ ወደሰሜን አሜሪካ ሄዶ አሜሪካዊ ዜግነት አግኝቶ እዚያው በመኖር ላይ ያለ ሲሆን ወ/ሮ ጎበኔ ነመራ ግን ድራማውን በሰራችበት ወቅት አዋሽ ባንክና  ኢንሹራንስ ኩባኒያ ስትሰራ የነበረች ስትሆን ከዓመታት በኋላ ሰሜን አሜሪካ በመኖር ላይ ትገኛለች  ፡፡

በ1980 ዓ.ም  ይህንኑ “ራጂዋቲሌ“ የተሰኘችውን ድራማ በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምፅ የአፋን ኦሮሞ  የእሑድ  ጧት መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ድምፃዊ ዳግም መኮንን በወቅቱ የ2ኛ ደረጃት/ቤት ትምህርቷን ትከታተል ከነበረችው አስቴር ዮናታን ይስሐቅ ከምትባል ተማሪጋር ተውነዋል፡፡

የሬድዮ ድራማ  ክፍያን በሚመለከት “ ገንዘብ ሚኒስቴር በሬድዮ ለአድማጮች ተዘጋጅተው ለሚቀርቡ የአፋን ኦሮሞ ድራማና ስነ ፅሁፍ እንዲሁም ለድራማው ደራሲና ለተዋንያን ክፍያ  የበጀት ርዕስ አልመደበልንም “ በሚል የአብዮታዊት የኢትዮጵያ ድምፅ ሬድዮ ፋይናንስ ክፍል  በዚያን ዘመን  ደራሲና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ሆርዶፋና ሌሎች የአፋን ኦሮሞ ሬድዮ ድራማ ደራሲያንና  ተዋንያን ለሰሩት ስራ ምንም ክፍያ አላገኙም፡፡ ቢሆንም ክፍያ የለንም  በማለት ሳይከፉና ተስፋ ሳይቆርጡ አርት ለጠማው የአፋን ኦሮሞ ሬድዮ አድማጮች በደስታ ይሰሩ ነበር፡፡

ከ1983 ዓ.ም በኋላ ግን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለአፋን ኦሮሞ ድራማ ደራሲያንና ለተዋንያን ክፍያ የሚፈፀም ቢሆንም ደራሲው የድርጅቱ ጋዜጠኛ ከሆነ ግንበወር ከሚያገኘው ደመወዝ ሌላ ከመደበኛ ስራው ውጪ ለጣቢያው ቢሰራ ለተጨማሪ ስራ ተጨማሪ ክፍያ አይኖረውም የሚል  መመሪያ ስለነበር የቴሌቪዥን ጣቢያው ጋዜጠኛ ድራማውን ደርሶ ክፍያ ለማግኘት የድራማውን ደራሲነት ስም በሌላ ጓደኛው ስም በማድረግ ክፍያ እንዲፈፀምለት  ማድረግ ይኖርበታል፡፡ደራሲ ኢሳያስ ግን  ስራዎቹን ለገንዘብ ሲል በሌላ ሰው ስም ሳያደርግ ከላይ የተዘረዘሩትን ድራማዎች ካለምንም ክፍያ በነፃ ለሚወደው የድራማዎቹ  ተመልካቾቹ ያቀርብ ነበር፡፡

በተለይ በአፋን ኦሮሞ ቴሌቪዥታሪክ ውስጥ  ሰኔ 16 ቀን 1983 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን የአንድ ሰዐት ፕሮግራም ስርጭት ሲጀምር ጋዜጠኛና ደራሲ ኢሳያሰ ሆርዶፋ በመጀመሪያ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ በማለት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማቅረብ የዕለቱን ፕሮግራም ያስተዋወቀና ከዚያን ቀን ጀምሮ  ፕሮግራም ክፍሉን በማስተባበርና በማደራጀት የክፍሉን ስራ ከሌሎች አራት የፕሮግራም አዘጋጆች ጋር በመሆን የጀመሩት ስራ ዛሬ  በዘመናዊ አደረጃጀት ተሻሽለው ለ24 ሰዓታትአገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙት በውጪ ሀገርና በሀገር ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ላሉት የመንግስትና የግል የአፋን ኦሮሞ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ጣቢያዎች ጋዜጠኞች ተምሳሌትና ለፕሮግራም ስርጭቱ ፈር ቀዳጆችና መስራቾች ከሆኑት አምስቱ ጋዜጠኞች ደራሲ ኢሳያስ አንዱ ነው፡፡

ከደራሲ ኢሳያስ ሆርዶፋ ጋር የአፋን ኦሮሞ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭቱን ሰኔ 16 ቀን 1983 ዓ.ም.የጀመሩት   ሳሙኤል ዳባ ፣ በድሪያ  መሐመድ፣  ዮሐንስ  ዋቆ እና በዳሳ ሲማ የሚባሉ  ጋዜጠኞች ሲሆኑ ከነዚህ  ውስጥ  ከሳሙኤል  ዳባ በስተቀር ይህ ፅሑፍ እስከተዘጋጀበት ድረስ ዛሬ ሁሉም  በህይወት  ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ  ቴሌቪዥን  ቆይታ  አስተዋፅኦውን በሚመለከት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አፋን  ኦሮሞ  ፕሮግራም   በተጀመረ በ11ኛው ዓመቱ  ለመጀመሪያ ጊዜ አብዲ  ቦሪ  በመባል የሚታወቀውን   የልጆች  ክ/ ጊዜ የፕሮግራሙን አሰራር የሚገልጥ  መመሪያ ( Programme manual)   በማውጣትና ፕሮግራሙን በማዘጋጀት ጥር1994 ዓ.ም. ማስተላለፍ የጀመረው ይሄው ጋዜጠኛና ደራሲ ነው፡፡ 

ደራሲ  ኢሳያስ ሆርዶፋ ከዚህም በቀር ”ጆርሴ”፣“ከን ጨባቱፈቴ”፣(ጨራ ጅግሲ)፣“ወርቄኮ“፣ “ከን ፋጫሳን ሃሙ”፣ የተባሉትን የቴሌቪዥን ድራማዎችን ደርሶ ለተመልካቾች አቅርቧል፡፡እነዚህና ሌሎችም የሬድዮና ቴሌቪዥን ድራማዎቹ ለዛሬው የኦሮምኛ የሬድዮና የቴሌቪዥን ድራማ እንዲሁም ለኦሮምኛ ፊልም ዕድገት ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡

ሌላው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ሲጀመር ሳይጠቀስ  ሊታለፍ   የማይገባ  ስራ   በጣቢያው የምስልና ድምፅ ክምችትክፍል  ውስጥ የነበሩት ዘፈኖች በጣም ጥቂት ስለነበሩ  የክፍሉን የሙዚቃ ክምችት ለማሟላት ድምፃዊያንን በማፈላለግ በያሉበት ስፍራ  በመሄድ በተለያዩ መናፈሻዎች፣ ትያትር ቤቶችና ወደ እስቱዲዮ አምጥቶ በመቅረፅ ጋዜጠኛናደራሲ  ኢሳያስ ከፍተኛ እስተዋፅኦ ማበርከቱ የሚረሳ ተግባር አይደለም፡፡

      የአፋን ኦሮሞ ልበ- ወለድ መፅሐፍት

ኢሳያስ   በጡረታ  ከተገለለ  በኋላ ወደ  ግል  የስነ ጽሁፉ  ስራው  በመሰማራት  የበርካታ የአፋን ኦሮሞ ልበወለድ  መፅሐፍት ደራሲያንን ፅሑፍ ተቀብሎ  በአርታኢነት በመርዳት  የምክር  አገልግሎት በመስጠት  ለአፋን  ኦሮሞ  ስነ  ፅሁፍ  እድገት  ከፍተኛ  አስተዋፅኦ  በማበርከት ላይ  ይገኛል፡፡ ከዚህም  በቀር  የኦሮሞ  ደራሲያን  ማህበር  ከሌሎች አራት  ደራሲያን  ጋር  በመሆን በ2002 ዓ.ም በመመስረት  የማህበሩ  ም/ፕሬዚዳንት በመሆን ለ6 ዓመት አገልግሏል ፡፡      

በኢትጵያ ብሮድካስቲንግ   ኮርፖሬሽን F.M 97.1 በየሳምንቱ ማክሰኞ ምሽት ከ 2 እሰከ 4 ሰዓት ለአድማጮች ይተላለፍ ለነበረው የኢትዮጵያ  ደራሲያን  ማህበር  የጥበብ  እልፍኝ  የተሰኘውን የሬድዮ ፕሮግራም የሬድዮ የፕሮግራም መስሪያ መመሪያ (programme production  manual) በማዘጋጀት የሬድዮው  ኤዲቶሪያል  ቦርድ  ም/ሰብሳቢ  በመሆን ስርጭቱ እንዲሳካ ከፍተኛ  እገዛ ያደረገ ሲሆን የጥበብ እልፍኝ ፕሮግራም በF.M 97.1 ላይ ያቀርብ የነበረውን ፕሮግራም በመተው በF.M.94.3 አሀዱ ሬድዮ ዝግጅቱን ማስተላለፍ ከጀመረ በኋላም የፕሮግራሙ ኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ይህ ጽሑፍ እስከ ተዘጋጀበት ድረስ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ 

ከዚያም ከ2006 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጽ/ቤት በሥራ አስኪያጅነት፡፡

ከ2007 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም “Siifsiin” ለተባለው ወርሃዊ የኦሮምኛ መጽሔት ዋና አዘጋጅ  በመሆን አገልግሏል፡፡

ከ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ በአፋን ኦሮሞ በሚተላለፈው ሞአ በተባለው የግል ቴሌቪዠን ጣቢያ በዋና አዘጋጅነት በኋላም በፕሮግራም አዘጋጅነት&በአጠቃላይ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 38ዓመታት በግልና መንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት  በጋዜጠኛነት ሙያ አገልግሏል

ከላይ ባጭሩ ለመግለፅ እንደ ተሞከረው248 ገፅ ብዛት ያላት ረዥም ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ታሪክ ያዘለች“ሀዊ”በኦሮምኛ ልበወለድ መፅሐፍት  ህትመት ታሪክ በ1995 ዓ.ም. ታትማ  ለኦሮምኛ አንባቢያን  ዘግይታ በመቅረብ አራተኛውመፅሐፍ  ብትሆንም   በሬድዮ ለአድማጮች በመቅረበየመጀመሪያ ኦሮምኛ ልበ-ወለድድርሰት ናት፡፡ይህ ፅሁፍ እስከ ተዘጋጀበት ድረስሰላሳሺህ ቅጂዎች ለ7ኛ ጊዜ ታትማለች፡፡ ይህም ቁጥር ከኦሮምኛ ልበ ወለድ መፅሐፍት ቀዳማዊ ያደርጋታል፡፡

ከዚህም በቀር ባለ 172 ገፅ ብዛት ያላት“ዬሮን ሲፍ ሃዲስቱ”፣በ2000 ዓ.ም አንድ ጊዜ 2013 ዓም ሁለት ጊዜ ታትማለች፤“ዮሚ ላታ? ”የተሰኘው ታሪካዊ ልበ ወለድ በ2002 ዓ.ምየኢትዮጵያ  ደራሲያን  ማህበር ባገኘው ተዘዋዋሪ ሂሳብ ታትሞ ለአፋን ኦሮሞ አንባቢያን የቀረበ  ዘመን ተሸጋሪ  279የገፅ ብዛት  ያለው ረዥም  ታሪካዊ ልበ-ወለድ መጽሐፍ ሲሆን እስከ 2013ለአምስት ሶስት ጊዜ ተደጋግሞ የታተመ በአፋን  ኦሮሞ አንባቢያን ዘንድእጅግ  የተወደደና የተደነቀ መፅሐፍ  ነው፡፡

ከዚህም  በቀርበ2005 ዓ.ም የታተመው“ፅጌሬዳፊ አሶሳሞታ ገገባቦ”፣ የተሰኘው  የአፋን ኦሮሞ አጫጭር ልበ ወለዶች ስብስብ ሲሆን  ከላይ እንደ ተገለጠው  ደራሲው  በሬድዮና  በቴሌቪዥን  ለአድማጮችና  ተመልካቾች ያቀረበውን  ድራማዎች   የኢትዮጵያ  ሬድዮና  ቴሌቪዥን የድምፅና ምስል ክምችት ክፍሎች አያያዝ በዚያን  ዘመን ኋላ ቀር ስለነበሩ በተለይ የሬድዮው በአሁኑ ወቀት ላይኖሩ  ይችላሉ በሚል ፣ የቴሌቪዥንም ምስል ክምችት አያያዝምአንዳንዶቹ ድራማዎች ጥራታቸውን ላይጠብቁ ይችላሉ ፣ አንዳንዶቹም  ከነጭራሹ ላይኖሩ ይችላሉ በሚል  ጥርጣሬ ደራሲው በእጁ የሚገኙትን የድራማዎቹን ፅሁፍ አሰባስቦ በመፅሐፍ መልክ በማሳተሙ  የዚያን  ዘመን የአፋን ኦሮሞ ሬድዮና ቴሌቪዥን  ድራማዎች ምን መልክ እንደነበራቸው ለተተኪው ትውልድ  እንዲተላለፍ ለማድረግ ያደረገው ጥረት ነው፡፡

ሌላው በመፅሐፍ  መልክ  የማስቀመጡ ጥቅም የቋንቋው  ተጠቃሚዎችና  የአፋን  ኦሮሞ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲሁም የአፋን ኦሮሞ  ፊልም  ስራዎች አነሳስና  ዕድገት ጥናት ማድረግ  ለሚፈልግ የቋንቋው ተመራማሪዎችእንደ  መነሻ ሐሳብ  ሊረዳቸው  ይችላል በሚል ግንዛቤ  ለህትመት አብቅቷል፡፡

ደራሲ  ኢሳያስ“አሊ በርኪ ጎታ ኦሮሞ “ (አሊ በርኪ የኦሮሞው ጀግና) የተሰኘውንም እውነተኛ ታሪክ 2008 ዓ.ምአሳትሞ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ ይህ 129  የገፅ ብዛት  ያለው መፅሐፍ  በ1969 ዓ.ም. ወራሪው የሞቃዲሾ ሶማሊያ መንግስት የምስራቁን የሀገራችንን ክፍል በኃይል  ወሮ በያዘበት ዘመን ከምዕራብ ወለጋ ቤጊ ከተባለው ወረዳ በሚሊሽያነት ተመልምሎ በታጠቅ ጦር ሰፈር ሰልጥኖ  ወደ ምስራቅ ጦር ግንባር በመዝመት የወራሪውን አምስት ታንኮችንና ብዙ ወታደሮችን በመማረክና በማስወገድ ከፍተኛ የጀግንነት ተግባር ፈፅሞ ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማሪያም እጅ  የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን  የተሸለመ ጅግና እውነተኛ ታሪክ  የሚያወሳ አምስተኛው ደራሲ ኢሳያስ  ለህትመት ያበቃው መፅሐፍ ነው፡፡


ይህ የጀግነው ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ የጀግንነት ታሪክ መፅሐፍ የእህቱ ልጅ በሆነችው ጋዜጠኛ ጥሩወርቅ ካሳ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በ2013 ዓም ለአማርኛ አንባብያን እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ 

ከዚህም በቀር ”ኢጆሌ ሜሀዱቢስኑ”የተባለውንየአፋን ኦሮሞ   የልጆች መፅሐፍ፣እንዲሁም፣“ወርቅ የማፍራት ጥበብ”“እና“አደሞ” የተባሉትንም የአማርኛ መፅሐፍትእንዲሁም “ ጉልሻን ፋጡማ “ የተሰኘውን መንፈሳዊ  እውነተኛ አስደናቂ የህይወት ምስክርነትየሚተርክ ፅሑፍ ወደ አፋን ኦሮሞ ተርጉሞ ለህትመት አዘጋጅቷል፡፡

ከዚህም በቀር“የፍቅር ደም ! “ የተሰኘውንም አንድ የወንጌል አገልጋይ በክፉ መናፍስት ዓለም ውስጥ ሆኖ እርኩሳን  መናፍስትን ያገለግል  በነበረበት ዘመን እየሱስ  ክርስቶስ ተገልጦለት  እንዴት ከዚያ እንዳስመለጠውና  የአውሬው ( 666) )አገልጋዮች በሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ጥፋትና የክፋት አሰራራቸውን የሚያጋልጥ 140 ገፅ ብዛት  ያለው እውነተኛ አስገራሚና አስደናቂ ታሪክ ያዘለ  መፅሐፍ  በአማርኛና ባፋን ኦሮሞ በመፃፍ  ለህትመት አዘጋጅቷል፡፡ ይህም በቅርብ ጊዜ ታትሞ ለአንባቢያን እንደሚቀርብ ተስፋ ያደርጋል፡፡

ከዚህም በቀር”ነሙማፊ አሶሳሞታ ጋጋባቦ ገረ ቢራ“ የተሰኘውን የአጫጭርየአፋን ኦሮሞልበ ወለዶች ስብስብከሌሎች ኦሮሚያ ደራሲያን ማህበር ደራሲያን ጋር በህብረትበመሆን ድርሰቶቻቸውን በማውጣጣት የሱቢ የህትመት ድርጅት ባደረገው የገንዘብ  ድጋፍ በ2003 ዓ.ም. በማሳተምስድስተኛውን ድርሰቱናለአንባቢያን  ያቀረበበ ትመፅሐፍ ነው፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ኢሳያስ ሆርዶፋ ሚጀና ከላይ ለአፋን ኦሮሞ ስነ ፅሑፍ ላበረከተው የረዥም ዘመን አስተዋፅኦው የካቲት 27 ቀን 2013 ዓም.በአንድነት ፓርክ በተደረገው የሜዳሊያ ሽልማት አሰጣት ሥነ ሥርዓት ላይ ከክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እጅ ;አሻራችሁን አሳርፋችኋልና ትመሰገናላችሁ;የሚል የተፃፈበት የክብር ሜዳሊያ ከመላው ኢትዮጵያ ለተመረጡ ለአርትና ስነ ፅሁፍ አስተዋፅኦ ካበረከቱ ታላላቅ ሰዎች አንዱ በመሆን ሊሸለም በቅቷል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ኢሳያስ ሆርዶፋ ባለ ትዳርና የአራት ወንድ ልጆች አባት ሲሆን  በአሁኑ ወቅት በሰበታ ከተማ ገዳ ፋጂ 03 ቀበሌ የጤና ባለሙያ ከሆነችው የትዳር ጓደኛው ሲስተር እታለም ብርሃኑ ጋር  በሰሩት የግል  መኖሪያ ቤታቸው  በመኖር ላይ ይገኛል፡፡














አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች