69. ዓለማየሁ ማሞ-  Alemayehu Mammo

    ዓለማየሁ ማሞ-  ዲያስፖራው ደራሲ- ከሸገር እስከ ዲሲ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ስእል ፤ በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከስነ-ጽሁፍና ድርሰት ዘርፍ ታሪኩ የሚሰነድለት ሰው  ዓለማየሁ ማሞ- ይባላል፡፡ 25 መጽሀፎችን ደርሶ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ነዋሪነቱን በባህር ማዶ ቢያደርግም ልቡ ያለው ሀገር ቤት ነው፡፡

        መግቢያ

የመድረክ ንግግሮቹን ሲጀምር ወይም ሲጨርስ አሊያም ራሱን ሲያስተዋውቅ አንድ ከአፉ የማትጠፋ አባባል አለችው። "በዘመናት መካከል ለጠበቀኝ ደግሜ ደግሜ ከተጋፈጥኩት እስትንፋስን ሊነጥቅ የሚችል አደጋ ለታደገኝና የሚጻፍን ታሪክ በሕይወቴ ላሳለፈ የሚጽፍ ብዕርንም በእጄ ላስያዘኝ የሰማይና ምድር ፈጣሪ ታላቅ ክብር ይሁን! አሜን ይሁን!" 

አሥር ሺህ ማይሎችን ርቆና ተዘልሎ የሚኖረው ደራሲ በሥራው ትጉህና ብዙም ያልታየለት መሆኑን ሰባ ደረጃ ይመሰክራል። ለመሆኑ ሰባ ደረጃ ምንድነው ቢሉ ምሥጢሩ ወዲህ ነው። ገብሬ ኡርጌ የተባለው ማሪን ኮማንዲስት የሆነ የቀድሞ ወዳጁ የዓለማየሁን መጻሕፍት ድርድር ፌስቡክ ላይ ተመልክቶ ተደነቀ። እንዲህ ሲልም አስተያየቱን አሰፈረ። “አሌክስ ሰባ ደረጃን አስመሰልከው እኮ!”።  ለመሆኑ ዓለማየሁ ማሞ ደረጃውን የገነባው እንዴት ነው? እዚህ የደረሰው ከየት ተነሥቶ ነው? በየት በየትስ አልፎ ነው? እነሆ ታሪኩ በአጭሩ...








   ልጅነትና መነሣሣት

  አለማየሁ ማሞ፣ በአገርኛው አቆጣጠር 1958 ዓ.ም በወርሐ ሚያዚያ በሃያ ስምንተኛውም ቀን አውቶቡስ ተራ አካባቢ በነበረው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተወለደ። በመዲናዋ ምሥራቃዊ ክፍል ቀበና ከተሰኘች መንደር አደገ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ቤቱ አጠገብ ከነበረውና በመንደሩ ስም ከተሰየመው የእውቀት ማዕድ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወንዙን ተሻግሮ ኮከበ ጽባሕ በመመላለስ አጠናቀቀ።  

ከእልፍ ገጠመኞቹና ከወላጅ እናቱ የትረካ ጥበብ መካከል ደራሲው ወደ ጥበብ ያዘነብል ዘንድ የገፉትን 3 ገጠመኞች ዝንተ- ዓለም አይረሳቸውም። የመጀመሪያ የካርዱ ላይ ሐተታ ነው።  “ይህ ካርድ ዓለማየሁ በልጅነቱ በተመላላሽነት የተከተበበት ነው” ሲል ይጀምራል የመጀመሪያው ዜና ትንታኔ። ይህን የጻፈው የ12 ዓመት ልጅ ሆኖ ነው። ከዚያ ስምንት ዓመታት ቀድሞ በመንደራቸው ቀበና አንድ አጋጣሚ ተከሰቶ ነበር። ያም የእብደት በሽታ ተጠናውቶታል የተባለ አንድ ከሲታ ውሻ በዳግማዊ ምንይልክ ሆስፒታል ቁልቁል ወደ ቀበና ብቅ ማለቱ ነው። የነከሳቸው ሰዎች ከሦስት ባይበልጡም የመንደሩ ሕፃናት በሙሉ ግን በነፍስ ወከፍ አርባ መርፌ ታዘዘላቸው። የተሰጠው ምክንያትም “ባይነክሳቸውም ተንፍሶባቸዋል” የሚል ነበር። ካርዱ ከዚህ የዘለለ ዘገባ አልነበረውም። ስለዚህ የተረፈውን ገጽ በሙሉ የመሰለውን ጻፈበት። አጭር የሕይወት ታሪኩን አስፍሮ የወደፊት ዕቅዱንም ነደፈበት። ገና ታሪክ ሳይኖረው ታሪኩም ሰነደበት።

ጥቂት ወደ ኋላ መለስ ሲል ደግሞ የአራተኛ ክፍል ተማሪና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሆኖ የአማርኛ መምህራቸው የሰጹቸውን የቤት ሥራ ያስታውሳል። ሁለት ገጽ ግጥም በቃላችሁ ያዙ ነበር ያሉአቸው። በሚቀጥለው ቀን በቃል ብቻ ሳይሆን በዜማ ጭምር አጥንቶት ሲቀርብ ትንሿ ክፍላቸው በጓደኞቹ ጭብጨባ ተናወጠች። ከመነሻው እስከ መድረሻው የሸመደደው እርሱ ብቻ ነበራ።

“አብዱል ብልሁ” የሚለውን ታሪክ ወደ አማርኛ ሲመልሰው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እንጂ ጎልማሳ አልነበረም። ገና ከፍንዳታው ዕድሜ መንደር መዝለቁ ነበር። ታሪኩን አንብቦ የገባውን በአማርኛ እንደጻፈ እንጂ ትርጉም እንዳልሠራ ግን የገባው ቆይቶ ነው። "ማሟሻ ነበረች" ይላታል ያችን አርባ ሁለት ዓመታት የዘለቀች ታሪከኛ ሥራ። “ከየት ተነሣህ” ሲባል መልሱ “ከዚሁና እንዲሁ” የሚል ነው። "ቀስ በቀስ ንባብና ጽሑፍ እንዲህ በውስጤ ሥር እየሰደደ ሄደ እንጂ እኔስ አንድ ቀን ጭሬ እንጀራዬን እቆርሳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም" ይላል ዓለማየሁ።

        ንባብ በባሕር ላይ

ዓለማየሁ በትምህርቱ ንቁ ነበር። ግን በተለምዶ "ማትሪክ" ይባል የነበረውን ፈተና እንደወሰደ የዘመኑ ጫና ውጤቱን እንኳ ለመጠበቅ የአምስት ወራት መቀመጫ ነሣው፡፡ የግዴታ ዘመቻ ከበሮ ጆሮውን አደነቆረው። እናም በ17 ዓመት ዕድሜው የዋኘበትን ወንዝ ተሰናብቶ ወደ ባሕር ዘለቀ። በሳምንት እድሜ ራሱን ለመርከበኝነት ከሚያበቃው ሥልጠና ፊት አገኘው። በዓሉ ግርማ "ሰሜናዊት ኮከብ" ካላት ከተማ ድረስ በፖስታ ታሽጎ የተላከለት የውጤት ወረቀት ወረቀት በሁለቱ ቋንቋዎች (አማርኛና እንግሊዘኛ) ጎጆ መሥራቱን (A) በማብሰር ቢጀምርም ስድስት ኪሎ የሚያስገባ ነጥብ ማስቆጠሩን ቢመሰክርም  ወደ ሸገር የመመለስ ዕድል ግን አልነበረውም። ግን ውጤቱ ቢያንስ የአማርኛን ጽሑፍ እና የእንግሊዘኛን ትርጉም እንዳይዘነጋ አሳስቦት አለፈ።

ባሕረኛው በአስራ ሰባተኛው ዕድሜ ሞዴል ስድስት ለመፈረም ከታደሉት ጥቂት ወጣቶች መካከል አንዱ ሆነ። ግን ከዕለቱ አድካሚ ሥራ ባሻገር የሌሊቱ የወደብ ዳርቻ ከተሞች የጭፈራ ምሽት ለሌላ ነገር ጊዜ አሳጣው። ደብዳቤ መጻፍ እንኳ ራሱን የቻለ ፈተና ነበር። በፈለጉ ጊዜ ወደ ቤተሰብና ወዳጅ መደወል መቻላቸው ራሱ አሰነፈው። ግን አንድ ነገር አልጣለም። ባሕር ላይና በመርከብ ጥላ ሥር ማንበቡን ቀጠለ። ብቸኛ መሸሸጊያም አደረገው።

ጥቂት ዓመታት እንዲያ ነጎዱ። በኋላ ግን በሕክምና ክፍል ውስጥ በተለማማጅነት እንዲቆይ ጊዜው ሲፈቅድም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ እንዲጓዝ የሚያስችለውን ውጤት ጨምሮ አመጣ። ከፍተኛ ለውጥ ነበር! በየሦስትና አራት ቀኑ ተረኛ ሆኖ ሆስፒታል ማደር ነበረበት። ከምሽቱ ስድስት ሰዓት የመጨረሻውን ፀረ ተኅዋስ መድኃኒት ለመስጠት ጥቂት የማይባሉ አብሮ አካሚዎች ይሸሹት ነበር።  ምክንያቱ ምንም ሳይሆን እንቅልፍ ቀድሞ ጣልቃ መግባቱ ነው። ዓሌክስ ደግሞ በተቃራኒው ይናፍቃታል። ለምን ቢሉ ለእርሱ ያች ጊዜ ልዩ ነበረች። የዕለቱን ጋዜጦች የተገኘውን መጽሔት ወይም ወይም መጽሐፍ በጸጥታ የሚያነብባት ጊዜ!

የያኔዎቹ ዝነኛ አምደኞች ተክለ ኃይማኖት ትዝታ ዘአራዳ፣ ዘለሌ ዘግንፍሌና አሸናፊ ዘደቡብ የብዕር ሥራዎች ግሩም ነበሩ። በርካታ መጻሕፍትም እጃቸው ይገቡ ነበር።   ያ ወቅት ትልቅ የንባብ ቅሪት ለራሱ ያስቀረበት እንደነበር ያምናል። ከጊዜ በኋላ “አንባቢ ያልሆነ ጸሐፊ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም” የሚለውን ታዋቂ አባባል ሲሰማ ብዕሩን ጥሎ እንዳይሮጥ የዚያ ዘመን የንባብ ስንቅ ሳይደግፈው አልቀረም። 

መሿለኪያው

በ1981 ዓ.ም አጋማሽ ከምፅዋ ወደ አሥመራ ለሕክምና ተጓዘ። "በዕድሜዬ ሁሉ ለጉዞ የዳረገኝ ብቸኛ ሕክምና ነበር" ይለዋል ባለታሪኩ። በዚያ የነበሩትን ዝነኛ የዓይን ሐኪም ማየት ነበረበትና። የትኛው መነጽር እንደሚሻለው ጊዜ ወስደው ሲመረምሩት ለዐይኖቹ ድጋፍ ሊሰጡ እንጂ ለመዘነጫ እንዳልሆነ ለእርሱም ለእርሳቸውም ግልፅ ቅኔ ነበር። ሁሉም እንደሚገምተው ሐኪሙ ከጠየቁት 101 ጥያቄዎች መካከል “ብዙ ታነባለህ?” የሚል ነበረበት። የባሕሩ ላይ ንባብ መሬት ባሉት ሐኪም ተደገፈ። ዓሌክስ ባለ መነጽር ሆነ። ያ መለያው ዓመታትን ዘልቋል። አንድ ጊዜ ለማሟያ ምርጫ ከተሰበሰቡት የሠፈሩ ባልቴቶች አንዷ ጥቆማ እንዳላቸው በመግለጽ አስፈቅደው ያሉት ነገር ቀበኖችን አስፈግጓል። "እኔ የምጠቁመው የእትዬ የሺን ልጅ ነው፤ መነጽር የሚያደርገውን!"።

ቤተልሔም ዕንቁሥላሴን የተዋወቃት ያኔ ነው። በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማኅበራዊ አስተዳደር ተማሪ ነበረች። ወደ ባሕር ሲመለስ መልካም ጓደኝነቷን አድንቆ ጻፈላት። መለሰችለት። መጻጻፋቸውን  ቀጠሉ። በዚያ የዕውቀት አምባ ሳሉ አምስቱ የአንድ መኝታ ቤት ተጋሪ ልጃገረዶች የምርጥ ደብዳቤ ክፍለ-ጊዜ ነበራቸው። ዓለማየሁ ለእርሷ መጻፍ ከጀመረ አንሥቶ የሳምንቱም ይሁን የወሩ ምርጥ ደብዳቤ የበላይ ሆኖ ነበር። ከዓመታት በኋላ በድንገት አራት ኪሎ ምንይልክ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት ሲገናኙም ቀድማ ያነሣችበት  ስለ ብዕር ወዳጅነታቸው ነበር።  ግን "በበሽታ ላይ የታወጀ ጦርነት ከፍተናል፤ የታመመውን በመድኃኒት፣ ያልታመመውን በክትባት!" እያለ ካራቀቃቸው ደብዳቤዎች አንዱን እንኳ ለእማኝነት ልታገኝለት አለመቻልዋ ይከነክነዋል። ያንን አጋጣሚ ግን ደራሲው መሿለኪያ ብሎ በልቡ ሐውልት አቁሞለታል።

መርከበኛው ጋዜጠኛ

ከየካቲቱ 1982 ጦርነት በኋላ የዓለማየሁና ባሕረኛ ባልደረቦቹ ዕጣ ፈንታ አቅጣጫ ቀየረ። በመቶ የሚቆጠሩ ቁስለኞችን ለማከም ከሕክምናው ቡድን ጋር የተሰለፈው ደራሲም ግራ እጁ ላይ መቁሰሉ እውነት ነበር። "የማልጽፍበት እጄ በከባድ መሣሪያ ፍንጣሪ መመታቱ መጭውን ዘመን ቢያመላክትም የሚፈሰው ደም ጋርዶኝ የቃጠሎው ጭስ ከልሎኝ ነበር" ሲል ማስታወሻውን አስፍሯል። በሁሉን ቻዩ አምላክ ቸርነት ከሞት ተርፎ ሁሉንም  አልፎ ሕይወትን ሀ ብሎ ሊጀምር ወደ መሐል አገር ሲመለስ መጻፍ የሚያስችለው በር በሰፊው ተከፍቶ አገኘው። በርካታ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች መታተም ጀምረው ነበርና። ከሚሠራበት የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ሆኖ መጻፍ ለርሱ ክብር እንጂ ችግር አልሆነም። ሐኪሞቹ መደበኛ ሥራቸውን ጨርሰው እስኪመጡ በሽተኞችን ከመመዝገብ የዘለለ ጥድፊያ አልነበረበትምና።

በዓመቱ መጨረሻ ማስታወሻው እንዳመለከተው ከሆነ 78 አጭርና ረጅም ጽሑፎች እንዲሁም አንድ ብቸኛ ግጥም ለሕትመት በቅተውለታል። ከአገራችን እንስት ገጣሚያን አንዷ የሆነችው የብዕር ወዳጁ፤ ኋላ የሥራ ባልደረባውና አሁንም የፌስቡክ ጓደኛው ስመኝ ግዛው “በላይነህ በማራቶን ዓለማየሁ በጽሑፍ የዓመቱን ሪኮርድ ሰብረዋል” ብላ የጻፈችውም ያለ ምክንያት አልነበረም።

ይህ በቀጣዩ ዓመት የበለጠ ለመጻፍ ጉልበት ሆነው። ግን ሁለት ወራት እንኳ ሳይቀጥል የሕይወቱን አቅጣጫ ያስቀየረ ሁለተኛ አጋጣሚ ተፈጠረ። የመጀመሪያው ሕይወቱን በቃለ -እግዚአብሔር አቅጣጫ መቃኘቱ ነው።  ከዚህም የተነሣ ከሺዎች መካከል የመትረፉን ተአምር እያሰበ ቀሪ ዘመኑን ለአምላኩ ክብር ሊወጣ ሊገባበት ጨከነ።  ሁለተኛው ደግሞ እንዲህ ነበር። በጽሑፎቹ የሚያውቀው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ቢሮው ድረስ ጠርቶ በጀማሪ ሪፖርተርነት እንዲሠራ ጠየቀው። ለማሰብ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ዘጠና ቀናት ሙሉ አወጣ፤ አወረደ፤ ደግሞም ጸለየ። በሦስት ወሩ ተመልሶ ቢሔድ አሁንም ቦታው ክፍት ነው። በብዙ ማመንታት ነጩን የሕክምና ካፖርት አውልቆ መቅረፀ ድምፁን አነገተ። መርከበኛው ጋዜጠኛ!

ሰኞ ተቀጥሮ ማክሰኞ ደብረዘይት ዘልቆ አንድን ወጋቸው የማይጠገብ ባለጋሪ ሲያነጋግር ታየ። ብዙ በሮችን የሚያስከፍት መታወቂያ ኪሱ ስለገባ ሁለገብ ጸሐፊ ለመሆን ከልብ ጣረ። ዜና መዘገብና ሐተታ መጻፍ የዕለት ተዕለት ሥራው ሆነ። ከስፖርት ዘገባ እስከ ባሕል መድረክ ከጉዞ ማስታወሻ እስከ ትርጉም ሥራ ያለውን ተመላለሰበት። በሳይንስና ቴክኖሎጂ አሕዝቦት (Popularization) ከታዋቂው ከድር ኢብራሒም ቀጥሎ ለሽልማት ሲወዳደር በዚህ መስክ ብቻ የጻፋቸው፣ ያረማቸውና ለሕትመት ያዘጋጃቸው ጽሑፎች 892 ገጽ እንደነበሩ ማስታወሱ በቂ ነው። ግዮን ሆቴል በተካሄደ ዓመታዊ ዝግጅት ላይ ታታሪ ጋዜጠኛ ተብሎ መሸለሙም የዚህና ሌሎችም ክንውኖች መገለጫ ነው። በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትርና ኋላም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ እጅ ስጦታውን መቀበሉ ግን የስንብት ዐዋጁም እንደሆነ ቆይቶ ተገለጠለት። 

       ትርጉምና አርትዖት

የፕሬስን ደሞዝ ሲበላ ሦስት ዓመት ሞልቶት ነበር። "የምረቃ ጊዜ ነው" አለ አንድ ማለዳ ባሕረኛው። ቀሪ ዘመኑን ሲያቅድና  በጽሑፍና ሕትመት አቅጣጫ በቂ ልምድ መሸመቱን ሲያረጋግጥ ሁለቱ ተገጣጠሙ። በዚያ ወቅት ከእግዚአብሔር ባገኘው ተሰጥዖ መልሶ የፈጠራትን ነፍስ የሚደርስና ከፍጆታ ያለፈ ሥራን በግሉ እንደ ማዘጋጀት ያለ በጎ ነገር አልታየውም። " ጋዜጦች ዜና መጻሕፍት ደግሞ ዘላቂ ናቸው" አለና  ራሱን ችሎ መሥራት እንደሚሻለው አምኖ ተንቀሳቀሰ። እናም በግሉ መጻፍ፣ መተርጎምና ማረሙን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው።

በተለይም ኤስ.አይ.ኤም ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር ፍሪላንስ ተርጓሚና አርታዒ በመሆን የተሳተፈባቸው የመጻሕፍት ዝግጅት ሥራዎች ጠቀም ካለ ክፍያቸው በዘለለ ጥሩ መረማመጃ ሆነውለታል። ከአምስት ዓመታት ባልዘለሉ ጊዜያት እዚያ የተወው አሻራ አሁንም በየመደብሩ የሚታይ ነው። "ርኅሩኅ ሁን" የተሰኘውን የዋረን ዳብሊው ዌርዝቢ መጽሐፍ ትርጉም ሥራ በአሥር ቀናት ውስጥ አርሞ ጨረሰው ቢባል ስንት ሰው ያምናል?

ዲያስፖራው ደራሲ

ዓለማየሁ እዚያው አልቆመም። ከባሕር ማዶ ጸሐፍትና አሳታሚዎች ጋር መገናኘትና መጻጻፉንም በረታበት። የመላላኪያው ወጪ ኪስ ቢቆነጥጥም ለዘለቄታው አልጎዳውም። ከኬንያ እስከ ናይጄሪያ ከኦስትሪያ እስከ አውስትራሊያ ጥሪዎች ደረሱት። በአውሮፓውያኑ 2000 ዓ.ም ለመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ወደ ለንደን ተጓዘ። የሁለት ወራት ቆይታው ለአእምሮውም ለሰውነቱም እንደተመቸው ያጤነው ወዳጁ “ዓሌክስ እንግሊዙ፣ ብቻውን ሲሄድ ይመስላል ብዙ” ሲል እሱና ጓደኞቹን አስቋቸው ነበር። ስደትን ከመረጠበት ከ2001 በኋላ ግን ወዳጆቹ እሱን ለመቀበል ቦሌ መምጣትም ይሁን ስንኝ መቋጠር አላስፈለጋቸውም። ዳላስ አውሮፕላን ማረፍያ ሲደርስ  ለራሱ ተቀኘና ዲያስፖራ መሆንን መረጠ። “ለዘመድ ጥየቃ ሲጠበቅ አርሲ፣ ዓሌክስ ያስቀድሳል ዋሽንግተን ዲሲ” ነበር ያለው።

በሩጫ የተመሰለው የአሜሪካ ኑሮ እንዲፈነጭበት ሳይፈቅድ  የሁለት ልጆች አባት መሆኑም እንዳይጽፍ ሳያግደው ሁለቱን አሠርት ዓመታት በውጤታማነት ተጉዞአል።  በርካታ መጻሕፍትን ከመጻፍም ባሻገር  በፌስቡክና በራሱ ብሎግ ላይ አያሌ ጽሑፎችን ማቅረብ ችሎአል። ገናም ይቀጥላል። ከ2013 ዓ.ም እ.አ.አ ጀምሮ በየዓመቱ ሳያቋርጥ ዓመታዊ የመጽሐፍ ወይም የመጻሕፍት ምረቃ ያካሂዳል።

ሜሪላንድ ካለው የሞንትጎመሪ ኮሌጅና ለኦሐዮ ክርስቲያናዊ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የአሶሼየት ዲግሪዎችን በማዕረግ ተቀብሏል። አሁንም ኬንታኪ ከሚገኘው የካምበርላንድስ ዪኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ ነው። እስካሁን በአካልም ይሁን በድረገጽ ሲማር ታዲያ አጋጣሚው በፈቀደ መጠን በርካታ ሥነ ጽሑፍ ነክ ኮርሶችን ወስዶአል። ደግሞ የተማረውን ለማካፈል አልቦዘነም። በየዓመቱ ወደተለያዩ ክፍለ ግዛቶችና ውጭ አገሮች ይጓዛል። በተመረጡ ጠቃሚ ርዕሶች ላይ ሴሚናር ያካሂዳል። መጻሕፍቱን ያሰራጫል። ተነሣሽነት ላላቸው የሥነ ጽሑፍ ሥልጠና ይሰጣል፤ ያበረታታል። እስካሁን ቦስተን እና ቶሮንቶን ጨምሮ እስካሁን 133 ጀማሪዎች ሥልጠናውን የተካፈሉ ሲሆን የራሳቸውን መጽሐፍ እስከ ማሳተም የዘለቁም አሉበት።







አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች