81. ሰብስቤ አበበ -sebsebe abebe
አባ ጃምቦ /1000 ክፍል የዘለቀ/ የአፋን ኦሮሞ የሬድዮ ድራማ ደራሲ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ 1000 ተከታታይ ክፍል ያለውን በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥነውን አባ ጃንቦ የተሰኘውን ድራማ በትጋት በመድረስ ይታወቃል፡፡ በአፋን ኦሮሞ የሬድዮ ድራማ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ እያኖረ ያለው ሰብስቤ አሁንም ከጽሁፍ አለም አልወጣም፡፡ በስነ-ጽሁፍና በሬድዮ ድራማ ዘርፍ ትልቅ ስራ የሰራው ሰብስቤን በእንዲህ መልኩ ታሪኩን እናቀርባለን፡፡
ሰብስቤ ማነው?
ሰብስቤ አበበ
ይባላል፡፡ በወርሀ ግንቦት 1968 ዓ.ም. አርሢ ሄጦሣ ቦሩጃዊ በምትባል ትንሽዬ የገጠር ከተማ ተወለደ፡፡ አንደኛ ደረጃና
የቄስ ትምህርቱን እዚህች ትንሽዬ ከተማ ውስጥ የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ "ሁሩታ"
የምትባል ከተማ ውስጥ ተከታትሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ
አግኝቷል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ
ተማሪ ሆና "አለቃ ሠርጡ" በሚል የብዕር ስም ለሚኒ ሚዲያ ጽሁፍ ያቀርብ ነበር፡፡ በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲ 1ኛ
አመት ተማሪ እያለ በአፋን ኦሮሞ "አባ ጃንቦ" የተሰኘውን ድራማ መጻፍ ጀመረ፡
በትምህርቱ ደግሞ የዋዛ አልነበረም
ሰብስቤ ያለ አባት
በእናቱ ያደገ ሲሆን ልጅነቱንም በደስታ ያስታውሰዋል፡፡ ያኔ በልጅነት ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ በትምህርቱ ደግሞ
የዋዛ አልነበረም፡፡ ደብል መትቶ ወይም በአንድ አመት 2 ክፍል
አልፎ ነበር የገባው፡፡ ሰብስቤ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲያስበው መምህር የመሆን ፍላጎት አድሮበት ነበር፡፡ በልጅነቱ እኩያ ጓደኞቹ ኳስ ሲጫወቱ እንደኮሜንታተር ሆኖ ሲያገለግል
የነበረው ሰብስቤ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ችሎ ነበር፡፡ ሰብስቤ ለእናቱ ታላቅ ፍቅር ከማሳደሩ የተነሳ ማገዶ በመልቀም
ትልቅ እገዛ ያደርግ ነበር፡፡
ወደ ኪነት አለም መዝለቅ
ሰብስቤ አበበ አፉን
የፈታው በአማርኛ ስለነበር በኢትዮጵያ ሬድዮ ይቀርቡ የነበሩ የትረካ መሰናዶዎችን ጥሞና ሰጥቶ ይከታተል ነበር፡፡ በተለይ
ለደጀኔ ጥላሁን ታላቅ አክብሮት ነበረው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከገባ
በኋላ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ክህሎቱን በሚገባ በማሳደግ የተለያዩ ጽሁፎችን መጻፍ ችሎ ነበር፡፡ አባ ጃንቦ የተሰኘውን ለ20
አመታት ወይም 1040 ክፍል የዘለቀውን ድራማ መጻፍ የጀመረውም ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ ነበር፡፡ በዚህ አይነት መንገድ
ሰብስቤ የደራሲነቱን አለም በይፋ ተቀላቀለ፡፡
ሰብስቤ አበበ ደራሲ
ብቻ አይደለም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንደጨረሰ "አባጃንቦ" የሬዲዮ ድራማ በሚተላለፍበት ሬዲዮ ፋና
በጋዜጠኝነት ተቀጠረ፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያውም እጅግ የተዋጣለት ጋዜጠኛም ነው፡፡ በተለይ አዳዲስ እና ተወዳጅ የሆኑ ፕሮግራሞችን
በመፍጠርና በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች በማቅረብ እራሱም በማዘጋጀት ጣቢያው ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን አድርጓል፡፡
አባ ጃምቦ ሲጀምር
ሰብስቤ በ1992 አ.ም አባ ጃምቦን ሲጀምር እርሱን ጨምሮ 2 ተዋናዮች
ብቻ ነበሩ፡፡ ዳንሴ አበራና ራሱ ደራሲው ሰብስቤ አበበ ፡፡ ዳንሴ አበራ የአባ ጃምቦን ልጅ ፋጤን ወክላ የተጫወተች ሲሆን ዛሬ
ስለዚህ ድራማ ስትጠየቅ ይገርማታል፡፡ በዚህ ድራማ ላይ እኔ ራሴ ተውኜ ብቃቴን ማስመስከር አለብኝ በሚል ውሳኔ ገብታ
የእውነትም ጥሩ ስራ መስራት መቻሏን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
ሌሎች ድራማዎች………
ደራሲና ጋዜጠኛ
ሰብስቤ አበበ ከ"አባጃንቦ" ታሪካዊ ድራማ ሌላ ከ100 በላይ ሌሎች ረጃጅምና አጫጭር የሬዲዮ ድራማዎችን ጽፎ
አዘጋጅቶና ተውኖ ለህዝብ ጆሮ አድርሷል፡፡ ጽፎ ካስደመጣቸው ድራማዎች መካከልም ሀወን ፣ ኢልኪ ፣ ፌንሳ ፣ ፊዮሳ ፣ ቆብቆቢ
፣ ኩሪሳ ፣ ሱቢ ፣ ቆጫ ፤ ሀጃቢ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከ10
የሚበልጡ የቴሌቪዥን አጫጭር ድራማዎችንም ጽፏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማርኛ የተጻፉ በድርጊት የተሞሉ የጀብድ ዘውግ ያላቸው 3
ፊልሞች ተጠናቀው በእጁ ይገኛሉ፡፡እንዲሁም ለህትመት ያልበቁ ዳጎስ ያለ ገጽ ያላቸው...3 በአማርኛ ፡ 2 በአፋን ኦሮሞ ፡
እንዲሁም 1 በእንግሊዝኛ የተጻፉ... በፍልስፍና በስነ-አምልኮ እና በስነ- አእምሮ ላይ ያተኮሩ "ታሪክ
ቀመሥ" ል'ቦለድ መጽሀፎች አሉት፡፡
በተለይ አሁን
በቅርቡ ለህዝብ አይንና ጆሮ የሚበቃ በ"ባንክ ሥራ" ላይ ትኩረት ያደረገና በአማርኛ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ
የሚቀርብ ረጅም የሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማ ከባንክ ባለሙያ ጓደኛው አፈወርቅ ደረበ ጋር አጠናቅሮ ጨርሷል፡፡
ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብከው አባ ጃምቦ
.ደራሲና ጋዜጠኛ
ሰብስቤ አበበ "አባ ጃምቦ" ድራማን ያለምንም ክፍያ ያለማቋረጥ በየሣምንቱ ለ20 አመታት በተከታታይ
ጽፏል፡ተውኗል፡አዘጋጅቷል፡ዳይሬክት አድርጓል፡፡ በወቅቱ አይነኬና አሥፈሪ የነበረውን የወያኔ ኢህአዴግ መንግሥትና ሥርአትን
በቆራጥነት ተጋፍጧል፡ ተችቷል፡፡ አጋልጧል፡፡ ደራሲው በድፍረትና
በቆራጥነት እውነትን ስለፃፈና... በዚህም ምክንያት ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ እስከ ዝቅተኛ ካድሬዎች ድረስ
ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ይደርሰው ነበር፡፡
ከተለመደው አጻጻፍ ውጪ "አባጃንቦ" አማርኛና ትግረኛ
ቋንቋዎችን በመጨመር አንድነትን ሰብኳል፡፡ "ኢትዮጵያዊነት" በተለይ በድርጅቱ ውስጥ ነውር በነበረበት ወቅቱ
አባጃንቦ ኢትዮጵያዊነትን በስነጽሁፍ ከሽኖ ያነበንብ ነበር፡፡ በዚህ ድፍረቱም የተነሣ የወቅቱ መንግሥት ልሣን የሆነው ሬዲዮ
ፋና ደራሢው ሌሎች ተራ ጋዜጠኞች የሚያገኙትን ጥቅማጥቅሞችና አርከን እንዳያገኝ አድርጓል፡፡
ይህ የሥነ-ጽሁፍ
"ከራማ" ያናወዘው ደራሢና ጋዜጠኛ" በአባ ጃምቦ" ድራማው ከ7 ከፍተኛ አለማቀፋዊና ብሄራዊ የሽልማት
ድርጅቶች የዋንጫ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ "አባ ጃንቦ" ድራማ ለ2 የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችና ለ1 የሁለተኛ
ድግሪ ተማሪ የመመረቂያ ጽሁፍ ሊሰራበት ችሏል፡፡
.በአፍሪካ
በርዝመቱና በተወዳጅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው የሬዲዮ ድራማን የደረሰ፡የተወነና ያዘጋጀ ደራሢና ጋዜጠኛ እንዲሁም አሁን ለኢትዮጵያ
የረጅም ድራማ ጸሀፍት የአጻጻፍ ዘዴ"Method " ፈር ቀዳጅ የሆነው ደራሢና ጋዜጠኛ ሰብስቤ አበበ ለ20
አመታት በተከታታይ በመጻፉ ታላቅ ሬድዮ ድራማ ጸሀፊ ያደርገዋል፡፡
በየካቲት 2012 በአባ ጃምቦ ድራማ ላይ ለተሳተፉ ተዋናዮችም የተለያዩ የእውቅና የምስከር ወረቀቶች እና ከ50 ሺህ
እስከ 100 ሺህ ብር ሽልማት በፋና ብሮድካስቲንግ ሊበረከት
ችሏል፡፡ ከ5 አመት በፊት አንድ ሰው ፌስ ቡክ ገጹ ላይ ለሰብስቤ አበበ ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ይላል
‹‹…….ከስሙ
መጠሪያ ይልቅ የሚታወቅበት “አባ ጃምቦ” በሚለው
ተከታታይ የኦሮምኛ የሬድዮ ድራማ ነው፡፡ በፋና ብሮድካስቲንግ
ኮርፖሬት እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለውን ይህንን ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ለ20 ዓመታት ያለማቋጥ
ጽፏል፡፡ በተውኔቱ ላይ ወጣት ሆነው የተሳተፉ ተዋንያን ጎልመሰዋል፣ ጎልማሶች አርጅተዋል፡፡ እሱም የጉርምስና ዘመኑን
ፈጅቶበታል፡፡›› ይልና ጸሀፊው ሀሳብ መስጠቱን ይቀጥላል፡፡
‹‹….20 ዓመት ሙሉ
በየሳምንቱ እየጻፉ፣ ድራማ እያዘጋጁ መኖር አድካሚ ቢሆንም ያስቀናል፡፡ ምናልባትም አሜሪካዊ ወይ እንግሊዛዊ ወይ አፍሪካዊ ቢሆን ስለዚህ ጸሃፊ ብዙ እንሰማ ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ እራሱ
ያወኩት በቅርብ ቀን ነው፡፡ አመናችሁ አለመናችሁም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብስቤ- ለ20 አመታት በየሳምንቱ ድንቅ ታሪኮችን ለአድማጭ አቀርቧል፡፡ ዛሬም
አባ ጃምቦ በኢትዮጵያ ሞገድ ላይ ያለ ከልካይ፣ እንደተወደደ ይናኛል፡፡ ሰብስቤ አበበም ይጽፋል፡፡ እዩኝ፣ እወቁኝ፣ ይህን
ያህል ጽፌያለሁ አይልም፡፡ በየጋዜጣው በየቲቪው ልታይ ብሎ አይወጣም፡፡
‹‹…..ዝም ብሎ
ይጽፋል፡፡ “አንተ እንዴት ቻልከው ይህን ሁሉ ዓመት ?`` ሲሉት ``ስራ አይደል`` ይላል፡፡ ``ተሸልመህ ወይም ስራህ
ተከብሮልህ ያውቃል?`` ሲባል ``ክብሬ ስራዬ ነው`` መልሱ፡፡ “እኔ መኖር መጻፍ ነው ስራዬ” ይላል፡፡
‹‹….እሱ በአባ ጃንቦ ስሜቱን፣ እምነቱን፣ ንዴቱን ፣ ደስታውን
ይተርካል፡፡›› ሲል የፌስ ቡክ ላይ ጸሀፊው ለሰብስቤ ያለውን ታላቅ አክብሮት ይገልጻል፡፡
ሰብስቤ አባ ጃምቦን
ለመጻፍ እንደመነሻ የሆነው በአብርሀም ወልዴ በኢትዮጵያ ሬድዮ ሲተላለፍ የነበረው ድራማ ነበር፡፡ ሰብስቤ ከልቦለድ ድርሰቶች ለወንጀለኛው ዳኛ የተለየ
አክብሮት እንዳለው ይናገራል፡፡
ሰብስብ አሁንም
ብእር ከወረቀት ማቆራኘቱን ቀጥሏል፡፡ አሁንም እንደድሮው ይጽፋል፡፡ ቀይ አፈር የተሰኘ በአማርኛ የተጻፈ ልቦለድ በቅርቡ
ይታተማል፡፡ the sender በሚል ርእስ የጻፈው የእንግሊዝኛ መጽሀፍም የህትመት ብርሀን ማየቱ አይቀርም፡፡ የ4 ልጆች አባት
የሆነው ሰብስቤ አበበ ከኪነ-ጥበብ ሙያ ውጭ ሌላ ስራ ርካታ
አይሰጠውም፡፡ ይህን ርካታውን የበለጠ ለማድረግ ደግሞ ቀን ከሌት ይሰራል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ