74. ከቤት ሰራተኝነት እስከ ረጅም ልቦለድ ደራሲነት- 'እነዬ ሺበሺ ንጋቱ-
የዚህ ታሪክ
አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ
፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ
እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ
የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን
እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ
ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ
የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር
ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል
ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው
ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው
ይዘከራል፡፡ በድርሰትና በስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ተሰማርታ 3 ረጅም ልቦለዶችን ያቀረበችልን እነዬ ሺበሺ ከቤት ሰራተኝነት እስከ
ረጅም ልቦለድ ደራሲነት ባሳለፈችው የ20 አመት ጉዞ በብዙ ውጣ ውረድ አልፋለች፡፡ እነሆ ታሪኳን ለትውልድ ዘክረነዋል፡፡እነዬ
ሺበሺ፡፡
ድክ ድክ
በአብዮቱ ማግስት፣
በዘመናዊነት በር መክፈቻ ላይ፡፡ ጥር16 በ1969 የአቶ ሺበሺ ንጋቱና የወ/ሮ ዓለምነሽ ካሳሁን 6ኛ ልጅ ተወለደች፡፡ እነዬ
ሺበሺ፡፡ የካሣሁን ገ/መድህን ሴት ልጅ የሆነችው እናቷ ወ/ሮ ዓለምነሽ ካሳሁንና የንጋት ቸኮለ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው አባቷ
አቶ ሺበሺ ንጋቱ የተጋቡት የመጀመሪያ ትዳራቸውን ፈተው ነበር፡፡ ሁለተኛው ትዳራቸው ግን 7 ልጆች የፈሩበት በሠላምና በፀጋ
የተከናወነ ነበር፡፡ ከእናቷ ይልቅ አባቷ የተሻለ ሴት ልጅ ያለው ቢሆንም ሴት ልጆችን አብዝቶ የሚወድ ነበር፡፡ ለዚህም ነው
ስትወለድ ያለደንቡ በደስታ ጥይት እንደተኮሰ የሚነገርለት፡፡ ወንድ ካልሆነ ሴት ልጅ ስትወለድ ጥይት አይተኮስም፡፡ ካልያም
እናትየዋ የሰራቂያን በሽታ ይዟት መሆን አለበት፡፡ ለማንኛውም ያችን ህጻን ግን አባቷ በወንድ ልጅ ክብር ተቀበላት፡፡ ድግስና
ከበርቻቻውን ያገዘፉት ግን ከፊት ከተወለዱት ልጆች ጋር በጋብቻ የተዛመዱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከአገቡኞች፣ ከአበልጆች…. የሚመጣው
ሙክት፣ ዱቄት፣ ዳቦ… ሁሉም የተለየ እንደነበር እናቷ ታስታውሳለች፡፡ አስተዳደጓም መቀባበል የበዛበትና በዘመድ አዝማድ
የተከበበ ነበር፡፡ ከዚህ መሃል የማይረሳት ግን የመምህራኑ ነው፡፡ እንደተባለውም በተሻለ ወቅት ላይ የተከሰተች እድለኛ ህፃን
ነበረች፡፡ ወቅቱ አዲስ መንግሥት አዲስ ታሪክ ለመፍጠር የሚሯሯጥበት ነበር፡፡ ትምህርትን በማዳረስ፣ መሀይምነትን ማጥፋት፡፡
ስለዚህ የሰፈሯ ህፃናት ከቤታቸው በታች ካለው ዋርካ ስር ፊደል መቁጠር ጀምረው ነበር፡፡ የመምህራኑ ከእነሱ አጠገብ መኖርና
እርሷን መንከባከብ ደግሞ ዕድሏን ያሰፋው ይመስላል፡፡ እሷ ድክ ድክ ማለት ስትጀምር ደግሞ ከቤታቸው ጀርባ ባለ አራት ክፍል
ት/ቤት ተሠራ፡፡ ቦታው ቅርብ መሆኑ ያለ እናቷ ፈቃድ መምህራኑ እያጫወቱ ይዘዋት እንዲሄዱ አስቻለ፡፡
እናቷ አልፈለገቻትም
ህጻን እነዬ በሚገባ መናገር ስትጀምርም የተቆረጠ እርሳስ፣ የተበጨቀ ወረቀት እየሰጡ፣
ከጀማሪዎቹ ጋር ቀላቀሏት፡፡ ቤት ውስጥ ለማገልገል ስላልደረሰች እናቷ አልፈለገቻትም፡፡ እንዲያውም ሳታስቸግር እዛው መዋሏ
እረፍት ነው፡፡ ለስራው ከፍ ከፍ ያሉ ሴት ልጆቿና የወንድ የልጆቿ ሚስቶች ነበሩ፡፡ የማይወዱት ይሄን ገበያ በሄዱ ቁጥር ይህን
ግዢልኝ፣ ያንን አምጭልኝ የሚል ነገሯን ነበር፡፡ እንደሌላው ልጅ ከረሚላ ማስቲካ በመጠየቅ ፋንታ ደብተር፣ እስክርቢቶ፣ ማለቷን
አልወደዱትም፡፡ ቢሆንም እንዳታለቅስባቸው አልፎ አልፎም ቢሆን ይገዙላት ነበር፡፡ እርሷም አስተማሪዎቿ ስለሚሰጧት ብዙ
አላስቸገረችም፡፡ እንደቀልድ የጀመረችውን ትምህርት ግን አንድ፣ ሁለት፣ ብላ 6ኛ ክፍል አደረሰችው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን
እናትና አባቷ ነገሩን ብዙም አላስተዋሉትም፡፡
ችግሩ ከዚያ በኋላ
ነው፡፡ ለሰባተኛ ወደ ከተማ መሄድ፣ ቀለብ እየጫነች፣ ተከራይታ፣ ከተገኘም ተጠግታ ለመኖር፡፡ ይሄ ደግሞ ለሁሉም ከባድ ነው፡፡
ከማታውቀው ቦታ፣ ከወላጅ ተለይታ የሚለውን ሲያስቡት ትምህርቱ እንዲቋረጥ ወሰኑ፡፡ እሷ ግን እምቢ ብላ አልቅሳ ክምር ድንጋይ
ከምትባለው አቅራቢያ ከተማቸው ተመዘገበች፡፡ ለፈጣን ተራማጂ የአምስትና የስድስት ሰዓት፣ ለእሷ ግን የሙሉ ቀን ጉዞ ነበር፡፡
ከድካሙ፣ ፍርሃቱ፣… ሁሉም ተጋግዘው ቶሎ ተስፋ አስቆረጡዋት፡፡ የተጠጋችባት የአጎቷ ልጅ ሚስትም በሁኔታው ደስተኛ እንዳልሆነች
ገብቷት ነበር፡፡ ብቻ ሁሉም ከገመተችው በላይ ምቹ አልነበረም፡፡ ከስድስት ወር በላይ መቀጠል አልቻለችም፡፡ ወደ ቤትም
አልተመለሰችም፡፡ ከዚህ ይልቅ በአጠገቧ ሲያጓራ የከረመውን መኪና ጠብቃ አዲስ አበባ ገባች፡፡
“አዲስ አበባ!”
“አዲስ አበባ!”
እንዳሰበቻት ደስታና በእርካታ ነገሮች የሚገኝባት የአበቦች መንደር አልነበረችም፡፡ እንዲያውም እያስፈራሯት ካደገችባቸው
ከቢለንንና ከጎለዬ ወንዞች ደራሽ ጎርፍ መሃል የገባች መሰላት፡፡ አየር እስከሚያጥራት የምትሄድበት አጣች፡፡ በዚህ ላይ
ከአጎትና ከአክስት ልጅ የቀረበ ዘመድ አልነበረም፡፡ ችግሩ ግን የኒያኑም አድራሻ በበቂ አለመያዟ ነው፡፡ እንደ አገሯ እገሌና
እገሊት ብላ ጠይቃ የምታገኛቸው ነበር የመሰላት፡፡ ደግነቱ ጉዞ ላይ የነበራትን ብቸኝነትና የአሁን ግራ መጋባቷን ያስተዋሉ
አንድ ሴት ቀረብ ብለው ጠየቋት፡፡ አብረዋት ሲጓዙ ስላየቻቸው አልፈራችም፡፡ አመጣጧንና የፈለገችውን በግልጽ ነገረቻቸው፡፡
ለካስ ስትሳፈር ጀምረው አስተውለዋት ኖሯል፡፡ “የየማን ነሽ ልጂ ለመሆኑ?” “የሺበሺ ንጋቱ! እናቴ ደግሞ ዓለምነሽ ካሣሁን
ትባላለች፡፡ “ካሳሁን ገብረመድህን? አሏት እሷም እናቷን የደገመችው አውቃ ነበር፡፡ ካሣሁን ገ/መድህን አርበኛና ዝነኛ ሃብታምም
ነበሩ ሲባል ሰምታለች፡፡ እንደንጉስ ሰባት ስምንት በሬ ጥለው አገሬውን ግብር ያበሉ ነበር ይሏቸዋል፡፡ እርሷ ግን ከሞቱ ከብዙ
ዓመታት በኋላ ነው የተወለደችው፡፡
በእርግጥም በሁሉም
መልክ ምን ያህል ታዋቂ እንደነበሩ ከአንድ የአያቷን ታሪክ ከምትፅፍ ጓደኛዋ ጋር ጎንደር አርበኞች ቢሮ ገብተን ለማረጋገጥ
ችላለች፡፡ ገና ስማቸውን ስትናገር በየዋህ ይሉኝታ የለሽ አነጋገር
“ኧረ አሁን ገና
የሰው ዘር… ሲሉ ስለ ካሣሁን ገ/ብረመድህን ሲያወሩ የነበሩ አርበኛ አባት አጋጥሟት ነበር፡፡ ሴትዮዋም ቢያንስ በእናት
አውቀዋታል፡፡ እርሷም ለጊዜውም ቢሆን የሚያውቃት ሰው በማግኘቷ ደስ አላት፡፡ ከቤታቸው አሳድረውም በነጋው አንድ የአጎቷን ልጂ
አፈላልገው አገናኟት፡፡ ለጊዜው ተቀበለቻት፡፡ ልታኖራት ግን አልቻለችም፡፡ እንደውም መስራት አትችይም፣ ይዞ የሚያስተምርሽ የለ
ሲሉ ተሰባስበው እንድትመለስ ወሰኑባት፡፡ አሁን አንቺ ደግሞ ምን ቸግሮሽ መጣሽ? የብዙዎቹ ጥያቄ ሆነ፡፡ በእርግጥም ምቾት
በጎተራ ሙሉ እህል በበረት ሙሉ ከብትና በጉርጅ ሙሉ ፍየልና በግ ከተለካ አወጣጧ የቅብጠት መባሉ አይገርምም፡፡ ወላጆቿ
አካባቢው የሚጠይቀውን ሃብት የታደሉ ነበሩ፡፡ የእሷ ረሃብ ግን ሌላ ነው፡፡ እናም ተመለሽ የሚል ጥያቄአቸውን እምቢ አለች፡፡
ግን ቆርጣ ነበር፤ ስለዚህ “ከሰው ቤት እንጀራ ከተደረደረው ይሻላል የእናት እጅ በወጭት ያደረው” የሚለውን የአገሯን ስንኝ
በሀዘን እያንጎራጎረች፡፡ የሰው ቤት ሥራን ተያያዘችው፡፡ የሰው ቤት እንደየ ሰው የተለያየ ቢሆንም የመጣውን ለመቀበል
ቆርጣለች፡፡ በየቤቱ እየሠራችም ከተወሰነ መቋረጥ በኋላ ትምህርቷን በማታ ቀጠለች፡፡ የመጀመሪያው ትምህርት ቤቷ ቤቴልሄም
የሚባል የህዝብ ት/ቤት ነበር፡፡ … ኢትዮጵያ አንድነት፣ አጼ ፋሲል፣ ኢትዮጵያ ትቅደም፣ ሚኒሊክ፣ እንደመኖሪያ ቦታዋ እየቀያየረች
የተማረችባቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ በመጨረሻም ዩኒቲ ዪኒቨርሲቲ በሕግ ለሶስት ዓመት ተምራ ነበር፡፡ ችግሩ ግን እሱንም
ሌላ የህይወት ገጠመኝ ተከሰተና አቋረጠችው፡፡ ወደፊት የመቀጠል ህልም ቢኖራትም እስካሁን አላሳካችውም፡፡
በሰው ቤት ሰራተኝነት ለ12 አመት የሰራችው እነዬ
እነዬ በ1984
ከሀገሯ ስትመጣ የ15 አመት ልጅ ነበረች፡፡ አጠቃላይ በሰው ቤት ሰራተኝነት ለ12 አመት የሰራችው እነዬ የማንበብ ልማዷ ግን
ልዩ ነበር፡፡ ሰው ቤት እየሰሩ መጽሀፍ ማንበብና መጻፍ አዳጋች ቢሆንም እርሷ ግን አድርጋዋለች፡፡ ከሁሉም ዘመድ ወዳጅ ርቃ
ልብ ወለድ መጽሐፍን ዘመድ ጓደኛ ያደረገችው ገና አዲስ አበባንና ሰዎቿን መረዳት እንደጀመረች ነበር፡፡ ራሷን ጸሃፊ ሆና
ያገኘችው ሳታስበው ነው፡፡ ትንሽ ብለው በናቁት ሥራዋ የገፏትን፣ ያለሰው ስላዩአት የሸሿትን እየተከተለች ለማናገር ከመጣር
ይልቅ በፈጠራው አለም ያሉ ገጸ ባህሪያትን መወዳጀትን መረጠች፡፡ እነሱ በመናቅም ሆነ በማራቅ የሚያደርሱባት ችግር የለም፡፡
እናም ከተለያየ ቤት በበርካታ ቤተሰብ መሃል ብትኖርም የእሷ ዓለም ሌላ ሆነ፡፡ በተለይ ከአንድ የተለየ ገጠመኟ ወዲህ ደስታቸው
እንዳያስደስታት፣ ሀዘናቸው እንዳያሳዝናት እርቀቷን አሰፋችው፡፡ ዕለቱ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወጣበት እለት ነበር፡፡
የምትኖርበት ግቢ ስምንትን ለበርካታ ጊዜ የወደቀች አንድ ልጅ ከዚህ በኋላ መኖር አልፈልግም በሚል ስሜት እራሷን ለማጥፋት
ስትል ትያዝና ግቢው በበርካታ ግርግር ተውጦ ይውላል፡፡ ብዙ ልጆች ይወድቃሉ ያለፉትም የተለየ ትኩረት አግኝተው እኩል
መነጋገሪያ ሆነው ይውላሉ፡፡ ግቢው በርካታ ነዋሪ የሚገኝበት ሰፊ ግቢ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ የደስታና የሃዘን ስሜት ጋር ስትወጣ
ስትወርድ፣ ማታ ስለምትቀበለው ስለራሷ ውጤትም ስታስብ ትውልና አመሻሽ ላይ ወደ ትምህርት ቤቷ ትሔዳለች፡፡ ዘግይታ ስለደረሰች
ሁሉም እየያዘ ሄዶ ስለነበር ውጤት ከሚሰጠው የትምህርት ቤቱ ሰራተኛ በቀር የእሷን ውጤት ያየው የለም፡፡ እሱም “ጎበዝ ነሽ
ዘንድሮ ብዙ ሰው ወድቋል!” ከማለት በቀር ብዙም አልተናገረም፡፡ ሰማንያ አምስት ነበር ያመጣችው፡፡ በደስታ እየሮጠች ወደ ቤት
ሄደች፡፡ ሆኖም የቀኑ የውጤት ዜና ቀዝቅዞ ነበር፡፡ እሷን የሚጠይቃት ሰው አላገኘችም፡፡ እሷም እንዲህ ነው ብላ ለመናገር
ፈራች፡፡ ምን ሊሏት እንደሚችሉ አታውቅም፡፡ ይህን ደስታ የሚካፈል ሰው ሲጠፋ ማዕድ ቤቷ ገብታ ማልቀስ ትጀምራለች፡፡
እያለቀሰች እያለ የቤቱ ባለቤት ያዩአትና “ኡኡቴ! ሙሉ ጊዜአቸውን የሰጡትም አልተሳካላቸው፡፡ እንኳ… በይ ተነሽና ሥራ ሥሪ
ይልቅ! ብለዋት ይሄዳሉ፡፡ እንደወደቀች ነበር የተሰማቸው፡፡ እሷን ግን ለሃዘኗም ያሳዩት ግዴለሽነት ይበልጥ አሳዘናት፡፡
በዚህም በቃ የእኔ ሃዘንም ሆነ ደስታ ለእነሱ ምንም አይደለም፡፡ የእነርሱም ለእኔ እንደዛው ብላ ወሰነች፡፡ ከዛ በኋላ
የሰርጋቸው ከበሮም ሆነ፣ የሃዘናቸው ወየታ ቅንጣት የስሜት ለውጥ የማይፈጥርባት ለግዳጅ የተሰማራች ቆራጥ ወታደር ሆነች፡፡
ወደ ደራሲነት …………
ብቸኝነቷን
የሚቀርፍላት ያው ልብ- ወለድ ብቻ የልብ ወዳጇ ሆኖ ቀጠለ፡፡ እሱን ያጣችበት አንድ አጋጣሚም ነበር ከንባብ ወደ ጽሑፍ
ያሸጋገራት፡፡ ድንገት ተነስታ ያለማቋረጥ መለቅለቅ ጀመረች፡፡ በዚህ ጊዜ ያነበበችው አንድ የጋዜጣ ማስታወቂያ ደግሞ ነገሩን
አጠናከረው፡፡ አዲስ ልብስ ተጠቅሎ የመጣ ጋዜጣ ነበር፡፡ ጠርጋ ካወጣችው በኋላ እያገላበጠች ታነበው ጀመር፡፡ ከአንደኛው ጎን
ላይ የሥነጽሑፍ ውድድር ማስታወቂያ ነበረው፡፡ የቀረው ግን አንድ ቀን ብቻ ሆነ፡፡ ቢሆንም ዕድሏን መሞከር ይኖርባታል፡፡
ምሽቱን ሙሉ ስታስብ አምሽታ ሌሊቱን አንድ አጭር ልቦለድ ፃፈች፡፡ የእጅ ጽሑፏ ግን ጥሩ አልነበረም፡፡ እናም የጎረቤት ልጅ
ለምና አስገለበጠችው፡፡ በአድራሻው ደውላም የአወዳዳሪ ድርጅቱን አድራሻ አገኘች፡፡ ሆኖም የስራ ቀን ስለነበር እራሷ መሔድ
አልቻለችም፡፡ ያኑ ልጅ ለምና የታክሲውን በመክፈል ላከችው፡፡ በዛ ውድድር አንደኛ መውጣቷም በራሷ ላይ ትንሽ እምነት
እንዲያድርባት አደረገ፡፡ የሙያውን ሰዎች አግኝታም የተለያየ ማበረታቻ ለማግኘት በቃች፡፡ ይሄ ደግሞ ከዚህ በፊት ለጊዜ
ማሳለፊያ የለቀለቀቻቸውን ሁሉ ዘወር ብላ እንድታይ አበረታታት፡፡ በድፍረት በኮምፒውተር አጽፋም በድፍረት የሚያይላት ባለሙያ
ማፈላለግ ጀመረች፡፡ ሰዎች ክፉ ብቻ እንዳልሆኑ ለማሰብ የተገደደችው ይሄኔ ነበር፡፡ ከእግዜር ቀጥሎ የምትፈራቸው ታላላቅ ሰዎች
ሁሉ እየተቀባበሉ ሥራዋን አዩላት፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርም የአርቲስቲክ ሰባ አምስተኛ ዓመት ሲከበር ሁለቱ በመተባበር
ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድሮ ያለፈ ሥራዋን “እሩብ ጉዳይ” በሚል ርዕስ በታተመ የአጫጭር ልቦለዶች መደብል ላይ በማካተት ሥራዎቿን
በመጽሓፍ መልክ እንድታይ አደረገ፡፡ ቆየት ብሎም ለእራሱ ለደራሲያን ማህበር ሃምሣኛ ዓመት በለቀቀው የተዘዋወሪ ሂሳብ የተለያዩ
መጻህፍትን አወዳድሮ ሲያሳትም “የገቦ ፍሬ” ዕድሉን አግኝቶ ለንባብ በቃ፡፡ የገቦ ፍሬ በ367 ገጽ የተጻፈ ልቦለድ ድርሰት
ሲሆን በ3000 ቅጂ ለንባብ የበቃ ነው፡፡ የዚህ መጽሀፍ ዋና ትኩረት ከአንድ ገጠር ወጥታ ከተማ የመጣችን ሴት ታሪክ የሚያወሳ
ሲሆን ወላጆች ለክብራቸው ሲሉ ልጆችን በምን አይነት መንገድ እንደሚገፉ ያሳያል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የ3 ረጃጅም ልቦለዶችና
የዘጠኝ በጋራ የተጻፉ የአጫጭር መድበሎች ባለቤት ናት፡፡ ለአምስት ጊዜም የአጫጭር ልቦለድ ውድድሮችን አሸንፋለች፡፡ የገቦ ፍሬ
የሚለው መጽሐፍ በታታመበት አመት “እናት ማስታወቂያ ድርጅትና ብራና ሬዲዮ ፕሮግራም ያዘጋጁትን የዓመቱ ተነባቢ መጽሐፍ ውድድር
ሲያሸንፍ ሁለተኛው ማለትም፣
“ያልጠራ ደም”
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ማበልጸጊያ ተቋም ያዘጋጀውን የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ ውድድር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ‹‹ ያልጠራ ደም››
በ3000 ቅጂ የታተመ ስራ ሲሆን በብር ደረጃም እነዬን 21500 ብር አስገኝቶላታል፡፡ ያልጠራ ደም የደም ውርስ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ልቦለድ ድርሰት ነው-በ317 ገጾችም የቀረበ ነው፡፡
ስውር ግዛት 3ኛው
የደራሲዋ ስራ ነው፡፡ Bold text
ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ገዛኸኝ ጸጋው ሰኔ 12 2013 በሚመረቀው የእነዬ ሺበሺ ስውር ግዛት መጽሀፍ ላይ የሚከተለውን ሀሳብ አስፍሯል
የተለያዩ የአጫጭር
ልብ- ወለድ ውድድሮችን በማሸነፍ የሥነ- ጽሑፉን ዓለም የተቀላቀለችውን እነዬን እኔ የተዋወኳት “የገቡ ፍሬ” በሚለው የረጅም ልቦለድ መጽሐፏ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም. የታተመው ይህ ረጅም ልቦለድ፣ ዝርዝር ሰብአዊ ሕይወትን በጥልቀት
የምናይበት እና ሐሳባዊ መንገድን የሚከተል ትልቅ መጽሐፍ ሲሆን፣ የገጸ-ባህሪዋን ጥልቅ የሕይወት እንቅስቃሴ በጥሩ ቋንቋ
ተከሽኖ ሳናቋርጥ ከዳር እስከ ዳር እንድንደርስ ያስገድደናል፡፡ የገቦ ፍሬ 2004 ዓ.ም. እናት ማስታወቂያና ብራና ሬዲዮ
ያዘጋጁትን የዓመቱ ተነባቢ መጽሐፍ ውድድር በማሸነፍ ተሸላሚ ሆኖላታል፡፡
እንደ ስሙ በደም
ውርስ ወንጀሎች ላይ እያጠነጠነ የተለያዩ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ በደሎችን የሚያሳየን የእነዬ ሁለተኛ ሥራ፣ “ያልጠራ ደም”
ይባላል፡፡ 2007 ዓ.ም. የታተመው ይኽ መጽሐፍ እንደ “ገቦ ፍሬ” ሁሉ የሕይወት ውጣ ውረዶችን እያስቃኘ፣ የአስተዳደር
በደልንና ደም ውርስን መሰናሰል እና ሳይጠሩ ለማጥራት የሚተጉ ሕገ ወጦችን ለማሳየት ይጥራል፡፡ ይኽ መጽሐፏ በ2008 ዓ.ም.
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባወዳደረው የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ ውድድር ከ“እመጓ” ቀጥሎ ሁለተኛ በመውጣት ተሸልሞላታል፡፡ ሦስተኛ
ሥራዋ እና የቅርብ እንግዳችን የሆነው “ስውር ግዛት”፣ እነዬ ከድሮው በተለየ መንገድ የመጣችበት ትልቅ ሥራ ነው፡፡ በሴራ እና
በፕሎት ጠንክሮ የመጣው ይኽ አዲስ መጽሐፍ፣ የራሷን የግል መቼት ፈጥራ የሀገራችንን የሻገተ የብሔር ፖለቲካ ያሳየችበት በሴራም
ሆነ በአወቃቀርከእስካሁኖቹ የተለየ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ በትልቅ ሴራ እና በራሱ መቸት የሚንቀሳቀስ እና ጠንካራ ሐሳብ
የሚንፀባረቅበት መጽሐፍ፣ ከሚያነሳው ጉዳይና ከመጣበት መንገድ አኳያ የአንባቢውን ቀልብ የመግዛት ትልቅ አቅም ይኖረዋል ብዬ
እገምታለሁ፡፡ በጥሩ ቋንቋ እና በጠንካራ ሴራ የታገዘ እንደመሆኑ ልብ አንጠልጣይነቱ መጽሐፉን ይበልጥ ተወዳጅ ያደርገዋል፡፡
እነዬ ከእነዚህ ሦስት መጻሕፍት በተጨማሪ በሰፊው የምትታወቅባቸው አጫጭር ልቦለዶቿ ናቸው፡፡ በርካታ ሥራዎቿን ከሌሎች ደራስያን
ጋር ለማሳተም የበቃች ሲሆን ከነዚህ ውስጥም፡- በያልተናበቡ ልቦች፣ በዓይናለም፣ በአዙሪት፣ በታጋቹ፣ በሩብ ጉዳይ፣ በዜማ
ብዕር 1 እና 2…. መድብሎች ላይ ይገኙበታል፡፡ በተለያዩ መድረኮች በርካታ ውድድሮችን በማሸነፍም ትታወቃለች፣ ለምሳሌ፣
በፖፕሌሽን ሚዲያ፣ በአዲስ አድማስ እና አዲስ ዜና ጋዜጦች የአዲስ አበባ መስተዳድር… ያዘጋጁአቸውን የአጫጭር ልቦለድ ውድድሮች
አሸንፋለች፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ጋዜጦች እና የሬድዮ ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ አጫጭር ልቦለዶችና ድራማዎችን ታቀርባለች፡፡
ቀደም ባሎት ዓመታት ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር በኢትዮጵያ ሬዲዮና በ97.1 ኤፍ ኤም በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራም ላይ ለረጅም ጊዜ
ታቀርብ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በዚሁ ድርጅት አዘጋጅነት በደቡብ ሬዲዮ እና በ97.1 በሚቀርቡት ፕሮግራሞች ላይ
የተለያዩ ጎጂ ልምዶችንና ኮረናን ለመከላከል እያዝናኑ የሚያስተምሩ ሥራዎችን በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡›› በማለት ዶክተር
ገዛኸኝ በመጽሀፉ መግቢያ ላይ ሀሳቡን አስፍሯል፡፡
እነዬ ሺበሺ በ15
አመቷ ከሀገር ቤት ወጥታ በቤት ሰራተኝነት ለ12 አመት አገልግላ እየተማረች ፤ መጽሀፍ እያነበበች ድርሰት እየደረሰች ዛሬ ላይ
ደርሳለች፡፡ የ44 አመቷ እነዬ በኢትዮጵያ የሴት ረጅም ልቦለድ ደራሲዎች ታሪክ ውስጥ ታላቅ አሻራ ካኖሩት በጣት ከሚቆጠሩት
አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡ ዛሬም ብእር ከወረቀት ማቆራኘቱን ቀጥላለች፡፡ ማንበብ -መጻፍ ዋና የህይወቷ መርህ ከሆነ ሰነባበተ፡፡
በብዙ ችግሮች አልፋ አሁን ላይ ደስተኛ የሆነችው ይህች ደራሲ በደማቅ ብእር ታሪኳ ሲከተብ ይህን ትመስላለች፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ