76. ደረጀ ትዕዛዙ ስመኝ-Dereje tizazu simegne

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 20 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል ደረጀ ትእዛዙ ስመኝ ይጠቀሳል፡፡  ደረጀ ከጋዜጠኝነቱ ሌላ ልቦለድ ይጽፋል፡፡    

ትውልድና እድገት

       የቤቱ ብቸኛ ወንድ

ደረጀ ትዕዛዙ ስመኝ አዲስ አበባ ውስጥ በአሁን አጠራር ልደታ ክፍለ- ከተማ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ መጋቢት ላይ በ1965 ዓ.ም ተወለደ፡፡ አባቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሃምሳ አለቅነት ማእረግ በመገናኛ ጦር ውስጥ በውትድርና ያገለገሉ ሲሆኑ፤ እናቱ ወይዘሮ አረጋሽ ነዲ የቤት እመቤት ናቸው፡፡ ከአራት እህቶቹ መካከል በብቸኝነት ወንድ ሲሆን፤ ለቤቱ ሁለተኛ ልጅ ነው፡፡ በዚያው ሰፈር ከእኩዮቹ ጋር በጨርቅ ኳስ እየተራገጠ፣ ድብብቆሹን፣ አባሮሹን፣ ሌባና ፖሊስነቱን፣ ኩኩሉን፣ ብዩን፣ ጠጠሩን እየተጫወተ፣ በመንደሩ ባለው ኩሬ እየተንቦራጨቀ፣ ጭቃ እያቦካ በፍቅርና በነጻነት አደገ፡፡

የልጅነት ሕይወቱንና ሰፈሩን አብዝቶ የሚወደው ደረጀ፤ የእግር ኳስ ጨዋታ እጅግ በሚወደድበት ዘመን  ፖሊስ ሜዳ /አባሲዮን/ በመንደሩ አቅራቢ በመሆኑ ሁለተኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ጨዋታዎችን በተለይ ከ1970 ዎቹ አጋማሽ እስከ 80 ዎቹ አጋማሽ ከእኩዮቹ ጋር ደስ እያለው በነጻ በመመልከት ይዝናና እንደነበር ያስታውሳል፡፡

     የሰፈሩን ሰዎች እየተመለከተ

በዚሁ ሰፈር /ሰላም ሰፈር/ በልጅነቱ እያያቸው አድጎ ኋላ ላይ ስራና ማንነታቸውን ሲያውቅ የተገረመባቸው ደራሲያን፣ የታሪክ ጸሐፍት፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች የጥበብ ሰዎች ኖረውበታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የታሪክ ተመራማሪውና ጸሐፊው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ደራሲ ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊው ጳውሎስ ኞኞ፣ ሰዓሊ አለፈለገሰላም እንዲሁም ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያም ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህን የሰፈሩ ሰዎች እየተመለከተ ማደጉ ኋላ ላይ በራሱ የማንነት ግንባታ ላይ በጎ ተጽዕኖ  እንዳረፈ ይናገራል፡፡

                             ትምህርት

ደረጀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሰፈሩ ባለ መዝገበ ብርሃን፣ ከዚያም መሠረተ ዕድገት እና በቀራኒዮ መድኃኒዓለም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ በባልቻ አባ ነፍሶ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከፍተኛ 7 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቋል፡፡

በእነዚህ የልጅነትና የትምህርት ጊዜያቱ ሁሉ ሬዲዮ መከታተል አብዝቶ ይወድ የነበረው ደረጀ፤ ተሳትፎውንም የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ በ70 ዎቹ አጋማሽ በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን ይተላለፉ የነበሩ ፕሮግራሞች ላይ ደብዳቤ እየጻፈ አስተያየቱንና ሃሳቡን በመስጠት ነበር ብዕሩን ያሟሸው፡፡

ቀስ በቀስ ይህንን ተሳትፎ እያሳደገ በሌሎች ሚዲያዎችም እያጎለበተ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ዘው አለ፡፡ እዚያው ሙያ ውስጥ ሆኖም በትምህርት እራሱን አሳደገ፡፡ በ1996 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ማስ ሚዲያ ማሰልጠኛ  ኢንስቲቲዩት ለሁለት አመታት በቀን መርሃ-ግብር ተከታትሎ በህትመት ጋዜጠኝነት በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡ በ2002 ዓ.ም ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡

                          ነጻ ተሳትፎ

በልጅነቱ በሬዲዮና በቴሌቭዥን ይተላለፉ በነበሩ የልጆች ክፍለ-ግዜ የጀመረውን የሚዲያ ተሳትፎ በወጣትነቱም የቀጠለው፤ በኢትዮጵያ ትምህርት ስርጭት አገልግሎት ስር ይተላለፍ በነበረው የለገዳዲ ሬዲዮ ‹‹ቅዳሜን ከኛ ጋራ›› እና ‹‹እሁድን ለአንድ አፍታ›› በተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ ነበር፡፡ በተለይ በደብዳቤዎች ማህደር እና በጥያቄና መልስ ፕሮግራሞች ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበር፡፡ በስልክ፣ በደብዳቤ እና በግንባር ቢሮ ድረስ በመሄድም የጥያቄ መልሶችን እና የተሳትፎ ጽሑፎችን ያቀብል እንደነበር ይናገራል፡፡ በተሳትፎው እንዲገፋበት የወቅቱ ፕሮግራም ኃላፊ ገበየሁ ደምሴ ያበረታታው እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ይህንኑ ነጻ ተሳትፎ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር በሚታተሙት በአዲስ ዘመን እና የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ቀጠለ፡፡ እንደ ሌሎች ጸሐፍት ጓደኞቹ ሁሉ የተለያዩ መጣጥፎችና አጫጭር ግጥሞችን ከዚያም አልፎ ቃለ -መጠይቆችን በጋዜጦቹ ላይ እንዲወጡለት እያደረገ ብዕሩን አተባ፡፡ ከ1980 ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ ድምጽ ዓለም አቀፍ አገልግሎት የቅዳሜ ምሽት መዝናኛ እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት የቅዳሜ ከሰዓት በኋላ መዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ በድምጽ ተሳትፎውን ቀጠለ፡፡

በእነዚህ ሚዲያዎች በጭውውት ጀምሮ የራሱን ግጥሞች፣ መጣጥፎች እና ልቦለዶች በድምጹ ሲያቀርብ ያለ ምንም ክፍያ ነበር፡፡ በዚህ ትጋቱ ጋዜጠኛ የመሆን ምኞቱ እንደሚሳካ ግን እርግጠኛ ነበረ፡፡ በቅዳሜ ከሰዓት መዝናኛ አቅርቧቸው የነበሩት እንደ ‹‹እምባ››፣  ‹‹ዋዜማ›› እና ‹‹ሰው›› የተሰኙ ርዕስ ያላቸው ልቦለዶቹ የማይዘነጉ ናቸው፡፡ በዚህ የሬዲዮ ተሳትፎው እንዲገፋበት ጋዜጠኛ ሂሩት መለሰ /ዛሬ ጀርመን ሬዲዮ ጋዜጠኛዋ/ ታበረታታው እንደነበር ይናገራል - ደረጀ፡፡

ለቀረጻ ወይም ጽሑፍ ለማቅረብ ከሜክሲኮ አደባባይ ወረድ ብሎ ፖሊስ ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኘው የለገዳዲ ሬዲዮ ስቱዲዮ፣ ባንቢስ አካባቢ የሚገኘው ዓለም አቀፍ አገልግሎት ስቱዲዮ፣ ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ የሚገኘው የብሔራዊ አገልግሎት ሬዲዮ ስቱዲዮ እና አራት ኪሎ የሚገኘው ፕሬስ ድርጅት ለመሄድ ግድ ይለዋል፡፡ ለዚህም ሳንቲም ካገኘ ከሰፈሩ የሦስት ቁጥር አውቶቡስን ይዞ አብዛኛውን መንገድ ይዘልቀዋል፤ አሊያም ደርሶ መልስ በአማካኝ በእግሩ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድን በእግሩ መጓዝ የውዴታው ግዴታ ነበር፡፡ 

በዚህ በዚሀ ተሳትፎው የህይወት ጥሪ ወደ ስነ- ጽሐፉ፣ በተለይም ወደ ጋዜጠኝነቱ አንደረደረችው፡፡ በዚያን ወቅት በደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል አሰባሳቢነት ለተወሰነ ጊዜ ብልጭ ብሎ በነበረው እንቡጥ የስነ ጽሑፍ ክበብ ውስጥ አባል መሆኑ  ጥበብን ይበልጥ እንዲጠበባቅ ዕድል ፈጥሮለት እንደነበረ ያስታውሳል፡፡

                     የጋዜጠኝነት ሕይወት

ደረጀ የነጻ የተሳትፎ ልምዱን በመጠቀም ቀጥታ ወደ ጋዜጠኝነቱ ሙያ ለመግባት አልከበደውም፡፡  እናም ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የግልና የመንግስት ሚዲያ ተቋማት ከ20 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ አገልግሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ዋልታ፣ ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ዘመን መጽሔት እና  ታዛ መጽሔት ይጠቀሳሉ፡፡ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ደረጃም ዘልቆ የሙያውን ከፍታ አይቷል፡፡ በስራው ከ375 ብር ደመወዝ እስከ 10 ሺ 500 ብር ደመወዝ አይቶበታል፡፡ አድጎበታልም፡፡

አጀማመሩ የሬዲዬ ቢሆንም ስሜቱ ያደላው ግን ወደ ህትመት ጋዜጠኝነቱ ነው፡፡ የህትመት ጋዜጠኝነት ትምህርቱን በአግባቡ እንደተጠቀመበት ባሳለፋቸው የስራ ሂደቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡  በተለይ በስምዓ ጽድቅ እና አዲስ ዘመን ጋዜጦች እንዲሁም ታዛ መጽሔት ላይ በሰራቸው ስራዎች እንደሚደሰት ይናገራል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ቆይታው ከትምህርቱ ጎን ለጎን የግቢ ጉባኤ ተማሪ በመሆኑ መሰረታዊ የሃይማኖት ትምህርትን ለመቅሰም ችሏል፡፡ ያገኘውን ዕውቀትም በማህበረ ቅዱሳን ስር በምትታተመው ስምዓ ጽድቅ መንፈሳዊ ጋዜጣ ላይ እንደተጠቀመበት፤ በዚያው ውስጥ ዕውቀቱንም እንዳጎለበተ ይናገራል፡፡

በዚህች ጋዜጣ ከ2000 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ለሦስት ዓመታት በሪፖርተርነትና በከፍተኛ ሪፖርተርነት ሲያገለግል ዜናዎችን፣ መጣጥፎችን ያቀርብ ነበር፡፡ መንፈሳዊ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቃለ- መጠይቅ እያደረገም በሃይማኖቱ ዙሪያ መረጃዎችና ትምህርቶች ለምዕመናን እንዲደርሱ እንደሌሎች አገልጋዮች ሁሉ እርሱም የድርሻውን ይወጣ ነበር፡፡

ብዙውን ግዜ ማህበራዊና በኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች፤ እንዲሁም የታዋቂ ሰዎችን ግለ- ታሪክ በመጻፍ ነው የሚታወቀው፡፡ ይህንንም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በነበረው ቆይታ አሳይቷል፡፡ በዚሁ ጋዜጣ በአርታኢነትና በአዘጋጅነት ከ3 ዓመት በላይ ሰርቷል፡፡ ታዋቂ ደራሲያንን፣ የቴአትር ባለሙያዎችን፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለሀገርና ለወገን በጎ ተግባር የፈጸሙ ምሁራንን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ሥራና ማንነታቸውን አሳይቷል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ከግብርናው ዘርፍ ዶክተር (ሳይንቲስት) መላኩ ወረደ፣ ከሀገር አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ከቴአትሩ ‹‹ሁለገብ የጥበብ ባለሟል›› ያላቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ፣ የእንግሊዝኛው ኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ያዕቆብ ወልደማሪያም እንዲሁም ደራሲ ተርጓሚና አርታኢ አማረ ማሞ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በማህበራዊ ጉዳይ፣ በኪነ ጥበብ፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በፍልስፍናና ተያያዥ ጉዳች ላይ በምታተኩረው ‹‹ታዛ›› መጽሔት ላይም በዋና አዘጋጅነት ደረጃ ለአንድ ዓመት (2011 ዓ.ም) ሰርቷል፡፡ በዚህች መጽሔት ሙያዊ ብቃቱን እንዳሳየ ይመሰከርለታል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ሆኖ ለዘገባ ሲነቀሳቀስ አብዛኛውን ሀገሪቱ ክፍሎችን አይቷል፡፡ ሃድያ (ሆሳዕና) ፣ ጉራጌ (ወልቂጤ) ፣ ጎንደር፣ ደብረብርሃን እና ጋምቤላ በተለያዩ ወቅቶች ለተወሰኑ ጊዚያቶች ተቀምጦባቸዋል፡፡ በቆይታውም  የየአካባቢዎቹን ባህልና ታሪክ ለማወቅና ለማጥናት ችሏል፡፡ በሙያው ዙሪያ በርካታ ገጠመኝና ትዝታዎችም አሉት፡፡ አንድ ጋዜጠኛ መስራት ያለበትን ሁሉ የሰራ፤ በችሎታው የሚተማመን ሰው ነው፡፡ በሳለፈባቸው የስራ ጊዜያቶች ሁሉ በጋዜጠኞች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ፈተናዎች ደርሰውበታል፤ ነገር ግን ፈተናው ሙያዊ ባህሪ መሆኑን ስለሚገነዘብ፣  ለሙያው የሚከፈል መስዋዕትነት እንደሆነ በመረዳት ፈተናዎቹን እየተጋፈጠ ስኬት ላይ ደርሷል፡፡ ዋናው የጋዜጠኝነት መርህ ገለልተኝነት መሆኑን ስለሚረዳ ፈተናዎች ቢገጥሙትም የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊም ሆነ አባል ሳይሆን ኖሯል፡፡

                                  መጽሐፍ

‹‹ጋዜጠኛ ሲያረጅ ደራሲ ይሆናል›› የሚለውን አባባል ፈጥኖ የተገበረ ሰው ነው ደረጀ፡፡ ልጅነቱን፣ ወጣትነቱንና ጉልምስናውን ለስነ ጽሑፍ እያዋለው ኖሯል፡፡ በ2006 ዓ.ም መጨረሻ ‹‹ ጳውሎስ ኞኞ ከ1926- 1984›› በሚል ርዕስ የጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ጳውሎስ ኞኞን የህይወት ታሪክና ስራዎቹን የዳሰሰ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ይህን የመጀመሪያ ስራውን ለንባብ ያበቃው በጋዜጠኝነት ስራው ውስጥ ሆኖ ነው፡፡

በቃለ-መጠይቅ የዳበረው፣ በመረጃ የዳጎሰው ይህ መጽሐፍ የጳውሎስን ሁለንተናዊ ሕይወት የዳሰሰ ድንቅ መጽሐፍ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡ በህይወት ታሪክ አጻጻፍ ለሌሎችም ጸሐፍት ምሳሌ ሊሆን እንደሚችልም መጽሐፉ የወጣ ሰሞን የተሰሩ የዳሰሳ ጽሑፎች / Reviews / ላይ ተንጸባርቋል፡፡ ይህን  በጥልቅ ጥናትና ፍተሻ የበሰለ መጽሐፍ ለማዘጋጀት 10 ዓመት እንደፈጀበትና በራሱ ወጪ አሳትሞ ለንባብ እንዳበቃው ይናገራል፡፡

በ2009 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ሳተናው እና ሌሎች›› በሚል ርዕስ የአጫጭር ልቦለዶችና የግጥም ስብስቦቹን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል፡፡ የስራ ገጠመኝና ልምዱን ተጠቅሞ በተለያየ መነጽር የማህበረሰቡን ህይወት በቃኘበት በዚህ መጽሐፍ፤ አንባቢንን የተለያዩ ስሜቶች ውስጥ የሚከት ጥበብን ተጠቅሟል፡፡ ሳቅን የሚያጭሩ ታሪኮች እንዳሉበት ሁሉ፤ በራሮት ውስጥን የሚለበልቡ ታሪኮችንም አካቶበታል፡፡ ‹‹ እንደጀማሪ የፈጠራ ስራ የማይታይ በሳል ስራ ነው … ›› ሲሉ ካወደሱት የዳሰሳ /Reviews/ ጸሐፊዎች መካከል አንጋፋው ጋዜጠኛ ማዕረጉ በዛብህ መጽሐፉ የወጣ ሰሞን በሰንደቅ ጋዜጣ ያሰፈሩት ይጠቀሳል፡፡

ደረጀ በአርትኦት ስራም አለበት፡፡ ዶክተር ዮሐንስ ክንፉ /ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር/ ስለ አባታቸው አንጥረኛው ቱጃር ደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔ ያዘጋጁትን የህይወት ታሪክ መጽሐፍ የንባብ ጣዕም እንዲኖረው አድሪጎ አርቶታል፡፡ የተለያዩ ታዋቂ ጸሐፍት ስራን ባካተተው ‹‹ደቦ›› በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥም የደረጀ ስራ አለ፡፡ 

ዛሬ ዛሬ ስሜቱ ወደ የህይወት ታሪክ / Biography / መጽሐፍ ላይ እያዘነበለ የመጣው ደረጀ፤ በእንግሊዝኛው የኢትዮጵያ ሄራልድ እና በኢትዮጵያ የሮይተርስ ጋዜጠኛ ሆነው ከ50 ዓመት በላይ ያገለገሉት የፀጋዬ ታደሰን የህይወት ታሪክ መጽሐፍ አዘጋጅቶ የጨረሰ ሲሆን፤ ህትመት ሂደቱን እየጠበቀ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የአንጋፋው የጥበብ ሰው የተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠን የህይወት ታሪክ እያዘጋጀ ሲሆን፤ የቀድሞው አንጋፋ ጋዜጠኞች የህይወት ታሪክና ስራዎቻቸውን የተመለከተ አንድ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ለማዘጋጀት እየተጋ መሆኑን ይናገራል፡፡

                            ደረጀ ዛሬ

ማንበብና መጻፍ እንደ እለት ቀለቡ ለአንድ ቀንም ቢሆን እንዲያልፈው አይሻም፡፡ ከፈጠራ ስራ ይበልጥ የግጥም መጽሐፍትን ማንበብ ይመርጣል፡፡ የሀገራዊ ታሪክና የግለሰቦች ታሪክን / Biography / የያዙ መጽሐፍትም ይመቹታል፡፡ እውቀቱንና ልምዱን ከታች ለሚመጡ ጋዜጠኞች በቀናነት በማካፈል ይታወቃል፡፡ ክፉነትን ይጠየፋል፡፡ በባህሪው ተግባቢ ሲሆን፡ አስፈላጊ በሆነ ቦታ መቀለድን ያውቅበታል፡፡ ብዙ ከመናገር ማድመጥን ነው የሚወደው፡፡ በዚህም በእውቀትና በእድሜ የበሰሉ ሰዎችን ወዳጅ ማድረግ አይከብደውም፡፡  

ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ኑሮውን በሰሜን አሜሪካ (ካናዳ) አድርጓል፡፡ እዚያም ሆኖ ከሙያው እንዳልራቀ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናግሯል፡፡ የያዘውን ትልም ለማሳካት እየተጋ ይገኛል፡፡ እንደ ሙያው ሁሉ ቤተሰባዊ ኃላፊነቱንም በትጋት እንደሚወጣ የሚነገርለት ደረጀ፤ ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባትም ነው፡፡

‹‹ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል›› የሚለውን አባባል የሚያምንበት ሲሆን፤ ‹‹ቀሪ ዕድሜያችን እንኳንስ ለጸብ ለፍቅርም አይበቃንም ›› የሚለው ጥቅስ መሰል አባባል እንደሚመቸው ይናገራል፡፡

በጋዜጠኝነት ስራው ውስጥም ሆነ በፈጠራ ስራዎቹ በተለያዩ መንገዶች ስለ ሀገር ክብርና ስለ ሀገር መውደድ ሲጠቃቅስ የኖረው ደረጀ፡ ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር እንደሆነች ያምናል፡፡ ወደ ቀደመ ክብሯና ገናናነቷ እንደምትመለስም ተስፋ ያደርጋል፡፡ በምድሯ ሰላም እንዲሰፍንም ይመኛል፡፡

                                                                 ግንቦት 23/2013 ዓ.ም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች