70. እስክንድር መርሐጽድቅ -ESKINDER MERHATSIDK GEBREEGZIABHER

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ላለፉት 20 አመታት የምናውቀው እስክንድር መርሐጽድቅ ብዙ ያልተነገረለት ግን ብዙ የለፋ ፤ የብዙዎችን የጋዜጠኝነት መስመር ያሳመረ እና ስራቸውን ያቃና ነው፡፡ ከጋዜጠኝነት ስራው ባሻገርም መጽሀፍትን የደረሰው  የእስክንድር መርሀጽድቅን ታሪክ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

      ትውልድ፣ እድገት እና የትምህርት ሁኔታ

መጋቢት 19/1963 ዓ.ም. የተወለደ ህጻን ልጃቸውን እያጠቡ ግድግዳው ላይ የተለጠፉትን ጋዜጦች እያነበቡ የነበሩት እናት ወ/ሮ ሐረገወይን ገ/መስቀል፣ "ኮማንደር እስክንድር ደስታ ለጉብኝት ወደ ለንደን ሄዱ" የሚል ዜና በማየታቸው አምስተኛ ልጃቸውን እስክንድር አሉት።

ፊደልን ከነንባቡ ከአባቱ ርዕሰ-ደብር መርሐጽድቅ ገ/እግዚአብሔር የቄስ ት/ቤት ለየ። የመጀመሪያውን ዙር የመሠረተ-ትምህርት ዘመቻ ከ100 ያህል ተማሪዎች ጋር ተምሮ በተሰጠው ፈተና ሦስት ተማሪዎች ደብል መትተው ወደ ሁለተኛ ክፍል ሲዛወሩ አንደኛ ስለወጣ ተዛወረ። እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርትም አርሲ/በቆጂ በሚገኙት መለስተኛ፣ ትግል ፍሬ እና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም አዲስ አበባ በሚገኘው ምሥራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተማረ።

የመጀመሪያው የጋዜጠኝነት ትምህርት በዲፕሎማ መሰጠት ሲጀምር ተምሮ የተመረቀ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ (በባህልና ኮሙኒኬሽን) የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

የጋዜጠኝነት ዝንባሌ

የዚህ ሙያ ጥንስሱ የተጀመረው ወላጆቹ አዘውትረው ከሚከታተሏቸው የኢትዮጵያ፣ የለገዳዲ፣ የጀርመን እና የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮዎች ነው። በተለይ አባቱ የሰሟቸውን ዜናዎች፣ "ፐ!" እያሉ ከሚያዳንቁት የክርስትና አባቱ ጋር ሆነው መረጃ ሲለዋወጡበት የበለጠ የማድመጥና ለሌሎች የማውራት (መዘገብ መሆኑ ነው) ፍላጎት አደረበት። የአባትን የማድመጥ ያህል እናት ደግም መጻፍ ይወዱ ነበረና እየነገሯቸው ከወንድሙ ጋር ሆኖ በርሱ የእጅ ጽሑፍ የመጀመሪያዋን ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ልጆች ክፍለ-ጊዜ፣

"የልጆች ጊዜ የምወዳት፣

እንደ ማር እንደ ወተት፣

ስላላት ጥሩ ትምህርት፣

እሰማታለሁ ማታና ጠዋት" ብሎ በ1975 ዓ.ም. የላካት ኤሮግራም ስለተነበበች ተሳትፎው ቀጠለ። ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለብዙዎቹ ፕሮግራሞች፣ ለለገዳዲ ሬዲዮ፣ ለአሜሪካና ጀርመን ድምጾች፣ ለአስመራ ሬዲዮ እና ለፖሊስ ጋዜጣ በመጻፍ ቆየ።

በ1980 ዓ.ም. አዲስ አበባ መግባቱ እና ከአባልነት እስከ ሊቀ-መንበርነት ባገለገለበት ውበት አማተር የጋዜጠኞች ክበብ በ1987 ዓ.ም. መቀላቀሉ ሙያዊ ልምምድን ከአባላቱ ጋር እንዲያደርግ አገዘው፣ ወደ መገናኛ ብዙኃን በአካል የሚቀርብበትም ዕድል ከፈተለት።

ከላይ ከተጠቀሱት ጋር በተለያዩ የግል መጽሔቶችና ጋዜጦች ከአንድ ሺ ያላነሱ ጽሑፎችን ጽፏል፤ በፌስቡክ ገጹም ከአጫጭር እስከ ረጃጅም ጽሑፎችን አውጥቷል።

  የሙያ ስልጠናና  ውድድር

ለአዲስ ዘመን እና የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ ጽሑፎችን ማቅረብ ጀምሮ በዚያው ዓመት ፕሬስ ድርጅት ባዘጋጀው የ20 ቀናት መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሥልጠና ለአማተር ጋዜጠኞች የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ ተከታትሏል። ከዚህ ሌላ ለአስር ወራት የፎቶና ቪዲዮግራፊ ስልጠናን በማስተር ማሠልጠኛ የወሰደ ሲሆን ይህንኑ ሙያ በቶም ቪዲዮግራፊ ማሠልጠኛ ለአንድ ወር ሰልጥኗል። ሁለት ጊዜ ደግሞ መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠናን ወስዷል፤ በዚሁ ዘርፍ የማሻሻያ ሥልጠናዎችንም ተከታትሏል፤ የአመራር ክህሎት ሥልጠናንም አግኝቷል። ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የሰጠውን የሙያ ማሻሻያ ስልጠናም ሁለቴ ወስዷል። በውድድር በኩል ብዙም ባይካፈልም ለአዲስ አበባ መግቢያ ምክንያት የሆነውን የግጥምና ስድ ጽሑፍ ውድድር በ1980 ዓ.ም. አርሲ/በቆጂ ላይ እና አንዴ አሁን በሚሠራበት መ/ቤት ተወዳድሮ አሸንፏል። ከመሠልጠን ሌላ ለበርካታ ጊዜያት መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎች በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ ሰጥቷል።

የሥራ ዓለም

በጋዜጠኝነት እንደተመረቀ በሙያው ሥራ ባለማግኘቱ ለአራት ወራት በኢንስቲትዩቱ ቤተ-መጻሕፍት ሠርቶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በመግባት በሪፖርተርነትና በኤዲተርነት ለአራት ዓመት ተኩል አገልግሏል። ከዋልታ ቀጥሎ በአዲስ ዜና ጋዜጣ ለስምንት ወራት በሪፖርተርነት የሠራ ሲሆን ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በገቢዎች ሚኒስቴር ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኅትመት ሚዲያው ላይ በመጻፍ እና በኤዲተርነት በመሥራት እንዲሁም የኅትመት ቡድኑን በመምራት ላይ ይገኛል።

   ያጋጠሙ ችግሮች

ዋልታ እየሠራ የሚያግዛትን ልጅ በከጀሉ ኃላፊዎች የተነሳ አሶሳ መቀየሩ እና አሁን በሚሠራበት መ/ቤት በሚገርም እና ካለምንም አሳማኝ ምክንያት ያለሙያው እና ያለችሎታው ወደ ሌላ ክፍል ተዛውሮ እንዲሠራ ተደርጎ የነበረበት በሥራ ዓለም ካጋጠሙት ዋነኞቹ ችግሮች ናቸው።

በዩኒቨርሲቲ  ቆይታው የታዘበው

ዛሬም  ድረስ  የሚያዝነው  ስለሚያስተምሩት  ትምህርት  በቂ  እውቀት  የሌላቸው፣  ተሳዳቢና  አንጓጣጭ፣ እንደ መንደርተኛ ወሬን ከተማሪ ወደነርሱ የሚያቀባብሉ፣ ለተማሪዎቻቸው ክብር የማይሰጡ እና ነጥብን ለወሲብ ጥማታቸው የሚሰጡ መምህራን በመኖራቸው ነው።

ከዋና ሥራ በተጨማሪ የሠራቸው ሥራዎች

በተለያዩ የኅትመት ውጤቶችና ፌስቡክ ላይ ከመጻፍ በተጨማሪ እውነተኛና ማኅበራዊ ሂሶች ላይ ያተኮሩ "ቀይ ሥሮች" እና "ለምን?" የተሰኙ ሁለት መጻሕፍትን አሳትሟል።

የሠራቸው ጥናትና ምርምሮች

ትውልዱ በሥርዓተ-ነጥብ እና የአማርኛ ፊደላት ላይ ስላለው የእውቀት ማነስ በግል እንዲሁም በአንድ የኦርቶዶክስ የሚዲያ ክፍል ላይ ከሌላ ሰው ጋር ጥናት አካሂዷል።

 በሙያው ውስጥ አርአያ

በሚዲያ ደረጃ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እሑድና ፖሊስ ፕሮግራሞች እንዲሁም የአሜሪካና የጀርመን ድምጾች፤ በግለሰብ  ንጉሴ አክሊሉ እና መዐዛ ብሩ።

የበጎ አድራጎት ሥራዎች

ዋልታ እያለ ዜና ከሠራባቸው አቤቱታዎች በራሱ ወጪ ዘላቂ መፍትሔ ያስገኘባቸው በጎ ተግባራት አሉ። ከዚህ ሌላ ሁለት ሴቶችን ከነበሩበት ችግር በማውጣት ለጥሩ ደረጃ መድረሳቸው ምክንያት ነው። አንደኛዋ ግን ከማስትሬት ዲግሪዋ በኋላ ዩኒቨርሲቲ እያስተማረች ሳለ በእጮኛዋ በመገደሏ በስሟ በምግብ እጥረት መማር ለሚቸግራቸው አርሲ/በቆጂ ላይ ለሚገኙ የሁለት አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ታዳጊዎች ምግብ፣ ልብስ እና የትምህርት መሳሪያዎች በቋሚነት ለመርዳት ድርጅት የማቋቋም ትልም ይዞ በጋዜጠኛ ሮዝ መስቲካ እና በትዕግሥት ተፈራ (አቢ) ገንዘብ ልገሳ ስለተረጂዎቹ ታሪክ፣ ስለሚረዱት ነገር ዋጋ እና ስለአረዳዱ በማስጠናት እንዲሁም ራሱ ቦታው ድረስ በመሄድ ሙሉ መረጃ አግኝቶ ነበር። ሆኖም፤ ሕጋዊነቱን የማግኘት ሂደቱ እና ለማቋቋም የሚፈጀው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ለጊዜው ቢቆምም ተግባሩን መንግሥት በስፋት ማካሄድ ስለተያያዘ ዓላማው አልተሰናከለም። ከዚህ ባሻገር ህጻናትና አረጋውያንን ለሚረዱ ድርጅቶች እገዛ አድርጓል።

የሕይወት መርሁ

1. "እውነትን ተናገር፤ እውነትን መናገር ከፈራህ ስለእውነት ለሚናገሩት መስክር፤ ይህም ካስፈራህ ግን ዝም በል"

ይህን የሚለው ብዙዎች ውስጣቸው ካለው እውነት ይልቅ ማስመሰል ስለሚቀናቸውና እውነት በሌላው እንዲነገርላቸው ስለሚፈልጉ ነው። እርሱ ግን የሚጽፈውም፣ የሚናገረውም ተጨባጭነት ያለውን ሆኖ ያለፍርሀት በድፍረት ነው። በተለይ በሚጽፋቸው ድክመቶች ከተራ ስድብ እስከ ማስፈራራት የደረሰበት ሲሆን በስብሰባዎች ላይ ሳይፈራ በሚያንፀባርቀው የፖለቲካ አቋሙ የድርጅት አባል ያለመሆኑ ተደምሮበት መድረስ ካለበት ደረጃ ተጎትቷል።

2. "የማንንም ምንም ስጦታ ብቀበልም ከሰጠኝ በኋላ ከሰጠኝ ነገር በታች አድርጎ ካየኝ የምንቀው እኔ ነኝ" ይላል፤ ብዙ ሰዎች ላይ ይህ ስለሚታይ እና እርሱንም ስለገጠመው።

 የወደፊት ዕቅድ

የተቋረጠበትን በምግብ፣ ልብስ እና የትምህርት መሳሪያዎች እጥረት መማር ለሚቸግራቸው ተማሪዎች የመርዳት ትልም መቀጠል እንዲሁም የራስን የሬዲዮ የአየር ሰዓት ከፍቶ ለየት ያለ ማኅበራዊ ፕሮግራም መሥራት።

አመለካከት

በብሔርም፣ በሃይማኖትም እኩልነት ያምናል፤ ያከብራል፤ በዚህ ከማያምኑት ጋር መጓዝ አይፈልግም። የሃይማኖት ጽንፈኝነትን ሲቃወም መቃወም የሚጀምረው ከራሱ ሃይማኖት ተከታዮች ነው። የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ባይሆንም ሰዎች፣ "አባል እንሁን ወይስ አንሁን?" ካሉት ግን ሁለቱንም አይመክርም አንዱን ሆነው ችግር ሲገጥማቸው እንዳያማርሩት በመስጋት።

የቤተሰብ ሁኔታ

ከ16 ዓመታት የትዳር ሕይወቱ የ15፣ የሰባት እና የአንድ ዓመት ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጆች አፍርቷል።






አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች