71. የሪፖርተሩ ካርቱኒስት ኤልያስ አረዳ

       ኤልያስ አረዳ  ፋንታዬ -ELIAS AREDA FANTAYE 

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡  በስእል ዘርፍ በተለይ ደግሞ በካርቱን ፤ በሀውልትና በቅርጻ ቅርጽ ስራው የሚታወቀው ኤልያስ አረዳ የሪፖርተር ጋዜጣን አዝናኝ ካርቱኖች ላለፉት 23 አመታት በብርታት የሰራ ነው፡፡ ኤሊያስ ማነው ? 






  ትውልድ እና ልጅነት 

ካርቱኒስት፣ሰዓሊ እና ቀራፂ  ኤልያስ አረዳ በአርሲ ፣አሰላ ከተማ ከእናቱ ወ/ሮ ፅጌ አረዳ እና ከአባቱ አቶ አረዳ ፋንታዬ በ1967 ዓ.ም ተወለደ፡፡

የተወለደው በጭላሎ ተራራ ስር ቀበሌ አስራ አራት ነውና ወደ ተራራው አናት ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር ይወጡ ነበር፤ይኸውም በመጋቢት በአካባቢው የሚበቅለውን የሃበሻ እንጆሪ ለመልቀም እና በክረምት ደግሞ ችቦ ለመልቀም ነበር፡፡

ዛሬ ላይ በስዕሎቹ የሚጠቀምባቸው ቀይ ረዥም ጥለት መነሻቸው ያኔ ወደ ጭላሎ ተራራ አናት ሲወጣ ርቀት ቢኖረውም ለጥ ብሎ እንደ ቀይ ጥለት ይመለከተው የነበረው ዝዋይ ሐይቅ ለዛሬው ስራው ትልቁ መነሻው ነው፡፡

የልጅነት ጊዜውን በመልካም ሁኔታ ያሳለፈ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በቅዱስ ገብርኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገና በለጋ እድሜው አጠናቋል፡፡

     የሥነ-ጥበባት ትምህርት

የአስራ ስድስት ዓመት ታዳጊ እያለም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነጥበባት ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት ተምሮ በ1987 ዓ.ም በግራፊክስ ዲዛይን በዲፕሎማ በልዩ ማዕረግ ተመርቋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጥበባት ትምህርት ቤት በቆየባቸው ዓመታት እንደ ሥነ ጥበብ ተቋም ብቻ ሳይሆን ብቻ ሳይሆን ከመምህራን ጋር የቤተሰብ እና የጓደኝነት ጊዜ ነበረው፤ለዚህም ደግሞ ምክንያት የነበረው በጊዜው የነበሩት መምህራን ከሶቪየት ሕብረት ተመርቀው የመጡ ወጣት መምህራን በመሆናቸው ነበር፡፡

ያኔ ልጅ እያለ ወደ ጭላሎ ተራራ እየወጣ የሚለቅመው የሃበሻ እንጆሪ ትዝታው በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ሳይለቀው ሚያዝያ ወር ላይ በግቢው የሚበቅለው ኮክ ዛፍ ላይ እየጠንጠላጠለ ሲለቅም በጓደኞቹ ዘንድ ይታወቅ ነበር፡፡

ከትምህርት ቤቱ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በተስፋዬ ገ/አብ  ይመራ በነበረው እፎይታ መፅሄት ላይ በካርቱኒስትነት ይሰራ የነበረውን ባለሙያ ተክቶ ቀድሞ የሰራቸውን ሦስት የካርቱን ስራዎቹን በአምስት አምስት ብር ለህትመት ያበቃበት ቀዳሚ ስራው ነበር፡፡

            ኤልያስ እና ሪፖርተር ጋዜጣ

 ኤልያስ አረዳ የጋዜጠኛ እና ሠዓሊ ሚሊዮን ወንድም ነውና በወቅቱ በርካታ ጋዜጠኞች ወደ ቤታቸው ይመጡ እና ያደንቁትም ነበር፤በወቅቱ የአድማስ ባሻገር ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ግርማ ደገፋ ከአቶ አማረ አረጋዊ ጋር አገናኝቷቸው በድርጅቱ ይሰሩ የነበሩትን አቶ በቀለ ኃይሌን ተክቶ በቋሚነት ስራ እንዲጀምር አድርጎታል፡፡

ኤልያስ ከ1989 ዓ.ም ወርሃ ሐምሌ ጀምሮ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በካርቱኒስት ተቀላቅሎ መስራት ጀምሮ ዛሬም በዚሁ ተቋም እያገለገለ ይገኛል፡፡ ኤሊያስ ባለፉት 23 አመታት ከ20000 በላይ ካርቱኖችን የሰራ ሲሆን ይህም ትልቅ ርካታ የሚሰጠው ነበር፡፡

ስራውን በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ሲጀምር ፓለቲካው እጅግ የጦዘበት ጊዜ ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ከፖለቲካው እጀጉን የራቀ ስለነበር ስራዎቹ ላይ የመወዛገብ፣ደጋግሞ የመስራት እና የመመላለስ ጊዜ ነበር፤ ግን በወቅቱ እድሉን የሰጡትን እና ዛሬ ላይ ለመድረሱ መሰረት የሆኑለትን አቶ አማረ አረጋዊን በመደጋገም ያመሰግናል፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣ ቆይታውም በማንበብ ፓለቲካውን ጠንቅቆ በመረዳት ርዕሰ- አንቀፁን የሚገልፅ ወይም የሚያጎላ ካርቱንን እየሰራ ይገኛል፤አንዳንዴ ከርዕሰ- አንቀፁ ይልቅ የካርቱን ስራው ጎልቶ የሚወጣበት ጊዜ አለ፡፡

  ተንባይ የካርቱን ስራው

በኤልያስ አረዳ የካርቱኒስትነት የህይወት ቆይታው በ1991 የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከጦርነቱ መጠናቀቅ በፊት በተምሳሌትነት የሰራው በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የመከላከያ ሰራዊቱን ልብስ ለብሰው የኤርትራውን ፕሬዚዳንት የሆኑትን አቶ  ኢሳያስ አፈወርቂን እየገረፉ ከባድመ ሲያባርሩ የሚያሳይ ተንባይ የካርቱን ስራው ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፤ይህም የካርቱን ጥበቡ አርብ ታትሞ ወጥቶ ኢትዮጵያ ባድመ እና ዛላምበሳን እሁድ ማስለቀቅ ችላ ነበር፡፡ እና ጋዜጣው መከላከያ ሰራዊቱ ድረስ በጦርነቱ ቦታ ሁሉ ተዳርሶ ነበር፤በኋላም በጣም ተወዳጅ ሆኖ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል በመከላከያ ሰራዊቱ ተቀይሮ በፓስተር ደረጃ ተሰርቶም ነበር፡፡

          አውደ-ርዕዮች

በካርቱኒስትነት በሰራባቸው 23 ዓመታት ህልቆ ማሳፍርት ካርቱኖችን የሰራ ሲሆን የግሉን የካርቱን ስራዎች የሪፖርተር ዓመታዊ በዓል ሲከበር በኤግዚቢሽን ማዕከል፣በሕብር ኢትዮጵያ እና በኢምፔሪያል ሆቴል የካርቱን አውደርዕዮችን አሳይቷል፤ከዚህ በተጨማሪም ከስድስት በላይ የካርቱን አውደርዕዮችን በጣሊያን ባህል ማዕከል እና በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ በቡድን አሳይቷል፡፡

ኤልያስ አረዳ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ስራዎች ላይም የተሳተፈ ሲሆን በአቶ ክቡር ገና በሚመራው በአፍሪካ ኢንሼቲቭ ግሩፕ ላይ 3 ጊዜ በተዘጋጀው አውደ-ርዕይ ከአራት ካርቱኒስቶች ጋር በጋራ በተዘጋጁ በአፍሪካ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትላልቅ ርዕሰ -ጉዳዮች ላይ ካርቱኖችን በመስራት ተሳትፏል፡፡

በየስድስት ወሩ ይታተም በነበረው እና በአቶ ባሕሩ ዘውዴ በሚመራው ሆርን አፍሪካ ጆርናል ላይ ላለፊት 7 ዓመታት ሰርቷል፤ከዚህ በተጨማሪም ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሰርቷል ፡፡

       የስኬት ጊዜ

በካርቱኒስትነት ሙያው ትልቁ የስኬት ጊዜ ሆኖ የሚጠቀሰው ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የፕሬስ ቀን ሲከበር ከኢትዮጵያ ከሀገራችን ካርቱኒስቶች ተመርጦ እጅግ ከተከበሩ ዓለም ዓቀፍ ካርቱኒስቶች ጋር ያደረገው ሙያዊ ልውውጥ እና ስለ ሀገራችን የካርቱን ግንዛቤ ፣የእድገት ደረጃ፣የፓናል ውይይቱ ላይ የነበረው ተሳትፎ እጅግ ግሩም ጊዜ ነበር፤ኢትዮጵያንም ወክሎ የኢትዮጵያ የካርቱን ምልከታ አሳይቷል፡፡

ካርቱኒስትነት በገንዘብ ካሰላነው በእኛ ሀገር ያን ያህል ጥቅም የለውም የሚለው ኤልያስ አረዳ ከካርቱኒስትነት ሙያው ባልተናነሰ በስዕሉ ጥበብ ላይም ይሰራል፤ከዚህ ቀደምም የተለያዩ የስዕል አውደ-ርዕዮችን በሀገር ውስጥ እና በውጪ አሳይቷል፡፡

ኤሊያስ በ1995 ትኩሳት የሚል ርእስ ያለው የስእል አውደ-ርእይ በአዲስ አበባ ሙዚየም ከፍቶ ነበር፡፡ የዚህ የስእል አውደ ርእይ ትኩረት በሀገራችን  የነበረውን ማህበራዊ ችግር ማንሳት ነበር፡፡ ማህበራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጉዳይንም የሚያነሳሱ ስእሎት ተካተውበት ነበር፡፡ ወደ 40 የሚጠጉ ስእሎች ቀርበው የነበረ ሲሆን ነገር ግን የስእል አውደ ርእዩ ከ2 ቀን በላይ አልታየም ነበር፡፡ በጊዜው የነበሩ የስራ ሃላፊዎች ስእሎቹ እንዳይታዩ ቢያደርጉም በአሊያንስ ፍራንሴስ ስእሎቹ ታይተው ከፍተኛ አድናቆት ለማግኘት ችለዋል፡፡ 

        በቅርፃ ቅርፅ እና ሐውልት ሥራ

በፋሽን ዲዛይነርነት አልገፋበትም እንጂ ከዚህ ቀደም በሸራተን አዲስ ሆቴል ከማኩሽ አርት ጋለሪ ጋር በትብብር ተዘጋጅቶ በነበረው  ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡

የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የሆነው ኤልያስ በቅርፃ ቅርፅ እና ሐውልት ሥራም እንዲሁ በርካታ አደባባዮችን  እና ሀውልቶችን ሰርቷል፤ከእነዚህም መካከል በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ውስጥ የተሰሩትን አብዛኞቹ ቅርፆችን፤በሰበታ ከተማ ደግሞ የኦሮሚያ እናት እና አባት የሚያሳይ ትልቁን ቅርጽ፣በመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅርጽ፣በሱሉልታ ከተማ ማዘጋጃ ቤቱ ፊት ለፊት የሚገኘውን የፈረስና አርበኛ ቅርፅን ከተስፋዬ ገብሬ ጋር በጋራ የሰሩት ነው፡፡ የቅርፃ ቅርፅ እና  የሀውልት ስራዎቹ ደግሞ በተለያዩ ከተሞች እንዲሁም ከላሊበላ ስቱዲዮ ጋር በመሆን በርካታ ስራዎች በዚሁ ዘርፍ ሰርቷል፡፡

በሀገራችን እየተሰሩ ያሉት የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች ኃላ ቀር በመሆናቸው ዓለም አሁን የደረሰበት ዘመናዊ ደረጃ ላይ ለማድረስ መስራት ይፈልጋል፡፡

ኤሊያስ  አሁን እየሰራቸው የሚገኙት ስራዎቹ የቤተ ክርስቲያን የስዕል ስራ ላይ ያተኮሩ ሆነዋል፡፡

ኤልያስ አረዳ ትልቁ ምኞት ዓለም ዓቀፍ አርቲስት መሆን ነው፤የሕይወት እና የስራ እሳቤው ጥበብ ሕይወትን በትክክል ከኖርክበት ምናኔ ነው፤የጥበብ ስራንም ለመስራት ከዚህ ዓለም ጣጣ እና ሁካታ መሰወርን ይፈልጋል፤ወደ ጥልቅ Meditation (ማሰላሰል) ያስገባልይላል እሱም ይሄንኑ ይከተላል፡፡











አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች