62. አስናቀ ብርሀኑ ሀይሌ -Asnake berhanu haile

 ቱሪዝም ከሚስባቸው  አንዱ ነው፡፡  የ37 አመት ሰው ሲሆን  በሚድያ ዘርፍም ሲንቀሳቀስ አመታት አልፈዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ አስናቀ አይነት ራእይ  ያላቸውን ሰዎች ታሪክ ለትውልዱ እያስተላለፈ ስለሆነ ትጠቁሙን ዘንድ እንጋብዛለን፡፡ የአስናቀን ብርሀኑ ሀይሌን ታሪክ እነሆ ብለናል፡፡  

          የልጅነት ዕድሜውን አጣጥሞ ያደገ

 አስናቀ ብርሀኑ ሀይሌ ከአቶ ብርሀኑ ሀይሌ እና ወ/ሮ ዘርፌ አበበ በ1976 በአዲስ አበባ ተወለደ። እድገቱ በአዲስ አበባ በተለምዶ ሳሪስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር፡፡ እድገቱም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአንዱ አባት የብዙሀኑ አባት እናትም የሁሉ እናት ሆነው የሚያሳድጉትን የሚናፈቅ ማህበራዊ ህይወት በልጅነት ዕድሜው አጣጥሞ ያደገ ነው። በአንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ 5 እና 6 አባወራዎች በሚኖሩበት የጋራ መኖሪያ ስፍራ በማደጉ ለግቢው ልጆች ሁሉ እኩል ልብስ እየተገዛ፣በትምህርት ቤት ሁሉንም ልጆች አንድ አባት ወክሎ እንደ ወላጅ ሀላፊነት የሚወስድበት፣ የአንዱ ጓዳ የሁሉ በሆነበት የተገኘውን  በተገኘው ቤት ተመግበው  ቁጣውንም ፍቅሩንም እኩል ተቀብለው ያደጉበት ህይወት ነበረና ይህ በኩራት የሚያወሳው ልጅነቱ የዛሬውን ህይወቱን በመልካሙ መንገድ ያቀናለት መሰረቱ እንደሆነ ያምናል።

 አብዮት ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 6ኛ ክፍል ከተማረ በኋላ በመጋቢት 28 ትምህርት ቤት ደግሞ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትሏል። በግንቦት 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል አጠናቀቀ። የከፍተኛ ትምህርቱን በተመደበበት ስፍራ የሚፈልገውን የትምህርት አይነት ማግኘት ባለመቻሉ በግል ለመማር ወሰነ፡፡ በመሆኑም አካውንቲንግ በመቀጠል ቢዝነስ ማኔጅመንት የተማረ ሲሆን አሁን ደግሞ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ማስተርሱን እየተማረ ይገኛል።በተለያየ ጊዜ ስልጠናዎችንም የተከታተለ ሲሆን በጋዜጠኝነት፣ በሶሻል ስኪል ፣ እና በሌሎችም በርካታ አጫጭር ስልጠናዎችን ተከታትሏል።

            ተቀጥሮ መስራት 

 የስራ አለምን በ2ኛ ደረጃ ተማሪነት ወቅት እየተለማመደ ቢቆይም ለመጀመሪያ ጊዜ ግን ጂ.ቲ.ዜድ ተብሎ በሚታወቅ አለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የኤች. አይ. ቪ መከላከል ስራ ላይ ሙቭ በተሰኘ ፕሮጀክት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ አስተባባሪ በመሆን ለ1 አመት ከ6 ወር ሰርቷል። በመቀጠል ሴቭ ላይቭ ኢትዮጵያ በተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ከወጣቶች ጋር በተያያዘ የሚሰራውን ስራ ለ1 ዓመት ከ2 ወር አካባቢ ሰርቷል። ከዛ እንደወጣ ‹‹ኸልዝ ኮምዩኒኬሽን ፓርትነርሺፕ›› በተሰኘ የአሜሪካ ድርጅት ውስጥ የካምፓስ ላይፍ በሚለው ፕሮግራም የወጣቶች ህይወት ላይ በማተኮር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አካል ሆኖ መስራት ጀመረ። በዚህ ድርጅት የነበረው ቆይታም ወደ ጋዜጠኝነት ህይወት እንዲቀርብ እንዳደረገው ይናገራል። በተለይም ‹‹ካምፓስ ላይፍ›› በሚል የምትዘጋጀውን መፅሄት አስተባብሮ በማሰራቱ ህይወቱን ከጋዜጠኝነት ጋር አስተሳስሮታል።

        ከተቀጣሪነት መላቀቅ 

 ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሀኑ ለተወሰነ ጊዜ ትምህርት በሬድዮ ከሚሰሩት ጋር ለመስራት መጣሩ በሬድዮ ላይ እንዲሰራ በር ሳይከፍትለት አይቀርም፡፡  በ2005 ዓ.ም ነበር ከተቀጣሪነት ህይወት ተላቆ የግሉን ድርጅት የከፈተው። ሀገረሰብ የተባለው የሬድዮ ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤፍ ኤም 96.3  በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በተለይም ቱሪዝም ላይ አተኩሮ የሚሰራ መሰናዶ ሲሆን በሀገራችን በቱሪዝም ዘርፍ በግል ሚድያ በቀዳሚነት የተጀመረ የሬድዮ ፕሮግራም ሳይሆንም አይቀርም።  ከዚህ በተጨማሪ ሀገር ቤት መፅሄት ብሎም ሀገረሰብ አርአያ በአመት የምትታተም የግለሠቦችን የህይወት ታሪክ የሚይዝ መፅሄት እንዲሁም ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን በተለይም ሙስናን የተመለከተ ሀሳብ የሚዳስስ  ‹‹ጉድባ›› የተሰኘች መፅሄት የሚያሳትም ሲሆን ኢትዮ አኒማል የተሰኘ በእንሰሳ ሀብታችን ላይ ብቻ ያተኮረ መፅሄት በድርጅቱ አማካኝነት ለህትመት ያበቃል።

      ይህ እንዴት ሊቀጥል ይችላል?

ጋዜጠኛ አስናቀ ከተቀጣሪነት ስሜት ለመላቀቅ የወሰነበትን ገጠመኝ አይዘነጋውም፤  ኸልዝ ኮምዩኒኬሽን ፓርትነርሺፕ በተሰኘው የአሜሪካ ድርጅት ውስጥ በሚሰራበት ወቅት በአንድ ቀን ማለዳ ከባልደረቦቹ ጋር  ወደ ስራ ሲያመራ ፕሮግራሙ ከአሁን በኋላ ታጥፏልና ስራው ተዘግቷል መባሉን ሲሰማ ይህ እንዴት ሊቀጥል ይችላል? የሚል  ጥያቄ ፈጠረበት፡፡ በጥያቄ ብቻ ግን አልቆመም፡፡ ለራሱ መልስ ለመስጠት ተንቀሳቀሰ።

አስናቀ እድገቱ ከማህበረሰቡ ጋር በተሳሰረ መንገድ መሆኑ መልካሙ መነሻው ከመሆኑ በላይ በተለያየ ጊዜ ሀገሩን የማየት ዕድልም በማግኘቱ ምን ላይ በምን ሁኔታ ብሰራ ይሻላል የሚለውን በብዙ አስቦበት ከጨረሰ፣ ከወዳጆቹም ጋር ከመከረ በኋላ የተገነባበትን ማንነት አጥብቆ ለመያዝ መረጠ፡፡ ሀገረሰብም ተወለደ   '' ሀገረሰብ'' በግዕዝ ሲተረጎም የሀገር ሰው የሚል ትርጓሜን ይይዛል።

         የቱሪዝም ሚድያ ፎረም

በስራው ላይ በነበረው ቆይታ ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሀኑ በግሉ ካደረገው አስተዋፅኦ አንፃር የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በሚድያ ሀላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ሲሆን የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ፣ ትኩረት የተነፈጋቸውም ትኩረት እንዲሰጣቸው ተደጋጋሚ ጥሪ በማድረግ፣እያወቅናቸው የዘነጋናቸውን የእኛ ጉዳዮች በማሳሰብ ጭምር እንደ ቱሪዝም ጋዜጠኛነቱ ሀላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ሲሆን በቱሪዝም ዘርፍ በግል ሚድያ በመስራትም ፈር ቀዳጅ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። ቱሪዝም በጠናከረ መልኩ ይሰራበት አልነበረምና ደካማ እንቅስቃሴ እንደነበረው አይካድም፡፡ ታድያ ዘርፉ የነበረበትን ድክመት ለመቅረፍ ያግዝ ዘንድ ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሀኑ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን  የቱሪዝም ሚድያ ፎረም እንዲቋቋምና ጋዜጠኞች በስፋት እንዲሰሩበት መንግስትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶት ቱሪዝም የሀገር ኢኮኖሚን በመደገፍ የሚኖረውን አቅም ለማጉላት የሚያግዝ ፎረም እንዲሆን ሰርተዋል፡፡ ውጤቱም የሚታይ ሆኗል።

         የባህል ፓሊሲ እንዲኖር

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የባህል ፓሊሲ እንዲኖር ግፊት ማድረግ ፣ የላሊበላ፣አባጅፋርና ሌሎች መዳረሻዎች እንዲታዩ እንዲጠገኑ ተደርጓል፡፡ በቱሪዝሙ ውስጥ ያልታዩ መዳረሻዎች እንዲካተቱም ተደርጓ፡፡ ብሎም ብሄራዊ ፓርኮቻችን ላይ ያሉ ችግሮች እንዲታዩ ጥበቃም እንዲደረግላቸው ፣በቱሪዝም ድርጅት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍም ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ላይ በፎረሙም ሆነ በማህበረሰብ ሬድዮ ፕሮግራሙ ተግቶ ሰርቷል። ከዚህ ጎን ለጎን ቱሪዝም ላይ ብቻ የሚሰሩ ጋዜጠኞች እንዲኖሩ ማድረግ ላይ ብሎም በቅርቡ እውን የሆነውን የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበርን በማቋቋም ትልቁን ሀላፊነት ተወጥቷል።

   ማጠቃለያ

 ብዙ ለመስራት አቅዶ እየተጋ የሚገኘው ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሀኑ እስካሁን የተሰራው ጅምር ስራ መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ እንደ ናሽናል ጂኦግራፊ አይነት አለምን የሚያንቀሳቅስ የቱሪዝም ሚድያን በሀገራችን ለማፍራት አልሞ እንደሚሰራ ያምናል፡፡  ሀገራችንን በቱሪዝም ተደራሽነት ይበልጡን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝም የኢኮኖሚዋ አንደኛው መሰረት እንዲሆን አልሞ  እንደሚሰራም ይናገራል። ይህ ተስፋ የሚጣልበት ወጣት ባለሙያ ለተተኪው ትውልድ አንድ አሻራ እያስቀመጠ በመሆኑ የነገው ትውልድ እነሆ ታሪኩን በዚህ ዊኪፒዲያ አስቀምጠነዋል፡፡






አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች