79. መሳይ ወንድሜነህ-በቀለ -Messay Wondimeneh Bekele
የዚህ ታሪክ
አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ
፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ
እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ
የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡
ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ
tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ
ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ
ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና
ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን
ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ
የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡
በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 15 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት ብርቱ እና ሁለገብ ጋዜጠኞች መካከል መሳይ ወንድሜህ አንዱ ነው፡፡
መሳይ ወንድሜነህ
(በጥር 17 ቀን 1974 ዓ.ም ተወለደ) በኢትዮጵያ የብሮድካስት ሚዲያ ውስጥ ከሚታወቁ ጋዜጠኞች መካከል ይጠቀሳል፡፡ መሳይ
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት) ኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 እና
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አዘጋጅቶ በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞቹ ይታወቃል፡፡ ከሬዲዮ "የዘፈን ምርጫ"፣ "ዜማ
እና ዜመኞች"፣ "ዜማ በየፈርጁ"፣ "የብዕር ትሩፋት" እና "የኤች. አይ. ቪ.
የቀጥታ ውይይት" የመሳሰሉ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ሲታወቅ፤ በቴሌቪዥን ደግሞ በ"የእሁድ መዝናኛ" እና
"አርሂቡ" ፕሮግራሞች ብዙዎች ያውቁታል፡፡
ከ2011 ዓ.ም
ወዲህ ደግሞ በግሉ "ማን ከማን - ከመሳይ ጋር" በተሰኘ የቴሌቪዥን ቶክሾው አዘጋጅ እና አቅራቢነት እየሰራ
ይገኛል፡፡
መሳይ ወንድሜነህ
አጭር የኋላ መረጃ
ውልደት ጥር 17
ቀን 1974 ዓ.ም
አርባ ምንጭ፣
ኢትዮጵያ
ሙያ • ጋዜጠኛ
• የቶክሾው አቅራቢ
• መድረክ መሪ
• የኮሙኒኬሽን
ኤክስፐርት
• የሰላም እና
ደህንነት ባለሙያ
መለያዎች • ኢቲቪ
• ኤፍ ኤም አዲስ
97.1
• ፋና ኤፍ ኤም
98.1
• ኢቢኤስ
• አቦል ቲቪ
(ዲኤስ ቲቪ)
ውልደት እና እድገት
መሳይ ወንድሜነህ
በቀለ ከአባቱ መቶ አለቃ ወንድሜነህ በቀለ እና ከእናቱ
ኢንስፔክተር ዘነበች አህመድ በጥር 17 ቀን 1974 ዓ.ም በአርባ ምንጭ፣ ኢትዮጵያ ተወለደ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን
በሲቀላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኩልፎ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡
ለጋዜጠኝነት እና
ስነ-ጽሑፍ በነበረው ዝንባሌ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይማር በነበረበት ወቅት ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ሚኒ-ሚዲያን
ጨምሮ በልዩ ልዩ ክበባት ውስጥ ይሳተፍ ነበር፡፡ አጭር የጋዜጠኝነት ስልጠናም ተከታትሏል፡፡
በ1993 ዓ.ም
12ኛ ክፍልን እንዳገባደደ የከፍተኛ ትምህርቱን ጋዜጠኝነትን በማጥናት መቀጠል ቢፈልግም፣ በወቅቱ በነበረው አሰራር በትምህርት
ሚኒስቴር ምደባ ወደ ጂማ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በአካባቢ ጤና ባለሙያነት ሰልጥኖ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ይሁን እንጂ በጂማ
ቆይታውም ቢሆን ከመደበኛ ትምህርቱ በተጨማሪ በዪኒቨርሲቲው የኪነ-ጥበባት ክበብ (በኋላ የኪነጥበብ ማዕከል) ውስጥ የነቃ
ተሳትፎ በማድረግ የማዕከሉ ሊቀመንበር በመሆን ጭምር አገልግሏል፡፡
የስራ ሁኔታ
መሳይ ወንድሜነህ
ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በ1996 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ በጤና ሚኒስቴር ተመድቦ በደቡብ ክልል፣ ጋሞ ጎፋ ዞን፣ ጎፋ ወረዳ (በአሁኑ
ጎፋ ዞን) የአካባቢ ጤና ኤክስፐርት በመሆን አገልግሏል፡፡ ነገር ግን በጋዜጠኝነት ሙያ ለመስራት ከነበረው ጥልቅ ፍላጎት
የተነሳ ስራውን ከሰባት ወራት በላይ ሊሰራ አልቻለም፡፡ በ1997 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት
ለኤፍ. ኤም. አዲስ 97.1 ሪፖርተሮችን ለመቅጠር ያዘጋጀውን ፈተና ከተፈተነ በኋላ፣ ውጤቱን እንኳ ሳያውቅ ስራውን በመልቀቅ
ወደ አዲስ አበባ ጠቅልሎ ገባ፡፡ ወቅቱ የ1997 ምርጫ ወቅት ስለነበር ይሁን በሌላ ምክንያት በአመቱ አጋማሽ የተወዳደረበት
ፈተና ውጤት በቶሎ ካለመገለጹ ውጪ የፈተናው ውጤት ይፋ ሲደረግም ከተመረጡ አራት ተፈታኞች መካከል ስሙ አልነበረም፡፡
በተጠባባቂነት ነበር የተያዘው፡፡ ምንም እንኳን ትቶት የመጣውን ስራ ተመልሶ መስራት ቢችልም፣ የሚወደውን የጋዜጠኝነት ስራ
ለመስራት ከነበረው የጸና ፍላጎት የተነሳ ለስድስት ወራት ያክል በስራ አጥነት በአዲስ አበባ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜም በኤፍ.
ኤም. አዲስ እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ በተሳታፊነት የስነ-ጽሑፍ ስራዎቹን ያቀርብ ነበር፡፡
በመስከረም ወር
1998 ዓ.ም ስራ አጡ መሳይ፣ የስራ ማስታወቂያ ለመመልከት ይኖርበት ከነበረው ጎላ አካባቢ ወደ ለገሃር አካባቢ ለማቅናት
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በር ሲያልፍ ግን በተጠባባቂነት የተመረጠበትን የጋዜጠኝነት ስራ ጥሪ ማስታወቂያ ተመለከተ፡፡ ወዲያውም
አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታ አሟልቶ፣ ከመስከረም 23 ቀን 1998 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት፣ ኤፍ.
ኤም. አዲስ 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ በጀማሪ ሪፖርተርነት ስራ ጀመረ፡፡
ያለውን ተሰጥኦ እና
ዝንባሌ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ከወሰደው የ3 ወር መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ስልጠና ጋር በማዋድ ስራ የጀመረው መሳይ
ወንድሜነህ ተሰጥኦ እና ዝንባሌውን በመደበኛ ትምህርት ለማገዝ በማሰብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን
የትምህርት ክፍል የብሮድካስት ጋዜጠኝነትን በማጥናት በ2002 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቋል፡፡
በሬዲዮ ጣቢያው
በቆየባቸው 11 አመታት ከፕሮግራም አስተዋዋቂነት እስከ ዜና አንባቢነት፣ ከመዝናኛ እስከ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች፣ ከቃለምልልስ
እስከ የቀጥታ ስልክ ውይይት፣ ያልተሳተፈበት የፕሮግራም ዓይነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የሆነው በጊዜው በነበረው የሰው
ኃይል ቁጥር አነስተኛ መሆን እና ጣቢያው ይከተለው በነበረው የአሰራር መንገድ መሰረት ጋዜጠኞች በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ
እንዲሳተፉ ያደርግ ስለነበር ነው፡፡ ይህም የስራ ሁኔታም ሁለገብ ጋዜጠኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳበረከተለት መሳይ
ይናገራል፡፡ እናም በጀማሪ ሪፖርተርነት አንድ ያለው የጋዜጠኝነት ሙያውን እያሻሻለ እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅ (Deputy
Editor-in-chef) ባሉ የሙያ ደረጃዎች ላይ ሰርቷል፡፡
በኤፍ. ኤም. አዲስ
97.1 በቆየባቸው ዓመታት ይሰራቸው ከነበሩ ፕሮግራሞች መካከል "የዘፈን ምርጫ"፣ "ዜማ እና ዜመኞች"፣
"ዜማ በየፈርጁ"፣ "ትዝታን በዜማ"፣ "የብዕር ትሩፋት"፣ "የሳምንቱ
እንግዳ"፣ "ለወጣቶች"፣ "ጤና አዲስ" እና "የኤች. አይ. ቪ. የቀጥታ
ውይይት" ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
የቴሌቪዥን ፕሮግራም
አቅራቢነት አጋጣሚ
ብዙ ሰዎች መሳይ
ወንድሜነህን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን "የእሁድ መዝናኛ" እና "አርሂቡ" ፕሮግራሞች ነው
የሚያውቁት፡፡ በእርግጥ መሳይ በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ቢሰራም የኢትዮጰያ ቴሌቪዥን መዝናኛ ክፍል ባልደረባ ግን አልነበረም፡፡
ከመደበኛ የሬዲዮ ስራው ውጪ እገዛ እንዲያደርግ ተጠይቆ በፈቃደኝነት ነበር የሚሰራው፡፡ አጋጣሚው የተፈጠረውም በ2000 እና
በ2001 የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ክብረ-በዓላት በልዩ ልዩ ተቋማት ይከበር ነበር እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት
ይህንኑ በዓል ሲያከብር በመድረክ መሪነት ሲሰራ የተመለከቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አመራሮች በቴሌቪዥን አቅራቢነት እንዲያግዛቸው
ሲጠይቁት ነው፡፡ ለሬዲዮ ጋዜጠኝነት ልዩ ፍቅር ያለው መሳይ በመጀመሪያ ጥያቄያቸውን ውድቅ ቢያደርገውም፣ በቋሚነት ወደ
ቴሌቪዥን መዝናኛ ክፍል እንደሚያዛውሩት ስለነገሩት የሚወደውን የሬዲዮ ስራ ላለመልቀቅ በሀሳባቸው ተስማምቶ የቴሌቪዥን
አቅራቢነትን ስራ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በመደበኛ ስራው ላይ ደርቦ መስራት ጀመረ፡፡
ማን ከማን -
ከመሳይ ጋር
ከአስራ አንድ
ዓመታት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የስራ ቆይታ በኋላ የቅጥር ስራውን በ2009 ዓ.ም በመልቀቅ በግሉ መስራት
የጀመረው ጋዜጠኛ መሳይ፣ ከተሰማራባቸው ሙያዊ ስራዎች መካከል ማን ከማን - ከመሳይ ጋር የተሰኘው የቴሌቪዥን ሾው ዋንኛው
ነው፡፡
ማን ከማን ከመሳይ
ጋር ሾው በመጀመሪያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) አንድ ምዕራፍ ከተላለፈ በኋላ
በፕሮግራም ይዘት ላይ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር በተፈጠረ አለመግበባት ተቋርጧል፡፡ በ2013 ዓ.ም ደግሞ በአቦል ቲቪ (ዲኤስ
ቲቪ) አማካይነት ዳግም ለስርጭት በቅቷል፡፡
ልዩ ቦታ የሚሰጣቸው
ስራዎች
ጋዜጠኛ መሳይ በስራ
በቆየባቸው ከአስራ አምስት በላይ ዓመታት ልዩ ቦታ ከሚሰጣቸው ሙያዊ ስራዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
የመጀመሪያው ከኢቢሲ
ከለቀቀ በኋላ ማዘጋጀት በጀመረው ማን ከማን - ከመሳይ ጋር ሾው ላይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር
ያደረገው ቃለ-ምልልስ ነው፡፡ ልዩ ቦታ የሚሰጥበት ምክንያት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ የመጀመሪያ የአንድ
ለአንድ ቃለምልልስ የሰጡበት ከመሆኑም በላይ የብዙዎች ጥያቄዎች የነበሩ ጉዳዮች ላይ በግልጽ እና በዝርዝር የተናገሩበት
ስለነበር ነው ይላል፡፡ (
ሌላው ልዩ ቦታ
የሚሰጠው ቃለምልልስ ከኢቢሲ ከመልቀቁ አስቀድሞ፣ በኢቲቪ የአርሂቡ ፕሮግራም ላይ ከደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ ጋር መስከረም 28 ቀን
2009 ዓ.ም ያደረገውን ቆይታ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአርሂቡ ፕሮግራም በቀጥታ ስርጭት (Live) የሚተላለፍ ነው፡፡ ወቅቱ
ደግሞ በመላ አገሪቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የበረታበት ነበር፡፡ እናም ደራሲ ኃይሉን ለቃለ-ምልልስ ሲጋብዘው በወቅታዊ ጉዳዮች
ላይ የሚሰማውን መናገር የሚችል ከሆነ ብቻ ግብዣውን እንደሚቀበል ይነግረዋል፡፡ ምንም እንኳ በዚያ ጊዜ ቀጥተኛ ትችቶችን
የመንግስት ሚዲያ ባያስተናግድም፣ ጋዜጠኛ መሳይ ግን በሃሳቡ ተስማምቶ የቀጥታ ቃለ-ምልልሱን አደረገ፡፡ )ይህ የአርሂቡ
ፕሮግራም ከተላለፈ በኋላ ከመንግስት አካል የመጣ ቀጥተኛ ጥያቄ ባይኖርም፣ ጋዜጠኛ መሳይ ግን ዳግም የአርሂቡ ፕሮግራም
ሳያዘጋጅ ከኢቲቪ ለቋል፡፡
በሬዲዮ የጋዜጠኝነት
ቆይታው ከሚደሰትባቸው ተግባራት መካከል ደግሞ የፕሮግራም መግቢያ ሙዚቃ አጠቃቀም ላይ የሰራቸውን ስራዎች ነው፡፡ በቀደመው ጊዜ
እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የአገራችን የሬዲዮ ፕሮግራሞች የመግቢያ ሙዚቃቸውን ከሚታወቅ ሙዚቃ ላይ በመውሰድ ነው የሚጠቀሙት፡፡
ጋዜጠኛ መሳይ ግን ለሚሰራቸው ፕሮግራሞችም ይሁን ለሌሎች ፕሮግራሞች በሙዚቃ አቀናባሪ የተሰሩ ወጥ (ኦሪጂናል) ሙዚቃዎችን
በመጠቀም ምሳሌ መሆን ችሏል፡፡
አስተዋጽኦ እና
ሽልማት
ጋዜጠኛ መሳይ
ከአስራ አንድ ዓመታት በዘለለ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የስራ ቆይታው ለተቋሙ ባበረከተው አስተዋጽኦ መነሻነት ልዩ
ልዩ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በመደበኛ ስራው ላይ ካሳየው መልካም አፈጻጸም በተጨማሪ በፈቃዱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ
ፕሮግራሞች ላይ የነበረው ተሳትፎ በ2002 እና በ2003 ዓ.ም የአመቱ ኮከብ ሰራተኛ ሽልማትን ካገኙ ጥቂት ሰራተኞች መካከል
አንዱ አድርጎት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪ ነጻ የትምህርት እድል በተቋሙ አማካይነት በሽልማት መልክ
ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መነሻነት በ2005 ዓ.ም የሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪውን በሰላም እና ደህንነት ጥናት ዘርፍ አግኝቷል፡፡
የሰላም እና ደህንነት ጉዳይን ከሚዲያ ስራ ጋር በማስተሳሰርም በሰላም ጋዜጠኝነት እና በግጭት አዘጋገብ ዙሪያ አጫጭር
ስልጠናዎችን በኢቢሲ እና ከኢቢሲ ውጪ በሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ስር ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ መሳይ
ወንድሜነህ ለጀማሪ ጋዜጠኞች ልምዱን በማካፈል እና በጥብቅ ሙያዊ ክትትል እና ድጋፍ ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ በማገዝም
ይታወቃል፡፡
በ2000 ዓ.ም
ከተቋሙ ውጪ በተካሄደ እና ኢንተርኒውስ የተሰኘ አለማቀፍ ተቋም ባዘጋጀው የሬዲዮ ፕሮዳክሽን ውድድር ላይ በመሳተፍ አሸናፊ በመሆኑ የምስክር ወረቀት እና መቅረጸ-ድምጽ
ተሸልሟል፡፡
የጋዜጠኛ መሳይ
ሌላው መታወቂያ በታላላቅ መድረኮች ላይ በመድረክ መሪነት ያለው ተሳትፎ ነው፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን
ጨምሮ በከፍተኛ አገር አቀፍ መድረኮች ላይ በመድረክ መሪነት በነበረው ሙያዊ ተሳትፎ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡
ከእነዚህም መካከል በ2003 ዓ.ም ከወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ የተቀበለው ሽልማት
ይጠቀሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም
ሙያውን የሚያዳብሩ አጫጭር ስልጠናዎችን ቢቢሲ፣ ኢንተርኒውስ፣ ብሪጅ እና ከመሳሰሉ ተቋማት ሰልጥኗል፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ እና
የወደፊት እቅድ
ጋዜጠኛ መሳይ
በአሁኑ ወቅት በአቦል ቲቪ (ዲኤስቲቪ) የሚተላለፍ ማን ከማን - ከመሳይ ጋር የተሰኘ ቶክሾው ላይ በዋና አዘጋጅነት እና
አቅራቢነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት የማማከር አገልግሎት ለልዩ ልዩ ተቋማት
ይሰጣል፡፡ የተለያዩ አገር አቀፍ መድረኮች ላይ በመድረክ መሪነት መስራቱን ቀጥሏል፡፡
የጀመራቸውን ስራዎች
እያሳደገ መቀጠሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወደፊት በኦንላይን ሚዲያ ዘርፍ ለውጥ ማምጣት የሚችል፣ በሙያተኞች የሚመራ ተቋም የመክፈት
እቅድ አለው፡፡
የቤተሰብ ሁኔታ
ጋዜጠኛ መሳይ
ወንድሜነህ በትዳር ህይወቱ ያፈራቸው ሁለት ልጆች (ብሌን መሳይ - 12 ዓመት እና አሜን መሳይ - 7 ዓመት) አባት ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ