77. አሰፋ ይርጋለም ፈለቀ -Assefa  yirgalem Feleke

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 10 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል አሰፋ ይርጋለም ይጠቀሳል፡፡ በሚድያ ዘርፍ የአሰፋ ታሪክ የሚዘከር ሲሆን እንዲያነቡት ተጋብዘዋል፡፡      

ውልደትና ዕድገት

አሰፋ ይርጋለም ፈለቀ ትውልድና ዕድገቱ በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ አጠራር በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ውስጥ ነው፤ ጊዜው ደግሞ ጳጉሜን 1 ቀን 1972 ዓ.ም፡፡ በኢትዮጵያ ትንሿ እና አሮጌውንና አዲሱን ወደምታገናኘው ባለአምስት እና አንዳንዴም ባለስድስት ቀኗ ጳጉሜን፡፡

የአሰፋ ይርጋለም ወላጅ አባት አቶ ይርጋለም ፈለቀ በግል ሥራ የሚተዳደሩና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ትጉህ ሰው ነበሩ፡፡ እናታቸው ወ/ሮ ያለምወርቅ እንግዳ ደግሞ የቤት እመቤት ሲሆኑ ዕድሜያቸውን ሙሉ ለልጆቻቸው ደስታ ኖረው ያለፉ መልካም እናት ነበሩ፡፡ ሁለቱንም አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡

ከአቶ ይርጋለም ፈለቀ እና ወ/ሮ ያለምወርቅ እንግዳ አብራክ ከተገኙት ዘጠኝ ልጆች መካከል ባለታሪካችን አሰፋ ይርጋለም በሁለተኛው ረድፍ ላይ ይገኛል፡፡ ቤተሰቡ ካፈራቸው ስድስት ሴቶችና ሦስት ወንዶች መካከል የወንዶቹን ጎራ በታላቅነት ይመራል፡፡

በህፃንነት ጊዜው (በአራስነት ዘመን) በጣም ታማሚ የነበረው አሠፋ ይርጋለም ከበሽታው መደጋገም የተነሣ ቤተሰቡን ከሚያሰቃያቸው ምነው ሞቶ በተገላገሉት የተባለለት ህፃን ነበር፡፡ የፈጣሪ ምህረት የጎበኘው ያ ህፃን በኋላ ላይ የቤተሰቡ ደስታ እና ቤተሰቡን በመልካም የሚያስጠራ ለመሆን በቅቷል፡፡







ትምህርት

አሠፋ ይርጋለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቁስቋም ጣይቱ ብጡል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የተማረ ሲሆን በት/ቤት ቆይታውም ስነ-ፅሑፍ ፣ ግጥም፣ በትምህርት ቤት መድረኮች በማቅረብ ነበር የዛሬ ሥራውን መለማመድ የጀመረው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በየካቲት 12 አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተማረ ሲሆን፣ በትምህርት ቤቱ የሚኒ-ሚዲያ ክበብ አባል በመሆን ጋዜጠኝነትን በአማተርነት የጀመረ ሲሆን፣ በትምህርት ቤቱ የቴአትር ክበብም ከዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ጋር በት/ቤት መድረክ በአንድ ቴአትር ላይ ለመጫወት ዕድሉን አግኝቶ ነበር፡፡

የከፍተኛ ትምህርት

የከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተም ከቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ 1996 ዓ.ም በቋንቋዎች በዲፕሎማ የተመረቀ ሲሆን፣  የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት በሚሰጡት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ፅሑፍ የትምህርት መስክ ደግሞ በባችለር ኦፍ አርትስ /ቢኤ.ዲግሪ/ ተመርቋል፡፡ አሰፋ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ፅሑፍ ቢያጠናበት ወቅት የስነ ጽሁፍ መምህራቸው የነበረው አንዱአለም ሐደሮ ስነ ጽሁፍን በተለየ ዓይን እንድመለከተው ያደረገኝ በመሆኑ ምስጋናዬ ወደር የለውም ይላል፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ መስክም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሰጠው የትምህርት ዕድል በማስተር ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ /MPH/ ከአዲስ ኮንቲኔንታል ኢንስቲትዩት ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ  በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ተመርቋል፡፡

የጋዜጠኝነት ጅማሬ

በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ስነ-ፅሑፍ በማቅረብ የጀመረው ጥረት በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚኒ ሚዲያ ፕሮግራም አዘጋጅነት ቀጠለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም በአዲስ አበባ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር በ1990 ዓ.ም አባል በመሆን በሙያና በፍላጎት ተመሳሳይ ከሆኑ አማተር ባለሙያዎች ጋር የመገናኘት ዕድል ፈጠረለት፡፡ በዚህ ማህበር ውስጥ ካገኛቸው አይረሴ ወዳጆቼ መካከል ጋዜጠኛ ኤልሣ አሰፋ፣ ሰላማዊት መዝሙር፣ ጌጡ ተመስገን፣ ተመስገን በየነ እና ዛሬ በየሚዲያው ስማቸው የሚጠቀሱ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡

በዚህ ማህበር ከአባልነት እስከ ማህበሩ ሊቀመንበርነት ያገለገለው አሰፋ ይርጋለም፣ ጋዜጠኝነትን ወደውና ሙያውን ፈልገው የሚመጡ ወጣቶችን መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ሥልጠና በአንጋፋና ልምድ ባላቸው ጋዜጠኞች ስልጠና በመስጠት የጋዜጠኝነትን ሀሁ በተለያዩ ዙሮች ሲያስጨብጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ በአሰልጣኝነት የሚጠቀሱት ጋዜጠኛ ጌታቸው ወልዩ ፣ ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ፣ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ፣ ትዕግስት ህሩይ፣ ነፍሳቸውን ይማረውና ጋሽ ደምሴ ጽጌ፣ ጎርፍነህ ይመር እና መሰል አንጋፋ ባለሙያዎች ወጣቶችን በመቅረጹ ረገድ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡

የ11 ዓመታት ቆይታ በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ

ጋዜጠኛ አሰፋ ይርጋለም ወደ ስራው ዓለም የተቀላቀለው የ21 ዓመት ወጣት እያለ ነበር፡፡ የስራ ማረፊያው ደግሞ በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ ስር በምትታተመው አዲስ ልሣን ጋዜጣ ነበር፡፡ በአዲስ ልሣን ጋዜጣ ̏መዲናችን ስትፈተሽ˝ በሚል አምድ ስር የተለያዩ መጣጥፎችን፣ ወጎችን በመዲናዋ የሚስተዋሉ እንከኖች እንዲታረሙ የሚያሳስበቡ ፅሁፎችን ያቀርብ ነበር፡፡

ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን የ11 ዓመት ቆይታው ረዘም ያለውን ጊዜ ያሳለፈው በዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ክፍል ነበር፡፡ በዚህም ለሬዲዮ፣ ለቴሌቭዥን ፣ ለህትመት (አዲስ ልሳን) የሚሆኑ ዜናዎችን እና ሪፖርታዦችን በመስራት ይታወቃል፡፡ “ጋዜጠኝነት ከምናለሽ ተራ እስከ ቤተመንግስት ድረስ እንድገባ እድሉን ሰጥቶኛል” የሚለው አሰፋ ይርጋለም፣ ከታችኛው ማህበረሰብ እስከ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እና የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጭምር ቃለምልልሶችን ሰርቷል፡፡ ኤጀንሲው በ2002 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው የኮከብ ሠራተኞች ሽልማት በከፍተኛ አፈፃፀም የገንዘብ ሽልማት ካገኙ ጥቂት ሠራተኞች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በዜና ክፍል ቆይታው የዜና አቀራረብ ፎርማትን ለመቀየር የሚረዳ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ በተቋሙ የለውጥ ስራዎች ላይም አሻራውን አኑሯል፡፡

በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ ቆይታው ከአንጋፋዎቹ ነፍሱን ይማረውና ከበትሩ ላቀው፣ ተስፋዬ መክብብ፣ ከወጣቶቹ ገዛኸኝ መኮንን እና ታገል ሰይፉን ከመሳሰሉ ባለሙያዎች እና ሀላፊዎች ጋር በመስራቴ ለእኔ ትልቅ ዕድል ነበር ይላል፡፡

በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ ዕረፍት የሚባል ነገር አይታሰብም የሚለው የቀድሞው የኤጀንሲው ባልደረባ አሰፋ ይርጋለም፣ በየዕለቱ ከማለዳ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ድረስ ስራ ላይ የሚቆይባቸው ጊዜያት በርካታ አንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ በአንድ ሌሊት የመስሪያ ቤቱ ሰርቪስ አስፓልት ዳር አውርዶት ወደ መኖሪያ መንደሩ ሲገባ ማጅራት ከመመታት በአምላክ ተአምር መትረፉን ይናገራል፡፡ ከዛ ጊዜ አንስቶ እናቱ እና እህት ወንድሞቹ ሰርቪስ የሚያወርደው ቦታ ላይ በየዕለቱ በቀዝቃዛ ምሽት ለመጠበቅ ተገደው ነበር፡፡ አሰፋ ያን ጊዜ ሲያስታውስ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ እኔን ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰቤን እዚህ ግባ በማትባል ደመወዝ ቀጥሮን ነበር በማለት ይገልፀዋል፡፡








ጉዞ ወደ ሕዝብ ግንኙነት ሙያ

ከህዳር 2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2010 ዓ.ም ድረስ ለ4 ዓመት ከአምስት ወር ገደማ በኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኖ ሰርቷል፡፡ እንዲሁም ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም ድረስ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣-ከሚያዝያ 2011 ዓ.ም እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም ድረስ በሠላም ሚኒስቴር የውስጥ ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ በመሆን የተቋሞቹ ቃለ አቀባይ በመሆን ሰርቷል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ህዝብ ግንኙነት ሙያን ከፖለቲካው ጋር ባለመቀላቀል ፕሮፌሽናል ስራ ብቻ እንዲሰራበት አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ  Clinton Health Access Initiative በተሰኘ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ በኮሙኒኬሽን አማካሪነት በማገልግል ላይ ይገኛል፡፡

ከመጽሐፍት ጋር ጓደኝነት

አቶ አሰፋ ለአቅመ ንባብ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በአባታቸው አቶ ይርጋለም ፈለቀ አበረታችነት በርካታ መፅሐፍትን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ለማንበብ በቅተዋል፡፡ ዛሬ ድረስ ጥሩ ህመም (የማልላቀቀው ሱስ) ለሆነኝ የማንበብ ልምድ አባቴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ይላሉ፡፡ መፅሐፍ፣ ጋዜጣ፣ መፅሔት ያለመታከት እየገዛ በማቅረብ ዛሬ ለደረሰበት የጋዜጠኝነትና የኮሙኒኬሽን ባለሙያነት መሠረቱን ጥለዋል፡፡ ዛሬም ድረስ በምሽት ቢያንስ ትንሽም ነገር ሳያነብ ወደመኝታ ክፍሉ አይሄድም፡፡

አቶ አሰፋ ካነበባቸው በርካታ መፅሐፍት ትልቁን ቦታ የሚይዙት ከአማርኛ ልብወለዶች የሀዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር፣ የበአሉ ግርማ ኦሮማይ፣ የሲሳይ ንጉሱ ሰመመን፣ የሰርቅ ዳንኤል ቆንጆዎቹ ሁሌም ደጋግሜ ባነባቸው ሰርክ አዲስ ናቸው ለእኔ ሲል ይደመጣል፡፡

ከእንግሊዘኛ ልብወለዶች የጆርጅ ኦርዌል “Animal Farm” ፣ የእርነስት ሄሚንግዌይ “The Old Man and the Sea” ፣ የአለን ፓቶን “Cry, the beloved Country” ፣ እንዲሁም በልጅነቱ እያለቀሰ ጭምር ያነበበው “The Diary of Anne Frank” ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ 

ጋዜጠኛና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አሰፋ ይርጋለም ከልጅነቱ ጀምሮ አንባቢ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የሬዲዮ አድማጭም ነበር፡፡ ለዜናና ወቅታዊ ነገሮች ከድሮ ጀምሮ ልዩ ትኩረት የነበረው ሲሆን፤ ዛሬም ድረስ በዜና ሠዓት ሰው ባያናግረው፣ ስልኩም ባይጠራ ይወዳል፡፡ ዜናን በሙሉ ቀልብና ትኩረት መከታተሉ የሕይወቱ ጥሪ ሆኖ 11 ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ በጋዜጠኝነት ለማገልገል  ስንቅ ሆኖታል፡፡ ጋዜጠኝነትን ከልጅነቴ ጀምሮ በፍቅር ስፈልገው ቆይቼ በኋላም ልኖረው በቅቻለሁ ይላል ጋዜጠኛ አሰፋ ይርጋለም፡፡

ጋዜጠኛ ባይሆን ሌላ መሆን የሚፈልገው ሙያ ምን ነበር?

ልጅ ሆኜ ከጋዜጠኝነት ውጪ ለመሆን አልም የነበረው ነገር የወንጀል መርማሪ መሆንን ነበር የሚለው አሰፋ ይርጋለም፡፡ ከአጋታ ክርስቲ በርከት ያሉ መጽሀፍት ጋር መተዋወቄ ወደዚህ የሙያ ፍላጎት የገፋኝ ይመስለኛል ይላል፡፡ የህይወት ዕጣዬ ወደ ምርመራ ስራ አልወሰደኝም እንጂ ጋዜጠኛ ወይም የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ባልሆን የወንጀል መርማሪ ሳልሆን አልቀርም ነበር ሲል ያጠቃልላል፡፡

የትርፍ ጊዜ ክንውኖች (Hobbies)

- ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት

- ማንበብ

- አልፎ አልፎ ፊልም ማየት

ከሀገራችንን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ አብዛኞቹን የጎበኘ ሲሆን (በተለይ የአክሱም ሀውልት እና የፋሲል ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገርም ኪነጥበባዊ አሻራ ያረፈባቸው በመሆኑ ለኔ የተለዩ ናቸው) ይላል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ውጪ የተጓዝኩባቸውን ሀገራትን የቱሪስት መስህቦች መጎብኘት ችያለሁ የሚለው አሰፋ፣ በተለይ የህንዱ ታጅ ማሃል፣ የሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ድንበር ጉብኝቴን አልረሳቸውም ሲል ያክላል፡፡

ሌላኛው የአሰፋ ይርጋለም የትርፍ ጊዜ ስራ መጽሀፍት ማንበብ ሲሆን፣ በወር በአማካይ እስከ አራት መጽሀፍትን እገዛለሁ፡፡ ለልጆቼ ማውረስ የምፈልገውም እውቀትና መጽሀፍትን እንዲሆን እፈልጋለሁ ይላል፡፡

አሰፋ ይርጋለም ከተለያዩ ተቋማት ያገኟቸው ሽልማቶች

- በ1989 ዓ.ም ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ አለም አቀፍ የህፃናት ቀንን በማስመልከት በተካሄደ አገር አቀፍ ውድድር 3ኛ በመውጣት የገንዘብ ሽልማት፤

- በ1992 ዓ.ም አለም አቀፍ የአረጋውያንን ቀንን በማስመልከት በተካሄደ የስነ-ፅሑፍ ውድድር 2ኛ ወጥቶ ተሸልሟል፡፡

- በ1997 ዓ.ም የአለም የቱሪዝም ቀንን አስመልክቶ በተካሄደ ውድድር አንደኛ በመውጣት ተሸልሟል፡፡

- በ2000 ዓ.ም በጋዜጠኞች መካከል በተካሄደ አገር አቀፍ የስነ-ፅሑፍ ውድድር /ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ላይ ያተኮረ ነው/ አንደኛ በመውጣት የገንዘብ ሽልማት አግኝቷል፡፡

የቀረቡ ጥናታዊ ፅሑፎች

- ለመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደተጠበቁ ሆነው፡፡

- በ2018 እ.ኤ.አ. በስፔን ማድሪድ Universal Health Coverage in Africa, towards Ethiopian Experience, በሚል ርዕስ በአለም አቀፍ መድረክ አቅርበዋል፡፡

-በ2014 እ.አ.አ. በናይጄሪያ አቡጃ የኢትዮጵያን የጤና መድህን ትግበራ ልምዶች በአለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ አካፍለዋል፡፡

በተለያዩ አገራት የተወሰዱ ሥልጠናዎች እና የልምድ ልውውጦች

- ህንድ፤ ኒውደልሂ /እ.አ.አ. 2013/ English Proficiency & essential IT Skills ለሦስት ወራት

- ናይጄሪያ፤ አቡጃ /እ.አ.አ. 2014/ Health for All, አለም አቀፍ ኮንፈረንስ፤

- ደቡብ ኮሪያ፤ ሴኡል /እ.አ.አ. 2014/ የጤና መድህን ትግበራ የልምድ ልውውጥ፤

- ስፔን፤ ማድሪድ /እ.አ.አ. 2018/ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ፤

- ናይጄሪያ፤ አቡጃ /እ.አ.አ. 2018/ በስራ ቦታ ማህበራዊ ምክክርን ማጎልበት ላይ ያተኮረ መድረክ፣

የትርፍ ጊዜ ክንውኖች (Hobbies)

- ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት

- ማንበብ

- አልፎ አልፎ ፊልም ማየት

ከሀገራችንን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ አብዛኞቹን የጎበኘው አሠፋ ይርጋለም (በተለይ የአክሱም ሀውልት እና የፋሲል ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገርም ኪነጥበባዊ አሻራ ያረፈባቸው በመሆኑ ለኔ የተለዩ ናቸው) ይላል፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ውጪ በተጓዝኩባቸውን ሀገራት የቱሪስት መስህቦችን የጎበኘ ሲሆን የህንዱ ታጅ ማሃል፣ የሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ድንበር ጉብኝቶቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ቀጣይ ዕቅድና የህይወት ፍልስፍና

በቀጣይም የሬዲዮ የአየር ሰዓት በመግዛት በጤና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፕሮግራም ለማስተላለፍ ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ወደ ጋዜጠኝነትና ህዝብ ግንኙነት ለመግባት የሚፈልጉ ወጣቶችን አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ለማገዝም አቅዷል፡፡

የአሰፋ ይርጋለም ልዩ መታወቂያው መልካምነት፣ የስራ ቦታ ዲሲፕሊን ፣ ታታሪነት ሲሆኑ፣ የህይወት ፍልስፍናውም መልካም ነገሮችን አብዝተህ አድርግ፣ መልካምነትህ እጥፍ አድርጎ ይከፍልሀል ነው፡፡

አሠፋ ይርጋለም በጥር ወር 2008 ዓ.ም በትዳር ከተጣመራት ገነት ኃይሉ ጋር በትዳር የሚኖር ሲሆን የአንድ ወንድ ልጅም አባት ነው፡፡








 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች