72. ሠመረ ካሳዬ ደስታ - ሠመረ ባሪያው Semere Kassaye
Desta – Semere Bariaw
የዚህ ታሪክ
አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ
፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ
እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን
ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com
ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን
የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና
ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ
ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ
የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል
እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ በተለይ ደግሞ ኮሜዲን በእውቀት
ተመስርቶ በመስራት ባለፉት 12 አመታት እየታወቀ የመጣው ሰመረ ካሳዬ ወይም ሰመረ ባሪያው ነው፡፡ ሰመረ ማነው?
ትውልድ ፤የልጅነት ጊዜና ትምህርት
የሚዲያ ባለሙያና
የሌሎች ብዙ ሙያዎች ባለቤት የሆነው ሠመረ ካሳዬ (ሠመረ ባሪያው) ነሐሴ 6 ቀን 1974 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካቲት
12 ሆስፒታል ተወለደ፡፡ ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ገነት መሰለ የእጽዋት ሳይንስ ባለሙያ ሲሆኑ ወላጅ አባቱ አቶ ካሳዬ ደስታ የኦዲት
ባለሙያ ነበሩ፡፡ ሠመረ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ብዙም ሳይቆዩ በስራ ምደባ ምክንያት ወደ ባህር ዳር በመሄዳቸው የመጀመሪያ
ደረጃ ትምህርቱን የጀመረው በባህር ዳር አፄ ሠርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን ከሁለት አመታት በኋላ ግን
አዲስ አበባ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደሚገኙትና ዘወትር ሁለተኛ እናቴ ወደሚላቸው አክስቱ (የእናቱ ታላቅ) ወ/ሮ ንግስት ተሠማ
ዘንድ በመምጣት የአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በራስ ስዩምና በቅዱስ ማርቆስ ት/ቤቶች ተከታትሏል፡፡
በመካከል ለሶስት አመታት ወላጅ እናቱ ዘንድ ባህር ዳር በመመለስ በፋሲሎ እና በጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ትምህርቱን
የተከታተለ ሲሆን በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶም በከፍተኛ 12 አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ 1991 ትምህርቱን
ተከታትሏል፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋኩሊቲ ከ1992 አንስቶ በመከታተል ያጠናቀቀ ሲሆን
በመቀጠልም በአለም አቀፍ ህግ፣ በሰብዓዊ መብት እና በህጻናት መብት ዘርፎች ላይ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ የተለያዩ የልህቀት
መርሀ- ግብሮችን ተከታትሏል፡፡
ጠያቂው ሰመረ
ሠመረን በልጅነቱ
የሚያውቁት አብሮ አደጎቹ ስለ አንድ ጉዳይ ሲያወራ ልጆች ሁሉ ከብበው የሚያደምጡት ተጫዋች እንደነበር ሲናገሩ ቤተሰቦቹና
የቤተሰቦቹ ቅርብ ወዳጆች የሆኑ ደግሞ ታዳጊውን ሠመረ ከልጅ ሊጠበቁ በማይችሉ ጠጣር ጥያቄዎቹ እና ልጆች ሊያስተውሏቸው
የማይችሉ ነገሮችን አስተውሎ በሚሰነዝራቸው ንግግሮቹ በግርምት ያስታውሱታል፡፡ ሠመረ በቤታቸው ውስጥ ካሉት የቤተሰብ አባላት
ሁሉ ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ስለነበረው የሰፈር የልጅነት ጓደኞቹ “ባሪያው” የሚል ቅጽል ስም የሰጡት ሲሆን እርሱም ይህንን
ተቀብሎና እስከ ዛሬም ይዞ መጥቶ እነሆ ዛሬ “ሠመረ ባሪያው” የሚለውን ስም በሚዲያ ላይ ትልቅና ታዋቂ ብራንድ ሊያደርገው
ችሏል፡፡
ሰመረ በሀይስኩል
ሠመረ የሁለተኛ
ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት “ሆሊውድ” እና “ፕሮፋይል” ለሚባሉ የመዝናኛ ጋዜጦች ኪነ ጥበብ ነክ ጽሁፎችን
በመላክ በአምድ ጸሐፊነት ይሳተፍ ነበር፡፡ በት/ቤት ውስጥም በተለያዩ ክበባት ውስጥ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ተማሪዎች
በሚሰባሰቡባቸው እንደ ስፖርት፣ የትምህርት መዝጊያ ቀን እና የወላጆች በዓል በመሳሰሉ አጋጣሚዎች በሰዎች ፊት ቆሞ አንዳች
ሀሳብ አንስቶ መናገርን ያዘወትር ነበር፡፡ በተጨማሪም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታ ዘመኑ በየአመቱ ትምህርት
በሚዘጋባቸው የክረምት ወራት የተለያዩ ኮርሶችን ወስዷል፤ በአምስት ኪሎ የስፖርት ማዕከል (ወሴክማ) የቅርጫት ኳስ ስልጠናና
በአዲስ አበባ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የስዕል ኮርስ የሚጠቀሱ ሲሆን ረዘም ላለ ጊዜ በአራት ኪሎ ስፖርትና ትምህርት ማዕከል
(ወወክማ) የክብደት ማንሳት ስፖርትን በማዘውተርም በሰውነት ቅርጽ ብቁ ተወዳዳሪ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ በክረምት ወራት
በሰፈር ልጆች ዘንድ “የበረኪና ዋንጫ” ተብሎ የሚታወቀውን የእግር ኳስ ውድድርና ሌሎችንም አይነት ውድድሮችና ጨዋታዎችን
በማሰናዳትም ሆነ በመሳተፍ ሠመረን የሚቀድመውም አልነበረም፡፡
የሙያ ስራ
ሠመረ በተማረበት
ሙያ በህግ አማካሪነት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የማሰልጠኛ ኢንስቲትውቶች በህግ መምህርነት እንዲሁም በአሜሪካ፣
ሀርትፎርድ፣ ኬኔክቲከት ከሚገኘው የድንበር የለሽ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር (Lawyers without Boarders) እና
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ጋር በሰብዓዊ መብት ኦፊሰርነት እና አለም አቀፍ የፍርድ ቤት ታዛቢነት ሙያዊ አገልግሎት ያበረከተ
ሲሆን አሁንም በግል የህግ ማማከር እና የህጋዊ ሰነድ ስነዳ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባዎችን እና ሌሎች
የአለምአቀፍ ተቋማት ስልጠናዎችን ጨምሮ በተለያዩ ታላላቅ ፕሮግራሞች ላይ የትርጉም ስራ (Interpretation) እየሰራ
የሚገኝ ሁለገብ ባለሙያ ነው፡፡
በተጨማሪም በህግ
ትምህርት ቤት የነበረውን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ የህግ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጥ በመሆኑና ተማሪዎች ከአብዛኞቹ
የህግ ቃላት ጋር በቶሎ ለመለማመድ እጅግ የሚቸገሩ በመሆናቸው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቢያንስ እንደ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል
“እንግሊዝኛ - አማርኛ የህግ ቃላት መፍቻ” በማዘጋጀት በ2013 ዓ.ም ለህትመት አብቅቷል፡፡ ይህ የህግ መዝገበ ቃላት
በመጽሐፍ ደረጃ ለሀገራችን የመጀመሪያ ሲሆን በውስጡም ከቃላት ፍቺ ባለፈ ለማንኛውም ዜጋ መሰረታዊ የህግ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ
የህግ ጽንሰ -ሀሳብ ማብራሪያ ተካትቶበታል፡፡
የሚዲያ ባለሙያ
ሠመረ ባሪያው
ከልጅነት እድሜ አንስቶ የነበረውን ነገሮችን በተለየ አቅጣጫ የመመልከትና ሀሳብን በአዝናኝና ግልጽ የንግግር ለዛ የመግለጽ
ተሰጥኦ ከህይወት ልምዱና የቀለም እውቀት ጋር አጣምሮ ወደ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይዞ የመጣው በ2001 ዓ.ም ተሰጥኦውን
በቅርበት የሚያውቁት ጓደኞቹ ባመቻቹት መድረክ ላይ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ያቀረበውን ዝግጅት ብዙ ወዳጆቹ እንደተገረሙበት
ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን አንድ የመዝናኛ ኪነ ጥበብ ዘርፍ ከማዝናናት ባለፈ ለማህበረሰብ ሊያበረክተው የሚገባ ትልቅ ቁም
ነገር ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት ቢኖረውም ሠመረ በተግባር ወደ ኪነጥበብ ዘርፍ ገብቶ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ይችል
ዘንድ የቅርብ ጓደኞቹ ያመቻቹለት ይህ መድረክ ፈር ቀዳጅ እንደነበረ ይናገራል፡፡
ከዚህ መድረክ በኋላ
በተለያዩ የኮሜዲ መድረኮች ላይ ተገኝቶ ስራዎቹን ያቀረበ ሲሆን በተለይም በሀርመኒ ሆቴል፣ በሸራተን አዲስ፣ በብሔራዊ ቲያትርና
በተለያዩ ክልሎች በተዘጋጁ ትልልቅ መድረኮች ላይ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡ በእነኚህ መድረኮች ላይ ያቀረባቸው ስራዎች ግን በውስጡ
ከነበረው ምኞት አንጻር ሲታዩ ብዙም አላረኩትም፤ ሠመረ ኮሜዲ ማህበረሰብን ለመለወጥ የሚችል አቅም አለው የሚል እምነት
ስለነበረው ስራዎቹ ከመድረክ አልፈው ለህዝብ ይበልጥ ተደራሽ በሆነ ሚዲያ መተላለፍ እንዳለባቸው ወሰነ፡፡ ሠመረ በ2007 ዓ.ም
ይህንን ሀሳብ ለማሳካት ሲል በተለያዩ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመዟዟር ሀሳቡን ያቀረበ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተቀባይነትን
ሊያገኝ አልቻለም ነበር፡፡
ጉዞውን ግን
አላቋረጠም፡፡
የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ
ሠመረ በኮሜዲ ዘርፍ
ይዞት የመጣውን የላቀ አቀራረብ በሚመለከት ከኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ከጀርመን ድምጽ ሬዲዮ (Deutsche Welle)፣ ከአሜሪካ
ድምጽ ሬዲዮ (VOA) እንዲሁም ከሌሎች አያሌ የሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር ካደረጋቸው ሰፋ ያሉ ቆይታዎች ባለፈ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ
ሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ ሀሳቦቹን በሬዲዮ ሞገድ ይዞ የመጣው በ2008 ዓ.ም "ፈገግታ" በተባለ በኤፍኤም
97.1 ላይ በሚተላለፍ የመዝናኛ ዝግጅት ነበር። ከዚህ ፕሮግራም ጋር በነበረው የአንድ አመት ቆይታው አያሌ ትምህርትና ልምድ
እንዳገኘ የሚናገረው ሰመረ በመካከል ጥቂት አመታትን ቆይቶ በ2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 በመግባት ታዲያስ አዲስ
የተባለውን ፕሮግራም ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር በተባባሪ አዘጋጅነት ይመራል።
የሳምንቱ ጨዋታ
በፋና ቴሌቪዥን
ሠመረ በ2009
ዓ.ም ክረምት ወር የቴሌቪዥን ዝግጅት የማቅረብ እቅዱን ለፋና ቴሌቪዥን አቅርቦ በዚያን ወቅት አዲስ በነበረው ጣቢያ ላይ
ስራውን በህዳር 2010 እንዲጀምር ተፈቀደለት፡፡ የሳምንቱ ጨዋታ በይዘቱ ጉዳይ ተኮር (Issue Based) ሆኖ ዋነኛ አላማው
የማህበረሰቡን የተለያዩ ጉዳዮች አንስቶ በተለየ የእይታ አቅጣጫ በመዳሰስ ህብረተሰብን እያዝናና በጥቅሉ ንቃትን መፍጠር ሲሆን
ፕሮግራሙ ጉዳዮችን አንስቶ በመተቸት በማህበረሰብ ዘንድ ሒስና አስተያየት የመስጠትና የመቀበል ልምድን ያጎለብታል፣ ግልጽነትንም
በማበረታታት ኮሜዲ ማህበረሰብን በአዎንታዊ መልኩ መለወጥ የሚችል አቅም እንዳለው ያሳያል፡፡
የሳምንቱ ጨዋታ
ከህዳር ወር 2010 አንስቶ ከ165 በላይ ለሆኑ ሳምንታት በተከታታይ የቀረበ ሲሆን በእያንዳንዱ ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያዊነትን፣
ጨዋነትን፣ የሀገር ፍቅርን፣ እና የማንነት ከፍታን በቀላልና በአዝናኝ አግባብ ለማስተማር ጥረት አድርጓል፡፡ ፕሮግራሙ
በአቀራረቡም ተፈጥሮአዊና ያልተሸመደደ በመሆኑ ሲጀመር አካባቢ በተመልካች ዘንድ ለመቀበል ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም ከጊዜ ወደ
ጊዜ እየተሻሻለ መጥቶ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ከግማሽ ሚልዮን
በላይ ተከታዮችን ያፈራ ለመሆን ችሏል፡፡ ሠመረ ለቴሌቪዥን አዲስ የሆነ ይዘትና አቀራረብ ከማስተዋወቅ ባለፈ ስለ ሀገር ከፍታና
ስለ ማንነት ክብር ያለመታከት የሚያነሳ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አስገኝቶለታል፡፡
የበጎ አድራጎት
ተሳትፎ
ሠመረን የሚያውቁት
ስለ በጎ አድራጎት ስራ እንቅስቃሴው ይናገሩለታል፡፡ በየአመቱ ትምህርት ቤት ሲከፈት ደብተሮችን እና የትምህርት ቁሳቁሶችን
አሰባስቦ ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች ከመስጠት አንስቶ እጅግ ሰፊ እስከሚባሉ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ድረስ ተሳትፎው የጎላ
ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን ደጋፊዎች ማህበር
ይህ ማህበር
ከተለያየ የሙያ ዘርፍ የተውጣጡ አባላትን የያዘ የስፖርት በጎ አድራጎት ማህበር ሲሆን ሠመረ የማህበሩ መስራችና ዋና ፀሐፊ
ነው፡፡ ማህበሩ ስፖርትን ከመደገፍ ባለፈ ወጣቶች ከመከፋፈል ይልቅ አንድነትን እንዲያጠብቁና ከምንም በላይ ሀገራቸውን
ኢትዮጵያን በማንኛውም መስክ እንዲያስቀድሙ የሚተጋ ነው፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም
ይህ ስለ ኢትዮጵያ
ዝም አንልም የተሰኘው እንቅስቃሴ ከተለያዩ የሀገራችን አርቲስቶች ጋር በመሆን የተካሔደ ሲሆን አላማውም በወንዶችና በሴት
ህጻናት ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃት እንዲቆምና ህጻናቱን ከጥቃት ሊከላከል የሚችል ጠበቅ ያለ የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ማድረግ
ነው፡፡ ሠመረ የዚህ እንቅስቃሴ አባል ብቻ ሳይሆን የህግ አማካሪ በመሆን ከሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት ጋር ህጉ
ስለሚሻሻልበት ሁኔታ በተደረጉ ጥናቶች ላይ ተሳትፏል፡፡
ሠመረ ለሙዚቃ
ሠመረ ለሙዚቃ
ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንኳን የቅርብ ወዳጆቹ በገጠመኝ የሚያውቁት ሰዎችም ጭምር ይመሰክሩለታል። በተለይም የኢትዮጵያን ሙዚቃ
አብዝቶ የሚወድ ሲሆን ሙዚቃችን ሳይበረዝና ሳይለወጥ ኢትዮጵያዊ ለዛና ጨዋነቱን እንደጠበቀ በአለምአቀፍ መድረኮች ላይ ገናና
መሆን ይችላል የሚል አመለካከት አለው። ሠመረ ዘንድ ያለውን የሙዚቃ ስብስብ ወዳጆቹ "አንድ መለስተኛ የሬዲዮ ጣቢያ
ወይም የማህበረሰብ ሬዲዮ (Community Radio) መክፈት ያስችላል" ሲሉ ይገልጹታል። የዩኒቨርስቲ ተማሪ
ከነበረበት ወቅት አንስቶ ባደራጀው የሙዚቃ ስብስብ ከ500 በላይ የቴፕ ካሴቶች፣ ከ120 በላይ የሪል ቴፕ ቅጂዎች እንዲሁም
ከ250 በላይ የሸክላ ቅጂዎች ያሉት ሲሆን በዲጂታል ቅጂ ከ150ሺህ በላይ ሙዚቃዎችን አሰባስቧል። በአንድ ወቅት ለረጅም ጊዜ
ሲያፈላልገው የነበረው የፍቅርአዲስ ነቃጥበብ የመጀመሪያ ካሴት ሐረር ከተማ አንድ ሰው ዘንድ እንደሚገኝ መረጃ የደረሰው ሠመረ
ይህንኑ ፍለጋ ሐረር ድረስ ተሳፍሮ ሄዶ ካሴቱን አስቀድቶ ይዞ መምጣቱን ወዳጆቹ ዛሬ ድረስ እንደ እብደት ያወሩታል።
ማጠቃለያ… ይህን
የዊኪፒዲያ ታሪክ ባዘጋጁት ሰዎች ጥናት የሰመረ ጨዋታዎች የዋዛ ቀልዶች ሳይሆን በምሁራዊ ቅኝት ተቃኝተው የተሰናዱ ናቸው፡፡
ሰመረ ከንባብ እና ታሪክን መርምሮ ካገኘው እውቀት እየጨለፈ ለዛ
ባለው የቀልድ አቀራረብ ታዳሚን ያዝናናል፡፡ ማህበራዊ ፖለቲካዊ
ጉዳዮችን በድፍረት ሲያነሳ ከጥናት ተነስቶ ነው፡፡ እንዲሁ ለማሳቅ ብሎ ሳይሆን አንድ ማህበራዊ ጉዳይን አንስቶ
ይነቅሳል፡፡ ያላየነውን ያሳየናል፡፡ መተቸት ያለበትን ያለ
ይሉኝታ ይተቻል፡፡ ይህን በብቃት ለመከወን ደግሞ የህግ ትምህርቱ ጠያቂ እና አንቂ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ሰመረ ኮሜዲያን ነው
ስንለው ሚድያ ላይ መረጃ ያስኮመኩመናል፡፡ የህግ ባለሙያ ነው ስንለው የህግ እውቀቱን እንደያዘ ታሪካዊ ሰነዶችን ይዞ ወግ
ያመጣል፡፡ ጨዋታ በእንዲህ መልኩ ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ የመዝናኛ ኢንዱስተሪ በንባብ እና በመደበኛ ትምህርት ሲታጀብ ምን መልኩ ያመረ እንደሚሆን
ከሰመረ ማየት ወይም ልምድ መቅሰም ይቻላል፡፡ ሰመረ ማንበቡን ቀጥሏል፡፡ ጨዋታውም ጓዙን ጠቅሎ መጥቷል፡፡ የእስካሁኑ የሰመረ
ጉዞም ከታሪክ መዝገብ ላይ እነሆ ሰፍሯል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ