80. አስቻለው ጌታቸው  ወሰኔ -Aschalew Getachew Wossenie

           ‹‹ኢትዮጵያን እንቃኛት›› የአስቻለው መለያ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 22 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል  ጋዜጠኛ አስቻለው ጌታቸው ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያን እንቃኛት በተሰኘው ፕሮግራሞ በርካታ ቦታዎችን ያስጎበኘው አስቻለው ከየት ከየት ተነሳ ? ማነው?

   ትውልድ እና ልጅነት፤ ትምህርት 

አስቻለው ጌታቸው  የተወለደው በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሐገር ገናሌ አውራጃ አዳባ ከተማ ነው ። እንደማንኛውም በትንሽ ከተማ እንደሚኖር ልጅ ደስ የሚል የልጅነት ጊዜ እንደነበረው ያስታውሳል።

- አብዛኛውን የልጅነትና የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈውም ከአያቱ እማሆይ ሂሩት ዱባለ ጋር ነበር። የአያት ልጅ ቅምጥል የሚባለው ግን እርሳቸው ጋር አይሰራም፡፡ ሽር አድርገው ነበር ያሳደጉት። የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በ ዲንሾ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ጎባ ሚሽን ትምህርት ቤት ነበር የተከታተለው ።

- የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ አዳባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ።

- በወቅቱ ማትሪክ ተፈትኖ ለእረፍት አዲስ አበባ በመጣበት አጋጣሚ እረፍቱ ረጅም ስለነበር አባቱ ፓስተር አንዳርጌ ጋራዥ እንዲለማመድ አስገብተውት እንደነበረ ያስታውሳል ።

        ዩኒቨርሲቲ የሚድያ ጉዞ

- በአጋጣሚ ማትሪክ ሲመጣ ውጤቱ ዩኒቨርሲቲን በዲግሪ መርሐ-ግብር የሚያስገባ ባለመሆኑና መምህራን ኮሌጅ ገብቶ ከሚማር  እዚያው እየሰራ የማታ ትምህርቱን እንዲከታተል ሐሳብ ከቤተሰብ በመምጣቱ ወዲያው አፍሪካ ትራንስፖርት የሚባል ድርጅት ሥራ ጀመረ።

- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታ ሥነ -ፅሁፍ መማር የጀመረው አስቻለው ከአሁኑ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እና ከሌሎች ጋር ትምህርቱን መከታተል ቀጠለ።

 የልጅነት ትልቁ ጉጉት  ሾፌር መሆን እንደነበር ያስታውሳል ። በወቅቱ የሚመጡ አዲስ ሞዴል መኪናዎችን በሽቦ በመስራት በማሽከርከር የሚቀድመውም አልነበረም ።

- ስለ ጋዜጠኝነትና ጋዜጣ ያወቀው ባሌ አዳባ ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ ነበር ። አብረውት ይማሩ ከነበሩት ውስጥ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የሚሳተፉ  ልጆች ስለነበሩ  ጋዜጣውን እንዲያነብ ዕድል ፈጥረውለታል ። ከዚያም ቀስ በቀስ እራሱ ለጋዜጣው መልዕክቶችን በመላክ መሳተፍ ጀመረ ። ከጋዜጣው በተጨማሪ በሬዲዮ መሳተፍ ቀጠለ። ከተማዋ ትንሽ ስለነበረችና በሬዲዮ የሚያደርገው ተሳትፎ በመምህራኖቹ በመታወቁም የትምህርት ቤታቸው ጋዜጠኛ እንዲሆን ዕድል ተፈጠረለት። ጠዋት ጠዋት ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል አደባባይ ላይ በመውጣት መረጃዎችን ያቀርብ ነበር ።

- 12ኛ ክፍል ማትሪክ ወስዶ አዲስ አበባ እንደመጣ ስልክ ቁጥሩን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በማውጣት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባብያን ክበብ አቋቁሟል ። ክበባቸውንም ከአንባብያን ክበብነት ወደ አማተር የጋዜጠኞች ክበብ በማሳደግ " ውበት አማተር የጋዜጠኞች ማህበርን " ከቡድኑ ጋር መሠረቱ ። ውበት አማተር የጋዜጦች ማህበር በመላ ሐገሪቷ 42 ከተሞች ቅርንጫፍ ክበባት ነበሩት ። በርካታ ጋዜጠኞችን በማፍራት ብዙ ሚዲያዎች ላይ በመስራትም ላይ ይገኛል ።

- አስቻለው አንድ ዓመት ዩኒቨርስቲ  እንደተማረ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም የሆነው ያኔ ማስ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ተከፈተ ። እዛ ተወዳድሮ  ሲያልፍ ሥራውንና የዩኒቨርስቲ የማታ ትምህርቱን ትቶ የቀን ተማሪ ሆነ ። በሬዲዮ ጋዜጠኝነትም በዲፕሎማ ተመረቀ ። ጊዜውም ከ1989-1990 ነበር፡፡

- ማስ ሚዲያ በግል ከገቡት ጥቂት ተማሪዎች በስተቀር አብዛኞቹ ከተለያዩ ሚዲያዎች በስራ ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ነበሩ ። በትምህርትም ከዲፕሎማ እስከ ማስተርስ የያዙ ነበሩ ። አንዳንዶቹ እንደውም የአስተማሪዎቻቸው ባቾች ናቸው፡፡ ታድያ ይሄ ለጀማሪዎች ከውጤት ጋር ተያይዞ ጫናው ከባድ እንደነበረ አይዘነጋውም ።








           ‹‹ኢትዮጵያን እንቃኛት›› የአስቻለው መለያ

-  በ1990 በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ተመርቆ ሥራ የጀመረው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው ። ‹‹ኢትዮጵያን እንቃኛት›› ፕሮግራም በፍቅር የሰራው ፕሮግራም ነው ። ለ10 ዓመት የፕሮግራሙ አዘጋጅ ሆኖ አገልግሏል ። ይህ ፕሮግራም በ1987 አየር ላይ መዋል የጀመረ ሲሆን አስቻለው በ1991 ከተቀላቀ ወዲህ በርካታ ቦታዎችን አስቃኝቷል፡፡  ‹‹ኢትዮጵያን እንቃኛት›› ሰኞ ማታ 3ሰአት ላይና  ማክሰኞ ጠዋት ይቀርብ የነበረ መሰናዶ ነበር፡፡ አስቻለው ከኢትዮጵያን እንቃኛት በተጨማሪም ብዙ ፕሮግራሞችንም አሰናድቷል ። ‹‹ኢትዮጵያን እንቃኛት›› በርካታ የሀገሬን ክፍል በሚገባ እንዳይ አድርጎኛል የሚለው አስቻለው ይህም በጋዜጠኝነቱ ስራ ይበልጥ እንዲገፋበት አድርጎታል፡፡ ፊልድ/መስክ/ አንድ ጊዜ ሲሄድ ለበርካታ ፕሮግራሞች የሚሆኑ ስራዎችን ይዞ እንደሚመጣ አስቻለው ይናገራል፡፡  አስቻለው በሳምንት እስከ 4 ፕሮግራሞችን አየር ላይ ያውል የነበረ ሲሆን በ ቅዳሜ የወጣቶች ፕሮግራም ላይም አቅሙን ሳይቆጥብ ይሰራ ነበር፡፡   

- በወቅቱ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴለቪዥን ድርጅት ይባል ስለነበር ቢፒአር ሲሰራ የመልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ ፕሮግራሞች ኤዲተር ሆኖ የተመደበው ጋዜጠኛ አስቻለው ነበር ። ከሬዲዮ ስራ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቴሌቪዥን ስራ የተዛወረውም በዚያ ወቅት ነበር።  ከቱሪዝም በአንዴ ወደ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ርዕሰ- ጉዳይ መግባት ከባድ ሆኖበት ነበር ። የቴሌቪዥን ሥራን ማወቅ አለብኝ በማለት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመስራት ጥረት ማድረጉን ግን አላቆመም። በዚያው አጋጣሚ ከካናዳ በመጣ ባለሙያ ስለ ዶክመንተሪ ስልጠና የመሳተፍ ዕድል አገኘ ። የተወሰኑ ዶክመንተሪ ፕሮግራሞችንም ሠራ ። ለቴሌቪዥን ሥራ እንግዳ እንዳልሆን ዕድል ሰጥቶኛል ይላል ያንን ጊዜ ሲያስታውስ ።

               ምርጥ አለቆች-ነጋሽና ብርቱካን 

ለእኔ የተለየ ስሜት ያለው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ነው ይላል ጋዜጠኛ አስቻለው። የነጋሽ ስክሪፕት የቋንቋው ቃና ብቻ ሳይሆን ዜናውን በምስል የማየት ያህል ምስል ከሳች ነው ስለዚህ ነጋሽ የተለየ ጋዜጠኛ ነው ለኔ ይላል ። በተለይ የሳምንቱን ታላቅ ዜና ሲሰራ  ዶክመንተሪ ፊልም የማየት ያህል ስሜት እንደሚሰጠው ይናገራል። ስለ ዲያና አሟሟት የሰራው ትንታኔ ትምህርት ቤት ስለ News Analysis ሲማር ማስተማሪያ እንደነበረም ያስታውሳል ። ምንም እንኳን ፕሮግራም ላይ ብሰራም ነፍሴ የዜና ናት የሚለው ጋዜጠኛ አስቻለው ፕሮግራም ላይ የቆየው ለኢትዮጵያን እንቃኛት ፕሮግራም ሲል ነበር። ። እንደዛም ሆኖ ለፕሮግራም የሚሰራው ኢንተርቪው ላይ ዜና መስራት ያስደስተዋል ። ለዜና ዘገባም ብዙ ጊዜ ሪፖርት ይላካል ። የዜና ክህሎቱን በማሳደግ ጉልህ ሚና የነበራት ደግሞ ጋዜጠኛ ብርቱካን ሀረገወይን ነበረች፡፡ ለዚህ ውለታዋ ምስጋናን ሳይቸራት አያልፍም። ምርጥ አርታኢ ናት ብሎም አድናቆት ይቸራታል፡፡

       ጉዞ ወደ ራስ ስራ

- ጋዜጠኛ አስቻለው ከሰራቸው ፕሮግራሞች በጣም የሚወደው ብዙ ቢሆንም በጣም የማልረሳው የሚለው ግን ራስ ደጀን ተራራ 3 ቀን በእግር ተጉዘው ከተራራው አናት ላይ ሆኖ የተሰማው  ስሜት እና ያንን ስሜት ለአድማጩ ለማጋባት የተጠቀመው መንገድ እርካታን የሚፈጥርለት የተለየ ገጠመኙ ነው። እንዲሁም አውራምባ ማህበረሰብ ሄዶ ከሴት አርሶአደሮች ጋር የነበረው ወግ ከውስጡ የማይወጣ ነበር ።  ከጋዜጠኝነቱ ትምህርት ባሻገር  በ1999 በቢዝነስ አስተዳደር ዲግሪውን የያዘው አስቻለው አንድ ቀን የራሴን ድርጅት መመስረት አለብኝ ብሎ ያልም ነበር፡፡ ይህንን ህልሙንም በ2006 ከ 7 አመት በፊት እውን አድርጎታል፡፡ አጠቃላይ ለ14 አመት ተቀጥሮ የሰራው አስቻለው አሁን የራሱን ስራ ፈጥሯል፤፡ 

-ጋዜጠኛ አስቻለው አሁን ማውንቴንስ ሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን የሚባል ድርጅት በማቋቋም በቱሪዝም ፣ ባህልና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በማተኮር የሬዲዮ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚያዘጋጅ ሲሆን ። ‹‹ውዳሴ›› የምትል መፅሔትም እንዲሁ ያዘጋጃል ። በሬዲዮ እያስተላለፈ የሚገኘው  የዱር ህይወት ፕሮግራምን በቴሌቪዥን ለመጀመር ቅደመ- ዝግጅት እያጠናቀቀም ይገኛል።  አስቻለው የአካባቢ ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት እንደመሰጠቱ የደኖች መጨፍጨፍና መራቆት ሀሳብ ውስጥ ይከተዋል፡፡

  በሰው ልጅ እኩልነት ፤ በሰብአዊነት ታላቅ እምነት ያለው አስቻለው እኔ የአለም ዜጋ ነኝ የሚል አመለካከት አለው፡፡ ይህ እሳቤ በተለየ መልኩ ከቼኩቬራ የሚመዘዝ መሆኑንም ያስረዳል፡፡ ስለሆነም በዋናነት የሰው መለኪያ ሰብአዊ ፍጡር መሆን ነው ብሎም ያምናል፡፡ ጋዜጠኛ አስቻለው የ2021 የዓለም የሬዲዮ ቀን አስመልክቶ EBC ባዘጋጀው ውድድር ላይ በሬዲዮ ፕሮዳክሽን 1ኛ ሆኖ ተሸልሟል ። ጋዜጠኛ አስቻለው የ2 ልጆች አባትም ነው፡፡











አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች